(ስዩም ተሾመ)

የሀገር ብልፅግና እንዲረጋገጥ በሁሉም የሕይወት ዘርፎች ቀጣይነት ያለው እድገት እና መሻሻል ሊኖር ይገባል። ይህን ማድረግ የሚቻለው የእድገትና መሻሻል መንፈስ በማሕብረሰቡ ዘንድ ማስረፅ ሲቻል ነው። የእድገት እና መሻሻል መንፈስን የሚፈጠረውና በማሕብረሰቡ ዘንድ የሚሰርፀው ዜጎች በሚያደርጉት ተግባራዊ እንቅስቃሴ ልዩነት ሲኖር ነው። በመሆኑም፣ የእድገት እና መሻሻል መንፈስ እንዲኖር በግለሰብ’ም ሆነ በቡድን በሚደረጉ ማህበራዊ፣ በፖለቲካዊና ኢኮኖሚዊ እንቅስቃሴዎች ዘንድ ልዩነት ሲኖርና ልዩነቱ እንደተጠበቀ ሆኖ መቀጠል ሲቻል ነው።

ከሁሉም የሕብረተሰብ ክፍሎች ጥቅም፣ በአጠቃላይ ከሀገር ብልፅግና እና እድገት አንፃር ሲታይ፣ ልዩነት ምንግዜም ጥቅም እንጂ ጉዳት የለውም። ምክኒያቱም፣ እያንዳንዱ የሕብረተሰብ ክፍል በእራሱ የሕይወት ፍልስፍና እና መርህ ላይ ተመስርቶ በሚንቀሳቀስበት ወቅት ለራሱም ሆነ ለሌሎች የሕብረተሰብ ክፍሎች አዲስ ልምድና ተሞክሮ ያስገኛል።Image - collaboration

የተወሰነ የሕብረተሰብ ክፍል የሚከተለው አቅጣጫ ለራሱና ለሀገሪቱ ብልፅግናን ከማምጣት አንፃር ጠቃሚ ወይም ጎጂ ሊሆን ይችላል። የሄዱበት አቅጣጫ ጠቃሚ ሆኖ ከተገኘ ሌሎች የሕብረተሰብ ክፍሎች እንዲከተሉት ምክንያት ይሆናል፣ ጎጂ ሆኖ ከተገኘ ደግሞ ለራስና ለሌሎች ትምህርት ይሰጣል። አንዳችን የምንከተለው የሕይወት መንገድ ትክክለኝነቱን ለሌላችን ለማረጋገጥ በምናደርገው የማያቋርጥ ጥረት ሁሌም አዲስ ተሞክሮና ልምድ መቅሰም ያስችለናል። በዚህ መልኩ፣ ሁላችንም በግላችን ‘መልካምና ትክክል ነው’ ብለን በመረጥነው መንገድ ስንጓዝ ለውጥና መሻሻል መንፈስ በሕብረተሰቡ ውስጥ ይሰርፃል። ስለዚህ፣ ልዩነት ባለበት ሁልግዜም አዲስ ነገር አለ። አዲስ ተሞክሮ እና ተጨማሪ ዕውቀት ባለበት እድገትና መሻሻል አለ። በተቃራኒው ልዩነት በሌለበት ማህብረሰብ ወይም ሀገር የለውጥና መሻሻል መንፈስ አይኖርም፣ እድገት እና ብልፅግናን ማረጋገጥ አይቻልም።

ከላይ ለመግለፅ እንደተሞከረው ልዩነት ሊገለፅ የሚችለው የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች በሚያደርጉት ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚዊ እንቅስቃሴዎች፣ እንዲሁም እንቅስቃሴያቸውን ከሚመሩበት የሞራል እሴቶች አንፃር ነው። ይህም አንድ ግለሰብ ወይም ቡድን ከሌላው ጋር በሚያደርገው ግንኙነት የሚገለፅ ይሆናል። አንድ ግለሰብ ከሌላ ግለሰብ/ቡድን፣ እንዲሁም አንድ ቡድን ከሌላ ቡድን/ግለሰብ ጋር የሚያደርገው ግንኙነት የሚመራበት ማህበራዊ ሥርዓት ‘የፖለቲካ ሥርዓት’ የምንለው ሲሆን ግንኙነቱ የሚመራበትን መርህ የሚያስቀምጠው እና የሚቆጣጠረው የፖለቲካ ሃይል አካል ያለው “መንግስት” ነው።

ስለዚህ፣ በምናደርገው ማህበራዊ እንቅስቃሴ ልዩነት እንዲኖር ከተፈለገ የፖለቲካ ሥርዓቱ የዜጎችን ‘ነፃነት’ ማክበርና ማስከባር ይኖርበታል። በአጠቃላይ፣ በማህብረሰቡ ውስጥ የለውጥና መሻሻል መንፈስ እንዲሰርፅ፣ በማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ሕይወት እድገትና ብልፅግና እንዲረጋገጥ፣ የሀገሪቱ የፖለቲካ አስተዳደር ልዩነትን በአግባቡ ማስተናገድ የሚችል መሆነ አለበት።

***********

* ጸሐፊው ስዩም ተሾመ በአምቦ ዩኒቨርሲቲ ወሊሶ ካምፓስ መምህር ሲሆኑ፤ በ [email protected] ኢሜይል አድራሻ ሊያገኟቸው ወይም ሌሎች ጽሑፎቻቸውን http://ethiothinkthank.com ላይ ሊያነቡ ይችላሉ፡፡

Seyoum Teshome is a Lecturer at Ambo University Woliso Campus and head of Management Department. He was born in Arsi, Assela, in 1979 and studied Management at Harameya University and MBA at Mekelle University. He also blogs at http://ethiothinkthank.com

more recommended stories