ተጠያቂው ማን ነው፡- መንግስት ወይስ እነጃዋር?

አቤት … ሀገር አቀፍ የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ፈተና ከመራዘም ጋር ተያይዞ ማህበራዊ ድረ-ገፆች ላይ ቀውጢ ሆኗል። በተለይ ደግሞ ፌስቡክ ላይ ብዙ  ነገር አያየን ነው። ትላንት ብዙ ነገር አየን፣ ዛሬም ብዙ እያየን ነው፣ ነገ ደግሞ ብዙ እናያለን። አዎ… ትላንት በዚሁ መድረክ ነበር “ሀገር-አቀፍ ፈተናውን አውጥቶ ማህበራዊ ድረገፅ ላይ ለህዝብ በመበተን ፉርሽ ለሚያደርግ ሰው የመቶ ሺህ ብር ወሮታ ይከፈለዋል” የሚል ማስታወቂያ ያነበብኩት። ዛሬ ደግሞ የሂሳብና እንግሊዘኛ ፈተና የጥያቄ ወረቀቶች ከነመልሶቻቸው ተለጥፈው አየሁ። ነገስ ምን እመለከት ይሆን?

በእርግጥ ትላንት እና ዛሬ በማህበራዊ ድረገፆች አማካኝነት የተከሰቱትን ነገሮች “ሾላ-በድፍኑ” ካየናቸው ነገ ላይ ምን ሊከሰት እንደሚችል መገመት ያዳግታል። ነገር ግን፣ ዛሬ የትላንት ውጤት ነው፣ ነገ ደግሞ የዛሬ ውጤት ነው። ትላንት የሆነውን በጥልቀት ስንመለከት፣ ዛሬ ላይ እየሆነ ያለውን እንገነዘባለን፣ ነገ ላይ ሊከሰት የሚችለውን መገመት እንችላለን። ከከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ፈተና ጋር ተያይዞ የተፈጠረው ነገር ነገም እንዳይደገም ለችግሩ ዘላቂ መፍትሄ መስጠት አለብን። ለዚህ ደግሞ የችግሩን ዋና መንስዔ መለየት ይጠበቅብናል።  የችግሩን ዋና መንስዔ በመለየት ከዘላቂ መፍትሄ ላይ ለመድረስ ግን ዛሬ መመለስ ያለበት አንድ ቁልፍ ጥያቄ አለ፡- “ለተፈጠረው ችግር ተጠያቂው ማን ነው?”። ለዚህ ጥያቄ የሚሰጡት ምላሾች እንደ ግዜው ይለያያሉ። በመሆኑም፣ ግዜውን “ትላንት፣ ዛሬና ነገ” ብለን በመክፈል ለጥያቄው ምላሽ እንፈልግ።

Photo - An Ethiopian school
Photo – An Ethiopian school

1ኛ፡- ዛሬ

በዛሬው እለት የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ፈተና ተቋርጧል። ለዚህ ዋናው ምክንያት በሀገር-አቀፍ የፈተናዎች ድርጅት የተዘጋጁ ሁለት የፈተና ወረቀቶች በትላንትናው እለት (ግንቦት 21/2008 ዓ.ም) ያለአግባብ በማህበራዊ ድረገፆች ላይ ከነመልሶቻቸው በይፋ ለህዝብ መለቀቃቸው ነው። ዛሬ ላይ ሆነን “ለችግሩ ተጠያቂው ማን ነው?” ብለን ስንጠይቅ፣ ተጠያቂዎቹ በዚህ ኃላፊነት የጎደለው ተግባር የተሳተፉት አካላት ናቸው። በዋናነት፤ የሙያ ስነ-ምግባርንና ህግን በመተላለፍ የፈተና ወረቀቶች አሳልፎ የሰጠው ግለሰብ፣ እነዚህን የፈተና ወረቀቶች ፍፁም ኃላፊነት በጎደለው መልኩ በማህበራዊ ድረገፆች ላይ የለቀቀው አቶ ጀዋር መሃመድ እና ግብረ-አበሮቹ ለችግሩ ዋና ተጠያቆች ናቸው። ፈተናው እንዲቋረጥ በማድረጉ ረገድ መንግስት ትክክለኛና ኃላፊነት ከሚሰማው አካል የሚጠበቅ ወሳኔ አስተላልፏል። በተቃራኒው፣ በአቶ ጀዋር መሃመድና በግብረ-አበሮቹ የተፈፀመው ድርጊት በግድ-የለሽነትና ማን-አለብኝነት የተፈፀመ ህገ-ወጥ ተግባር ነው። ይሁን እንጂ፣ ይህ ድምዳሜ እውነትነቱ ለዛሬና ዛሬ ብቻ ነው። ምክንያቱም፣ የትላንቱ እውነት የዚህ የተገላቢጦሽ ነው።

2ኛ፡- ትላንት

ከህዳር ወር መጨረሻ አከባቢ ጀምሮ በኦሮሚያ ክልል ለተነሳው የህዝብ ተቃውሞና አለመረጋጋት መንግስት አስቸኳይ መፍትሄ እንዲሰጥ ብዙዎች ሃሳብና አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። ከከዚህ ቀደሙ በተለየ አብዛኛው የሕብረተሰብ ክፍል ለችግሩ አፋጣኝ መፍትሄ እንዲሰጠው ሲጠይቅ ነበር። ለምሳሌ፣ እኔ እንኳን በግሌ በችግሩ ዙሪያ ብዙ ተከታታይ ፅሁፎችን አቅርቤያለሁ። ከእነዚህ ውስጥ፣ የክልሉ የፀጥታ ሃይሎች በጥድፊያ የወሰዱት የኃይል እርምጃ እንዴት ችግሩን እንዳባባሰው የሚያሳይ – “ወሊሶ-ከሰላም ወደ ሱናሚ” የሚል፤ የችግሩ ዋና መንስዔ የመልካም አስተዳደርና የፍትህ እጦት እንደሆነ ለመጠቆም – “የአ.አ ማስተር ፕላን ማስቀረት ስህተትን መሳሳት ነው” የሚል፤ እንዲሁም ከዛሬው ችግር ጋር በቀጥታ የተያያዘውና መንግስት አስቸኳይ የመፍትሄ እርምጃ እንዲወስድ የሚጠይቀው -“የኦሮሚያ ተቃውሞና ትምህርት፡ መስከረም 03 እንገናኝ” የሚለውንና ሌሎች ተመሣሣይ  ፅሁፎችን በዚሁ ድረገፅ ላይ አውጥቼ ነበር።

በወቅቱ ከመንግስት ሲሰጥ የነበረው ምላሽ በግድየለሽነትና ማን-አለብኝነት የታጀበ ነበር። ለምሳሌ፣ ጠ/ሚ ኃይለማሪያም ደሳለኝ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው በክልሉ ለተከሰተው “ሁከትና አለመረጋጋት” መንስዔው የዴሞክራሲ ጥያቄ እና መልካም አስተዳደር እጦት እንደሆነ በመግለፅ ለተፈጠረው ችግር በይፋ “ይቅርታ” ከጠየቁ በኋላ ወጣቶቹን ወደ ጦላይ ወስዶ ማሰር ከግድየለሽነት ሌላ ምንም ሊባል አይችልም። በተመሣሣይ፣ ዛሬ ላይ እነ ጀዋር መሃመድ በማን-አለብኝነት ፈተናው እንዲቋረጥ ያደረጉበት ሁኔታ፣ የኢትዮጲያ መንግስት “OMNን” ጨምሮ “ESAT” እና ማህበራዊ ድረገፆችን በአንዳንድ የክልሉ አከባቢዎች እንዲቋረጡ ካደረገበት የማን-አለብኝነት ውሳኔ ጋር ፍፁም ተመሣሣይ ነው። በአጠቃላይ፣ ዛሬ የተፈጠረው ችግር መንስዔው ትላንት መንግስት በግድየለሽነት እና በማን-አለብኝነት የወሰዳቸው እርምጃዎች እንደመሆናቸው፣ የኢህአዴግ መንግስትም ለችግሩ ተጠያቂ ነው።

3ኛ፡- ነገ

ዛሬ የትላንት ውጤት፣ ነገ ደግሞ የዛሬ ውጤት ነው። ነገ እነ ጀዋር መሃመድ ጥያቄዎቻቸውን በአግባቡ ማቅረብና አስቸኳይ ምላሽ እንዲሰጣቸው በሰለጠነ መንገድ መጠየቅ አለባቸው። ሆኖም ግን፣ ልክ እንደ ዛሬው ነገም በግድየለሽነትና በማን-አብኝነት የሚቀጥሉ ከሆነ በትውልድና በሀገር ሃብት ላይ ቁማር እንደመጫወት ይቆጠራል። በተመሣሣይ፣ መንግስት ከተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ዘንድ ለሚነሱ ጥያቄዎች፣ በተለይ ደግሞ የክልሉ ወጣቶች ለሚያነሱት ጥያቄዎች ስር-ነቀልና ዘላቂ የሆነ መፍትሄ መሻት ይጠበቅበታል። ነገር ግን፣ ልክ እንደ ትላንቱ፣ ነገንም በግድየለሽነትና በማን-አብኝነት ለማለፍ የሚሞክር ከሆነ በራሱና በሀገሪቱ ህልውና ላይ ቁማር እየተጫወተ መሆኑን ሊያውቅ ይገባል።

በመጨረሻም፣ ዛሬ ለተፈጠረው ችግር እነ ጀዋር መሃመድ ተጠያቂዎች ናቸው። ትላንት ለተፈጠረው ችግር ግን መንግስት ተጠያቂ ነው። ነገ ለሚፈጠረው ችግር ደግሞ ሁለቱም ተጠያቂዎች ናቸው። እንደ አጠቃላይ ሲታይ ግን፣ ትላንት ባይኖር  ዛሬና ነገ የሉምና፣ ለችግሩ ዋና ተጠያቂ መንግስት ራሱ ነው።

*********

Seyoum Teshome is a Lecturer at Ambo University Woliso Campus and head of Management Department. He was born in Arsi, Assela, in 1979 and studied Management at Harameya University and MBA at Mekelle University. He also blogs at http://ethiothinkthank.com

more recommended stories