ልዩነት እና ተመሣሣይነት| ፍቅር ጥናት ምርምር በአስተርጓሚ

ባለፈው ክፍል “ባርነትን ሳያውቁ ነፃነትን የሚናፍቁ ህዝቦች” በሚል ርዕስ ባቀረብኩት ፅሁፍ አብዛኞቹ የአፍሪካ ሀገራት አስተሳሰብ ባርነት (Conceptual Colonization) ስር እንዳሉ ለማሳየት ሞክሬያለሁ። የኢትዮጲያ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የጥናትና ምርምር ሥራና አሰራርን እንደመነሻ በመውሰድ በሀገሪቱ ያለውን የሥነ-ዕውቀት ቀውስ (Epistemological Crisis) ለማሳየት እሞክራለሁ። በዋናነት በማህበራዊ ሣይንስ ዘርፍ የከፍተኛ ት/ት ተቋማት መምህራንና ተመራማሪዎች፣ እንዲሁም የሁለተኛ ድግሪ ተማሪዎች የሚሰሯቸው ጥናታዊ ሥራዎች ከተደራሽነት፣ ስርፀት፣ እና ውጤታማነት (ችግር-ፈቺነት) አንፃር ያለባቸው ውስንነት እንዴት ከእንግሊዘኛ ቋንቋ ጋር በቀጥታ የተያያዘ እንደሆነ እንመለከታለን።

በኢትዮጲያ የከፍተኛ ት/ት ተቋማት ብዛት ወደ 33 አድጓል፣ የመምህራን እና ተማሪዎች ቁጥር በብዙ እጥፍ ጨምሯል። እየታየ ያለው አንፃራዊ የመሰረተ-ልማቶች ግንባታና መሻሻል ለብዙ የሀገሪቱ ዜጎች የከፍተኛ ትምህርት ዕድል እንዲያገኙ አስችሏቸዋል። የጥናት እና ምርምር ሥራ የተቋማቱ ዋና የሥራ ሂደት እንደመሆኑ በዘርፉ የሚሰሩ ሥራዎችን ብዛት፣ ዓይነትና ጥራት እንደሚያሳድገው እሙን ነው።

ለምሳሌ ከ1996 እስከ 2014 ድረስ ባለው ግዜ ውስጥ በኢትዮጲያዊያን ተሰርተው በታዋቂ ጆርናሎች የታተሙ ሥራዎች ብዛት 10,866 ነው። በተመሳሳይ ግዜ ውስጥ ደቡብ አፍሪካ 155ሺህ፣ ናይጄሪያ 51ሺህ፣ እንዲሁም ጐረቤታችን ኬኒያ 20ሺህ ሥራዎችን አሳትመዋል። ከዚህ አንፃር ሲታይ የኢትዮጲያ ድርሻ በጣም ዝቅተኛ ነው። ሆኖም ግን፣ በቅርብ ዓመታት ውስጥ የሀገሪቱ የከፍተኛ ትምህርት መስፋፋት ጋር ተያይዞ የታየው ለውጥ አመርቂ ሊባል የሚችል ነው። ለምሳሌ፦ ከ1996-2005 ድረስ 2766 ሥራዎች፣ በአማካይ 276.6 ሥራዎች ታትመዋል። ከ2006 – 2014 ባለው ግዜ ውስጥ ግን በድምሩ 8100 የታተሙ ሲሆን በአማካይ 900 ሥራዎች በአንድ አመት ታትመዋል።

ከላይ ለማሳየት እንደተሞከረው፣ በኢትዮጲያዊያን የሚሰሩ የጥናትና ምርምር ሥራዎች ብዛትና ዓይነት በፍጥነት እያደገ መሆኑንና ለጥናትና ምርምር ሥራዎች ትኩረት መሰጠቱን ያሳያል። ነገር ግን፣ በዘርፉ ዘላቂ የሆነ ለውጥና እድገት ሊመጣ የሚችለው ሥራዎቹ የላቀ ጥራትና ውጤታማነት ሲኖራቸው ነው። በመሆኑም፣ በሀገራችን የሚሰሩ የጥናትና ምርምር ሥራዎች፤ አዳዲስ ግኝቶችና ፈጠራዎች እና ሥራና አሰራርን የሚያሻሽሉ ዜዴዎች በማበርከት ለተለያዩ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና አከባቢያዊ ችግሮች ዘላቂ መፍትሄ መስጠት መቻል አለባቸው። በዚህም ተጠቃሚ ሊሆን የሚችለውን የሕብረተሰብ ክፍል በከፍተኛ ትምህርት ዕድል ተጠቃሚ ከሚሆነው በእጅጉ የላቀ ነው።

Chart - Research Country Ranking Ethiopia 1996-2014

ነገር ግን፣ የሀገሪቱን ልማትና እድገት በማስቀጠሉ ረገድ የሚጠበቅባቸውን ሀገራዊ ፋይዳ እንዲወጡ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚሰሩ ጥናትና ምርምሮች ‘ተግባር-ተኮር፣ ችግር-ፈቺ እና ተደራሽ ናቸው’ ብሎ ለማለት አያስደፍርም። የጥናትና ምርምር ሥራዎቻችን ትክክለኛውን መረጃ በመሰብሰብና ሞያዊ ትንታኔ በመስጠት የሚገኘው መረጃና ዕውቀት መሰረት በግለሰብ ሆነ በማህብረሰብ ደረጃ ላሉ ችግሮች መፍትሄ ማምጣት ካልቻልን፣ በእኛ እና በሌሎች ሕይወት ላይ እሴት መጨመር ከተሳነን፣ እንደ ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን አገላለፅ “መማራችን መሰልጠን ሳይሆን መሰይጠን ነው”።

የሀገሪቱ የከፍተኛ ትምህርት ፖሊሲ ሆነ የተቋማቱ ሥራና አሰራር በሀገራችን ካለው ነባራዊ እውነታ አንፃር ሳይሆን በምዕራባዊያንን እምነት፣ እሳቤና እሴት ላይ የተቃኘ ነው። በማህበራዊ ሣይንስ ዘርፍ የሚሰሩ ጥናቶች በሙሉ በ’አባሪነት’ የሚያይዙት ‘የመጠይቅ ቅፅ’ የችግሩ ዋና መገለጫ ነው።

የመጠይቅ ቅፅ (Questionnaires) የጥናትና ምርምር ሥራው በግብዓትነት የተጠቀመውን ሃሣብ፣ አስተያየት፣ መረጃ፣ አመለካከት፣…ወዘተ ለመሰብሰብ የሚውል ነው። በጥናቱ መፍትሄ ስለሚሰጠው ‘ማህብረሰባዊ ጉዳይ/ችግር’ መረጃ ለመሰብሰብ እንዲቻል የጥናቱ ተሣተፊዎች በሚናገሩት ’ቋንቋ’ ይተረጎማል። ለዚህ ሲባል፣ መጠይቆች በመጀመሪያ በእንግሊዘኛ ከተዘጋጁ በኋላ እንደ አከባቢው ወደ አማርኛ፣ ኦሮምኛ፣ ትግሪኛ ወይም ሌሎች የሀገራችን ቋንቋዎች ይተረጎማሉ። ይሁን እንጂ፣ በጥናቱ ተሳታፊዎች ከሚሞላው መጠይቅ በስተቀር ያለው የጥናታዊ ወረቀቱ ይዘት፦ የጥናቱ ንድፈ-ሃሳብ፣ አላማና ግቦቹ፣ የሥራ መረሃ-ግብሩ፣ የተሰበሰበው ጥናታዊ መረጃ ትንታኔና ውጤት፣ እንዲሁም ተመራማሪው በጥናቱ መሰረት የሚያቀርበው ማጠቃለያ እና የመፍትሄ/ውሳኔ ሃሣብ፣…ወዘተ ሁሉም በእንግሊዘኛ ቋንቋ ነው የሚቀርበው።

በሁሉም የሀገሪቱ የከፍተኛ ት/ት ተቋማት ውስጥ የተለመደና ተቀባይነት ያለው አሰራር፣ ይህ በሀገር ቤት ቋንቋ ጠይቆ – በባዕድ ሀገር ቋንቋ የሚመልስ አሰራር እንዴት ሆኖ ነው ውጤታማና ችግር-ፈቺ የሚሆነው? በአፋርኛ ሆነ ሶማሊኛ ወይም ሲዳሚኛ፣ ትግርኛ፣ ኦሮምኛ፣ አማርኛ፣ አገውኛ፣ ወይም ሌላ ቋንቋን ለመጠየቅ እንጂ ውጤት እና መፍትሄውን ለመንገር የማይጠቀም አሰራር ይዘን እንዴት ስርፅትና ተደራሽነትን ማሳደግ ይቻላል? በአጠቃላይ፣ በአፍ-መፍቻው ቋንቋው “ችግርህ ምንድነው? ሃሳብ፥ አስተያየትህ…?” ብሎ ጠይቆ፣ ምላሹን እንደ ግብዓት ተጠቅሞ ካጠናና ከመረመረ በኋላ ውጤቱን ህዝቡ ማንበብና መፃፍ በማይችለው ቋንቋ ፅፎና ጠርዞ በቤተ-መፅሃፍት እና በቢሮ መደርደሪያ ላይ የሚያከማች አሰራር በፍፁም ተግባር-ተኮር አይደለም፣ ችግር-ፈቺ ሊሆን አይችልም።

እ.አ.አ በ2007 ዓ.ም የህዝብና ቤት ቆጠራ መሰረት ከኢትዮጲያ ህዝብ ውስጥ ማንበብና መፃፍ የሚችለው 39%ቱ ብቻ ነው። ስለዚህ፣ 61%ቱ ህዝብ በአፍ-መፍቻ ቋንቋው እንኳን ከመስማትና መናገር አልፎ ማንበብና መፃፍ አይችልም። እንኳን የቀበሌ፣ የወረዳና የዞን ቢሮ ኃላፊዎች፣ …ከፍተኛ የክልልና የፌድራል ኋላፊዎች እንኳን በእንግሊዘኛ መግባባት በማይችሉባት ሀገር የጥናትና ምርምር ሥራዎቻችንን በዚህ ቋንቋ የምናዘጋጅበት ምክንያት ምንድነው?

‘በሥራዎቻችን ለአለም አቀፉ ማህብረሰብ ተጨማሪ ዕውቀት እናበረክታለን፣ ወይም በሥራዎቻችን ለእንግሊዘኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች ተደራሽ ለማድረግ ነው’ እንዳይባል እነሱ የጥናትና ምርምር ሥራዎች እጥረት የለባቸውም። ለምሳሌ እ.አ.አ. በ2014 ብቻ አሜሪካ 495,000፣ እንግሊዝ 141,000 የጥናትና ምርምር ሥራ ውጤቶችን በታወቁ ጆርናሎች ላይ አሳትመዋል። በተመሣሣይ አመት ኢትዮጲያ በ1,490 የጥናትና ምርምር ሥራዎችን በማሳተም ከአፍሪካ 7ኛ፣ ከአለም 75 ደረጃ ላይ ትገኛለች። ኢትዮጲያ በ19 ዓመታት (1996 – 2014) ውስጥ ያሳተመቻቸው የጥናትና ምርምር ሥራዎች (10,866) ደቡብ አፍሪካ በአንድ ዓመት ካሳተመቻቸው 16,000 ባጣም ያነሰ ነው።

በእንግሊዘኛ ቋንቋ በሚገባ ሃሳቡን መግለፅ የማይችል ተመራማሪ መጠየቅን በእንግሊዘኛ አዘጋጅቶ፣ ከእንግሊዘኛ ወደ ሀገርኛ ቋንቋ ተርጉሞ፣ በተሳታፊዎች የተሰጠውን ምላሽ ወደ እንግሊዘኛ ተርጉሞ፣ ውጤቱን አብዛኛው የሕብረተሰብ ክፍል ሊናገርው፣ ሊያዳምጠው፣ ሊያነበው ሆነ ሊፅፈው በማይችለው ቋንቋ የሚቀርብበት ሥራና አሰራር… በቀጥታ መናገር፣ ማዳመጥ፣ ማንበብና መፃፍ እየተቻለ በትርጉም የሚናገር፣ የሚያዳምጥ፣ የሚያነብና የሚፅፍ… ይሄ ነው የደንቆሮዎች ጫጫታ፣ የስውሮች ግርግር፣ …::
**************

Seyoum Teshome is a Lecturer at Ambo University Woliso Campus and head of Management Department. He was born in Arsi, Assela, in 1979 and studied Management at Harameya University and MBA at Mekelle University. He also blogs at http://ethiothinkthank.com

more recommended stories