ብልሹ አስተዳደርን የዴሞክራሲ ምህዳር በማስፋትና በተቋማት ግንባታ(ሜ/ጄ አበበ ተ/ሃይማኖት)

አበበ ተክለሃይማኖት(“ጆቤ”)
(ሜጀር ጄኔራል፣ PhD Candidate)

Highlights:-

* በዴሞክራታይዜሽን እና ኢ-ዴሞክራታይዜሽን ሂደቶች ሁሌም መሳሳብ እና ዉጥረት ይኖራል። መንግስት እንደ መንግስት ግን የዴሞክራታይዜሽን አጋዥ አልያም የኢ-ዴሞክራታይዜሽን አሳላጭ ነው መሆን እሚችለው፤ መሀል ላይ የሚንገዋለል መንግስታዊና ተቛማዊ አቛም ሊኖር አይችልም።

* ባጠቃላይ ሲታይ ብዙ ማንነቶች፤ በርካታ ፖለቲካዊ ፍላጎቶች፤መልስ እንሻለን የሚሉ የተለያዩ ጥያቄዎች ባሉበት አገር አንድ ግንባር (ኢህአዴግ) እና አጋሮቹ 100% መቀመጫውን መቆጣጠር እሚያሳየን ነገር፤አንድም ባጠቃላይ ፖለቲካዊ ስርዓቱ ላይ ችግር መኖሩን አልያም የምርጫ ስርዓቱ ችግር እንዳለበት ወይም ተግባራዊነት ላይ ችግር እንደነበረበት ነው፤ 100% እሚባል ውጤት አስቂኝ ግን ደግሞ አደገኛ ነው ፡፡ ይሄ ዉጤት አርቆ ለሚያስብ ሰው የአደጋ እንጂ የድል ምልክት ተደርጎ መቆጠር አይችልም። መሬት ላይ ያለዉን የተለያየ ፖለቲካዊ ፍላጎት እማያንፀባርቅ የምክር ቤት ሁኔታ የስጋት እንጂ የኩራት ምንጭ መሆን አይችልም።

* ዲሞክራሲያዊ ምህዳሩ በጠበበ ቁጥር የዜጎች ተስፋ እተሟጠጠ ስጋታቸው እና ፍርሃታቸው እየጨመረ ከቁጥጥር ውጪ የመሆኑ እድል ይሰፋል፡፡ ይህን መሰል ሁኔታም ከውስጥም ከውጪም ለነሱ ለሚችሉ ፅንፈኛ ሃይሎች ምቹ ሁኔታ ስለሚፈጥር አገሪትዋን ወደላስፈላጊ መንገድ ሊመራ ይችላል፡፡ ፍትህ ተራ ፍርድ የማግኘት ጉዳይ አይደለም፡፡ ፍትህ የማህበራዊ ተቛም የመጀመርያ ፀጋው ነው ይላል ጆን ራዉልስ፡፡ ሙስናና መልካም ያልሆነ አስተዳደርም ሃገርን ሊበትን የሚችል፤እየታየ ያለውን ኢኮኖሚያዊ እድገት ገደል የመክተት አቅም ያላቸው ስርዓታዊ በሽታዎች ናቸው፡፡የሶስቱም እናት ደግሞ የጠበበ ወይም የኮሰመነ የዲሞክራሲ ምህዳር ነው፡፡

* ከባዱ ስራ ግን ቀጥሎ መከሰት ያለበት እርምጃ ላይ ነው፤ከባድ እና ውስብስብ እሚሆነብት ምክኒያትም ትግሉ ከሞላ ጎደል ግልፅ ከሆነ ዉጫዊ ሃይል ወይም ተቛም ጋር ሳይሆን ከገዢው ፓርቲና መንግስታዊ መዋቅር ይዘው ከሚገኙ አመራር እና የነሱ ተባባሪዎች ጋር መሆኑ ነው።

* በተለይ ከ 10ኛው የኢህአዴግ ጉባኤ ማግስት በአንድ በኩል የመቀዛቀዝ በሌላ በኩል ደግሞ ችግሮች ቢኖሩም ብዙ እሚያስጨንቁ አይደሉም የማለት እና የማጣጣል አዝማምያዎች እየታዩ ነው። ጠቅላይ ሚንስቴር ሃይለማርያም ደሳለኝ ምክርቤቶችን አስመልክተው፤ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስቴር አቶ ደመቀም ሚድያን አስመልክተው የተናገሩት ነገር ገምቢ እና አበረታች ቢሆንም ሌሎች የመንግስት አካላት ግን ችግሩ ቀለል አድርገው ሲመለከቱ እያየን ነው።

* ያገሪትዋን ከፍተኛ ስልጣን በህገ መንግስት የተረጋገጠለት ተቋም አሁን ያሉት አማራጮች ሁለት ናቸው፡፡ አንደኛው አማራጭ ህገ መንግስታዊ ስልጣኑን ተጠቅሞ የዜጎችን ጥቅም ማስከበር ሁለተኛው አማራጭ ህገ መንግስታዊ ስልጣኑን መጠቀም እማይቻል እና የህዝባችን አደራ መሸከም ካልቻለ ያገሪትዋን ሃብት ያላግባብ ከሚባክን ህዝበ ውሳኔ አዘጋጅቶ አይረቤነቱን ህጋዊ ድጋፍ ሰጥቶ ተቋሙን ማፍረስ፡፡

* [ወይን መፅሄት በ ሃምሳኛ እትሙ] የትግራይ ህዝብ እየለበለበው ያለዉን የብልሹ አስተዳደር ችግር እያለ እንደ ድሮ መሳፍንት ‘ራስ እገሌ ከ እገሌ ይበልጣል’ ዓይነት ፅሁፍ ይዞ መዉጣቱ በጣም የሚያሳፍር ነው። መወየን ተራማጅነትን የሚገልፅ ቢሆንም እየተደረገ ያለው ግን የ አድሃርያን ተግባር ነው፤ ወያነነቱም የት ሄደ? ያስብላል። ለመሆኑ ወይን በስራ ላይ ካሉት ኢታማዦር ሹም ምን ቢፈልግ ነው የህዝቡን ድምፅ ማሰማት ሲገባው ወደ ወረደ መሳርያነት ራሱን ያሸጋገረው? ፖለቲካዊ ዘመቻም ከሆነ ጡረታ ሲወጡ ያደርግላቸዋል። ሁለቱም ኢታማዦር ሹሞች የየራሳቸው እና የጋራ የሚያኮራ ታሪክ እያላቸው የ ‘አንዱ ይበልጣል’ ንፅፅር ምን አመጣው?

* ወይን መፅሄት “አብ መከላኸሊ ሓይሊ እዉን ክግበር ዝኽእል ዘይሕጋዊ መማረፂታት እንተልዩ ምሕሳብን ምፍታንን ጀሚሮም” ይላል። ትርጉም “በመከላከያ ሃይል ዉስጥም ማድረግ እሚቻል ህጋዊ ያልሆነ አማራጭ ካለ ብለው ማሳብና መሞከር ጀመሩ” ይላል። ለሌተናል ጄኔራል ፃድቃን እና እኔ ባለፉት ወራት አንዳንድ ከትጥቅ ትግሉ ጋር የተያያዘ የምናውቀዉን ፅፈን ነበር፤ ሰው ሊስማማ ላይስማማ ይችላል። የሚገርመው ግን ወይን ወይም ስፖንሰሮቹ “ህገ ወጥ ድርጊት በማስብ እና በመሞከር” ብለው ለማስፈራራት የሞከሩት ነገር ነው። ከአስራ አምስት ዓመት በኃላ ይህ ማስፈራርያ ለምን መጣ? አርፋቹህ ተቀመጡ ለማለት ነው? ወይንና ‘እማይታወቀው’ መሐመድ በወቅቱ የነበሩት ጠቅላይ ሚኒስቴር መለስ ዜናዊ (ነብሳቸው ይማርልን) እያወቁ “ምህረት” አድርገዋል፤ አሁን ግን የሚምራቹህ ሰው የለም እያሉን ይሆን እንዴ?

* ጠንካራ የሃገር መከላከያ የዴሞክራሲያዊ ስርዓታችን ዘበኛ ቢሆንም፤ ከልክ በላይ ካበጠ ግን የ ኢ-ዴሞክራስያዊ ሃይሎች መሳርያ ስለሚሆን በዚህ ረገድ የተሰማሩ ሙሁራን ወታሃደራዊ ክፍሉ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ወይ ቅልበሳ (democratization and de-democratization) ላይ የሚኖረዉን ሚና እንዲያጠኑት መንግስት ሁኔታዎችን ማመቻቸት አለበት፤

* የህወሓት 40ኛ አመት በትግራይ ቴሌቪዥን የወራት ሙሉ ሽፋን እንዲሁም በኢቢሲ (EBC) ላቅ ያለ ሽፋን የተሰጠው የምርጫ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ትንፋሽ ለመተንፈስ እንኳ የማትበቃ ጥቂት ደቂቃ በተመደበላቸው የምርጫ ወቅት መሆኑ ስንገነዘብ ነው የመንግስትና የህዝብ የመገናኛ ብዙሃን ባህሪ እና ማንነት መረዳት እምንችለው፡፡ እስኪ ህወሓት በትግራይ ቴሌቪዥን እና EBC ላሰራጨው የወራት ፕሮግራም ክፍያ ፈፅመዋል? ቢፈፅምስ ይህ ተገቢ ተግባር ነውን?

* ይህ የተጠቀሰው ዶክመንት በገፅ 123 ላይም እንዲህ ይላል “መላውን ህዝብ /አብዛኛው ክፍል/ ለአመታት ለአንድ ፓርቲ አመለካከት በማጋለጥ፣ ሌሎችን በመከላከል የሚደረግ አሰራር መከተል በሃሳቦች መካከል ነፃ ውድድር እንዳይኖር የሚያደርግ ነው የሃይለስላሴና የደርግ መንግስታት ይህም ማድረጋቸው የሚያመላክተው ፀረ ዴሞክራስያዊ ባህርያቸው ነው” (ኢህአዴግ፣ 1992 ዓ.ም ገጽ 123)።

ንዑሳን-ርዕሶች

1. መግቢያ
2.ችግሮቻችን ምንድን ናቸው? መልካም አስተዳደር የወቅቱ ቁልፍ ችግር
2.1 በአሁኑ ግዜ የችግሮቻችን አውራ መልካም አስተዳደር ያለማስፈን ችግር ነው ተብሏል፡፡ ለመሆኑ መልካም/ዴሞክራስያዊ አስተዳደር ምን ማለት ነው?
2.2.የመልካም/ ዴሞክራስያዊ አስተዳደር ችግሮች ስፋትና ጥልቀት
3. የችግሮቻችን መሰረታዊ ምንጭ ምንድን ነው?
4. በኢህአዴግ እሚመራው መንግስት የዴሞክራሲ ምህዳሩ በማስፋት መልካም አስተዳደርን ለምን አላረጋገጠም?
5. የመፍተሄ ሀሳቦች
5.1 ጠንካራ ተቛማዊ ስብእና (Strong Institutional Integrity)
5.2 ምክር ቤቶች የዴሞክራስያዊ እንቕስቃስያችን ወሳኝ አምዶች ናቸው
5.2.1 ህገ መንግስታችን እና የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት
5.2.2 የተወካዮች ምክርቤት ዓይነቶች
5.2.3 የተወካዮች ምክር ቤት እውነተኛ ገፅታ
5.3 የመገናኛ ብዙሃን
5.4 የአንድ ለአምስት ተቋም
6. ንቅናቄው እንዴት ይቀጣጠል?
– ማህበራዊ ንቅናቄ (Social Movement) ምንድን ነው?
-የግል መልእክት
– ዋቢ ምንጮች

1.መግቢያ

በኢህአዲግ የሚመራው የኢትዮጵያ መንግስት “ሩቅ አስባ ሩቅ ለመደር እየተጋች ያለች አገር” በሚል መሪ ቃል ስር ላሳካዉ አንፃራዊ መረጋጋት እና ተጠቃሽ ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ምስጋናየ ላቅ ያለ ነው፡፡ይሄም ስኬት ኩሩው የኢትዮጵያ ህዝብ ደስተኛ እንዲሆን እና ወጣቱም ተስፈኛ እንዲሆን እያስቻለው ነው፡፡ ባለፈው አስር ዓመት ኢትዮጵያ ከአለማችን ፈጣን ኢኮኖሚዎች በመጀመርያ ረድፍ እምትጠራ አገር ሁናለች። ይህ ፈጣን የኢኮኖሚ እድገትም ተጨባጭ እና ሊካዱ እማይችሉና እሰየው እሚያስብሉ ልማታዊ እና ማህበራዊ ለውጦችን አስከትልዋል። ከሞላ ጎደል የተሳካው የምእት አመቱ የልማት ግቦች፣ እንደ ህዳሴው ግድብ አይነት ታላላቅ ፕሮጀክቶች፣ እየተሳለጡ ያሉ ሰፋፊ የሱካርና የማዳበርያ ፋብሪካዎች ተከላ ሲታይ ይህን እዉን ያደረገዉን መንግስት እና አመራሩን ማመስገን ተገቢ ነው ብየ አምናለሁ።

በቅርቡ ጠቅላይ ሚንስቴር ሃይለማርያም ደሳለኝ ያገኙት የ South-South ሽልማትም የዚህ ጥረት ማሳያ ነው፤ ክቡር ጠቅላይ ሚንስቴር እኔም እንዃን ደስ አልዎት ማለት እፈልጋለሁ። የእድገት እና ትራንስፎርሜሽን አንድ (GTP 1) አጠቃላይ አገራዊ ያፈፃፀም ደረጃዉም አበረታች ነበር ማለት ይቻላል፤ በክልሎች መሃል ሊታረም እሚገባው አለመመጣጠን እንዳለ ሆኖ ማለት ነው። በኢኮኖሚው መስክ አገራችን ኢትዮጵያም ገፅታዋንም በፍጥነት እየቀየረች ትገኛለች። GTP 1 አስፍቶ ማስብን እና አግዝፎ መስራትን ያስተማረ እቅድ ስለነበር እያንዳንዱ ዜጋ ላይ የፈጠረው መነሳሳት እንደ ቀላል የሚታይ አይደለም። የተለጠጠ እቅድ ይዘህ እጅግ በጣም ብዙ አልመህ ብዙ ብትሰራ በ ፐርሰንት ሲታይ ትንሽ ቢመስልም ትንሽ አቅዶ እስዋን ብቻ ከማሳካት ግን ሺ እጥፍ ይሻላልም ይበጃልም። ስለዚ ambitious ፕላን መሆኑ ሊደነቅ ይገባዋል። ክጀርባው ያለው እሳቤም ማደግ ካለብን ማህበረ ኢኮኖምያዊ ሽግግር ያስፈልገናል ይህ ለማድረግ ደግሞ ተለቅ ያለ ስራ መስራት አለብን ነው። ይሄም በጎ እሳቤ ነው። ትልቅ ነገር ሳያስቡ ትልቅ አገር መገንባት አይቻልም። ባጠቃላይ በትምህርት መስፋፋት (በተለይ የከፍተኛ ትምህርት ተቛማት መስፋፋት)፣ በጤና ኬላዎች መዳረስ፣ ለ አርሶ እና አርብቶ አደሩ የሚደረጉ ድጋፎች፣ ስፋፊ የትራስፖርት አውታሮች ያሳካ የኢኮኖሚ እድገት፣ ሃብታም ገበሬዎችን መፍጠር የቻለ ግብርና፣ ብዙ ወጣቶችን የፈጠራ እና የሃብት ባለቤት ማድረግ የቻለ ጉዞ ተገቢ እዉቅና ማግኘት አለበት። የኢንዱስትሪ ክፍሉም በብዙ ችግሮች የተሞላ ቢሆንም መንግስት ለዘርፉ የሰጠው ትክረት የላቀ መሆኑ ሊደነቅ ይገባል።

አንፃራዊ ሰላም እና መረጋጋት በማስፈን እና ሰላም ላጡ ህዝቦች የሰላም ሃይል በመሆን እሚደረገው የዲፕሎማሲ እና የመከላከያ ሃይላችን ጥረትም እጅጉን እሚመሰገን ነው።ኢትዮጵያ ላይ የሰፈነው አንፃራዊ ሰላም እና መረጋጋት ዝቅ ተደርጎ ሊታይ እሚችል አይደለም፤ እነ ሶርያ እና ሊብያ ከነ ሙሉ ሃብታቸው ምን አይነት ሁኔታ ላይ እንዳሉም መርሳት የለብንም። እነ ኬንያ እና ሶማልያ በአሸባሪዎች ሲታመሱ በሰላም ተኝተን እምናድረው የሰፈነዉን አንፃራዊ ሰላም ተማምነን ነው። ዋናው የሰላማችን ምንጭ ህገ-መንግስታዊ ስርዓታችን ቢሆንም የፀጥታ ሀይሎቻችን ልዩ ምስጋና ይገባቸዋል፡፡

Photo - General Abebe Teklehaimanot

በተለይም ትህዴንን (TPDM ) ለአዲስ ዓመት ስጦታ በማበርከታቸው አድናቆቴን መግለፅ እወዳለሁ፡፡ በተጨማሪም ከአባይ ወንዝ አጠቃቀም ጋር ተያይዞ የሚታየው የሶስትዮሽ ስምምነትም የኢትዮጵያ መንግስት አስተዋይነት እና ለብሄራዊ ጥቅሙ ያለው ተቆርቛሪነት ያረጋገጠበት ድርጊት ተደርጎ ሊቆጠር እሚገባው ነው።ተስፋ ሰጪ በሆነው አጠቃላይ እንቅስቃሴ ምክንያት የተፈጠረው አገራዊ የህዳሴ መንፈስም ከምንም ሳይሆን መሬት ላይ ካለው እዉነታ የሚመንጭ አወንታዊ ቁጭት ስለሆነ ለለዉጥ ጉዞው እጅግ ጠቃሚ ግብአት ነው። ይሁን እንጂ የኑሮ ውድነት እጅግ እየሻቀበ በመሄዱና በሃብታምና ድሃ ያለው ልዩነት በዚህ ፍጥነት ከቀጠለ አድገኛ ስለሆነ ተገቢ እርምት መወሰድ አለበት እላለሁ፡፡

ልማታዊ ስኬቶቹ የመንግስትን ልማታዊነት ያሳያሉ ማለት ግን ዴሞክራስያዊነቱን ይገልፃል ማለት አይቻልም። ባጭሩ ሰላማዊ እና ልማታዊ ማለት ዴሞክራስያዊ ማለት አይደለም።ዴሞክራስያዊ ድባቡ እየሰፋ ነው ወይስ እየጠበበ ነው? የሚለው ማየት ተገቢ ነው። ይህን ለመመለስ መለከያ ያስፈለገናል፡፡ መመዘኛችን ህገ-መንገስታችን፤ የመንግሰትና የገዢው ፓረቲ አቑዋሞች መሰርት አድርገን ብናየው ስርኣቱን በበለጠ ለማየት ያስችለናል ብየ እገምታለሁ፡፡ “በትግላችንና በከፈልነው መስዋዕትነት የተገኘውን ዴሞክራሲና ሰላም ዘላቂነቱ ለማረጋገጥ” እና ለሌሎች ተዛማጀ “ዓላማዎችና እምነቶች ማሰርያ” እንዲሆን ህገ መንግስቱ መፅደቁ መግብያው ላይ ሰፍሮ እናገኛለን። ለዚህም ነው ሰላማችንንና ዴሞክራስያችንን ዘላቂነቱን ለማረጋገጥ የሚደረግ ጥረት ህገ-መንግስቱን ለማረጋገጥ የሚደረግ ጥረት ነው የምለው።

በ1994 ዓ.ም የማስታወቅያ ሚንስቴር “በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ጉዳዮች” በሚል ርእስ ባሳተመው ፅሁፍ ‘ዴሞክራሲና መልካም አስተዳደር የህልዉና ጥያቄ ነው’ ይላል።ይህ ሰነድ የተሟላ የዴሞክራሲ አስተሳሰብ የተቀመጠበት በመሆኑ የመመዘኛችን መነሻ እነዲሆን ወድጅያለሁ፡፡ ሰነዱ ዘርዘር አድርጎ የተመለከታቸው የዴሞክራሲ ተቛማት ብዙ መሆናቸው መገንዘብ ይቻላል። ይሄው የ 1994ቱ ሰነድ ምክርቤቶችን በተመለከተ እንዲህ ይላል “ምክር ቤቶች የህዝቡ ሉአላዊነት መገለጫ የዴሞክራስያዊ አስተዳደር እምብርትና የዴሞክራስያዊ አገዛዝ አውራ ተቛሞች ናቸው” ይላቸዋል። ሆኖም መሬት ላይ ያለው እውነታው ግን ከዚህ የራቀ ይመስላል። ለምን?

በተመሳሳይም በ 1992 ዓ.ም ለውይይት በተዘረጋው የኢህአዴግ ፅሁፍ ላይ ትምርህርት ቤቶችን በተመለከተ እሚከተለው ሰፍሮ እናገኛለን “ትምህርት ቤቶችን ወደ ኢህአዴግ ትምርህርት ቤትነትን ለመቀየር የማይቻል ከመሆኑም በላይ ሃቀኛ ዴሞክራስያዊም አይሆንም። መላዉን ህዝብ /አብዛኛው ክፍል/ ለአመታት አንድ ፓርቲ አመለካከት በማጋለጥ፣ ሌሎችን በመከላከል የሚደረግ አሰራር መከተል በሃሳቦች መካከል ነፃ ዉድድር እንዳይኖር የሚያደርግ ነው። የሃይለስላሴና የደርግ መንግስታት ይህን ማድረጋቸው የሚያመላክተው ፀረ ዴሞክራስያዊ ባህሪያቸዉን ነው።” አሁንም እውነታው ከዚህ የራቀ ይመስላል።ለምን?

ከአምስት ዓመት በኃላ በ 1999 ዓ.ም የመልካም አስተዳደር ችግር ፈጦ የወጣ ችግር ነው የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሶ ከስረ መሰረቱ እንፈታዋል ተብሎ ተዝምሮለትም ነበር። ነበር ሆኖ ቀረ!! አሁንም በ 2007 ዓ.ም መጨረሻ ኢህአዴግ መልካም አስተዳደር ዋናው ችግሬ ነው እያለ ነው። ይህ ለምን ሆነ? የዚህ ፁሁፍ አላማም ለምን ይህ ችግር ሳይቀረፍ አለ ከተባለበት ግዜ ምንም መሻሻል ሳያሳይ እንደዉም ለምን እየተባባሰ እንደመጣ ለማሳየት እና የመፍትሄ ሃሳቦችን ለመጠቆም ነው።

ኢህአዴግ በኢኮኖሚው መስክ ከሞላ ጎደል ያለመዉን እያሳካ ይታያል፤ ከዴሞክራሲ አዃያ ግን እግሩ ሲጎተት መመልከት የተለመደ ሁነት ከሆነ ሰነባብቷል። በዚህ ዙርያም በዴሞክራሲው መስክ ችግሮች እየታዩ ነው ብሎ ኢህአዴግ በ 1992-93 ዓ.ም ከገመገመበት ወቅት እስከ አሁንዋ ሰዓት ይህ ነው ሊባል እሚችል የሰፋ የዴሞክራሲ ድባብ ሳይፈጠር ካለንበት ደረጃ ላይ ደርሰናል።ችግሩ የክልስ ሃሳብ አለመሆኑ ሰነዶችን በመመልከት መገንዘብ ይቻላል።

GTP 1 በሚፈለገው መጠን እና ፍጥነት እንዳይሳካ ካደረጉት ምክንያቶች የመልካም አስተዳደር ችግር በዋናነት መጠቀስ ይቻላል። ካጠቃላይ የዴሞክራሲ ድባብ መጥበብ ጋር ተያይዘው የሚከሰቱ የመልካም አስተዳደር አለመኖር፣ የሙስና እና የፍትህ መጏደል ናቸው የGTP 1ን አፈፃፀም በሚፈለገው ፍጥነት ያላስኬዱት። መልካም/ዴሞክራስያዊ አስተዳደር ማስፈን ከተበላሸ/ ካልተቻለ GTP 2 አይሳካም ብቻ ሳይሆን ከዚህ በፊት አገራችን የሰራቻቸው የሚያፈርስ፣ሰላማችን እና መረጋጋታችን እንድናጣ የሚያደርግ በመሆኑ እዛ ላይ አተኩሬ ትዝብቴን እገልፃለሁ። ይህ ፅሁፍ በጥልቀት በተሰራ ጥናት እና ምርምር ሳይሆን ባጠቃላይ ቅኝት (General Observation) የተሞረኮዘ ሲሆን፤ የማነሳው ጉዳይ ሰፋ እና ዘርዘር ያለ ምርምር እንደሚያስፈልገውም መጠቆም እወዳለሁ። በጥልቅ ጥናት ላይ ያልተመሰረተ በመሆኑ አንዳድ ሁኔታዎችን በሚገባ ያልገለፅኩት ካለ ወይም በጣም ካጋነንኩት አንባብያንን ከወዲሁ ይቅርታ እጠይቃለሁ።

የዚህ ፅሁፍ ፀሀፊ በዲሞክራሲ ዙሪያ የሚታዩ እጥረቶች (Democratic deficiency) የችግሮቹ መንስኤዎች ሲሆኑ ቀጣይነት ያለው የተሟላ ዲሞክራሲያዊ እና ህገመንግስታዊ ተቋማት መገንባት ደግሞ መፍትሄዎቹ ናቸው ብሎ ያምናል:: ለዚህ ፅሁፍ ሲባል የህዝብ መወከያ ተቋማት (ፓርላማ እና በሁሉም ደረጃ የሚገኙ ምክርቤቶች)፤የመገናኛ ብዙሃን እና የአንድ ለአምስት አደረጃጀት ልቃኝ መርጭያለሁ፡፡ የፁሁፉ አወቃቀር እንደሚከተለው ይሆናል፤ በመጀመርያ አሉ ያልኳቸዉን መሰረታዊ ችግሮቻችንን ከዘረዘረ እና በሁለተኛው ክፍል ዋና መንስኢዎቻቸው ላይ ገለፃ ካድረገ በኃላ በሶስተኛው ክፍል ቀጣይነት ያለው የዴሞክራሲ ግምባታ የችግሮቻችን መፍትሄ የሚል ርእስ ላይ ያተኩራል። በመጨረሻም ንቅናቄው እንዴት መቀጣጠል እንዳለበት የሚያመላክት የመሰለኝኝ ሃሳብ አቀርባለሁ፤ መልካም ንባብ።

2.ችግሮቻችን ምንድን ናቸው? መልካም አስተዳደር የወቅቱ ቁልፍ ችግር

2.1 በአሁኑ ግዜ የችግሮቻችን አውራ መልካም አስተዳደር ያለማስፈን ችግር ነው ተብሏል፡፡ ለመሆኑ መልካም/ዴሞክራስያዊ አስተዳደር ምን ማለት ነው?

የመልካም ወይም ዴሞክራስያዊ አስተዳደር ምንነት በጣም አከራካሪና ሰፋ ያለ ሙግት እሚካሄድበት መስክ እንደሆነ ግንዛቤ ዉስጥ በመክተት ነው በዚህ ንዑስ ርእስ ስር ለዚህ ፅሁፍ ሲባል የተወሰኑ መሰረታዊ ነገሮች ላይ ማተኮር የመረጥኩት። መስተዳድር ወይም አስተዳደር የሚለው ንድፈ ሃሳብ አዲስ ያልሆነና ለተለያዩ ሰዎች የተለያየ ትርጉም የሚሰጥ ነገር ነው። እንደ ናንዳ (Nanda, 2006: 271) ገለፃ አስተዳደር የሚለው ሃሳብ የትርጉም እልባት ያላገኝ እና ትርጉሙም ልናሳካ በምንፈልገው አላማ እና በምንከተለው ዘይቤ እንደሚመሰረት ታብራራለች። አስተዳደር የነባራዊው ፖለቲካዊ ስርዓት ነፀብራቅ ሲሆን በመጠነ ስፋቱ እና ተዛማጅ ትርጉሙም ከግዜ ወደ ግዜ እንዲሁም ከቦታ ወደ ቦታ የሚለያይ ነገር ነው። በፍፁማዊ የዘዉድ አገዛዝ እና ሌሎች የአምባገነን መንግስታት አስተዳደር ሊያሳካ እሚችለው የመጨረሻው አላማ የአስተዳደር ቢሮክራስያዊ ገፅታው፤ ማለትም ዉጤታማነት እና ብቁነት (ቅልጥፍና) ነው።

ማህበረ -ኢኮኖምያዊ እና ፖለቲካዊ እድገቶችን እና የዴሞክራሲ ጅማሬን ተከትሎ ግን አስተዳደር የሚለው ሃሳብ መልካም አስተዳደር ወይም ዴሞክራስያዊ አስተዳደር የሚሉትን በማካተት መልካም አተደዳደርን የዴሞክራሲ ፀጋ አድርጎ መቁጠር የተዘወተረ ነገር መሆን መጀመሩ መገንዘብ ይቻላል። መልካም አስተዳደር ወይም ዴሞክራስያዊ አስተዳደር ከዉጤታማነት እና ብቁነት የሰፋ እና የገዘፈ ሃሳብ ሲሆን፤ ላጠቃላይ የፖለቲካ ስርዓቱ የሚቆምና የዜጎችን ፖለቲካዊ እና ሰብአዊ መብቶች እና ነፃነቶች የሚያስከብርና ማንኛዉምም ዓይነት አድልዎ የማይቀበል ሂደት ነው። ግልፅነት እና ተጠያቂነትም በሲቪል ሰርቪሱ ብቻ የማይታጠር በፖለቲካ አመራሩ እና ተቛማት ሊተገበር እሚገባው ቁልፍ የመልካም አስተዳደር አካሎች ናቸው።

ገብረቭቢ ‘Democracy, Democratic Institutions and Good Governance in Nigeria’ በተሰኘው ፁሁፉ አልካሊ የተባለ ተመራማሪን ጠቅሶ እንደሚለው አስተዳደር ማለት የፖለቲካ ስልጣንን ህዝባዊ ጉዳዮችን ለማስኬድ ማዋል እንደሆነ ይጠቅስና፤ አስተዳደር የሚዳስሳቸው ጉዳዮች ብሎ የህግ የበላይነትን፣ ተጠያቂነትና ግልፅነትን፣ ልማት ተኮር አመራርን፣ ራስን የመግለፅና የመደራጀት መብትን፣ መልስ ሰጪነትን፣ ሃላፊነት መዉሰድን፣ ወካይነትን፣ ዉጤታማነት እና ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠትን እንደሚያካትት ይገልፃል። ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚነሳው መልካም አስተዳደር እሚለው ጽንሰ ሃሳብ ነው፡፡ ሻቢር ቼማ እንደሚለው “መልካም አስተዳደር ያለዉን ሃብት ለጋራ ችግሮች እንዴት መዋል እንዳለባቸውና በምን አኳሃን መመራት እንዳለባቸው የሚመለከት እንደሆነ ይጠቅሳል። መገለጫ መርሆቹም አሳታፊነት፣ ግልፅነት፣ ተጠየቂነት፣ የህግ የበላይነት፣ ዉጤታማነት፣ ፍትሃዊነት እና ስትራቴጅያዊ ራዕይ መጨበጥን ያካትታል ይላል።” (2005:33).

አዳምስም በተመሳሳይ ስለ ዴሞክራስያዊ አስተዳደር የሚከተለውን ይላል ዴሞክራስያዊ አስተዳደር የህዝባዊ ተቛማት ግልፀኝነት እና ተጠያቂነት ይፈልጋል። ዜጎችም ስለ መንግስት ፖሊሲ፣ ዉሳኔዎች እና ተግባራት መረጃ የማግኝት መብት ሊኖራቸው ይገባል። በኛ አገር ሁኔታ ይህ እንዳይሆን እንቅፋት ከሆነው አንዱ የመንግስት የመረጃ አያያዝ ደካማነት፣ የዜጎች መረጃ የማግኘት መብት እንዳላቸው አለመገንዘብ እና በዋናነት ደግሞ ሚስጢራዊ እና ሚስጢራዊ የሆኑ መረጃዋች መለየት አለመቻል ነው፤ ይህ ሁኔታ ካልታረመ መሰረታዊ የዜጎች መረጃ የማግኘት መብት ስለሚጋፋ ለዴሞክራሲ ምህዳር መጥበብ የራሱ አስተዋፅኦ ማድረጉ አይቀርም። አዳምስ አያይዞም በሃላፊነት ያሉ ሰዎች ለድርጊታቸው እና ላፈፃፀም ግብራቸው ተጠያቂ መሆን አለባቸው ይላል። የተጠያቂነት እና ግልፀኝነት መርህ መንግስት አካባቢ ለሚኖረው ሙስና ለመግታት እና የዜጎች ተሳትፎ ለማበርታት ጠቃሚ ነገሮች ናቸው ይላል። ዜጎች ሃሳብን እና ራስን በነፃ የመግለፅ፣ የመደራጀት እንዲሁም ማንንም ሳይፈሩ ድርጅት የመመስረት እና የተመቻቸውን ድርጅት የመቀላቀል መብት ሊኖራቸው እንደሚገባ ያትታል።ከዚህ መረዳት እምንችለው መልካም/ዴሞክራስያዊ አስተዳደር ሲባል ቁንፅል ፖለቲካዊ ሃሳብ ሳይሆን የዜጎችን ስብአዊ እና ዴሞክራስያዊ መብቶችን በአስተዳደር መዋቅር እና ትግበራ ከግምት ማስገባት ማለት እንደሆነ ነው::

እንደ ተመዱ የኤስያና ፓስፊክ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ኮሚሽን አረዳድ መልካም አስተዳደር ስምንት ዋና ባህርያት አሉት ይላል። እነዚህም አሳታፊነት፣ መግባባት ላይ ያተኮረ (Consensus oriented) ፣ ተጠያቂነት፣ ግልፅነት፣ መልስ ሰጪ (Responsive)፣ ዉጤታማ እና ብቁ (ቅልጥፍና)፣ፍትሃዊ እና ሁሉን አቃፊ (equitable and inclusive) እንዲሁም የህግ የበላይነት ናቸው ይላል። መልካም አስተዳደር የህዳጣን (Minorities) እና የሌሎች ተጋላጭ የህብረተሰብ ክፍሎች ሃሳብ እና ድምፅ በዉሳኔ መስጠት ሂደት ላይ ግምት ዉስጥ መክተትንም ይጨምራል ይላል። አሁን ላለው እና ወደፊት ለሚመጣው ማህበረሰባዊ ፍላጎትም ጭምር ዝግጁ የሆነና መልስ መስጠት የሚችል አቅም እና መዋቅር መፍጠር ነው መልካም አስተዳደር። ሰለዚ አንድን ሰርአት መልካም ነው ወይስ መጥፎ አስተዳደር ነው ያለው የሚለዉን ለመገንዘብ ከነዚህ መለክያዎች አንፃር ነው ማየት ያለብን።

ዴሞክራስያዊ ፖለቲካዊ ስርዓት መንግስታዊ ስልጣን የያዙ ሰዎች ላይ ህጋዊ ገድብ ያስቀምጣል። ስልጣን ለተለያዩ የመንግስት አካላት የሚሰጥበት ምክንያትም በተወሰኑ ተቛማት ወይም ግለሰቦች ብቻ ሃይል እንዳይከማች ከሚል እሳቤ ነው። የተለያዩ የመንግስት አካላት በቂ የሆነ አቅም እና ነፃነት ኑሮዋቸው አንዱ መዋቅር ሌላኛዉን እሚቆጣጠርበት እና ህገ መንግስታዊ ሚዛን እሚጠብቅበት አሰራር ያስፈልገዋል። ወታደራዊ ተቛሙም በ ሲቪልያን ቁጥጥር ስር ማድረግ መቻል ለዴሞክራስያዊ አስተዳደር በጣም ወሳኝ ነው ይላል ፍራንሲስ አዳምስ። እንደ አዳምስ አነጋገር ወታደራዊ ሃይሉን በበላይነት የማዘዝ ስልጣኑ በምርጫ በሚቛቛመው አገራዊ ፖሊሲዎችን በሚያወጣው እና ያለ ወታሃደራዊ ጣልቃ ገብነት ስራዉን በሚተገብረው ሲቪል አስፋፃሚ መሆን አለበት ይላል።

[የኢፌዴሪ ህገ መንግስት አንቀፅ 74/1 እንደሚለው “… ጠቅላይ ሚኒስቴሩ የጦር ሃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ነው” እንዲሁም በአንቀፅ 87/2 መሰረት “የመከላከያ ሚኒስቴር ሆኖ የሚሾመው ሲቪል ይሆናል” ይላል።]

2.2.የመልካም/ ዴሞክራስያዊ አስተዳደር ችግሮች ስፋትና ጥልቀት

ባጠቃላይ የሃገራችን ሁኔታ ሲታይ መልካም አስተዳደር ማረጋገጥ አለመቻል፣ ሙስና፣ እና የፍትህ እጦት ሶስት አደገኛ የስርዓቱ በሽታዎች ናቸው፡፡ እነዚህ በሽታዎች አጠቃላይ የዲሞክራሲ ሁናቴው ሲቀጭጭ ከቁጥጥር ውጪ የመሆን እድላቸው ይሰፋና ማስተካከያ እርምጃ ለመውሰድ አዳጋች ይሆናል፡፡ እነዚህን ሶስት አደገኛ በሽታዎች ለዘመናት ከኛ ጋር የኖሩ እና አሁንም በከፍተኛ ሁኔታ እየተፈታተኑን የሚገኙ ስለሆኑ ኢኮኖሚያዊ ከሆኑ መንገዶች በተጨማሪ ሌላ መፍትሄ ማበጀት ካልተቻለ በቀጣይነት ግዝፈታቸው እየጨመሩ መሄዳቸው እማይቀር መሆኑ መገንዘብ አለብን:: ባጭር አማርኛ ችግሮቹ አብረውን የነበሩና አሁንም እያኗኗሩን ያሉ በሽታዎች ናቸው፡፡ ኢህአዲግ መሰረታዊ የስርዓቱ በሽታ ብሎ የዘረዘራቸው ሙስና፤ መልካም ያልሆነ አስተዳደር እና የፍትህ መጓደል እስካሁኑ የተገኙት ድሎችን መና ሊያስቀር እንደሚችል እውቅና መስጠቱም ይብል የሚያስብል ነው፡፡

አሁን ኢትዮጵያ ላይ ያለው የዴሞክራሲ ድባብ ሲታይ ዜጎች የሚስማቸውን ቅሬታ ለመግለጽ አብዛኞቹ መንገዶች የሳሱበት ፣ አማራጭ የመረጃ ምንጮች በከፍተኛ ፍጥነት እየቀጨጩ፣ የማበህራት ነፃነት እተገፋፋ፣ የመናገር እና ባጠቃላይ ሃሳብን የመግለጽ መብቶች በሚታዩ እና በማይታዩ ዘዴዎች እየተዳከሙ ያለበት ሁኔታ እታዘባለሁ፡፡ መልካም አስተዳደር ህልም የሆነበት ሙስና የያንዳንዱ መንግስታዊ መዋቅር እና ሰዎች “ልሙድ ተግባር” የሆነበት፣ ፍትህ ከርትዕ ርቆ የጉልበተኞች መጫወቻ እየሆነ ባጠቃላይ ዜጎች በፍርሃት የተሸበቡበት ፖለቲካዊ ሁኔታ ነው ያለው፡፡ የፍርሃት ዋና መንስኤ ደግሞ ጤንነቱ የተዛባ የፖለቲካ ሁኔታ ነው።

አካፋን አካፋ ካላልን ግብዝነት ይነግሳል፣ ውሸት ሃይል አግኝቶ እውነትን ይተካል፡፡ በመንግስት በኩል ደግሞ የ “ማን አለብኝነት” ትእቢት እና ተቛሚዊ አሰራር መጥፋት እና ሌሎች ተደማምረው የአምባገነንነት ዝንባሌዎች (Dictatorial Tendency) እየታዩ ነው፡፡ 10ኛው የኢህአዴግ ጉባኤ ችግሮች ብሎ የለያቸው ሰናይ ከላይ የገለፅኩት ምስል ነው የሚያሳየን:: ለምሳሌ መቐለ በተካሄደው በኢህአዴግ 10ኛው ጉባኤ ዋና ዋና ድክመቶች ተብለው በጉባኤው ተቀባይነት ካገኙት ካነሳነው ጉዳይ ተያያዥ የሆኑትን ልጥቀስ፡፡ ምንጮቼ በጉባኤው በታዛቢነት ተሳትፎ አድርጎ የነበረዉ ሪፖርተር ጋዜጣና ያነጋገርዃቸው ተሳተፊዎች ናቸው።

* “ህዝባዊነት በግለኝነት እየተሸራረፈ ነው፡፡ ህዝብ የበላይ ወሳኝና ተቆጣጣሪ መሆኑ እየተዘነጋ የግል ጥቅም እና ምቾት ለማሳካት መንቀሳቀስ በኢህአዴግ ውስጥ እየተስፋፋ መጥቷል፡፡

* ኪራይ ሰብሳቢነት እና ሙስና እየተስፋፋ ነው፡፡

* መልካም አስተዳደር እየጠፋ ነው፡፡

* የፍትህ ስርአቱ እየተዳከመ ነው፡፡

* ተጠያቂነት እየጠፋ ነው፡፡

* የማህበራዊ አገልግሎት አቅርቦት ችግር አለ፡፡

ኢህአዴግ ባጭሩ እያለን ያለው “የሙስና፣ መልካም አስተዳደር የማሰፋን እና የፍትህ ችግሮች እየተባባሱ ነው” ነው፡፡ይህም በመሰረቱ ትክክል ነው። ህዝብን እሚሰማ እየጠፋ ‘እኔ አውቅልሃሎህ’ ባይ እየበዛ፣ ህዝቡ ችግሩ ሲናገር ከተቃዋሚዎች ጋር እያስተሳሰሩ ማሳደድ፣ ዝም ሲል ደግሞ እንደተመቸው አድርጎ ማሰብ፣ እንደ ፓርላማ የመሳሰሉ የዴሞክራሲ ተቋማት ግዴታዎችን በበቂ ሁኔታ አለመወጣታቸው የስራ አስፈፃሚውን ጡንቻ እያሳበጠ ሄዶ ሄዶ አሁን ላለንበት ሁኔታ አድርሶናል፡፡ የዚህ ሁሉ ድምር ውጤት ነው ዴሞክራሲያዊ ሁኔታውን ያጠበበው፣ የዚህ መጥበብ ልጆች ናቸው እነ ፍትህ ማጣት፣ ሙስና እና መልካም ያልሆነ አስተዳደር እሚባሉ በሽቶች፡፡

3. የችግሮቻችን መሰረታዊ ምንጭ ምንድን ነው?

ለበሽታዎቻችን እንደ የአቅም ማነስ፣ ድርጅታዊ ድክመት፣ ያልዳበረ ህዝባዊ የተሳትፎ ባህል የመሳሰሉት ነገሮች መነሻ ምክንያት ሊሆኑ ቢችሉም ዋናው እና ተጠቃሽ ምክንያት ግን አጠቃላይ የዴሞክራሲያዊ ሁናቴ እጥረት ነው፡፡ እንከን የለሽ ዴሞክራሲ እሚባል ነገር እንደሌለና ኢትዮጵያችንም ጀማሪ ዴሞክራሲ መሆንዋንም እረዳለሁ፡፡ በዚህ ምክንያትም ነው በኢትዮጵያ ዴሞክራያዊ ስርዓት ለመገንባትም ለመቀልበስም ሊያግዙ እሚችሉ ነገሮች በብዛት እሚገኙት፤ ለዚህም ነው ጀማሪ ዴሞክራሲያችንን ሊቀለብሱ እሚችሉ ሃይሎች እና ሁኔታዎችን በቅጡ ተገንዝበን እና ለይተን በቁርጠኝነት አረንቋውን ማድረቅ ያለብን፡፡ ለዚህም ነው ቲሊ ዴሞክራታይዜሽን መቼም ሙሉ መሆን እማይችል እና የ ኢ ዴሞክራታይዜሽን አደጋ ሊያጋጥመው የሚችል ተለዋዋጭ ሂደት ነው የሚለው። ኢ ዴሞክራታይዜሽን ማለት ቅልበሳ ማለት ነው። በተለያየ አቅጣጫ ተቀራርበው እሚንቀሳቀሱ ሂደቶች ዴሞክራታይዜሽንን እና ቅልበሳዉን ሊያመጡ ይችላሉ ይላል። “Closely related processes, moving in opposite directions, produce both democratization and de democratization”፡፡ ሙለር እና በርግማን እንደሚሉት ዴሞክራሲ ቀላልም ቀጥ ያለም ያልሆነ ግን ደግሞ ሊሳካ የሚችል ነገር ነው:: በነዚህ እና በሌሎች ምክንያት ነው አገሬ ላይ እዉን ሆኖ ማየት እምፈልገው ዴሞክራሲ ሃሳባዊ የሆነና ምንም እንከን የሌለው ዴሞክራሲ አይደለም የምለው፡፡

የአገራችን የዴሞክራሲ ሁኔታ ለጋ ነው ስል የሚከተለውን የቲሊ አባባል ያስታዉሰኛል፤ በቲሊ አረዳድ “We are not trying to explain yes-no swiches between undemocratic and democratic conditions. We are not trying to explain degrees and changes of democracy” ስለዚህ ስለ አገራችን የዴሞክራሲ ሁኔታ ሳወራ ስለ ሂደት እንጂ ህልመኛ ሆኜ መሆን የማይችለውን እና እስከአሁን አለም ላይ የሌለውን ገነት መሳይ ዴሞክራሲ ፈልጌ አይደለም፡፡ ለምሳሌ እ.ፋ.አ ከ 1789 ጀምሮ ፈረንሳይ በትንሹ አራት የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ክፍሎች ስታይ በትንሹ ደግሞ ሶስት የዴሞክራሲ ስርዓት ቅልበሳ ግዝያቶች አሳልፋለች፡፡ ዘመናችን የዴሞክራሲ በመሆኑ እንደዚህ ኣይነት የቅልበሳ የቅንጦት (luxury of de-democratization) አማራጭ ግን የለንም። በኛ ሁኔታ ተደጋግሞ እንደተገለጸው ዴሞከራሲ የህልውና ጉዳይ ነው፡፡ እየተንገራገጨ ቢሆንም ሁሉ ግዜ ወደፊት መጏዙን ማረጋገጥ ይኖርብናል እንጂ አጠቀላይ ቅልበሳ አገሪቱ ወደ አደገኛ ቀዉስ ይመራታል፡፡

የዲሞክራሲ እጦት የተመረጠ እና ልዩ የመጥፎ አስተዳደር ማዳበሪያ ነው፡፡ የፈለገው ልማት ቢመጣ ዲሞክራሲያዊ ምህዳሩ መጥበብ ካሳየ ሶስቱም በሽታዎች አለን!! አለን!! አለን!! ምን አባታቹህ ታመጣላቹህ! እያሉ መፈንጨታቸው አይቀርም::በሽታዎቹ እንዳይፈነጩብን በመሰረቱ የሚከላከልልንን ዲሞክራሲያዊ ህገ መንግስት አለን፡፡ ችግሩ ተግባር ላይ ሲዉል ህገ-መንግስቱ ባስቀመጠው መንፈስ (Sprit of the Constitution) አለመተግበሩ ነው፡፡ ከፍ ያለ ኢ-ህገ-መንግስታዊነት ሲበረታ ሶስቱ በሽታዎች የራሳቸው ሰንደቅ አላማ እያውለበለቡ ‘አሸናፍናቹህ፤ ረታናችሁ’ ይሉናል:: አጠቃላይ የዲሞክራሲ ከባቢው እየጠበበ ሲሄድ ሶስትም በሽታዎች ተጠናክረው፤ ተበረታተው፤ ተባዝተው እና ተኳኩለው ይፈነጩብናል፡፡ በዴሞክራታይዜሽን እና ኢ-ዴሞክራታይዜሽን ሂደቶች ሁሌም መሳሳብ እና ዉጥረት ይኖራል። መንግስት እንደ መንግስት ግን የዴሞክራታይዜሽን አጋዥ አልያም የኢ-ዴሞክራታይዜሽን አሳላጭ ነው መሆን እሚችለው፤ መሀል ላይ የሚንገዋለል መንግስታዊና ተቛማዊ አቛም ሊኖር አይችልም። ስለዚ ምርጫው አንድ እና አንድ ነው፤ ለዴሞክራሲ መስራት ወይም የፀረ ዴሞክራሲ ሃይል መሆን።

ዲሞክራሲያዊ ሁኔታ እና ሶስቱ በሽታዎች በተቃራኒ መንገድ ነው ጉዞአቸው፡፡ ዲሞክራሲያዊ ሁኔታው ሲሰፋ በሽታዎቹ መጠጊያ እና መሸሸጊያ ፍለጋ ይኳትናሉ፡፡ ምሽግ ፈልገው ወይም ቆፍረው ይደበቃሉ፤ልክ የወባ በሽታ ከህክምና በኃላም ቢሆን በሆነ የሰውነታችን ክፍል እንደምትደበቀው፤ ይሄ ለመደበቅ እምታሳየው ባህሪ ነው፡፡ ዲሞክራሲያዊ ምህዳሩ ሲጠብ ደግሞ በሽታዎቹ ወደ አደባባይ እየወጡ ህጋዊ ልባስ እየተጎናፀፉ መገናኛ ብዙሀንን ጭምር እየተጠቀሙ ይፈነጫሉ፤ ህዝብንና አገሪትዋንም በኃሊት ማርሽ ወደ አዘቀት ይከቷታል፡፡ ከስር እምታዩት ስእላዊ መግለጫ ይህንን ሃሳብ የበለጠ ለማስረዳት በፀሃፊው የተዘጋጀ ነው::

Diagram one
Diagram one

[ምስል አንድ: የዴሞክራሲ ምህዳር ሲሰፋ በሽታዎቹ ይቀጭጫሉ፤ በተቃራኒው የዴሞክራሲ ምህዳሩ ሲጠብ በሽታዎቹ ጎልተው እና ጠንክረው ይወጣሉ።]

ልማት የዴሞክራሲ አካል መሆኑ ሳንዘነጋ፤ ህገ-መንግስቱን የመተርጎም ችግር አለ ሲባል ከዲሞክራሲ አኳያ የተደነገጉት የሲቭል እና ፖለቲካዊ መብቶች ተፈፃሚ አለማድረግ ማለት ነው:: በተጨማሪም በየጊዜው መንግስትን ለማቋቋም በሚደረገው ምርጫ የፍትሃዊነት እና የህዝባዊ ተቀባይነት (Legitimacy) ችግር ሲኖር ነው ህገ-መንግስቱ በአግባቡ እየተተረጎመ አይደለም የሚባለው፡፡

የ2007 ምርጫ ማሸነፍ ያለበት ፓርቲ አሸነፎል፡፡ በእጅጉ ከፍተኛ ድምጽ መመረጡም ይገባዋል እላለሁ፤ ይችን አገር ከውድቀት አስነስቶ በመግቢያ እነደገለጽኩት ወደ ተስፋ ያላት አገር ወደ መሆን እቅጣጫ እየመራት ነው፡፡ አሸናፊነት አይበዛበትም፡፡ የተቃዋሚዎች ድክመት ተጨምሮበት በእጅጉ ከፍተኛ ድምፅ ቢመረጥ አያስገርምም:: ነገር ግን ለምሳሌ ያህል እኔ በመረጥኩበት የምርጫ ክልል እቤት ድረስ የዘለቀ የነበረው መዋከብ እና በኣንዳንድ ምርጫ ክልል አንድ ላምሰት የነበረው አሉታዊ ተጽእኖ ስሰማ፣ የመገናኛ ብዙሃን አጠቃቀም የነበረው ከፍተኛ ኣድልዎ ስገነዘብ ምርጫው እንከን የለሽ ነው ሲባል እስቃለሁ። ህዝቦቻችን መብታቸውን ለማስጠበቅ ባልቻሉበት፡ ህገ-መንግስታዊ እና ዴሞከራሲያዊ ተቓሞቻችን ባልጠነከሩበት ሁኔታ፡ የመልካም አስተዳድር ችግር ባለበት ሁኔታ ሙሉ ለሙሉ ዴሞክራስያዊ ነው ማለት አይቻልም።

ባጠቃላይ ሲታይ ብዙ ማንነቶች፤ በርካታ ፖለቲካዊ ፍላጎቶች፤መልስ እንሻለን የሚሉ የተለያዩ ጥያቄዎች ባሉበት አገር አንድ ግንባር (ኢህአዴግ) እና አጋሮቹ 100% መቀመጫውን መቆጣጠር እሚያሳየን ነገር፤አንድም ባጠቃላይ ፖለቲካዊ ስርዓቱ ላይ ችግር መኖሩን አልያም የምርጫ ስርዓቱ ችግር እንዳለበት ወይም ተግባራዊነት ላይ ችግር እንደነበረበት ነው፤ 100% እሚባል ውጤት አስቂኝ ግን ደግሞ አደገኛ ነው ፡፡ ይሄ ዉጤት አርቆ ለሚያስብ ሰው የአደጋ እንጂ የድል ምልክት ተደርጎ መቆጠር አይችልም። መሬት ላይ ያለዉን የተለያየ ፖለቲካዊ ፍላጎት እማያንፀባርቅ የምክር ቤት ሁኔታ የስጋት እንጂ የኩራት ምንጭ መሆን አይችልም።

የሰፋ ዴሞክራስያዊ ምህዳር ሲኖር የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶች እና ግለሰቦች በእኩልትን አለን የሚሉትን አማራጭነት ለህዝቡ እንዲያቀርቡ ያስችለዋል፡፡ ዴሞክራሲ ማለት እኮ የተለያዩ ሃሳቦች በእኩልነት ለዉድድር እሚቀርቡበት ፖለቲካዊ ገበያ ማለት:: ይህ ተጨባጭ ምሳሌ የሚነግረን ነገር አንድ እና አንድ ነው፤ እሱም አጠቃላይ የዲሞክራሲ ምህዳሩ ሲጠብ ሶስቱም በሽታዎች በግላጭ ባንዲራቸውን ለማውለብለብ እንደማይቸገሩ ነው፡፡

ህዝቡ በሶስቱም በሽታዎች ሲጠቃ ለምንድን ነው በሚሰማ ሰላማዊ ሰልፍ ፤ህዝባዊ ስብሰባዎች ፤ተወካዮችን በመሳብ (recall) እና ሌሎች መንገዶች ተጠቅሞ ምሬቱን ማሰማት ያልቻለው? እሚለው በደንብ መጤን አለበት ፡፡ ልክ በ10ኛው የኢእሀዴግ ጉባኤ እንደተገለፀው ‘ደህና ፤ ይስተካከሉ ይሆናል’ ከሚል መነሻ ሊሆን ይችላል፤ ሌሎች ምክኒያቶች ግን ሊኖሩ እንደሚችሉ መገመት አለብን፡፡ለምሳሌ ህዝብ ዝም ያለው መብቶቹን እሚያረጋግጥበት ሁኔታ ስላላገኘ ሊሆን ይችላል፡፡ አንዳንዴ መሰረታዊ በሆኑ የመኖር ጉዳይ ላይ እያማረረ እለታዊ እንቅስቃሴውም ጭምር ማከናወን እየተሳነው እያለም በግልጭ ተቋውምውን ማሰማት ያልቻለው ለምን ይሆን? ወይስ ተቓዉሞ መግለፅ እሚያስከፍለው ዋጋ ካቅሙ በላይ ስለሆነበት ነው? ወይስ ተባብሮ የመስራት ችግር (Collective Action Problem) ነው? ወይስ አፋኝ መዋቅሮች አላንቀሳቅስ ብለዉት ነው?

በውሃ ፤መብራት እና ሌሎች አገልግሎቶች በብዛት የሚማረር ህዝብ እንኳን መብቴ ተጣሰ ብሎ ውስጥ ለውስጥ ከማንሾካሾክ አልፎ መብቱን ሲያስከበር አይታይም:: ለምን? እሚለው ጥያቄ በጥልቀት ስንመረምር ነው ብዙ ነገር ሊገባን የሚችለው:: ይህ በንዲህ እንዳለህ አጠቃላይ ዲሞክራሲያዊ ሁኔታው እየሰፋ እና አመቺ እየሆነ ካልሄደ ሶስቱም በሽታዎች ህዝብ ላይ መፈንጨታቸው አይቀርም፡፡ ሁኔታዎች እንዲህ ባለ ጠባብ የዲሞክራሲ ምህዳር ሲቀጥል እሚያስከትሉት መዘዝ ዘርፈ ብዙና ብዙ ዋጋ ያስከፈለና ወደ ፊትም እሚያስከፍል ስለመሆኑ ለመተንበይ ነብይ መሆን አይጠበቅብንም፡፡ GTP 1 በሚፈለገው መጠን ተግባራዊ እንዳይሆን ብቻ ሳይሆን GTP 2ንም ጭምር አደጋ ላይ ሊጥለው እሚችለው ይሄው ጠበብ የዲሞክራሲ ምህዳር ነው፡፡

ዲሞክራሲያዊ ምህዳሩ በጠበበ ቁጥር የዜጎች ተስፋ እተሟጠጠ ስጋታቸው እና ፍርሃታቸው እየጨመረ ከቁጥጥር ውጪ የመሆኑ እድል ይሰፋል፡፡ ይህን መሰል ሁኔታም ከውስጥም ከውጪም ለነሱ ለሚችሉ ፅንፈኛ ሃይሎች ምቹ ሁኔታ ስለሚፈጥር አገሪትዋን ወደላስፈላጊ መንገድ ሊመራ ይችላል፡፡ ፍትህ ተራ ፍርድ የማግኘት ጉዳይ አይደለም፡፡ ፍትህ የማህበራዊ ተቛም የመጀመርያ ፀጋው ነው ይላል ጆን ራዉልስ፡፡ ሙስናና መልካም ያልሆነ አስተዳደርም ሃገርን ሊበትን የሚችል፤እየታየ ያለውን ኢኮኖሚያዊ እድገት ገደል የመክተት አቅም ያላቸው ስርዓታዊ በሽታዎች ናቸው፡፡የሶስቱም እናት ደግሞ የጠበበ ወይም የኮሰመነ የዲሞክራሲ ምህዳር ነው፡፡

4. በኢህአዴግ እሚመራው መንግስት የዴሞክራሲ ምህዳሩ በማስፋት መልካም አስተዳደርን ለምን አላረጋገጠም?

አሁን ካሉት በርካታ ፓርቲዎች የ ሃያኛው እና ሃያአንደኛው ክፍለ ዘመን ቅይጥ አተሳሰብ ያላቸው ናቸው። የ1960ዎቹ ትውልድ “እኔ ያልኩት ካልሆነ ሌላው ዉድቅ ነው” የሚለው አስተሳስብ በትጥቅ ግዜ በነበረው ሁኔታ የድርጅቶች የመጥፋት አጋጣሚ በነበረበት ግዜ የተለያዩ ሃሳቦች እንዳይንሸራሸሩ እማያበረታታ ሁኔታ ሲፍጠር እየጎለበተ ሁኔታዎች ሲረጋጉ አየቀነስ እንደገና ድርጅቶቹ ከዓላማዎቻቸው በላይ ሲሆኑ “ድርጅታችን ልትጠፋ ነው፤ እንዳትጠፋ እናድናት” የሚለው አስተሳሰብ አሁንም በሰላሙ ግዜ ሲንጸባረቅ ይታያል:: ዴሞክራሲ የሚጠይቀው ተጣጣፊነት፣ መቻቻል እና የጋራ መግባባት በተወስኑ ኣመራር እና ወጣት ክፍል ቢንጸባርቀም አሁን ያለው ገዢ አስተሳሰብ ግን ያለመታረቅ ባህል፣ የመጋፈጥ ፖለቲካ እና መራራቅ (uncompromising militancy, confrontational politics and polarization) ነው።

ፈጣሪ ለኢህኣደግ ብቻ ልዮ ስጦታ እንደሰጠ በሚያስመስሉ ሁሉ “ከኢህአዴግ መንገድ ውጪ ሁሉም የጥፋት መንገድ ነው” እሚል አስተሳሰብ ህዝቦቻችን አማራጭ ሓሳቦችን ተዘርዝረው እና ተደራጅተው በዚህ መሰረት በፈለጉት ጉዳይ ላይ ይህን አማራጭ መሰረት አድርገው እንዲወስኑ ዕድል አይሰጣቸዉም። 1992-1993 በኢህአዴግ ዉስጥ የነበረው የዉስጥ ቀዉስ (Intra-party crisis) አፈታት እሚያሳየንም ይህንኑ ነው። “አንጃዎች” የተባሉት ከሌላኛው የፓርቲው ወገን የነበራቸው ልዩነት ለህዝቡ ለማቅረብ የመንግስት ሚድያ እድል ነፈጋቸው። ያሸነፈው “አንጃ” ግን የመንግስት ሚድያ ልክ የኢህአዴግ ሚድያ እንደሆነ በማድረግ እንደፈለገ ሲጠቀምበት ያለ ምንም ሃፍረት ነበር። ይህ አስተሳሰብ እስካልተወገደ ድረስ የዴሞክራሲ ምህዳሩ መስፋት አጠራጣሪ ነው።ዲሞክራሲያዊ ምህዳሩን በሁሉም መልኩ እየኮሰመነ እንዲሄድና ህገ-መንግስቱም በታለመለት መንፈስ እንዳይተገበር እያደረገ ያለ ይመስለኛል፡፡ በመቐለ ከተማ በግላጭ ባደባባይ ተቋዋሚዎች ኳኺቶ (አደገኛ እሾህ) የሚል ስያሜ ተሰጥቷቸው መወገድ እንዳለባቸው አረም ተቆጠረው መቅረባቸው አሳፋሪ እና ፀረ ህገ-መንግስት የሆነ ድርጊት ነው፡፡

ዴሞክራሲ በአለም ዋና አጀንዳ በሆነበት ሁኔታ በኛ ሃገርም ተደጋግሞ ይዘመራል። በ 1992 ዓ.ም እና 1994 ዓ.ም በኢህአዴግ እና በመንግስት የቀረቡት ፁሁፎች በ ቀዉስ ማግስት የተፃፉ ናቸው። ቀደም ብሎ እንደተገለፀው በተነፃፃሪ ስለ ዴሞክራሲና ተቛሞቹ ጥርት ያለ ሃሳብ አለው። እነዚህ ዶክመንቶች ቀዉሱ ካለቀ በኃላ፤ ማለት መረጋጋት ከተረጋገጠ በኃላ፤ ሳይተገበሩ ሲቀሩ ሸልፍ ማሳመርያ ይሆን እንዴ የተፃፉት? እንድል ያደርገኛል። ዋናው ችግሩ ዴሞክራሲ እሚባል ነገር ከአፋ በላይ ሄዶ ሊዋሃደን አለመቻሉ ነው። Internalize አልተደረገም።

ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ በትጥቅ ትግል የነበረዉን አደረጃጀት እና አስተሳሰብ በመሰረቱ ሳይቀይር ነው መንግስትነትን የቀጠለው። እዚህ ጋ መሰመር ያለበት ጉዳይ የትጥቅ ትግል task እና መንግስት ከተሆነ ወዲህ የሚኖሩት tasks በአጠቀለይ በተለይ ከዴሞከራሲ ስርኣት በመሰረቱ የተለያዩ መሆናቸው ነው። በትጥቅ ትግል ወቀት እንድን ህዝብ ወይ አከባቢ በብቸንነት እንድትቆጣጠር የሚያስገድድ ህዝቡን በዋናነት ደርግን ለመድምስስ ሞቢሊዝ ማድርግ ሲሆን በኢፊዴሪ ሕገ-መንግሰት ግን ሕብረ-ፓርቲ ስርኣት መሆኑን መገንዘብ አለብን፡፡ ኢህአዴግ ለሕብረ-ፓርቲ ስርኣት በተማላ አልተዘጋጀም፡፡

ከድህነትና ከስላም ማጣት የባሰ የህዝብ ጠላት የለምና፤ በፀረ-ድህነት ትግሉ በስላም ማረጋግጥ አመረቂ ወጤት እየተመዝገበ በመሆኑ ህዝባዊነትና የዓላማ ፅናት የሚያሳይ ቢሆንም በዴሞክራሲና በመልካም አስተዳደር ዙሩያ እየታዩ ያሉት መሰረታዊ ችግሮች ህዝባዊነቱ እየተሸረሽሩ ድርጅቱ በመንታ መንገድ እየተጓዘ የገኛል:: በቀጣይነት እሚማር ተማሪ የሆነ ድርጅት (learning organization) መሆኑ እያቛረጠ በመምጣቱ አቅሙ እያሟጠጠ ምናልባትም ከ GTP2 በሃላ ወገቤ የሚል ደርጅት እንዳይሆን ያስጋል፡፡ ሁኔታው መሰረታዊ ለውጥን ይጠይቀል፡፡ የትውልድ እና ያስተሳሰብ መተካካት የሚጠይቅ ሁኔታ ተፍጥሯል፤ እያየን ያለነው መድረኩ የሚፈልገው መተካካት ሳይሆን መሸጋሸግ ነው። ዴሞከራቲክ አስተሳሰብ እና ብቃት ያለው መጪዉን ለመምራት የሚችል በአንፃራዊነት ሲታይ በዴሞክራቲክ ሁኔታ ያደገ ወጣት ሆኖ ህዝባዊ ተቆርቛሪነቱ የላቀ ሙሁር ወደ ስልጣን ከማምጠት እርስ በረሱ ይህ ይሻለል ያኛው እኬል ቡዙ ኣመት ስርተዋል ይተካ አይነት አባካኝ የሰዎች ዝውወር ነው እየተመለከትን ያለነው፡፡ ግዜው ቀጣይነት የለው የአስተሳሰብ ለወጥ ሲጠይቅ ይህን የሚያቀለጠፍ ሂደት ኣልተደራጀም፤ በኔኣረዳድ ወጣት ሆኖ ህዝባዊ ተቆርቛሪነቱ የላቀ ሙሁርና ኢህአዴግ ገና አልተቀራረቡም።ኢህአዴግ ያለማውን ሙሁር ወጣት መጠቀም የማይችል ድርጅት ይመስለኛል፡:

በመንግስት መስርያ ቤቶች ያለው አመዳደብ በብቃት ሳይሆን ከገዢው ፓርቲ ባለው ቅርርብ በመሆኑ ጥቅመኛ (Opportunist) እንዲነግስ ያደርጋል። በማይገባው ቦታ የተመደበ ብቃት የሌለው ሰው ዋናው መሳርያው ኢ-ዴሞክራስያዊ አካሄድ ነው። ይህ እሚሆነው በራሱ ስለማይተማመን ነው። ተቛማት ማእከል ተደርጎ የተሰራ ስራ በጣም ደካማ በመሆኑ የተሻለ አስተሳሰብ እና ብቃት ያላቸው እየደገፉ ወሳኝ ቦታዎችን እንድይዙ ማድረግ አልተቻለም። እላይ የተጠቀሰው አስተሳሰብ እስካልተቀየረ ድረስ ዴሞክራሲ ሊስፋፋ አይችልም። አዲስ አስተሳሰብና ብቃት ባለው አዲስ ትውልድ ሲተካ ነው ዴሞክራሲ የሚያብበው። ይህ ለማድረግ 24 ዓመታት እጅግ ቡዙ ነው ባይባልም ትርጉም ያለው ለውጥ ሊመጣ ይችል ነበር፡፡

5. የመፍተሄ ሀሳቦች

ብዙ ጊዜ ሃላፊነትን ወደታችኛው እርከን ማሻገር በተለመደበት አህጉር ኢህአዴግ በድፍረት ዋናው ተጠያቂ የበላይ አመራር ነው ብሎ ማለቱ ምስጋና እንድቸረው ያደርገኛል፡፡በሽታውን እና ምልክቶቹን እውቅና ሰጥቶ ሃላፊነት መውሰድ ለለውጥ ሂደቱ እንደ መጀመሪያ እርምጃ መቆጠር አለበት፡፡ ከባዱ ስራ ግን ቀጥሎ መከሰት ያለበት እርምጃ ላይ ነው፤ ከባድ እና ውስብስብ እሚሆነብት ምክኒያትም ትግሉ ከሞላ ጎደል ግልፅ ከሆነ ዉጫዊ ሃይል ወይም ተቛም ጋር ሳይሆን ከገዢው ፓርቲና መንግስታዊ መዋቅር ይዘው ከሚገኙ አመራር እና የነሱ ተባባሪዎች ጋር መሆኑ ነው። ባጭሩ ሃላፊነት የወሰደው የበላይ አመራር ከሆነ ትግሉም እዛ ጋር ስለሚሆን ፈታኝ እና ውስብስብ እንደሚሆን ግልፅ ነው፡፡ የኢህአዲግ 10ኛው ጉባኤም ያስተጋባውም ወደፊት ብዙ መሰራት ያለባቸው ነገሮች እንዳሉ ነው፡፡

ከፍተኛ አመራሩ (በደፈናውም ቢሆን) አደገኛ ሆነው ለተገኘት በሽታዎች ዋና ሃላፊነት ወሳጆች እኛው ነን ብለዋል። በርግጥ ስልጣን ሃላፊነትን ጭምር ተሸክሞ ስለሚመጣ በዴሞክራሲ በበለጸጉ አገራት ይህ የተለመደ ተግባር ነው፡፡ እንደ ምልአት ህዝቡና የአህአዴግ አመራር ግንዛቤ በግዜ ተፈትኖ ስራውን በአግባቡ ማከናወን ሲገባው ድክመት ያሳያው አመራሩ ነው ማለቱ ባጭር ግዜ ሲታይ ህዝባዊ ተቀባይነት እና እምነት ሊጣልበት ቢችልም (ሃቅን በመቀበላቸው ምክንያት) ተከትሎ ሊመጣ እሚገባው ቀጣይ እርምጃ ካልተከላበት ግን ሃላፊነት ወስደናል እሚለው ውሳኔ ትርጉም አልባ ከመሆን አልፎ ተመልሶ ከፍተኛ አመራሩን ጥርስ ውስጥ እሚያስገባ ነገር መሆኑ አይቀርም፡፡

ካለው ነባራዊ ሁኔታ ተነስቼ ስቃኝው መንግስት ከሁለት እና ሶስት አመት በሃላ ‘እንዲህ ብለን ነበረ’ እያለ ችግሮቹ ሳይፈታ ሸፋፍኖ የመሄድ እድል አይኖረውም ማለት ይቻላል፡፡ከፍተኛ አመራሩ ሃላፊነት ወስጂያለው ሲል ከሙስና፣ መልካም ካልሆነ አስተዳደር እና የፍትህ መጏደል አኳያ እንዴት ነው በዝርዝር መታየት ያለበት? ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው:: ሃላፊነት እምንወስደው እኛ የበላይ አመራር ነን የሚለው ውሳኔ በሆነ አይነት ህጋዊ፣ አስተዳደራዎ ወይም ፖለቲካዊ እርምጃ ካልታጀበ ትርጉሙ ምንድ ነው?

መፍትሄው ህዝብን ማእከል ያደረገ እንቅስቃሴ መሆን እንዳለበት የኢህአዴግ 10ኛው ጉባኤ ጭምር አመላክተዋል፡፡ ሆኖም የመፍትሄው እንቅስቃሴ (ንቅናቄ) ህገ መንግስታዊና ዴሞክራሲያዊ ተቋማትን መሰረት ያደረገ ካልሆነ ዘላቂነት ባለው መንገድ የሚፈለገው ውጤት አይገኝም፡፡ እነዚህ ተቋማት ለዴሞክራሲ ንቅናቄው ዋስትና መሆን እንደሚቻሉት ሁሉ፣ እየጎለበተ ላለው ፀረ ዴሞክራሲ ዝንባሌም መሳርያ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ህገ መንግስታዊ ዴሞክራያዊ ተቋማት ስል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ስራ አስፈፃሚው ህግ ተርጓሚ በየእርከኑ ያሉትን ኮሚሽኖች እና ባለስልጣን መስርያ ቤቶች የፖለቲካ ድርጅቶች እና የሲቪል ማህበረሰቡን የሚያካትት ሰፊ ሃሳብ ነው፡፡

ለዚህ ፅሁፍ ሲባል ግን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤቶች፣ የመገናኛ ብዙሃን እና የአንድ ለአምስት አደረጃጀትን ብቻ ለማየት መርጭያለሁ፣ ምክንያቱም ሁሉንም ተቋማት ማየት እማይቻልና የተመረጡበት መሰረታዊ ምክንያት ደግሞ ለነዚህ ሶስት ተቋማት እሚደረግ መሰረታዊ ለውጥ ላጠቃላይ የዴሞክራሲ ንቅናቄው እንደ መነሻ ከመጥቀም አልፎ የንቅናቄውን ቀጣይነትም ስለማያረጋግጥ ጭምር ነው፡፡ ይህ ሰላማዊ ንቅናቄ ካለ ስራ አስፈፃሚው ቅን እይታ ተሳትፎና አመራር ሊሳካ እንደማይቻል እምነነቴ ነው፡፡ ሆኖም መደረግ ላለበት የዴሞክራሲ ንቅናቄ የጎላ ተቃውሞ እሚመጣዉም ከስራ አስፃሚው እንደሚሆን ይገባኛል፡፡ ይህ ቀላል ነገር አይደለም፡፡ ስራ አስፈፃሚ አካል ብዙ ስልጣኖች፣ አለም አቀፍ ትስስሮች፣ ጠንካራ የፋይናንስ አቅም፣ አደረጃጀት፣ ታንክ ያሉትና የደህንነት ተቋማት የሚያንቀሳቅስ አካል በመሆኑ የዚህ ክፍል ተቃውሞ ክብደቱ እጅግ የጎላ ያደርገዋል፡፡

ላሉት ዘርፈ ብዙ ችግሮች ዕውቅና መስጠት እና ተያይዞ የመጣው የአመራሩ ሃላፊነቱ የኛ ነው የሚል ድምዳሜ ትልቅ እርምጃ ቢሆንም የችግሮቹ መሰረታዊ መንስኤዎች እና ሊወሰዱ ስለሚገባቸው መፍትሄዎች ግን በጥልቀት የታየ አይመስለኝም። በተለይ ከ 10ኛው የኢህአዴግ ጉባኤ ማግስት በአንድ በኩል የመቀዛቀዝ በሌላ በኩል ደግሞ ችግሮች ቢኖሩም ብዙ እሚያስጨንቁ አይደሉም የማለት እና የማጣጣል አዝማምያዎች እየታዩ ነው። ጠቅላይ ሚንስቴር ሃይለማርያም ደሳለኝ ምክርቤቶችን አስመልክተው፤ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስቴር አቶ ደመቀም ሚድያን አስመልክተው የተናገሩት ነገር ገምቢ እና አበረታች ቢሆንም ሌሎች የመንግስት አካላት ግን ችግሩ ቀለል አድርገው ሲመለከቱ እያየን ነው። ይሄ ተቃርኖም የራሱ ተፅእኖ ሊያሳድር ስለሚችል ሊታሰብለት ይገባል። አሉን ለተባሉት ችግሮቻችን ተቛማዊ መልክ ያለው የዴሞክራሲ ተቛሞች ግንባታ ነው መሰረታዊው መፍትሄ። እነዚህ ተቛማት ገንቢ ሚና ሊጫወቱ እሚችሉት ተገቢ ስራቸዉን በአግባቡ ማከናወን ሲችሉ ነው። ይህ ለማድረግ ደግሞ ጠንካራ ተቛማዊ ስብእና መላበስ ይኖራቸዋል። ይህ ምን ማለት ነው?

5.1 ጠንካራ ተቛማዊ ስብእና (Strong Institutional Integrity)

ቀደም ብሎ እንደተገለጸው የዴሞክራሲ ተቋማት ግንባታ ሙስና፣ ብልሹ አስተዳደር እና የፍትህ እጦት ለሚባል በሽታዎች ዋና መፍትሄ ነው፡፡ ተቋም ሲባል ግን እምነት እሚጣልበት እና ቅንነት ያለው ሲሆን ብቻ ነው፡፡ በእንግሊዝኛው Institutional intergirty እንደሚባለው፡፡ ለአንድ ተቛም ስብእና ማለት የልቀት፣ የታማኝነት እና ህጋዊነት መመዘኛዎችን አካቶ ለመልካም የስራ ባህሪ ሁኔታዎችን ለማመቻቸት የሚይሳየው ቁርጠኝነት ነው።ሮቢን ክረይኪ ውጤታማ የ ተቛማዊ ስብእና መለክያ አለ ይለናል፡፡ እንደሱ አገላለፅ መጀመርያ የስርዓቱ ጤንነት እንደ መፈተሻ ሊጠቅሙን እሚችሉ ስራዎች መለየት፣ በሁለተኛ ደረጃ የስራዎቹ ስኬታማ አፈፃፀም ሊያመላክቱ እሚችሉ መመዘኛ ወይም መለክያዎችን ማበጀት፣ በሶስተኛ ደረጃ ያስቀመጥነዉን መለክያ መሰረት አድርገን ሪፖርት እምናቀርብበት ስርአት መገንባት፣ በመጨረሻም ተሰሩ የተባሉትን ስራዎች በተጨባጭ መስራታቸዉን (መሬት ላይ መኖራቸዉን) ቀድመን ካዘጋጀነው መለክያ ወይም መመዘኛ አንፃር ምን እንደሚመስሉ መገምገም ነው ይለናል። (2013).

የግለሰብ ስብእና የፓርቲ ስብእና እና ለመረጠው ተቛም ያለው ስብእና ተፃራሪ ሊሆን ይችላሉ። በቀጣይ ዉጥረትም ይኖራሉ። ለምሳሌ በተወካዮች ምክር ቤት ብንወስድ ከህገ መንግስታዊ ግዴታ ስንነሳ በአንድ በኩል ለህሊናው መቆም አለበት ይላል፤ በሌላ በኩል ለህገ መንግስቱ ይላል፤ በተጨማሪም የፓርቲ አደረጃጀት አባሉ ለፓርቲው ማሳየት ያለበት ስብእና አለ። በነዚህ ሶስት መሃል ያለው ቅራኔ አፈታት ዴሞክራሲዉን ወደፊት ወይም ወደሃላ ሊያስቀጥለው ይችላል። በአንድ በኩል ያለምንም ጥያቄ ለፓርቲ አቛም ድምፅ መስጠት አማራጭ ሃሳቦችን ያቐጭጫል፤ በሌላ መንገድ እያንዳንዱ የመሰለዉን ብቻ ከወሰነ ተደራጅቶ መታገልን ዉድቅ ያደርጋል። ጤናማ ዴሞክራሲ በነዚህ መሃል ያለዉን ዉጥረት አቻችሎ ይሄዳል። አብዛኛው ግዜ ለፓርቲ ዉሳኔ ድምፁን ቢሰጥም ከፓርቲው ወይም ከህገ መንግስታዊ መርሖች ወይም ስብእናው ተነስቶ ሊቃወም ይችላል። እንዲህ ዓይነት አቻቻይ ስርዓት ሲዘረጋ ጤናማ ዴሞክራሲ በተቛማት አለ ሊባል ይችላል።

የማዂዋየር መዝገበ ቃላት ስብእና ማለት የሞራል መርሆች እና ባህሪዎች ጥንካሬ፣ ቀናነት እና ቅንነት ነው ይላል። ሙሉ እና ሳያንሱ መገኘት ወይም አለመታወር ነው ይላል።. እያንዳንዱ ተቛም ስብእናዉን ጠብቆ የተጣለበትን ሃላፊነት መወጣት እና መብቶቹን ባግባቡ መጠቀም እሚችልበት ድባብ መፍጠር ቁልፍ መፍትሄ ነው። መንግስት የተቛማቱን ተገቢ ስብእና እሚጠብቁ እርምጃዎች እያከበረ የዴሞክራታይዜሽን ሃይል መሆን ገንቢው አማራጩ ሲሆን ይህን ችላ ካለ ግን መሃል ላይ መስፈር ብሎ ነገር ስለማይኖር የኢ-ዴሞክራታይዜሽን ሃይል ነው ሊሆን እሚችለው።

ያለን ህገ መንግስት በጥብቅ ተግባራዊ ማድረግ ዋናው መፍትሄ ነው፤ ይህን ለማድረግ ህገ መንግስቱ በጥብቅ ተግባራዊ ሲሆን ለበሽታዎቻችን መፍትሄ ማግኘት እንደሚቻል እሚያምን ቁርጠኛ አመራር ያስፈልጋል፡፡ ይህ ማለት የህግ አስፈፃሚው አካል ቁርጠኝነት በጣም ያስፈልጋል ማለት ነው። ቀደም ብሎ በተጠቀሰው የኢህአዴግ ፅሁፍ የሚከተለውን ሰፍሮ እናገኛለን፡፡ “የህግ አስፈፃመሚ አካል የህግ የበላይት ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስፈልጉ እንደ ፖሊሲና የመከላከያ ሃይል ያሉ ተቋሞችን የሚቆጣጠር በመሆኑ ለዴሞክራያዊ ስርዓት ግንባታው ታማኝ ካልሆነ የዴሞክራሲ ተቋሞችን አፈራርሶ ስርአቱን ለአደጋ ሊያጋልጠው ይችላል፡፡ በተግባርም የዴሞክራሲ ስርአትን የመፈታተን አደጋ የሚመነጨው በአብዛኛው ከህግ አስፈፃሚው አካል ነው” ይላል በገጽ 70 ላይ፡፡

ስለዚህ ህገ መንግስት በጥብቅ ተግባራዊ ማድረግ ማለት ህገ መንግስታዊነት በተግባር ማረጋገጥ እና ለሁሉም ዘላቂ ዋስትና መሆን የሚችል ህገ መንግስታዊ ዴሞክራሲያዊ ስርአት መገንባት ማለት ነው፡፡ ይህ ሲሆን ብቻ ነው አንድ ህገ መንግስት ትርጉም እና አርባና የሚኖረው፡፡

አገራዊ እና መንግስታዊ መዋቅሮች ከፓርቲ ተፅዕኖ አንፃራዊ ነፃነት እንዲኖራቸው ማስቻል፡፡ አንዱ የዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ ምሰሶ የሆነው የተቋማት እርስ በርስ የመቆጣጠር እና ሚዛን የመጠበቅ ነው፡፡ ይህን እውን ለማድረግ የሚቻለው ደግሞ የመንግስት፣ የፓርቲ እና አገራዊ የሆኑትን ተቋማት ተገቢ ድንበራቸው ጠብቀው በተለይ ከፓርቲ መዋቅር ተነፃፃሪ ነፃነት ሲያገኝ ነው፡፡ ፓርቲ መንግስታዊ እና አገራዊ ተቋማትን በብቸኝነት ሲቆጣጠር በእኩልነት የተመሰረተ የምርጫ ውድድር አይኖርም በዚህም ምክንያት የህዝብ መሰረታዊ ዴሞክራያዊ እና ህገ መንግስታዊ መብቱ ይጣሳል፡፡ ይህ አንድ ምሳሌ ነው፡፡ በተጨማሪም ፓርቲ፣ መንግስት እና ቋሚ አገራዊ ተቋማት አንድ እና አንድ ሆነው የፓርቲው መሳርያ ከሆኑ፣ በፓርቲው ውስጥ የሚከሰቱ ችግሮች ባጭር ግዜና በቀጥታ ወደ መንግስታዊ እና አገራዊ ተቋማት ተዛምተው መላ አገሪትዋን ሊበታትን የሚችል ክፍተት እና ተጋላጭነት ሊያስከትል ስለሚችል ጉዳቱ በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡ ይሄም ለዴሞክራያዊ ስርዓት ግንባታ እንቅፋት ይሆናል፡፡

ሎርድ አክተን የሚባል ሰውዬ “Power corrupts, and absolute power corrupts absolutely” ይላል፡፡ የፓርቲ መዋቅር የመንግስት እና አገራዊ ተቋማትን ነፃነት ነፍጎ የግሉ ካደረገ ፍፁማዊ ሃይል ሆኖ ለቁጥጥር እሚያስቸግር ፈላጭ ቆራጭ የሆነ ፀረ ዴሞክራሲያዊ አስፈፃሚ ነው እሚሆነው፡፡ በዚህ እና በብዙ ሌሎች ምክንያቶች ምክንያት ነው የመንግስት እና አገራዊ ተቋማት ከፓርቲ መዋቅር አንፃራዊ ነፃነት ያስፈልጋቸዋል የምንለው፡፡ከስር እምታዮት ምስል በዴሞክራስያዊ አስተዳደር ተቛማት እና ሂደቶች፣ የነዚህ ጥራት እና ጥራቱ ላይ ተፅእኖ እሚያሳድሩ አላባውያን መሃል ያለው ግንኙነት እሚያሳይ ሞዴል ነው። በተለይ የቡዙሓነት ፀጋ በተጎናፀፉት እንደኛ ያሉ ታዳጊ አገሮች የሚገኙ የዴሞክራሲ ተቛማት በህዝቦች መሃል ሊገኝ የሚችለዉን የተለያዩ ፍላጎቶች እና እሴቶችን መሰረት አድርገው መንቀሳቀስ ይኖርባቸዋል።

Diagram two

የአስተዳደር ይዘት እና ጥራት ላይ ተፅእኖ እሚያሳድሩ ዓዉዳዊ አላባውያን የሚለው፤ የተለያየ ማንነት ያላቸው የብሄር፣ በሄረሰብ፣ሃይማኖት፣የፆታ እና ሌሎች የማንነት ጥያቄዎች ሊያነሱ የሚችሉ ጉዳዮች ስርዓቱ እንዴት ያቻችላል (Accommodate ያደርጋል) የሚለዉን ማየት ጠቃሚ ነው። በተለይ የተለያዩ ቁሳዊ ፍላጎቶች እና የእሴት ጥያቄዎች ባለበት እነዚህ ሃይሎች ፍላጎታቸውን እና እሴቶቻቸዉን ማራመድ የሚችሉበት ድባብ መፈጠር አለበት። ሃሳባቸዉን ሳይሸማቀቁ መግለፅ መቻል አለባቸው፤ ይህ እንዲሆን የዴሞክራሲ መስተዳድር መኖር እና ዉጤታማ ተቓሞችና ሂደቶች በስምነቱ ባህርያት መለካት ያስፈልጋቸዋል:: ሃሳባቸዉን ሳይሸማቀቁ መግለፅ መቻል አለባቸው፤ ጠባብ፣ ትምክህተኛ፣ አክራሪ ተብለው ሳይፈረጁ። ጠባብነት፣ ትምክህት እና አክራሪነት ቢኖርም እኚህ ታርጋዎች እሚለጠፉት የማስረዳት አቅም ሲታጣ እንደሆነ እየተገነዘብን ነው።

ጠባብነት፣ ትምክህተኝነት እና አክራሪነት እንዲያብቡ እና ጉልበት አግኝተው የስጋት ምንጭ ሊሆኑ እሚችሉት መልካም አስተዳደር ሲጠፋ እና ፍት ሃዊ ልማት ማረጋገጥ ሳይቻል ሲቀር ነው። አሳታፊ፣ ግልፅ፣ ተጠያቂነት ያለው ለሚነሱ ጥያቄዎች ባፋጣኝ መልስ መስጠት የሚችል ብቁ እና ቀልጣፋ አስተዳደር ካለ ጠባብነት፣ ትምክህተኝነት እና አክራሪነት ሊፋፉበት እሚችሉበት እድል ስለሚዘጋ የስጋት ምንጭ አይሆኑም። ስለዚ ለጠባብነት፣ ትምክህተኝነት እና አክራሪነት ምቹ ሁኔታ የሚፈጥረው የቀጨጨ የዴሞክራሲ ሁኔታ ስለሆነ እነዚህ ችግሮች ማስወገድ ካለብን ምንጫቸው የቀጨጨ ዴሞክራስያዊ ሁኔታ መሆኑ መገንዘብ አለብን። መሰረታዊ ምንጩ ሳይገባን ችግራችን ጠባብነት፣ ትምክህተኝነት እና አክራሪነት ነው ማለት ግን አጠቃላይ ሁኔታው እንዳለመረዳት ይቆጠራል።

5.2 ምክር ቤቶች የዴሞክራስያዊ እንቕስቃስያችን ወሳኝ አምዶች ናቸው

በኢፌድሪ ህገ መንግስት አንቀጽ 8 መሰረት የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦች የኢትዮጵያ ሉዓላዊ የስልጣን ባለቤቶች ናቸው ይላል፡፡ በዚህው አንቀጽ ንኡስ አንቀጽ 3 መሰረትም “ሉዓላዊነታቸውም የሚገልፀው በዚህ ሕገ መንግስት መሰረት በሚመርጧቸው ተወካዮቻቸውና በቀጥታ በሚያዳርጉት ተሳትፎ አማካይነት ይሆናል” ይላል፡፡ ህዝቦች የሚወከሉባቸው ምክር ቤቶች (በየደረጃው ያሉት) መንግስት ወይም አስፈፃሚው አካል በሚያከናውናቸው ተግባራት ዙርያ ይወያያሉ፣ ይራከራሉ፣ ቁጥጥር ያደርጋሉ፣ የተሰራውን ለህዝብ ያስተውቃሉ፣ የህዝብን አስተያየት እና ፍላጎት ላስፈፃሚ ያደርሳሉ፣ እንዲሁም አስፈፃሚው አካል ገቢ እሚሰበሰብበትን እና ስራ ላይ እሚያውልበትን አግባብ አሳይተው ተግባሩ እንዲያከናውን ስልጣን ይሰጣሉ፡፡ ይህንን ትልቅ ሃላፊነት ከሚወጡበት የአሰራር አይነቶች ደግሞ መንግስት በሚያቀርባቸው ረቂቆች ላይ ተወያይቶ መወሰን፣ የጥያቄ /ተጠየቅ መድረኮችን ማሰናዳት እና ቋሚ ኮሚቴዎችን አቋቁሞ ክትትል እና ቁጥጥር ማድረግ ነው፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞ በነሐሴ 1992 ዓ.ም “የዴሞክራሲ መሰረታዊ ጥያቄዎች በኢትዮጵያ” በሚል ርዕሰ ለውይይት በቀረበው የኢህአዴግ ፅሁፍ ላይ የሚከተለው ሰፍሮ እናገኛለን “አብዮታዊ ዴሞክራሲ ይህ (የህግ የበላይነት መርህ) በተሞላ መልክ ሊተገበር የሚችለው ከግልፅነትና ከተጠያቂነት ጋር ተዛምዶ መፈፀም ሲችል ነው የሚል እምነት አለው:: ግልፅነት ሲባል በየደረጃው ያሉ የመንግስት ሃላፊዎች የሚወሰንዎቸው ውሳኔዎች ምን እንደሆኑ፣ በየትኛው አግባብ እንደሚወሰኑ፣ ለምን እንደሚወሰኑ፣ ውጤቱ ምን እንደሆነ ግልፅ መሆን አለባቸው መደበቅ የለባቸውም ማለት ነው” (1992፡42) ይላል፡፡ ባጭሩ ተጠያቂነት በሌለበት የህግ የበላይነት በተሟላ መልክ ለመተግበር አይቻልም ይላል፡፡ ይህ ሰነድ አስከትሎም አብዮታዊ ዴሞክራሲ ህዝቡ ተወካዮችን እንዲመርጥ ብቻ ሳይሆን በሚገባ የሚቆጣጠርበት አሰራርም ይከተላል …. በዚህ መስክ አብዮታዊ ዴሞክራሲ የሚከተለው አሰራር ሊበራል ዴሞክራሲን መድረስ ወደሚችለው ከፍተኛ ጫፉ የሚያደርሰስና ህዝባዊ ባህሪ እንዲኖረው የሚያደርግ ነው” (1992፡62) ይላል።

መሪው ድርጅት ኢህአዴግ የምክር ቤቶችን የበላይነት አስመልክቶ ቅድም በተጠቀሰው ፅሁፍ እንዲህ ይላል “አብዮታዊ ዴሞክራሲ በህዝብ የተመረጡ ምክር ቤቶች ብቸኛ ህጋዊ የሆኑ ወሳኝ አካላት መሆናቸውንና በዚህ መንፈስ መስራት ያለባቸው መሆናቸውን ይቀበላል” (1992፡63) ይላል። አያይዞም ህዝቡ ምን እንደተወሰነ ብቻ ሳይሆን በማንና ለምን እንደተወሰነም ሊያውቅና ሊከታተል ይገባል፡፡

5.2.1 ህገ መንግስታችን እና የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት

የኢፌድሪ ህገ መንግስት አንቀጽ 50/3 ላይ የፌዴራል መንግስት ከፍተኛ የስልጣን አካል የፌዴራሉ መንግስት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነው፡፡ ተጠሪነቱም ለሀገሪቱ ህዝብ ነው፤ የክልል ከፍተኛ የስልጣን አካል የክልሉ ምክር ቤት ነው፤ ተጠሪነቱም ለወከለው ክልል ህዝብ ነው ይላል፤ ቀደም ብለን እንደጠቀስነው ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግም ህገ መንግስታዊ ድንጋጌውን እንደሚቀበል አይተናል፡፡ ህገ መንግስቱ አስከትሎም የምክር ቤቱ አባላት የመላው ህዝብ ተወካዮች ናቸው፡፡ ተገዥታቸውም፤

ሀ. ለሕገ መንግስቱ

ለ. ለሕዝቡ እና

ሐ. ለሕሊናቸው ብቻ ይሆናል” ይላል።

በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 55 መሠረትየሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሰፋ ያለ ሥልጣንና ተግባር የተሰጠው ሲሆን፤ በአንቀፅ 72/2 መሰረት ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትሩና ካቢንያቸው ተጠሪነነታቸው ለተወካዮች ምክር ቤት መሆኑ ይደነግጋል። በማስታወቅያ ሚኒስቴር ፕሬስና ኦድዮቪዥዋል መምርያ በ 1994 ዓ.ም በታተመው “በኢትዮጵያ የዴሞክራስያዊ ስርአት ግንባታ” እሚለው ፁሁፍ ላይ የሚከተለዉን ሰፍሮ እናገኛለን። “ምክር ቤቶች የህዝቡ ሉአላዊነት መገለጫ የዴሞክራስያዊ አስተዳደር እምብርትና የዴሞክራስያዊ አገዛዝ አዉራ ተቛሞች ናቸው። ሌሎች የዴሞክራስያዊ አገዛዝ ተቛሞች እና ድርጅቶች የሚመሰረቱት በምክር ቤቶቹና ምክር ቤቶቹ በሚስርዋቸው ስራዎች ላይ ነው። በመሆኑም የነዚህ ምክርቤቶች መቛቛምና መጠናከር ለዴሞክራስያዊ ስርአታችን መጠናከር ወሳኝ ነው።” (ገፅ, 58-59)

5.2.2 የተወካዮች ምክርቤት ዓይነቶች

ዊልያም ሮቢንሰን እና ኔልሰን ፖልስፐይ በዓለም ላይ ያሉ የተወካዮች ምክር ቤቶችን በአራት ይከፍላዋቸዋል። እነዚህም፡- A. Transformative Legislature; B. Arena Legislatures; C. Emerging Legislatures; D. Rubber Stamp Legislature በማለት ይዘርዝርዋቸዋል።

1.Rubber Stamp Legislature

ማህተም መቺ ምክርቤቶች (Rubber Stamp Legislature) በጣም ቀላል የምክርቤት አይነቶች ናቸው። እነዚህ ምክርቤቶች ሌላ ቦታ የተወሰነን ዉሳኔን ማፅደቅ ነው ስራቸው። የዚህ ዓይነት ምክር ቤቶች ዓይነተኛ ምሳሌዎች በአምባገነን መንግስታት ስር የሚገኙ ምክርቤቶች ሲሆኑ የስራ አስፈፃሚው ዉሳኔዎችን ሳያንገራግሩ ለይምሰል ከማፀደቅ ያለፈ ሚና የላቸዉም። እንዲህ አይነት ምክር ቤቶች ኢ-ዴሞክራስያዊ በሆኑ አገሮች ብቻ እሚገኝ አይደለም ይላሉ አጥኚዎቹ። ለምሳሌ ባደጉ አገራት እሚገኙ የሰራተኞች ህብረት ምክርቤቶች የመሪዎቻቸዉን ዉሳኔ ለማፅደቅ ነው እሚሰበሰቡት ብለው እንደ አብነት ይጠቅሱታል። ዓይነተኛ አብነት ተድርጎ እሚወሰደው ደግሞ የ ቀደሞው ሶቭየት ህብረት ምክር ቤት ነው።

2.Arena Legislatures

እንዲህ አይነት ምክርቤቶች ደግሞ በማህበረሰቡ ዉስጥ ያሉ የተለያዩ ሃሳቦች እሚወከሉበት እና ተናጋሪ እሚያገኙበት ዓይነት ምክር ቤት ነው። ሞቅ ያለ የፖሊሲ ክርክር እና መንግስትን በተለያየ መለክያ መገምገም እሚችል ዓይነት ፓርላማ ነው። ዓይነተኛ አብነት ተድርጎ እሚወሰደው ደግሞ የኢንግሊዝ የታችኛው ምክር ቤት (House of commons) ነው። እንዲህ ዓይነት ምክርቤቶች በማህበረሰቡ ያሉ የተለያዩ ፍላጎቶች መወከል ስለሚያስችሉ ነው እንዲህ ተደርገው እሚተገበሩት። ስለዚ ዋና ስራቸው በጉዳዮች ዘርያ መከራከር እና ከተለያየ አቅጣጫ ግምገማ ማካሄድ ነው። ስለዚ እንዲህ ዓይነት ምክር ቤቶች ስራቸዉን በአግባቡ ማከናወን እሚያስችላቸው ዉስጣዊ አደረጃጀት እና አሰራር ያስፈልጋቸዋል።

3. Emerging legislatures

እንዲህ ዓይነት ምክርቤቶች በሽግግር ወቅት እሚፈጠሩ ዓይነት ምክርቤቶች ናቸው። በዚህ አዃሃን የተለመደው መንገድ ብዙ ዉስጣዊ መዋቅር እና አቅም ሳይኖረው ማህበረሰቡን በመምራት ረገድ የራሱን አስተዋፅኦ ለማድረግ እሚሞክር የምክር ቤት ዓይነት ነው። የቦሊቭያው እና በርከት ያሉ የላቲን አሜሪካ እንዲሁም የቀደሞ ሶቭየት ህብረት አባል ሃገራት የነበሩ ምክርቤቶች የዚህ ዓይነት ምክር ቤት ተጠቃሽ አብነቶች ናቸው። በቅርቡ ሜክሲኮ ላይ እየታየ ያለ ከ አንድ ፓርቲ የበላይነት በዉድ ድር ወደሚመሰረት ስርዓት የሚደረገው ሽግግርም የምክርቤቱን አቅም እሚገነባ እና ከአስፈፃሚው ጥገኝነት እሚያላቅቀው ነው ይላሉ አጥኒዎቹ።

4. Transformative legislatures

ይህ ዓይነት ምክርቤት ደግሞ ብርቅየና እምብዛም እማይገኝ የምክርቤት ዓይነት ነው ይሉታል። እንዲህ ዓይነት ምክር ቤቶች የዉክልና ዓቅማቸዉም የማህበረሰቡን ፍላጎት ቅርፅ ማስያዙንም የሚችል ዓይነት ምክር ቤቶች ናቸው። ባጭሩ እንዲህ አይነት ምክርቤቶች የዉክልና ባህሪያቸው እንደተጠበቀ ሆኖ መምራት ላይም ይሳተፋሉ። ይህ ለምድረግ እንዲህ ዓይነት ምክር ቤቶች ስራቸዉን ባግባቡ ለማከናወን እሚያስችል ዉስጣዊ መዋቅር እና ግጭቶችንና ልዮነቶችን እሚያስተናግዱበት አሰራር ይፈልጋል። የአሬናው ዓይነት ምክርቤት ባካባቢው ያለዉን ሙቀት እንደሚለካ ቴርሞሜትር ሲሆን የ ትራንስፎርማቲቩ ምክርቤት ደግሞ አካባቢው ላይ ምን ያህል ሙቀት መኖር አለበት ብሎ እንደሚወስን ተርሞስታት ነው ይላል። እንደኔ እምነት የአሜሪካው ምክርቤት ለሰርዓቱ የቆመ ምክርቤት እና ዉግንናው ከጭቁኖች ያልሆነ መዋቅር ስለሆነ ትራንስፎርማቲቭ እሚሆነው ስርዓቱን ለመጠበቅ እና የዋና ፖለቲካዊ ተዋንያንን ጥቅም ለማስከበር የቆመ መዋቅር ነው እላለሁ።

5.2.3 የተወካዮች ምክር ቤት እውነተኛ ገፅታ

የኢትዮጵያ ምክርቤት በ Emerging እና በ Rubber Stamp መሃል እሚገኝ፤ አስፈላጊ መሰረታዊ ለውጥ ከተደረገለት ተገቢ ሚናዉን መጫወት እሚችል ምክርቤት ነው ያለን። ተወካዮች ምክር ቤት ከላይ በህገ መንግስቱ እንደተዘረዘረው ግዴታዉ እየተውጣ ነዉ የሚለዉ ለመመለስ መዋቅራዊ መነሻዉ ማጥናት ተገቢ ነዉ፡፡ መንግስትና ገዢ ፓርቲ አንድ እና አንድ ሆነዉ የማይለዩበት በሆኑበት ምክር ቤት አባላት አንድ የሚታይ ዉጥረት ነዉ፡፡

ይሄ ውጥረት በተወካዮች ህሊና፣ ለወከሉት ማህበረሰብ እና ለህገ መንግስቱ ባላቸው ታማኝነት፣ ለፓርቲ ማስመስከር በሚገባቸው ታማኝት እና የኑሮ ጉዳይ በሚፈጥረው ግፊት ምክንያት የሚፈጠር ውጥረት ነው፡፡ ባጭሩ ሲገቡ በሚፈፅሙት መሃላ እና የፓርትያቸው ዲሲፒሊናዊ አሰራር እና ኑሮ መሃከል የሚከሰት ውጥረት ነው፡፡ ይህ ነው ስብእናዎችን ሚዛናዊ በሆነ መልኩ አቻችሎ አለመሄድ እሚያስከትለው መዘዝ። እዚህ ላይ ልብ ማለት ያለበን ጉዳይ መንግስት ዋና ኢንቨስተር መሆኑን ብቻ ሳይሆን የElected dictatorship”ም አለማዊ እውነታ መሆኑ ነው፡፡

ከዚህ ተነስተን ፓርላማው ባለፈው የGTP1 ዘመን በኢኮኖሚ አድገቱ እና በዴሞክራሲ ዙሪያ ምን ሚና ነበረው? ስንል የሚሰጠን ምስል ደብዛዛ ነው፡፡ በተመዘገበው የኢኮኖሚ እድገት አወንታዊ ሚና ነበረው አልነበረዉም ብሎ አስተያየት ከመስጠት በፊት፤ በመጀመርያ ምክር ቤቱ አሳታፊ፣ ግልፅነት እና ተጠያቂነት የነበረው አሰራር ነበረው ውይ? ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው። እኔ እስከማውቀው ድረስ ከአስፈፃሚው የመጣዉን አዋጅ/ሹመት ወይም ሌላ ነገር ምክርቤቱ ተገቢ ከመሰለው ሳይቀበል ቀርቶ reject ሲያደርግ፤ መስተካከል ካለበት ማስተካከያ እንዲደረግ መልሶ ወደ ስራ አስፈፃሚወ ልከዋል የሚል በመገናኛ ብዙሃን የሰማሁበት ግዜ አላስታዉስም። ህዝቦች የማወቅ መብት እና ምክር ቤቱ የማሳውቅ ግድታ እነዳላቸው ልብ ይሏል::

ሁልግዜ የምንሰማዉ በሙሉ ወይም በአብላጫ ድምፅ ፀደቀ ሲባል ነው። ከቅርብ ግዜ ወዲህ አስፈፃሚዉን የመቆጣጠር አዝማምያ ቢኖርም ወጥነት የሌለው እና የተቆራረጠ ነገር ነው።ባጠቃላይ ሲታይ ምክር ቤቱ የመጣለትን የየዉሳኔ ሀሳብ ሲቅረብ ለዝረዝር እይታ ወደ እሚመለከተው ኮሚቴ መስተላለፍ እና የህዝብ ድምፅ የሚስማበተ መድርክ ማዝጋጀት እንደ ጥሩ አስራር ሊወሰድ የሚችል ሆኖ ድመፁ መከብሩን ግን የምናዉቅበት መንገድ የለም። የምክር ቤት አባሎች ለህገ-መንገሰቱ ና ለህሊናቸው ተገዥ መሆንና የመረጣቸው ህዝብና የፓርቲያቸው መመረያ በሚጋጭበት ሁኔታ የሚከተሉት አቅጣጨ ምን እንደሆነ የሚታወቅበት ሁኔታ የለም፡፡ እንደ ተቛም እለይ በተቀመጡት መስፍርቶች ሲመዘንም መልሱ ያው ነው፡፡እጅ እያወጡ ከማፅደቅ የዘለለ ከፍተኛ ትርጉም ያለው ሚና ነበረው ለማለት ያስቸግራል፡፡ በቅርብ ግዜ ት ዝታችን የተባበሩት የአሜሪካ መንግስታት ኮንግሬስ የኢራን ኑክሌር ስምምነት እነ እከሌ የሚባሉት ዴሞክራቶች ተቃወሙት ሲባል እንስማልን፡፡ የተባበሩት ኪነግደም ገዢው ኮነስረቫቲቭ ፓርቲ አውሮፓ ሕብረት ሪፈረነደም አካሄድ እሚመለከት የቀረበው የውሳኔ ሃሳብ የተወሰኑ አባሎቹ ስላልደገፉት ውድቅ ሆነ እነስማልን ወ.ዘ.ተ። እኛ አገር ዝምታ ነው ምናወቀው ነገር የለም:: የመረጥነዉን ወኪል እምንመዝንበት መረጃ የለንም፤ ለፓርቲ ነው የመረጣቹሁት ካልተባለን በስተቀር!! ድበቅነት በዛ ከልክ ያለፈ ሆነ!!!

ከዴሞክራሲ አኳያ ፓርላማው በ GTP 1 የነበረው ሚና ካነሳን ግን ምንም ሚና አልነበረውም ለማለት ያስደፍራል፡፡ እጅግ ብዙ ችግሮች እያሉ ሁሉም ነገር ሰላም እንደሆነ በሚያስመስል መልኩ “ዝምተኛ” ሆኖ አልፎታል፡፡ ፍትህ ሲጠፋ፣ ዜጎች ሲበደሉ፣ አስፃሚውን ደፍሮ የታገለበት አግባብ ስላልነበረ በዚህ ረገድ “የሉዓላዊ የስልጣን ባለቤትነቱ” ሳያረጋግጥ እንዳለፈ ይቆጠራል፡፡

የህዝቡ ተወካዮች ምክር ቤት የመረጣቸውን መራጭ ህዝብ ንቁና ቀጣይነት ያለው ተሳትፎ እሚያደርጉበትን ሁኔታ ማመቻቸት አለበት፡፡ አሁን ባብዛኛው እንደምታዘበው የመራጭ ህዝብ እና የተመራጭ ግለሰብ ግንኙነት ጎልቶ የሚታየው በምርጫ ሰአት ግዜ ነው፡፡ መራጮች ተወካዮውን በቀጣይነት እያገኝ ወቅታዊ ሁኔታቸውን ፍላጎታቸውንና ስጋቶቻቸውን እሚያስረዱበት አሰራር እና ሁኔታ መፈጠር ተገቢ ነው፡፡ ሲጀምር የህዝብ ተወካዮች እንደመሆናቸው መጠን የህዝቡን የልብ ትርታ ተቋማዊ በሆነ መልኩ በቀጣይነት እንዲገነዘቡ መራጩ ህዝብ ለተሳትፎ እና ቁጥጥር እሚመች ሁናቴ ማግኘት መቻል አለበት፡፡ አለበለዝያ በየአምስት አመቱ ምርጫ በመጣ ቁጥር ብቻ እየተገናኘ ትክክለኛ የመራጩን ህዝብ ተወካይ ናቸው ለማለት ያስቸግራል፡፡

ያገሪትዋን ከፍተኛ ስልጣን በህገ መንግስት የተረጋገጠለት ተቋም አሁን ያሉት አማራጮች ሁለት ናቸው፡፡ አንደኛው አማራጭ ህገ መንግስታዊ ስልጣኑን ተጠቅሞ የዜጎችን ጥቅም ማስከበር ሁለተኛው አማራጭ ህገ መንግስታዊ ስልጣኑን መጠቀም እማይቻል እና የህዝባችን አደራ መሸከም ካልቻለ ያገሪትዋን ሃብት ያላግባብ ከሚባክን ህዝበ ውሳኔ አዘጋጅቶ አይረቤነቱን ህጋዊ ድጋፍ ሰጥቶ ተቋሙን ማፍረስ፡፡ ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መንግስትነት ነው እሚከተለው በሚል ሃገር በልማቱም በዴሞክራሲውም ላይ የጎላ ሚና መጫወት እማይችል ፓርላማ ትርፉ ሃብትን፣ ጉልበትን እና ግዜን ማባከን ነው፤ በዚህ ምክንያትም ነው “እውን ኢትዮጵያ ፓርላማ አላትን?” ብለው ብዙዎች የሚጠይቁት፡፡ ምክርቤቱ ህገ መንግስታዊ ሃላፊነቱ እየተወጣ መሆን ያለበትን እየሆነ ከሄደ የዴሞክራታይዜሽን ሃይል መሆኑ አይቀርም፤ ይህን ችላ ካለ ግን መሃል ላይ መስፈር ብሎ ነገር ስለማይኖር ሃብት አባካኝ ተቛም ከመሆን አልፎ የኢ-ዴሞክራታይዜሽን ሃይል ነው ሊሆን እሚችለው።

የኢትዮጵያ መንግስት በ 1994 ዓ.ም ባሳተመው ፁሁፍ ላይ የሚከተለዉን ይላል “በመጀመርያ መቀመጥ ያለብት ችግር የአባላቱ (የምክር ቤቱ) ብቃት ነው። የምክር ቤቶቹ ስልጣንና ተግባር ምን ያህል ሰፊና ወሳኝ እንደሆነ፤ ምክር ቤቶቹ ሃላፊነታቸዉን በሚገባ መወጣታቸው ለዴሞክራስያዊ ስርአታችን ማበብ ምን ያህል ወሳኝ እንደሆነ በመገንዘብ ረገድ በምክር ቤት አባላትም ሆነ በሌላው የህብረተሰብ ክፍል፣ በየደረጃው ባሉ የህግ አስፈፃሚ አካላት ወዘተ በቂ ግንዛቤ የተያዘበት ጉዳይ አይደለም።” አሁንስ ከ 14 ዓመት በኃላ የተለየ ሁኔታ አለ ወይ? ለዚህም ነው ተቛማቱ ስለ ተግባር እና ሃላፊነታቸው ጠንከር ያለ ግምገማ እና ራስን መፈተሽ አስፈላጊ ሆኖ የሚገኝው።

5.3 የመገናኛ ብዙሃን

የመገናኛ ብዙሃን በመንግሰት፤ በድርጅት እና የግል በሚል ለያይቶ ማየት ይበጃል:: የመገናኛ ብዙሃን ህዝቡን ለልማት ባመዘጋጀት እና በማንቀሳቀስ እንዲሁም ዴሞክራሲያዊ ከባቢው እንዲሰፋ እና እንዲጠናከር የሚጨወቱት ሚና ላቅ ያለ ነው፡፡ በህዝብ እና በመንግስት መሃል ክፍተት እንዳይሰፋ፣ መንግስትም የህብዝን ነባራዊ ችግር ለመገንዘብ እሚረዳው መረጃ እሚያገኝበት፣ ህዝብም መንግስት እያደረገ ስላለው እንቅስቃ እሚገነዘብበት መሳርያ ነው ሚድያ፡፡ ከህግ አውጪው፣ ህግ ተርጓሚው እና ህግ አስፈፃሚው አካል ጎን ለጎን አራተኛው አምድ እየተባለ እሚጠቀሰው ሚድያ በመንግስት አሰራር ግልፅነት፣ ተጠያቂነት፣ ፍትሕ፣ ህገ መንስታዊ ሚዛን እንዲኖር ከፍተኛ ሚና ይጫወታል፡፡ እንዳለመታደል ሆኖ በሃገራችን ትላልቅ የሚድያ ተቋማት በመንግስት ስር ያሉ የመገናኛ ብዙሃን ናቸው፡፡

እነዚህስ ቢሆኑ ከልማት እና ከዴሞክራሲ አኳያ የነበራቸው ሚና ምን ይመስላል? በኢኮኖሚያዊ ልማቱ ዙሪያ ምልአተ ህዝቡን በሚፈለገው መንገድ አንቅተዋል፣ ተአማኒ ሆነው ህዝብን አንቀሳቅሰዋል ለማለት ቢከብድም የተወሰነም ቢሆን አስተዋፅኦ ነበረው ማለት ይቻላል፡፡ ከዴሞክራሲ አኳያ ግን ሚናቸው አግላይ ነበር፡፡ እነዚህ “የህዝብ” መገናኛ ብዙሃን ከፓርቲ የፕሮፓጋንዳ መሳርያነት ያለፈ ማንነት መላበስ ሳይችሉ ስልጣን ላይ ያለውን ግንባር በግልፅ አድልዎ እያገለገሉ GTP 1ን ጨርሰውታል::

በልማቱ ዙርያ ፈጠራ በታከለበት መንገድ ምልአተ ህዝቡን በሚፈልገው መንገድ አንቅቷል፣ ተአማኒ ሆነው ህዝቡን አንቀሳቅሷል ለማለት ሙሉ ለሙሉ ቢከብድም አስተዋፅአቸው ቀላል ሊባል አይችልም። ሆኖም ከላይ ወደ ታች በሚፈስ የድጋፍ ማሰባሰብና አፅድቅልኝ ስራ ካልሆነ ህዝቡ መስማት እና መደገፍ ብቻ ሳይሆን በአገሪቱ ልማት አስተያየት እየሰጠ፣ እያስተካከለ፣ እየጨመረ ልማቱን የሚያሳልጥበት፤ መንግስትም ግብረ መልስ (feedback) የሚያገኝበት ከታች ወደላይ የሚንሸራሸር ሓቀኛ እንቅስቃሴ አልነበረም ማለት ነው።

ከዴሞክራሲና መልካም አስተዳደር አዃያ ግን ሚናቸው አሉታዊ ነበር። ህዝቡ በብልሹ አስተዳደር ሲለበለብ የህዝቡ አለኝታ ብሎም የመንግስት አለኝታ ሆነው ችግሩ የሚፈታበትን መንገድ ከመፈለግ ይልቅ አበረታች፣ አመርቂ፣ተስፋ ሰጪ የሚሉ አድበስባሽ ቃላቶችን በመጠቀም የብልሹ አስተዳደር ተባባሪ ሁነዋል። አንዱ እንደሚለው አበረታች፣ አመርቂ፣ተስፋ ሰጪ እና የመሳሰሉት ቃላት የኢህአዴግ ማደንዠዣ ቃላት ከሆኑ ሰነባብቷል።

ከዚህ ባሻገር ብዙሃነትን የተረዱበት መንገድ ጠብብ እና አግላይ ነበር፡፡ ለምሳሌ በቅርቡ የተከበረዉን የዘመን መለወጫ በዓል እንዃን ብንመለከት አቀራረቡ እና የፕሮግራሙ ይዘት ቅዱስ ዩሃንስን እና የዘመን መለወጫ በዓልን በማይለይ ጠላ፣ ጠጅና ዶሮ ወጥ ማእከል ያደረገ ከእንዲህ አይነት ባህል እና ልማድ የተለዩት ኢትዮጵያውያንን የማያካትት ሆኖ እናገኘዋለን። ብዙሃነት ሲባል የጭፈራ፣ የመጠጥና እና ያልባሳት ብቻ አድርገው በመቁጠር በተለያዩ የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ያለ የግጭት አፈታት እና የእርቅ ዘይቤዎች፣ የተለያዩ የአስተዳደር መንገዶች፣ ውብ ባህላዊ አደረጃጀቶች እና አገር በቀል እውቀቶች አይዳስሱም፡፡ ስለ መተካካት ሲወራ ከኮንሶው ካራ ወይም ከኦሮሞው ገዳ ከመማር ይልቅ ከዉጭ ብቻ መማር እንደሚገባን እምናስበው የራሳችን አገር በደምብ ስለማናውቅ ጭምር ነው፡፡

አረ ለመሆኑ እንደነ ሪፖተር ያሉ ኃላፊነት የሚሰማቸው ጥቂት የግል ሚዲያዎች ለአመታት የፍትህ ያለህ፣ የመልካም አስተዳደር ያለህ፣ ሙስና በዛ ብለው ሲጮሁ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን፣ አዲስ ዘመን እና ሌሎች የመንግስትና የህዝብ የመገናኛ ብዙሃን የት ነበራችሁ? ዴሞክራሲ ቀጨጨ፣ የጉልበተኞች ዘመን እየሆነ ነው፣ ሰዎች በስልጣን እየባለጉ ነው፣ ፣ ውሃ፣ መብራት እና ስልክ እየተቆራረጠ ነው እያሉ እነ ሪፖተር ሲጮሁ የመንግስት /የህዝብ ሚድያዎች የት ነበሩ? እነ ሪፖተር የህግ የበላይነት ይከበር ዜጎቹ ኑሮ ከበዳቸው ሲሉ የመንግስት ሚድዎችሆይ የት ነበራችሁ? ደግ የሆነውና ያልሆነውን ደግ አድርጎ በማቅረብ ኢትዮጵያ ፍትህ የነገሰባት፣ መልካም አስተዳደር ሞልቶ የተረፈባት ከሙስና የፀዳች አገር አርጋችሁ ስታቀርቡ ግዜ እኔም “እነዚህ ሚድያዎች ውግንናቸው ከማን ጋር ነው ከማለት አልፌ ምን ያህል ጠባብ የዴሞክራሲ ከባቢ የባሰ እያጠበባቹህ እንደሆነ ስታዘብ አዝናለሁ፡፡ የመንግስት ሚድያዎች ምርመራዊ ጋዜጠኝነት እንደ አንድ ዘይቤ በመቁጠር መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን፣ ሙስና እንዲቀንስ እና ፍትህ እንዲነግስ የበኩላቸው አስተዋፅኦ ማበርከት አለባቸው።

እንደኔ ሃሳብ፣ ሚድያዎችን የመንግስት፣ የድርጀት እና የግል ብየ ፈርጄ ትዝብቴን ለመፃፍ ነበር ሃሳቤ። ነገር ግን የድርጅት ሚድያ ላይ ያለኝ ትዝብት ደካማ በመሆኑ የግል እና የመንግስት ሚድያ ማእከል አድርጌ ይህንን ፅሁፋ በማጠቃለል እያለሁ አንዱ ጏደኛየ “ምስጋና ነቲ ተጋዲሉን አጋዲሉን ናብ ዓወት ዘብፀሐና ህዝቢ ትግራይ” (ትርጉም:ምስጋና ታግሎ ላታገለን የትግራይ ህዝብ) በሚል ርእስ በኔ ተፅፎ በብቸኛዋ የትግርኛ መፅሄት ዉራይና ከወራት በፊት የታተመዉን ፅሁፍ መሰረት አድርጎ የተፃፈ ነገር ስላለ እየው ብሎ ላከልኝ። አየሁትም፤ ገና የዉስጥ ይዘቱ ሳላይ ደነገጥኩኝ፤ እዉነት መሆኑ ለማረጋገጥ ደጋግሜ ሳየም ቅዠት አለመሆኑን አረጋገጥኩ :: ይህ ሳይ አንድ ነገር ብለጭ አለብኝ፡፡

በህወሓት ጉባኤ ወቅት የተወሰኑ ጄኔራሎች መቐለ አካባቢ ያንዣብቡ ነበር ብለው አንድ ሁለት እዛ የነበሩ ሰዎች ገለፁልኝ፤ ታድያ ምን አለበት ለራሳቸው ጉዳይ ሂደው ከጉባኤው ጋር ተገጣጥሞ ሊሆን ይችላል አልኳቸው። አንደኛው “አይ ማታ ማታ ከፖለቲካዊ መሪዎች ጋር ይገናኙ ነበር “ አለኝ። እኔም የድሮ ጏደኞቻቸው በአጋጣሚ አግኝተው እየተጫወቱ ይሆናል አልኳቸው። “አይ ብዙ ሰው የተለያየ ትርጉም ነው የሚሰጠው” አሉኝ። በነገሩ ግራ ገባኝ እና አይ ጉባኤዉን በቀጥታ ተፅእኖ እያሳደሩበት ነው እያልክ ከሆነ እንዲህ የሚያደርጉ አይመስለኝም፤ ህገ መንግስቱን ጠንቅቀው ያዉቁታል፤ በኮርት ማርሻል (ወታሃደራዊ ፍርድ ቤት) የሚያስቀጣቸዉና በቀጥታ ከሰራዊት የሚያባርራቸው መሆኑን በሚገባ ስለሚያውቁት አይሞክሩትም አልኩኝ። አይ እኔ እንጃ ብዙም አላውቅም አለኝ::

በሌላ በኩል ግን ብታየዉስ ህወሓት የመከላከያ ጄኔራሎች በፖለቲካው ገብተው እንዲዘባርቁ የምትፈቅድ አይመስለኝም አልኩት። ፖለቲካዊ ትርጉሙ መሰረታዊ ነው። ብዙ አንፀባራቂ ታሪክ ስርታ እዚህ የደረሰች ድርጅት ይህን ከፈቀደች ሞታለች ወይም አንድ እግሯ ጉድጏድ ዉስጥ አስገብታለች ማለት ነው አልኩት። ከሌሎች የአህአዴግ ድርጅቶች ጋር በመሆን መንግስት ተመስሮቶ እንዴ ሌላው ተቛም ፖሊሲ በማውጣት ብቻ ሳይሆን የሲቪል አስፈፃሚው ወታደራዊ ክፍሉን መቆጣጠር የሚያጠናክርበት ሆኖ እያለ እንዴት የተገላቢጦሽ ይሆናል ስል አግራሞቴን ገለፅኩለት። በተጨማሪም የድርጅቱ ሊቀመንበር የጄኔራሎቹ ፖለቲካዊ ጣልቃ ገብነት የሚቀበሉ አይመስለኝም አልኩት፤ ሳዋራው የነበረው ሰዉየም የሊቀመንበሩ አፍቃሪ ስለነበር “ይሄስ እዉነጥን ነው” አለኝ።

ወይን መፅሄት በ ሃምሳኛ እትሙ ህገ መንግስቱን በግላጭ የጣሰና አሁን ተፍጥሮ ያለዉን ህዝባዊ እንቅስቃሴ ለማደናቀፍ ኢ-ዴሞክራስያዊ ሃይሎች ምን ማድረግ እንደሚችሉ እሚያሳይ ደንበኛ ምሳሌ በመሆኑ ስፋ አድረርጌ ለማየት ተገድጅያለሁ። የ “ወይን” ስፖንሰሮች የፌዴራል ሚኒስቴር መስርያ ቤቶች፣ መከላከያ ሚኒስቴር ሳይቀር፣ የአዲስ አበባ ቢሮዎች፣ የዞን ፅህፈት ቤቶች፣ ከትግራይም ከክልል ቢሮዎች እስከ ወረዳ ድረስ ያሉ የመንግስት መዋቅሮች ናቸው። ጥያቄዉም የመንግስት መስርያ ቤቶች የአንድን ፖለቲካዊ ድርጅት ልሳን የሆነን መፅሄት ስፓንሰር ማድረግ ይችላል ወይ? ቢሆንም የግል ድርጅቶች ተጨምረውበት በማስታወቅያ የታጨቀ ሃምሳ ብር የሚሸጥ ሃምሳኛ እትም መፅሄት ነው ሊባል እሚችል ሁኖ አግኝቼዋለሁ።

እነዚህ የመንግስት ተቛሞች የአንድ ፖለቲካዊ ድርጅት ልሳን እንዲደጉሙ ዓቅም እንዲፈጥሩ ሕገ መንግስቱ ወይም ሌሎች ህጎች ይፈቅዳሉ ወይ? በተለይ በህገ መንግስቱ አንቀፅ 87/5 መሰረት ከፖለቲካዊ ወገናዊነት ነፃ በሆነ መንገድ ስራዉን ማከናወን ያለበት መከላከያ ስፖንሰር ሆኖ ማየት አስገራሚ ነው። ዕብሪት ነው!!! መንግስት ከህግ ዉጪ አንድን ፓርቲ መደጎም የለበትም። አይ… ህገ መንግስቱ አይከለክልም ከተባለም እንግዲህ ህጋዊ ሆነው ተመዝግበው እሚንቀሳቀሱ እንደነ የመድረክ፣ የዓረና እና የመኢአድ ልሳኖችን ስፖንሰር ቢያደርጉ ደካማ የፋይናንስ አቅም ስላላቸው ለዴሞክራስያዊ ስርዓት ግንባታ ድጋፍ ይሆን ነበር። ከዲያስፖራ ጥገኝነትም ያላቅቃቸው ነበር።

ወደ ዝርዝር ይዞታው ከመሄዳችን በፊት ግን የኤርትራ ጦርነት በአብዛኛው ትግራይ ዉስጥ የተካሄደ በመሆኑና አገራችንም በድል ብትወጣውም አሁንም ለአስራ አምስት ዓመታት የ No War No Peace ድባብ በሃገር ደረጃ ያለው ተፅእኖ እንዳለ ሆኖ ለትግራይ ህዝብ ግን ጫናው ከፍተኛ ነው። ግንባሩ ያለበትና አብዛኛው ሰራዊትም እዛ ስላለ ትርጉም ከፍተኛ ነው። የኢትዮጵያ ሰራዊት ልጆቹ ስለሆኑ በሙሉ ልቡ ተቀብሎ የሚቻለዉን እያደረገ እንደሆነ ስለማዉቅ የትግራይ ህዝብን ማመስገን ተገቢ ነው። የፌዴራል መንግስት ይህ ሁኔታ የሚፈጥረው አሉታዊ ተፅእኖ በሚገባ አጥንቶ ተገቢ ፍትሃዊ እርምጃ እንዲወስድ ይጠበቅበታል። ይህ ለወይን መፅሄት የተደረገው ድጎማ ህጋዊነት የሌለው ከመሆኑም አዃያ ለማይረባ ፖለቲካ ከሚዉል በ No War No Peace ድባብ የበለጠ የተጎዳዉን ህዝብ ለመደገፍ እና ሁኔታው የፈጠረው ኢኮኖምያዊ፣ ስነ ምህዳራዊ፣ ስነልቦናዊና ማህበራው አሉታዊ ተፅእኖ ለማጥናት ቢዉል በአገሪቱ ሞራላዊ ግዴታ ለመወጣት የመጀመርያው እርምጃ በሆነ ነበር።

የመፅሄቱ ዝርዝር ይዞታ ሳይ ደግሞ በእውነት የህወሓት ልሳን ነው ወይ? የሚል ጥያቄ እንዳነሳ አስገድዶኛል። ከመልካም አስተዳደር ጋር ተያይዞ በኢህአዴግ ዉስጥ የተፈጠረው መነቃቃት፤ የህወሓት ጉባኤ ደግሞ ከሌሎች የግንባሩ ድርጅቶች የሰላ እንደነበር፤ የዚህ የሰላ ጉባኤ ምልክት ተደርገው በህዝቡ ክብር ያገኙት ቄስ ገብረገርግስ ገብረማርያምም የጉባኤዉን ሂደት ሲገልፁ “ፊት ንፊት ገጢምና እንተወሐደ ንለባም ክርደኦ ገይርና አለና! ቀይናን እዉን ሰንቢዱ አሎ” ትርጉም፥ “ቢያንስ ፊት ለፊት ገጥመን ልባሙን እንዲረዳ አድርገናን! ጠማማው ደግሞ ደንግጥዎል” ነበር ያሉት ከ ዉራይና መፅሄት ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ። ሁኔታው ይህ ሆኖ ሳለ ትግራይ ዉስጥ የተፈጠረው ማዕበል ከወይን ሳልሰማ ስቀር ግን ግርምት ፈጥሮብኛል። በኔ አመለካከት ወይን ቁጥር ሃምሳ (ሌሎች እትሞችን ስላላነበብኩ አስተያየት ለመስጠት ያስቸግረኛል) የዴሞክራሲ ማዕበሉን ያስፈራቸው የድርጅቱ አመራር ወይም ከበስተጀርባቸው የሚደጉምዋቸው ሃይል ልሳን ነው እንጂ የህወሓት 12ኛ ጉባኤ መንፈስ የሚያንፀባርቅ አይደለም።

ህወሓትም እንደሌሎች የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ስለ GTP 1 አፈፃፀም ጠንካራ እና ደካማ ጎን በአንድ በኩል፤ GTP 2 የሚጀምርበት ውቅትም በመሆኑ የህዝቡን አስተያየት አካቶ ህዝቡን በዙርያው እንዲሰለፍ ለማድረግ ይሞክራል ተብሎ ሲጠበቅ አጀንዳው ሌላ ሆነ፤ በዚህም ይህ እትም የወደቀ እና የሚያሳፍር ይመስለኛል። ትልቅ ፖለቲካዊ ትርጉም ግን አለው:: ማዕበሉ ሲጀምር ከሁሉም በላይ ለማደናቀፍ የሚሞክሩት በፓርቲ/በመንግስት ያሉ የተወሰኑ ሹማምንት መሆኑን ያሳያል። የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለመፍታት ዴሞክራስያዊ ምህዳር ለማስፋት የሚታገል ህዝብ፣ ፓርቲ እና መንግስት የመጀመርያው ምልክት ነው። እንደ ማስጠንቀቅያ መወሰድ ይኖርበታል፤ ትግሉም ከዚህ መጀመር ይኖርበታል። ወይን ቁጥር ሃምሳ ህገ መንግስቱን በግላጭ የደፈረ ሲሆን ከወቅቱ ፖለቲካም የ ኢ-ዴሞክራስያዊ ሃይሎች መሳርያ ሆኗል።

ወደ ይዘቱ ስንመጣ የሚያስገርም ነው። “አብ ቅድሚ መለስን ስዉአትን ዝተአተወ ረዚን ቃል” ትርጉሙ “በመለስ እና በሰማእታት ፊት የተገባ ከባድ ቃል” በሚል የህወሓት ሊቀመንበር ሰፋና ሁሉኑም ያቀፈ ቃለ መጠይቅ እንዲሁም በተመሳሳይ የቀድሞ የትግራይ ሲቨል ስርቪስ ሃላፊ የነበሩት የተደረገ ቃለ መጠይቅ እናገኛለን። ካሉት ሌሎች ፁሁፎች አንዱ በአቶ ገብሩ አስራት የተፃፈውን “ሉእላዊነት እና ዴሞክራሲ በኢትዮጵያ” የሚለው መፅሃፍ ላይ እኔ ለፃፍኩት ፅሁፍ ‘ሂስ’ የሚያቀርብ ሲሆን ሌሎቹ ግን ከ 24 ዓመት በፊት በትጥቅ ትግል የነበረው ሁኔታ ነው የሚያትቱት። ከቃለ መጠይቁ ዉጭ ስለ GTP 1፣ GTP 2፣ ስለተፈጠረው ማዕበልና ስለ አዲሶቹ አመራሮች ምንም እሚለው ነገር የለም። የጀግኖቻችን (በሂወት ያሉትም የተሰዉትም) ደማቅ ታሪክ መሰነድ አለበት፤ በየግዜዉም ከተሞክሮቻቸው መላው የኢትዩጵያ ህዝቦች እንዲማርበት ይገባል። እኔም እኮራባቸዋለሁ። የወቅቱ ፖለቲካዊ ትኩሳት (ማዕበል) ለማቀዝቀዝና አጀንዳ ለማስቀየር ሲዉል ግን ያሳዝናል። ወይን ባሉትም በተሰዉትም ጀግኖቻችን ስም መሸቀጥ የለባትም እላለሁ።

በጥቅሉ በህጋዊ መንገድ በመንቀሳቀስ ላይ ያሉትን የመድረክ፣ የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀ መንበር፣ የዓረና የቀድሞ ሊቀመንበር፣ በፓርላማው ብቸኛው የተቃዋሚ ፓርቲ ወኪል የነበሩትን ሰዎች በፎቶግራፍ አስደግፈው “በጥፋትና በሁከት መንገድ የሚደረግ የስልጣን እሽቅድድም ላሁንም ለዘላለሙም ተቀባይነት የለዉም” ብለው ወይን እንዲፅፉ እንዴት እነዛ መስርያ ቤቶች ስፖንሰር ያደርጋሉ? እነዚህ መሪዎች ከህግ ዉጪ ከሄዱ የሚጠይቃቸው መንግስት እያለ፤ ይህ እስካልሆነ ድረስ ግን የትኛዉም ፖለቲካዊ ዓላማ ይያዝ የመንግስት መስርያ ቤቶች በተለይም መከላከያ ስፖንሰር ማድረጉ ወይንን “እዉነትህ ነው” እንደማለት አይቆጠርም ወይ?

“ሸፈጥን አነነትን እንትሓብሩ” ትርጉም “ሸፈጥና እኔነት ሲያብሩ” የሚለው ፅሁፉ ጠቅላላ ይዘቱ በስልጣን ያሉትን ኢታማዦር ሹምን ለማሞገስ እና በጡሮታ የተገለሉትን የቀድሞ ኢታማዦር ሹምን የሚያንኳስስ ‘የማን ይበልጣል?’ ዓይነት ፁሁፍ ነው። የትግራይ ህዝብ እየለበለበው ያለዉን የብልሹ አስተዳደር ችግር እያለ እንደ ድሮ መሳፍንት ‘ራስ እገሌ ከ እገሌ ይበልጣል’ ዓይነት ፅሁፍ ይዞ መዉጣቱ በጣም የሚያሳፍር ነው። መወየን ተራማጅነትን የሚገልፅ ቢሆንም እየተደረገ ያለው ግን የ አድሃርያን ተግባር ነው፤ ወያነነቱም የት ሄደ? ያስብላል። ለመሆኑ ወይን በስራ ላይ ካሉት ኢታማዦር ሹም ምን ቢፈልግ ነው የህዝቡን ድምፅ ማሰማት ሲገባው ወደ ወረደ መሳርያነት ራሱን ያሸጋገረው? ፖለቲካዊ ዘመቻም ከሆነ ጡረታ ሲወጡ ያደርግላቸዋል። ሁለቱም ኢታማዦር ሹሞች የየራሳቸው እና የጋራ የሚያኮራ ታሪክ እያላቸው የ ‘አንዱ ይበልጣል’ ንፅፅር ምን አመጣው?

ወይን መፅሄት “አብ መከላኸሊ ሓይሊ እዉን ክግበር ዝኽእል ዘይሕጋዊ መማረፂታት እንተልዩ ምሕሳብን ምፍታንን ጀሚሮም” ይላል። ትርጉም “በመከላከያ ሃይል ዉስጥም ማድረግ እሚቻል ህጋዊ ያልሆነ አማራጭ ካለ ብለው ማሳብና መሞከር ጀመሩ” ይላል። ለሌተናል ጄኔራል ፃድቃን እና እኔ ባለፉት ወራት አንዳንድ ከትጥቅ ትግሉ ጋር የተያያዘ የምናውቀዉን ፅፈን ነበር፤ ሰው ሊስማማ ላይስማማ ይችላል። የሚገርመው ግን ወይን ወይም ስፖንሰሮቹ “ህገ ወጥ ድርጊት በማስብ እና በመሞከር” ብለው ለማስፈራራት የሞከሩት ነገር ነው። ከ አስራ አምስት ዓመት በኃላ ይህ ማስፈራርያ ለምን መጣ? አርፋቹህ ተቀመጡ ለማለት ነው? ወይንና ‘እማይታወቀው’ መሐመድ በወቅቱ የነበሩት ጠቅላይ ሚኒስቴር መለስ ዜናዊ (ነብሳቸው ይማርልን) እያወቁ “ምህረት” አድርገዋል፤ አሁን ግን የሚምራቹህ ሰው የለም እያሉን ይሆን እንዴ?

‘ቁም ነገር’ ማስፈራራቱ ነው፤ ‘የምናውቀው ሚስጢር ስላለ ተጠንቀቁ’ እንደማለት ነው። ይህ ጉዳይ የአንድ መፅሄት ነገር ቢመስልም የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ የጠቅላይ ሚኒስቴሩ ቢሮ እና መስርያ ቤቶቻቸውን ሊመረምሩት እና ማስተካከያ ሊያደርጉበት ይገባል እላለሁ። ይህ የጥቂት ሰዎች ድርጊት የጀግናው መከላከያ ስራዊታችንን አጠቃላይ ስብእናው እንዳይጎዳዉም ጭምር እሰጋለሁ፤ በመፅሄቱ የተንፀባረቀው ሃሳብም ሁሉም የመከላከያ የበላይ አመራሮች እንደማይቀበሉት አውቃለሁ። ወይን አብዮታዊ (ወያናይ) ስብእናዉን መጠበቅ ካለበት የማንም መፈንጫ መሆን የለበትም::

በተለይ የመከላከያ ጉዳይ አሳሳቢ ነው። በታዳጊ አገር ሰለምንገኝ እና ዴሞክራቲክ ተቛሞቻችን ደካማ በሆኑበት ግዜ የታጠቀው ሃይል ወይ ራሱ ንጉስ (King) ወይም እንጋሽና አፍራሽ (King Maker and breaker) ለመሆን ይዳዳዋል። አሁን የታየው ምልክት እንዳይሰፋ ከወዲሁ መጠናት አለበት፤ የሲቪልያን ቁጥጥሩም ጠበቅ ማለት አለበት። ጠንካራ የሃገር መከላከያ የዴሞክራሲያዊ ስርዓታችን ዘበኛ ቢሆንም፤ ከልክ በላይ ካበጠ ግን የ ኢ-ዴሞክራስያዊ ሃይሎች መሳርያ ስለሚሆን በዚህ ረገድ የተሰማሩ ሙሁራን ወታሃደራዊ ክፍሉ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ወይ ቅልበሳ (democratization and de-democratization) ላይ የሚኖረዉን ሚና እንዲያጠኑት መንግስት ሁኔታዎችን ማመቻቸት አለበት፤ እኔ እስከምናውቀው በዚ ዙርያ ኢትዮጵያን ማእከል አድርጎ የተጠና ጥናት አላገኘሁም።

በተያያዘ መልኩም የግል ሚድያው እንደነ ሪፖርተር፣ዉራይና፣ አዲስ አድማስ እና ሰንደቅ የመሳሰሉ ሃላፊነት የሚሰማቸው ጥቂት ሚድያዎች ቢኖሩም አብዛኞቹ ግን መልካም አስተዳደር ለማስፈን፣ሙስናን ለመታገል እና ፍትህን ለማንገስ ይቅርና በግላጭ መካድ እማይቻለዉን ማህበረ-ኢኮኖምያዊ ለውጦችን እሚክዱ መሆናቸው ስታዘብ ራሳቸዉን ማስተካከል እንዳለባቸው እረዳለሁ። በነጋ በጠባ ቁጥር አመፅን እና ሁከትን እሚሰብኩ፤ ዘመናዊ የሰለጠነ ፖለቲካ አለርጂክ የሆነባቸው የግል ሚድያዎች የሞያዊ ስነ ምግባር ጉድለት እና ህገ-ወጥነት ሲታከልበት ከጥቅማቸው ይልቅ ጉዳታቸው እየጎላ ይሄዳል። ሃላፊነት እሚሰማቸው ሚድያዎች እሚያደርጉት ጥረት መደገፍ ያለበትና ለሌሎቹም ትምህርት የሚሆን ስለሆነ በርቱ መባል መቻል አለባቸው።

በስራ ላይ ያሉት የመንግስት እና የህዝብ የሚባሉት የመገናኛ ብዙሃን የኢትዮጵያ ህዝብ መረጃ እና አማራጭ ሃሳቦች ማግኘት እንደሚገባው የተገነዘቡ ሳይሆን የኢህአዴግ ልሳኖች መሆናቸው በተግባር ያረጋገጡ ሚድያዎች ናቸው፡፡ ያገሪትዋ መገናኛ ብዙሃን በአድልዎ የተሞላና ህጋዊ ተቃዋሚ ፓርቲዎች እና ከገዢው ፓርቲ የተለየ አቛም ያላቸዉን ሰዎች የሚያገል አሰራር እና ባህሪ ያለው ተቛም ነው። በጅምር ዴሞክራሲ በብዙ ጫና እና ድካም እሚንቀሳቀሱትን ተቃዋሚ ፓርቲዎች እንደማገዝ ፈንታ ስህተቶቻቸውን እየፈለጉ እና እየለቃቀሙ ለህዝቡ በማቅረብ የኢህአዴግን ጠንካራነት እና አይበገሬነት ሲሰብኩ ማየት የተለመደ ተግባራቸው ከሆነ ብዙ ግዜ ቆጥረናል፡፡

የመንግስት የመገናኛ ብዙሃን ትዕቢትና ህግ መንግስትና ሌሎች ያገሪትዎን ህጎች ከቁብ እንደማይቆጥሩት በተግባር እያሳዩን ነው፡፡ የህወሓት 40ኛ አመት በትግራይ ቴሌቪዥን የወራት ሙሉ ሽፋን እንዲሁም በኢቢሲ (EBC) ላቅ ያለ ሽፋን የተሰጠው የምርጫ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ትንፋሽ ለመተንፈስ እንኳ የማትበቃ ጥቂት ደቂቃ በተመደበላቸው የምርጫ ወቅት መሆኑ ስንገነዘብ ነው የመንግስትና የህዝብ የመገናኛ ብዙሃን ባህሪ እና ማንነት መረዳት እምንችለው፡፡ እስኪ ህወሓት በትግራይ ቴሌቪዥን እና EBC ላሰራጨው የወራት ፕሮግራም ክፍያ ፈፅመዋል? ቢፈፅምስ ይህ ተገቢ ተግባር ነውን?

ከመንግስት ዉጪ የሆነ በግል ድርጅት ባለቤትነት ስር የሚገኝ የቴሌቭዥን ጣብያ እስካሁን አገራችን ላይ አለመኖሩ እሚገርም ነገር ነው። የዚህ ዋና ምክንያት ምንድን ነው? ብሎ መጠየቅ መቻል አለብን። ሲጀመር ፍቃድ የሚሰጠዉስ ግልፅነት፣ ተጠያቂነት እና ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ነው? መንግስትስ ከአብዮታዊ ዴሞክራሲ አስተሳሰብ የተለየ ሃሳብ ያላቸዉን ዜጎች የቴሌቭዥን ፍቃድ ቢጠይቁ የመስጠት ድፍረት አለዉን? ወይስ ለመንግስት እማያጎበድድ ከሆነ ፍቃድ አያገኝም? አልያም ለ “ጨዋዎቹ” ብቻ ነው ‘ሊራራ’ እያሰበ ያለው?

የዚህ ፅሁፍ ፀሃፊ የካቲት 11 መከበር ያለበት በዚህች አገር ታሪክ የዴሞክራሲ እና የልማት የማዕዘን ድንጋይ የተቀመጠበት ቀን ነው ብሎ ያምናል፡፡ ሆኖም ቀኑን ለርካሽ ግዝያዊ ፕሮፓጋንዳ ህገ መንግስታዊ ድንጋጌዎችን በመጣስ ሌሎች ተፎካካሪ ፓርቲዎችን ለማፈን መዋል የለበትም ብሎ ያምናል፡፡ የምንወደው እና የምናከበርው በዓልም ህገ መንግስትን ባከበረና ለዴሞክራያዊ ስርኣት ግንባታ አስተዋፅኦ በሚያደረርግ መልኩ መከበር አለበት፡፡ የካቲት 11 ሁሌም መከበር እና መዘከር ያለበት በዓል ነው። ይህ ስል ግን በሰማእታት ደም እየነገዱ ለመኖር ባለመ ሁኔታ መከበር እንደሌለበትም በማሳሰብ ነው። አንዳንዴ ለበዓሉ እሚወጣወ የገንዘብ እና ሌሎች ሃብቶች ሳስስተዉል ግን ምናለ በንዲህ ከሚጠፋ ለጥናት እና ምርምር ፈሰስ ተደርጎ ባይ እሚል ጥያቄ ይጭርብኛል።

ከዚህ ጋር በተመሳሳይ መልኩ በትግራይ ቴሌቭዥን ‘አንጃ’ ‘የበሰበሰ’ ወዘተ ማለትን ይዘወተራል፤ አንዱን የፓርቲው ወገን ደግፎ ሌላዉን መዘርጠጥ የተለመደ ስለሆነ ብዙ ሀተታ አያስፈልገዉም። የዴሞክራሲ ስርዓት ለሚያውቅ ግን አሳፋሪ ነው። በሆነ ዴሞክራስያዊ ስርዓት የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች የተለያዩ ብሄር /ብሄሮች ሃይማኖት፣ ፆታ፣ የተለያዩ መደቦች (እንደ ገበሬ) እና ሌሎች ያሉበት ስለሆነ የተለያዩ ፍላጎቶች ማንፀባረቃቸው አይቀርም። የፍላጎትና የእሴት ጉዳይ ስለሆነ ባብዛኛው ፖለቲካዊ ገፅታው የተወሰኑ ሰዎች ባቛቛሙት ድርጅት ሊገለፅ ይችላል። ለምሳሌ በአሜሪካ ኮንግረሰ የቀኝ አክራሪዎች ቀጣይነት ባለው ወጣ-ገባ ነው እሚካሄደው። በቅርብ የ ኮንግረሱ አፈ ጉባኤ ስራ ለመልቀቅ የቻሉት በነዚህ ግፊት ነው። አንጃ (Faction) መፍጠር የተለመደ እና ፓርቲው አቻችሎ እሚሄደው ነገር ነው። የተለያዩ ፍላጎቶች በፓርቲው ዉስጥ መንሸራሸራቸው ባህርያዊ ነው። ይሄም በቛሚነት የሚታይ ባህሪ/ permanent ternd ነው። በአንድ ጉዳይ ላይ በአንድ ፓርቲ የሚገኙ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተለያየ ፍላጎት እና አዝማሚያ ሊያንፀባርቁ ይችላሉ፤ ዴሞክራስያዊ አካሄድ ደግሞ ይህን አቻችሎ መሄድን ይጠይቃል። አብዮታዊ ዴሞክራሲ ሊበራል ዴሞክራሲን መድረስ ወደ ሚገባው ጫፍ ለማድረስ እሚንቀሳሰ ከሆነ የተለየ ሃሳብ ያራመዱትን ለምን እያሳደደ እንደሚኖር አይገባኝም። ከዴሞክራሲ አኳያ ስብሰባን ረግጦ መዉጣት አገርን እንደመሸጥ ተደርጎ ሊቆጠርበት የሚችል ሁኔታ ኢ-ዴሞክራስያዊ ሁኔታ ብቻ ነው።

አንድ ጏደኛየ አንጃ ምንድን ነው? ብየ ስጠይቀው ማስፈራርያ በትር ነው አለኝ። ልክ ደርግ ወያነን መግለፅ ሲይቅተው “ወያኔ በጣም ትላልቅ ጆሮዎች ያላቸው ጭራቆች ሲሆኑ፤ አንደኛው ይነጠፉታል፣ አንደኛው ይለብሱታል” ሲል እንደነበረው መሆኑ ነው። ከዴሞክራስያዊ ባህል አዃያ ሲታይ የተለየ አቛም ያለው “በሰበሰ” ማለት ከራስ የተለየን ሃሳብ የማክበርን ዴሞክራስያዊ መርህ ይፃረራል።

በተመሳሳይ መንፈስ ህዳር 11 መከብር መዘከር ያልበት ታሪካዊ ቀን ነው ነገር ግን የክብረ በዓሉ አጀማመሩ ልክ እንደ ህወሓት ይመስላል። ጋዜጠኞች ወደ ትግል ቦታ ተወስደዋል፤ በማን በጀት? የክልል ፓርላማ ግልፅ በሆነ መንገድ ከወሰነም የክልሉ መንግስት ይህ ለማድረግ ህገ መንግስቱ ይፍቅድለታል ወይ? በጀቱስ ስንት ነው? ብአዴን በአማራ ክልል ቴሌቭዥን እና በ EBC ለሚያሰራጨው ፕሮግራም ክፍያው ማን ይከፍለዋል? አሁንም የበዓሉ አከባበር ህገ መንግስቱ እና ሌሎች ህጎች የተከተለ ነው ወይ? እስከ ምንድረስስ አሳታፊ፣ ግልፅ እና ተጠያቂነት በሚያረጋግጥ አዃሃን እየተሰራ ነው? እስከ ምን ድረስ ሚዛናዊ መረጃስ ለህዝብ ያቀርባል? እሚሉት ጥያቄዎች መመለስ አለባቸው።

ይህ ሃቅ ኦህዴድንም ደኢህድንንም የሚመለከት ነው፡፡ በቅርቡ ካየነው እንኳን ከዜና አንባቢው ጀርባ እምናየው ሽፋን የኢህአዴግ 10ኛ ጉባኤ መፈክር ነበር፡፡ ይህ ምን ማለት መሆኑ በራሱ እሚነግረን ብዙ ነገር አለ፡፡ ለምሳሌ ዓረና መድረክ ወይም አብኮ ድርጅታዊ ጉባኤ ቢያካሂዱ EBC እንዲህ ያደርጋል? ሲጀምርስ በተሟላ አኳሃን ይዘግበዋል? መምቻ ይሆናል ብሎ ካሰበ ግን መልሱ አዎ “በደምብ ነው እንጂ” ነው እሚሆነው፡፡ይህ ግላጭ ፀረ ህገ መንግስትነት በግዜ መታረም አለበት።

መሬት ላይ ያለው እውነታ ከላይ እንደተገለፀው ቢሆንም፤ ኢህአዴግ በ1992 ለውይይት ያቀረበው ሰነድ ግን እንደሚከተለው ይላል፡ “ህዝቡ ነፃና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ መወሰንና መሳተፍ አለበት ሲባል ቅንና ሳይንሳዊ የሆኑ ሃሳቦችን ብቻ መስማት አለበት ማለት አይደለም፤ የተሳሳተና ኋላቀር ሃሳብንም በነፃ መስማት አለበት፡፡ ሰምቶ ከተከተለው መከተል ይችላል፡፡ በሂደት በተግባር ከስህተቱ ተምሮ ወደ አብዮታዊ ዴሞክራሲ አስተሳሰብ ይመለሳል፡፡ ካልተቀበለው ደግሞ ይበልጥ በነፃ ፍላጎቱና በሚያስተማምን አግባብ ቅን ወደሆነው ሃሳብ ይገባል፡፡ አብዮታዊ ዴሞክራያዊ የአስተሳሰብ ልዕልናውን የሚጣረጋግጠው የተሳሳቱ ሃሳቦችን በማፈን አይደለም፡፡ የተሳሳቱ ሃሳቦን ማፈን ማለት የሚያጋልጣቸውና የሚታገላቸው ሳይኖር ውስጥ ለውስጥ እንዲጎለብቱና እንዲጠነክሩ በር መክፈት ማለት ነው” ይላል በገፅ 65 ላይ፡፡

ይህ የተጠቀሰው ዶክመንት በገፅ 123 ላይም እንዲህ ይላል “መላውን ህዝብ /አብዛኛው ክፍል/ ለአመታት ለአንድ ፓርቲ አመለካከት በማጋለጥ፣ ሌሎችን በመከላከል የሚደረግ አሰራር መከተል በሃሳቦች መካከል ነፃ ውድድር እንዳይኖር የሚያደርግ ነው የሃይለስላሴና የደርግ መንግስታት ይህም ማድረጋቸው የሚያመላክተው ፀረ ዴሞክራስያዊ ባህርያቸው ነው” (ኢህአዴግ፣ 1992 ዓ.ም ገጽ 123) ። ምን ዋጋ አለው ሰነድ ሌላ እዉነታ ሌላ ሁነ እንጂ!!!

የነፃ ሚዲያ እድገት ሃሳብን ከመግለጽ መብት ጋር የተቆራኘ ነገር ነው፤ ሃሳብን የመግለጽ መብት ደግሞ መሰረታዊ ሰዎች ሰብአዊ መብት ነው፡፡ የዚህ መብት በሰው ሂወት ያለውን እርባና ሰፋ አርገን መገንዘብ አለብን ይላሉ የዘርፉ ባለሞያዎች (ቢአታ ሩዞሚሎቪችስ) እንደሚለው የሰው ልጅ ያለበትን ሁኔታ፣ስጋቶቹ እና ፍላጎቶቹን መግለፅ እና ለሌሎች ማስተላለፍ እስካልቻለ ድረስ ሂወቱ ሙሉ ነው ማለት አይቻልም ይላል ቢአታ።

ከዚህ መረዳት እምንችለው ሃሳብን በነጻ የመግለፅ እና ተያያዥ መብቶች ሰው መሆንን ሙሉ እሚያደርጉ እና ለሂወት አስፈላጊ አምዶች እንደሆኑ ነው፡፡ ዴሞክራሲ ሰዎች ሙሉእነታቸው በሚያረጋግጡበት ክብሮች /values/ የታጀበ ነው ሲባልም ለዚህ ነው:: ሂወት የመማማር ሂደት የምትሆነው ሃሳባችንን በነፃ መግለፅ ስንችል እና የሌሎችን ሃሳብ በነፃነት ማግኘት ስንችል ጭምር ነው ይላል ቢአታ (2002:13)፡፡ መገናኛ ብዙሃንም እውነተኛ መገናኛ ብዙሃን የሚሆኑት በህብረተሰቡ ያሉትን የተለያዩ ሃሳቦች አቅማቸው በፈቀደ መጠን በእኩልነት ሲያስተናግዱ ነው፡፡ ይህ ባልሆነበት ሁኔታ የመገናኛ ብዙሃን “ደግ ደጉን” ብቻ እሚያወሩ የአንድ ፓርቲ አፈ-ቀላጤ ከሆኑ ህዝቡን እና የፖለቲካ ሃይሎች ወደ ፅንፉ እየገፋ አውዳሚ ሊሆኑ ለሚችሉ የሚድያ ተቋማት በር መክፈታቸው አይቀርም ፤እየሆነ ያለዉም ይሄው ነው፡፡ የህዝብ እምነት ያጡ ሚዲያዎች ለልማቱም ለዴሞክራሲውም እሚያበረክቱት አስተዋፅኦ ላይኖር ይችላል፡፡ ሚድያ በገበያ ሃይሎችም ይሁን በመንግስት በብቸኝነት በቁጥጥር ስር ሲውል ከዴሞክራሲ አኳያ አደገኛ የስጋት ምንጭ ነው እሚሆነው፡፡የግል የመንግስት እና የድርጅት ሚድያዎች ተገቢ ሚናቸዉን በተገቢ አዃሃን ከተጫወቱ የዴሞክራታይዜሽን ሃይል ሆነው የላቀ ጥቅም ይሮራቸዋል፤ ይህ ሳይሆን ሲቀር ግን አጥፊ እና የኢ-ዴሞክራታይዜሽን ሃይል መሆናቸው አይቀርም።

5.4 የአንድ ለአምስት ተቋም

አንድ የቆየ ዋዛ ከቁም ነገር ነው፤ ሴትየዋ መልካም የሚባል ትዳር አንዳላትና መሰረቱም ከባልዋ ጋር ያላቸው የስራ ክፍፍል እንደሆነ በደስታ እንዲህ ስትል ትመሰክራለች “ባሌ ትላልቅ ውሳኔዎችን ይወስናል፤ እኔ ደግሞ በትናንሽ ነገሮች ላይ እወስናለሁ፡፡ ባሌ እሚወስናቸው ነገሮች ልክ እንደ ‘ቻይና የተባበሩት መንግስታት አባል ያድርጋት? አያድርጋት?’ እሚሉት ነገሮች ላይ ሲወሰን፤ እኔ ግን የት አካባቢ መኖር እንዳለብን እና ልጆቻችን የት ይማሩ እሚሉትን ጉዳዮች ላይ እወስናለሁ” አለች፡፡ የዚህ ተረት መልእክቱ ባልየው ውጤታማ ሳይሆን ቅዠታም ወይም ብቸኛ እና አማራሪ በፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ፍላጎት ያለው እና የሆነ የጥናት መስክ “የፖለቲካ ተሳትፎ” ያደርጋል ብሎ ሊፈርጀው እሚችል ዓይነት ሰው ሲሆን፤ ሚስቱ ግን የምትወስነው ውሳኔ ተፅዕኖ የሚፈጥር እና የተፈፃሚነት መጠኑም ከፍ ያለ ነው፡፡ በእርባና አኳያም የሚስትየው ተሳትፎ እጅግ ጠቃሚ ነው፡፡

አንድ ለአምስት አደረጃጀትም ለህዝቡ የቀረበና የሚወስዱት እርምጃዎችም ቀጥተኛ ተፅዕኖ የሚፈጥሩ በመሆናቸው ሊጠኑ እና በጥልቀት ሊዳሰሱ ይገባቸዋል፡፡ ይህ አደረጃጀት እታች ወርዶ የተፈጠረ ተቋም ሲሆን አጠቃላይ ህዝቡን ለልማት አነቃንቆ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ባህላዊ እና ፖለቲካዊ አወንታዊ ለውጦችን በማስመዝገብ መዋቅራዊ ለውጥ ለማምጣት ሊያግዝ እሚችል ፈጠራ የታከለበት አደረጃጀት ነው፡፡ በአግባቡ ካልተያዘ ግን የድህንነት ተቋም ተቀጥያ ሊሆን ይችላል፡፡ ለጠባብ የፓርቲ ፖለቲካዊ መሳርያነት ከተጠቀምንበትም ጉዳቱ የከፋ ይሆናል፡፡ በቤተሰብ ዉስጥ ስለላን እና ጥራጣሬን ሊተክል ይችላል፤ አለን እምንለው የቆየ ማህበራዊ እሴትንም ድምጥማጡ ሊያጠፋው ይችላል።

ኢህአዴግ እሚመራው መንግስት ወደ ህዝቡ ወርዶ ለማገልገል እና ድህነትን ለመቅረፍ እሚያደርገው ትግል ላቅ ያለ ምስጋና ይገባዋል፡፡ ማዳበርያ፣ ምርጥ ዘር፣ የእርሻ ቴክኖሎጂዎች እና አስተምህሮዎች፣ ለገበያ እሚያበቁ ምርቶች እንዲያመርቱ እሚደረገው ማበረታቻ፣ ውሃ፣ የጤና እና የትራንስፖርት አገልግሎት ወደ ገበሬው ለማድረስ እሚደረገው ጥረትም ይበል እሚያስብል ነው፡፡ እንዲሁ በስመ ነፃ ገበያ እና ሊበራል ዴሞክራሲ ከላይ የተጠቀሱት አገልግሎቶች እና ግብአቶች መንግስት አይመለከተኝም በገበያ ህግ ይመራ ቢል ምን ሊከሰት እንደሚችል እስኪ አስቡት? በአስር ሺዎች እሚቆጠሩ የጤና እና የግብርና ባለሞያዎች አሰልጥኖ፣ አሰማርቶ እና ደሞዝ ከፍሎ ወደ ገበሬው ማሰማራት ምን እንደሆነ እስቲ አጢኑት? በተጨማሪም ከጎጥ እስከ ፌዴራል መንግስት እሚገኝ ባለስልጣናት ይህን እንዲመሩ ሲደረግ ትርጉሙ ምን እንደሆነ አስቡት? ይህ ሁሉ ኢንቨስትመንት በግዜ፣ በገንዘብ፣ በእውቀት እና በጉልበት ተምኑት፣ ወደድንም ጠላንም ይህ ጥረት አስገራሚ ለውጦችን ማስመዝገብ ችለዋል፤ በትንሹ ከአጭር ግዜ አኳያ፡፡

ሆኖም ይህ ዘላቂ ነውን? ብለን መጠየቅ ተገቢ ነው፡፡ ዘላቂነት የሚረጋገጠው መሰረታዊ የተቋሙን (አንድ ለአምስት) ችግር ሲፈታ ነው፤ መሰረታዊ ችግሩ ደግሞ ሌላ ሳይሆን የዴሞክራሲ እጥረት (democratic deficiency) ነው:: በዚህ ዙርያ ብዙ ነገሮች ይነሳሉ፡፡ ጥልቅ ጥናት እሚፈልግና ከቦታ ወደ ቦታ ሊለያይ የሚችል ነገር መሆኑ ሳንዘነጋ ካጠቃላይ ከባቢው (General environment) እና ከምታዘባቸው ነገሮች ተነስቼ ስለ ጉዳዩ ጥያቄ ማንሳት ግን ጠቃሚ ይመስለኛል፡፡ በትንሹ የገጠርን እንኳን ብንወስድ ከኢትዮጵያ ህዝብ ከ 80% የሚሆነውን ህዝብ እሚያንቀሳቅስ አደረጃጀት መሆኑ ስንገነዘብ በዚህ ጉዳይ መፃፉ ምን ያህል ጠቃሚ እንደሚሆን እንረዳለን፡፡

አንድ ለአምስት እሚባለው ተቋም /አደረጃጀት/ ሰዎች በራሳቸው ተነሳሽነት እሚመሰርቱት ተቋም ተደርጎ ሊታይ ይችላል፡፡ በዚህ ሂደት አባላት ያጭር እና የረጅም ግዜ ፍላጎታቸው እሚወስኑበት እና እንዴት እና በማን ያላቸውን ሰብአዊ እና ቁሳዊ ሃብታቸውን አንቀሳቅሰው አሳታፊ በሆነ መንገድ ውሳኔ ላይ የሚደርሱበት አደረጃጀት ተደርጎ ሊታይ ይችላል፡፡ የተቋሙ አባላት ለራሳቸው ጥቅም ሲሉ የተደራጁ ናቸው ብንል እንኳ ከውጭ እሚሰጥ አመራርም ቁልፉ ነገር ነው፡፡ ነገሩ እንዲህ ነው ብንል ከዴሞክራሲ አኳያ ግን መመለስ ያለብን ጥያቄዎች አሉ፤ መሬት ላይ ያለውን ሃቅን መሰረት አድርገን በመነሳት፡:

እውን አሁን ያለን አንድ ለአምስት አደረጃጀት በአባላት በጎ ፍቃድ የተመሰረቱ ናቸው? ፍላጎታቸውን መሰረት አድርገው በነፃነት ራሳቸው ይወስናሉ? የቀረበላቸው ግብአት መርጠው የመቀበል እና እምቢ የማለት መብት አላቸው? “ህዝብ ከራሱ ተሞክሮ ይማራል” እምትል ዴሞክራስያዊ መፈክር ተግባር ላይ እየዋለ ነው? ግምገማውስ ምን ይመስላል? አንድ ሰው በተለያየ ምክንያት ማዳበርያ ወይም ምርጥ ዘር አልገዛም ቢል ሰውዬው ላይ ምን ይከተላል? ይሄስ እንዴት ነው ሪፖርት የሚደረገው? ባለስልጣናት በቅጣት ሊታጀብ እሚችል ማስገደድ እያከናወኑ አይደለምን? የኔ ቅኝት በጣም አሉታዊ እና የተፈጠረውን በጎ ውጤት ሊያቀጭጭ ይችላል የሚል ድምዳሜ ነው ያለኝ ፡፡ ዘላቂነቱ መረጋገጥ ካለበት መሰረታዊ የተቋሙ በዲሞክራሲ ዙሪያ የሚታይ እጥረቶች መታከም መቻል አለባቸው፡፡ ይህ አገር ሙሉ እሚያንቀሳቅስ ተቋም በፀረ ዴሞክራሲ አሰራር እና ባህል ከተተበተበ ኢትዮጵያ ላይ የሚያስከትለው ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ኪሳራ ለመገመት እሚያስቸግር ቀውስ ነው እሚፈጥረው፡፡

ባጭሩ ተቛሙ ቀና ለሆነ ልማታዊና ዴሞክራስያዊ ተግባር እንዲዉል ከተደረገ የዴሞክራታይዜሽን ሂደቱ ዋና መዋቅራዊ መሰረት ይሆናል፤ ምክንያቱም ከስማንያ ፐርሰንት የሚሆነው ህዝባችንን እሚያንቀሳቅስ ተቛም ስለሆነ ነው። በተቃራኒው ይህ ተቛም ወይም አደረጃጀት ከታለመለት አላማ አፍትልኮ የጠባብ ፖለቲካዊ ፍላጎት እና የቁጥጥርና ስለላ መዋቅር ተቀጥያ ከሆነ ግን የኢ-ዴሞክራታይዜሽን ሃይል ነው እሚሆነው።

6. ንቅናቄው እንዴት ይቀጣጠል?

እንደ መፍትሄ የሚደረገው እንቅስቃሴ አጠቃላይ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ሽግግሩን መሰረት ያደረገ አስተሳሰብ ፤ ያደረጃጀት እና የአሰራር ለውጥ ሲሆን ነው የተጠቀሱት ሶስት በሽታወዎች ተፅእኖአቸውን ደካማ ማድረግ የሚቻለው፡፡ እነዚህ ሶስት አደገኛ በሽታዎችን ለመከላከል፣ ለመቆጣጠር እና በተወሰነ ደረጃ ለማከም (ለማምከን) አዳገች ወይም የማይቻል የሚያደርጋቸው ህብረተሰቡ ውስጥ ያሉትን ዲሞክራሲያዊ ተቋማት ማእከል አድርገው የሚካሄዱ ዲሞክራሲያዊ እንቅስቃሴዎች ሲቀዛቀዙ ወይም ሙሉ በሙሉ ሲጠፉ ነው፡፡

የቻለ ይሩጥ ያልቻለ ያዝግም፣ የተቸከለ ይወገድ! የተፈጥሮ መረጣ ሂደትን አስቀጥሎ ህዝብን ማእከል ያደረገ ንቅናቄን መምራት እና እመርታ ማስመዝገብ!

ኢትዮጵያ በዚህ ሰዓት በመስቀለኛ መንገድ ላይ ትገኛለች:: በኢኮኖሚ መስክ መሃከለኛ ገቢ ያላቸውን አገራት ለመቀላቀል ውጤታማ ስራ እየሰራች ሲሆን በዲሞክራሲ ረገድ ግን ፖለቲካዊ ስርዓቱ በከፍተኛ ፍጥነት ወደ ሃላ እያሽቆለቆለ እየነጎደ ይገኛል፡፡ ይህ ተጨባጭ ሁኔታ ማህበራዊ ንቅናቄ (Social Movement) የግድ አስፈለጊ ያደርገዋል፡፡ ሳራሞጎ እንደሚለው ሁኔታዎች ፈላጎትን ይፈጥራሉ፤ ፍላጎቶችም በበቂ ደረጃ ሲጎለብቱ ሁኔታዉን ይፈጥሩታል “The circumstances create the need, and the need, when it is great enough creates the circumstances”. ያለው ሁኔታ ማህበራዊ ንቅናቄን የግድ እሚል ሲሆን ይህ ፍላጎት በብዙዎች ዘንድ ሲስፋፋ ሁኔታውን ሊፈጥር ይችላል። ይህ ማህበራዊ ንቅናቄ ጎላ ያለ ዲሞክራሳዊ ምህዳር ፈጥሮ GTP 2ን ለላቀ የአፈፃፀም ደረጃ እያስኬደ አያይዞም የዲሞክራሲ ተቋማት ተገቢ ሚናቸው እንዲጫወቱ እሚያስችል ይሆናል፡፡

በህወሓት ታሪክ የቻለ ይሩጥ ያልቻለ ያዝግም፣ የተቸከለ ይወገድ (ዝኸአለ ይጉየ፣ ዘይኸአለ ይሳለ ዝተሸኸለ ይታአለ!) በሚል መፈክር ስር የተደረገው ንቅናቄ ህወሓት ትንሽ እና ድሃ ህዝብ ይዞ መላው ህብረተሰብ ያነገበውን አላማ ይዞ እንደየ አቅሙ እንዲሰለፍና የተቸከሉት ደግሞ እንቅፋት እንዳይሆኑ በመከላከል ይህ ንቅናቄ ደርግን ለመጣል በተደረገው ትግል ትልቅ አስተዋፅኦ ነበረው፡፡ ይህ በእሳት ተፈትኖ ውጤታማነቱ በተግባር ያረጋገጠ የንቅናቄ ሂደት ኢህአዴግና መላው ህዝብ ካለንበት ነባራዊ ሁኔታ ጋር አዛምደው ሊጠቀሙበት ይገባል ብየ አስባለሁ፡፡ በአንድ ማህበረሰብ የነበረ ወይም ያለ ልምድ ወደ ሁሉም የኢትዮጵያ ክፍል መዘርጋት የብሄር ብሄረሰቦች እና ህዝቦች እሴቶች ወደ ሁሉም መዘርጋት ስለሚሆን ጥንካሬያችንን ነው እሚገልፀው፡፡ ከምዕራባውያን፣ አሁን ደግሞ ከምስራቁ አለም ብቻ ሳይሆን የሚጠቅመንን አገራዊ ተሞክሮ ሲገኝም ካንዱ የኢትዮጵያ ጫፉ ወደ ሌላው ማስፋፋት ጠቃሚ ተግባር ነው፡፡

እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1915 አንድ የተከፋ ቻይናዊ ሙሁር ወጣቶቹ ወግ አጥባዊ ከመሆን ተላቀው ተራማጅ እንዲሆኑ እንዲህ ሲል መከራቸው “የምድራችን እድገት ወደ ፊት ብቻ እንደሚዘሉ እንደ ሸምጥ ጋላቢ የፈረስ መንጋ ነው፤ ብልሃተኛ ሆኖ ራሱን ከዓለም ጋር መቀየር ያልቻለ ራሱን እሚያገኘው ከዓለም ተወግዶ ነው” (ቴንግ እና ፌየር ባንክ, 1967:242):: ይህ ሙሁር እያረጋገጠል ያለው የሰው ልጅ በጋራ ድርጊት ማድረግ እንዳለበትና ይህም ካደረገ ድርጊቱ የማህበራዊ ለዉጥን እሚያስከትል ተራማጅነት እንደሚፈጥር ነው። ያለንበት ሁኔታ ደግሞ ስር የሰደደ ብልሹ አስተዳደር ያለበትና ይህም ካልተገታ እና መታረም ካልቻለ የከፋ ሰፊ አድጋ ማስከተሉ ስለማይቀር፤ እንዲሁም መላው ኢትዮጵያዉን እያሳመመ ያለ በሽታ በመሆኑ ስፊ ማህበራዊ እንቅስቓሴ ነው እሚያስፈልገው። ለመሆኑ ማህበራዊ ንቅናቄ ምንድን ነው?

ማህበራዊ ንቅናቄ (Social Movement) ምንድን ነው?

ተርነር እና ኪልያን እንደሚሉት በዉን የተመራ ይሁን አይሁን የሆነ ማህበራዊ ንቅናቄ የተፈጥሮ መረጣ ችሮታ ማሳየቱ የተለመደ ነው ይላሉ፡፡ ቀጥለውም ማህበራዊ ንቅናቄ ሰዎች በሚኖሩበት ማህበረሰብ ለውጥን ለማምጣት ወይም ለዉጥን ለመቃወም እሚያደርጉት የጋር ድርጊት ነው ይላሉ።

ላንግስ (1961፡507) በሚገባ እንዳስቀመጠው ማህበራዊ ንቅናቄ ራሱ በማህበረሰቡ ወስጥ ለውጥ ለማምጣት እሚደረግ የጋራ ጥረት ቢሆንም ከንቅናቄው ዉጪ ከሆነው የማህበራዊ ሁኔታዎች መለዎጥን ተከትሎ የሚመጣ ክስተት ነው። ማህበራዊ ለውጥ ማህበራዊ ንቅናቄን ይወልዳል ማህበራዊ ንቅናቄ ደግሞ ማህበራዊ ለውጥ ያስከትላል፡፡ ባጠቃላይ ማህበረሰቡ ላይ የሚታዩ ለውጦች የንቅናቄዎቹን እድገት ላይ የራሳቸው ተፅእኖ ያሳድራሉ፡፡ ሮበርት ላቨር እንደሚለው በትልቅ ማህበረሰብ ዉስጥ ማህበራዊ ንቅናቄን ማጥናት በተረጋጋ ማእቀፍ ዉስጥ እንቅስቃሴን ማጥናት ማለት አይደለም። ይልቁንስ በንቅስቃሴ ዉስጥ ያለን እንቅስቃሴ ማጥናት ማለት ነው። ማህበራዊ ንቅናቄን ስናነሳ ሁለት የተቆራኙና የሚገኛኑ ሂደቶችን ነው እምናየም፤ እነዚህም አንደኛው የንቅናቄው ሂደት ራሱ ሲሆን፣ ሁለተኛ ደግሞ ንቅናቄው በሚንቀሳቀስበት ማህበረሰብ ዉስጥ ያለን እንቅስቃሴ ነው።

በዚህ መረዳት አንፃር ስናየው የጠራ የንቅናቄ አላማ እና ስትራቴጂዎች ተነድፈው ሁሉም ዜጋ እንደየ ፍላጎቱና አቅሙ የበኩሉን ድርሻ እሚወጣበት የዴሞክራሲ ንቅናቄ ማድረግ የ GTP2 ወሳኝ አካል ማድረግ የግድ የሚልበት ሁኔታ ላይ እንገኛለን፡፡ የተቸከለና ያልቻለ በጣም በመቀነስ መሮጥ የቻለውንና እሚችለውን በማብዛት የተማረ ቁርጠኛ ወጣት መሪነቱ እሚያረጋግጥበት እቅስቃሴ መሆን ይገባዋል፡፡ የንቅናቄው አላማም ይህ መሆን አለበት፡፡የተማረ ቁርጠኛ ወጣት ስል የህብረተሰቡን ሁኔታ መቀየር አለበት ብሎ የሚያምን እና ለዚህም የበኩሉን ለማበርከት በፅናት እሚተጋ ማለቴ ነው። ተቋም ማእከል ሳያደርግ የሚካሄድ ንቅናቄ ግን ግዜያዊ የቅሬታ ማስተንፈሻ እንቅስቃሴ ከመሆን ስለማያልፉ ቁልፉ ተግባር መሆን ያለበት ተቋም ማእከል ያደረገ የንቅናቄ እንቅስቃሴ ማድረግ ነው፡፡

ለዚህም ሲባል

1. ዴሞክራስያዊው ንቅናቄ ማሳካት የሚፈልገው አላማ ህዝባዊ አላማ በመሆኑና ያለ ህዝቡ ተሳትፎ እሚሳካ አንዳችም ነገር ስለማይኖር ንቅናቄው ትርጉም ያለው መሆን ካለበት ምልአተ ህዝቡን በሰፊው ማሳተፍ ንቅናቄዉን ለመለኮስ ወሳኝ ድርጊት ነው።ፈጠራ በታከለበት አሰራር የህዝቡን ቀጥተኛ ተሳትፎ ማረጋገጥ ለነገ የሚባል ስራ አይደለም። ህዝቡም ያለበትን ሁኔታ ለማስተካከል ያለው ቁርጠኝነት በተለያየ መንገድ እየገለፀ ስለሚገኝ እሚያሳትፍ መድረክ ካገኝ ለመሳተፍ ዝግጅ ነው። ቼማ (2005) የተባለ ተመራማሪ እንደሚለው ህዝቦች በፖለቲካዊ ሂደቱ ለመሳተፍና በሃገራዊና አካበብያዊ ፖሊሲዎች እና ፕሮግራሞች ተፅእኖ ለማሳደር ሲሉ እሚያደርጉት መደራጀት ብቸኛዉና የላቀ የሰዉን ልጅ ሁኔታ ሊያሻሽል እሚችል ነገር ነው ይለዋል። ሁለም የህበረተሰብ አደራጃጀተች ስምንቱን የመልካም አስተዳድር ባህርያት ከሁኔታቸው አጣጥመው አስተሳሰበቸው አሰራራቸው አስተካክለው ሁነኛ ኣመራሮች መርጠው ክፉኛ የኢ-ዴሞከራሲ ተከታዮች አስወግደው መንቀሳቀስ ይኖረባቸዋለ፡፡ ከላይኛው አካል ጀምሮ በየደረጃው እንቅስቃሴዉን የሚደግፍ ብቃት ባላቸው ኮሚቴዎች እንዲመሩ አጠቃላይ ትላን ወጥቶለት በየግዜው እየተገመገመ የሚሄድ እንቅስቃሴ አመራር ያስፈልገዋል።

2. መንግስት፣ ያገሪትዋ የፖለቲካ ተዋንያን እና ሊሂቃን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና ሌሎች መዋቅሮች ከ ስድሳዎቹ “የኔ መንገድ ብቻ ነው የእዉነት መንገድ” ከሚለው ኃላ ቀር አስተሳሰብ ተላቀው ዘመኑ እና ህገ መንግስታችን የሚፈልጉትን ዴሞክራስያዊ የመቻቻል ባህል ማዳበር እንዳለባቸው ሊገነዘቡ ይገባል። ይህ ለማከናወን እነዚህ አካላት ራሳቸዉን መገምገምና ተጨባጭ ቁመናቸው ትውልዱን እሚመጥን እና እማይመጥኑ መሆናቸው መገንዘብ ይኖራቸዋል። በተለይ ገዢው ፓርቲ ከኢህአዴግ ዉጪ ያሉት ሁሉም አማራጮች የጥፋት መንገድ ናቸው እሚለው አመለካከቱ ማስተካከያ እሚፈልግ መሆኑ ተገንዝቦ አመራሩን እና አባላቱን ወደ ዴሞክራስያዊ ቅኝት ማስገባት መቻል አለበት። ይህ ሃላ ቀር አስተሳሰብ በቅርቡ ገዢው ፓርቲ ‘ከተቃዋሚዎች ጋር አብሬ መስራት እፈልጋለሁ’ ከሚለው ዉሳኔው ጋር ስለሚጋጭ አፋጣኝ እርምት ያስፈልገዋል።

3. ዴሞክራሲ በአንድ ጀምበር እሚዳብር ነገር አይደለም፤ የትውልዶች መወራረስ እሚገነባው ሂደት በመሆኑ መንግስት ቲንክ ታንኮችንና ሙሁራንን ድጋፍ በመስጠት ሰፋፊ የጥናት እና ምርምር ስራዎች እንዲሰሩ ማድረግ። ያለንበት የዴሞክራሲ ሁኔታ፣ መሆን ያለበት እና ሊኖሩን የሚችሉ አማራጮች እንዲሁም ምን በጎ እና አደናቃፊ ሆኔታዎች እንደተጋረጡብን ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ መጠናት ስላለበት መንግስት አገር ዉስጥም ካገር ዉጭም ያለውን ሙሁራዊ አቅም መጠቀም መቻል አለበት።

4. ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (Democratic movement) የሚለውን ሀሳብ በአግባቡ መረዳት፡፡ ይሄ መረዳት ከከፍተኛ አመራር ጭምር ንቅናቄውን ለመግታት ከባድ ጥረት ሊደረግ እንደሚችል መገንዘብ፡፡ በዋናነት እየተመዘገበ ያለውን ኢኮኖሚያዊ ድል ዘላቂ እንዲሆን እና ዴሞክራሲም ለአገራችን የህልውና ጥያቄ በመሆኑ ነው ይህ የታለመው የዴሞክራሲ ንቅናቄ ያስፈለገው፡፡ ሁሉም ተቋማት ራዕይና ተልእኳቸውን እንዲሁም የስነ ምግባር ደንባቸው ላይ ትርጉም ያለው ውይይት እንዲያካሄዱ ማድረግ ህገ መንግስታዊ ተቋማት ህገ መንግስታዊ ድንጋጌዎችን እና ተጨባጭ ተግባሮቻቸውን በማነፃፀር መገምገም፡: ስራ አስፈፃሚ እና ህግ አውጪው (ምክር ቤቶች) የተቋሞቻቸውን ሁኔታ ስርአት እና መስፈርት ያለው ግዜውን የጠበቀ እና ጥርስ ያለው የግምገማ ስርአት ማበጀት:: 

ምክር ቤቶች በተመቻቸው አካሄድ፤ ማለት በተለያዩ ኮሚቴዎች ወይም አንድ ላይ ወይም በደረጃው የሚካሄድ ግምገም በማድረግ ከሀገ መንግስቱ ጋር የሚፃረሩ አስተሳሰቦች ለመቀነስ ፣ አሰራሮች በማስወገድ ከንግዲህ የህዝቡን እዉነተኛ ፍላጎቶች እና ቅሬታዎች ትክረት ስጥተው የሚወያዩበት አሰራር መዘርጋት አለባቸው። ህጉች የሚወጡበት የ ማህተም መቺ አዝማምያ (Rubber Stamp) የሚያስወግዱበት ፤ስራ አስፈፃሚው የመከታተል እና የመቆጣጠር ሃላፊነቱ በኩል የታዩትን ድክመቶች ገምግሞ እንዴት ብለው ተጠናክረው ህገ መንግስታዊ ግዴታቸዉን እንደሚወጡ ማስቀመጥ ይኖርባቸዋል። በተለይ በስራቸው ያሉትን ኮሚሽኖችንና ሌሎች እንደ መንግስት ማስ ሚድያ ያሉ ተቛማትን እነሱ በገመገሙበት መንፈስ እንዲያስተካክሉ መምራት ይጠበቅበታል። ዴሞክራሲያዊ ድባብን የሚያጠቡ ህጎችን ለማሻሻል በቁርጠኝነት መነሳት ይኖርባቸዋል።

ህግ አስፈፃሚው በገንዘብ ታጭቆ፣ ጠበንጃ ታጥቆ፣ ዓለም አቀፍ ፋይናንስ እና ሌሎች ተንተርሶ በመዋቅሩ ደግሞ ሁሉን የህብረተሰብ ክፍል የሚያዳርስ በመሆኑ በዚህ እንቅስቃሴ ልዩ ትኩረት ያስፈልገዋል። ህግ አስፈፃሚው በአገራችን መልካም አስተዳደርን በማንገስና ዴሞክራሲን በማስፈን ልዩ ሚና የሚኖረው ያህል ኢ-ዴሞክራስያዊ ድባብ እንዲያብብ አስተዳደርን በማበላሸት ረገድም ዋና ተዋናይ ይሆናል። ከህግ አዉጪዉም ከህግ ተርጏሚዉም ሲነፃፀር እጅግ ፈርጣማ ነው። ልጏም ካላበጁለት እንደ አባይ ፈረስ ደፍጥጧዋቸው መሄድ እንደሚችል መገንዘብ ያስፈልጋል።

ስራ አስፈፃሚው እጅግ ግዙፍ በመሆኑ ከዋናዎቹ ዘርፎች (Sectors) የተወሰኑትን መርጦ እንደ ሞዴል በመውሰድ በማእከል ገምግሞ ሌሎች ሚኒስቴር መስርያ ቤቶችም በላይኛው ኮሚቴ መሪነት በህገ መንግስቱ እና በሌሎች ህጎች ካላቸው ራዕይ እና ተልእኮ እንዲሁም ከስምንቱ የመልካም አስተዳደር መርሆች አዃያ መገምገም አስፈላጊ ነው።

5. የሲቪል ሰርቪስ ሰራተኞችን ሞራላዊ እና ቁሳዊ ፍላጎታቸውን እንደ አዲስ በማጤን አስፈላጊ ማሻሻያ ማድረግ፡፡የሲቪል ሰርቪስ ሰራተኞች የህዳሴው ግድብ ዓይነት ፕሮጀግቶች የአገራችን የወደፊት ተስፋ እና የኢኮኖሚ ሃያልነታችን ምልክቶች ቢሆኑም፤ ከአጠቃላይ የሰው ሃይል ልማታችን በንፅፅር ሲታዩ አሁንም ፕሮጀክቶቹ በሁለተኛ ደረጃ የሚታዩ ናቸው። ዋናው አቅማችን የሰው ሃይል ስለሆነ።

ከሰው ሃይላችን መሃከል መልካም አስተዳደር በማንገስ ቁልፍ ሚና ሊጫወት የሚችለዉን በንሮ ዉድነት እየተጎሳቆለ፣ በሚረባና በማይረባ ስልጠናና ግምገማ እየተንገላታ፣ እንዲሁም ራሱ ጭምር የመልካም አስተዳደር እጦት ተጠቂ የሆነበት ሁኔታ ይታያል። አገራችን ገና እያደገች በመሆንዋ የልጆችዋን ቁሳዊ ፍላጎት በሚፈለገው መጠን ለሟሟላት እንደሚቸግራት የታወቀ ነው። ለወደፊቱ እድገት ሲባል ሲቪል ሰርቪሱም ጭምር በንሮው መስዋእትነት መክፈሉ የግድ ቢሆንም እና ከፈተኛ መንገዋለል (Dillema)ቢኖርም፤ መንግስት የሲቪል ሰርቪሱ ኑሮ ለመቀየር ስር ነቀል መዉሰድ ይጠበቅበታል።

ሰማንያ ቢልዩን ብር አካባቢ የሚፈልገዉን የህዳሴ ግድብ መስራት ይሻላል ወይስ የሲቪል ሰርቪሱ ቁሳዊ ፍላጎት በመጠኑም ቢሆን ሟሟላት ይሻላል” እሚል የዕብድ የሚመስል (Crazy Idea) ሃሳብ ቢቀርብ የሚያስገርም አይሆንም። “መንግስት ደሞዝ እንደከፈለ ያስመስላል፤ እኛ ሰራተኞችም ስራ እንደ ሰራን እናስመስላለን” እምትለዋ በየስብሰባው እምትነሳ ነገር በመጠኑም ቢሆን መሰረት አለው። እላይኛው አመራር ቢሆንም በቢልየኖች ብር ላይ እየወሰነና እያሰማራ ተገቢ (Decent) የሆነ ኑሮ የሚያስኖረው ገቢ ከሌለው “እኔ ዓይኔን ጨፍኝያለሁ አንተ እንደፈለግከው አድርግ” እንደ ማለት ነው። የታችኛው ሰራተኛ ቢሆንም ከያንዳንዱ ተገልጋይ “ግብር” እንዲያስከፈል “መመርያ” እንደተሰጠው በሚያስመስል መንገድ ሲንቀሳቀስ ማየት የተለመደ ክስተት ሁኗል። ለልማታዊ መንግስት ስኬት አንዱ ወሳኝ ሁኔታም ብቁ እና ቀልጣፋ የሲቪል ሰርቪስ አገልግሎት መሆኑን መርሳት የለብንም።

በአጠቃላይ እየታየ ያለው ዴሞክራስያዊ ድባብ ዉስጥ ሆነው መብታቸው በሚገባ ያልተከበረላቸው የ ሲቪል ሰርቪስ ሰራተኞች በማይረባ ስልጠና እና ግምገማ ሕብረተሰቡን ከማገልገል ተገለው፤ ፍትሃዊ ባልሆነ ግምገማ እና እርምጃ መወሰን የማይችል ፈሪ በሆነበት እና ከብቃት ይልቅ የፓርቲ ታማኝነት ቅድምያ የተሰጠበት ሆኔታ ነው እምንታዘበው። ቁሳዊ እና ሞራላዊ ፍላጎቱ የማይሟላለት የሲቪል ስርቪስ ሰራተኛ ይዞ መሄድ ማለት “መልካም አስተዳደር እንጦርጦስ ግባ” እንደ ማለት ነው እሚቆጠረው።

6. ሚድያዉም መሰረታዊ እሚባሉ የመልካም አስተዳደር እሴቶችን መሰረት አድርገን መገምገም አለብን። ኢቢሲ እና ሌሎች የመንግስት እና የህዝብ ብቻ መሆናቸዉን የሚያረጋግጥ፤ ከኢህአዴግ የፕሮፖጋንዳ መሳርያነት የሚያላቅቅ አሰራር እና የህግ አውጪው ክትትልና ቁጥጥር ያስፈልጋል። ኢቢሲን ብንመለከት ሙሁራን እንዃን ሲጋብዝ በተጠየቁበት ጉዳይ የተናገሩት ደካማ እና ጠንካራ ጎን ሳይሆን፤ ለገዢው ፓርቲ ፕሮፖጋንዳ በሚጥም መልክ ተቆራርጦ እና በፓርቲው ፍላጎት ልክ ተሰፍቶ ነው እሚቀርበው። ጣብያው የተለየ ሃሳብ ሳይሆን የገዢው ፓርቲ ሃሳብ እና ግምገማ እሚያጠናክር ብቻ እየመረጠ በርካታ ሙሁራን ደግመው እማይሳተፉበት ተቛም ለመሆን በቅቷል።

የኢትዮጵያ ህዝብ እንደኔ ብቻ አስብ ወይም ከኔ ሃሳብ ዉጪ መስማት የለብህም ዓይነት እንደምታ ካለው የ መገናኛ ብዙሃኖቻችን አሰራር ተላቀው በሀገሪትዋ ያሉት የተለያዩ ድምፆች መሰማት መቻል አለባቸው። ከነዚህም የተቃዋሚ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች ያላቸዉን አማራጭ ለህዝቡ እሚያቀርቡበት ሁኔታ መመቻቸት መቻል አለበት። በተጨማሪም ከቡር የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ በአዲሱ ምክርቤት መክፈቻ ንግግራቸው ላይ እንዳሳሰቡት የመንግስት እና የህዝቡ መገናኛ ብዙሃን የምርመራዊ ጋዜጠኝነትን መርህ በመተግበር መጥፎ አስተዳደርን በመዋጋት ጂቲፒ 2 በተሳካ ሁኔታ እንዲተገበር የበኩላቸዉን አስተዋፅኦ ማበርከት አለባቸው። በአጠቃላይ ሚድያዉ በአስተሳሰብ እና በአደረጃጀት እንደገና እንዳዲስ መሰራት አለበት፡፡

የግል መልእክት

በቅርብ ግዜ አንድ ሶስት አርቲክል በመፃፌ የተለያዩ አስተያየት ሳሰባስብ ነበር። ለዚህም ሲባል የተወሰኑ ሰዎችን አሰማርቼ ነበር። ሁለቱም አርቲክሎች የትግራይ ህዝብ እንደሌላው የኢትዮጵያ ህዝቦች ለአገሩ ለዓላዊነት የከፈለው መስዋእትነት እጅግ ከፍተኛ ሆኖ ሳለ፤ የደርግን ስርዓት በመደምሰሱ እንደ ከዳተኛ ከሚከሱት ሃይሎች ጥቃት ለመከላከል ያለሙ ሲሆኑ ሌላኛው ደግሞ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ደህንነትና የዉጭ ጉዳይ ፖሊሲ ላይ የምደግፈዉን በመደገፍ ድክመቶችን ለመጠቆም የሞከርኩበት ፁሁፌ ነበር።

የብዙዎቹ ሰዎች ምላሽ ታድያ አወንታዊ እንደነበርና፤ አንዳንድ ሰዎች ደግሞ ጆቤ አቶ ገብሩ አስራትን አስበልቶ ከባለስልጣናቱ ጋር ለመታረቅ ፍልጎ ይሆን እንዴ? የሚሉ ሃሳቦችም እንደ ነበሩ ለዳሰሳ ያሰማሩሃቸው ሰዎች ነገሩኝ። የትግራይ ብሎም የኢትዮጵያ ታሪክ በሚጎድፍበት ግዜ ይህን የመከላከል ሞራላዊ ግዴታ እንዳለኝ እንደሚሰማኝ እና ዋናው ፁሁፌ የአቶ ገብሩ መፅሃፍ ላይ ያነጣጠረ ቢሆንም በኢህአዴግ ያለን የሚታየኝን መሰረታዊ ጉድለቶች ዓቅሜ የቻለዉን ያህል ለመጠቆም መሞከሬን ገለፅኩላቸው። በተጠቀሰው ያለፈው ፁሁፌ አቶ መለስን (ነብሳቸው ያማርና) እና ጄኔራል ሳሞራን መከላከል ያስፈለገዉም የዚሁ የጥቃት ሰለባ በመሆናቸው እና ተነጥለው ስለተጠቁም ጭምር ነው።

ከጄኔራል ሳሞራ በአንጃ ግራንጃ ጉዳይ ብንለያይም፤ አብረን ብዙ ስለሰራን ብንታረቅ ነውር እንደሌለውና ጡረታ ከወጡ በኃላ ቡና ለመጠጣት እና ስላለፈው ጥሩ ግዜ እንድናወራ ብጋብዛቸው ደስ እንደሚለኝ ለዳሰሳ ያሰማሩሃቸው ሰዎችን ነገርኳቸው። ስልጣን ለማግኝት የምሞዳሞድበት ምክንያት እንደሌለኝና ፖለቲካዊነት የህይወቴ አካል ቢሆንም ፕሮፌሽናል ፖለቲከኛ ለመሆን ፍላጎቱም ብቃቱም እንደሌለኝ እንዲሁም ባለኝ ግዜ ለወጣቱ ትውልድ ያለኝ ተሞክሮ በጥናት እየደገፍኩ ማስተላለፍ ከፍተኛ እርካታ እንደሚሰጠኝና ህገ መንግስቱም የታገልኩለት ዓላማ ማሰርያ በመሆኑ እና ካሁን በፊት ከነበረኝ እምነት አሁን ትንሽ ባወቅኩኝ ቁጥር የበለጠ የሚያረካኝ እንደሆነም ገለፅኩላቸው። ህገ መንግስቱ በተገቢ መንፈሱ ሲተረጎም የዓቅሜን ድጋፍ የምሰጠዉን ያህል ሲያኮላሹትም (ከኢህአዴግ ይሁን ከሌላ) የመከላከል ሞራላዊ ግዴታ እንዳለብኝ እንደሚሰማኝም ገለፅኩላቸው።

አመሰግናለሁ::

አበበ ተክለሃይማኖት/ጆቤ (ሜ/ጄ)

መስከረም 29, 2008

ዋቢ ምንጮች

* Adams, Francis, (2003) Deepening Democracy: Global Governance and Political Reform in Latin America (Westport, CT: Praeger, 3,

* Beata Rozumilowicz, “1: Democratic Change,” in Media Reform: Democratizing the Media, Democratizing the State, ed. Monroe E. Price, Beata Rozumilowicz, and Stefaan G. Verhulst (London: Routledge, 2002)

* Belgian Development cooperation DEMOCRATIC GOVERNANCE – THE KEY TO DEVELOPMENT

* Cheema, Shabbir (2005) Building Democratic Institutions: Governance Reform in Developing Countries (West Hartford, CT: Kumarian Press, , 2,

* Eduard Grebe and Minka Woermann, Individual integrity, the institutions of integrity and the integrity of institutions.

* Elihu Katz, “6: Mass Media and Participatory Democracy,” in The Changing Nature of Democracy, ed. Edward Newman and John Keane (Tokyo: United Nations University Press, 1998)

* FDRE Constitution, 1995 Ethiopia.

* Gberevbie, Daniel (2014) “Democracy, Democratic Institutions and Good Governance in Nigeria,” Eastern Africa Social Science Research Review 30, no. 1,

* Democratic Governance

* Democratic Governance – The Key to Development

* Common Principles for Support to Parliaments

* Governance

* Johnson and Robert T. Nakamura. A Concept Paper on Legislatures and Good Governance Based on a Paper prepared by John K. for UNDP July 1999

* Jose Saramago, as cited by Goodwin and Jasper (2004), Rethinking Social Movements, Rowman & Littlefield Publishers, INC, New York

* Kaare Strøm, Wolfgang C. Muller, and Torbjörn Bergman, eds., Delegation and Accountability in Parliamentary Democracies (Oxford, England: Oxford University Press, 2003)

* Larry Diamond,, Jonathan Hartlyn, and Juan J. Linz, “1: Introduction: Politics, Society, and Democracy in Latin America,” in Democracy in Developing Countries, ed. Larry Diamond,, Jonathan Hartlyn, Juan J. Linz, and Seymour Martin Lipset (Boulder, CO: Lynne Rienner, 1999)

* Macquire Dictionary

* Nanda, Ved (Jan., 2006), The “Good Governance” Concept Revisited. The Annals of the American Academy of Political and Social Science Vol. 603, Law, Society, and Democracy: Comparative Perspectives pp. 269-283 Sage Publications, Inc.

* Reporter Magazine Amharic Version Published on 02 September 2015

* Robert H. Lauer, ed., Social Movements and Social Change (Carbondale, IL: Southern Illinois University Press, 1976)

* Robin Creyke, “Integrity in Tribunals,” University of Queensland Law Journal 32, no. 1 (2013)

* Tilly, Charles (2007-04-02). Democracy (Kindle Locations 109-111). Cambridge University Press. Kindle Edition.

* Turner and Killian, 1957: Robert H. Lauer, ed., “Social Movements and Social Change” (Carbondale, IL: Southern Illinois University Press, 1976) UNESCAP

* ዉራይና መበል 19 ሕታም መስከረም 2008 ዓ. ም

* በማስታወቅያ ሚኒስቴር ፕሬስና ኦድዮዚዥዋል መምርያ “በኢትዮጵያ የዴሞክራስያዊ ስርአት ግንባታ ጉዳዮች” 1994 ዓ.ም

* አህአዴግ ‘የዴሞክራሲ መሰረታዊ ጥያቄዎች በኢትዮጵያ’ ለዉይይት የቀረበ ነሓሴ 1992 ዓ.ም

* የኢህአዴግ 10ኛ እና የህወሓት 12ኛ ጉባኤ አጠቃላይ ዉሳኔዎች

*******************

* አበበ ተክለሃይማኖት(ጆቤ) (LLB, LLM and PhD Candidate) የህወሓት/ኢህአዴግ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል የነበሩ፣ ከ1983-1986 የሰሜን ማዕከላዊ እዝ አዛዥ እና በጡረታ እስከ ተሰናበቱበት 1993 ዓ.ም የኢትዮጵያ አየር ሃይል አዛዥ የነበሩ ሲሆን፣ በተሰናበቱበትም ወቅት የሜጀር ጄኔራል ማዕርግ ደርሰው ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሚገኘው የሰላም እና ደህንነት ጥናት ተቛም የዶክትሬት ዲግሪ እያጠኑ ይገኛሉ።

Guest Author

more recommended stories