አርሶ-አደርን ከመሬቱ ከማስነሳት ይልቅ ማጠጋጋት

ቀጥሎ የማነሳው ጉዳይ ከመሰረተ-ልማት ግንባታ ጋር በተያያዘ፣ በተለይ ከመሬት ይዞታቸው ለሚፈናቀሉ አርሶ-አደሮች የሚሰጠው የካሳ ክፍያ እና የመልሶ ማቋቋም መርሃ-ግብርን በተመለከተ ሲሆን ጉዳዩ የሚመለከታቸው የክልልና የፌደራል መንግስት ሃላፊዎች ፅሁፉን በጥሞና እንዲያነቡትና አስቸኳይ የማስተካከያ እርምጃ ሊወስዱ እንደሚገባ ከወዲሁ ለመጠቆም እወዳለሁ።

ባለፉት ሁለት ወራት ከአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ጋር በተያያዘ ተከታታይ የሆነ ተቃውሞ መከሰቱ ይታወቃል፡፡ መንግስት፣ በእንደዚህ ያሉ አጋጣሚዎች የሚነሱ ጥያቄዎችን መቀበል፣ የችግሩን መንስዔ በአግባቡ መፈተሸ እና ለውጥና መሻሻል በሚሹ ቦታዎች ላይ አስፈላጊውን የማስተካከያ እርምጃ መወሰድ እንዳለበት ግልፅ ነው። እንደ ግለሰብ ሰሞኑን የተከሰተው የህዝብ ተቃውሞ እኔንም አሳስቦኛል። ስለዚህ ከሀገሪቱ የመሰረተ-ልማት ግንባታዎች ጋር ተያይዞ ያለውን አሰራር በአንክሮ መታየት እንዳለበት በማመን የግሌን ጥረት አድርጌያለሁ።

በመጀመሪያ ትኩረቴን የሳበው ጉዳይ “በሞጆ-ሀዋሳ የመንገድ ግንባታ ምክንያት 20,950 ሰዎች ከይዞታቸው ይፈናቀላሉ” በሚል በታህሳስ ወር መጀመሪያ ላይ የወጣውን የAddisfortune ዘገባ ከተመለከትኩ በኋላ ነው። በሰኔ ወር 2005 ዓ.ም ላይ የተዘጋጀው የሞጆ-ሀዋሳ መንገድ ፕሮጀክት የመጀመሪያ ክፍል የአከባቢያዊና ማህበራዊ ተፅዕኖ ዳሰሳ ጥናት እና የመልሶ ማቋቋም መርሃ-ግብርን ከኢንተርኔት በማውረድ ይዘቱን ለማየት ሞክሬያለሁ። የሞጆ-ሀዋሳ ፕሮጀክት የመጀመሪያ ክፍል የሆነው የሞጆ-ዝዋይ ፈጠን መንገድ 93 ኪ.ሜ ርቀት ያለው ሲሆን ልማታዊ ፋይዳው ከኢትዮጲያ አልፎ በአፍሪካ ደረጃ የሚታይ ነው፡፡ ነገር ግን፣ በዚህ ክፍል ብቻ 2,149 የቤትና ንብረት ባለይዞታዎች ተጠቂ መሆናቸውና በዚህ ምክንያት ተጠቂ የሚሆኑት ሰዎች ብዛት በድምሩ 16,280 እንደሚደርስ ተጠቅሷል።

በመሆኑም፣ በመንገዱ ግንባታ ምክንያት በከፊልም ሆነ ሙሉ ለሙሉ ለሚፈናቀሉ ቤተሰቦች የካሳ ክፍያ ተመን ተቀምጧል። ይሁን እንጂ፣ በዚህ ፅሁፍ በዋናነት የማተኩረው ከመንገዱ ግንባታ ጋር ተያይዞ ለአርሶ-አደር ገበሬዎች ሊሰጥ በታሰበው የእርሻ መሬት የካሳ ክፍያ መጠን እና የመልሶ ማቋቋም መርሃ-ግብር ላይ ነው። ምክንያቱም፣ የዳሰሳ ጥናቱ እንደሚያሳየው ከተፈናቃዮቹ ውስጥ 98.9%ቱ አርሶ-አደር ገበሬዎችና ቤተሰቦቻቸው ናቸው። እንዲሁም፣ በፕሮጀክቱ የመጀመሪያ ክፍል ግንባታ ከሚያስፈልገው 734.78 ሄክታር መሬት ውስጥ 676.48 ሄክታር መሬት ከአርሶ አደር ገበሬዎች የእርሻ መሬት ነው።

ፕሮጀክቱ ዙሪያ ባሉ ወረዳዎች ውስጥ የአንድ ገበሬ አማካይ የመሬት ይዞታ መጠን ከአንድ ሄክታር በታች ነው። ከገበሬዎቹ ተወስዶ ለመንገዱ ግንባታ ለሚውለው እርሻ መሬት፣ አንድ ሄክታር የእርሻ መሬት በአመት የ19,735 ብር ጊቢ ያስገኛል በሚል ታሳቢ ተደርጎ ካሳውን የመሬቱን 10 ዓመት ገቢ (19,735 x10=197,350) ብር እንደሚከፈል ተጠቅሷል። በፕሮጀክቱ ለሚወሰደው 676.48 ሄክታር የእርሻ መሬት በድምሩ 133,499,381 ብር ካሳ እንደሚከፈልም በጥናቱ ውስጥ ተጠቅሷል።

Image - Modjo – Hawassa Road Project Phase I

ሆኖም ግን፣ በመንገዱ ግንባታ ምክንያት በሚፈናቀሉ በተለይ በአርሶ-አደር ገበሬዎች ላይ ከሚያደርሰው ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተፅዕኖ እና ከመልሶ ማቋቋም መርሃ-ግብር አንፃር የሞጆ-ሃዋሳ መንገድ ፕሮጀክት የሚከተሉት ሁለት መሰረታዊ ችግሮች አሉበት።

አንደኛ፦ በፕሮጀክቱ የደሰሳ ጥናት መሰረት ለአንድ ሄክታር የእርሻ መሬት የሚከፈለው የካሳ (Compensation) መጠን፣ በአመት የ19,735 ብር ጊቢ እንደሚያስገኝ ታሳቢ ተደርጎ፣ የ10 ዓመት 197,350 ብር (19,735 x10) ነው። እስከ መጨረሻው (Permanently) ለሚወሰደው የእርሻ መሬት የሚከፈለው የካሳ መጠን በአንድ እስኩዌር ሜትር ሲሰላ 19.74 ብር ይሆናል። በጠቅላላ ለመንገዱ ግንባታ ለሚወሰደው 676.48 ሄክታር የእርሻ መሬት የሚከፈለው ብር መጠን በድምሩ 133,499,381 ብር እንደሆነ ተጠቅሷል። ይህ፣ መሬታቸው ለመንገዱ ግንባታ በመዋሉ ምክንያት አርሶ-አደሮቹ ለሚያመልጣቸው የብልፅግና እና ምቹ አጋጣሚ (Development & Opportunity Cost) ካሳ እንደሆነ ተጠቅሷል። ነገር ግን፣ የተመደበውን ጠቅላላ የበጀት መጠን ለሚወሰደው የእርሻ መሬት ስፋት ሲካፈል (133,499,381÷ 676.48) ከላይ ከተጠቀሰው ዋጋ (19.74ብር) ጋር እኩል ነው። ስለዚህ፣ ለአርሶ-አደሮቹ ከሚከፈላቸው የ19.74 ብር በአንድ እስኩዌር ሜትር ካሳ በስተቀር ለሚያመልጣቸው የብልፅግና እና ምቹ አጋጣሚ የሚከፈል ካሳ የለም።

ሆኖም ግን፣ በ2001/02 ዓ.ም በፕሮጀክቱ ዙሪያ ያሉ ወረዳዎች ውስጥ 128,419 ሄክታር መሬት ታርሶ የነበረ ሲሆን አጠቃላይ የምርት መጠኑ 2,118,626 ኩንታል እንደነበረ ተጠቅሷል። በዚህ መሰረት ምርታማነቱ 16.5 ኩንታል በሄክታር ሲሆን፣ ይህ ለመሬቱ ከሚከፈለው የካሳ ክፍያ አንፃር ሲታይ በአማካይ ለአንድ ኩንታል ምርት የሚከፈለው 1197 ብር ይሆናል። ይሁን እንጂ፤ በአከባቢው የሚመረቱት እንደ ማሽላ፥ ስንዴ፥ ባቄላና ጤፍ የመሳሰሉት ሰብሎች መሆናቸው፣ አርሶ-አደሩ የግብርና ተረፈ-ምርቶችን ለእንስሳት መኖነት፥ ለማገዶነትና ለግንባታ ሥራ የሚገለገልባቸው መሆኑ፣ ወደፊት ከግብርና ግብዓቶች አጠቃቀምናና የአሰራር ዘዴዎች መሻሻል ጋር ተያይዞ የመሬቱ ምርታማነት፣ እንዲሁም ከመንገዱ ግንባታ ጋር ተያይዞ የመሬቱ ዋጋ እንደሚጨምር ታሳቢ ሲደረግ በአንድ እስኩዌር ሜትር የተተመነው የ19.74 ብር ካሳ በጣም አነስተኛ ነው።

ሁለተኛ፦ በፕሮጀክቱ ምክንያት ለሚፈርሱ የመኖሪያ ቤት እና የሥራ (የቢዝነስ) ቦታዎች ምትክ የሚሆን መስሪያ ቦታ እና የገንዘብ ካሳ እንደሚከፈል የተጠቀሰ ሲሆን ከእርሻ መሬታቸው ላይ ለሚፈናቀሉ አርሶ-አደሮች ግን የመሬቱን የአስር አመት ካሳ 197,350 ብር ከመክፈል በስተቀር ሌላ የሚደረግላቸው የመልሶ መቋቋም ድጋፍ የለም። በፕሮጀክቱ ምክንያት ለሚፈርሱ የሥራ/ቢዝነስ ተቋማት ከቀድሞው የተሻለ የመስሪያ ቦታ እንዲያገኙ ከማስቻል ባለፈ የገቢ አቅማቸው ወደ ቀድሞው ደረጃ እንዲመለስ ድጋፍ እንደሚደረግላቸው ይገልፃል። ነገር ግን፣ 676.48 ሄክታር ከሚሆነው የእርሻ መሬት ላይ በከፊልም ሆነ ሙሉ ለሙሉ ለሚነሱ አርሶ አደሮች ካሳ በመክፈል ብቻ፣ ያለምንም የመልሶ ማቋቋሚያ ድጋፍ፣ ለዘመናት ከኖሩበት አከባቢና የኑሮ ዘይቤ ማፈናቀል በጣም አሳሳቢ ተግባር ነው። በተለይ፣ በፕሮጀክቱ ተጠቂ ከሆኑት ውስጥ የ1ኛና 2ኛ ደረጃ ት/ት የመማር ዕድል ያገኙት 13.6%ቱ ብቻ መሆናቸው፣ አብዛኞቹ ተፈናቃዮች (59.4%) ግን ማንበብና መፃፍ እንኳን የማይችሉ መሆናቸው ሲታሰብ ሁኔታውን የበለጠ አሳሳቢ ያደርገዋል።

ከሞጆ-ሃዋሳ የፈጣን መንገድ ግንባታ ፕሮጀክት፣ በተለይ የመጀመሪያ ክፍል የሆነው ከሞጆ-ዝዋይ ያለው መንገድ ግንባታ ከላይ የተጠቀሱት ሁለት መሰረታዊ ችግሮች እንዳሉበት አይተናል። የእርሻ መሬት የሚከፈለው ካሳ ዝቅተኛ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ያለውን ችግር ለመቅረፍ በዋናነት የካሳ ክፍያ አተማመኑ ነባራዊ እውነታውን ያገናዘበና የአርሶ-አደሩን ዘላቂ ጥቅም በማይነካ መልኩ መሆን እንዳለበት ግልፅ ነው። ሁለተኛውን ችግር ለመቅረፍ ግን መሰረታዊ የአስተሳሰብና የአሰራር ለውጥ ማድረግ ያስፈልጋል። በዚህ ረገድ ከመሰረተ-ልማት ግንባታና የከተሞች መስፋፋት ጋር ተያይዞ ላጋጠመ ተመሳሳይ ችግር ህንድ (India)፣ በተለይ “ጉጅራት” (Gujarat) በሚባለው ግዛት ያለውን አሰራር እንደ ጥሩ ልምድ መውሰድ ይቻላል።

በመሰረቱ፣ በዚህ ፅሁፍ ያየነው የሞጆ-ሃዋሳ ያሉ የመንገድና የሌሎች መሰረተ-ልማት ግንባታ ፕሮጀክቶች ለሀገርም ሆነ ለአከባቢው ማህብረሰብ ያላቸው ጠቀሜታ ከፍተኛ መሆኑ ግልፅ ነው። በፕሮጀክቶቹ ምክንያት የሚፈናቀሉ ሰዎች መኖራቸውም እርግጥ ነው። ነገር ግን፣ ከልማቱ ተጠቃሚ የሚሆነው አብዛኛው የሕብረተሰብ ክፍል እንደመሆኑ ችግሮቹንም በጋራ መካፈል አለበት፡፡ አብዛኛው የሕብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ ለሚሆንበት ጉዳይ የተወሰኑ ግለሰቦች ዋጋ መክፈል የለባቸውም፡፡ ማህብረሰብ እንደ ማህብረሰብ በጋራ ተጠቃሚ እንደመሆኑ መጠን በመሰረተ-ልማት ግንባታው ምክንያት በግለሰቦች ላይ የሚደርሰውን ተፅዕኖም አብሮ መጋራት መቻል አለበት፡፡ ጉዳዩ የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ደግሞ ለዚህ አመቺ የሆነ አሰራር መዘርጋት መቻል ይጠበቅባቸዋል፡፡

ከላይ በጠቀስኩት የህንድ ግዛት የሚኖር የከተማ ዕቅድ (Urban Planning) ባለሞያ በአንድ የውይይት መድረክ ላይ ስለአሰራሩ የሰጠውን ምሳሌ እንደ መነሻ መውሰድ ፅንሰ-ሃሳቡን በቀላሉ ለማብራራት ይቻላል። ለምሳሌ በአንድ ክፍል ውስጥ ብዙ ሰዎች ተጠጋግተው የተቀመጡ ቢሆንና እኛ በመሃል ለማለፍ የሚያስችል መንገድ ለመፍጠር ብንፈልግ፤ “መሃል ላይ የተቀመጡትን የተወሰኑ ሰዎች እንዲነሱ ያደርጋሉ?” ወይስ “ሁላችሁም እስኪ ትንሽ ተጠጋጉ” በማለት በመሃል የሚያሳልፍ መንገድ ይፈጥራሉ? ከሕብረተሰቡ ውስጥ የተወሰኑ ግለሰቦች መሬታቸውን ሙሉ በሙሉ ከሚያጡ፣ ሁሉም የሕብረተሰብ አባል ትንሽ-ትንሽ ቢያጡ ይመረጣል።

Photo - Modjo – Hawassa Road Project

በመንገዱ መገንባት ተጠቃሚ የሚሆነው ሕብረተሰቡ እንደመሆኑ፣ በግንባታው ምክንያት ለሚፈናቀሉ አርሶ አደሮች የተወሰነ መሬት በማዋጣት ባለእንጀሮቻቸውን ከመፈናቀል መታደግ አለባቸው። ይህን ተግባራዊ ለማድረግ ምቹ የሆኑ ማህበራዊ እሴቶች አሉን። የቀድሞው ጠ.ሚ መለስ ዜናዊ በጥናታዊ ፅሁፋቸው ላይ እንደገለፁት “ምቹ የሆኑ ማህበራዊ እሴቶች የሀገር ልማትና እድገት መሰረተ-ልማቶች ናቸው” በማለት ይገልጿቸዋል። ኢትዮጲያ ውስጥ ህዝቡ ሥራን በደቦ ተጋርቶ ነው የሚሰራው፣ መከራን በዕድር ተካፍሎ ነው የሚኖረው፣ ቢዝነሱን በዕቁብ ብር ነው የሚያንቀሳቀሰው። ይህ፣ በሚመለከታቸው የመንግስት ሃላፊዎች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ዘንድ ፍቃደኝነቱና ተነሳሽነቱ ካለ፣ አስፈላጊው የግንዛቤ ማስጨበጪያ እና የማስተባበር ሥራ ከተሰራ ከላይ የተጠቀሰውን ፅንሰ-ሃሳብ ወደ ተግባር መቀየር በጣም ቀላል ነው።

ከአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ጋር ተያይዞ የታየው የህዝብ ተቃውሞ ከላይ የተጠቀሰው አይነት የግብሩ-ይውጣ ሥራና አሰራር በኦሮሞ ህዝብ ዘንድ ምን ያህል ብሶትና ቁጭት እንደፈጠረ መረዳት ይቻላል። አንድ አርሶ አደርን 20 ብር በእስኩዌር ሜትር ካሳ ከፍሎ ለዘመናት ከኖረበት መሬትና የኑሮ ዘይቤ ማፈናቀል “ከድጥ ወደ ማጥ” የሚሉት ዓይነት ነው።

በካሳ መልክ ለአንድ ሄክታር የእርሻ መሬት የሚከፈለው 197,350 ብር፣ ምንም ዓይነት የገንዘብ አጠቃቀምና የዕቅድ ክህሎት ለሌለው፣ ማንበብና መፃፍ በማይችል አርሶ አደር ገበሬ እጅ ላይ ከሁለትና ሦስት አመት በላይ አይቆይም። ለመንገዱ ግንባታ ለሚያስፈልገው 676.48 ሄክታር የእርሻ መሬት የሚከፈለው 133,499,381 ብር ግን ወደ ወደ አርሶ-አደሩ እጁ ከመበተን ይልቅ በአንድ ላይ አቀናጅቶ አንድ አትራፊ የሆነ የቢዝነስ አክሲዮን ማቋቋም ይቻላል። የእርሻ መሬታቸው ለተወሰደባቸው አርሶ አደርዎች ሁሉም የአከባቢው አርሶ አደር የተወሰነ የእርሻ መሬት እንዲያዋጣ ማድረግ። እያንዳንዱ ገበሬ ባወጣው የመሬት መጠን ልክ የአክሲዮን ድርሻ እንዲኖረው ማድረግ።በዚህ አንድ’ም አርሶ-አደር ከቀዬው ሳይፈናቀል፣ ሁሉም አርሶ-አደሮች በፈጠን መንገዱ ምርቶቻቸው ወደ ገበያ እያቀረቡ ከቢዝነሳቸው አመታዊ ትርፍ ዳጎስ ያለና ቋሚ የሆነ ገቢ ያገኛሉ። ይሄ ሁሉ ከእኛ፣ ተማርን ካልነው ሰዎች የሚጠይቀው ብቸኛ ነገር ለአርሶ-አደሩ ሕይወት ዋጋ መስጠት ብቻ::

***********

Seyoum Teshome is a Lecturer at Ambo University Woliso Campus and head of Management Department. He was born in Arsi, Assela, in 1979 and studied Management at Harameya University and MBA at Mekelle University. He also blogs at http://ethiothinkthank.com

more recommended stories