የተገኘዉን ሰላምና እድገት የሚንድ የአመራር ዘይቤ ባስቸዃይ ይታረም!(ሜ/ጄ አበበ ተ/ሃይማኖት)

አበበ ተክለሃይማኖት(“ጆቤ”)
(ሜጀር ጄኔራል፣ PhD Candidate)

ታላቁ የሰላምና ደህንነት ሙሁሩ ጆሃን ጋልቱንግ ስለ ሰላም እሚከተለዉን ይላል “Peace is a revolutionary idea; peace by peaceful means defines that revolution as nonviolent. That revolution is taking place all the time; our job is to expand it in scope and domain. The tasks are endless; the question is whether we are up to them.” (Galtung et al, 2002: xi) ትርጉም: “ሰላም አብዮታዊ ሃሳብ ነው፤ ሰላም በሰላማዊ መንገድ ሙሆኑ አብዮቱን ከሁከት የራቀ ያደርገዋል። አብዮቱ ሁሌም የሚካሄድ ነገር ነው፤ የኛ ስራ መሆን ያለበት ይህንን ማስፋት ነው። ስራው መጨረሻ የለዉም፤ ጥያቄው ግን እኛ ለዛ ስራ እምንመጥን መሆናችን ላይ ነው” ይላል።

መግቢያ

ኢትዮጵያ መንታ መንገድ ላይ ትገኛለች። በአንድ በኩል በክፈተኛ ፍጥነት ከሚያድጉት አገሮች አንድ ሆኖለች፤ እሰይ አገሬ እደጊ ተመንደጊ የሚያሰኝ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ አገራችንና ህዝቦቿ የጀመሩትን የዴሞክራታይዜሽን ሂደት ከፈተኛ አደጋ ተጋርጦበት ይገኛል። በዴሞክራታይዜሽን እና ኢ ዴሞክራታይዜሽን ሃይሎች መሃከል የሞት ሽረት ትግል እየተካሄደ ነው። ቻርለስ ቲሊ የተባለ የዘርፉ ተመራማሪ ዴሞክራታይዜሽን እና ኢ ዴሞክራታይዜሽን በሚመለከት እንዲህ ይላል:

“Democratization means net movement towards more equal, more protected and more binding constitution. De democratization, obviously then means net movement towards narrower, more un equal, less protected and less binding constitution” (Charles Till: 2007). ትርጉም: ዴሞክራታይዜሽን ማለት ወደ በለጠ እኩልነት፣ ወደ በለጠ ከለላ፣ ወደ በለጠ ሁሉንም ሊገዛ ወደሚችል ህገ መንግስት የሚደረግ ድምር እንቅስቃሴ ነው። ኢ ዴሞክራታይዜሽን ድግሞ ወደ ጠባብ፣ የበለጠ እኩል ያልሆነ፣ ዝቅተኛ ከለላ ሊሆን ወደሚችልና ተፈፃሚነቱም አነስተኛ ወደሆነ ህገ መንግስት የሚድረግ ድምር እንቅስቃሴ ነው ይላል።

ዴሞክራቲክ ምህዳሩ እየቀጨጨ “ዴሞክራሲ” የህልዉና ጥያቄ መሆኑን ጎልቶ የሚታይበት ግዜ ነው ያለነው። ኢ ዴሞክራቲክ ሃይሎች በመንግስትም በፓርቲዉም ካሸነፉ እስካሁን የተገኘዉን ሰላምና እድገት መና ሆኖ ይቀራል። ብዙህነት ባግባቡ ማስተናገድ ባለባት ኢትዮጵያ ኢ ዴሞክራቲክ ሃይሎች የበላይ መሆን ማለት መዘዙ ከዚ እስከዚ ተብሎ በቀላሉ ተነግሮ የሚታለፍ ነገር አይደለም። ለኢትዮጵያ ዴሞክራሲ የምርጫ ጉዳይ አይደለም።

የአገራችን ህዝቦች የደርግን ስርዓት አሽቀንጥረው የጣሉት ዴሞክራስያዊ ስርዓት በመከጅል ነው። ለነዚህ ህዝቦች ዴሞክራሲ ይቆይልህ፤ አሁን ልማት ላይ ብቻ አተኩር ማለት ሞኝነት ነው። ዴሞክራስያዊ ምህዳሩ በጠበበ ቁጥር ልማት ይቀጭጫል፣ ሰላም ይደፈርሳል ፣ በድምሩ የአገራችን ህልዉና አድጋ ላይ ይወድቃል። አሁን የአደጋ ደወሎች እያቓጨሉ ነው። በዚህም ምክንያት የተገኙትን ኢኮኖምያዊ እድገት እያጣጣምን፣ ህዝቦቻችንና መንግስታችን በቁርጠኝነት የዴሞክራሲ ሂደቱን ማስቀጠል ይኖርብናል ሲባል የልማትና የዴሞክራሲ እንከፎች መሰረታዊ መፍትሄ ማግኝት አለባቸው ማለት ነው። ለዚህም ሲባል መንግስት በታክቲክና በታችኛው አመራር ከማተኮር ይልቅ በዋናነት ከላይ ባሉት ተቋማት እና አመራር፣ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች፣ እንዲሁም አደረጃጀት እና አሰራር በማስተካከል አመራርነቱን ማረጋገጥ የግድ ይለዋል። ተቋማት እዉነተኛ የዴሞክራሲ ተቋማት እንዲሆኑ በማድረግ ዴሞክራቲክ ብሄርተኝነት ያስፋፋ። ቁርጠኝነት እና ጥበብ በተሞላበት መንገድ ከተሰራ አሁንም እማይቻል ነገር የለም፤ ምክንያቱም ኢህአዴግ ከሞት አፋፍ ተነስቶ፣ አንሰራርቶ ለድል የመብቃት ባህል አለውና።

የኢትዮጵያ የዴሞክራስያዊ አስተዳደር ሁኔታዎችና የመፍትሄ አቅጣጫዎች

መስከረም 2008 በተሰራጨው “ብልሹ አስተዳደር የዴሞክራሲ ምህዳርን በማስፋት እና ቀጣይነት ባለም የዴሞክራሲ ተቋማት ግንባታ በወሳኝነት ይፈታል” በሚለው መጣጥፌ “100% አሸናፊነት አስቂኝና አደገኛ ነው” ብየ መጠቆሜ ይታወሳል። የጠቅላላ ምርጫው ዉጤት ከታወጀበት 6 ወር ባልሞላ ግዜ ዉስጥ 100% ያሸነፈው ኦህዴድ/ኢህአዴግ ትጥቅ የተቀላቀለበት ህዝባዊ ዓመፅ ተቀሰቀሰበት ። ህዝቡ በዴሞክራስያዊ/ መልካም አስተዳደር እጦት እየተለበለበ እያለ ነበር የ 100% አሽናፊነት ጡሩንባ የተነፋው። 100% አሸንፍኩ ሲል አሲቂኝ ሆኖ እንዳገኘነው፤ የቅርቡ ግዜ ክስተቶች ደግሞ አደገኛነቱ አሳይተዉናል።

ኣማራጭ ድምፅ (Alternative Voice) የማጣት ጉዳይ እንዴት ወደ ተደራጀ ተቃዉሞ ሊሸጋገር እንደሚችልና፤ ፀረ ሰላምና ፀረ ኢትዮጵያ ሃይሎች እንዴት የኦሮሞና ሌሎች ህዝቦች ለዴሞክራስያዊ መብታቸው የሚያደርጉት ትግል እንዴት መጥለፍ እንደሚችሉና ለኣዉዳሚ ኣላማቸው ሊበዘብዙት እንደሚችሉም ፍንጭና ትምህርት የሰጠ ክስተት ነው። የኮንሶና የቅማንትም እንዲሁ። በግዜውና በውቅቱ መልስ እና ሰሚ ያላገኙ ጥያቄዎች ተከማችተው ምን አይነት ማዕበል ፈጠረው አገራዊ ድህንነትን ሊፈታተን የሚችል ክስተት እንደሚፈጥርም ጭምር ትምህርት ወዉሰድ ለሚችል ሰው የሚያስተምር ነገር ነው።

የዴሞክራስያዊ/ የመልካም አስተዳደር ድክመቶች በሁሉም የአገሪቱ ክልሎችና በፌዴራል መንግስት በስፋት እና በጥልቀት እየተከሰቱ ያሉ ችግሮች ናቸው። መሰረታዊ ችግሮቹ በሁሉም ተመሳሳይ ቢሆኑም በመልክ (form) እና በጥልቀታቸው (Depth) ግን ሊለያዩ ይችላሉ። ከተለያዩ ህዝቦች የሚገኘው ግብረ መልስም በተለያዩ objective and subjective ምክንያቶች በመልክም በግዜም ሊለያዩ ይችላሉ። ሁሉም ህዝቦች በ ዴሞክራስያዊ አስተዳደር እጦት እየተለበለቡ ናቸው። የኦሮሞ ተቃዉሞ የቀዘቀዘ ቢመስልም፤ በሌሎች ህዝቦች በዛ ደረጃ ተቃዉሞ ባይታይም የዴሞክራቲክ አስተዳደር ጉድለቶች ደረጃ በደረጃ መሰረታዊ መፍትሄ ካልተበጀለት “የተዳፈነ እሳት” መሆኑ አይቀርም።

100% አሸናፊነት የፖለቲካዊ ስርዓቱ ችግሮች ምልክት መሆኑ ታዉቆ ማስተካከል ይገባል። የህዝቦችና ብሎም ያገራችንን ህልዉና የሚፈታተኑት መሰረታዊ ችግሮቻችን በሚገባ ተጠንተው ህዝባችንን በተሟላ ባሳተፈ ግልፅነትና ተጠያቂነት በሰፈነበት፤ የህግ የበላይነት በመከተልና ዴሞክራስያዊ ሕገ መንግስታዊ ተቛሞችን በመገምገም አጠቃላይ ስርዓቱን መፈተሽ ይገባል። ብዝሃነት ባለበት አገር አንድ ፖለቲካዊ ሃይል ሁሉንም ነገር ጠቅልሎ ከያዘ አንድ አደገኛ በሽታ እየያዘው መሆኑ መንገንዘብ መቻል አለበት።

የኢትዩጵያ የዉጭና የብሄራዊ ድህንነት ፖሊሲ ያገራችንን ድህንነት የሚፈታትኑ ዋናዎቹ የስጋት ምንጮች ዉስጣዊ (internal) እንደሆኑና እነሱም ድህነት፣ ሃላቀርነትና፣ በዴሞክራሲ ዙርያ የሚታዩ ችግሮች መሆናቸዉን በማያወላዉል መልኩ እንደሚከተለው ያስቀምጠዋል “የዴሞክራሲና የኢኮኖሚ እድገት አለማምጣት ማለት ድህንነት አደጋ ላይ ወደቀ ማለት ነው። ይህ ማለት ጥገኞች እና ድሆች መሆናችንን እራሳችንን ቀና አድርገን እንዳንሄድ ያደርገናል ማለት ነው። የመበታተን አደጋ ሊጋረጥ ይችላል።” (ኢወብድፓ: 18) ከዚህ መረዳት የምንችለዉ ነገር እንደኛ ዓይነት ፍላጎቶች በስርዓቱ ባልተሟሉበት ማህበረሰብ የከፋ ድህነትና ብልሹ ኢ ዴሞክራስያዊ አስተዳደር ማለት ተራ የፖለቲካ ጉዳይ ሳይሆን የደህንነት አደጋ የሚደቅን ነገር መሆኑ ነው፤ ተመሳሳይ ችግር በገጠማቸው አገሮች እንደምናየው ደግሞ አገር ተበተነ ማለት መዘዙ የከፋ ብቻ ሳይሆን፤ መልሶ የማገገም እድልም ላይኖረው ይችላል።

በአሁኑ ግዜ መንግስት “መልካም አስተዳደር የህልዉና ጉዳይ ነው” በማለት ችግሮችን ለመፍታት እየተንቀሳቀሰ ነው:: በ 1994 ዓ.ም በያኔው ማስታወቅያ ሚኒስቴር የታተመው “የኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ጉዳዩች” በሚል ርእስ ባሳተመው ፁሁፍ “ዴሞክራሲና መልካም አስተዳደር የህልዉና ጥያቄ ነው” ይላል። ኣያይዞም “ምክር ቤቶች የህዝብ ሉኣላዊነት መገለጫ የዴሞክራሲያዊ አስተዳደር እምብርት፤ የዴሞክራስያዊ አገዛዝ ኣዉራ ተቛሞች” ናቸው ይላል። የፌዴራል፣ የክልልና የወረዳ ምክርቤቶች በዚህ መመዘኛ ምን ይመስላሉ? ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው።

ችግር አለብን የሚለው እዉቅና የመፍትሄው አንድ እርምጃ ነው። መልካም አስተዳደር የሚለው ፅንሰ ሃሳብ (Concept) በዴሞክራቲክ አስተዳደር አገላለፅ እንደ አማራጭ (Alternative concept of democratic governance) አድርጎ ካስቀመጠው ከ ብሄራዊ ድህንነት ፖሊሲ ብዙም የሚጋጭ አይሆንም።መልካም አስተዳደር ከዴሞክራቲ አስተዳደር በተለየ እንደ ቢሮክራቲክ አስተዳደር ብቻ ሆኖ ከቀረበ ግን ክህገ መንግስት በመለስ ትልቅ የአገሪትዋ ሰነድ ከሚባለው የ ብሄራዊ ድህንነት ፖሊሲ ጋር እንዲጋጭ ያደርገዋል። የተምታቱ መግለጫዎች ባሉበት፣ አንዴ ችግሩ የፖለቲካ አይደለም፤ ከዴሞክራሲ ጋር ተያያዥነት የለዉም ሲባል ፤ መንግስት መልካም አስተዳደር እና ዴሞክራቲክ አስተዳደር አንድ እና አንድ ናቸው እያለ እንዳልሆነ መገመት ይቻላል። እየተደረገ ያለው ግምገማ በመካከለኛና ታችኛዉ አመራር እና ሲቪል ሰርቫንቱ ላይ እየተወሰደ ያለዉን እርምጃ ሲታይ መንግስት ሕገ መንግስትና የብሄራዊ ድህንነት ፖሊሲ መሰረት አድርጎ ሰፊ ጥናት ኣካሂዶ እየመራ ነው ወይ? የሚል መሰረታዊ ጥያቄ እንድናነሳ ያደርገናል።

መልካም አስተዳደር ማለት ዴሞክራስያዊ አስተዳደር ማለት ነው ከተባለ እና የህልዉና ጥያቄ ነው ከተባለ መሰረታዊ ፖለቲካዊ ጉዳይ እየተነሳ (የድህነት (Poverty) አደጋ እንዳለ ሆኖ) የፀረ ዴሞክራቲክ እንቅስቃሴ እየጎለበተ መጥቷል ማለት ነው። የዴሞክራቲክ አስተዳደር እጥረት ነው ከተባለ የኢትዮጵያ ህዝቦች ስብኣዊና ዴሞክራስያዊ መብቶች ( የግልና የቡድን መብቶች) ያለማረጋገጥ ችግር መሆኑን ያመላክታል። ሕብረተሰቡ በብልሹ አስተዳደር ሲለበለብ ሕገ መንግስታችን ባወቀለት መብት ማለትም፤ በፁሁፍ፣ በስብሰባ፣ በሰላማዊ ስልፍ፣ የመረጠዉን ወኪል በማስጠራት (recall) አደጋዉን ለምን በእንጭጩ ኣላስቀረዉም? የሚል ጥያቄ ያስነሳል። መልሱ ሕብረተሰቡ በኃላ ቀር አስተሳሰብ (ደካማ የዴሞክራሲ ልምድ ስላለው) ስለተተበተበ ወይ ደግሞ ዴሞክራስያዊ ምህዳር በመጥበቡ ሊሆን ይችላል። ሁለቱም የተሳሰሩ ናቸው። በኔ አመለካከት የዴሞክራሲ ምህዳሩ (Democratic space) መጥበብ ማለት ኢ ዴሞክራታይዜሽን ድባብ (environment) መግነን ነው፤ ዋና ችግሮችም እነኚህ ናቸው።

ህዝቦች በተደራጀ መንገድ የሚታገሉ ሲሆኑ ነው ዉጤታማ የሚሆኑት። ዴሞክራስያዊ ምህዳሩ በቀጣይነት እየሰፋ እንዲሄድ ህዝቡን የሚመሩት ሕገ መንግስታዊና ዴሞክራቲክ ተቋሞች ተጠናክረው ሕገ መንግስቱ ያስቀመጠዉን ስልጣን እና ግዴታ በአግባቡ ሲወጡ ነው። “የህልዉና ጉዳይ” የሚለው ጠንከር ያለ ሃሳብ መሰረታዊ ፖለቲካዊ ትርጉሙ እነዚህ ተቋሞች በሚገባ አልሰሩም ወይም ከህዝቦች አደራ እና ከሕገ መንግስቱ አዃያ ሽባ ሆነዋል ማለት ነው። ምክንያቱም ሕገ መንግስቱ ለሁኔታችን በቂ በመሆኑ በቀጣይነት ተግባራዊ እየሆነ ከሄደ ብልሹ አስተዳደር እየቀጨጨ፣ የህዝቦቻችን ተስፋ እየለመለመ የዴሞክራሲ ምህዳሩ እየስፋ መሄዱ አይቀሬ ይሆናል።

“የህልዉና ጥያቄ” ነው ካልነው የችግሩ ዋነኛ ምንጭና ወሳኝ ሃይል የቀበሌ/ወረዳ ወይም የዞን አመራር አካባቢ ያሉ የቀን ተቀን ስራ አንቀሳቓሾች (Operators) ፤እና የታክቲክ ስህተቶች ሊሆን አይችልም። በፌዴራል/ክልል ደረጃ ያለው የአስተዳደር መዋቅር እነዚህን ነገሮች በግዜው ሊያስተካክላቸው ይችላል። ሰርዓቱ (System) ጤናማ ከሆነ ራሱን እያከመ የሚሄድ እና ለዚህም ሁሌም እሚሻሻል አስራር ስለሚኖረው ስርዓቱ መላዉን ህዝብ በማሳተፍ “የህልዉና ጉዳይ” ከመሆን በመለስ ችግሮቹን ይፍታል። የፌደራል መንግስት በቢልየን የሚገመት ሃብት የሚያንቀሳቅስ መንግስት እንደመሆኑ በፌዴራል ደረጃ የሚፈፀም ሙስና፣ እንዝ ህላልነትና አቅም ማነስ የሚያስከትለው አደጋ ከፍተኛ ነው። ሆኖም የፌዴራል መንግስት ይህን ከግንዛቤ ያስገባ አይመስልም፤ ወይስ አገሪትዋ ከወረራት በሽታ ነፃ ነኝ እያለ ነው?

“የህልዉና ጉዳይ” ከሆነ ሕገ መንግስት የመተግበር ጉዳይ፣ የፖሊሲና ስትራቴጂ እና የመሰረታዊ መዋቅራዊ ጉድለቶች ችግር ነው ማለት ነው የሚሆነው። በሌላ አነጋገር በበላይ አመራር ያለ ችግር ነው ማለት ነው። የበላይ አመራሩን ሳይነካ መሃከለኛና የበታች አመራርን እርምጃ መዉሰድ ስርዓታዊ ችግሩን እማይፈታ “ፍየል ወዲህ ቕዝምዝም ወድያ? ከመሆኑም በላይ ኢሞራላዊም ነው። በፌዴራልና በክልል ሕግ አዉጪ፣ ሕገ ተርጏሚ፣ ሕግ አስፈፃሚ እንዲሁም አራተኛው መንግስት የሚባለው ሚድያ ሽባ ሲሆኑ ነው ስርዓታዊ የህልዉና ችግር የሚባለው። የህልዉና ጉዳይ ነው የሚለው የመንግስት አነጋገርም ትርጉም የሚኖረው የሚወሰደው እርምጃ ጉዳዩን የሚመጥን እስከሆነ ድረስ ነው፤ ካልሆነ ግን በችግሩ ብያኔና (Definition of the problem) በሚወሰደው እርምጃ መሃል ትልቅ ገደል አለ ማለት ነው።

ስርዓታዊ ችግር ማለት የሚወጡት ህጎች፣ ትግበራ እና አተረጏጎም የህዝቦች ተሳትፎ የማመቻቸት መሰረታዊ ችግር አለባቸው ማለት ነው። ይህ ሲባል ህዝቦች የሚተዳደሩበት አማራጮች የመቀመርን፣ መረጃዎች የማግኘትን፣ የምጫው ስርዓት ፍትሃዊነት ጥያቄ ዉስጥ ሲገባ፣ ቢሮክራስያዊ አስተዳደሩ የሚፈፅማቸዉን በደሎች በሰለማዊና በተደራጀ አግባብ ሊታገሉትበት የሚያስችል ሁኔታ የሌለ መሆኑን የሚያመላክት ነው። ያገራችንን ሁኔታ በዝርዝር ለማየት እንዲያስችለን የሲቪል አስተዳደርና የድህንነት አስተዳደር በሚል ክፋፍለን እንየው።

የሲቪል ዴሞክራስያዊ አስተዳደር

የሲቪል ዴሞክራሲ አስተዳደር ስንል ሁሉም አቀፍ አስተዳደር ማለታችን ነው። የሲቪል አስተዳደሩ ድህንነትን ጭምር እሚመራ መሆኑን በቅድምያ መታወቅ አለበት። እዉቁ የዴሞክራሲ ጉዳዮች ተመራማሪው ሮበርት ዳል እንደሚለው ለዴሞክራሲ አስፈላጊ ያላቸው ሶስት ነገሮች ይዘረዝራል። አነዚህም ወታደራዊና የፖሊስ ሃይል በህዝብ በተመረጡ ሰዎች ቁጥጥር ስር ማድረግ፣ ዴሞክራስያዊ እምነቶችና ፖለቲካዊ ባህል መዳበር፣ ለዴሞክራሲ ተፀባኢ ከሆነ የዉጭ ሃይል ቁጥጥር ስር አለመዉድቅ ናቸው። ለዚህም ነው ሲቪል አስተዳደር ሁሉን አቀፍ ነው የምለው። በፌዴራል፧ ክልል ደረጃ እላይ የተገለፁት ተቛሞች ከመልካም አስተዳደር በሁለት ቁልፍ መመዘኛዎች መገምገም ተገቢ ይመስለኛል።

Organization for Secutity and Co-operation in Europe (OSCE) የተባለ ድርጅት ዴሞክራስያዊ አስተዳደርን እንደሚከተለው ይገልፀዋል “democratic governance is a system of government where institutions function according to democratic process and norms, both internally and in their interaction with other institutions” ትርጉም: ዴሞክራስያዊ አስተዳደር ማለት ተቛሞች በዉስጣዊ ስራቸዉም ይሁን ከሌሎች ተቛማት ጋር የሚያደርጉትን ግንኙነት በዴሞክራስያዊ አሰራር እና ወጎች መሰረት አድርጎ የሚንቀሳቀስ መንግስታዊ ስርዓት ነው:: እንደ የተባበሩት መንግስታት የኤስያና ፓስፊክ ማሕበራዊ ኮሚሽን አረዳድ መልካም አስተዳደር ስምንት ዋና ባህርያት አሉት። መግባባት ላይ ያተኮረ (consensus oriented) ተጠያቂነት፣ ግልፅነት፣ መልስ ሰጪነት፣ ሙጤታማነትና ቅልጥፍና፣ ፍትሃዊነትና የህግ የበላይነት ናቸው። ለዚህ ፁሁፍ ሲባል ከስምነቱ ባህርያት በሁለቱ ማለት በተጠያቂነትና በህግ የበላይነት አተኩራለሁ።

ተጠያቂነት

መንግስት በአጠቃላይ ሃላፊነት በመዉሰዱም ተቛሞቻችን እንደ ተቛም እና ባለስልጣኖቻችን በየግል በተሟላና የችግሩ ክብደት በሚመጥን ደረጃ ሃላፊነት አልተወጡም ፤ ሃላፊነታቸው አልተቀበሉም። እንደ ተቛም ስንል ሕገ መንግስት/ታት ያስቀመጠላቸዉን ስልጣን እና ግዴታ ለመወጣት ያስቀመጡትን ፖሊሲዎችና መመርያዎች ተቀባይነትና አቅም (Legitimacy and capacity) ለመገንባት ያደረጉት ጥረት እና አባሎቻቸው (ከፍተኛ አመራሩን ጨምሮ) ለዴሞክራቲክ አስተዳደር ያላቸዉን ብቃት እና ቁርጠኝነት ማለታችን ነው።

ለምሳሌ ህግ አስፈፃሚው (ከሁሉም ተቛሞች በተጨባጭ የበረታው ስለሆነ ነው ያስቀደምኩት) ቢያንስ ቢያንስ ለ አስራ ሁለት ዓመታት “መልካም አስተዳደር ቁልፍ ችግር ነው” እያተባለና እየተዘመረ ሳለ ለምን ችግሩ እየገነነ መጣ? ለምን አልተፈታም? ብሎ አጠቃላይ ስርዓቱን ማለት ፖሊሲዎችን፣ ስትራቴጂዎችንና አሰራሮችን መፈተሽ ይኖርበታል። ያለ ተጨባጭ ድርጊት የ “ችግር አለብን” መዝሙር መዘመር ተስፋ አስቆራጭና አሰልቺ ነው፤ ዋናዉ ቁም ነገሩ ምን ተሰራ ነው።

የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት የአስፈፃሚዉን የሚንስትሮችና የዳኞች ፕሮፖሳል ያልተቀበለበት ሁኔታ አለን? ወይስ የመጣለትን ፕሮፖዛል መሰረታዊ ለዉጥ እንዲደረግለት ወደ መጣበት እንዲመለስ ያደረገበት ሁኔታ ነበር? በኔ ግንዛቤ መልሱ አሉታዊ ነው፤ ከነበረም ግልፅነት አልነበረዉም መለት ነው። እንዲህ ከሆነ የተወካዮች ምክርቤት ለምን ያስፈልጋል?

የሚኒስትሮችና ኮሚሽነሮች ብቃት እና ቁርጠኝነት መዳሰስ፤ እንዲሁም ፖለቲካዊ፣ አስተዳደራዊ እና አስፈላጊ ሕጋዊ እርምጃ መዉሰድ ይኖርበታል። ከሁሉም በላይ ግን ሕግ አዉጪው ሕግ ተርጏሚዉን ሽባ በማድረግ የነበረዉን ሚና በግልፅ ማስቀመጥና ሃላፊነት መዉሰድ ይጠይቃል። የገዢ ፓርቲው ከፍተኛ ስልጣን በመቆናጠጡ በማእከላዊነት (ጥርናፈ፥ Centralism) ሕገ መንግስቱን በመናድ ሕግ አዉጪው የህግ አስፈፃሚው ተከታይ ብሎም ሕግ ተርጏሚው ተቀጥያና ማህተም መቺ (Rubber Stamp) ያደረገበትን ፤በተለይ በመንግስትና በገዢው ፓርቲ መኖር የነበረበትን ተነፃፃሪ ነፃነትን (Relative Independence) መጥፋቱና ከብቃት ይልቅ ለፓርቲ ተኣማኒነት ቅድሚያ በመስጠት ሲቪል ሰርቫንቱ እንዲሽመደመድ ማድረጉ፤ ፖሊሲዎችን፣ አስራሮችን፣ የምልመላ፣ሹመትና ምደባ ሰርዓቱ መሰረታዊ ማስተካከያ ለማድረግ ሃላፊነት እና ቁርጠኝነት ማሳየት ይኖርበታል። ሁሉም ተቛሞችና የሚመርዋቸው አመራሮች ሃላፊነት በመዉሰድ የረጅምና የአጭር ግዜ መፍትሄ ማስቀመጥ ሁሉንም ተቛማት በዳሰሰ መልኩ መከናወን አለበት።

ለምሳሌ የፍትህ መጏደል አለ ብለን ምን መደረግ አለበት ስንል:

ሀ) ከረጅም ግዜ አንፃር

በአራቱ የመንግስት አካላት ሕገ መንግስቱን መሰረት በማድረግ የኢትዮጵያን ሁኔታ ባዛመደ መልኩ ሰፊ ጥናት ማካሄድ። አጠቃላይ ህጎች (Substantive Laws) በተለይም የስነስርዓት ህጎች (Procedural Laws) ተመልሶ ማየትና ማሻሻያ ማድረግ፣ የፍትህ አካላትን ትምህርት ቤቶችን (እንደ ህግ ትምህርት ቤቶች፣ ፖሊስ እና አቃቤ ህጎች ማሰልጠኛ) ወዘተ ዓላማና አደረጃጀት፣ ብቃት ማጥናትና አስፈላጊ ማስተካከያ ማድረግ።

ለ) ከአጭር ግዜ አንፃር

– የዳኝነት፣ ዓቃቤ ሕግ፣ ፖሊስ መኮንኖች ወዘተ ምልመላ፣ ምደባ፣ ዕድገትና ሹመት ማጥናት እና አደረጃጀቱን ማስተካከል።
– የፍትሕ መጏደል ላይ የዳኞች አስተዳደር ጉባኤ ሚና፣ ከህግ አዉጪው፣ ሕግ ፈፃሚው እና ተርጏሚው አንፃር መገምገምና አስፈላጊ እርምጃ መዉሰድ።
– የዳኝነት፣ ዓቃቤ ሕግ፣ ፖሊስ መኮንኖች ወዘተ ሞራላዊና ቁሳዊ ፍላጎቶችን ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ማስተካከል።
– የሕግ ተርጏሚው ነፃነት በግላጭና በስዉር እሚጥሱት ላይ የማስተካከያ እርምጃ መዉሰድ።
– ለሃምሳ ዓመታት ህዝብን አገልግለናል እያለ በትእቢት የሚፎክረው የመንግስት ሚድያ ሃምሳ ዓመት ሙሉ የፍትህ መጏደል መሳርያ እየሆነ ነው፤ እርምት ይወሰድበት። የአፄ ሃይለስላሴ ስርዓት መለኮታዊ መዝሙር ሲያስተጋባ የኖረና፤ የደርግን አምባገነናዊ ስርዓት መሳርያ በመሆን “የፍየል ወጠጤን” እየዘመረ ለደም መፋሰስና ለአገራዊ ዉድቀት ሲጮህ ከርሞ፤ አሁንም የህገ መንግስቱ አንቀፅ ሃያ ሰጠኝ በመጣስ “ያለ ኢህአዴግ መንገድ ሁሉም የጥፋት መንገድ ነው” የሚለዉን ኢ ዴሚክራስያዊ አስተሳሰብ በተለያዩ መንገዶች ሲያሰራጭ ፍትህ በከፍተኛ ደረጃ እየተጏደለ “ሁሉም ነገር አበረታች ነው፣ ተስፋ ሰጪ ነው፣ አመርቂ ነው፣ ሰዉም ደስተኛ ነው” ብሎ ቱልቱላዉን የሚነፋ ተቛም ነው። መሰረታዊ ባህሪው እና አሰራሩ ለተመለከተው የኢትዮጵያ/የክልል መንግስታት ሚድያ ነው ወይስ የኢህአዴግ ልሳን ወይም የአባል ድርጅቶቹ ነው ብሎ ለመለየት አስቸጋሪ የሆነ ነገር ነው። የፍትህ ስርዓቱን በማኮላሸት እየተጫወተው ያለዉን ሚና በድፍረት መገምገምና ማስተካከል ይገባል።

በአጠቃላይ ሕገ መንግስታዊና የዴሞክራሲ ተቛማቱ በዴሞክራሲያዊ አስተዳደር ዙርያ ለሚታየው ችግር ሃላፊነት እንዲወስዱ፤ ከፍተኛ አመራሮቹም በግልና በቡድን ተጠያቂ የሚሆኑበት እና ለህዝቦች በግልፅ የሚታወቅበት ሁኔታ መፍጠር በዚህም ስርዓቱን እንዲያስተካክሉ ማድረግ ለነገ የማይባል ስራ ነው።

Photo - General Abebe Teklehaimanot
Photo – General Abebe Teklehaimanot

የህግ የበላይነት

ፍራንሲስ ፉኩያማ Political Order and Political Decay በሚለው መፅሃፉ “ Rule of law should be distinguished from what is sometimes referred to as ‘rule by law’. In the latter case, law represents commands issued by the rulers but is not binding on the ruler himself” ባጭሩ ሲተሮገም የህግ የበላይነትና በህግ መግዛት የተለያዩ ናቸው ይላል። እንደሚታወቀው የህግ የበላይነት ማለት ህግ የበላይ ሆኖ ሁሉንም ሰው በእኩል ሲያይ ነው። በህግ መግዛት ግን ህግ ከ መሪዎች የሚወርዱ ትእዛዛት ሆነው መሪዎቹ ላይ ተፈፃሚ መሆን እማይችሉ ሲሆኑ ነው።

የፌዴራልና የክልል ተቛሞች እና አመራሮች እንደ ተቛም እና እንደ ግል ሃላፊነት ሳይወስዱ፣ መደረግ ያለበትን ማስተካከያ ሳያደርጉ በኣንዳንድ ተጠያቂ መሆን ባለባቸው የበላይ አመራሮች ላይ እርምጃ ሳይወስዱ “አዲስ አበባ አስተዳደር እና ክልሎች በሺዎች የሚቆጠሩ የመካከለኛና የበታች አመራሮችና ተራ ሲቪል ሰርቫንት ላይ እርምጃ ወሰዱ” ያዉም በግምገማ የሚል ዜና ስሰማ በጣም ደነገጥኩኝ። ምን ኣይነት ሃላፊነት የጎደለው እርምጃ ነው? አልኩኝ። የዉሳንያቸውና ድርጊታቸው ምክንያት ሊገባኝ አልቻለም። የህልዉና ጉዳይ ነው የተባለው ብልሹ አስተዳደር ዋነኛ ተጠያቂዎቹ እርምጃ የተወሰደባቸው ናቸው ማለታቸው ይሆን? በየግዜው፤በተለይ በሲቪል ሰርቪሱ የሚወሰደው እርምጃ፤ መንግስት በ 25 ዓመት ዉስጥ መጠነኛ ተአማኒነት ያለው ሲቪል ሰርቫንት ላለመገንባት የሚኖረው ሚና ምን ይሆን? የሚለው ጥያቄም ጫረብኝ።

ፖሊሲ፣ መመርያ፣ ሕግ፣ አደረጃጀት ወዘተ የሚያወጡት፤ አመራሮቹን የመለመሉ፣ የመደቡ፣ የሾመ ስርዓት ሲኮፈሱበት የነበሩ ላይኛው አመራር እንዴት ቢሆን ነው ግምገማው እና እርምጃው እነሱን የማይነካው እና እርምጃ እማይወሰድባቸው። ከ 5-10 ዓመት የክልል ፕሬዚዳንት/ ከንቲባ/ ካቢኔ ሆነው ሲያገለግሉ የብልሹ አስተዳደር መሪዎች እንዳልነበሩ የተገኘው ኢኮኖምያዊ እድገት በነሱ መሪነት እንደመጣ እንዳልፎከሩ፤ የብልሹ አስተዳደር ችግር ሲነሳ ሃላፊነት ሳይወስዱ ሳያስተካክሉ፤ እርስ በርሳቸው የእከክልኝ ልከክልህ ግንኙነት ፈጥረው 360 ዲግሪ ተገልብጠው የመልካም አስተዳደር አርበኞች ሲሆኑ ማየት ከማስገረም አልፎ ያስቃል፤ ያናድዳል፤ 100% አሽንፈው የለ!

እርምጃ ከተወሰደባቸው ሰዎች የእዉነት ጥፋተኞች ይኖራሉ፤ንፁሃንም ሊኖሩ ይችላሉ። አካሄዱ ግን አጠቃላይ ዓዉዱን (Context) በሙሉ ሳይዳስስ ፣ በህግ የተረጋገጠ መረጃ ሳይኖር እንዴት ፍትሃዊ ሊሆን ይችላል? የህግ የበላይነት እንጦርጦስ ገባ፤ ሕግ ደካማዉ በጉልበተኛው የሚመታበት መሳርያ ሆነ፤ ህግ ዝሆኖችን የማትነካ የስልጣን መከታ የሌላቸው የታችኛው አመራርና ሲቪል ሰርቫንቱ መምቻ ሆና እንደማየት ምን እሚያሳቅቅ ነገር አለ? በህግ መግዛት ነገስ፤ የመልካም አስተዳደር እንቅስቃሴ ከጅምሩ እየተኮላሸ ነው። ካልተስተካከለ የዉድቀት መንገድ ነው።

የህወሓት/ኢህወዴግ የትግል ግዜ አስታወሰኝ::

ህወሓት/ኢህወዴግ መሰረታዊ ችግሮች በግለሰቦችና በተለይ በታችኛው አመራሮች ሲያላክክ የመዉደቅ አዝማምያ፣ የተስፋ መቁረጥና የመበታተን አደጋ ያጋጥመው ነበር። መሰረታዊ የችግሮቹ ምንጭ የሚሊተሪ ዶክትሪን፣ የፖለቲካ ፖሊሲ፣ አደረጃጀትና አሰራር ናቸው ብሎ ከፍተኛ አመራሩ ሃላፊነት ሲወስድ በሚገርም ሁኔታ ባጭር ግዜ ከሌሎች አጋሮቹ እና ህዝቦች ጋር ሆኖ ተአምር ሊባል የሚችል ስራን ሰርቶ ደርግን ደመሰሰ።

አሁን እሚታየው አካሄድ ግን ሌላው ቢቀር በችግሮቹ ምንጭ ላይ እንዃን ጠለቅ ያለ ሃሳብ ሳይዳብር ነው ተገቢ ወደልሆነው ሃላፊነት የጎደለው የማባረር እርምጃ የተገባው። ለዛዉም ከፈተኛ አመራሩ ራሱን ንፁህ አድርጎ የበታቹን አካል እየቀጠቀጠና እያንቀጠቀጠ ነው። ሲቢል ሰርቫንቱ ከድጡ ወደ ማጡ እንዲሉ፡፡

የደህንነት አስተዳደር /Security Governance/

የዴሞክራቲክ/መልካም አስተዳደር ችግር በአንድ ፖሊቲካዊ ስርዓት እንደወረርሽኝ መታየት አለበት፣ ሁሉም የስርዓቱ ተቋሞች በአንድም በሌላ መንገድ ይነካካሉ፡፡ ደረጃቸው ይለያያል እንጂ በፖሊቲካ ያለው ችግር ሁሉንም ያዳርሳል፡፡ የደህንነት ተቋሞች በቀጥታ ይሁን በተዘዋዋሪ በሲቪል ክፍሉ ስለሚመሩ ጠንካራ ዴሞክራቲክ አስተዳደር የሚኖርበት ጊዜ የደህንነት ኃይሎች የተሻሉ ባለሙያ ለሕገ-መንግስቱ ታዛዣ፣ እንደሌላው የተጠያቂነትና ግልጽነት፣ የሕግ የበላይነት ያለበት አካል ይሆናል፡፡ እየተመካከረ የመስራት ባህል ያዳበረ የሚያስተማምን የአገር አለኝታ ይሆናል፡፡

በዴሞክራቲክ አስተዳደሩ ችግር በሚኖርበት ጊዜ የደህንነት ተቋሞች የሚስጥራዊነት ባህሪ እና በተለይ የመከላክያ ሰራዊት አጠቃላይ ዝግጅቱ ጦርነት እንዳይኖር፤ ጦርነት ሲታወጅም በአጭር ጊዜ በተነጻጻሪ አነስተኛ ኪሳራ ለማሸነፍ የዕዝና የቁጥጥር ሰርዓቱ ጠበቅ ያለ በመሆኑ ለብልሹ አስተዳደር የበለጠ ተጋላጭ ያደርገዋል፡፡ በእዝ ሰንሰለት የሚንቀሳቀስ በመሆኑ ለመባለግ (Abuse of Power) የተጋለጠ ይሆናል፤ ይህ የሚሆነው ቀደም ብሎ እንደተጠቀሰው በሲቪል አስተዳደሩ የዴሞክራቲክ አስተዳደር ችግር ሲኖር ነው።

ችግሮቹ ከግዜ ወደ ግዜ እየከፉ ከሄዱም ወታደራዊ ክፍሉ የራሱን ፖለቲካዊ ፍላጎት አዳብሮ በጡንቻው ለመንገስ ሊፈልግ እንደሚችል ከተለያዩ ሃገራት ተሞክሮ መማር ይቻላል፤ ይህ እንዃን ማድረግ ባይችል አንጋሽ እና አፍራሽ (King Maker and Breaker) የመሆን ልዩ ፍላጎት ሊያዳብር ይችላል። ወታደራዊ ክፍሉ በሲቪልያን ቁጥጥር ስር ካልዋለ መንግስት ባለበት አገር ሌላ ራሱን የቻለ መንግስት (State within a state) ሊሆን ይችላል፤ ልክ እንደ ግብፅ መከላከያ ሆነ ማለት ነው። ጠብመንጃ ዴሞክራቲክ አስተዳደርን እሚያዝበት ሁኔታ መኖር የለበትም።

በተለይ በታዳጊና በሽግግር ያሉ የሦሥተኛ ዓለም የደህንነት ተቋሞች ብዙውን ጊዜ የበለጠ የተደራጀ፣ የታጠቀ በመሆናቸው ከሌሎች መንግስታዊ ተቋሞች የበለጠ ተሰሚነት እንዲኖራቸው የሚጥሩና ምርጫና መንግስት በመመስረት ሂደት በቀጥታ ይሁን በተዘዋዋሪ ተጽእኖ የሚያደርጉ መዋቅሮች ናቸው፡፡ አንድ የፖለቲካ ሃይል የፀጥታ/ የደህንነት ኃይሎት በቀጥታ ወይም በተዘዋዋሪ ካልደገፉት በምርጫ የማሸነፍ ዕድሉ ይጠባል፡፡ አሸናፊው ፓርቲ መንግስት ለመመስረት እንኳን ሊቸገር ይችላል፡፡ በዚህ መሰረት ዴሞክራቲክ ተቋሞች ባልዳበሩባቸው እንደኛ ያሉ አገሮች ሙያተኛነት በጣም ያደገ ባለመሆኑ የጦር ሃይሉ ገለልተኛ ሊሆኑ አይችሉም፡፡ በዚህ ምክንያት የኢ-ዴሞክራቲክ ኃይሎች መሳሪያ የመሆን ዕድል ከፍተኛ ነው፡፡

መከላኪያ ሚኒስቴር የወይን መጽሔት ስፖንሰር ማድረጉን ከሕገ-መንግስቱ አኳያ ስሕተት መሆኑንና መታረም እንዳለበት ጽፌ ነበር፡፡ ይህን ተከትሎ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዣ ወይም የመከላኪያ ሚኒስቴሩ ምን እንዳደረጉ ባላውቅም/ ከዚህ ጋር በተያያዘ የተለያዩ ጥያቄዎችና ሀሳቦችን ተነስተው ነበር፤ የፃፈከው ትክክል ንው ይስማማናል ያሉ እነዳሉ ሁሉ ተቃዉሞም የስነዘሩ ኣሉ።

በመጀመሪያ ተቃውሞ ያዘለው ጥያቄ ‘እንዴት መከላኪያ ትነካለህ?’ የሚል ነበር፡፡ ምን ማለት ነው? ብዬ ጠየቁት፡፡ ‘አለኝታችን ነው በሌላ አገላለጽ የመከላኪያ ሰራዊታችን ችግሮች በአደባባይ መግለጽ ለጠላት አሳልፎ እንደመስጠት ይቆጠራል’ አለኝ፡፡ አዎ ሚስጢር የሚባሉ ነገሮች በጥብቅ መጠበቅ አለባቸው፡፡ ሁላችንም ጠላቶች ሚስጢሮቻችን እንዳያውቁ በከፍተኛ ደረጃ የመከላከል ግዴታ አለብን አልኩት፡፡ የመከላከያ ሰራዊታችን ኮር ሃይል በእሳት የተፈተኑ ጀግኖች፤ ብቃታችው በተግባር ያረጋገጡ የምንመካባችው ከፍተኛ መኮነኖች ያሉበት ተቛም ነው፡፡ የተስተካከለ ስርኣት ሲኖር የነዚህ ጀግንነት እና ብቃት እየጎላ ሰራዊታችንም ለምናልባቱ ጦርንት በተሟላ ዝግጁ ይሆናል፡፡ ብልሹ ኣስተዳደር ካለ ግን እነዚህ ጀግኖች “በፍቃዳቸው ይሰናበታሉ”፤ ሳይፈልጉ ይወጣሉ ወይም ይደበቃሉ፡፡ ሌሎች መድረኩን ይቆጣጡሩታል፡፡

ነገር ግን ሰራዊታችን ሕገ-መንግስቱን በመፃረር በፖለቲካዊ ጉዳዮችን እጁን ቢያስገባ ወይም አንዱን ፓርቲ ደግፎ ሌላውን ለማዳከም ሲሞክር ዝም እንላለን ወይ አልኩት፡፡ የኢትዮጵያ የውጭ እና ብሔራዊ ደህንነት ፖሊሲ የደህንነት ጉዳዮች፣ ሚስጢራዊ ከሚባሉ በስተቀር፣ ሕብረተሰብ በዝርዝር እንዲያውቃቸው ከሩቅ መከላክያን የመፍራት ጉዳይ እንዳስቀረ ገለጽኩለት፡፡ አቅማማ ነገር ግን ‘መከላከያ ሰራዊታችን የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ሰራዊት አይደለም ወይ?’ አለኝ፡፡ ሰራዊታችን የሊበራል ዴሞክራሲ፣ የሶሻል ዴሞክራሲ ወይም የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ፓርቲዎች ሊሆን አይችልም፤ ሕገ-መንግስታችን አንቀጽ 87/5/ እንዲህ ይላል አልኩት “የመከላኪያ ሰራዊቱ ተግባሩን ከፖሊቲካዊ ድርጅቶች ወገናዊነት ነፃ በሆነ አኳሀን ያከናውናል”፡፡

ሌሎች ሁለት ሆኖው ‘በአሁኑ ጊዜ ጠባብነትም ትምክህተኛም በትግራይ ተወላጆች የሚያነጣጥርበት ጊዜ እንዴት መከላከያን ትተቻለህ?’ አለኝ፡፡ እንዴት ብዬ ጠየቅኩት ‘ዋስትናችን ነው’ አለኝ፡፡ ከ27-28 ዓመት በፊት የሆነውን በመተረት ስርዓቱ ዴሞክራሲያዊና ፍትሃዊ እስከሆነ ድረስ ችፍ ኦፍ ስታፉ ከየትኛው ብሔር ይምጣ፡፡ ሰራዊቱ የሕገ-መንግስት ታዛዥ እስከሆነ ድረስ የሁሉም ህዝቦች ዋስትና እንደሚሆን ነገር ግን ስርዓቱ ጸረ-ህዝብ ከሆነ ለሁሉም ህዝብ ፀረ ህዝብ እንደሚሆን አንድ ታሪክ አዉስቼ አጫወትኩት፤ ታሪኩ እንዲህ ነው፡፡

የህውሓት ሰራዊት መንዝ ሸዋ በገባበት ጊዜ የተከሰተ ነው፡፡ በዛ ዘመን ከነበሩት ድርጅቶች ዴሞከራስያዊ ብሄረተኝነት ለማጎልበት ትልቁና ባመዛኙ ውጤታማ ስራ የሰራው ህወሓት ከኣንዳድ ጀማሪ ታጋዮች በኩል ጥያቄ ተነሳበት፡፡ ወደ ሰራዊቱ የተቀላቀሉት አዲስ ታጋዮች መንዝ ሲገቡ የህዝቡ የኑሮ ሁኔታ ሊገባቸው አልቻለም፡፡ የህዝቡ ኑሮ ከትግራይ ህዝብ በምንም ሁኔታ የማይሻል ሆኖ ሲያገኙት አንዳንዶቹ ተዋከቡ፡፡ የአማራ ገዥ መደብና የአማራ ህዝብ መለየት አልቻሉም፡፡ ‘እንዴት ነው አማራ ጠላታችን ነው ያላችሁት ተታልለን ነው የታገልነው’ አሉ፡፡ በነባሮቹ እና በአዲሶቹ መካከል የጠፎ ክርክር ተካሂዶ በመጨረሻ ተማመኑ፡፡ ህወሓት ሲያስተምራቸው የነበረው ግልፅና መሆኑ እሱም “የአማራ ገዥ መደቦች በአማራ ስም ሲነግዱም ለራሳቸው ካልሆነ ለአማራው ምንም እንዳልሰሩለት እና አማራም እንዳሌላው ህዝብም እንደሚጨቆን” ተማመኑ፡፡

በመቀጠልም የአማራ ዴሞክራሲያዊ በሔርተኝነት በሚል በብሄረ ኣማራ ዴሞከራስያዊ ድርጅት (ብኣዴን) በ1985 በተፃፈው መሰረት የነፍጠኛው ስርዓት በአማራው ህዝብ ላይ ያስከተላቸው መዘዝ እንዲህ እንደሚል ገለጽኩላቸው፡፡
1. ሰፊው የአማራ ህዝብ ለኃላቀርነት ለብዝበዛ ተጋልጧል፤
2. የአማራ ህዝብ የዴሞክራሲያዊ መብቶቹ ታፍነዋል፤
3. የአማራ ሰፊ ህዝብ የጦርነት ሰለባ ሆነዋል፤
4. ሌሎች ህዝቦች በአማራ ህዝብ ላይ ጥርጣሬ እንዲያሳድሩ አድርጓል
የሚለውን ገለጽኩለት፡፡

የደህንነት አስተዳደሩ ጤናማ ሊሆን የሚችለው የሲቪሊያን ቁጥጥር ተገቢና ከፍተኛ ሲሆን ይህም በዋናነት ሊረጋጥ የሚችለው በተሟላ የብሔራዊ ደህንነት ካውንስል እና በጣም በተጠናከረ የድህንነት አስተዳደር ሲክሬታርያት ነው፡፡ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ የብሔራዊ ደህንነት ፖሊሲ ስለ ደህንነት ማኔጅመንት የሚለው ነገር የለም፡፡ ትልቅ ድክመቱን እዚህ ነው ያለው፡፡ ያለ ግልጽ የማኔጅመንት አደረጃጀት ፖሊሲው የትኛው ያህል ብቁና ግልፅ ቢሆንም ጠንካራ የማኔጅመንት ስርዓት እስከሌለው ድረስ የሲቪላያን ቁጥጥር ሊታሰብ የሚችልም ጉዳይ አይደለም፡፡ ከዴሞክራሲያዊ አስተዳደር አኳያ መጀመሪያ መገምገም ያለበት የፖሊሲውን ማኔጅመንት ነው፡፡ ሌላው አሰራሩ ግልጽነትና ተጠያቂነት ያለው መሆኑ ነው መግመግም ንው፡፡ ጀግኖችና ብቃት ያላቸው ወደ አመራር የሚመጡበት ስርዓት አለ ወይ?ካለስ ስርዓቱስ በትክክል ተግባራዊ ይሆናል? ወይስ ትዉዉቅ (Nepotism) እና ግላዊ ፍላጎት መሰረት ተደርጎ ነው እየተሰራ ያለው? ብሄራዊ አስተዋፅኦ ለማስተካከል እየተሰራ ያለ ስራ ምን ይመስላል? ወዘተ መፈተሽ አለበት።

የሲቪል አስተዳደሩ ቁጥጥር ሊረጋገጥ የሚችለው በሰፊ ትንተና የታጀበ በርከት ያሉ አማራጭ ሃሳቦች (Scenarios) ማቅረብ የሚችል ብሄራዊ (አገራዊ) የድህንነት ምክርቤትና ይህንን ስራ የሚያስተባብር ፅህፈት ሲኖር ንው። ይህ ሳይሆን ሲቀር ግን ወታደራዊ ክፍሉ በሲቪል አስተዳደር ቁጥጥር ስር ለማድረግ አዳጋች ይሆናል ብቻ ሳይሆን የታጠቀው ሃይል ክፍተቱን እንዲጠቀምበት ያስችለዋል። የሕዝብ ተወካዮች ምክር የኢትዮጵያ ህዝብ ሉኣላዊ የስልጣን ባለቤትነት ማረጋገጫ ተቛም እንደመሆኑ መጠን፤ የጦር ሃይላችን ፖሊሲ፣ በጀት፣ ግዢ፣ እድገት የመከታተል ሕገ መንግስታዊ ስልጣኑን በመጠቀም ጭምር ነው ወታደራዊ ክፍሉ በሲቪል አስተዳደር ቁጥጥር ስር እንዲዉል ማድረግ የሚችለው። የድህንነት አስተዳደር የህዝቦች ሂወት፣ እሴት እና ድህንነት ላይ ከፍተኛ ተፅእኖ እሚያሳድር ነገር ስለሆነ ለስራ አስፈፃሚው ወይም ለ ወታደራዊ ክፍሉ ብቻ ሊተው አይገባዉም። የሲቪል አስተዳደር ቁጥጥሩ ጥብቅ ካልሆነ የወታደራዊ ክፍሉ የፌዴራል ስርዓቱን (በተለይ በታዳጊ ክልሎች የባላባታዊ ምስለኔ ዓይነት) ጣልቃ ገብነት ሊያስከትል ስለሚችል ከወዲሁ ጥንቃቄ ሊደረግበት ይገባል።

ዴሞክራሲያዊ ብሄርተኝነት መጠናከር የዴሞክራቲክ አስተዳደር መጎልበት መሰረት ነው!

ዴሞክራሲያዊ ብሄርተኝነት ብዙ ብሄር ብሄረሰቦች ባሉባት አገር የአንድ ብሄር/ብሄረሰብ ብሄራዊ ጥቅም ከብሄሩ ሰፊ ህዝብ ጥቅም ማስከበር የተመሰረተ ነው፡፡ በህዝቦች መካከል መሰረታዊ የጥቅም መቃረንና መጋጨት ስለማይኖር ደግሞ የሌሎች ብሄር/ብሄረሰቦች ብሄራዊ ጥቅም በተሟላ መንገድ መሟላት አለበት ብሎ ማመን ነው፡፡ የሌላ ብሄር/ብሄረሰብ ጥቅም ወይም ጉዳት የራሱን ጥቅም ወይም ጉዳት አድርጎ የማየት አስተሳሳብ ነው፡፡ ብዙሕነትን የሚያስተናግድ ዴሞክራቲክ አስተሳሰብ ማለት ነው፡፡ የሕዝቦች ዴሞክራቲክ አንድነትን የሁሉም ህዝቦች ጥቅሞች በሚያረጋጥ በመሆኑ ለአንድነት የቆማል፡፡

በዚህ ረገድ የኢፌዴሪ ሕገ መንግስት በመግቢያ ላይ የስነሐሳብ ግልጽነት ባለውና በተሟላ መልኩ በብዝ ሃነት ዉስጥ ስላለው አንድነት እንደሚከተለው ይላል: “እኛ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ በሔረሰቦች እና ህዝቦች የእራሳችን ዕድል በእራሳችን የመወሰን መብትን እና በእራሳችን ፈቃድ ላይ የተመሰረተ አንድ የፖሊቲካ ማሕበረሰብ በጋራ ለመገንባት ቆርጠን በመመነሳት…”በዚህ መሰረት ይህንን የሕገ-መንግስቱን አላማ በተሟላ መንገድ መቀበል፣ ማሳደግ እና መተግበር ነው፡፡

አንድ የፖሊቲካ ማሕበረሰብ በሚለው ስነሐሳብ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች መሰረታዊ የዴሞክራሲ፣ የልማት እና የድህንነት ዋስትና መሆኑን በግልጽ ያስቀምጣል፡፡ የጋራ ታሪክ /በበጎም በመጥፎም/ ያላቸው ህዝቦች እንደሆነ እንደ አንድ ዋና መነሻ አስቀምጦ ነገር ግን ዋናው በወደፊት አንድ የፖሊቲካ ማህበረሰብ በጋራ የመገንባት አንፃር ነው፡፡ ሕገ-መንግስቱ የነበረውን አሃዳዊ አስተዳደር እንደአዲስ በማደራጀት /reengineering/ ፌዴራላዊ ስርዓት መመስረቱ የህዝቦች መፃኢ ዕድል በጋራ የመገንባት መሰረት ጥሏል፡፡ይህ እንደ አዲስ በማደራጀት የተገኘ አዲስ የኢትዮጵያዊነት ማንነት የሽግግርና የማጠናከር 
ሥራን ይጠይቃል፡፡

ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት ኢትዮጵያውነት እና የብሔር/ብሔረሰብ እና ህዝቦች ማንነት አጣምሮ፣ አጣጥሞ ማስኬድ የሚችል አስተሳሰብ ነው፡፡ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ኢትዮጵያዊነት ወይም አንዱን እንዲመርጡ መገደድ የለባቸውም፡፡ ዴሞክራስያዊ ብሄርተኝነት ኢትዮጵያውነት የሚፃረር ተደርጎ መታየት የለበትም፡፡ የኢትዮጵያ ጥንካሬ የሚመሰረተው በብሔር፣ ብሔረሰብ እና ህዝቦች ብርታት ነውና!!

በኦሮሚያ የተቀሰቀሰው ተቃውሞ እና በአማራ ክልል አካባቢ የታየው ብጥብጥ የጠባብ ብሔርተኝነትና ትምክህት እንደገና መጎልበቱ እና በዚህ አገር ላይ አደጋ እንደሆነ መወያያ ሆኖ ሰንብቷል፡፡ ተገቢ ስጋት ነው፡፡ አንዳንዶቹ ፌዴራል ስርዓት ያመጣው ጣጣ ነው ሲሉ በአንዳንዶቹ እጅግ መደናገጥ ይታያል፡፡ በእኔ አመለካከት ጠባብነት ይሁን ትምክህት በሕብረተሰቡ ውስጥ በሚኖሩ የተወሰኑ ልሂቃን በቀጣይነት ለራሳቸው ጥቅም ስሉ የመጠቀም አመለካከቶች ናቸው፡፡ ፌዴራላዊ ስርዓቱ በተማላ መንገድ እስኪጠናከር ድረስ አንዴ ብልጭ አንዴ ድርግም እያሉ አንዴ ተጠናክረው አንዴ ተዳክመው የሚታዩ ክስተቶች ናቸው፡፡ በሕብረተሰቡ ያሉ ኃላቀር አስተሳሰብ ቢሆንም አብዛኛውን የሕብረተሰብ ክፍል የሚጎዳ እንጂ አይጠቅምም፡፡ ፖሊቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ስጋትና ፍርሐት በሕብረተሰቡ በሚያይልበት ጊዜ፣ የሚያጎለበቱ ክስቶቶች ናቸው፡፡

ትምክህት አንድ ገዢ መደብ ህዝቦችን ለመጨቆንና ለመበዝበዝ ከሚጠቀምበት መሳርያዎች አንዱ ነው። ጠባብነትም ጭቆናን የመቃወም ግብረ መልስ (reaction) ሊሂቃን ወደ አንድ ጫፍ የሚወስዱበት አስተሳሰብ ነው። ሁሉም የሚጎለብቱት የፍትህና የእኩልነት መጏደልና አጠቃላይ ጭቆና ሲነግስ ወይም ጭቆና አለ ብለው ሲያስቡ ነው። የነዚህ ኃላቀር አስተሳሰብ አደገኛነት ሕብረተሰቡን ማስተማር ተገቢ ነው፡፡ ዋናው መፍትሔ ግን ለስጋትና ፍርሐት የሚዳርጋቸው ተጨባጭ ወይም ታሳቢ የሚደረጉ ዴሞከራስያዊ አሰተዳድር በደሎች በስርዓት ና በቀጣይነት ማስተካከል ነው፡፡ ጠባብ ብሔርተኝነትና ትምክህት ለብቻቸው የቆሙ አስተሳሳቦች አይደሉም እና፡፡ትልቁ አደጋ ግን በህዝቦች የመብት ዴሞክራሲያዊ እንቅስቃሴዎች ልክ እንድ ደርግ ገንጣይ አስገንጣይ ብሎ በመፈረጅ የህዝቡን ትግል ለመጨፍለቅ የሚደረግ ሙከራ ነው፡፡ ትልቁ የኣድጋ ደወል ይህ ነው!!!

ሰሙኑን በኦሮሚያ የነበረው ተቃውሞ ጸረ-ሰላም ኃይሎች ወደ ሌላ ለመቀየር ቢሞክሩም በህዝቦች መካከል ጥርጣሬ እንዲኖር የቻሉትን ቢያደርጉም የህዝቡ እንቅስቃሴ ግን ሕጋዊ እና ዴሞክራሲያዊ መሆኑን የህዝቡን ጥያቄዎች ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ እና ሕገ-መንግስታዊ ተቋሞች በመገንባት መፈታት ያለበት ነው፡፡ የህዝቡ ጥያቄ የዴሞክራቲክ አስተዳደር ጉዳይ ነው፡፡ እራሱ በራሱ የሚያስተዳድር መበቶችን የማጠናከር እንቅስቃሴ ነው፡፡ በአስተዳደሩ ያለው ልፍስፍነት የመቃወም ጉዳይ ነው፡፡ ይህ ስለሆነ በመሰረቱ የኦሮሞ ጥያቄ የዴሞክራሲ ጥያቄ ነው፤ ለዚህም ዴሞክራስያዊ ምላሽ ያስፈልገዋል።

ከወጣት ኦሮሞ ምሁራን ጋር በዚህ ጉዳይ ላይ የመወያየት ዕድል አግኝቼ ነበር፡፡ ከውይይታቸን የተረዳሁት በመሰረቱ በኦሮሚያ ክልል ላይ ያለው ችግር በተመሳሳይ በሌሎች ክልሎች ያለ የዴሞክራሲያዊ አስተዳደር ችግር ነው፡፡ ነገር ግን እስከ አሁን እነዚህ ጉዳዮች በኦሮሞ ልሂቃን መሀከል በስፋት ውይይት እና መፍትሔ የተደረገላቸው አይደሉም፡፡ ይህን ለማድረግ አገር ዉስጥ ባለው ጠባብ የፖሊቲካ ምህዳር እድል አልሰጣቸውም::

ሁለቱም እንዲህ ሲሉም ነገሩኝ “የኢፌዴሪ ሕገ-መንግስት የኦሮሞ ህዝብ ፍላጎት የሚያሟላ ነው፤ ነገር ግን አተገባበር ላይ እየሾቀ ነው፡፡ የኦሮሞ ህዝብ የተዋጋለት ሕገ-መንግስት ነው፡፡ ይሁን እንጂ እኛ በአገሪቱ በቁጥራችን ብዙ ብንሆንም የስልጣን ማእከል ግን መሆን አልቻልንም፡፡ ባለፉት 25 ዓመታት ኦሮሞዎች ስማዊ ብቻ የሆነውን የፕሬዚዳንትነት ስልጣን ብቻ ነው የተሰጣቸው፡፡ እንዲሁም ወሳኝ በሚባሉ የፖሊቲካ ወይም የደህንነት አመራር ቦታ ላይ አልተደለደሉም፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የአፋን ኦሮሞ ቋንቋ የፌዴራል መንግስት ቋንቋ እንዲሆን ፍላጎት አለ፡፡ በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 49/5/ የተቀመጠው የኦሮሚያ ክልል ልዩ ፍላጎትና ጥቅም በ21 ዓመት ውስጥ ሕግ ሳይወጣለት ቀርቶ አሁን እየተጠና ነው ይሉናል፡፡ በአዲስ አበባ እና አጎራባቶች ማስተር ፕላን የኦሮሚያ ልዩ ፍላጎትና ጥቅም የሚያረጋግጠው ሳይወጣ የተሰራ መሆኑ ራሱ ህገ-ወጥ ነው” አሉኝ።

በመቀጠል የመገንጠል አዝማምያ እንደፍላጎት በኦሮሞ ሊሂቃን አለ ወይ ብዬ ጠየቅኩቸው፡፡ ጥያቄ በጥያቄ መለሱት “ማን ከማን ነው የሚገነጠለው?” አለኝ፡፡ “ያው የኦነግ ፕሮግራም የሚያራምዱ ማለቴ ነው” አልኩት፡፡ አንዱ ተናደደና “ኦነግን በኦሮሞ ልሂቃን ጀግና የምታደርጉት እናንተ ሐበሾች ናችሁ፡፡ አበሾች አይደለንም ብንል እንኳን የኦነግ አስተሳሰብ ነው ትላላችሁ፡፡ የኦሮሞ ህዝብ ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ የሚደረግ ማናቸውም እንቅስቃሴ ይከፋቹኃል፡፡ የኦነግ አስተሳሰብ ነው ብላችሁ ኦነግን ትሸልማላችሁ፡፡ ይህ ኢ-ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ በእኛ ላይ ጥርጣሬ እንድታሳድሩ እያደረገ ነው፡፡ ጥርጣሬ ደግሞ የባሰ ጥርጣሬ ይወልዳል፡፡ ዙርያ ጥምጥም ችግር የሄ ነው፡፡ በእኛ አመለካከት ዴሞክራሲያዊ ኢትዮጵያ በመገንባት የእኛ የኦሮሞች ጥቅም ያስጠብቃል ብለን እናምናለን፡፡ እንኳን የኢትዮጵያ እንብርት ሁነን ትልቅ ብሔር ሆነን በአንድ የኢትዮጵያ ጫፍ የሚኖር ብሔር እንኳን በዴሞክራዊያዊት ኢትዮጵያ ይጠቀማል። ስለዚህ እናንተ ሓበሾች አንድነት ጠባቂዎች እኛ ብቻ ነን የምትሉት አባዜ እርግፍ አግርጋችሁ ተው፡፡ ፍትሐዊና ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ እስካለች ድረስ ሁሉም ለዚህ አንድነት ይታገላል” አለኝ፡፡ በመጨረሻም ኢትዮጵያ ከ25 ዓመት በፊት እንደ ነበረችው ባትሆንም አሁንም የአቢሲንያ ማእከላዊነት የሚጫናት አገር እየሆነች በመሆኑ የተጀመረው የዴሞክራሲ ሂደት አደጋ ውስጥ እየወደቀ ያለባት አገር እንዳትሆን እንደሚሰጋ ገለፀልኝ።

ሕገ-መንግስቱ የኦሮሞ ህዝብ ፍላጎት የሚያስከብር መሆኑ እሙን ነው፡፡ የእኛ ትውልድ ቢያንስ ቢያንስ ያን የመሰለ ሕገ-መንግስት አስረክብዋል፡፡ ከእንግዲህ እናንተ ወጣት ሙሁራ በአተገባበር ላይ ያለ ችግር እያማረራችሁ መኖር መቆም አለበት፡፡ መሪነቱን ለመንጠቅ መንቀሳቀስ አለባችሁ፡፡ለምሳሌ የጠቅላይ ሚኒስቴር ያነሳችሁት ጉዳይ እንኳን በብዛት ከማንኛውም ብሔረሰብ ትልቁ ህዝብ ከአናሳም የሚመረጥበት ሁኔታ አመቻችቷል፡፡ እንደምታውቁት በኢሕአዴግ ውስጥ ካሉ አራት ፓርቲዎች የውስጥ ውይይት እና ማቻቻል በማድረግ ነው፤ ጠቅላይ ሚኒስቴሩ የሚመርጡት፡፡ እንግዲህ ይህን ሂደት ነው መመርመር ያለባችሁ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስቴሩ ከሌላ ብሔረሰብ በመሆኑ ኦሮሞ ወይም ሌላ ብሔር ይጎዳሉ ወይም ኦሮሞ በመሆኑ ሌሎችን ብሔሮች በመጉዳት የኦሮሞ ይጠቅማል የሚለው አስተሳሰብ የተሳሳተ ነው፡፡ ነገር ግን ጥያቄው ተቀባይነት (Legitimate) ያለው በመሆኑ በመጀመሪያ በኢሕአዴግ ውስጥ መሪነታችሁ ማረጋገጥ አለባቹህ፡፡ ኦሆዴድ የማያሳራ ድርጅት ነው ካላችሁ በራሳችሁ ድርጅት መስርታችሁ መታገል ነው አልኩዋቸው፡፡ ከሌሎች ወጣት ሙሁራን ኢትዮጵያውያን ጋር ውይይት ብታደርጉ መልካም ነው አልኩዋቸው፡፡

ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት እየተመነገደ ካልሄደ የዚች አገር እጣፈንታ ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ ነው፡፡ ሆኖም ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት አስተሳሰብ የበላይነት እስኪይዝ ጊዜ ይጠይቃል፡፡ ትዕግስት ያለው ዴሞክራቲክ አመራር ያስፈልጋል፡፡ እስከዛ ድረስ ደግሞ እየተንገራገጨ መሄድ የማይቀር ነው፡፡ አዲሱ የስልጣን ግነኙነት በፌዴራል እና በክልሎች ሲተገበር እንደማንኛውን አዲስ ሙከራ እንደመሆኑ ወደ ትክክለኛ የሚዛን ምጣኔ እስከሚመጣ ድረስ ወደ ግራ ወደ ቀኝ መወዛወዙ ወይም መንገራገጩ የማይቀር ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ትዕግስት እና ማቻቻል እና ህዝቦች ከተሞክራቸው እንዲማሩ ዕድል መስጠት አስፈላጊ ነው፡፡ ህዝቦች የራሳቸው ዕድል በራሳቸው የመወሰን መብታቸው በሚያደርጉት እንቅስቃሴ በተለይ ግትር ያልሆነ፣ ጥቅሞችን በማጣጣም እና በጋራ ስምምነት የሚመራ አመራር ይጠይቃል፡፡

እንደአለመታደል ሆኖ የእኛ አመራር /በገዢ ፓርቲ ይህን በተቃዋሚነት ያለ (ምናልባት ከኢዴፓ ዉጪ) ድርቅና የሚያጠቃው መቻቻል ሽንፈት የሚመስላቸው እና አጥፊ ተጋፋጭነት (Destructive Confrontation) ነው ያለው፡፡ ዴሞክራቲክ ብሔርተኝነት ይህ አመራር ይዞ ሊጎለብት በሚችልበት ዕድል ጠባብ ነው፡፡ ይህ በመሆኑ የትውልድ አመራር ለውጥ አስፈላጊነት በግልጽ ይታያል፡፡

በኢህአዴግ አመራር የተፈጠረ አዲስ ትዉልድ አለ፤ ይህ ትዉልድ አለም አቀፍ ትስስር ያለው፣ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ እዉቀት እና ክህሎት ያለው፣ የተሻለ የትምህርት እድል ያገኝ በሙሉ ቁመናው ካለፈው ትዉልድ በብዚ መመዘኛ የሚሻል ወጣት ሙሁር ትዉልድ ተፍጥሯል። ይህ በኢህአዴግ የአመራር ግዜ የተፈጠረው ወጣት የመምራት እድል ሊሰጠው ይገባል።አዲስ ትውልድ ከ25 ዓመት በፊት ያልነበሩ ተግዳሮች እና ጥያቄዎች መመለስ የሚችል የልማት አመራር ያስፈልጋል፡፡ እያንዳንዱ ትዉልድ የራሱን ፍላጎት በሚረዱ የራሱ ዘመን ሰዎች መመራት አለበት።

ድምዳሜ

በስካሁኑ ሂደታችን ተጠቃሽ ሰላምና የኢኮኖሚ እደገት ማስመዝገብ ችለናል፤ ሆኖም በዴሞክራስያዊ አስተዳደር ዙርያ ስኬቶቻችንን ሊንድ በሚችል መልኩ ወደ ኃላ እየተጎተተ ይገኛል። የኢትዮጵያ ህዝቦች መብቶቻቸዉን ማስከበር አልቻሉም፤ የሚመለከታቸው ተቛማትም ለህዝቡ ፍላጎት ተገቢ መልስ መስጠት አልቻሉም። ፖለቲካዊ ስርዓቱ አድጋ ላይ ነው፤ መሪዎቻችን የአመራር ዘይቤያቸውና አመራራቸዉን መገምገምና ችግሩ ሰርዓታዊ (systemic) መሆኑ መገንዘብ ይኖርባቸዋል። የህግ የበላይነትና ተጠያቂነትም ከላይ እንጂ ከታች እንደማይጀምር መገንዘብ የግድ ይላል። በተጨማሪም ያለው ችግር ሁሉንም ተቛማት በተለያየ ደረጃ የበከለ መሆኑ መረዳት አለብን። መፍት ሄዉም ዴሞክራስያዊ ተቛማት ሂወት እንዲዘሩና ምልአተ ህዝቡ እንዲሳተፍ ማድረግ ነው። ሰላምና ልማት እዉን ያደረገው አመራር ቁርጠኝነትና ብልሃት ከታጠቀ አሁን የገጠመንን ችግር መፍታት ይችላል።

**********

* አበበ ተክለሃይማኖት(ጆቤ) (LLB, LLM and PhD Candidate) የህወሓት/ኢህአዴግ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባልየነበሩ፣ 1983-1986 የሰሜን ማዕከላዊ እዝ አዛዥ እና በጡረታ እስከ ተሰናበቱበት 1993 . የኢትዮጵያ አየር ሃይልአዛዥ የነበሩ ሲሆን፣ በተሰናበቱበትም ወቅት የሜጀር ጄኔራል ማዕርግ ደርሰው ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባዩኒቨርሲቲ በሚገኘው የሰላም እና ደህንነት ጥናት ተቛም የዶክትሬት ዲግሪ እያጠኑ ይገኛሉ።

ተዛማጅ፡- ብልሹ አስተዳደርን የዴሞክራሲ ምህዳር በማስፋትና በተቋማት ግንባታ(ሜ/ጄ አበበ ተ/ሃይማኖት)

Guest Author

more recommended stories