ልዩነት እና ተመሳሳይነት | ያለልዩነት የለም ነፃነት

ባለፈው ፅሁፌ ለመግለፅ እንደሞከርኩት፣ እድገትና ብልፅግና እንዲቀጥል የለውጥና መሻሻል መንፈስ በሕብረተሰቡ ውስጥ መስረፅ እንዳለበት እና ይህ መንፈስ በቋሚነት እንዲኖር ደግሞ ልዩነት የማህበራዊ ሕይወታችን አካል ሆኖ መቀጠል እንዳለበት አይተናል። በዚህ ክፍል፣ ልዩነት በሕብረተሰቡ ውስጥ ያለ ነፃነት ነፀብራቅ ስለመሆኑ እናያለን። ከዚያ በፊት ግን፣ ስለ ነፃነት ምንነት ምሉዕ ግንዛቤ ሊኖረን ይገባል።

እርግጥ በነፃነት መኖር የማይፈልግ ሰው ያለ አይመስለኝም። ይሁን እንጂ፣ “የማያውቁት ሀገር አይናፍቅም” እንዲሉ፣ ነፃነት’ም ካላወቁት አይናፍቅም። ነፃነትን የማያውቅ ሰው የነፃነትን ትርጉምና ፋይዳ አይረዳም፣ ነፃነቱን አያስከብርም፣ የሌሎችን ነፃነት አያከብርም። ሊዮ ቶልስቶይ የተባለው የሩሲያ ታላቅ ምሁር “War & Peace” በሚለው መፅሃፉ እንዳብራራው፤ “ነፃነትን መገንዘብ ያልቻለ ሰው ሕይወትንም መገንዘብ አይችልም፣ …ምክንያቱም የሰው-ልጅ ጥረት ሁሉ፣ ለሕይወት ያለው ስሜት በሙሉ፣ ‘ነፃነት’ን ለማሳደግ ብቻ ሲባል የሚደረግ ነው። እንደ ቶልስቶይ አገላለፅ፣ ሀብት እና ድህነት፤ መፈለግ እና አለመፈለግ፤ ሃይል እና ተገዢነት፤ ጤና እና በሽታ፤ ባህል እና አላዋቂነት፤ ሥራ እና ምቾት፤ ጥጋብ እና ረሃብ፤ መልካም እና መጥፎ፣ ሁሉም በአንፃራነት የነፃነት ማነስ እና መብዛት ውጤቶች ብቻ ናቸው። በአጠቃላይ፣ ስለ ነፃነት ሙሉዕ ግንዛቤ የሌለው ሰው የሕይወትን ትርጉምና ፋይዳ እንኳን መገንዘብ አይችልም። ስለዚህ ነፃነት ምንድነው?

የነፃነትን ፅንሰ-ሃሳብ በዝርዝር ለማስረዳት ያመች ዘንድ በቅድሚያ በእንግሊዘኛ “freedom” የሚለውን ቃል ትርጉም እንመልከት። “ነፃነት፦ ነፃ-መሆን፣ ነፃ-መውጣት፣ የመንቀሳቀሻ-ቦታ ልቀት፣ ስፋት፣ ርዝመት፤ ነፃ የመንቀሳቀሻ-ቦታ፣ ሙሉ-የመንቀሳቀሻ ቦታ፤ ለመንቀሳቀስ ምቹ የሆነ ቦታ፤ ነፃ ቦታ፣ ነፃ ይዞታ፤ ነፃ-ሰው፣ ነፃ-የወጣ ሰው፤ ራስ-ገዝ፣ ራስ-አመራር፣ ነፃ-ማውጣት፣…ወዘተ እንደማለት ነው። ስለዚህ፣ “ነፃነት” የሚለው ቃል፤ ነፃ-መሆንን፣ የመንቀሳቀሻ-ቦታ መኖርን፣ የመሄጃ-ቦታ መኖርን፣ በራስ-መንገድ መሄድን፣ በራስ-ፈቃድ መመራትን፤ እንደወደዱት፣ እንደፈለጉትና እንደመረጡት ማድረግን፤ በራስ-መቆምን፣ በራስ-እግር መቆምን፣ ለራስ-መሆንን…ወዘተ፣ የመሳሰሉት ተግባራት እና ሁኔታዎች ይገልፃል። በአጠቃላይ፣ ነፃነት “ያለገደብ መንቀሳቀስ መቻል ወይም እንቅስቃሴን የሚገድብ ውጫዊ ኃይል አለመኖር” በሚል ፅንሰ-ሃሳብ ላይ ተመሰረተ ነው። ነገር ግን፣ የሰው-ልጅ ነፃነት በዚህ መልኩ የሚገለፅ ቢሆን ኖሮ ሕይወት ፍፁም የተለየ ገፅታና ትርጉም በኖራት ነበር።

ሰው ነባራዊ እውነታን በመገንዘብ፣ የነገሮችን ምንነት እና የምልክቶችን ትርጉም በመረዳት፣ እንዲሁም በሃሳቦች መካከል ያለውን ምክንያታዊ ተያያዥነት በመገንዘብ፤ ሃሳቦችን ይፈጥራል፣ ያዳብራል፣ ይለውጣል። በመሆኑም፣ በአዕምሮው ውስጥ ያሉ ሃሳቦችን ከመገንዘብ፣ ከነባራዊ እውነታ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ከማነፃፀር፣ በመካከላቸው ያለውን ምክንያታዊ ተያያዥነት ከማስላት አንፃር ሰው ቀጥተኛ ኃይል (active power) አለው። ስለዚህ፣ ሰው ሃሳባዊ እንቅስቃሴን ለማድረግና ላለማድረግ፣ በእንቅስቃሴው ለመቀጠል ወይም ላለመቀጠል መወሰን ይችላል። ሰው ሃሳባዊ አንቅስቃሴውን ተግባራዊ የማድረግና የመለወጥ አቅምና ብቃት አለው።

በሃሳቡና በፍላጎቱ መሰረት አካላዊ እንቅስቃሴ ለማድረግ ወይም ላለማድረግ፣ እያደረገ ያለውን እንቅስቃሴ ለመቀጠል ወይም ለማቋረጥ የሚያስችል ተፈጥሯዊ ኃይል ስላለው፣ ሰው በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ ስለ አንድ ነገር ለማሰብ ወይም ላለማሰብ፣ በሃሳቡ መሰረት አካላዊ እንቅስቃሴ ለማድረግ ወይም ላለማድረግ መወሰን ይችላል። ስለዚህ፣ ሰው በእራሱ ፈቃድ ሃሳባዊ እንቅስቃሴን የማድረግ፣ እንዲሁም በሃሳቡና አስተሳሰቡ መሰረት የተወሰነ የሰውነት ክፍሉን ማንቀሳቀስ ይችላል።

በዚህ መሰረት፣ “ፍቃድ “ (Will) ማለት፣ በሃሳብ ላይ ብቻ በመመስረት አንድን ነገር ለመፍጠር ወይም ለማድረግ መሞከር ይሆናል። አንድ ሰው፣ የተወሰነ ሃሳባዊ ወይም አካላዊ እንቅስቃሴ በማድረግ ወይም ባለማድረግ ፍቃዱን በተግባራዊ እንቅስቃሴ ሲገልፅ “መፍቀድ ወይም መምረጥ“ (willing or volition) ይባላል። “ፍቃደኛ“ (voluntary) የሚለው፣ በእራስ ሃሳብ ላይ ተመስርቶና ያለ ምንም ውጫዊ ኃይል አስገዳጅነት መንቀሳቀስ ወይም ከእንቅስቃሴ መቆጠብ እንደማለት ሲሆን፣ ከዚህ ውጪ የሆነ ማንኛውም ዓይነት እንቅስቃሴ “ያለውዴታ“ ወይም “በግዴታ” (involuntary) የሚደረግ ተግባር ነው።

ማንኛውም ግለሰብ አንድን ነገር በእራሱ ፈቃድ ለመፍጠር ወይም ለማድረግ የሚያስችለውን አካላዊ እንቅስቃሴ ከመጀመሩ በፊት፣ በቅድሚያ በጉዳዩ ላይ ሃሳባዊ እንቅስቃሴ ማድረግ ይኖርበታል። ምክንያቱም፣ በተወሰነ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ለመሳተፍ ፍቃደኛ ከመሆኑ በፊት ስለ እንቅስቃሴው ማወቅ አለበት። ይህ ካልሆነ፣ በራስ ሃሳብ ላይ ያልተመሰረተ እንቅስቃሴ በፍቃደኝነት ሳይሆን በሁኔታዎች አስገዳጅነት የሚደረግ ነው። ስለዚህ፣ በፍቃደኝነት የሚደረግ ማንኛውም ዓይነት እንቅስቃሴ በራስ ሃሳብ፣ ዕውቀትና ግንዛቤ ላይ የተመሰረተ መሆን አለበት።

ሰው፣ እውነታን ለመገንዘብና ለመረዳት፣ በዚህም በዙሪያው ስላሉ ነገሮች ምክንያታዊ ድምዳሜ ላይ ከመድረሱ በፊት፣ በቅድሚያ እራሱን ማወቅ አለበት። ስለዚህ፣ በዙሪያው ስላሉ ነገሮች ለማወቅ የእራሱን ያለበትን ነባራዊ ሁኔታ ማወቅ፣ የሚኖርበትን ሁኔታ ለማወቅ በሕይወት መኖሩን ማወቅ ይኖርበታል። አንድ ሰው በሕይወት መኖሩን የሚያረጋግጥበት አንድና ብቸኛ መንገድ፣ በእራሱ ፈቃድ አካላዊ ወይም ሃሳባዊ እንቅስቃሴ በማድረግ ነው። ሰው በፍቃዱ ለመንቀሳቀስ እንዲችል ራሱን ማወቅ አለበት፣ ለዚህ ደግሞ በራሱ መፍቀድ አለበት።

ሰው አንድን ተግባር በፈቃዱ ለመከዎን በቅድሚያ ማሰብ ያለበት ሲሆን፣ ስለ ተግባሩ ለማሰብ ግን በቅድሚያ ፍቃደኛ መሆን አለበት። ተግባራዊ እንቅስቃሴ ከማድረጉ በፊት፤ ምን፣ ለምን እና አንዴት እንደሚንቀሳቀስ መረዳትና ማወቅ ያለበት ሲሆን፣ “ምን?”፣ “ለምን?” እና “እንዴት?” የሚሉትን ጥያቄዎች ለመመለስ ግን በቅድሚያ ፍቃደኛ መሆን አለበት። በማሰብ ስለ አንድ ነገር ያውቃል፣ ነባራዊ ሁኔታን ይረዳል። ስለዚህ፣ ለመፍቀድ ማሰብ – ለማሰብ መፍቀድ አለበት፣ ለማወቅ መፍቀድ – ለመፍቀድ ማወቅ አለበት። በዚህ መሰረት፣ ፈቃድ (will) እና መገንዘብ/መረዳት (understanding) የሰው-ልጅ ልዩ ተፈጥሯዊ ባህሪያት ናቸው።

ሰው፣ አንድን ተግባር በፈቃዱ ለማከናዎን መረዳት፣ ተግባሩን ለመረዳት ደግሞ በቅድሚያ መፍቀድ ካለበት፣ ፈቃድ እና መረዳትን በተናጠል ማየት አይቻልም። በመሆኑም፣ ፈቃድን ከመረዳት ወይም መረዳትን ከፈቃድ መነጠል እስካልተቻለ ድረስ፣ ሁለቱን በጥምረት ማየት ያስፈልጋል። ይህ የሚሆነው ፈቃድ እና መረዳትን እንደ መነሻ ምክንያት መውሰድ የሁለቱን ጥምር ውጤት በመገንዘብ ይሆናል። በፈቃድ እና መረዳት ጥምረት የሚፈጠር ወይም የሁለቱ ድምር ውጤት የሆነው ነገር ደግሞ “ነፃነት” (liberty) ነው።

“ነፃነት” ማለት ያለ ምንም ውጫዊ ኃይል ወይም አስገዳጅ ሁኔታ (necessity) ነፃ ሆኖ ማሰብ ወይም ማድረግ ነው። ስለዚህ፣ ነፃነት የሚለው ፅንሰ-ሃሳብ፣ ያለ ውጫዊ ኃይል ወይም የሁኔታዎች አስገዳጅነት “አካላዊ እንቅስቃሴ” (motion) ወይም “ሃሳባዊ እንቅስቃሴ” (thinking) ማድረግ መቻል ነው። ነፃነት ሊኖር የሚችለው የተንቀሳቃሹ አካል በራሱ-ተነሳሽነት እና ግንዛቤ መሰረት መንቀሳቀስ ሲችል ነው።

ማንኛውም ሰው ቢሆን አንድን ተግባር በእራሱ ፍቃድና ግንዛቤ መሰረት መጀመር ወይም አለመጀመር፣ እያደረገ ያለውን እንቅስቃሴ ለመቀጠል ወይም ለማቋረጥ የሚያስችል ተፈጥሯዊ ኃይል አለው። አንድ ሰው ነፃነት የሚኖረው በተረዳው መንገድ ለመንቀሳቀስ ራሱና ለራሱ መፍቀድ ሲችል ነው። ሆኖም ግን፣ በፈቃዱ መሰረት፣ ማለትም በተረዳው መንገድ ለመንቀሳቀስ ካልቻለ ግን ነፃነት የለውም። ስለዚህ፣ ነፃነት ማለት ተግባራዊ እንቅስቃሴን በተረዳነው መልኩ ለማድረግ መፍቀድ መቻል ነው።

በአጠቃላይ፣ “ነፃነት” ማለት በራስ ፍቃድና ግንዛቤ መሰረት ተግባራዊ እንቅስቃሴ ማድረግ መቻል ነው። እያንዳንዱ ግለሰብ በማህበራዊ ሕይወቱ የሚያደርገው እንቅስቃሴ በራሱ ፍቃድና ግንዛቤ ላይ ተመሰርቶ እስከሆነ ድረስ ሁልግዜም ልዩነት ይኖራል። ምክንያቱም እንኳን ሕብረተሰብ ሁለት ግለሰቦች ተመሳሳይ ፍቃድ፡ አንድ ዓይነት ፍላጎትና ምርጫ እና ተመሳሳይ ግንዛቤ ሊኖራቸው አይችልም። ስለዚህ፣ ነፃነት ባለበት ማህብረሰብ ውስጥ ያለማቋረጥ ልዩነት ይኖራል። በግለሰቦች ዘንድ ያለ ልዩነት ከቦታና ግዜ አንፃር እየሰፋ፣ እየጠበበ እና በሌላ እየተተካ ስለሚሄድ፣ በተለያዩ ቡድኖችና የሕብረተሰብ ክፍሎች መካከል የአዳዲስ ሃሳቦች፣ አመለካከቶች፣ እምነትና እሴቶች ልውውጥ ይኖራል። በእንደዚህ ያለ ሕብረተሰብ ውስጥ ሁልግዜም የለውጥና መሻሻል መንፈስ፣ በዚህም ዘላቂ እድገትና ብልፅግና ይኖራል።

***********

* ይህ ጽሑፍ ‹‹ልዩነት እና ተመሳሳይነት›› በሚል ዐብይ ርዕስ ሥር በተከታታይ የማቀርበው ጽሁፍ ሦስተኛው ነው፡፡

Seyoum Teshome is a Lecturer at Ambo University Woliso Campus and head of Management Department. He was born in Arsi, Assela, in 1979 and studied Management at Harameya University and MBA at Mekelle University. He also blogs at http://ethiothinkthank.com

more recommended stories