“ከጓንታናሞ እስከ ማዕከላዊ” በሚለው ተከታታይ ፅሁፍ፤ በክፍል-1 “የፀረ-ሽብር ሽብር” – ሽብርተኝነትን በፀረ-ሽብር ዘመቻና ጦርነት/ዘመቻ መግታት እንደማይቻል፤ በክፍል-2 “ፍርሃትን በፍርሃት” – በፍርሃት የሚወሰዱ አብዛኞቹ የፖለቲካና ወታደራዊ እርምጃዎች ስህተት እንደሆኑ፤ እንዲሁም በክፍል-3 “የአሸባሪዎች ሕግ” – የሽብር ጥቃት በደረሰ ማግስት የሚወጡ አዋጆችና መመሪያዎች የዜጎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ሊገድቡ እንደሚችሉ ተመልክተናል። በመጨረሻው ክፍል-4 ደግሞ በሽብር ወንጀል ተጠርጥረው በታሰሩ እስረኞች ላይ ስለሚካሄደው የስቃይ ምርመራና ከዚያ ጋር ተያይዞ ያለው የተሳሳተ እሳቤና ተፅዕኖ በዝርዝር እንመለከታለን። በአብዛኛው የስቃይ ምርመራ (torture interrogation) የሚተቸው ከተጠርጣሪ እስረኞች የሰብዓዊ መብት መከበር ጋር በተያያዘ ነው። የሕግ ጉዳይ እንዳለ ሆኖ፣ ይህ ፅሁፍ በተለይ የሚያተኩረው ግን ከፖሊሲ አንፃር ባለው ተፅዕኖ ላይ ነው። በእርግጥ በተጠርጣሪ እስረኞች ላይ የስቃይ ምርመራ ማድረግ ፍፁም ኣላዋቂነትና ግልብ ስሜታዊነት ከመሆኑም በላይ የምርመራ ባለሞያዎችን የመርህና ብቃት አልባነትን የሚያሳይ ነው።

እንደሚታወቀው የቀይ-ሽብር ጭፍጨፋና ስቃይ የተጀመረው ጓድ መንግስቱ ኃ/ማሪያም እ.አ.አ ሚያዚያ 17/1977 በመስቀል አደባባይ “አብዮቱን እንከላከል” በሚል ያደረገውን ንግግር ተከትሎ ነው። ከዚያን ዕለት ማታ ጀምሮ፣ በምስራቅ ጀርመን ደህንነት “Stasi” አባላት እየታገዘ፣ “ፀረ-አብዮት” በተባሉ ሰዎች ማሰርና መግደል እንደተጀመረ ይታወቃል። ስለዚህ፣ ደርግ የስቃይ ምርመራን የጀመረው በደረሰበት የነጭ-ሽብር ጥቃት ፍርሃት ውስጥ ሆኖ ነው። ከዚህ በተጨማሪ፣ ስለሀገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ በቂ ግንዛቤ በሌላቸው የውጪ ሀገር የደህንነት ባለሞያዎች ምክር ላይ የተመሰረተ ነው። በተመሣሣይ፣ ፕ/ት ጆርጅ ቡሽ ከአሜሪካ ግዜት ውጪ የሚስጥር እስር ቤቶች እንዲቋቋሙና የስቃይ ምርመራ እንዲጀመር ለC.I.A. መመሪያ የሰጡት የአልቃይዳ የሽብር ጥቃት በደረሰ በስድስተኛው ቀን፣ እ.አ.አ September 17, 2001 ዓ.ም ላይ ነበር። ነገር ግን፣ “Ali H. Soufan” የተባለው የቀድሞ የF.B.I. ባልደረባ ሚያዚያ 2009 ዓ.ም (እ.አ.አ) “My Tortured Decision” በሚል ርዕስ ባወጣው ፅሁፍ፣ የስቃይ ምርመራ ለማድረግ ጥያቄ ያቀረቡት የC.I.A. ባልደረቦች ሳይሆኑ ለዚህ ተግባር ኮንትራት የወሰዱ ተቋራጭ ድርጅቶች እንደሆኑ ይጠቅሳል። ጉዳዩን አስመልክቶ የቀረበው የአሜሪካ ሴኔት ሪፖርት እነዚህ ተቋራጮች ስለወንጀል ምርመራ ሆነ ስለአልቃይዳ ድርጅት ምንም አይነት መረጃና ዕውቀት እንዳልነበራቸው አረጋግጧል። በኢትዮጲያና በአሜሪካ የስቃይ ምርመራ የተጀመረው፣ በሽብር ጥቃቱ ፍርሃትና ግራ-መጋባት መጋባት ውስጥ በወደቁ አመራሮችና በነባራዊ እውነታና በወንጀል ምርመራ ረገድ በቂ ግንዛቤ በሌላቸው ሰዎች እንደነበር መገንዘብ ይቻላል። በዚህ መሰረት፣ የስቃይ ምርመራ “ፍርሃትን በፍርሃት” ለመታገል በስሜታዊ ግብዝነት የተጀመረ ኢሰብዓዊ ድርጊት ነው። 

በአሜሪካ ጓንታናሞ ሲደረግ የነበረውና በማዕከላዊ እየተደረገ ያለው የስቃይ ምርመራ (torture interrogation –  አንዳንድ የአሜሪካ ባለስልጣናት እና C.I.A ኃላፊዎች “enhanced interrogation techniques” በማለት ይጠሩታል) የዕውቀትና ክህሎት ማነስ ውጤት ነው። የስቃይ ምርመራ እውነትን በጉልበት ለማግኘት የሚደረግ ጥረት ነው። የወንጀል ምርመራ ግን የሙያ ክህሎት እንጂ የጉልበት ሥራ አይደለም። የወንጀል ምርመራ በመረጃና ሙያዊ ክህሎት እንጂ በአካላዊ ጥንካሬ የሚሰራ ሥራ አይደለም። በቅድሚያ ስለወንጀሉና ተጠርጣሪው መረጃ ያሰባሰበ የወንጀል መርማሪ ያለውን ክህሎት ተጠቅሞ ትክክለኛ መረጃ ማግኘት ይችላል። ተጠርጣሪውን በማሰቃየት እውነትን በጉልበት ለማግኘት የሚጥር መርማሪ የሀሰት መረጃ ያገኛል። ባለፉት ዓመታት ከሽብርተኝነት ጋር ተያይዞ በጓንታናሞ እና በማዕከላዊ እስር ቤቶች የተደረገው ምርመራና የተገኘው ውጤት የሚያረጋግጠው ይሄን ነው።

በተለያዩ የሚስጥር እስር ቤቶች ውስጥ የስቃይ ምርመራ ሲያደርጉ የነበሩት የአሜሪካ ማዕከላዊ የድህንነት መስሪያ ቤት (C.I.A.) ባልደረቦች እና ለዚሁ ተግባር ውል የገቡ ተቋራጮች (ኮንትራክተሮች) ድርጅቶች ናቸው። ከዚህ በተቃራኒ፣ የሀገሪቱ የፌደራል የወንጀል ምርመራ መስሪያ ቤት (F.B.I.) ባልደረቦች ግን በተጠርጣሪዎች ላይ ይካሄድ የነበረውን የስቃይ ምርመራ አጥብቀው ይቃወሙ ነበር። የወንጀል ምርመራ መስሪያ ቤቱ ባልደረቦች የወንጀል ምርመራ በሙያዊ ጥበብና ክህሎት የሚከናወን እንጂ በኃይልና ጉልበት እንዳልሆነ ይጠቅሳሉ። ለዚህ ደግሞ አሊ ሱፋን “Ali H. Soufan” የተባለው በሽብር ወንጀል ምርመራ ታዋቂ የሆነው የቀድሞ የF.B.I. ባልደረባ ሚያዚያ 2009 ዓ.ም (እ.አ.አ) “My Tortured Decision” በሚል ርዕስ ያወጣው ፅሁፍ እንደ ማስረጃ የሚጠቀስ ነው። ይህ ወንጀል መርማሪ ስለ “አቡ ዙባይዳህ” (Abu Zubaydah) እና የመስከረም 1 (9/11) የሽብር ጥቃት ዋና አቀነባባሪ ስለሆነው “ካሊድ ሼክ መሃመድ” (Khalid Shaikh Mohammed) የሚከተለውን ፅፏል፡-

“It is inaccurate, however, to say that Abu Zubaydah had been uncooperative. Along with another F.B.I. agent, and with several C.I.A. officers present, I questioned him from March to June 2002, before the harsh techniques were introduced later in August. Under traditional interrogation methods, he provided us with important actionable intelligence. …We discovered, for example, that Khalid Shaikh Mohammed was the mastermind of the 9/11 attacks.”

“አቡ ዙባይዳህ” የተባለው ተጠርጣሪ አንድ አይኑ እስኪጠፋ ድረስ የስቃይ ምርመራ ተደርጎበታል። ከዚህ በተጨማሪ፣ “ካሊድ ሼክ መሃመድ” የአሜሪካው የሽብር ጥቃት ዋና አቀነባባሪ እንደሆነ የጠቆመው እሱ ነው። ነገር ግን፣ ከላይ መርማሪ አሊ ሱፋን እንደጠቀሰው፣ ይህ መረጃ የተገኘው ተጠርጣሪው ገና በፌደራል የወንጀል ምርመራ መስሪያ ቤት (F.B.I.) ስር እያለ እንጂ ወደ ማዕከላዊ ድህንነት መስሪያ ቤት (C.I.A.) ከተዘዋወረ በኋላ አይደለም። የቀድሞው የአሜሪካ ፕረዜዳንት ጆርጅ ቡሽ እና የማዕከላዊ ድህንነት መስሪያ ቤት (C.I.A.) ኃላፊዎች፤ “የስቃይ ምርመራ ዘዴ የጥቃቱን ዋና አቀነባባሪ ለመያዝ የሚያስችል መረጃ አስገኝቷል” በማለት በተደጋጋሚ ሲናገሩ ቢሰማም፣ ጉዳዩን በቅርበት የሚያውቁ ሰዎች ግን ሃሰት እንደሆነ ይናገራሉ። ለዚህ ደግሞ በጉዳዩ ላይ በቀረበው የሴኔት ሪፖርት ጥሩ ማረጋገጫ ነው። የሴኔትን ሪፖርት ዋቢ በማድረግ የዘገበው “New Yorker”፣ በስቃይ ምርመራ አማካኝነት ከአቡ ዙባይዳህ እና ከካሊድ ሼክ መሃመድ ምንም አይነት ጠቃሚ መረጃ እንዳልተገኘ እንደሚከተለው ገልጿል፡-

“Abu Zubaydah, a Saudi, got the full C.I.A. treatment: he was stripped, deprived of sleep, kept in a coffin-size box for days on end, and waterboarded at least eighty-three times. But the Senate report demonstrates that Abu Zuybadah’s role in Mohammed’s capture was essentially nonexistent—and that torture had nothing to do with it. Abu Zubaydah did indeed identify him as the lead 9/11 plotter, but that was when he was in F.B.I. custody, before the C.I.A. got him.” …..The Senate report, which drew almost entirely on the C.I.A’s internal communications, makes a convincing case that while the interrogation of Mohammed produced some valuable information, the interrogators never got what they wanted. No information provided by Mohammed led directly to the capture of a terrorist or the disruption of a terrorist plot.…. [Mohammed] also claimed that much of the information he had given under torture was false, and in at least several instances that turned out to be correct. ….According to the agency’s own records, Mohammed explained that he was “under ‘enhanced measures’ when he made these claims and simply told his interrogators what he thought they wanted to hear.”

ከላይ በጥቅሱ ውስጥ እንደተገለፀው፣ በስቃይ ምርመራ አማካኝነት መረጃ ለማግኘት የሚደረገው ጥረት ውጤታማ አይደለም። በሽብርተኝነት ወንጀል ምርመራ ከፍተኛ ልምድና ብቃት እንዳለው የሚነገርለት አሊ ሱፋን በስቃይ ምርመራ አማካኝነት መርጃ ለማግኘት መሞከር ፍፁም አላዋቂነትና ነገሮችን አርቆ-ያለማስተዋል እንደሆነ ይገልፃል። አቡ-ዙባይዳህ (Abu Zubaydah) በተባለው ተጠርጣሪ እስረኛ ላይ የመደበኛ የምርመራ ዘዴዎችን በመጠቀም ምርመራ ሲያደርግ የነበረውን ኢሊ ሱፋን በሀገሪቱ የማዕከላዊ ደህንነት መስሪያ ቤት (C.I.A.) ጣልቃ ባይገባ ኖሮ በዚሁ መንገድ ብዙ መረጃ ሊገኝ ይችል እንደነበር ገልጿል። አያይዞም በሽብርተኝነት ተጠርጥረው ከሚታሰሩ ሰዎች ትክክለኛውን መርጃ ለማግኘት መደበኛ የምርመራ ዘዴዎች መጠቀም አማራጭ እንደሌለው ይገልፃል። የአሜሪካውን የሽብር ጥቃት ስላቀነባበረው ካሊድ ሼክ መሃመድ ለመጀመሪያ ግዜ መረጃውን ያገኘው አሊ ሱፋን ነው።

ኢሊ ሱፋን መረጃውን ለማግኘት በአቡ ዙባይዳህ ላይ የተጠቀመውን የምርመራ ስልት አስመልክቶ የቢቢሲ ሬድዮ ባዘጋጀው አንድ ፕሮግራም ላይ ገለፃ አድርጎ ነበር። በመደበኛ የምርመራ ዘዴ (traditional interrogation techniques) በመጠቀም አቡ-ዙባይዳህ ገና በሁለተኛ ጥያቄ መተባበር እንደጀመረ ይናገራል። መርማሪው በመጀመሪያ ያቀረበው ጥያቄ፡ “ስምህ ማን ይባላል?” (What is your name?) የሚል ሲሆን፣ አቡ ዙባይዳህ፡ “ዳውድ” (Dawood) በማለት የሃሰት ስም ተናገረ። በመቀጥል መርማሪ አሊ ሱፋን፡ “’ማሬ’ ብዬ ብጠራህስ?” (What if I call you ‘Honey’) ብሎ ሲጠይቀው ተጠርጣሪው ግራ ተጋባ። ምክንያቱም፣ “ማሬ” (Honey’) የሚለው ስም የአቡ-ዙባይዳህ ቤተሰቦች በልጅነት እድሜው የሚያቆላምጡበት የቅፅል ስሙ ነበር። ስለዚህ፣ አቡ-ዙባይዳህ “የሕፃንነት ቅፅል ስሙን እንደማውቅ ሲያውቅ፣ ስለእሱ የማውቀውና የማላውቀው ነገር ተምታታበት” ይላል መርማሪው። በዚህ ቀላል በሆነ መደበኛ የወንጀል ምርመራ ዘዴ በመጠቀም በፀረ-ሽብር ጦርነቱ በጣም ተፈላጊ የነበረውን የአልቃይዳ የሽብር ጥቃት አቀነባባሪ፣ ካሊድ ሼክ መሃመድ መሆኑን እንደደረሰበት ተናግሯል።

እስካሁን ድረስ በአሜሪካ የፌድራል ወንጀል ምርመራ ቢሮ (F.B.I.) በፀረ-ሽብር ወንጀል ምርመራ ከፍተኛ ልምድና ተሞክሮ ያለውን መርማሪ ዋቢ በማድረግ ስለ ትክክለኛው የወንጀል ምርመራ ዘዴዎች ለማየት ሞክረናል። በመቀጠል፣ በኢትዮጲያ የፌዴራል ፖሊስ ኃይል ማዕከላዊ የወንጀል ምርመራ ቢሮ (Ethiopian Federal Police Force Central Bureau of Criminal Investigation)፣ ወይም በተለምዶ “ማዕከላዊ” (Ma’ekelawi) በመባል በሚታወቀው የኢትዮጲያው አቻ መስሪያ ቤት ያለው አሰራር ምን እንደሚመስል ለመቃኘት እንሞክራለን። በሽብርተኝነት ወንጀል ተጠርጥረው ታሰው ከነበሩት የዞን9 ጦማሪያን ናትናዔል ፈለቀ እና በፍቃዱ ኃይሉ ያወጧቸው ፅሁፎች በማዕከላዊ ስላለው የወንጀል ምርመራ ዘዴ ጥሩ ምልከታ ይሰጣሉ።

ናትናዔ ፈለቀ በማዕከላዊ እስር ቤት በነበረው ቆይታ በተደጋጋሚ ሲቀርቡለት ከነበሩት ጥያቄዎች ውስጥ፤ “ይህ መንግስት ምን በድሎሃል?” እና “እንዴት እንደዚህ አይነት አቋም ልትይዝ ቻልክ?” የሚሉት እንደነበሩ ያስታውሳል። አያይዞም፣ ለእነዚህ ጥያቄዎች መልሱ “ነጻነቴን ዋጋ እሰጠዋለሁ!” የሚል ብቻ እንደነበር ገልጿል። ሌላኛው ደግሞ “አያ ጅቦ ሳታመኻኝ ብላኝ” በሚል ርዕስ በፍቃዱ ኃይሉ ባወጣው ፅኁፍ ደግሞ ‹‹ታዲያ ጥፋቴ ምንድን ነው ትላለህ?!›› ተብለው እንደሚጠየቁ ይገልፃል። እንደ በፍቃዱ አገላለፅ፤ “ተጠርጥረን የተያዝንበትን ጉዳይ የሚያረጋግጥ ሥራ ሠርተን ባለመገኘታችን ‘ታዲያ ጥፋትህ ምንድን ነው?’” ተብለው እንደሚጠየቁና የጥያቄው ዓላማም የተጠርጣሪውን ነፃ መሆንና አለመሆን ለማጣራት ሳይሆን “ጥፋት ለማግኘት” እንደነበር ይገልፃል፡፡ እንደዚህ ዓይነት ጥቄዎች የሚጠየቁበትን ምክንያት ለመረዳት “Addis Standard” መፅሔት በቅርቡ ባወጣው ትንታኔ ላይ ዶ/ር ፀጋዬ አራርሳ የተባሉ ግለሰብ የሰጡትን አስተያየት መጥቀስ ይበቃል። ግለሰቡ በሰጡት አስተያየት “የኢትዮጲያ ፖሊስ ኮሌጅ በወንጀል ምርመራ “criminal investigation” የሰለጠነ ሰው የለውም” መባላቸውን ያስታውሳሉ። ይህ ከሆነ፣ በወንጀል ምርመራ ሙያ ከፍተኛ የብቃትና ክህሎት ችግር እንዳለ ይጠቁማል። ለዚህ ማጠናከሪያ እንዲሆን፣ በፍቃዱ ኃይሉ “ምርመራ ማዕከላዊ ስታይል” በሚል ባቀረበው ፅሁፍ ውስጥ የሚከተለውን እንመልከት፡-

“ምርመራ በማዕከላዊ ከብልጠት ይልቅ ጉልበት ይበዛበታል፡፡ መርማሪዎቹ የምርመራ ችሎታቸው ተጠርጣሪውን የተጠረጠረበትን ጉዳይ ከማውጣጣት ይልቅ የምርመራ ችሎታ እንዳላቸው ለማሳመን የሚጥሩበት ጊዜ ይበዛል፡፡ ይህም አልሰራ ሲል ጥፊ፣ ካልቾ፣ ከአቅም በላይ ስፖርት ማሰራት እና ግርፋት ድረስ ይዘልቃሉ፡፡ …በምርመራው ሂደት የተረዳነው ነገር ቢኖር የማዕከላዊ መርማሪዎች ብቃት (Intelligence) አርጩሜ ብቻ መሆኑን ነው፡፡”

ናትናዔል ፈለቀ በማዕከላዊ ያሉ የወንጀል መርማሪዎችን አስመልክቶ እንዲህ ይላል፤ “እነዚህን በአንድ በኩል መረጃ የተደፈኑ ሰዎች ሌላኛውን ጎን ማሳየት በሌላ አማራጭ የማያገኙት መረጃ ምንጭ መሆን ስለሆነ” በማለት በተገኘው አጋጣሚ ያለባቸውን የዕውቀት ችግር ለመቅረፍ መሞከር አግባብ እንደሆነ ያሰምርበታል። በተመሣሣይ፣ በፍቃዱ ኃይሉ፣ የማዕከላዊ እስር ቤት ያለው የምርመራ ሂደት በመርህ እና ዕውቀት የሚመራ አለመሆኑን ጠቅሶ፣ ተቋሙ ፈርሶ እንደገና ሊቋቋም እንደሚገባ ይገልፃል። ምክኒያቱም፣ “ይህ…የአገሪቱን ደህንት አደጋ ውስጥ የሚጥል ጉዳይ በምርመራው ድክመት ሳይታወቅ ሊታለፍ ይችላል።” እኔ የምለው፤ በምርመራ ስም እየተደበደብክ እያለ፣ እንደ ናትናዔል “መርማሪውን ለማስተማር”፣ እንደ በፍቃዱ “ስለ ሀገር ድህንነት ለማሰብ” አይከብድም? በእርግጥ ‘ማዕከላዊ ዕውቀትን በጉልበት ለመግዛት ጥረት የሚደረግበት ቦታ አይደለም’ ትላላችሁ? 

በአጠቃላይ፣ ከፍል-1 ጀምሮ በዝርዝር ለመግለፅ እንደተሞከረው፤ በማዕከላዊ እስር ቤት የሚካሄደው የስቃይ ምርመራ መረጃን በጉልበት ለማግኘት ጥረት የሚደረግበት፣ ከፍተኛ የሆነ የዕውቀትና የብቃት ችግር ስለመኖሩ ማሳያ ነው። ትክክለኛ መረጃ በሙያዊ ክህሎትና ብቃት እንጂ በጉልበት አይገኝም። ትክክለኛ መረጃ በዕውቀት የሚገኝ ሃቅ እንጂ በጉልበት የሚፈነቀል ቁስ አይደለም። ከዚህ በተጨማሪ፣ ማዕከላዊ እስር ቤት አንድ ትውልድ እርስ በእርሱ የተጫረሰበት፣ የነጭ-ሽብር እና የቀይ-ሽብር ፍርሃት የወለደው የስቃይ አምባ ነው። በዚያ ሀገርን መሃን ባደረገ የሽብር ዘመን ማዕከላዊ የትውልድ ማጨናገፊያ ሆኖ ሲያገለግል የነበረ ቦታ ነበር። ይህ ቦታ እስካልተዘጋ ድረስ የዚያ ክፉ ዘመን ቁስል እንዳመረቀዘ ይቀጥላል። የትውልድ ስቃይና ሰቆቃ የተሰመባት ተቋም ተዘግቶ፣ ለዚያ ክፉ ዘመን መታሰቢያ መሆን ሲገባው፣ አሁንም ድረስ ለተመሣሣይ አላማ እየወለ መሆኑ ፣ እንደ ሀገርና እንደ መንግስት ትልቅ የፖለቲካና የሞራል ኪሳራ ነው። ስለዚህ፣ ማዕከላዊ እስር ቤት መዘጋት አለበት!!!

*********

ከጓንታናሞ እስከ ማዕከላዊ ተከታታይ ፅሁፍ

Seyoum Teshome is a Lecturer at Ambo University Woliso Campus and head of Management Department. He was born in Arsi, Assela, in 1979 and studied Management at Harameya University and MBA at Mekelle University. He also blogs at http://ethiothinkthank.com

more recommended stories