መታመን ከወዴት አለ? | የኢትዮጵያውያን ጓዳ(ክፍል-1)

(ፀጋዝአብ ለምለም ተስፋይ)

ሀገራችን ኢትዮጵያ በዓለም ከምትታወቅባቸው ነገሮች አንዱና ዋነኛው ረዥም ጊዜ ያስቆጠሩና አኩሪ ታሪክ ያላቸው የሃይማኖት ተቋማት መገኛ መኾኗ ነው፡፡ ይህም ረዥም ታሪክ ያለው ከጥንት ጀምሮ በታሪክ የሚታወቅ – ዛሬ ደግሞ በኹለንተናዊ የአኗኗር ዘይቤ ውስጥ የሚገለጥ ሰለመኾኑ የማይሳት ጥሬ ሃቅ ነው፡፡

ሃይማኖተኛነት በጽንሰ ሀሳብ አልያም በይዘት ደረጃ ሁለት ዐበይት የተሳሰሩ ቁልፍ አምዶችን የያዘ ነው፡፡ ማመንና መታመንን – አንዱ ከሌላኛው ጋር እጅጉን የተጣመረና ተለያይቶ የማይታይ የአማኝነት መገለጫ ነው፡፡ እነዚህም ሃይማኖት ያለውና የሌለውን የመለያ መስመሮች ናቸው፡፡

ይህም በመኾኑ የቀደሙ አባቶቻችን ከጥንት አንሥቶ በሕገ ልቦና ፈጣሪያቸውን ያመልኩ እንደነበር – ኃላም በሕገ ኦሪት ይገዙና ይፈጽሙ እንደነበር – በጊዜ ሂደት ደግሞ በሕገ ወንጌል እንዲሁ አምነውና ታምነው እየኖሩ ከክርስትናው ባሻገር በየዘመናቱ የተነሡ አዳዲስ ዕሳቤዎችን በነጻ ፍቃድ እየተቀበሉ በ7ኛው ክፍለ ዘመን ደግሞ እስልምና ወደ ሀገራችን እንደገባ የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ፡፡

Photo - Collage of various Ethiopian religious events
Photo – Collage of various Ethiopian religious events

የማመን ብቻ ሳይኾን የመታመን መገለጫ የኾኑ ሌላውን የማክበር፣ እንግዳ ተቀባይነት፣ የመደጋገፍና የመረዳዳት ዕሴት፣ አርቆ ማሰብ፣ ይሉኝታ፣ የሌላውን ነጻ ፍቃድ ማክበር፣ ፈሪሃ ፈጣሪ፣ ለእውነት የመቆም – – – ወዘተ ሃይማኖታዊ ጠባያት በዘመኑ እንደነበረው የሰው ልጅ የአመለካከትና አስተሳሰብ ደረጃ እንደነበራቸው በተለያዩ ያለፉ የአኗኗር አሻራዎቻችን ላይ የታዩ ኹለንተናዊ ገጽታዎቻችን ናቸው፡፡

 የሃይማኖት ዕሳቤና አስተምህሮት ልዩነት እንኳ ቢኖር ሁሉንም የጋራ የሚያደርጋቸው ለእውነት የመቆም፣ ሃቀኛነት፣ ራስ ላይ እንዲደርስ የማይፈልጉትን ሌላው ላይ አለማድረስ ይልቁንስ ለራስ እንዲደረግ የሚሹትን ለሌላው ማድረግ፣ ግልጽነት፣ አሳቢነት፣ አርቆ ማሰብ፣ ፍቅር፣ ሕብረት፣ አንድነት፣ ይቅር ባይነት፣ ለጋስነት፣ – – – ወዘተ በክርስቲያኑም ኾነ በሙስሊሙ ያለ ልዩነት የሚቀነቀኑ ዕምነታዊ ባሕሪያትና ጠባያት ናቸው – የእውነተኛ የሃይማኖቱ ተከታይ መለኪያ ተደርገውም ይወሰዳሉ፡፡

ስለኾነም ዝርዝሩን እያነሱ እንዲህና እንዲያ ነው ማለት ለአላስፈላጊ ትርጓሜ (Misunderstanding) የመጋለጥና የማጋለጥ እድሉ እጀግ ከፍተኛ ስለኾነ ከማዕቀፍ አንጻር በጥያቄ መልክ ነገሮችን እስኪ እንመልከት፡፡

ሃይማኖተኛ የኾነ ሰው ድንበር፣ ቀለም፣ የሀብት ልዩነት፣ የሀሳብ ልዩነት፣ የኹኔታዎች ምቹ መኾንና አለመኾን ሳይገድበው ምንጊዜም ለእውነት፣ ለነጻነት፣ ለፍትህና ለነጻ ፍቃድ መከበር ኹለንተናዊ መስዋዕትነት የሚከፍል ስለመኾኑና ያለ መስዋዕትነትም እውነተኛ ክርስትናም ኾነ እስልምና እንደሌለ አስተምሮታቸው በተለያየ ዐውድ ያስቀምጣል፡፡

ይህም መኾኑ ባያጠያይቅም የእኛ ሃይማኖተኛነት በአንጻሩ በታሪክም ኾነ ዛሬ በብዙዎች ዘንድ የተመሰከረ ቢኾንም ቅሉ ፖለቲካችን ለዘመናት በሥልጣን ፖለቲካ ውስጥ ስለመኖሩና ዛሬም ድረስ በዛ ውስጥ የምንኖር ስለመኾናችን ያ ሃይማኖተኝነታችንን ያበሰረን የታሪክ ድርሳንና አኗኗራችን ያሳየናል፡፡

የሥልጣን ፖለቲካ በባሕሪው ጥብቅ (rigid)፣ ወግ አጥባቂነት (conservatism) የሚጎላበት፣ ለለውጥ እጅግ ዘገምተኛ (static behaviours) የሚኾን፣ ከወደፊት ይልቅ ከኃላ ትላንት አንጻር ነገሮችን የሚመለከት /የትላንት ማዕቀፍ ቅኝ ተገዢ/፣ በትንሹ የሚረካ፣ የታሪክ ፍጻሜ ቅኝ ተገዥ /በታሪክ ለመኖር የሚተጋ/፣ የገዥነት /managerial/ ባሕሪያትና ጠባያትን የሚላበስ፣ ትርጉም ያለው ትውልድ ተሻጋሪ ርዕይ፣ ግብና ዓላማ የሌለው፣ በሀሳብ ድህነት እጅጉን የተዋጠ፣ ጠላትነትን ከህልውናው ጋር ያስተሳሰረ፣ በኹኔታዎች የሚመራ እንዲሁም የራስ አሸናፊነትን ብቻ ሳይኾን የሌላውን ተሸናፊነት ጭምር በተግባር ማረጋገጥ የሚሻ፤ ከመኖር ባሻገር የሌላው አለመኖርን፤ ከማግኘት ባሻገር የሌላው አለማግኘትን/ማጣትን፤ ከመበልጸግ ባሻገር የሌላው መደህየትን፤ ከግማሽ ማግኘት ሙሉ ማጣትን፤ ከመቆጣጠር ባሻገር የሌላው ሎሌነትን፤ ከመተባበር ባሻገር የሌላው አለመተባበርን የሚሻ – እንደጦርነት ስልት ራስን ከማጠንከር ባሻገር ሌላውን ማዳከምን የሚይዝ – ሁለት ስለት ያለው ጠላት ፈላጊ እንዲሁም ጠላት ‘ፈጣሪ’/አድራጊ ነው፡፡

‘የሥልጣን ፖለቲካ’ ትልቁ መለያ እንደኔ ካላሰባችሁ፣ እንደኔ ካልኾናችሁ፣ እንደኔ ፈቃድ፣ የኔ መንገድ ብቻ፣ እኔን ብቻ፣ በጋራ እናስብ – – – የሚል ኾኖ የምናገኘው በመኾኑ በእጅጉ ከእውነተኛ የሃይማኖተኛ ባሕሪያትና ጠባያት የራቀና ከሱ ጋር የሚቃረን ነው፡፡ በዚህ ለዘመናት የተገዛ፣ የሚገዛም ኾነ እየተገዛ ያለ ሕዝብ እውነተኛ ሃይማኖተኘነትን እንዴት በሕይወቱና በኹለንተናዊ መስተጋብሩ ሊያሠለጥን ይችላል?

ሀሰተኛነት ከእውነተኛነት፣ ድብቅነት ከግልጽነት፣ አስመሳይነት ከሃቀኛነት፣ ቂመኛነት ከይቅር ባይነት፣ ሴረኛነት ከአሳቢነት፣ የታሪክ ቅኝ ተገዢነት ከታሪክ ሰሪነት ዕሳቤ፣ ጠላትነት ከአፍቃሪነት፣ ፈራጅነት ከርህሩህነት፣ ተሳዳቢነት ከመራቂነት፣ ጨካኝነት ከይሉኝታ፣ ስይጡንነት ከፈሪሃ ፈጣሪ ማንነት፣ አርቆ አለማሰብ ከአርቆ አሳቢነት፣ በኃይል መመካት በፈጣሪ ከመደገፍ፣ ትዕቢተኝነት ከትህትና፣ ድንቁርና ከአዋቂነት፣ ርዕይ አልባነት ከርዕይ ባለቤትነት፣ ራስ ወዳድነት ሌለውን እንደራስ ከመውደድ፣ ባርነትን ከነጻነት፣ ነጻ ፍቃድን አፍራሽነት ነጻ ፍቃድን ከአክባሪነት፣ ስይጡንነትን ከሥልጡንነት – – –  ወዘተ ጋር እንደምን ያለ ሕብረትና አንድነት ሊኖረው ይችላል? የቀደመው የሥልጣን ፖለቲካ ባሕሪያትና ጠባያት ሲኾኑ ተከታዩ የሃይማተኛነት ባሕሪያትና ጠባያት አይደሉምን?

ሃይማኖተኛ የኾነ ሕዝብ ኢ-ሃይማኖተኛ የኾነ ባሕሪያትና ጠባያትን እንደምን ለዘመናት ሊሠለጥኑበት ቻለ? እውነተኛ ሃይማኖተኛነት በነጠላ፣ በቡድንና በተቋም ደረጃ ሲዳብር በኹለንተናዊ እንቀስቃሴ መታየት ያለበት አይደለምን? ትላንት እንደቀላል ለሥልጣን ፖለቲካ መሣሪያነት በሃይማኖት ስም የገቡ ጽሑፎች፣ ድርሳናትና መጻሕፍቶች ዛሬ ዛሬ ድንበር የማበጂያ፣ የመለያያ፣ የመነቋቀሪያ፣ በጥላቻ የመተያያ መሣሪያ መኾናቸውን በአደባባይ እየተመለከትን ስለመኾኑ አኗኗራችን ዐቢይ ምስክር ነው፡፡

ያለፈውና የቀደመውን እንኳ ብንተው ዛሬ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ትላንት በእንግዳ ተቀባይነቱ የሚታወቅ ሕዝብ እርስ በራሱ ሲፈነቃቀል፤ ትላንት ለነጻ ፍቃድ መከበር አብነት የኾነ ሕዝብ የነጻ ፍቃድ ጠንቅ የኾኑ ተግባራት ሲፈጽምና ሲፈጸምበት አልተመለከትንምን?

ዛሬ በአኗኗራችን ሃሰተኛነት፣ አስመሳይነት፣ ከባቢያዊነት፣ ምቀኛዊነት፣ ሴረኛዊነት፣ ጠላታዊነት – – – አልሠለጠነብንምን? ቂመኝነትንና  መጠላለፍን ባሕላችን አላደረግንምን? በየቦታው የምንመለከታቸው ድርጊቶች ማሳያ አይደሉምን? ከድርጊቱ በላይ ድርጊቱን የፈጠሩና የተሸከሙ እምነቶች (አስተሳሰብና አመለካከቶች) እና እውቀቶች አደገኛ አይደሉምን? ለአብነት:- በማሕበራዊ ሚድያዎች ያለው እጅግ ጫፍ የወጣ መሰዳደብ፣ መናናቅ፣ መናቆር፣ መጠላላት፣ መፈራረጅ፣ መጠፋፋት፣ – – – ወዘተ ከእውነተኛ ሃይማኖተኛነት ጋር አብሮ የሚሄድ ነውን? በድርጊቱ ከሰው በላይ ፈጣሪ ያየኛል፣ ይሰማኛል ብሎም ይቀጣኛል ከሚል ዕሳቤና አስተምህሮ ጋር አብሮ የሚሄድ ነውን?

ትላንት ከጥቂት ዓመታት በፊት ወንድሞቻችን በሊቢያ በረሃ በአሸባሪዎች ሲታረዱ ይህ የግፍ ግፍ የአውሬ ተግባር ነው ከማለት አልፈን እንዲህ አይነት ሰዎች ፈጽሞ ሃይማኖት የሌላቸው የዲያቢሎስ ደቀ መዛሙርት ናቸው አላልንምን? የነሱን ድርጊት በየቤተ ክርስቲያኑና መስጊዱ አላወገዝንምን?

ሩቅ የመሰለን የክፋት ተግባር ምቹ ኹኔታ ሲያገኝ በታሪክ ከክፍለ ዘመናት በፊት በብዙዎች ላይ እንደተፈጸመው ኹሉ ከጥቂት ወራት በፊት በዘመናችን ለዘመናት ባዳበርነውና ባሕል ባደረግነው የሥልጣን ፖለቲካችን የተነሣ ቅድስት በኾነች ሀገር – ሃይማኖተኛ ሕዝብ ባለባት ሀገር – ዜጎች በአደባባይ ብዙዎች ቆመው እየተመለከቱ በድንጋይ ተቀጥቅጠው ሲገደሉ አልተመለከትንምን?

በታሪክ በሕገ ኦሪት የምናውቀውን በቁም የማሰቃየትና መከራን የማቀበል ተግባር – እኛው ሀገር በ21ኛው ክፍለ ዘመን በአደባባይ ብዙዎች ቆመው እየተመለከቱ – በዝምታ ብዙዎች እየተባበሩ – ጥቂቶች ቀጥቃጭና ደብዳቢ ኾነው ዜጎች ሲገደሉ፣ ዜጎች ሲታረዱ፣ በተኙበት ዜጎች ሲጨፈጨፉ፣ በማንነታቸው ተለይተው ዜጎች ቤታቸው ሲቃጠል – ሲሰደዱ – ሲፈናቀሉና ሲታሰሩ ተመልክተናል፡፡

ገዳይም ኾነ ተገዳይ፣ ቀጥቃጭ ኾነ ተሰዳጅም ኾነ አሳዳጅ፣ ታሳሪም ኾነ አሳሪ፣ ተፈናቃይም ኾነ አፈናቃይ ኢትዮጵያዊ ናቸው፡፡ ይኸው ኢትዮጵያዊ ምክንያቱ ምንም ይኹን ምን ድርጊቱን ፈጽሟል፡፡ ተፈጽሞበታል፡፡ ድርጊቱ ደግሞ በየትኛውም መለኪያ ኢ-ሃይማኖታዊ አልያም ከሃይማኖት ዕሳቤና አስተምህሮ አንጻር ፈጽሞ የተወገዘ ተግባር ነው፡፡ ታድያ ሃይማኖተኝነታችን ከወዴት ገባ? መታመናችን ከወዴት አለ?

ይህ ሲነሣ በቀጥታ ይህን በአስተውሎት ከመመለስ ይልቅ “አይ ጥቂቶች ናቸው የፈጸሙት!” ብሎ ነገሩን የማቃለል ተግባር በአደባባይ ይሰማል፡፡ የሚያሳዝነው የሰው ልጅ ታሪክ የሚያስረዳን ነገር ቢኖር እንዲህ አይነት ተግባር የሚፈጸመው በጥቂቶች መሪነት፣ በጥቂቶች አንቀሳቃሸነትና በብዙዎች ተባባሪነት (ብዙዎች ድርጊቱን በዝምታ በመተባበር) እንደሚፈጽሙት ነው፡፡

ክርስቶስን የሰቀሉት ጥቂቶች፣ የገረፉት ጥቂቶች፣ ለሥልጣን ፖለቲካቸው ሲሉ ገዥዎችም ኾነ ካህናቱ የፈረዱበት ጥቂቶች ኾነው – አብዝሃን ግን አነሣሥተውና አነቃቅተው የድርጊታቸው ተባባሪ አድርገዋል፡፡ ብዙ መከራና ስቃይን የተቀበሉ ሃዋርያትና ቅዱሳን ታሪክም ከዚህ የተለየ አይደለም፡፡ በእስልምናም ነብዩ መሐመድን ያሳደዱና ብዙ መከራን እንዲቀበሉ ያደረጉ ጥቂቶች ሲኾኑ አብዝሃ በዝምታና በጥቂቶች አነሣሽነት ተባብሮ የኾነው ኾኗል፡፡

ዞሮ ዞሮ ዋናው ነጥብ አመክንዮው እጅግ የወረደና ትክክለኛ ባይኾንም ከሕግ የበላይነት አለመከበር በላይ የሃይማኖቶች አስተምህሮና ዕሳቤ መሸርሸርና መናድ መታየቱ የአደባባይ ጥሬ ሃቅ ነው፡፡ በዛን ወቅት ብሎም ዛሬም ድረስ ማሕበራዊ ድህረ ገጾች ድርጊቱን በሚያወግዙና በሚያደንቁ ኢትዮጵያውያን ተጥለቅልቆ እንደነበርና እንዳለ ይታወቃል፡፡

ዝርዝሩን ትተን ቢያንስ በትንሹ ሃይማኖትና የሃይማኖት ዕሳቤና አስተምህሮ ዓለም አቀፍ ነው፡፡ ድንበር ይሻገራል ብሎም ያሻግራል፡፡ ዛሬ በሀገራችን ከባቢያዊነት ዝቅ ሲል መንደርተኝነት ለሀገር ህልውና ስጋት በሚኾን ደረጃ ሠልጥኖ ይገኛል፡፡ የምንከተላቸው፣ የምናምናቸውና እንታመንላቸዋለን እያልን የምንገልጻቸው ሃይማኖቶቻችን (ክርስትናም ኾነ እስልምና) ዓለም አቀፍ ኾነው ሳለ እንደምን ዘረኛነት (ከባቢያዊነትና መንደርተኛነት) በኹለንተናዊ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎቻችን ሊሠለጥንብን ቻለ?

በአደባባይ ሃይማኖተኞች ብንመስልም ጓዳችን ግን የዛ ተቃራኒ ኾኖ ይኾን? ትንቢቱ ይፈጸም ዘንድ ግድ ስለኾነ የትንቢት መፈጸሚያ ኾነን ይኾን? በአኗኗራችን ሀሰተኛነት፣ አስመሳይነት፣ ሴረኛነት፣ ቂመኛነት፣ ምቀኝነት፣ ድብቅነት፣ ጠላትነት፣ ፈራጅነት፣ መንደርተኛነት፣ ከባቢያዊነት – – – ወዘተ እንደምን ሊሠለጥንብን ቻለ?

 ለአብነት፡- ከ41 ጊዜ በላይ በመጽሐፍ ቅዱስ – ልብ እንበል! መጽሐፍ ቅዱስ ያለፈ፣ ያለና የሚመጣን የሚገልጽ መኾኑን ሳንዘነጋ ኢትዮጵያ ተጠቅሳ ሳለ – ከባቢያዊነትና መንደርተኛነት በእምነት (በአስተሳሰብና አመለካከት)፣ በእውቀት (በአሰራር፣ በስልትና በትንታኔ)፣ በድርጊት (በተግባር እንቅስቃሴ) እንደምን ሊሠለጥንብን ቻለ? በርግጠኝነት ሁለት ፍጹም ተቃራኒ የኾኑ ነገሮች ስምምነትና ሕብረት ሊኖራቸው አይችልምና – እውነተኛ ማንነታችን የቱ ነው?

በመኾኑም እኛ ኢትዮጵያውያን በምናምነው፣ በምናውቀውና በምናደርገው ኹለንተናዊ ማሕበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች ሃይማኖታዊ ባሕሪያትና ጠባያት ይዘናልን? ከማመን ባሻገር ታምነናል? ማመናችን በግለሰብ፣ በቡድንና በተቋም ደረጃ እንደሚገለጸው መታመናችን በግለሰብ፣ በቡድንና በተቋም ደረጃ በኹለንተናዊ አኗኗራችን በእምነት (በአስተሳሰብና አመለካከት)፣ በእውቀት (በአሰራርና በስልት) እና በድርጊት (በተግባር እንቅስቃሴ) ተገልጻልን? ዕውን አደባባያዊና ጓዳዊ ማንነታችን ተመሳሳይ ነው? ይህ ሳይኾን እንደምን እርስ በራሳችን ልንስማማና በመንፈስ ልንግባባ፣ ፈጣሪ ሊሰማንና ኹለንተናዊ መሠረታዊ ለውጥ ልናመጣ እንችላለን? ፈጣሪ ሀገራችን ነጻ ፍቃድን የኹሉ ነገር ማዕከል ወደ ሚያደርግ የዕሳቤ ሂደት ትገባ ዘንድ ይርዳን!

ቸር እንሰንብት!

***************

* ፀጋዝአብ ለምለም ተስፋይ – የኢኮኖሚክስ መምህርና ጸሓፊ (ሸክም የበዛበት ትውልድ፡ 2009 እና የምሥራቃዊት ኮከብ፡ 2010 መጻሕፍት አዘጋጅ)

Guest Author

more recommended stories