ልዩነት እና ተመሣሣይነት|ባርነትን ሳያውቁ ነፃነትን የሚናፍቁ ህዝቦች

“ብራቮቮቮ…!” ብዬ ስጮህ፣ ሁሉም መምህራን በአግራሞት ይመለከቱኝ ጀመር። ከዛ… አንዱ መምህር ምን እንዳስደሰተኝ ሲጠይቀኝ የሰጠሁት ምላሽ ግን የሁሉንም አስተያየት በቅፅበት ከአግራሞት ወደ ግራ-መጋባት ቀየረው። ሁሉም፣ “ሁለት የአፍሪካ አገሮች ከእንግሊዝ ቅኝ-ግዛት ሙሉ-በሙሉ ነፃ ወጡ!” የሚለውን ምላሽ አልጠበቁም። እንኳን እነሱ፣ በአሁኗ ቅፅበት ራሱ “እስካሁን በቅኝ-አገዛዝ ሥር ያለ ሀገር አለ እንዴ?…” የሚል ሃሳብ በእናንተ አዕምሮ ውስጥ እየተመላለሰ ነው።

የፅሁፉን ፅንሰ-ሃሳብ በደንብ መረዳት የሚሻ አንባቢ በቅድሚያ “የቅኝ-አገዛዝ ሥርዓትን በሃይል አሸንፋና ነፃነቷን አስከብራ የኖረች ብቸኛዋ አፍሪካዊ ሀገር…” የሚለውን የውሸት ቀረርቶ ከአዕምሮው ውስጥ ማውጣት አለበት። እያንዳንዱ ኢትዮጲያዊ በዚህ ጉዳይ ላይ ምክንያታዊ ግንዛቤ እንዲኖረው ከፈለገ በመጀመሪያ በልጅነት ዘመኑ የሰማውን ተረት-ተረት እውነት አድርጎ ማሰቡን ማቆም አለበት።

ኢትዮጲያን ጨምሮ ሁሉም የአፍሪካ ሀገራት በቅኝ-አገዛዝ ሥርዓት ስር ወድቀዋል። እዚህ’ጋ፣ የአምስት አመቱ የፋሽስት ኢጣሊያ ወረራን እንደ ቅኝ-አገዛዝ ሥርዓት ወስጄው ከመሰላችሁ ተሳስታችኋል። የኢጣሊያን ወረራ ከቅኝ-አገዛዝ ሥርዓት ቀዳሚው ተግባር ቢሆንም፣ በሀገራችን አርበኞች ትግልና መስዋዕትነት አገዛዙ የመጀመሪያውን ደረጃ እንኳን ማለፍ የተሳነው ነበር። ታዲያ…በኢትዮጲያ ላይ የቅኝ-አገዛዝ ቀንበር የጣለው ማን ነው? መልሱ እኛ…አዎ እኛው ራሳችን ነን! እኛው ራሳችን በምዕራባዊያ የቅኝ-አገዛዝ ቀንበር ውስጥ አንገታችንን አስገብተን፣ የቀንበሩን ማነቆ አጥብቀን ያሰርነውም እኛው ራሳችን ነን። እንዴት፣ ለምንና መቼ የሚሉ ጥያቄዎችን ለመመለስ በቅድሚያ ስለቅኝ-አገዛዝ ሥርዓት ግልፅ የሆነ ግንዛቤ ሊኖረን ይገባል።

Photo - Julius Nyerere
Photo – Julius Nyerere

አብዛኞቹ የአፍሪካ ልሂቆች እና የቅኝ-አገዛዝ ሥርዓት ታጋዮች እንደሚገልፁት፣ እንደ ፖርቹጋል፣ እንግሊዝና ፈረንሳይ ያሉ የቅኝ ግዛት ሃይሎች በአፍሪካ የዘረጉት ሥርዓት በዋናነት ሁለት ደረጃዎች ነበሩት። የመጀመሪያው አካላዊ አገዛዝ (Physical Colonialism) የሚባለው ሲሆን አንድን ሉዓላዊ ሀገር ወይም ግዛት በወታደራዊ ሃይል መቆጣጠርና የራስን አስተዳደራዊ ሥርዓት መዘርጋት ነበር።

በሁለተኛ ደረጃ ላይ ያለው ደግሞ፣ የተዘረጋውን አስተዳደራዊ መዋቅር በመጠቀም ህዝቡ ለዘመናት ያካበተውን ባህላዊ ትውፊት፣ እሴት፣ እውቀት፣…ወዘተ ሙሉ-በሙሉ በማውደም ሥርዓቱን የሚቃወም አስተሳሰብ እና የሞራል ስብዕና ከሕብረተሰቡ ውስጥ ተሟጦ እንዲጠፋ ማድረግ ነው። በቅኝ-አገዛዝ ዘመን ፍፁም ተገዢና ጥገኛ የሆነ ሕብረተሰብ የተፈጠረበት ሂደት የአስተሳሰብ ባርነት (Conceptual Colonization) ይባላል። ይህ’ም ቅኝ-ገዢዎች በጦር መሳሪያ የተቆጣጠሩት ህዝብ የራሳቸውን ሥርዓተ-ትምህርት በራሳቸው ቋንቋ እንዲማር በማድረግ ነው።

በዚህ ፅሁፍ፣ ስለችግሩ ስፋትና ጥልቀት ከመጠቆም፣ ዝርዝር ትንታኔ ለመስጠት አመቺ አይደለም። ስለዚህ፣ በቅኝ-አገዛዝ ሥርዓት የተዘረጋውና እስከሁኑ የ21ኛው ክ.ዘመን ድረስ በአፍሪካዊያን ላይ ተጭኖ ስላለው የአስተሳሰብ ባርነት እና የዕውቀት ጥገኝነት በግልፅ ለመረዳት የሚያስችሉ ጥናታዊ ሥራዎችን በመጠቆም ማለፉ የተሻለ መስሎ ይሰማኛል። በጉዳዩ ዙሪያ ጥልቅ ትንታኔ ከሚገኝባቸው ሥራዎች ውስጥ፤ የቀድሞው የታንዛኒያ ፕረዘዳንት “Julius Nyerere (1968): “Education for Self-Reliance“፥ በጋናዊው ፈላስፋ “Kwasi Wiredu” በ”Conceptual Decolonization” ዙሪያ የተፃፉ ፅሁፎች፥ Abdi A. (2006): “Eurocentric Discourse and African Philosophies and Epistemologies of Education“፥ Nyamnjoh F. (2004): “A Relevant Education for African Development-some Epistemological Considerations“፥ እና የመሳሰሉት ይገኙበታል።

እርግጥ ነው፣ ለአንዳንዶቻችን በራስ ቋንቋ መማር-ማስተማርን ከቅኝ-አገዛዝ ሥርዓት ነፃ ከመውጣት ጋር ያለው ቁርኝት ጎልቶ ላይታይን ይችላል። ይህ ግን ስለቋንቋ ካለን የተዛባ እሳቤ፣ እንዲሁም፣ ስለቅኝ-አገዛዝ ሥርዓት ካለን ቁንፅል ግንዛቤ የመነጨ ነው። በመሰረቱ፣ ቋንቋ መግባቢያ ብቻ አይደለም። ከመግባቢያነት አልፎ እውነታን የምንገነዘብበት፣ የምናገናዝብበት እና የምንረዳበት ተፈጥሯዊ ክህሎት ነው። ስለዚህ፣ ከመግባቢያነት ባለፈ ሰው በቋንቋው ይገነዘባል፥ ያስባል።

አፍሪካዊያን በአስተሳሰብ ባርነት ውስጥ የወደቁት ቅኝ-ገዢዎች የራሳቸውን ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች የሚዳስስ፣ በራሳቸው ቁስ-አካላዊ እና ሃሳባዊ ውስን እሳቤና ግንዛቤ ላይ የተመሰረተ፣ የራሳቸውን እምነት፣ አመለካከትና እሴት ብቻ በሚያንፀባርቅ መልኩ በራሳቸው ቋንቋ ያዘጋጁትን ሥርዓተ-ትምህርት በህዝቡ ላይ በመጫን ነው። አስተማሪው ከነባራዊ እውነታ ጋር የማይገናኝ፥ በንድፈ-ሃሳብ (በቲዎሪ) ደረጃ ብቻ የሚያውቀውን ውስን ዕውቀት፣ ለተማሪዎቹ በማይገባቸው ቋንቋ እንዳይገባቸው አድርጎ እያስተማረ ባለበት ሁኔታ ምን ዓይነት ዕውቀትና ክህሎት እንዲቀስሙ ይጠበቃል?

ከላይ በተገለፀው መሰረት፣ እስከዚህ ዓመት ድረስ ሙሉዕ የሆነ ነፃነቷን መቀዳጀት የቻለች፤ አካላዊ ቅኝ-አገዛዝን በማስወገድ ሉዓላዊነቷን ያረጋገጠች፣ የዜጎቿን ዕውቀትና የሞራል ስብዕናን ከአስተሳሰብ ባርነት ነፃ ያወጣች አንድና ብቸኛ አፍሪካዊት ሀገር “ታንዛኒና” ነች። ከላይ ለማጣቀሻነት የተጠቀሰው የቀድሞው ፕረዘዳንት ጥናታዊ ሥራ የታንዛኒያ የትምህርት ፖሊሲ ሆኖ በማገልገል ሀገሪቱ ነፃ ከወጣችበት ግዜ ጀምሮ የስዋህሊኛ ቋንቋን በሁሉም የትምህርት ደረጃዎች የማስተማሪ ቋንቋ እንዲሆን ተደርጓል።

ለዚህ ፅሁፍ መነሻ የሆነኝና በመግቢያው ላይ የጠቀስኩት አስደሳች ዜና “የጋና ትምህርት ሚነስቴር ሚኒስትር Prof. Jane Naana Opoku-Agyeman ቢቢሲ ባዛጋጀው ፓነል የውይይት ላይ ሀገራቸው የእንግሊዘኛ ቋንቋን በሁሉም የትምህርት ደረጃዎች የማስተማሪያ ቋንቋ መሆኑ እንዲያበቃ መወሰኗን አስታወቁ” የሚለው ነው። የ”allAfrica.com” ድህረ-ገፅ ጥቅምት 30/2015፣ የጋናን ውሳኔ ተከትሎ በሳምንቱ ዝምባብዊም ተመሳሳይ ማስተላለፏን ዘግቧል። በድህረ ገፁ ላይ “Dr Charles Mubita” የተባሉ ፀሃፊ “Indigenous Languages Are Fundamental to Development” በሚል ርዕስ የሰጡትን ጥልቅ ትንታኔ በዚህ ሊንክ ማንበብ ይቻላል።

“የአፍሪካ የነፃነት ምልክት” እያልን የምናቆለጳጵሳት “ሀገራችን ኢትዮጲያ’ስ?” የሚል ጥያቄ መነሳቱ አይቀርም። ከላይ በዝርዝር ለመግለፅ እንደተሞከረው የቅኝ-አገዛዝ ሥርዓት ሁለት ዓይነት ደረጃ አለው። በአንድ በኩል ኢትዮጲያ የተቃጣባትን አካላዊ-አገዛዝን (Physical Colonialism) በሃይል በመመከት ከሁሉም የአፍሪካ ሀገሮች የተለየች ያደርጋታል። በሌላኛው በኩል ደግሞ ኢትዮጲያ የአስተሳሰብ ባርነትን “Conceptual Colonialism” በራሷ ፍቃድና ምርጫ በህዝቦቿ ላይ የጫነች ብቸኛ ሀገር ናት። (በኢትዮጲያ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ በዝርዝር የሚያሳይ፣ በኢትዮጲያ የከፍተኛ ተቋማት የጥናትና ምርምር ሥራና አሰራርን እንደ ማሳያ በመውሰድ “ፍቅር-ጥናት-ምርምር በአስተርጓሚ…” በሚል ርዕስ የተዘጋጀ ፅሁፍ በሚቀጥለው ክፍል እንደሚቀርብ ከወዲሁ እጠቁማለሁ)

በቅኝ-አገዛዝ ቀንበር ሥር የነበሩ ሀገራት፣ ቢያንስ የቅኝ-ገዢዎች ሥርዓተ-ትምህርት እና ቋንቋ የአስተሳሰብ ባርነት መሣሪያ እንደሆነ ከተገነዘቡ ቆይተዋል። የደቡብ ኮሪያው ፕረዘዳንት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት “እኛ (ኮሪያ) በቅኝ-አገዛዝ ስር ወድቀን ነበር። ኢትዮጲያ ግን አልወደቀችም። አሁን ግን እኛ ሥርዓተ-ትምህርት የምንቀርፀው በራሳችን ቋንቋ ነው። የእናንተ ግን አይደለም…” በሚል የሰጡት አስተያየት እንደ ሀገር ሊያነቃን ይገባ ነበር። አሁንም የጋና የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር “አፍሪካ ከድህነት አረንቋ እንድትወጣ ጥራትና አግባብነት ያለው ትምህርትን በትክክለኛው መንገድ በማቅረብ ላይ ትኩረት ልታደርግ ይገባል” በማለት የእንግሊዘኛ ቋንቋን የማስተማሪያ ቋንቋ ሆኖ እንዳይቀጥል ያደረጉበትን ምክንያት አስረድተዋል።

ይሁን እንጂ፣ ራሱን ለባርነት አሳልፎ የሰጠ ሀገርና መንግስት የጭቆና ቀንበር አይከብደውም፣ የባርነት ማነቆ አይሰማውም። የችግሩ ገፈት ቀማሽ የሆኑት እንደ ታንዛኒያና ጋና ያሉ ሀገራት የእንግሊዘኛ ቋንቋ የእንግሊዝ የቅኝ-አገዛዝ ሥርዓት ማስፈፀሚያ መሳሪያ መሆኑን አውቀው ራሳቸውን ከአስተሳሰብ ባርነት ነፃ ሲያወጡ፣ ራሳችንን ለባርነት አሳልፈን በሰጠነው ኢትዮጲያኖች ዘንድ እንግሊዘኛ አሁንም የዕውቀትና ዘመናዊነት ስብዕና መገለጫ ሆኖ እያገለገለ ይገኛል። የደቡብ ኮሪያ፣ ታንዛኒያ፣ ጋናና ዝምባብዌ የትምህርት ፖሊሲ ለውጥ የሚያሳየው ነገር ቢኖር፣ በቅኝ-አገዛዝ ሥርዓት ጭቆና ስር ወድቀው የባርነትን ገፈት የቀመሱ ህዝቦች ነፃነትን ሲናፍቁ፣ እኛ ግን በባርነት ስብዕና የምንመፃደቅ መሆናችንን ነው።

“ልዩነት”፦ ልዩ መሆን፣ …ራስን መሆን፣ ራስን መቻል ነው። “ተመሣሣይነት”፦ መሳይ፣ አስመሳይ፣ መምሰል ነው። እኛ ኢትዮጲያዊያን፣ … ልዩነት ያስፈራናል፣ መምሰል ይቀለናል። ከራሳችን ይልቅ የሌላ ይመቸናል። እኛን የሚመስል ሳይኖር ሌላን ለመምሰል እንታትራለን። ልዩነታችንን ማድነቅ ተስኖን ከፈረንጅ ለመመሳሰል አብዝተን ተጋን። እነሱ በጦርነት መጫን የተሳናቸውን ባርነት፣ እኛ በትምህርት ተማርነው። እኛው-በእኛ ላይ የጫነው የባርነት ቀንበር ለእኛ አይታየንም፥ አይሰማንም፥ አይከብደንም…። አዎ… የነፃነትን ትርጉምና ፋይዳ አናውቅም፣ ባርነትን የሚፀየፍ ስብዕና የለንም። እርግጥ ነው፣ እኛ ኢትዮጲያዊያን ባርነትን አናውቅም፣ ነፃነት አይናፍቀንም!!!

**********

Seyoum Teshome is a Lecturer at Ambo University Woliso Campus and head of Management Department. He was born in Arsi, Assela, in 1979 and studied Management at Harameya University and MBA at Mekelle University. He also blogs at http://ethiothinkthank.com

more recommended stories