ከጓንታናሞ እስከ ማዕከላዊ፡ ክፍል 3 – “የአሸባሪዎች ሕግ”

በዚህ “ከጓንታናሞ እስከ ማዕከላዊ” በሚለው ተከታታይ ፅሁፍ፤ በክፍል-1 “የፀረ-ሽብር ሽብር” – የሽብር ጥቃትን በፀረ-ሸብር ጦርነት/ዘመቻ መፍትሄ ለመስጠት መሞክር በተሳሳተ እሳቤ ላይ የተመሰረተ ስለመሆኑ ተመልክተናል። በክፍል-2 ደግሞ “ፍርሃትን በፍርሃት” በሚል ርዕስ የአሸባሪዎችን ጥቃት በፈጠረው ፍርሃትና ስጋት ውስጥ ሆኖ የሚወሰድ የፖለቲካና ወታደራዊ እርምጃ ውጤቱ ሌላ ተጨማሪ ፍርሃትና ስጋት እንደሆነ አይተናል። የዚህ ክፍል ዋና ትኩረት ደግሞ “የሕዝብን ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ በሚል በመንግስት የሚወሰዱ ማናቸውም ዓይነት እርምጃዎች የዜጎችን ነፃነት መገደብ የለባቸውም” የሚለው ፅንሰ-ሃሳብ ነው። በዚህ መሰረት፣ ሀገርና ህዝብን ከሽብርና አሸባሪነት ለመከላከል የሚወሰዱ የፀጥታና ደህንነት ስራዎች ከዜጎች ነፃነት ጋር ያላቸውን ቁርኝነት በዝርዝር እንመለከታለን። በተለይ ሽብርተኝነትና የሽብር ወንጀሎችን ለመከላከል የወጡ የሕግ አዋጆች የዜጎችን መብትና ነፃነት ከማረጋገጥ አንፃር ያላቸውን አሉታዊ ተፅዕኖ በዝርዝር ለማየት እንሞክራለን።

ባለፉት ክፍሎች በተደጋጋሚ ለመግለፅ እንደሞከርነው፣ የአሸባሪዎች መሰረታዊ ዓላማ በሕብረተሰቡ ውስጥ የፍርሃትና ስጋት ድባብ መፍጠር ነው። ስለዚህ፣ የሽብር ጥቃትን ለመከላከል በሚል የሚወጡ አዋጆችና መመሪያዎች ለዚህ የአሸባሪዎች ዓላማ ተገዢ መሆን የለባቸውም።

ነገር ግን፣ የአሜሪካ መንግስት የበላይ አቃቢ-ህግ የሆኑት “Eric Holder” በፕ/ት ጆርጅ ቡሽ የፀረ-ሽብር ጦርነት ከአሜሪካኖች የሲቪል ነፃነት ጋር የዜሮ-ድምር ግብግብ ውስጥ እንደነበር እንዲህ ሲሉ ይገልፃሉ፤ “Too often over the past decade, the fight against terrorism has been viewed as a zero-sum battle with our civil liberties,…Not only is that school of thought misguided, I fear that in actuality it does more harm than good.” በዚህ መሰረት፣ የሽብር ጥቃቱ በፈጠረው ፍርሃትና ስጋት ውስጥ ሆኖ የሚወጡ የሕግ አዋጆች እና መመሪያዎች ከዜጎች ነፃነትና መብት አንፃር አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሚፈጥሩ መገንዘብ ይቻላል።

በዚህ ረገድ፣ የቀድሞዋ እንግሊዝ የሀገር ውስጥ ደህንነት (MI5) ዳይሬክተር “Eliza Manningham Buller” በሽብር ጥቃት ማግስት የሚወጡ ሕጎች በአብዛኛው ስህተት ናቸው በማለት ትናገራለች። እንደ እሷ አገላለፅ፡-

“…political and media pressure to “do something” in response to such events can lead to unnecessary, even counter-productive initiatives and new laws, which may offer false assurance that they will prevent the recurrence of the event which triggered them. …

Certainly rushing to legislate in the wake of a terrorist atrocity is often a mistake. It may be a well-intentioned mistake, designed to make us safer, but it would be better to reflect on the long term wisdom of what may look immediately appealing. Since 9/11 there has been a slew of counter-terrorist legislation, some of it helpful, some of it justified as exceptional, partly because of the “War on Terror” language. Quite rightly it has been scrutinized by parliament and the courts and some of it amended. Laws which involve reducing people’s rights can themselves frighten the public.”

የአልቃይዳ የሽብር ጥቃትን ተከትሎ የወጣውና አሜሪካ በታሪኳ ለፈፀመችው አሳፋሪ የነፃነትና መብት ጥሰት በዋና ምክንያትነት የሚጠቀሰው “የ9/14 ሕግ” ከላይ ለተጠቀሰው የ“Eliza Manningham Buller” ሃሳብ ጥሩ ማሳያ ነው። ይህ፣ የመስከረም 1 (9/11) የሽብር ጥቃት በደረሰ በሦስተኛው ቀን፣ እ.አ.አ መስከረም 14, 2001 ዓ.ም፣ በሀገሪቱ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት የፀደቀውና ለፕረዜዳንት ፍፁም የሆነ ስልጣን የሚሰጠው፣ እንዲሁም ይህ ሕጉ በፀደቀ ሌላ ሦስተኛ ቀን፣ እ.አ.አ መስከረም 17, 2001፣ ፕ/ት ጆርጅ ቡሽ ለሀገሪቱ የደህንነት መስሪያ ቤት (Central Intelligence Agency – CIA) ከአሜሪካ ግዛት ውጪ የሚስጥር እስር ቤቶችን እንዲያቋቁምና የስቃይ-ምርመራ እንዲያደርግ መመሪያ ለመስጠት ያበቃቸው ሲሆን፣ እሱም የሚከተለውን ነው፡-

“The president is authorized to use all necessary and appropriate force against those nations, organizations, or persons he determines planned, authorized, committed, or aided the terrorist attacks that occurred on September 11, 2001, or harbored such organizations or persons, in order to prevent any future acts of international terrorism against the United States by such nations, organizations or persons.”

በዚህ አንቀፅ መሰረት የተሰጠው ስልጣን ፕረዜዳንቱን ፍፁም አምባገነናዊ ከማድረጉም በላይ፣ የትኛውም የዓለም ክፍል የሚገኝ ሀገር፣ ድርጅትና ሰው ላይ የፍርሃትና ስጋት ድባብ የፈጠረ ነበር። ምክንያቱም፣ ለምሳሌ ልክ እንደ አፍጋኒስታን በትክክለኛ መረጃ ወይም ደግሞ እንደ ኢራቅ በተሳሳተ መረጃ ወታደራዊ እርምጃ ሊወሰደብት ይችላልና።

ያኔ የፀረ-ሽብር ጦርነቱ ሲታወጅ ፕረዜዳንት ጆርጅ ቡሽ “ወይ ከእኛ ጋር ናችሁ፣ አሊያም ከአሸባሪዎች ጋር ናችሁ!” የሚል ጅምላ-ፍርጃ ሲያስቀምጡ ያልደነገጠ የሀገር መሪ አልነበረም። የአሜሪካኖች ማስጠንቀቂያ ፍርሃት የወለደው ሌላ ፍርሃት ስለነበር በእርግጥ ያስፈራል። የአልቃይዳ የሽብር ጥቃትን ተከትሎ አሜሪካ ራሷን ወደ “ዓለም-አቀፍ አሸባሪነት” ተቀይራ ነበር። በፍርሃት ወደ አስፈሪ እብደት ከተቀየረችው አሜሪካ ጋር አብረው ካበዱ ሀገሮች አንዷ ኢትዮጲያ ናት። ለዚህም በሃሰት መረጃ ላይ ለተመሰረተው የኢራቅ ጦርነት ኢትዮጲያ የአየር ክልሏን ለአሜሪካን ጦር ስትፈቅድ የቀደማት አልነበረም።

ከአሜሪካን ጋር አብራ ያበደችው ኢትዮጲያ እብደቷ የአየር ክልል በመፍቀድ ብቻ አላበቃም። በፀረ-ሽብር ስም ጭራሽ የራሷን ሕዝብ የሚያሸብር የፀረ-ሽብርተኝነት አዋጅ እስከማውጣት አድርሷታል። የኢትዮጲያ የፀረ-ሸብር አወጅ ከአሜሪካኖቹ የፀረ-ሸብር ጦርነት የባሰ በተሳሳተ እሳቤ ላይ የተመሰረተ፣ ከአሸባሪዎች የበለጠ ዜጎችን በፍርሃትና ስጋት የሚያርድ ነው። ይህ ሕግ የዜጎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ከመሸራረፍና ከሕገ-መንግስቱ መርሆች ጋር ተፃራሪ ከመሆኑም በተጨማሪ መሰረታዊ ዓላማውን የሳተ ነው። በመሰረቱ፣ የፀረ-ሽብር ሕጉ የፀደቀበት ዓላማ ህዝቡን ከሽብር ጥቃት ለመከላከል ሳይሆን ንቁ የሆነ የፖለቲካ እንቅስቃሴና ተሳትፎ እንዳይኖር ለማገድ ይመስላል። በዚህ ላይ በቅርቡ የወጣው የኮምፒውተር ወንጀል አዋጅ ሲጨመርበት፣ በሀገሪቱ የፖለቲካ ነፃነት የሚባል ነገር ተሟጥጦ እንዲጠፋ ምክንያት ሆኗል።

በኢትዮጲያ የፀረ-ሽብር ሕግ መሰረት ማንኛውም የፖለቲካ እንቅስቃሴ “በአሸባሪነት” ሊያስከስስ ይችላል። ለምሳሌ፤ “‘የፀረ-ሽብር ሕጉ ይሻሻል!’ የሚል መፈክር ይዛችሁ ውጡ” ማለት – “አመፅና ሁከትን በማነሳሳት – ‘inciting violence and protest’” በሚል ያስከስሳል፤ በሰላማዊ ሰልፍ መንገድ ከተዘጋ – “የሕዝብ አገልግሎትን በማቋረጥ – “disruption of public services’” በሚል አንቀፅ፤ ሰልፈኞቹን “አይዟችሁ በርቱ” ብሎ የተናገረ – “ለአሸባሪዎች የሞራል ድጋፍ በመስጠት – ‘providing moral support or …advice’”፤ “ኦነግ በሰላማዊ መንገድ’ ለመታገል ቆርጧል” ማለት – “አሸባሪነትን በማበረታታት – ‘encouragement of terrorism’” በሚለው አንቀፅ ያስከስሳል። አሁን ባለው ሁኔታ፣ ጠዋት አሸባሪነትን ለመቃወም አደባባይ የወጣ ከሰዓት “በሽብር ወንጀል ተከሶ” ራሱን ማዕከላዊ እስር ቤት ሊያገኘው ይችላል።

የኢትዮጲያ የፀረ-ሸብርተኝነት አወጅ፤ የዜጎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች የሚሸራርፍና የሕገ-መንግስቱ መርሆች የሚፃረር፤ በዚህም ከአሸባሪዎች ጥቃት የበለጠ ኢትዮጲያኖችን እያሸበረ ነው። በተለይ ለአዲሱ ትውልድ ትልቅ የፍርሃትና ስጋት ምንጭ ሆኗል። አብዛኞቹ በማዕከላዊ እስር ቤት የሚገኙ እስረኞች የዚህ ሕግ ሰለባዎች ናቸው። በዚህ መሰረት፣ የሀገራችን የፀረ-ሽብርተኝነት አዋጅ የዜጎችን መብትና ነፃነት የሚገድብና የፍርሃትና ስጋት ምንጭ በመሆኑ መሰረታዊ ዓላማውን ስቷል። እንደ “Eliza Manningham Buller” አገላለፅ፡-

“…What terrorism does is frighten us through its random effect and deter us from behaving normally. But we compound the problem of terrorism if we use it as a reason to erode the freedom of us all. ….We must recognize the limits of what any government can do and be deeply cautious of anything that leads to security being seen as the opposite of liberty rather than essential to it.

Governments should aim to limit and reduce the threat of terrorism, encourage its causes to be recognized and addressed, protect what it can, and be ready to react with calm when it happens, reasserting our belief in our freedoms and the rule of law. …[Generally], governments need to practice a foreign policy that, while acknowledging the world as it is, tries to secure freedom for others – and to pursue a domestic policy that protects the liberties we value and which the terrorist tries to destroy.”

በአጠቃላይ፣ ሽብርን በሌላ የሽብር ለመከላከል የሚደረገው ጥረት በራሱ አሸባሪነት ነው። የሽብር ወንጀልን ለመከላከል በሚል የወጣው የኢትዮጲያ የፀረ-ሽብርተኝነት አዋጅ የዜጎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብትና ነፃነት በመገደቡ የህዝብን ሰላምና ደህንነት ሳይሆን፣ የአሸባሪዎች ዓላማና ግብ ማስፈፀሚያ እየሆነ ነው። በመሆኑም፣ የፀረ-ሽብርተኝነት አዋጁ በእውን የእኛ ሳይሆን ፍርሃትና ስጋትን በህዝብ ላይ ለመጫን የሚሰሩት “የአሸባሪዎች ሕግ” ሆኗል። በመጨረሻም፣ በኢትዮጲያ በፀረ-ሽብር ወንጀል ተጠርጥረው በማዕከላዊ በታሰሩ እስረኞች ላይ ዛሬም ድረስ የስቃይ ምርመራ መኖሩንና ከዚያ ጋር ተያይዞ ያለውን የተሳሳተ እሳቤ በክፍል.4-“እውነትን በጉልበት” በሚል ርዕስ ተመልሰን እንገናኛለን።

*********

ከጓንታናሞ እስከ ማዕከላዊ ተከታታይ ፅሁፍ

-> ክፍል 4 – “እውነትን በጉልበት”

Seyoum Teshome is a Lecturer at Ambo University Woliso Campus and head of Management Department. He was born in Arsi, Assela, in 1979 and studied Management at Harameya University and MBA at Mekelle University. He also blogs at http://ethiothinkthank.com

more recommended stories