የኢኮኖሚ እድገታችን እዳ ከፋዮች

(አዲስ ከድሬዳዋ)

መንግስት ትላልቅ ፕሮጀክቶችን ተግባራዊ በማድረግና በሚፈለገው ደረጃ ባይሆንም ኢንቨስትመንቶችን በማስተናገድ ኢኮኖሚው እያደገ ነው፡፡ ዋነኛው የኢኮኖሚ አንቀሳቃሽና የስራ እድል ፈጣሪ መንግስት በሆነበት ሁኔታ በመንግስት ሜጋ እና ትናንሽ ፕሮጄክቶች አማካኝነት ወደገበያው እየተለቀቀ ያለው ገንዘብና ከገበያው የሚሰበሰበው የገንዘብ መጠን ልዩነቱ ሰፊ በመሆኑ የግሽበት ተጋላጭነታችን ከፍተኛ ነው፡፡ ባንድ ወቅት ከ40 ፐርሰንት በላይ ደርሶ የነበረው የሀገራችን የዋጋ ግሽበት አሁን ወደ ባለአንድ አሀዝ ግሽበት(ከ10 ፐርሰንት በታች) መውረዱ እንደትልቅ ስኬት እየተነገረ ነው፡፡

ለመሆኑ ቀድሞ ነገር ኢንፍሌሽኑ እንዴት ጀመረ፣ አሁንስ እንዴት ሊቀንስ ቻለ

ኢንፍሌሽኑ የጀመረው በተደጋጋሚ እንደሚነገረው መንግስት በሚያስተገብራቸው በርካታ ፕሮጀክቶች አማካኝነት ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ወደገበያው እየለቀቀ ስለሆነ ነው፡፡

በኢኮኖሚስቶች የሚመከረውና መንግስት ኢንፍሌሽኑን ለማረጋጋት መውሰድ ያለበት እርምጃ በዋናነት ወደገበያው እየለቀቀው ያለውን ገንዘብ መቀነስ ነው፡፡ መንግስት ግን ይህ ኢኮኖሚያዊ እድገቱን ያቀዘቅዝብኛል በሚል ተመራጭ እርምጃ አድርጎ አልወሰደውም፡፡ አንድ አመት በከፊል ሞክሮት የነበረ ቢሆንም ቀጣይነት ግን አልነበረውም፡፡ መንግስት ይልቁንም በገበያው ላይ ያሉ ተጫዋቾች ላይ ቁጥጥሩን በማጥበቅ፣ ቁጠባን በማበረታታትና የግብር መሰብሰብ አቅሙን ለማሳደግ ጥረት በማድረግ ነው ችግሩን ለመፍታት የሞከረው፡፡ በእርግኑን ይህንን አማራጭ በመከተሉ ፈጣን ኢኮኖሚያዊ እድገቱ ሳይቀዛቀዝ ኢንፍሌሽኑን በእጅጉ መቀነስ ችሏል፡፡ ሆኖም ለዚህ የተወሰኑ ዜጎች ያለአግባብ ዋጋ እንዲከፍሉም ተደርጓል፡፡Photo - Ethiopian_currency

ሁለቱን ልጥቀስ

የመንግስት ሰራተኞች፡- በ1994 ዓ.ም. የነበረው 400 ብር የመግዛት አቅም በ2004 ከነበረው 1000 ብር ጋር ተመጣጣኝ በሆነበት ሁኔታ የመንግስት ሰራተኞች ደሞዝ በእነኚህ አስር አመታት 250 ፐርሰንት ሊያድግ ይገባ ነበር፤ የኢኮኖሚያዊ እድገቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ከተፈለገ ደግሞ ከዚህም በላይ ሊጨመርላቸው ይገባ ነበር፡፡ በተጠቀሱት አመታት የነበረው ጭማሪ ግን 100 ፐርሰንት እንኳ የሚሞላ አልነበረም፡፡ ልዩነቱን መንግስት በተለያዩ ዘርፎች ኢንቨስት እያደረገው ነው፡፡ አዎ መንግስት ኢፍትሀዊ በሆነ መንገድ ከመንግስት ሰራተኞች ገንዘብ እያስቀረ ልማቱን እየደጎመበት ነው፡፡ በዚህ ጊዜ ግን በሌሎች ዘርፎች የተሰማሩት ከመንግስት ሰራተኞች ጋር ያላቸውን የኑሮ ልዩነት በእጅጉ እያሰፉ ነው፡፡ቀድሞ በግል ስራ ላይ በተሰማራ ባለሙያና በመንግስት ሰራተኛ መካከል የነበረው የኑሮ ልዩነት እምብዛም ነበር፤ አሁን ለንፅፅር እንኳ አይቀርብም፡፡

የሀገራችን ኢኮኖሚ በዘመነ ደርግ ባለበት የሚረግጥና ወደታች ያሽቆለቁል የነበረ ቢሆንም በዚህ ሁኔታ ውስጥ የነበረው የያኔው የመንግስት ሰራተኞች የኑሮ ደረጃ ግን አሁን ፈጣንና ተከታታይ እድገት እያስመዘገብን ካለንበት ወቅት ጋር ሲነፃፀር በእጅጉ እንዳሽቆለቆለ ማንም ሊረዳው የሚችለው ነገር ነው፡፡ በዚህ ረገድ መንግስት በተደጋጋሚ ደሞዝ ሲጨመር የምርቶችና አገልግሎቶች ዋጋም የመጨመር ስጋትን ደሞዝ ላለመጨመር በተደጋጋሚ በሰበብነት ሲናገር ብንሰማውም መንግስት ልቆጣጠረ ካለ እንደሚችል ግን ባለፈው አመት አሳይቶናል፡፡ አስቀድሞ ከረጂም አመታት በፊት ዝግጅት ሳይደረግ በተደረገ የደሞዝ ጭማሪ ተከስቶ የነበረውን የዋጋ መናር በተደጋጋሚ እየጠቀሱ ደሞዝ ላለማስተካከል ሰበብ ማድረግ መንግስት ሰራተኛው የኢንፍሌሽኑን ዋጋ እንዲሸከም ሆን ተብሎ የተደረገ ነው ወይ ያስብላል፡፡

ገበሬዎች፡- ሁሉም ሳይሆኑ የምግብ እህል አምራቾችም በቀጥተኛና ተዘዋዋሪ ጥብቅ ቁጥጥር የሚያመርቱት የምግብ እህል ዋጋ ኢንፍሌሽኑን ተከትሎ ማደግ ጀምሮ የነበረ ቢሆንም የመንግስት ጥብቅ ቁጥጥር ግን ከተወሰነ ጊዜ ጀምሮ ከሞላ ጎደል ዋጋው ባለበት እንዲቆም አድርጎታል፡፡ እናም በተወሰነ ደረጃ እህል አምራች ገበሬዎችም ተጎጂ ነበሩ ማለት ነው፡፡

በርግጥ እንደአጠቃላይ ዋጋ ርካሽ የሆነባት ሀገር ኢንቨስትመንትን ለመሳብና ለማደግ፣ እንዲሁም በቀላሉ ለዜጎቿ መኖሪያነት ምቹ ለማደረግ አትከብድም፡፡ ሆኖም በቁጠባም ሆነ በግብር ሊሰበሰብ ከሚችለው በላይ ከፍተኛ ገንዘብ ወደገበያው እየለቀቁ ኢንፍሌሽን(የዋጋ ውድነት) እንዳይኖር መመኘት የዋህነት ነው፡፡ ገንዘቡን እየለቀቅን ኢንፍሌሽን እንዳይኖር ማድረግ ቻልን ማለት ደግሞ እዳውን የተሸከመ ወይም የወደቀበት የተወሰነ የህብረተሰብ ክፍል አለ ማለት ነው

አንድ ምሳሌ እንጥቀስ፡፡ የሐገራችን ጤፍ አምራች ገበሬዎች እንደ ሰሊጥና ቡና አምራች ወገኖቻቸው ምርታቸውን ወደውጪ እንዲልኩ ቢፈቀድላቸው የጤፍ ዋጋ አሁን ካለበት 1600 ብር ምናልባት በአጭር ጊዜ በእጥፍ ሊያድግ እንደሚችል መገመት አይከብድም፡፡ የሐገራችንን ጤፍ ኤርትራውያንና እስራኤል ያሉ ቤተእስራሌሎችን ጨምሮ በመላው አለም የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ሌሎች የጤፍን ተፈላጊነት የሰሙ ሁሉ ይፈልጉታል፡፡ አለም አቀፍ የጤፍ ምርት ደግሞ ይህንን ፍላጎት መሸፈን የሚችል አይደለም፡፡ በቅርቡ ለንደን ውስጥ በትንሽ የፕላስቲክ ከረጢት የታሸገ ጤፍ ዱቄት 40 ፓውንድ ሲባል ሰምቻለሁ(ኪሎው ትንሽ ነው በግምት ከ2 – 4)፡፡ አሜሪካ ኤክስፖርት የተደረገ እንጀራ ዋጋም እጅግ የተጋነነ ነው፡፡ መሃል ላይ ያሉ አቀባባዮች ከጨመሩት እሴት እጅግ የበለጠ ትርፍ እንዲያገኙ ያስቻላቸው ገበሬው ጤፍን ገበያው ነፃ ቢሆን ሊሸጥ በሚችልበት ዋጋ እንዳይሸጥ በመደረጉ ነው፡፡በገበያ ዋጋ ይሽጥ ቢባል ጤፍ በቀላሉ 3000 ብር ሊገባ ይችላል፡፡ ይህ ደግሞ ሸማቹ ላይ ከሚፈጥረው ጫና ባሻገር የሌሎች ምርትና አገልግሎቶቸም ዋጋ እንዲጨምር በማድረግ ኢንፍሌሽኑን ሊያባብስ ስለሚችል ጥብቅ ቁጥጥር እየተደረገበት ነው፡፡ ለዚህም የአማራና ኦሮሚያ ጤፍ አምራቾች ገበያው የሚፈቅድላቸውን ዋጋ እንዳያገኙ በማድረግ ኢንፍሌሽኑ እንዳያንሰራራ እየተደረገ ነው፡፡

ባጠቃላይ በእድገታችን የምንኮራውን ያህል እድገቱ ሁሉንም ተጠቃሚ አለመድረጉና ይባስ ብሎ ዋጋ እያስከፈላቸው ያሉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች መኖራቸው የሆነ ማስተካከያ ሊደረግ እንደሚገባ አመላካች ነው፡፡ ለእድገቱ ዋጋ እየከፈሉ ያሉ በሆነ መልኩ ሊካሱ ይገባል፡፡

************

አዲስ ከድሬዳዋ - Frm. journalist; currently communicator

more recommended stories