ቦጫቂና ወጋሚ ጋዜጠኞች – በሞላበትና በመሸበት…

ባለፉት አራት ወራት በኦሮሚያ ክልል የታየው የህዝብ ተቃውሞ ከብዙ ጋዜጠኞች ጋር ለመገናኘት አጋጣሚ ፈጥሮልኛል። በተለይ በታህሳስ ወር የመጀመሪያ ሳምንት በወሊሶ ከተማ ከፍተኛና ያልተጠበቀ የሕዝብ ተቀውሞ ተካሂዶ ስለነበር በዚያ ዙሪያ ወደ ዘጠኝ የሚጠጉ ጋዜጠኞች በስልክና በአካል አነጋግረውኛል። ከእነዚህ ውስጥ ሦስት ጋዜጠኞች ሁኔታውን ለመዘገብ ወደ ወሊሶ መጥተው የነበረ ሲሆን አንዱ ኢትዮጲያዊ፣ የተቀሩት የእንግሊዝ እና የአሜሪካ ዜጋ ነበሩ። ስለሁኔታው ለማጣራት ከነበራቸው ፍላጎት፣ እንዲሁም በተጨባጭ መረጃ ላይ የተመረኮዘ ዘገባ ከማቅረብ አንፃር በሦስቱ ጋዜጠኞች መካከል የጎላ ልዩነት አላየኹም። ከሀብትና ንብረት አንፃር ግን የጎላ ልዩነት እንዳለ ለመታዘብ ችያለሁ።

የዉጪ ሀገር ጋዜጠኞቹ ለክፍለ ሀገር ጉዞ የምትሆን መኪና፣ በጣም ዘመናዊ የሆኑ ኮምፒውተሮች፣ ካሜራዎች፣ የራሳቸው አስተርጓሚ ይዘው በመምጣት በአንድ ትልቅ ሆቴል ውስጥ ነው ያረፉት። እኔ’ም ያረፉበት ሆቴል ድረስ ሄጄ ነው ያነጋገርኳቸው።የሀገር ውስጥ ጋዜጠኛው ደግሞ፣ ያው ብዙዎቻችሁ እንደምትገምቱት፣ ወደ ወሊሶ የመጣው በህዝብ ትራንስፖርት ነበር። እንደ አጋጣሚ ስልኬ ባትሪ ጨርሶ ተዘግቶ ስለነበር፣ እኔን በአካል ለማግኘት መስሪያ ቤት ድረስ ሄዶ የካምፓሱ ፖሊሶች አላስገባ አሉት። ከዚያም ወደ ሰፈር መጥቶ የመኖሪያ ቤቴን ቢጠይቅ የሚጠቁመው ሰው አጣ። በዚህ ምክንያት፣ ከጋዜጠኛው ጋር በአካል ሳንገናኝ ተመልሶ ሄደ።

ከላይ የጠቀስኩት ኢትዮጲያዊ ጋዜጠኛ የሚፅፈው በራሱ ድረገፅ ላይ ነው። አሁን ባለበት ሁኔታ ድረገፁ የብዙ አመታት ልምድ ካላቸው ድረገፆች እና የህትመት ሚዲያዎች አንፃር ድርጅታዊ አቅሙና ተደራሽነቱ አነስተኛ ነው። ሆኖም ግን፣ ጋዜጠኛው ለሞያውና ለሥራው ያለው ከፍተኛ ተነሳሽነትና ቁርጠኝነት የድረገፁን አቅምና ተደራሽነት በአጭር ግዜ ውስጥ እንደሚያሳድገው መገመት ይቻላል።

እነዚህ ትላልቅ የሚዲያ ተቋማት ግን፣ ምንም ያህል የዳበረ ድርጅታዊ አቅም ቢኖራቸውም፣ ያሉባቸው መሰረታዊ ችግሮች መቅረፍ እስካልቻሉ ድረስ መጨረሻቸው ውድቀት ነው የሚሆነው። እነዚህ ተቋማት ያሉባቸውን መሰረታዊ ችግሮች ለማሳየት በባለፈው ሳምንት በመጋቢት 17/2008 የወጣውን የአዲስ አድማስ ጋዜጣ መመልከት ብቻ በቂ ነው።

ሁለቱ የዜና ዘገባዎች በጣም አስገራሚ ናቸው። የመጀመሪያው ዘገባ በኦሮሚያ ስለተፈጠረው ግጭትና በኢንቨስትመንት ላይ ስለሚኖረው አሉታዊ ተፅዕኖ ያትታል። ዘገባው “ፎሬይን ፖሊሲ” (foreign policy) እና “ዘ ኢኮኖሚስት” (the economist) በተባሉ ሁለት የውጪ ሀገር መፅሄቶች ላይ የቀረበን ትንታኔ ወደ አማርኛ በመተርጎም የተሰራ ነው። ነገር ግን፣ ከዜናው ርዕስ ስር “ፀሐፊው” (Written by) አቶ ለማየሁ አንበሴ እንደሆነ ተጠቅሷል።

በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ስለተፈጠረው ግጭትና በኢንቨስትመንት ላይ ስለሚኖረው ተፅዕኖ ተጨባጭ መረጃ እና ትንታኔ መስጠት የነበረበት እዚህ አዲስ አበባ የሚገኘው የአዲስ አድማስ ጋዜጣ ነው ወይስ አሜሪካ ኒውዮርክ የሚገኘው “ፎሬይን ፖሊሲ” መፅሄት? ትንታኔውን የሰሩት፤ “የፎሬይን ፖሊሲ” ተንታኟ “ጄሲ ፎርቲን” እና ስሙ ያልተገለፀው “የዘ ኢኮኖሚስት” ፀሐፊዎች ናቸው። ነገር ግን፣ በግጭቱ ተሳታፊ የሆኑ አካላትን በቀላሉ ማግኘትና በአከባቢው ማህብረሰብ ቋንቋ በቀላሉ ተግባብቶ በግጭቱ መንስዔና መፍትሄ ዙሪያ ትንታኔ መፃፍ የነበረበት አቶ አለማየሁ አንበሴ ወይስ የባዕድ አገሯ “ጄሲ ፎርቲን”? ይህ እንዳለ ሆኖ፣ በጋዜጣው ላይ የአቶ አለማየሁ ድርሻ በእንግሊዘኛ ያነበበውን ወደ አማርኛ ተርጉሞ ማቅረብ ነው። ይህ ከሆነ ደግሞ፣ “ትርጉም-በአለማየሁ አንበሴ” ተብሎ እንጂ፣ በራሱ ባልፃፈው ትንታኔ ላይ “ፀሃፊ” የሚል ካባ ሊደርብለት አይገባም።

ሁለተኛው ዘገባ ደግሞ እጅግ በጣም አስደንጋጭ ነው። “ጋዜጠኝነት በሙስና የተዘፈቀ ነው ተባለ” በሚል የቀረበው ሲሆን ፀሃፊው አሁንም አቶ አለማየሁ አንበሴ ነው። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሽን መምህር በሆኑት በአቶ አሰማኸኝ አስረስ የቀረበን ጥናታዊ ፅሁፍን ዋቢ በማድረግ፣ 83.3% የሚሆኑት የኢትዮጲያ ጋዜጠኞች ለሚሰሩት ዘገባ ገንዘብ ወይም ሌላ ጥቅማ-ጥቅም እንዲሰጣቸው እንደሚፈልጉ የሚገልፅ ነው። ከዚህ በተጨማሪ፣ በጥናቱ ተሳታፊ የሆኑ አካላት ይህን አሳፋሪ ተግባር “ቡጬ” በሚል “የአራዳ” ቃል ሲያቆላምጡት፣ ይህን ፀያፍ ተግባር የማይፈፅሙ ጋዜጠኞችን ደግሞ “ወጋሚ” በሚል የንቀት ስያሜ እንደሚጠሯቸው ተጠቅሷል።

በፅሁፌ መጀመሪያ ላይ የተጠቀሱት ዓይነት፣ ለጋዜጠኝነት ሥራና ሥነ-ምግባር ክብር የላቸው፣ እውነትን ፈልፍሎ ለማውጣትና በተጨባጭ መረጃ ላይ የተመሰረተ ዜና ለመስራት የሚጥሩ ጋዜጠኞች ብዛት ከቁጥር አይገባም። ለሥራና ሞያቸው ተነሳሽነት የነበራቸው ከፊሉ አሁን ያሉት በስደት አሊያም እስር ቤት ነው። አብዛኛው የሕብረተሰብ ክፍል፣ በተለይ በከተማው ማህብረሰብ ዘንድ የመንግስት ባለስልጣናትን “ሌባና ሙሰኛ” ይበል እንጂ፣ እያንዳንዱ ግለሰብ አጋጣሚውን ሲያገኝ ራሱ ሌባና ሙሰኛ ሆኖ ይገኛል። ባላሰልጣናቱም ያለ ማህብረሰቡ የሞራል ድጋፍ እንዲህ ቅጥ-ያጣ ሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነት ውስጥ ሊዘፈቁ አይችሉም። ከዚህ’ም ይባስ ብሎ፣ ስለ ሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነት የሕብረተሰቡን ንቃተ-ህሊና ያዳብራል የተባለው ጋዜጠኛ ራሱ “በሙስናና የጥቅም ሱስህሊናው ታውሮ እውነትና ዕውቀትን ማየት ተስኖታል” ሲባል ምን ይባላል?

አንዳንድ ሰው “አሁን ጋዜጠኞች ለሚዘግቡት ዘገባ፣ ያውም ደግሞ በአብዛኛው ከግል ተቋማት ገንዘብና ጥቅማ-ጥቅም መፈለጋቸው ይሄን ያህል የሚጋነን አይደለም?” ሊል ይችላል። በእርግጥ ይሄ የሀገራችንን ነባራዊ ሁኔታ ካለመረዳት የመነጨነ ነው። እስኪ እንደው የመንግስት ሚዲያዎችን በትኩረት ለመታዘብ ሞክሩ። በአብዛኞቹ የመንግስት ተቋማት የሚሰጡ መግለጫዎች በውሸትና ግነት የታጨቁ ናቸው። በግሉ ዘርፍ ደግሞ ለጋዜጠኞች ጉቦና ጥቅማ-ጥቅም የሚውል “በጀት” እስከ መመደብ የደረሱ ተቋማት እንዳሉ ከላይ በተጠቀሰው ጥናት ተረጋግጧል። መደበኛ ሥራውን በመስራቱ ገንዘብና ጥቅማ-ጥቅም ያገኘ ጋዜጠኛ ከሚውጠው በላይ የጎረሰ ነው። ከሚውጠው በላይ የጎረሰ ሰው እውነትን መናገር አይችልም። እና ታዲይ፣ የግል ተቋማት በገንዘባቸው፣ የመንግስት ተቋማት በስልጣናቸው ውሸትና ግነትን የሚግቱን ከሆነ መጨረሻችን ምን ሊሆን ነው።

በዚህ በኪራይ ሰብሳቢነት በናወዘ ማህብረሰብ ውስጥ፤ ውሸትና ሌብነት እንደ መልካም ዕሴት ይወሰዳል፣ ሃቀኝነትና የሞያ ሥነ-ምግባር እንደ ኋላቀርነት ይቆጠራል። እውነትና እውቀት ዋጋ ያጣሉ። በእርግጥ ሃቀኝነት የህሊና ዕረፍት እንጂ ቁሳዊ ጥቅም የለውም። የእውነትና ዕውቀት ሽልማቱት የሞራል የበላይነት ነው። “እውነትን ተናግሮ የመሸበት ማደር” የሚሉ “ወጋሚዎች” ለሞያቸው ሆነ ለራሳቸው ክብር የሚሰጡ፣ ከፍተኛ የሞራል የበላይነት ያላቸው ጋዜጠኞች ናቸው። በሚያውቋቸው ሰዎች ዘንድ ክብር ይኖራቸዋል፣ ከፀፀት የፀዳ ህሊና ስላላቸው ወደ ፈለጉት ሄደው፥ በመሸበት ያድራሉ። በአንፃሩ “ውሸትን ተናግሮ የመሸበት ማደር” የሆኑት “ቦጫቂዎች” ግን፣ እንደ ቁስ በገንዘብ የሚገዙና የሚሸጡ፣ ጥቅም ከሞላበት ቤት ደጃፍ የማይጠፉ ተራ የጥቅም ሱሰኞች ናቸው።

******

Seyoum Teshome is a Lecturer at Ambo University Woliso Campus and head of Management Department. He was born in Arsi, Assela, in 1979 and studied Management at Harameya University and MBA at Mekelle University. He also blogs at http://ethiothinkthank.com

more recommended stories