ከጓንታናሞ እስከ ማዕከላዊ፡ ክፍል-1 “የፀረ-ሽብር ሽብር”

ስለማዕከላዊ (Ma’ekelawi) እስር ቤት እና ስለቀይ-ሽብር ሲነሳ እፈራለሁ። በቃ… “ቀይ-ሽብር” ሲባል የታሪክ ጠባሳ፤ “ማዕከላዊ” ደግሞ ምድራዊ ሲዖል ስለሚመስሉኝ ስለዚያ ጉዳይ ማሰብ ራሱ ያስፈራኛል። በተለይ ጋዜጠኛ ማዕዛ ብሩ እና ገጣሚና ተርጓሚ ነብይ መኮንን በሸገር ሬድዮ ያደረጉትን ብዙ ሳምንታት የፈጀ ጭውውት እንደምንም አዳምጬ ከጨረስኩ በኋላ፣ ሌላ ተጨማሪ ነገር መስማትም ሆነ ማንበብ አልሻም ነበር። ባለፈው ሳምንት ግን እንደ አጋጣሚ በፌስቡክ ገፄ ላይ እንደዋዛ የተጫንኩት የአዲስ ስታንዳርድ መፅሔት ማያያዣ ከምሸሸው እውነት ጋር መልሶ አላተመኝ። በመጀመሪያ በመፅሔቱ የቀረበውን ትንታኔ በዝግታ አነበብኩ። ቀጠልኩና በፅኁፉ ውስጥ የተቀመጡ አንዳንድ ማያያዣዎችን እየተጫንኩ አነበብኩ። በቀይ-ሽብር ዘመን በዜጎች ላይ ያ ሁሉ ስቃይና ሰቆቃ የተፈፀመበት የስቃይ አምባ ዛሬም ድረስ ክፍት ነው። “ማዕከላዊ” እንደ የቀድሞ ታሪክ በትውስታ የሚነሳ ሳይሆን ዛሬም ድረስ በእውን ያለ መሆኑ ይበልጥ አስፈራኝ። ስለዚህ፣ ይህን ‘አስቀያሚ እውነት’ ፊት-ለፊት ከመጋፈጥ በስተቀር መሸሽ እንደማያዋጣኝ አምኜ ገባሁበት።

ላለፉት ሁለት ሳምንታት የተለያዩ መረጃዎችን በማሰባሰብ፣ የኢትዮጲያ ማዕከላዊ እስር ቤት ከአሜሪካው የጓንታናሞ እስር ቤት ጋር ያለውን ተያያዥነት በጥልቀት ለማየት ሞከርኩ። ትላንት ላይ “ሀገራዊ እና ዓለም-አቀፋዊ” ከሚል የቦታ ልዩነት፣ እንዲሁም ከግዜ የ25 ዓመት የግዜ ልዩነት በስተቀር በማዕከላዊ እና በጓንታናሞ እስር ቤቶች መካከል ልዩነት የለም። ያለምንም ልዩነት ሁለቱም እስር ቤቶች፤ የሽብር ውጤቶች ናቸው፣ የስቃይ አምባዎች ናቸው፣ ለአሸባሪነት የድል ምልክቶች ናቸው። የአሜሪካ መንግስት የጓንታናሞ እስር ቤትን ለመዝጋት ወስኗል፣ ማዕከላዊ ግን እስካሁን አልተዘጋም። በመሆኑም፣ ቀይ-ሽብር “የታሪክ ጠባሳ” አይደለም፣ ዛሬም ድረስ ያመረቀዘ ቁስል ነው። የቀይ-ሽብር ዘመቻ ሀገርን መሃን ሲያደርግ፣ ማዕከላዊ የትውልድ ማጨናገፊያ ቦታ ነበር። ይህ የስቃይ አምባ እስካልተዘጋ ድረስ መሃንነት ከትውልድ ትውልድ እየተላለፈ ይቀጥላል። “ከጓንታናሞ እስከ ማዕከላዊ” በሚል ርዕስ በአራት ተከታታይ ፅኁፎች የማዕከላዊ እስር ቤት ለምን መዘጋት እንዳለበት፤ ከሀገር ሰላምና ደህንነት፣ ከምርመራ ሙያዊ አሰራር፣ እንዲሁም ከፖለቲካና የሞራል ዕሴት አንፃር ዝርዝር ማብራሪያ ለመስጠት እሞክራለሁ።

በተለምዶ “ማዕከላዊ” (Ma’ekelawi) የሚባለው ሙሉ መጠሪያ ስሙ፣ “በኢትዮጲያ የፌዴራል ፖሊስ ኃይል ማዕከላዊ የወንጀል ምርመራ ቢሮ” (Ethiopian Federal Police Force Central Bureau of Criminal Investigation) ነው። የማዕከላዊ እስር ቤት የተገነባው በቀዳማዊ ኃይለስላሴ መንግስት ዘመን ሱሆን በወቅቱ “ማዕከላዊ የወንጀል ምርመራ ክፍል” (Central Investigation Department (C.I.D.)) ተብሎ ይጠራ እንደነበር በወቅቱ በተማሪዎች እንቅስቃሴ ተሳታፊ የነበረና በቦታው ታስሮ የነበረ ግለሰብ አጫውቶኛል። በንጉሱ ዘመን ለመደበኛ የወንጀል ምርመራ ተግባር ከመዋሉ ባለፈ፣ የስቃይ ምርመራ (torture interrogation) ይደረግበት ነበር ለማለት የሚያስችል መረጃ አላገኘሁም። በደርግ መንግስት ግን፣ በተለይ ከቀይ-ሽብር ዘመቻ ጋር ተያይዞ፣ ይህ የወንጀል ምርመራ ክፍል ወደ የስቃይ አምባነት መቀየሩ እሙን ነው። ደርግ ከመደበኛ የወንጀል ምርመራ ዘዴዎች ባለፈ በተጠርጣሪዎች ላይ የስቃይ የጀመረበትን መሰረታዊ ምክንያት ለመረዳት ከቅርብ ግዜ አለም-አቀፍ ክስተቶች ጋር አያይዞ ማየቱ ጠቃሚ ይመስለኛል። ለዚህ ደግሞ የመስከረም 1 (9/11) የሽብር ጥቃት ተከትሎ የአሜሪካ መንግስት እንደ ጓንታናሞ (Guantanamo) ባሉ እስር ቤቶች ለምንና እንዴት የስቃይ ምርመራ እንዲካሄድ እንደፈቀደ መገንዘብ በቀይ-ሽብር ዘመን በኢትዮጲያ የነበረውን ሁኔታ በግልፅ ለመረዳት ያግዛል።

በማዕከላዊ እስር ቤት የስቃይ ምርመራ በስፋት የተጀመረው በኢትዮጲያ ሕዝቦች አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) መሪነት በደርግ አባላትና ደጋፊዎች ላይ “የነጭ-ሽብር” ጥቃት ከፈፀመ በኋላ ነው። በተመሣሣይ፣ አሜሪካም በጓንታናሞ የስቃይ ምርመራ የጀመረችው ከአልቃይዳ የሽብር ጥቃት በኋላ ነው። መስከራም 11/2001 ዓ.ም (እ.አ.አ) በአሜሪካ ላይ የደረሰውን የሽብር ጥቃት ተከትሎ፣ የፕረዜዳንት ጆርጅ ቡሽ የመጀመሪያ እርምጃ ጥቃቱን “የሽብር ወንጀል” ከማለት ይልቅ በአሜሪካ ላይ የተቃጣ ይፋዊ “ጦርነት” (War) መሆኑን ማወጅ ነበር። በዚህ መሰረት የዓለም-አቀፉ የፀረ-ሽብር ጦርነት መታወጅን ተከትሎ በተለያዩ እስር ቤቶች የስቃይ ምርመራ ተጀመረ። እንደ ገጣሚና ተርጓሚ ነብይ መኮንን ያሉ የስቃይ ምርመራ የተፈፀመባቸው ሰዎች፣ ደረግ በማዕከላዊና ሌሎች እስር ቤቶች የስቃይ ምርመራ የጀመረው፡ “በኃይል (በነጭ-ሽብር) ሞክራችሁኛል፣ እኔም በኃይል ልክ አስገባችኋለሁ” በሚል አምባገነናዊ እሳቤ እንደነበር ይጠቅሳሉ። ስለዚህ፣ ጓድ መንግስቱ ኃይለማሪያም ሚያዚያ 1977 ዓ.ም (እ.አ.አ) መስቀል አደባባይ ላይ በደም የተሞላ ጠርሙስ ይዘው ሀገር-አቀፉን የቀይ-ሽብር ዘመቻ (Red Terror Campaign) ያወጁበት ሁኔታ ከፕረሄዳንት ቡሽ የፀረ-ሽብር ጦርነት (War on Terror) አዋጅ ጋር ተመሣሣይ ነው።

የቀይ-ሽብር ዘመቻ ከዛሬ 40 ዓመት በፊት በአንዲት ደሃ ሀገር ውስጥ በአንድ አምባገነን መሪ የታወጀ የሽብር ዘመቻ ነው። ዓለም-አቀፉ የፀረ-ሽብር ጦርነት ደግሞ ከ15 ዓመት በፊት በልዕለ-ሃያሏ አሜሪካ ፕረዜዳንት መሪነት የታወጀ የፀረ-ሽብር ጦርነት ነው። ነገር ግን፣ ከቦታና ግዜ በስተቀር፣ የኢትዮጲያ ቀይ-ሽብር ዘመቻ እና የአሜሪካ የፀረ-ሽብር ጦርነት በአንድ-ዓይነት የተሳሳተ እሳቤ የተፈፀሙ ታሪካዊ ስህተቶች ከመሆናቸው በተጨማሪ አንድ-ዓይነት የመነሻ ምክንያትና ውጤት ያላቸው ሲሆን፣ እሱም፡-ሽብር ነው። በመሆኑም፣ ሁለቱም በተመሣሣይ ሁለት የተሳሳቱ እሳቤዎች የተፈፀሙ ስህተቶች ናቸው። አንደኛ፡- ሁለቱም በአንድ ቡድን የተፈፀመን የሽብር-ጥቃት ወደ ሉዓላዊ-ጥቃት አግዝፎ የማየት፤ የሽብርተኝነት-ወንጀልን ከሉዓላዊነት-ጦርነት ጋር አዛብቶ የማየት ችግር አለባቸው። ሁለተኛ፡- ሁለቱም በአንድ ቡድን የተፈፀመ የሽብር ጥቃትን በሌላ የሽብር ጥቃት አፀፋ ለመስጠት፤ ሽብርን በሌላ ሽብር ለመከላከል የተደረጉ ሙከራዎች ናቸው። በዚህ ክፍል እነዚህ ሁለት መሰረታዊ ስህተቶች ያስከተሉትን “የፀረ-ሽብር ሽብር” በዝርዝር እንመልከታለን።

Photo - Taliban and al-Qaida suspects in orange jumpsuits at Guantanamo Bay prison complex [Credit: Zuma press/eyevine]
Photo – Taliban and al-Qaida suspects in orange jumpsuits at Guantanamo Bay prison complex [Credit: Zuma press/eyevine]

1ኛ፡- ለወንጀል ጦርነት ማወጅ በራሱ ወንጀል ነው!

የሽብር ጥቃት “ወንጀል ወይስ ጦርነት ነው?” የሚለውን ጥያቄ ከመመለሳችን በፊት በቅድሚያ “የአሸባሪዎች ዓላማ ምንድነው?” ማየት ይኖርብናል። የሽብር ጥቃት መሰረታዊ ዓላማ በሕብረተሰብ ዘንድ የፍርሃትና ስጋት ድባብ (climate of fear) በመፍጠር የራሳቸውን የፖለቲካና የኢኮኖሚ ጥቅምና ማስከበር ነው። ለምሳሌ፣ በአሜሪካ ላይ የሽብር ጥቃት የፈፀመው የአልቃይዳ መስራችና መሪ የነበረው ኦሳማ ቢላደን የተነሳለት ዋና ዓላማው በሀገሩ ሳውዲ ዓረቢያ ያለውን የንጉሳዊ ቤተሰብ ከስልጣን ማውረድ ነበር። የቢላደን ምክትል የነበረው አማን አልዛዋህሪ ደግሞ በግብፅ የሙስሊም ወንድማማቾች (Muslim Brothers) አባልና በቀድሞው የግብፅ ፕረዜዳንት፣ አነዋር ሳዳት ግድያ ተጠርጥሮ በእስር ላይ የነበረ ግለሰብ ነው። የእነዚህና የሌሎች ከከፍተኛ እስከ መካከለኛ የአመራር ደረጃ ላይ ያሉ የአሸባሪ ድርጅት መሪዎች፣ በራሳቸው ማህብረሰብ ዘንድ፤ የፖለቲካ ለውጥን፣ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን እና የመንፈሳዊ እምነት ተቀባይነትን ለማረጋገጥ ዓላማ ያላቸው ናቸው። የአሜሪካ መንግስት ግን ከላይ በምሳሌነት ከተጠቀሱት የአልቃይዳ መሪዎች ዓላማ ተፃራሪ የሆነ አቋም የሚያራምድ ነው። ስለዚህ፣ የአሜሪካ መንግስት እንደ ግብፅና ሳውዲ ዓረቢያ ላሉ አምባገነንና ጨቋኝ መንግስታት የሚያደርገውን የፖለቲካ፣ ኢኮኖሚና የጦር ኃይል ድጋፍ ማቋረጥ አስፈላጊ ነው። በዚህ መሰረት፣ በአልቃይዳ የተፈፀመው የሽብር ትቃት ዋና ዓላማ በአሜሪካኖች ላይ የፍርሃትና ስጋት ድባብ በመፍጠር ለሀገራቱ የሚያደርጉትን ዘርፈ-ብዙ ድጋፍ እንዲያቋርጡ ለማስገደድ ነው።

በኢትዮጲያ የነጭ-ሽብር ጥቃት የተፈፀመው ሀገር ውስጥ ባለ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅት፣ በኢትዮጲያ ሕዝቦች አብዮታዊ ፓርቲ (ኢህአፓ) ነው። በተመሣሣይ፣ የነጭ-ሽብር ጥቃት በአባላቱና ደጋፊዎቹ ላይ የፍርሃትና ስጋት ስሜት በመፍጠር ደርግ በአቋራጭ የያዘውን ሀገሪቷን የማስተዳደር ስልጣን በኃይል ለማስለቀቅ ያለመ ነበር። በእርግጥ ደርግ የዘመኑን ትውልድ የለውጥ አብዮት አጨናግፏል። ሆኖም ግን፣ ኢህአፓ በደርግ አባላትና ደጋፊዎች ላይ የፈፀመው የነጭ-ሽብር ጥቃት መሰረታዊ ዓላማ ከአልቃይዳ የሽብር ጥቃት ጋር ተመሣሣይ ነው። በደርግ አባላትና ደጋፊዎች ዘንድ ፍርሃትና ስጋት በመፍጠር የራሱን የፖለቲካ፣ ኢኮኖሚና ማህበራዊ አጀንዳ የማስፈፀም ዓላማ ነው የነበረው። የደርግ አባላትና ደጋፊዎች በሽብር ጥቃቱ ምክንያት ፍርሃትና ስጋት ውስጥ ገቡ።

የአልቃይዳ የሽብር ጥቃትን ተከትሎ የፕ/ት ጆርጅ ቡሽ አስተዳደር ከፍተኛ ባለስልጣናት መስከረም 17/2001 ዓ.ም ባደረጉት ስብሰባ ለፕረዜዳንቱንና ለሀገሪቱ የደህንነት ኃላፊዎች ከማንኛውም የሕግ ተጠያቂነት ነፃ የሚያደርግ፣ በሽብር ጥቃቱ ተሳታፊ/ተጠርጣሪ በሆኑ ሰዎች ላይ ማንኛውም ዓይነት የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዲፈፅሙ የሚፈቅድ ውሳኔ በሚስጥር አሳለፈ። ከዚያ በኋላ፣ የአሜሪካ የማዕከላዊ ደህንነት ኤጀንሲ (Central Intelligence Agency (C.I.A.)) በሽብር ጥቃቱ የተጠረጠሩ ሰዎች ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች የእያፈሰ በመጀመሪያ በሚስጥራዊ እስር-ቤቶች፣ ቀጥሎም በጓንታናሞ፣ ባግራምና አቡ-ግሬብ እስር ቤቶች የስቃይ ምርመራና የተለያዩ ኢሰብዓዊ ድርጊቶችን መፈፀም ጀመረ። በተመሣሣይ፣ መንግስቱ ኃይለማሪያም በ1977 ዓ.ም (እ.አ.አ) መስቀል አደባባይ ላይ የቀይ-ሽብር ዘመቻን በይፋ ካወጀ በኋላ ማንኛውም “አብዮት ጠባቂ” በሚል የጦር መሳሪያ የተሰጠው የቀበሌ ታጣቂ፣ ምንም ዓይነት የህግ ተጠያቂነት በሌለበት ሁኔታ፣ “ፀረ-አብዮት ነው” ባለው ሰው ላይ የማሰርና የመግደል መብት ተሰጠው። የሕዝብን ሰላምና ደህንነት ከማስከበር ይልቅ “የመደብ ትግሉን ማፋፋም” (intensification of the class struggle) የሀገሪቱ ፖሊስ ተልዕኮ እንዲሆን ወሰነ።  ከዚህ በኋላ ነው፣ ቀድሞ የወንጀል ምርመራ ክፍል (Central Investigation Department (CID) በነበረው “ማዕከላዊ” (Ma’ekelawi) እስር ቤት የስቃይ ምርመራ በስፋት የተጀመረው።

ሁለቱም መንግስታት በአንድ አንድ ቡድን ለተፈፀመባቸው የሽብር ጥቃት ምላሽ ለመስጠት በሚል፣ እንደ መንግስት በቁጥጥራቸው ያለውን የሀገርና የህዝብን ሰላምና ደህንነት ለማስከበር የተዘረጋውን የመንግስት መዋቅር እና ንብረት በመጠቀም የፀረ-ሸብር ጦርነት አወጁ። ነገር ግን፣ የሽብር ጥቃትን በፀረ-ሽብር ጦርነት ለመመከት መሞከር፣ ሽብርን በሽብር እንደመመከት ነው። ቀጥሎ በተ.ቁ 2 ላይ በዝርዝር እንደምናየው፣ ሽብርን በፀረ-ሽብር ጦርነት/ዘመቻ ምላሽ መስጠት “ዓይንን በዓይን” የሚሉት ነው። ወደዚያ ከማለፋችን በፊት ግን፣ “ሽብርተኞችን በወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ከመቅጣት ይልቅ ጦርነት መግጠም ለምን አስፈለገ?” የሚለውን እንመልከት።   

የሽብር ወንጀልን ከጦርነት እኩል አዛብቶ የማየቱ ፋይዳ የሕግ ተጠያቂነትን ማስቀረት ነው። ለዚህ ደግሞ የአልቃይዳ የሽብር ጥቃትን ተከትሎ የአሜሪካ መንግስት በፍርሃትና ስጋት ውስጥ ሆኖ ያሳለፋቸውን ውሳኔዎች ማየት በቂ ነው። የጆርጅ ቡሽ አስተዳደር ከፍተኛ ባለስልጣናት መስከረም 17/2001 ዓ.ም ባደረገው ስብሰባ ለፕረዜዳንቱንና ለሀገሪቱ የማዕከላዊ ደህንነት ኤጀንሲ (Central Intelligence Agency (C.I.A.)) ከማንኛውም የሕግ ተጠያቂነት ነፃ የሚያደርግ ሚስጥራዊ ውሳኔ አሳለፈ። ከዚያ በመቀጠል፣ በፀረ-ሽብር ጦርነቱ የተያዙ ሰዎችን፤ እንደ ማንኛውም የጦር ምርኮች በጄኔቩ ድንጋጌ መሰረት መብታቸው እንዳይከበር “ተጠርጣሪ እስረኞች” (Detainees) የሚል ስያሜ ተሰጣቸው። እንደ ማንኛውም የወንጀል ተጠርጣሪ በአሜሪካን ሕግ መሰረት እንዳይዳኙ ደግሞ እንደ ጓንታናሞ፣ ባግራምና አቡ-ግሬብ ያሉ የስቃይ ምርመራ የሚደረግባቸው እስር ቤቶችን ከሀገሪቱ ግዛት ውጪ እንዲቋቋሙ አደረገ። በዚህ መሰረት፣ በፀረ-ሽብር ጦርነቱ ተሳትፎ/ተጠርጥሮ የተያዘ ማንኛውም ሰው፤ እንደ የጦር ምርኮኛ በጄኔቫ ኮንቬንሽን (Geneva Convention) መሰረት ሰብዓዊ መብቱ እንዳይከበር፣ እንደ ተጠርጣሪ ወንጀለኛ በሀገሪቱ ሕግ መሰረት ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቱ እንዳይከበር ተደረገ።

ከላይ ለመግለፅ እንደተሞከረው፣ አልቃይዳ የሽብር ጥቃት ተጠርጥረው የሚያዙ ሰዎች፤ የጦር ምርኮኛ (Prisoners of war) እንዳይባሉ “እስረኞች” (Detainees) ተብለዋል፣ ተጠርጣሪ “ወንጀለኞች” እንዳይባሉ በቁጥጥር ስር የዋሉት በወንጀል ተከሰው ሳይሆን በአሜሪካ ጦርነት ከፍተዋል በሚል ተጠርጥረው ነው። ስለዚህ፣ በአሜሪካ መራሹ የፀረ-ሽብር ጦርነት የተያዙ ሰዎች የጦር ምርኮኞች አይደሉም፣ ተጠርጣሪ ወንጀለኞች አይደሉም። በመሆኑም፣ በአሜሪካ ቁጥጥር ስር በሚውሉ ሰዎች ላይ ኢሰብዓዊ ድርጊት ቢፈፀም ሊያስጠይቅ የሚችል በግልፅ የተቀመጠ ሀገራዊ ሆነ ዓለም-አቀፋዊ ሕግ የለም። በዚህ መልኩ ጥፋተኞችን ከሕግ ተጠያቂነት ነፃ ካደረጉ በኋላ በቁጥጥራቸው ስር ባዋሏቸው ሰዎች ላይ የስቃይ ምርመራን (torture interrogation) ጨምሮ የተለያዩ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ለመፈፅም የሚያስችል ምቹ ሁኔታ ፈጠሩ። ከዚህ በኋላ፣ የሕግ ተጠያቂነት በሌለበት አሰራር አሜሪካ በታሪኳ ከፍተኛ የሆነ የፖለቲካና የሞራል ኪሳራ ያስከተለባትን የሰብዓዊ መብት ጥሰት ፈፀመች። በአጠቃላይ፣ ሽብርና ሽብርተኝነት የፍርሃትና የስጋት ድባብ በመፍጠር የራስን የፖለቲካ፣ ኢኮኖሚና መንፈሳዊ አጀንዳ ለማስፈፀም የማቀድና የመሞከር ወንጀል እንጂ በሉዓላዊነት ላይ የተቃጣ ቀጥተኛ ጥቃት አይደለም። ስለዚህ፣ የሽብር ጥቃት ወንጀል እንጂ ጦርነት አይደለም። በወንጀልና ወንጀለኛ ላይ ጦርነት የማወጅ ዓላማው የቂም-በቀል ጥቃት ለመፈፀምና የሕግ-ተጠያቂነትን ለማምለጥ ነው። ስለዚህ፣ ለወንጀል ጦርነት ማወጅ በራሱ ወንጀል ነው!

2ኛ፡- የፀረ-ሽብር ሽብር: “ዓይንን በዓይን”

የመንግስቱ ኃይለማሪያም እና የጆርጅ ቡሽ አስተዳደር በየፊናቸው ያጋጠማቸውን የሽብር ጥቃት ከወንጀልነት ባለፈ በሉዓላዊነት ላይ እንደተቃጣ ጦርነት መውሰዳቸው ስህተት መሆኑን ለማሳየት ተሞክሯል። ይህን ተከትሎ የተፈጠረው ደግሞ ሽብርን በሌላ ሽብር አፀፋ ለመስጠት የተሞከረባቸው አሳዛኝ የታሪክ አጋጣሚዎች ናቸው። የአሜሪካ መንግስት የፀረ-ሽብር ጦርነት እና የኢትዮጲያው የቀይ-ሽብር ዘመቻ ሁለቱም ሽብርን በሌላ ሽብር ለመከላከል የተደረጉ ሙከራዎች ናቸው። በዚህ መልኩ የተደረገው ሙከራ ግን ከመጀመሪያው የባሰ የሰውና የንብረት መጥፋት አስከትሏል። ሀገራቱን ለከፍተኛ የፖለቲካና የሞራል ኪሳራ ዳርጓል። የአሜሪካ መንግስት በአልቃይዳ ለተፈፀመበት የሽብር ጥቃት የፀረ-ሽብር ጦርነትን በማወጅ አፀፋ ሲሰጥ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ንፁሃን የኢራቅ፣ አፍጋኒስታን፣ ፓኪስታን፣ የመን፣…ወዘተ ዜጎች በግፍ ተጨፍጭፈዋል። ከተለያዩ የዓለም ሀገራት እየታፈኑ በተወሰዱ የሌላ ሀገር ዜጎች ላይ አሰቃቂ የሆነ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተፈፅሟል። በተመሣሣይ፣ የደርግ መንግስት ባካሄደው የቀይ-ሽብር ዘመቻ የተማረውን ትውልድ በግፍ ጨፍጭፏል። እንደ ማዕከላዊ ባሉ እስር ቤቶች አሰቃቂ የሆኑ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በዜጎቹ ላይ ፈፅሟል።

በአሜሪካ ላይ የሽብር ጥቃት የፈፀመው አልቃይዳ መቀመጫው አፍጋኒስታን ያድርግ እንጂ የአሸባሪ ቡዱኑ መሪዎች የትውልድ ቦታና የድጋፍ መሰረት ያለው በመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ነው። በፀረ-ሽብር ጦርነቱ የመጀመሪያ ተጠቂዋ ሀገር አፍጋኒስታን ብትሆንም በጥቂት አመታት ውስጥ ጦርነቱ ወደ  ከአፍጋኒስታን ወደ ፓኪስታን፣ ቀጥሎም ወደ ኢራቅ እያለ፣ አሁን እንደሚታየው ከናጄሪያ እስከ አፍጋኒስታን፣ ከሶሪያ እስከ ሶማሊያ ተስፋፍቷል። በደርግ አባላትና ደጋፊዎች ላይ የተፈፀመው የነጭ-ሽብር ጥቃት መነሻው አዲስ አበባ ቢሆንም በትንሽ ግዜ ውስጥ ወደ መላ ሀገሪቱ ተስፋፍቷል። በዚህም፣ በመቶ ሺህዎች ለሚቆጠሩ የሀገሪቱ ዜጎች ሕልፈት ምክንያት ሆኗል። በአሜሪካ መስከረም 1 (9/11) የተፈፀመው የሽብር ጥቃት የሞቱት በሺህ የሚቆጠሩ ዜጎች ናቸው፣ በፀረ-ሽብር ጦርነቱ የተገደሉና የተፈናቀሉ ሰዎች ብዛት ግን በሚሊዮኖች የሚቆጠር ነው። በነጭ-ሽብር ጥቃት የተፈፀመባቸው የደርግ አባላትና ደጋፊዎች በቀይ-ሽብር ከተገደሉት ኢትዮጲያኖች ጋር ለንፅፅር እንኳን የሚቀርብ አይደለም።

በእርግጥ በሁለቱም ሀገሮች የተፈፀሙ የሽብር ጥቃቶች ለችግሩ መነሻ ናቸው። ነገር ግን፣ ከመጀመሪያዎቹ የሽብር ጥቃቶች እጅግ በባሰ ሁኔታ የሰው ሕይወት መጥፋት፣ የንብረት ውድመት እና የሰብዓዊ መብት ጥሰት የተፈፀመው በፀረ-ሽብር ጦርነቱ ወቅት ነው። በአሜሪካ የፀረ-ሽብር ጦርነት እና በኢትዮጲያ የቀይ-ሽብር ዘመቻ የደረሰው የፖለቲካና የሞራል ኪሳራ በአልቃይዳና በነጭ-ሽብር ጥቃት አማካኝነት ከተከሰተው ጋራ በፍፁም ሊነፃፀር አይችልም። በአሜሪካ ላይ የተፈፀመው የሽብር ጥቃት ከሁሉም በላይ አሜሪካን አሸብሯዋል፣ በአፀፋው የታወጀው የፀረ-ሽብር ጦርነት ግን እስካሁን መላ ዓለምን ነው እያሸበረ ይገኛል። በደርግ ላይ የተወሰደ የሽብር ጥቃት የደርግ አባላትና ደጋፊዎችን አሸብሯል፣ በአፀፋው የታወጀው የቀይ-ሽብር ዘመቻ የፈጠረው ጠባሳ ግን እስካሁን ከኢትዮጲያኖች ፊት ላይ አልጠፋም። ስለዚህ፣ የፀረ-ሽብር ጦርነት/ዘመቻ በራሱ ሽብርን በሌላ ሽብር ለመመከት የተደረገ ነው። ለአንድ ቡድን የሽብር ጥቃት የአንድ ሀገር ሕዝብና መንግስት የለየለት ሽብር የሚያስገባ፣ የበለጠ ሰውና ንብረት የሚያጠፋ፣ የባሰ የመብት ጥሰትና ጭካኔ የሚያፈፀምበት፣ የበለጠ ፍርሃትና ስጋት የሚነግስበት ነው። ይህ ሽብርን በሽብር ለመመከት የሚደረገው ጥረት “ዓይን-በዓይን” መርህ የሚመራ ነው። “ዓይን-በዓይን” ስንል የሁላችንም ዓይን ይጠፋል።

*********

ከጓንታናሞ እስከ ማዕከላዊ ተከታታይ ፅሁፍ

-> ክፍል-2 “ፍርሃትን በፍርሃት”

Seyoum Teshome is a Lecturer at Ambo University Woliso Campus and head of Management Department. He was born in Arsi, Assela, in 1979 and studied Management at Harameya University and MBA at Mekelle University. He also blogs at http://ethiothinkthank.com

more recommended stories