ሚዲያዎቻችን በህዝብ ዘንድ መታመንን ያስቀድሙ – ሌላው ይከተላል!!

እዚህ ድሬዳዋ በአቶ ሬድዋን ሁሴን እና አቶ ሽመልስ ከማል መሪነት እየተካሄደ ባለው ሀገር አቀፍ የኮሚዩኒኬሽን ፎረም የመጀመሪያ ቀን ከሰዓት ላይ ለተወሰኑ ሰዓታት የመሳተፍ እድል አግኝቼ ነበር፡፡ ውይይታቸው በጣም ደስ የሚል እና ላወቀበት ብዙ ግብዓት የሚገኝበት ነበር፡፡ ዓላማዬ ስለፎረሙ ሪፖርት ማቅረብ ስላልሆነ በዚህ ዙሪያ የምለው ነገር አይኖረኝም፡፡ እኔ በራሴ ግን ቀድሞውንም በዚሁ ዙሪያ ሳብላላቸው የነበሩ ሀሳቦችን በዚህ አጋጣሚ ለማቅረብ እንጂ

ሚዲያዎቻችን ከንጉሱ ዘመን ጀምሮ በመንግስት ፕሮፓጋንዳ መሳሪያነት መንግስት የሚፈልገውን መረጃ መርጦ ወይም ቀባብቶ ለህዝቡ የሚግቱበት ታሪክ ነው ያላቸው፡፡ ይህ በመደረጉ ማን ተጠቀመ. . . መንግስት. ህዝብ ወይስ ሀገር፣ . . . .ማንም አልተጠቀመም፡፡ ይልቁንም ሚዲያዎች ተዓማኒነት እንዳይኖራቸው በማድረግ ህዝብን አስፈላጊ ሲሆን ሞቢላይዝ ለማድረግ ወይም ያልተረጋጉ ሁኔታዎች ሲፈጠሩ ለማረጋጋት እንዳይችሉ ነው ያደረጋቸው፡፡

በደርግ ዘመን ይወርድ የነበረው ያ ሁሉ ፕሮፓጋንዳ ድንጋይ ላይ ውሃ ማፍሰስ እንደነበረ በዛ ዘመን ነፍስ ያወቃችሁ ሰዎች የምትመሰክሩ ይመስለኛል፡፡ በዘመኑ ብዙ ሰዎች ትክክለኛ መረጃ ለማግኘት የአሜሪካና ጀርመን ድምፅ ሬዲዮ ጣቢያዎች ላይ ጥገኞች ነበሩ፡፡

የሩቁን ዘመን እንተወውና ሁላችንም የምናስታውሰውን ምርጫ 97ን ማየት ይቻላል፡፡ በዚያ ዘመን መንግስት በሚዲያዎች ያስተላልፋቸው የነበሩ መረጃዎች ምን ያህል ተዓማኒ ነበሩ፣ ምን ያህልስ የተፈጠሩ ግርግሮችን ለማረጋጋት ይረዱ ነበር፡፡ መረጃዎቹ እውነትም ውሸትም ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ሆኖም ህዝቡ ሚዲያዎችን ስለማያምን በዋና የመረጃ ምንጭነት የሚጠቀማቸው የግል እና የውጭ ሚዲያዎችን፣ እንዲሁም ሰዎች ከሚያውቋቸው ሰዎች የሚሰሟቸውን መረጃዎች ነበር፡፡ አዲስ አበባ አንዱ ያወራው ነገር በቀናት ውስጥ በመላ ሀገሪቱ ሊስፋፋ ይችላል፡፡ በዚህ ሁሉ መሀል ሚዲዎቻችን ስራ አልፈቱም ነበር – የሚሰማቸው/ የሚያምናቸው አልነበረም እንጂ፡፡ ይህ ለሚዲያ ሞት ነው!!Logo - Ethiopian Broadcasting Corporation

ሚዲያዎቻችንን ለፕሮፓጋንዳ መሳሪያነት መጠቀም ውጤቱ ይሔው ነው – ሚዲያዎች ተዓማኒ እንዳይሆኑ ማድረግ፡፡

ባለፉት አመታት የተደረጉ ለውጦች አሉ፤ ለውጦቹ ግን የቅብ( ኮስሞቲክ) እንጂ መሰረታዊ አይደሉም፡፡ ሚዲያዎች ተደማጭነታቸውን ለመጨመር ስፖርት እና መዝናኛን የስራቸው ዋና አካል እያደረጉት ነው፡፡ ይህ ግን ሰዎች የመዝናኛ ፕሮግራሞችን እንዲያዳምጥ ከማድረግ አልፎ መደበኛ ፕሮግራሞቻቸው ተደማጭ እንዲሆኑ ግን ዋስትና አይሆንም፡፡

ሚዲያዎቻችን እየተንቀሳቀሱ ያሉት በጠራ አቅጣጫ አይደለም፡፡ አብዛኛው መንግስታዊ ሚዲያ ልማታዊ ጋዜጠኝነትን እንደመርሁ ቢጠቅሰውም አተገባበሩ ግን ብዙ ጊዜ ለህዝብ የሚያስፈልገውንና የሚጠቅመውን እኔ አውቅለታለሁ የሚል አስተሳሰብ የሚንፀባረቅበት ሆኖ ነው የሚታየው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በመንግስት ስራዎች የሚታዩ እንከኖችን ለመዘገብ ፈራ ተባ የሚል ወይም ለልማቱ አስፈላጊ አይደለም በሚል ሰበብ “ገመና” ደባቂ መሆንን የሚመርጡ ናቸው፡፡ ክፍተቶችን አልፎ አልፎ የሚዘግቡትም በመርህ (በግልፅ ኤዲቶሪያል ፖሊሲ) ላይ ተመስርተው መሆኑን የሚያሳይ ነገር የለውም፡፡

የችግሮቹ ቁልፍ ሚዲያዎች ከራሳቸው ወይም ከህዝብ እና ሀገር ይልቅ ለመንግስት መታመንን ስለሚያስቀድሙ ነው ልማታዊ ጋዜጠኝነትን በአግባቡ መረዳትም መተግበርም ያልቻሉት፡፡ መንግስትም ሚዲያዎች ፕሮፌሽናል አሰራርን እንዲከተሉና ገለልተኛ ሆነው እንዲያመሰግኑት ወይም እንዲተቹት ቁርጠኛ መሆኑን እስካሁን አላሳየንም፤ የወደፊቱን አብረን እናያለን፡፡

እስኪ የተወሰኑ የእስከዛሬ አሰራሮቻቸውን እንይ

1.. መለስ ዜናዊ የሞቱበትን ሶስተኛ አመት መታሰቢያን፣ ወይም የህዳሴው ግድብ ግንባታ የመሰረት ድንጋይ የተጣለበትን 4ኛ አመት፣ ወይም የባራክ ኦባማን ጉብኝት፣ ወይም የብሔር ብሔረሰቦችን ቀንን ፣ . . . . ወዘተ በተመለከተ ሚዲያዎች እንደሚዲያ ተቋም – አዎ እንደ ሚዲያ ተቋም ለሁነቶቹ እንዴት ነው ሽፋን መስጠት ያለባቸው

በተጨባጭ እኔ የምከታተላቸው የመንግስት ሚዲያዎች ለእነኚህ ሁነቶች ክብደት እንደሚሰጧቸው ለማሳየት ይሁን የኢትዮጵያ ህዝብ አንድ ነገር መቶ ጊዜ ካልተነገረው አይገባውም ብለው ስለሚያስቡ ይሁን ባላውቅም ዕለቱ ከመከበሩ በፊትና በኋላ ከአንድ ወር ላላነሰ ጊዜ በማስታወቂያ፣ ዜናና ፕሮግራም እስኪያንገሸግሸን ድረስ ተመሳሳይ መረጃ ሲግቱን ይቆያሉ፡፡ ይህ ሚዲያን ከፕሮፓጋንዳ መሳሪያነት ለይቶ ማየት የማይችለው ነባሩ አስተሳሰብ ውጤት እንጂ ፕሮፌሽናል ጋዜጠኛ ቀርቶ ምክንያታዊ አስተሳሰብ ያለው አንድ ተራ ሰው እንኳ የሚያደርገው ነው ለማለት ያስቸግረኛል፡፡

2.. በሀገራችን አለምአቀፍ የፋይናንስ ጉባዔ ሲካሄድ፣ ኦባማ ሲጎበኙን፣ ወይም ጠቅላይ ሚኒስትራችን ወደውጭ ለጉብኝት ሲሄዱ ፣ . . . ወዘተ ሚዲያዎቻችን ጥቅል ነገር ካልሆነ የረባ መረጃ ሰጥተውን አያውቁም፣ ዝርዝር መረጃዎችን ስንፈልግ ወደውጭ ሚዲያዎች የምናማትርበት ጊዜ ቀላል አይደለም፡፡ ለምሳሌ በፋይናንስ ጉባኤው ላይ ሁለት ፅንፍ የያዙ ሀሳቦች መስማማት ባልቻሉበት ሁኔታ ኢትዮጵያና ደቡብ አፍሪካ አማራጭ ሀሳብ ማቅረባቸውን እና ሌሎችንም ዝርዝር መረጃዎችን የሰማሁት ከውጭ ሚዲያዎች ሲሆን ጉባዔው ከተጠናቀቀ በኋላ የውጭ ጉዳይና ፋይናንስ ሚኒስትሮቻችን ጋዜጣዊ መግለጫ ሲሰጡ ነው የኛዎቹ ሚዲያዎች ስለሁኔታው ሰምተው ያሰሙን፡፡ ይህ የፕሮፌሽናል እውቀት ማነስ ሊሆን ይችላል፤ በተጨማሪም በኦፊሴል የመንግስት አካላት መግለጫ ካልሰጡበት ዜናን ማነፍነፍና የመረጃ ምንጮቻቸውን ማስፋት እንዳለባቸው ካለማወቅም ሊሆን ችላል፡፡

3.. አንድ አለምአቀፍ ኩባንያ ኢትዮጵያ ውስጥ ኢንቨስት ለማድረግ እንቅስቃሴ ከጀመረ ነገርዬውን ከኢትዮጵያ ሚዲያዎች የምንሰማው በቤተመንግስት ወይም ውጭ ጉዳይ ኦፊሴላዊ መግለጫ ከተሰጠ ብቻ ነው፡፡ሌሎችም የኛ ሚዲያዎች ያልሰሟቸው በውጭ ሚዲያዎች የሚዘገቡ የሐገር ውስጥ ዜናዎች እጅግ በርካታ ናቸው – ለምሳሌ ሲጋራ ህዝብ በተሰበሰበባቸው ቦታዎች ማጨስ መቀሌ ላይ መከልከሉን ለመጀመሪያ ጊዜ የሰማሁት ከውጭ ሚዲያ ነው፡፡ ይህም ሚዲያዎቻችን የመረጃ ምንጮቻቸውን ኦፊሴላዊ መድረኮችን ብቻ በማድረጋቸው፣ እንዲሁም በቁርጠኝነት እና አቅም ማነስ የሚፈጠር ነው፡፡

4.. እስኪ የኢቢሲን ሎጎ ተመልከቱት፤ አረንዴ-ቢጫ-ቀይ መሀሉ ላይ በሰማያዊ ኢቢሲ ፊደሎች ተፅፈዋል፡፡ ይህ እንግዲህ ቀድሞ በጎጆ ቤት አናት ላይ አንቴና ያነበረበትን ለረጂም ጊዜ የቆዬ ሎጎ የተካው አዲስ ሎጎ ነው፡፡ሎጎው ፌደራላዊት ኢትዮጵያን እንጂ ሚዲያውን የሚገልፅ ነገር የለውም፤ መሪቃሉ የሆነው የህዳሴና የብዝሀነት ድምፅ የሚለውም እንዲሁ ከሚዲያ ተቋም ይልቅ ኢትዮጵያን የሚገልፅ መሪ ቃል ነው፡፡ ከድሬቲቪ እና ኤሪቲቪ ጀምሮ የትም ሀገር ብትሄዱ እንደዚህ አይነት ሚዲያነቱን ረስቶ ፖለቲካ ማስተማርን ያስቀደመ ቀሽም ሎጎና መሪቃል አይቼ አላውቅም( በነገራችን ላይ የድሬ ቲቪ መሪ ቃል የእርሶ ቀዳሚ የመረጃ ምንጭ የሚል ነው) ሎጎው ግን ሚዲያዎቸችን በሚናቸው ላይ ያላቸውን የተሳሳተ ግንዛቤ በከፊል የሚያሳይ ነው፡፡

5.. ዘንድሮ የኤልኒኖን ክስተት ተከትሎ የዝናብ እጥረት ተከስቷል፤ ልብ በሉ እጥረቱ የተከሰተው ክረምት ላይ ሳይሆን ከዚህ ቀድሞ በበልግ ጊዜ ጀምሮ ነው፡፡ ሆኖም በልግም አልፎ ክረምትም ተጋምሶ ነሀሴ ሲገባ ነው ሚዲያዎች ዜናውን የነገሩን፡፡ መንግስት ምርጫ፣ የፋይናንስ ጉባዔና የኦባማ ጉብንት ተከታትለው ስለመጡበት ትኩረታችን በሙሉ በጎ በጎው ላይ እንዲሆን ሊፈልግ ይችላል( ይህ በራሱ ትልቅ ስህተት ነው) ሆኖም በዚህ ጊዜ ሚዲያው አብሮ ማሽቃበጥ ሳይሆን ምን እየሰራችሁ ነው ብሎ መጠየቅ ነበረበት (በዚህ ረገድ ሁሉም ላይ ክፍተት ቢኖርም ቀድሞ ዝምታውን የገፈፈው የአማራ ቲቪ ሊመሰገን ይገባል)፡፡

ይህ አንድ ክስተት ነው፤ በሌሎችም ሀገራዊና አካባቢያዊ ጉዳዮች ላይ መንግስትን ከመጠበቅ ይልቅ መንግስትን መጠየቅ ያለብን ሁኔታዎች መኖራቸውን ማሰብ ይጠይቃል፡፡ ለዚህ ደግሞ የሚዲያ ተቋማት በእስካሁን የመንግስት አገልጋይነት አስተሳሰባቸው ሳይሆን ራስን አስፈላጊ ሲሆን ከመንግስት በላይ አድርጎ በማየት የሚመጣ ነው (4ኛ መንግስት የሚሉትን ያስታውሷል)፡፡

6.. መንግስት የስርዓቱ ዋና አደጋ ሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነት ነው ሲል ንግግር ለማሳመር አይመስለኝም፡፡ በዚህ ረገድ ቁርጠኛ ከሆነ ሚዲያዎች ገመና መሸፈን ወይም ሁሉን ነገር አልጋ ባልጋ አድርጎ ማሳየት ማቆም አለባቸው፡፡ ይህ ማለት ስህተት ፈላጊ መሆን አለባቸው ማለት አይደለም፡፡ ሆኖም የሙስና ወይም የዝርክርክነት ዜናዎች ሲዘገቡ መንግስት የሚተችባቸው ለተወሰነ ጊዜ ብቻ ነው – በዚህ ረገድ በቁርጠኝነት እና በዘላቂነት ከተሰራ ትችቶቹ ከመንግስት ወርደው ወደግለሰቦቹ ይሸጋገራል (መንግስት እነሱን መሸከም እንደማይፈልግ ስለሚታወቅ)፡፡ እስካሁን ግን መንግስት ብቃት ያነሳቸውን እና የብልሹ ሹማምንቶቹን ገመና መሸፈን በመምረጡ የነሱ ጥፋት የመንግስት ጥፋት ሆኖ ቆይቷል፡፡ በሙሰኞች ላይ የሚወሰደው እርምጃም አልፎ አልፎ ብቻ ስለሆነ የመንግስት ቁርጠኝነትን ከማሳየት ይልቅ ለሌሎች አሉባልታዎች መፈጠር መንስዔ ነው እየሆነ ያለው፡፡

ባጠቃላይ ሚዲያዎቻችን ከሁሉ አስቀድሞ በህዝብ ዘንድ ተዓማኒ መሆንን ግባቸው ሊያደርጉ ይገባል፤ ሲቀጥል ብልሹ የመንግስት አካላት የሚፈሯቸው መሆን አለባቸው፡፡ መንግስት በቂ ነፃነት ሊሰጣቸው እና ዘገባዎቻቸውንም በግብዓትነት የሚጠቀምበት ሊሆን ይገባልፕሮፌሽናሊዝምን መርሃቸው ሊያደርጉ ይገባል፡፡ በልማታዊ ጋዜጠኝነት ሽፋን በነባሩ አሰራር ለመቀጠል የሚደረግ ጥረት በዝምታ መታየት የለበትም፡፡ የታዩ ክፍተቶች 100 ፐርሰንት ይጋለጡ ማለት ባይቻል እንኳ በዚህ ሰበብ ሙሰኞች ሽፋን እየተሰጣቸው ሊቀጥሉ አይገባም፣እዚህ ላይ ግልፅ አቋም ሊኖር ይገባል፤ ተግባራዊ እንዲሆንም በቁርጠኝነት ሊሰራ ይገባል፡፡

ያኔ ህዝቡ ብልሹነትን መንግስት እንደሚሸፋፍን ያስቡ የነበረውን ትተው ከመንግስት ጎን ሙስናና ብልሹ አሰራርን ለመዋጋት ይሰለፋሉ፤ መንግስት በፖሊሲዎቹ እንጂ በግለሰቦቹ ዝቅጠት መተቸቱ ይቀራል፡፡ ህዝብም ለአሉባልተኞችና ስህተት ፈላጊ ሚዲያዎች አይጋለጥም፡፡ ከዚህ በኋላ ነው ሚዲያዎች በአግባቡ ልማትን ደገፉ ማለት የሚቻለው፡፡ ያኔ ሚዲዎች ተደማጭ ለመሆን ድራማ ወይ ስፖርት መቀላቀል ላያስፈልጋቸው ይችላል፡፡

************

አዲስ ከድሬዳዋ - Frm. journalist; currently communicator

more recommended stories