ልዩነት እና ተመሳሳይነት | ውድቀት በተመሣሣይነት

አብዮት በልዩነት እና በተመሣሣይነት ሃይሎች መካከል ያለው ቅራኔ ተካሮ ከፍተኛ ደረጃ ሲደርስ የሚፈጠር መሰረታዊ ለውጥ ነው። የልዩነት ሃይሎች ከተለመደው፥ ከመደበኛው የተለየ ወይም የማይመሳሰል የፖለቲካ አቋምና አመለካከት ሲያራምዱ፣ የተመሣሣይነት ሃሎች ደግሞ ተመሣሣይ፥ አንድ ዓይነት የፖለቲካ አቋምና አመለካከት ብቻ ለማስረፅ ጥረት ያደርጋሉ። ለምሳሌ፦ በኢትዮጲያ በ1966 ዓ.ም የተካሄደው አብዮት እና የ1983ቱ አብዮታዊ ዴሞክራሲ በእነዚህ ሁለት ሃይሎች መካከል የነበረው ተቃርኖ ከፍተኛ ደረጃ በመድረሱ የተከሰቱ ናቸው።

“ተመሳሳይነት” የሚለው ቃል ቀጥተኛ ፍቺ፤ “በመልክ፥ በመጠን፥ በባህሪ የተቀራረበ፣ አንድ የሆነ” የሚል ነው። በአጠቃላይ፣ በአንድ ሀገር ውስጥ ያሉ የሕብረተሰብ ክፍሎች በተለያዩ ማህበራዊ ጉዳዮች፥ በፖለቲካዊና ኢኮኖሚዊ እንቅስቃሴዎች፣ እንዲሁም እነዚህን በሚመሩባቸው የሞራል እሴቶችና መርሆች አንፃር ‘ተመሣሣይ’ አቋምና አመለካከት የሰፈነ መሆኑን ያመለክታል። ባጭሩ የ”ተመሳሳይነት” ፅንሰ-ሃሣብ የ”ልዩነት” ፅንሰ-ሃሣብ ቀጥተኛ ተቃራኒ ነው። (የ”ልዩነት” ፅንሰ-ሃሣብ ባለፈው ጽሑፍ በተወሰነ ደረጃ ተብራርቷል)

ብዙውን ግዜ በአብዮታዊ ንቅናቄ የሥርዓት ለውጥ በማምጣት የፖለቲካ ስልጣን የጨበጠ ሃይል የፖለቲካ አስተዳደር መዋቅር መዘርጋትና መምራት ሲጀምር አቋምና አመለካከቱን በቀጥታ ከልዩነት ወደ ተመሳሳይነት ይቀይራል። ምክንያቱም አስተዳደራዊ ሥርዓቱ በአሸናፊው የፖለቲካ ሃይል አቋምና መርህ የተቃኘ ከመሆኑ በተጨማሪ ከእሱ የተለየ አቋም የሚያራምዱ ሃይሎችም በዚህ ማዕቀፍ ውስጥ እንዲገቡ ስለሚያደርግ ነው። “አብዮት ወረት ነው” የተባለበት ዋና ምክንያት በልዩነት ወደ ስልጣን የመጣ አብዮተኛ ሌላ ልዩነትን ማስተናገድ ስለሚሳነው ነው።

ለምሳሌ ከኢህአዴግ የተለየ የፖለቲካ አቋምና አመለካከት የሚያራምዱ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች በሀገሪቱ ዋና የፖለቲካ መድረክ ያላቸው ድርሻ መቀነሱ ለዚህ እንደ ማሳያ ሊጠቀስ ይችላል። የተቃዋሚ ድርጅቶች በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያላቸው ድርሻ ከፓርላማ ወንበር ብዛት አንፃር ሲታይ በ1997 ዓ.ም ከነበረበት 31.9% በ2007 ዓ.ም ወደ 0.0% ወርዷል።

ይህ “የፖለቲካ ምህዳሩ ጠቧል፣…ሰፍቷል” ከሚለው ግርድፍ እይታ በዘለለ ጥልቅ ትንታኔ የሚሻ ጉዳይ ነው። በተለይ ከብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መብትና እኩልነት አንፃር የተለየ የፖለቲካ አቋም ይዞ በአብዮታዊ ዴሞክራሲ ወደ ስልጣን የመጣው ኢህአዴግ ከእሱ የተለየ አቋምና መርህ በሚያራምዱ የፖለቲካ ሃይሎች ላይ እያደረሰ ያለው ከፍተኛ የተመሳሳይነት ጫና ነፀብራቅ ነው። አብዛኞቹ የፖለቲካ ልሂቃን በዚህ አመለካከት ተፅዕኖ ስር ያሉ በመሆናቸው ጉዳዩን ይበልጥ አወሳስቦታል።

ለምሳሌ፣ “ለዘብተኛ” ከሚባሉት ከፍተኛ የመንግስት አመራሮች ውስጥ አንዱ የሆኑት የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶ/ር ቴድርስ አድሃኖም በፌስቡክ ገፃቸው ላይ የሰጧትን አንዲት ዓ.ነገር እንደ ማሳያ ልውሰድ። በዚህ ዓመት መስከረም ወር ላይ ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም “የፖለቲካ አስተሳሰብ ልዩነት ቢኖረን ችግር የለውም…“ የሚል አስተያየት ሰጥተው ነበር። ነገር ግን፣ አስተያዬቱን ከግዜና ቦታ አንፃር አስፍተን ካየነው የባሰ ችግር የሚመጣው ሚኒስትሩ ካሰቡት በተቃራኒ አቅጣጫ፥ “የፖለቲካ አስተሳሰብ ልዩነት ከሌለ” እንደሆነ መረዳት ይቻላል። ከረጅም ግዜ እይታ አንፃር፣ በሀገሪቱ ግልፅ የሆነ የፖለቲካ አስተሳሰብ ልዩነት መኖሩ ከዴሞክራሲዊ ሥርዓት ግንባታ በተጨማሪ ከሀገሪቱ እድገትና ብልፅግና ጋር ጥብቅ የሆነ ቁርኝት አለው።

የምዕራብ አውሮፓ የህዳሴው ዘመን ፈላስፎች ውስጥ አንዱ የሆነው እንግሊዛዊው ስቱዋርት ሚልስ ‘On Liberty’ በሚለው መጽሐፉ፤ “ሀገራትና ህዝቦች እድገትና ብልፅግናን በዘላቂነት ማስቀጠል የሚሳናቸው ለምንድነው?፣ የእድገትና መሻሻል መንፈስ ከማህብረሰቡ ውስጥ ተንጠፍጥፎ የሚያልቀውስ መቼ ነው?፣ …” የመሳሰሉ ጥያቄዎች በማንሳት ሰፊ ትንታኔ ሰጥቶበታል። የመፅሃፉ ጭብጥ፤ አንዲት ሀገር በብልፅግና ጎዳና ዘላቂና ቀጣይነት ያለው ጉዞ እንዳታደርግ የሚያግዳት ነገር፣ ወይም የእድገትና መሻሻል መንፈስን ከማህብረሰቡ ውስጥ ተሟጥጦ የሚጠፋው ከልዩነት ይልቅ በ”ተመሳሳይነት” ላይ ማዕከል ያደረገ የፖለቲካ ሥርዓት በሀገሪቱ ሲዘረጋ ነው የሚል ፅንሰ-ሃሳብ ነው።

በተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች መካከል ያለ “ልዩነት” የሚጠፋው የአንደኛው ክፍል እምነት፣ መርህ እና መመሪያ በሌሎቹ ላይ ሲጫን እና ሁሉም የሕብረተሰብ ክፍሎች ተመሣሣይ የሆነ አቋም፣ መርህ እና መመሪያ ሲኖራቸው ነው። ስለዚህ፣ ልዩነት በተመሳሳይነት ሲተካ፤ የዜጎች ተግባራዊ እንቅስቃሴ፥ አንድ ዓይነት ባህሪ ብቻ የሚንፀባረቅበት፣ በተመሳሳይ የአኗኗር ዜይቤዎችና የአሰራር ስልቶች፣ እንዲሁም በተመሳሳይ የሞራል እሴቶች የሚመራ ይሆናል። በመሆኑም፣ ተመሳሳይነት ላይ ማዕከል ያደረገ መዋቅርና አስተዳደር በሀገሪቱ ያሉ የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎችን በራሳቸው የተለየ አቅጣጫ እና መርህ መሰረት እንዳይንቀሳቀሱ እንቅፋት ስለሚሆን የዚህ ዓይነት ፖለቲካዊ አስተዳደር ሥርዓት የግለሰቦችንና የቡድኖችን ነፃነት በፅኑ ይጋፋል።

በሕብረተሰቡ ውስጥ ያለ የእድገት እና መሻሻል መንፈስ ለሀገሪቱ ዋና የብልፅግ/ የሥልጣኔ አቅም ነው። ይህ መንፈስ መሰረቱ በተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች መካከል ያለ “ልዩነት” ነው፤ ይህ ደግሞ በግለሰብ ደረጃ ሲታይ “ነፃነት” ይሆናል። በመሰረቱ፣ ሰው በተፈጥሮው ነፃ ነው። ነፃነት የሰው-ልጅ ተፈጥሯዊ ባህሪ ነው። የሰው-ልጅ ትርጉምና ፋይዳ ያለው ሕይወት መኖር የሚችለው ነፃነት ሲኖረው ነው። ነፃነት ደግሞ በሕይወት ምርጫችን ይንፀባረቃል፤ ከሌሎች ጋር ባለን ልዩነት ይገለፃል። የሕይወት መንገድ ምርጫችን በግል እሳቤ እና አመለካከት የሚወሰን እንደመሆኑ መጠን የተለያዩ የሕይወት መንገዶች ይኖራሉ። እለት-በእለት በምናደርጋቸው ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች የራሳችን የሆነ፣ ልዩ አቅጣጫ፥ የተለየ መርህ በመከተል በልዩነት ያለንን ነፃነት እናፀባርቃለን።

ለምሳሌ፣ ሁለት ሰዎች የተለያየ አቋም የሚያራምዱ ከሆነ፣ ከሁለት አንዱ ወይም ደግሞ ሁለቱም የተሳሳተ ግንዛቤ ይዘ(ዟ)ዋል፣ የተሳሳተ አቅጣጫ እየተከተሉ ናቸ(ነ)ው። ስለዚህ፣ ልዩነታቸው የአንደኛውን አዋቂነት እና የሌላኛውን አላዋቂነት፣ ወይም ደግሞ የሁለቱንም አላዋቂነት የሚመለከቱበት መስታዎት ነው እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል። አቋማቸው ተመሣሣይ ከሆነ ግን ስለትክክለኝነቱ ምንም ማረጋገጫ ሊኖራቸው አይችልም። ተቃራኒ ሃሣብ በሌለበት ‘የእኔ ሃሣብ ትክክል ነው’ ብሎ ማሰብ ልክ በጭለማ ክፍል የተሰቀለን መስታዎት እየተመለከቱ ቁማናን እንደማድነቅ ይሆናል።

ግለሰቦች የግል አመለካከት እና እምነት በሚያራምዱበት ወቅት የተለያዩ ቡድኖችን ይፈጠራሉ። እነዚህ የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች በሚያደርጉት ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚዊ እንቅስቃሴዎች፣ እና እንቅስቃሴያቸውን ከሚመሩበት የሞራል እሴቶች አንፃር ልዩነት ሲኖር፣ አዲስ ነገር ይኖራል፤ አዲስ ተሞክሮ እና ተጨማሪ ዕውቀት ባለበት መሻሻል እና ለውጥ ይኖራል። በዚህ ምክንያት በሕብረተሰቡ፣ ብሎም በሀገር ደረጃ የእድገት እና መሻሻል መንፈስ ይሰርፃል።

በተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ዘንድ ያለው “ልዩነት” ሲጠፋ፤ ማህብረሰቡ በተለያዩ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ረገድ ያለውን “ልዩነት” ማስተናገድ ሲሳነው፣ በሌላ አነጋገር “ልዩነት” በ“ተመሣሣይነት” ሲቀየር፤ ሕብረተሰቡ በልዩነት ሊያገኝ የሚችላቸው ጥቅሞች ይቀራሉ። በዚህ ምክንያት በሕብረተሰቡ፣ ብሎም በሀገር ደረጃ የሥልጣኔ እቅም፥ የለውጥና እና መሻሻል መንፈስ ይከስማል። ይሄን ግዜ ሀገር የሥልጣኔ ማሳያ ከሆኑት እድገትና ብልፅግና ፋንታ ለውድቀቷ ማሳያ በሆኑት ድህነትና ድንቁርና ትዘፈቃለች።

***********

* ይህ ጽሑፍ ‹‹ልዩነት እና ተመሳሳይነት›› በሚል ዐብይ ርዕስ ሥር በተከታታይ የማቀርበው ጽሁፍ ሁለተኛው ነው፡፡

Seyoum Teshome is a Lecturer at Ambo University Woliso Campus and head of Management Department. He was born in Arsi, Assela, in 1979 and studied Management at Harameya University and MBA at Mekelle University. He also blogs at http://ethiothinkthank.com

more recommended stories