ጠቅላይ ሚንስትር አብይ ስርአቱን ለማጠናከር እንጂ ለማፍረስ አልመጡም

1/ መግቢያ

የቀድሞዉ ጠቅላይ ሚንስትርና የኢህአዴግ ሊቀመንበር የነበሩት አቶ ኃይለማርያም ደሣለኝ ይዘዉት የቆዩት ከፍተኛ ስልጣን በግላቸዉ ከሚሰጣቸዉ የላቀ ክብርና ጥቅም ይልቅ ለሀገርና ለህዝብ ቅድሚያ በመስጠት በሀገራችን ብቻ ሳይሆን በአፍሪካ አህጉር ባልተለመደ ሁኔታ በገዛ ፈቃዳቸዉ ስልጣን መልቀቅን ተከትሎ በፓርላማ በይፋ በተከናወነዉ የስልጣን ርክክብ ስነስርአት ስልጣኑን በይፋ የተረከቡት ዶ/ር አብይ አህመድ በበአለ ሲመታቸዉ ላይ ባደረጉት ንግግር የብዙዎችን ቀልብ ለመማረክ የቻሉ ሲሆን ከዚያን ዕለት ጀምሮ አስካሁንም ድረስ ስለሳቸዉ የሚሰጠዉ አስተያየት ሲጨምር እንጂ ሲቀንስ አልታየም፡፡

ዶክተር አብይ ቃለመሃላ ከፈጸሙበት እለት አንስቶ እሰካሁን ድረስ ባገኙት አጋጣሚዎች ሁሉ ያለመታከት ለህዝብ እያደረጉት ባለዉ እጅግ አስደማሚ ንግግሮቻቸዉ መላዉ የሀገሪቱ ዜጎች ከሰሜን አስከ ደቡብ ፤ከምስራቅ እስከ ምዕራብ ኦሮሞዉ አማራዉ ጉራጌዉ ትግራዋዩ አፋሩ ወዘተ ሁሉ ያለልዩነት ለሳቸዉ ያላቸዉን አድናቆትና አክብሮት በተለያዩ አጋጣሚዎች እየገለጹ ይገኛሉ፡፡ በሳቸዉ ንግግር ስሜታቸዉ በመነካቱ በርካታ ሰዎች በደስታ አንብተዋል፡፡ ኢትዮጵያዊያን ለዓመታት ያጡትና አሁን ገና ያገኙት ይመስል ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት በክብር ሲነሱ ስሜት ፈንቅሎአቸዉ ሴት ወንዱ ህጻን አዛዉንቱ በደስታ እንባ ሲራጩ ማየት በርግጥም አስደማሚ ነዉ፡፡

ጠቅላይ ሚንስትር አብይ ህዝቡ ምን መስማት እንደሚፈልግ ምን እንደሚያስደስተዉና ምንስ እንደሚያስከፋዉ ጠንቅቄዉ ተረድተዋል፡፡ ህዝባቸዉ ከሁሉም በላይ መስማት የሚሻዉ የልዩነትና የክፍፍል ቃላትን ሳይሆን ኢትዮጵያዊ አንድነትን ፍቅርን አብሮነትን መሆኑን ገብቷቸዋል፡፡ ዶክተር አብይ ስለ ኢትዮጵያ ተናግረዉ የሚሰለቹ አይመስሉም፡፡ በብዙ ችግሮች ለተተበተበች ሀገር መሪ ሆኖ መመረጥ እርግማን ነዉ ባይባልም ብዙም የሚያስፈነድቅ አይደለም፡፡ በተለይም ለእያንዳንደ ቅንጣት የህዝብ ጥያቄ ተገቢዉን መልስ መስጠት አለብኝ በሚል ቆርጦ ለተነሳ እንደ ዶ/ር አብይ ላለ መሪ ጠቅላይ ሚንስትርነት ከባድ የሃላፊነት ሸክም እንጂ የሚኩራሩበት አይደለም፡፡

ለዘመናት በመቻቻልና በፍቅር ለኖረና ጠንካራ አንድነቱን ጠላቶች ሳይቀሩ ያረጋገጡለት፤ ለየትኛዉም የዉጭ ወራሪ ሀገሩን ሳያስደፍር ለቆየ፤ እንኳን በቋንቋና በጎጥ መለያየት ቀርቶ የትም ሀገር ባልታየ ሁኔታ አስደናቂ የሆነ ሃይማኖት መቻቻል የነበረዉ ህዝብ ዛሬ ያ ለዘመናት እብሮት የቆየዉ የአብሮነት ባህሉና አኩሪ እሴቱ ክፉኛ ተሸርሽሮ ዉስጣዊ አንድነቱ ሰላምና መረጋጋት ርቆት እርስበርስ በጎርጥ ከመተያየት አልፎም በብሄር ላይ በተመሰረተ ጥላቻ ምክንያት ዜጎች በህገመንግስቱ በተረጋገጠላቸዉ መብት ተጠቅመዉ ባሰኛቸዉ ቦታ ተንቀሳቅሰዉ መስራትና መኖር እንኳን ተስኖአቸዉ ለዘመናት ከኖሩበት ቀዬ በአስርሺዎች የሚፈናቀሉበት፤ ዓይንህን ላፈር እየተባለ በዜጎች ላይ ብሄር እየተለየ አስከሞት የሚደርስ ጉዳት የሚደርስበትና ንብረታቸዉ የሚወድምበት፤ የጋራ ሀገራዊ ጉዳይ የሚባል ተዳክሞ በምትኩ ሁሉም በየጎጡ የየራሱን ጠባብ አጀንዳን ማራመድ ወግ ሆኖ እየተለመደ በመጣበት ሀገር ባጠቃላይ እርስበርስ ጥላቻና መናቆር በሰፈነባት ሀገር የተዳከመዉን የአብሮነት፤ የአንድነትና ኢትዮጵያዊነት ስሜት እንደገና በመቀስቀስ በጋራ ራእይ ላይ የጋራ ሰልፍን በማሳመር የሁላችንም እናት ለሆነችዉ ሀገር መላዉ ህዝብ በአንድት እንዲቆም ማድረግ መቻል ለአዲሱ ጠቅላይ ሚንስትር እጅግ ፈታኝ ተግዳሮት መሆኑ ባያጠያይቅም እሳቸዉ ግን በእልህ በቁጭትና ከልብ በመነጨ የቁርጠኝነት መንፈስ በመነሳታቸዉ ይሄዉ ገና ካሁኑ ጥረታቸዉ ዉጤት ማሳየት ጀምሯል፡፡ ትንሽ ሰንበትበት ስንል ደግሞ እጅግ አስደናቂ ለዉጥ እንደሚመጣ ቅንጣት አንጠራጠርም፡፡

ይህን ጥቂት አድለኞች ካልሆኑ በስተቀር ብዙዎቹ መሪዎች ሊፈጽሙት የማይችሉት ቢሆንም ዶ/ር አብይ ግን አንድ ወር ባልበለጠ አጭር ቀናት ዉስጥ ይህን ማድረግ ጀምረዋል፡፡ ጠ/ሚንስትሩ በየደረሱበት ሁሉ ፍቅርና አንድነትን በመስበክ ጠዉልጎ የነበረዉን ኢትዮጵዊነትን እየኮተኮቱና እያለመለሙ እንደገና ነፍስ እንዲዘራ እያደረጉ ነዉ፡፡

ለአዲሱ ጠቅላይ ሚንስትራችን እዉቅና ያልሰጠና ያልተደሰተ ኢትዮጵያዊ ያለ አይመስለኝም፡፡ ወጣት አዛዉንቱ እርሶአድሩና ምሁሩ ፤አፍቃሪ ኢህአዴግም ሆኑ ኢህአዴግ ጠል የሆኑ ዜጎች ሁሉ በሳቸዉ ያለጥርጥር ተደስተዋል፡፡ ሌላዉ ቀርቶ ለወትሮዉ ከገዥዉ ፓርቲ ጋር ዓይንና ናጫ ሆነዉ የቆዩት የተቃዋሚ(ተፎካካሪ) ፓርቲ አመራሮች ሳይቀሩ የተለመደዉ ጥርጣሬአቸዉ አሁንም ባይለቃቸዉም በአብዛኛዉ በዶክተር አብይ ወደ ስልጣን መምጣት ደስተኞች መሆናቸዉን ነዉ እየገለጹ ያሉት፡፡

ዶ/ር አብይ የወጡበት የአሮሞ ህዝብ በሳቸዉ መሾም ምክንያት አገር ምድሩን በሚደበላልቅ ሁኔታ ደስታዉን ሊገልጽ ይችላል የሚል ግምት ተይዞ የነበረ ቢሆንም ነገር ግን እጅግ ጨዋና አስተዋይ የሆነዉ ይህ ህዝብ ስሜቱን ሲገልጽ የነበረዉ ከሌሎች ህዝቦች ባልተለየ ሁኔታ መሆኑን አይተናል፡፡ የአሮሞ ህዝብ የዶ/ር አብይ ጠቅላይ ሚንስትርነት ለሁሉም የሀገሪቱ ህዝቦች እንጂ ለአሮሞ ህዝብ ብቻ አለመሆኑን ስለሚረዳ አጋጣሚዉ ፈቅዶልኛል በሚል ከሌላዉ ህዝብ እየነጠቀ እሱ ብቻ ተጠቃሚ ለመሆን የሚሻ አይደለም፡፡ የአሮሞ ህዝብ የደስታዉ መነሾ በዶ/ር አብይ አሮሞነት ሳይሆን ለመላዉ የሀገሪቱ ህዝቦች የመብት ጥያቄ ተገቢዉን ምላሽ ይሰጣሉ የሚል እምነት በመያዙ ነዉ፡፡ በአጠቃላይ የዶክተር አብይን ያህል በዚህች ሀገር ባንድ ጊዜ በሁሉም የሀገሪቱ ዜጎች እኩል ተቀባይነትና አክብሮት ያገኘ ሌላ መሪ ስለመኖሩ አልሰማሁም፡፡ እንደዚህ ዓይነት መሪ ይዘን በአጭር ጊዜ ካሰብንበት እድገት ደረጃ ላይ የማንደርስበት ምክንያት አይኖርም፡፡

2/ በጠ/ሚ አብይ ዙሪያ እየተሰነዘሩ ያሉ የተዛቡ አስተያየቶች፤

ጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር አብይን በሚመለከት እየተሰነዘሩ ያሉት አስተያየቶች ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ በተስፋ የተሞሉና እሳቸዉን የሚያሞግሱ የሚበዙበት ቢሆኑም በአንጻሩ እጅግ በጣም ጥቂት ነገር ግን አደገኛና የተዛቡ አስተያየቶችም አልጠፉም፡፡ በጎ አስተያየት የሰነዘሩትን ትቼ የተዛቡ አስተያየቶችን እየሰነዘሩ ያሉ ወገኖችን ጠቅለል ባለ መልኩ በሁለት ምድብ በመፈረጅ አስተያየት ለመስጠት እሞክራለሁ፡፡ የመጀመሪያዎቹ ከገዥዉ ፓርቲ ዉጭ ያሉ ገለልተኛም በተቃዉሞ ጎራ የሚገኙትንም የሚመለከት ሲሆን በጠ/ሚ ቀጣይ ግስጋሴ ላይ እምብዛም ጫና መፍጠር የማይችሉ ናቸዉ፡፡ ሁለተኛዉ ምደብ ዉስጥ የሚካተቱት የገዛ ድርጅታቸዉ-ኢህአዴግ አባላት የሆኑና በተለይ በታችኛዉ እርከን አመራር ላይ የሚገኙና በአብዛኛዉ ደግሞ ድርጅቱን በዓላማ ሳይሆን ለጥቅም የተጠጉ አክራሪ ካድሬዎች ናቸዉ፡፡

እነዚህ ጥቂት የፓርቲዉ አባላት መለያቸዉ ከህዝቡ ጥቅም ይልቅ የግል ጥቅማቸዉን የሚያስቀድሙና ድርጅቱ ራሱን በማደስ ለህዝብ ጥያቄ ተገቢዉን ምላሽ እንዳይሠጥ እንቅፋት ሲፈጥሩ የነበሩ ናቸዉ፡፡ መደበኛ ስራቸዉ ግማሽ ቀን ካድሬ ግማሽ ቀን ድለላ የሆነዉ እነዚህ ወገኖች በአንድ ወይም በሌላ ምክንያት የለመዱት ጥቅም እንደሚቀርባቸዉ የተረዱና ከኪራይ ሰብሳቢና ጥገኞችና ዘራፊዎች ጋር የጠበቀ ቁርኝት ያላቸዉ በመሆናቸዉ የድርጅቱን መስመር በማስጠበቅ ሽፋን ማንኛዉንም የለዉጥ እርምጃ ከማደናቀፍ የማይመለሱ ናቸዉ፡፡ በዚህ አጭር የስልጣን ቆይታ ጊዜያቸዉ ዶ/ር አብይን መተቸት አጉል ችኩልነት ካልሆነ በስተቀር ተገቢነት ባይኖረዉም ነገር ግን ገና ካሁኑ አካሄዳቸዉ ያላማራቸዉና ስጋትም የፈጠረባቸዉ እነዚህ ወገኖች በቁጭትና በብስጭት መንፈስ አፍራሽ አስተያየት ከመስጠት አልተቆጠቡም፡፡ በዚህ ጽሁፍ ዋነኛዉ ትኩረት ያደረኩትም ዶ/ር አብይን በሚመለከት በበጎ የሚያነሱ ብዙሃንን የሚወክሉ አስተያየቶች ላይ ሳይሆን የተዛቡ ናቸዉ ባልኳቸዉ ላይ የግል አስተያየት መስጠት ነዉ፡፡ ቀጥሎ በአጭሩ ቀርቧል፤

2.1/ ዶ/ር አብይን ከድርጅታቸዉ ዉጭ ማሰብ አይቻልም!

ዶ/ር አብይ የርዕሰ መስተዳዳርነት (የመንግስት)ሃላፊነት ብቻ ሳይሆን የፓርቲያቸዉ ድርጅታዊ ሃላፊነትም አለባቸዉ፡፡ አብዛኛዉን ጊዜያቸዉንና ጉልበታቸዉን ለፓርቲያቸዉ እንዲያዉሉ ሊገደዱ ስለሚችሉ ድርጅቱ ሲጠቀምበት በነበረዉ 70% ለፓርቲ 30% ለመንግስት ስራ በሚለዉ መመሪያዉ መሰረት ዶ/ር አብይ ለኛ ሊሰሩልን የሚችሉት ከፓርቲያቸዉ በተረፈች አነስተኛ ጊዜ ሊሆን እንደሚችልም መጠበቅ ያለብን ይመስለኛል፡፡

የመጀመሪያዉ የተዛባ አስተያየትም ከዚህ የሚጀምር ሲሆን አሳቸዉን ከእናት ደርጅታቸዉ-ኢህአዴግ ዉጭ የማየት ብቻ ሳይሆን ከድርጅታቸዉ በአካልም በአስተሳሰብም ለመነጠል የሚደረግ ሙከራ ነዉ፡፡ ዶክተር አብይ ያለ ድርጅታቸዉ ፍላጎት ጠቅላይ ሚኒስትር መሆን የቻሉና ወደፊትም ከፓርቲያቸዉ ፖሊሲ ዉጭ እንዳሻቸዉ መንቀሳቀስ የሚችሉ አድርጎ መቁጠር ትክክል አይመስለኝም፡፡ የዚህ ዓይነት ነገር ምናልባት ፕሬዝደንታዊ ስርአት በሚከተሉ ሀገሮች የሚቻል ቢሆን ባላስገረመ ነበር፡፡

ነገር ግን እኛ በምንከተለዉ ፓርላሜንታዊ ስርአት አንድ ጠቅላይ ሚኒስትር የቱንም ያህል በህዝብ ተወዳጅ ቢሆን ፓርቲዉ ካላመነበት በግሉ ምንም ሊያደርግ እንደማይችልና መጀመሪያዉኑ ለጠ/ሚኒስትርነትም እንደማይታጭ የዘነጋን ይመስለኛል፡፡ ለምሳሌ የገዥዉ ፓርቲ-የኢህአዴግ ጥቂት ወግ አጥባቂና አክራሪ አመራሮች ዶክተር አብይ ላይ የተለያዩ እንከኖችን በመደርደር በተለይም በሚቀጥለዉ ምርጫ በስልጣናቸዉ እንዳይቀጥሉ ቢያደርጉ ህዝቡ “አብይን እንጂ ኢህአዴግን አንፈልገዉም” የሚልበት እድል ወይም አሰራር አይኖርም፡፡ ስለዚህ ዶክተር አብይ ለዚህ ቦታ የበቁት በሀገሪቱ በተፈጠረዉ ሁኔታ ግፊት መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ነገር ግን የፓርቲያቸዉ ፍላጎት ባይታከል ኖሮ ሊሳካ የሚችልበት እድል ባልኖረ ነበር፡፡ ወደፊትም ቢሆን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለኢትዮጵያ ህዝብ ሊሰሩለት ያቀዱት ምርጥ እቅዶቻቸዉ የብቻቸዉ ሳይሆን ያለጥርጥር

የድርጅታቸዉ እቅድ መሆኑና ተግባራዊ ለማድረግም ቢሆን የድርጅታቸዉን ሙሉ ድጋፍ ማግኘት የግድ መሆኑን መዘንጋት አይገባንም፡፡

ዶ/ር አብይ ህዝብ አስካሁን ከለመደዉና እጅግ ከተሰላቸበት ወጣ ያለ አቋም ይዘዉ በመምጣታቸዉ ከፍተኛ ህዝባዊ ተቀባይነት ማግኘት መቻላቸዉ የሚያጠራጥር አይደለም፡፡ እሳቸዉ በህዝብ ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት ማትረፍ በመቻላቸዉም ፓርቲያቸዉ ቢደሰት እንጂ ሊከፋዉ አይችልም፡፡ ምክንያቱም የሳቸዉን ህዝባዊ ተቀባይነት በመጠቀም ኢህአዴግ እየተመናመነበት የመጣዉን የህዝብ አሜኔታ ለማደስ እንደ መልካም አጋጣሚ ሊጠቀምበት ይፈልጋልና፡፡ ስለዚህ አብይን ከፓርቲዉ መስመር እንዳይወጡ እየተቆጣጠረ ይጠቀምባቸዋል እንጂ እሳቸዉን የሚያደናቅፍበት ምክንያት አይኖርም፡፡

ዶክተር አብይም ቢሆኑ ከፓርቲያቸዉ አፈንግጠዉ አንዳችም ሊሰሩልን የሚችሉት በጎ ነገር ስለማይኖር እሳቸዉን ከድርጅታቸዉ ለመነጠል አጉል ባንደክም ጥሩ ነዉ፡፡ ተሰናባቹ አቶ ኃይለማርያም ጠቅላይ ሚንስትርነትን የሚያክል ትልቅ ስልጣን “በአፍንጫዬ ይዉጣ፤ይቅርብኝ!” በሚል ተማረዉ ቤተመንግስቱን ጥለዉ ለመዉጣት የተገደዱበትን ምስጢር አስካላወቅን ድረስ ዶክተር አብይን ሁሉም ነገር አልጋ ባልጋ እንደሚሆንላቸዉ መጠበቅ ያለብን አይመስለኝም፡፡ አቶ ኃይለማርያም ለኛ ያልተነገረን እሳቸዉ ብቻ የሚያዉቀት ስንት ፈተና ችለዉ ለስድስት ዓመት መቆየት እንደቻሉና አሁን ግን ለምን ለመልቀቅ እንደተገደዱ እዉነተኛዉን ምክንያት ለተተኪያቸዉ ለዶ/ር አብይ ሹክ ሳይሏቸዉ የቀሩ አይመስለኝም፡፡ እናም በበጎም ይሁን በክፉ የድርጅትን ሚና መናቅ ያለብን አይመስለኝም፡፡

2.2/ ዶ/ር አብይ የተበላሸዉን ለማረም እንጂ ስርአቱን ለማፍረስ አልመጡም!

ሁለተኛዉ የተዛባ አመለካከት ደግሞ ከአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር የሚጠበቀዉ የተበላሸ ነገር እንዲያስተካክሉና መልካም ስራዎችን አጠናክረዉ እንዲቀጥሉ መሆኑ ቀርቶ በፊት የተሰሩ መልካም ስራዎችን ሁሉ ማፍረስና ያለፉ ስኬቶችንም እንዲክዱ የሚፈልግ አመለካከት ነዉ፡፡ ገዥዉ ፓርቲ ያበላሻቸዉና ያለወደድንለት በርካታ ጥፋቶች እንዳሉት እናዉቃለን፡፡ ድርጅቱ ራሱ እኛ ስለድክመቱ ካወራነዉ በበለጠ ስለ ራሱ ድክመቶች ያለአንዳች መደባበቅ በተደጋጋሚ ሲነግረን ቆይቷል፡፡ ነገርግን ስለገዥዉ ፓርቲ ድክመቶች የቱንም ያህል አስክታክተን ብንዘረዝር የሰራቸዉን ጠንካራ ስራዎች እንድንክድ ሊያደርገን አይገባም፡፡ እኔ እንደምመስለኝ ዶክተር አብይን ሊያሳስባቸዉ የሚችል አንድ ጉዳይ ቢኖር ይሄዉ ሚዛናዊነት የጎደለዉ አስተያየታችን ይመስለኛል፡፡ ስናጥላላም ስናሞጋግስም ገደብ አለመኖሩ፡፡

ጠ/ሚንስትሩ እንደማንኛችንም ሰብአዊ ፍጡር ናቸዉና ሊሳሳቱ ይችላሉ፡፡ ቃል የገቡልንን ሁሉ በአንድ ጀምበር በተግባር ሊያላዩን አይችሉም፡፡ እናም ትንሽ ስህተት ቢሰሩ ዛሬ ያመሰገናቸዉንና ያደነቅናቸዉን ያህል ነገ አምርረን ልንጠላቸዉና ልናዝንባቸዉ እንደምንችል እሳቸዉም ለመገመት የሚከብዳቸዉ አይመስለኝም፡፡ ከሰሞኑ እንኳን ገና ምኑም ሳይያዝ “እዚህ ቦታ ላይ በዚህ ቃንቋ ለምን ተናገሩ፤ ስለእንትን ጉዳይ ለምን እንትን አሉ፤ አቶ ኃይለማርያምን ለምን የክብር ድፕሎማ ሸለሙ….”ወዘተ እየተባለ ነቀፈታ መሰንዘራችን ባያስከፋቸዉ እንኳን ቢያንስ ጠንቀቅ እንዲሉ ሳያደርጋቸዉ የሚቀር አይመስለኝም፡፡

ዶክተር አብይ ብዙ እንዲሰሩልን እየፈለግን ጥቂት እንኳን እንዲሳሳቱ እድል የማንሰጣቸዉ ከሆነ በራስ መተማመን መንፈስ ያለማመንታት ፈጣን ዉሳኔ እየወሰኑ ከማስፈጸም ይልቅ ወደ መጠራጠር ስለሚገቡ አንድም የረባ ነገር ሳይሠሩልን የስልጣን ቆይታ ጌዜያቸዉ ሊያበቃ ይችላል፡፡ በዚህ ሀገር ባለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት አንድም የሚጠቀስ መልካም ስራ አልተሰራም የሚለዉን የአንዳንዶቻችን አመለካከት ራሳቸዉ ዶክተር አብይም የሚጋሩት አይመስለኝም፡፡ ከሳቸዉ የምንጠብቀዉ ሁሉን ነገር አፍርሰዉ እንዳዲስ ከዘሮ እንዲጀምሩ ሊሆን አይገባም፡፡ ከዚህ በፊት የተሰሩ መልካም ስራዎችን እንዳልተሰራ አድርገዉ እንዲክዱ መጠበቅም አይኖርብንም፡፡ ሚዛናዊነት በጎደለዉ የአንዳንዶቻችን አስተያየት ምክንያት ዶ/ር አብይን ካሁኑ ተስፋ አንዳናስቆርጣቸዉ መጠንቀቅ ይኖርብናል፡፡ ”ስህተት እየሰራሁም ቢሆን ቃል የገባሁትን ለመፈጸም እሞክራሉ” የሚለዉን ህልማቸዉን አናጨልምባቸዉ፡፡

በዶክተር አብይ መሾም አብዝተን የፈነደቅን ዜጎች ስርአቱን ያፈርሱልናል ህገመንግስቱንም በጫጭቀዉ ይጥላሉ በሚል እሳቤ አይደለም፡፡ ህዝብ ከሳቸዉ የሚጠብቀዉ የተበላሸዉን አስተካክለዉና ተዘርዝሮ የማያልቅ የህዝብ ጥያቄን እንዲመልሱና ስርአቱን አጠናክረዉ ሀገሪቱን ወደተሻለ እድገት እንዲያሸጋግሩ እንጂ ሁሉንም ነገር አፈራርሰዉ ከዘሮ እንዲጀምሩ አይደለም፡፡ እሳቸዉም ቢሆኑ ህገመንግስታዊ ስርአቱን አፈርሳለሁ የሚል አመለካከት እንደማይኖራቸዉ ግልጽ ነዉ፡፡ መሪ በተቀያየረ ቁጥር አንድ ስርአት እንዳዲስ እየፈረሰ አይገነባም ፡፡ ደርግ ወደ ስልጣን የመጣበት ሰሞን በመንግስት ሚዲያ በተደጋጋሚ ስንሰማዉ የነበረዉን አንድ አባባል አስካሁን አልዘነጋሁም፡፡ “ማፍረስ ቀላል ባይሆንም መገንባት ግን እጀግ ከባድ ነዉ” የሚል ፡፡ ከአርባ ዓመት በፊት የተነገረ ቢሆንም ዛሬም በአንዳንዶቻችን ላይ ለሚስተዋለዉ ሁሉንም ለማዉደም መጣደፍ አባዜ ዛሬም ገላጭነት አለዉ፡፡ በእጅ ያለንን ጠበቅ አድርገን ነዉ ሌላ የተሻለ መሻት፡፡

ያለበለዚያ የቆጡን አወርድ ብላ የብብቷን ጣለች እንደሚባለዉ አማራጭ ሳናዘጋጅ ብዙ የተደከመበትን ለማዉደም እምብዛም ባንጣደፍ ጥሩ ነዉ፡፡ በግላችን በስርአቱ ዉስጥ የማይስማማን ብዙ ነገር ሊኖር ይችላል ፡፡ በአንጻሩ ስርአቱን ለህልዉናቸዉ ዋስትና አድርገዉ የሚቆጥሩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ከህገመንግስቱ አንድ አንቀጽ በተነካ ቁጥር “እሸፍታለሁ !” በሚል የሚያስፈራሩንም ብዙ ናቸዉ፡፡ ስለዚህ ዶክተር አብይ ዋነኛዉ ስራቸዉ “ማከም” እንጂ ገድሎ ለማዳን መሞከር አይደለም፡፡ የሳቸዉ ተልእኮ “አፍርሶ መልሶ ማልማት” ይመስል ስርአቱን ለማፍረስ የመጡ አድርገን አንቁጠር፡፡ ለዚያዉም ቢሆን ጠቅላይ ሚኒስትራችን ከእያንዳችን ትብብር ዉጭ ብቻቸዉን ሆነዉ ሊሰሩት የሚችሉት አንዳችም ነገር አይኖርምና በምክር እያገዝናቸዉ አብረናቸዉ ልንሰራ ይገባል፡፡ ከዚያ ዉጭ እንዲሰሩ የማይገባቸዉን ስራ ሁሉ እየሰጠናቸዉ ሸክሙን ባናበዛባቸዉ መልካም ይመስለኛል፡፡

2.3/ የዶ/ር አብይ ተግባር ፍቅርና አብሮነትን ማስፈን እንጂ የቂምበቀልና የጥላቻ መወጣጫ መሳሪያ መሆን አይደሉም!

ሶስተኛዉ የተዛባ ብቻ ሳይሆን አደገኛም የሆነ አመለካከት ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትሩን የቅም በቀል መወጣጫ መሳሪያ አድርጎ ለመጠቀም የመፈለግ አመለካከት ነዉ፡፡ ዶክተር አብይ ከህዝብ ጋር በተገናኙ ቁጥር በየአካባቢዉ እየቀረበላቸዉ ካሉ ቅሬታዎች መካከል ሌላዉን ህዝብ እንደ ህዝብ የሚከስ አበቱታቸዉ መኖራቸዉን እያየን ነዉ፡፡ የህዝቡን አንድነት መንፈስ ለማደስ ጥረት እያደረጉ ላሉት ጠቅላይ ሚንስትራችን የዚህ ዓይነት ክሶችን መስማት ምቾት እንደማይሰጣቸዉ ግልጽ ነዉ፡፡ በሚመሩት ሀዝብ መካካል የዚህ ዓይነት መካሰስ ካሁኑ ተስፋ ሊያስቆርጣቸዉም የሚችል ነዉ፡፡

በዚህ ረገድ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ የሚያሻዉና በአግባቡ ልጓም ካልተበጀለት ወደ አልተጠበቀ እርስበርስ ጠብ ሊያስገባን የሚችል ነገር ካለ ጥቂት ግለሰቦች በህዝብ ስም በሰሩት ጥፋት ህዝብን እንደህዝብ የመጥላት አዝማሚያ መታየቱ ነዉ፡፡ ጊዜ የፈቀደላቸዉ ጥቂት ባልስልጣናትና የገዥዉ ፖርቲ አመራሮች ከህዝብ ይልቅ የግል ጥቅማቸዉን ማሳደድ ስራዬ ቢለዉ በመያዝ ለዝርፊያ እንዲያመቻቸዉም ራሳቸዉን የአንድ ህዝብ ተወካይ አድርገዉ በመቁጠር ሌላዉን እየበደሉ ራሳቸዉን ሲያበለጽጉ የኖሩ ይህም ሳይበቃቸዉ በህዝቦች መካከል ሆን ቢለዉ ጥላቻና ቅም በቀልን በመዝራት ሲያጣሉ የኖሩ እንዳሉ ይታወቃል፡፡ እነዚህ ግለሰቦች በድርጊታቸዉ የትኛዉንም ህዝብ የማይወክሉ ሆነዉ እያለ ነገር ግን በሰሩት አስጸያፊ ስራ ምክንያት የወጡበትን ህዝብ ያለሃጥያቱና ያለጥፋቱ በዳይ አድርገን በመቁጠር መሸማቀቅና መገለል እንዳይደርስበት መጠንቀቅ ያለብን ይመስለኛል፡፡

እዚህም እዚያም በተለያዩ ምክንያቶች የተከሰቱ አለመግባባቶች፤በተለያዩ አጋጣሚዎች በተለይም ደካማና ራስ ወዳድ በሆኑ አንዳንድ አመራሮች ተንኮል በህዝቦች መካከል የተፈጠሩ ጊዜያዊ ግጭቶችን በህገመንግስታዊ አግባብ መሰረት ከመፍታት ይልቅ የቆየ የክስ ፋይል እያቀረበን ጠ/ሚንስትሩን የቅም በቀል መወጣጫ መሳሪያ ልናደርጋቸዉ አይገባም፡፡ አሳቸዉ እስካሁን በተቻላቸዉ መጠን ስለሰላም ስለፍቅር ስለአንድነትና ስለአብሮነት እየነገሩን አንድነታችንን ሊያጠናክሩ ደፋ ቀና ሲሉ እኛ “እገለ የሚባል ብሄር እንዲህና እንዲህ አድርጎን” እያልን ህዝብን በጅምላ እየፈረጅን መክሰስና በደል እየዘረዘርን ብሶት ማሰማት ያለብን አይመስለኝም፡፡

ባለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት በየምክንያቱ በደል የደረሰባቸዉ ያለጥፋታቸዉ የታሰሩ በየእስርቤቱም ስቃይ ደረሰብን ወዘተ የሚሉ ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ አንዳንዱ ደረሰብን የሚሉትን እጅግ ዘግናኝ ድርጊቶችን ለማመን የሚከብድ ቢሆንም እኛ አምነን ለመቀበል ፈለግንም አልፈለግንም እዉነታዉን አይቀይረዉም፡፡ በዚህ ረገድ የተሰራ ጥፋት የለም ቢሎ መከራከሩም ለማናችንም አያዋጣም፡፡ ዋነዉ ነገር ጥፋቱን እንደ ህዝብ የተፈጸመ አድርገን ሳንቆጥር ወደፊት በህጋዊ መንገድ ተጣርቶ የድርጊቱ ፈጻሚዎች ተገቢዉ ቅጣት እንዲሰጣቸዉ ማድረግ ነዉ፡፡

ከአጥፊ ግለሰቦች በቁጥር በዛ የሚሉት በአጋጣሚ የዚህ ወይም የዚያ ቋንቋ ተናጋሪ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ በዚህ የጥፋት ድርጊት የአንድ አካባቢ ሰዉ መብዛት የአጋጣሚ ሳይሆን ሆን ተብሎ የተደረገና በበላይ መመሪያ የታገዘ ነዉ የሚል እምነት ካለ መንግስት ሁኔታዉን አጣርቶ አጥፊዎችን በህግ ሊጠይቅ ይገባል፡፡ ከዚያ ዉጭ ምንም እንዳልተፈጠረ ተደርጎ በዝምታ ማለፍም ህዝብን በጅምላ ያለጥፋቱ እንዲጠላ ሊያደርግ የሚችል ስለሚሆን ለአብሮነታችን ሲባል ነጻ የሆነ አካል ተቋቁሞ ሊጣራ ይገባል፡፡ በተረፈ ከማንነት ጋር ተያይዞ ለሚነሱ አበቱታዎች ጠ/ሚኒስትሩ ዛሬዉኑ ብይን ካልሰጡን ብሎ ማስጨነቅም ተገቢ አይመስለኝም፡፡

የግለሰቦችን እኩይ የጥፋት ድርጊት በአንድ ቋንቋ ተናጋሪ ህዝብ ጋር ማቆራኘትና በጅምላ መደፍደፍ ለአብሮነታችን የሚበጅ አካሄድ አይደለም፡፡ በዶ/ር አብይ መሾም ደስተኛ የሆኑት ማንም ከማንም ሳይለይ ሁሉም ህዝቦች መሆናቸዉን ልብ ሊባል ይገባል፡፡ በሳቸዉ ወደ ስልጣን መምጣት በተለየ የከፋዉ ህዝብ ይኖራል ብዬ አላስብም፡፡ ነገርግን ከዚህ በፊት በግለሰቦች የተሰሩ ጥፋቶችን አንድን ህዝብ ነጥለን ያልሰራዉን ሃጥያት ተሸካሚ የምናደርግ ከሆነ በሳቸዉ አስተዳደር ተስፋ እንዲቆርጡና እንዲቆጩ ልናደርጋቸዉ እንችላለንና ከዚህ መሰሉ አጓጉል አመለካከት ልንቆጠብ ይገባል፡፡

ግለሰቦች በሰሩት ጥፋት ህዝብ ያለጥፋቱ ሊወነጀልና ያለበደሉ ማፈርና መሸማቀቅ አይኖርበትም፡፡ በድለዉናል በሚል በጅምላ የምንከሳቸዉ ወገኖች ላይ በችኮላ እርምጃ እንዲወስዱ እሳቸዉን ከማሳሳትና ሆነ ከመገፋፋት ልንቆጠብ ይገባል፡፡ ጥቂት ግለሰቦች በሰሩት ጥፋት አንድን ህዝብ በጅምላ መጥላት ቢሎም ማግለልና በሃፍረት አንገት ማስደፋት ተገቢ ስላልሆነ ክቡር ጠቅላይ ሚንስትራችን የዚያ ዓይነቱን አጓጉል አመለካከት ተሸካሚ የሆኑ ወገኖች ካሉ እንዲታረሙ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ለሳቸዉም ቢሆን እርስበርሱ በጥላቻ የጎርጥ የሚተያይ ህዝብ አንድ አድርጎ ለማስተዳደር ስለሚቸግራቸዉ እንደ ህዝብ በዳይና ተበዳይ፤ ከሳሽና ተከሳሽ ፤ የሚክስና የሚካስ የሚባል አንዳይኖር ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡

3/ የአክራሪ ካድሬዎች ጫና-የጠ/ሚኒስትሩ ትልቁ ፈተና ነዉ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሁንም ሆነ ወደፊት የሚጠብቃቸዉ ትልቅ ተግዳሮት ቢኖር የፓርቲያቸዉ ጫናና ተቃዉሞ ነዉ፡፡ ለዚህ ግምቴ መነሻ የሆነኝ ከፓርቲያቸዉ ጋር ቅርበት ባላቸዉ አንዳንድ ሚዲያዎች ካሁኑ እየተሰጡ ያሉት ቅሬታ ያዘሉ አስተያየቶች ናቸዉ፡፡ ሁኔታዉን በአንክሮ የተከታተለ ሰዉ መረዳት እንደሚችለዉ በሳቸዉ አካሄድ የተከፉና ካሁኑ ስጋት የገባቸዉ በልባቸዉም የሸመቁ ጥቂት ግለሰቦች መኖራቸዉን ነዉ፡፡

ጠቅላይ ሚንስትር አብይን አስመልክቶ በድርጅታቸዉ አክራሪ ካድሬዎች እየተሰጠ ያለዉ ነቀፌታ ያዘለ አሰተያየት የሚጀምረዉ ለዚህ ስልጣን ለመታጨት ካበቃቸዉና ተጅምሮ አስክያልቅ ከህዝብ ተሳትፎ ዉጭ ከመጋረጃ ጀርባ ከተሰራዉ የድርጅቱ የመሪ ምርጫ ስርአት ነዉ፡፡ በድርጅቱ ዉስጣዊ አሰራር መሰረት ህዝብ ባልተሳተፈበት ሁኔታ በር ተዘግቶ በተካሄደዉ ምርጫ ድምጽ ከሰጡ መካከል ከ36 ከመቶ ያላነሰ ያልመረጣቸዉ በመኖሩ 100 %የድጋፍ ድምጽ ባለማግኘታቸዉ የድርጀቱ ዲሞክራሲያዊ ማእከላዊነት መርህ ተጥሷል በሚል ቅሬታ አዘል አስተያየቶችን እየተሰነዘሩ ነዉ፡፡

ለዲሞክራሲ የተሻለ ቅርበት ያለዉ በትንሽ ድምጽ ልዩነት ማሸነፍ እንጂ መቶ በመቶ ድምጽ በማግኘት ሊሆን ባልተገባ ነበር፡፡ ሆኖም 60% አካባቢ በሆነ ድምጽ መመረጣቸዉን የኢህአዴግ መዳከም ተደርጎ ነዉ የተቆጠረዉ፡፡ ለድርጅቱ መሪ (ሊቀ መንበር) ለመምረጥ በተደረገዉ ምርጫ ዶ/ር አብይ የሁሉንም የድጋፍ ድምጽ አለማግኘታቸዉና በወቅቱ የድምጽ መከፋፈል መታየቱ ለምን እንዳልተወደደ ግልጽ አይደለም፡፡

ይህ ሁኔታ ወደፊት በሚደረጉ ምርጫዎች ወቅትም በድርጅቱ ላይ ችግር ማስከተሉ አይቀርም፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ በፓርላማ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለማጽደቅ ድምጽ በተሰጠበት ሂዴት ላይም አዋጁ ለዜጎች ደህንነት ሲባል አስፈላጊነቱ ባያጠያይቅም ነገር ግን የግድ 100 በ100 የድጋፍ ድምጽ አግኝቶ ማለፍ እንዳለበት ተደርጎ በመቆጠሩ አንዳንድ በታቀዉሞ ድምጽ የሰጡ ወገኖችን ማንነታቸዉን መነሻ ባደረገ መልኩ እንደተለመደዉ ከነ ጃዋርና ኦነግ ጋር ለማቆራኘት የተሞከረበት አካሄድም አጅግ አስተዛዛቢ ነዉ፡፡ አንድም ተቃዋሚ በሌለበት ፓርላማ ሌላዉ ቀርቶ ለማስመሰል እንኳን ጥቂት የተቃዉሞ ድምጽ ለማየት አለመፍቀድና በፓርላማ ላይ በያዙት አቋም ግለሰቦችን ከሽብር ኃይሎች ጋር ለመፈረጅ መሞከር ድርጅቱ ከዲሞክራሲ ጋር ጠበኛ መሆኑን አንድ ሌላ ማሳያ ሲሆን በአመለካከት ደረጃም በህገመንግስቱ አንቀጽ 54/5 የም/ቤቱ አባላት በሰጡት ድምጽ ወይም አስተያየት አይከሰሱም የሚለዉን ድንጋጌም የሚቃረን ነዉ፡፡ ፡

ዶክተር አብይ ጠቅላይ ሚኒስትር ብቻ ሳይሆኑ የኢህአዴግ ሊቀመንበርም ጭምር በመሆናቸዉ የፓርቲዉን ጉዳይ ችላ በማለት የመንግስትን ስራ ብቻ አስራለሁ በሚል አንዲት ጋት ወደፊት መግፋት እንደማይችሉ መረዳት አለባቸዉ፡፡ ፓርቲዉን እንደመሳሪያ ሳይጠቀሙ ብቻቸዉን ብዙ መዝለቅ አይችሉም፡፡ ምናልባት በፓርቲዉ አካሄድ ወይም መስመር ላይ ያልጣማቸዉ ነገር ካለ እንደ ድርጅት መሪነታቸዉ በሂዴት ፓርቲዉን አዲስ አቅጣጫ ማስያዝ ይችላሉ፡፡

ነገርግን የተሻለ አማራጭ አይዲኦሎጂ ወይም መስመር እንዳላቸዉ ግልጽ ባልሆነበትና እሳቸዉም በፓርቲዉ አብዛኛዉ አባላት ዘንድ ገና ጠንካራ ተቀባይነት እንዳላቸዉ እርግጠኛ ባልሆኑበት፤ ከሁሉም በላይ ደግሞ ሀገሪቱ ሙሉ በሙሉ ከቀዉስ ባልወጣችበት ወቅት ላይ ከፓርቲዉ መስመር ለማፈንገጥም ሆነ አዲስ አካሄድ ለመከተል አድል ያላቸዉ አይመስለኝም፡፡ የተለየ አማራጭ ካላቸዉም ብቻቸዉን ሊወጡት የሚችሉት ስላልሆነ በፓርቲዉ ዉስጥ የተሟላ ደጋፊ ኃይል አስከሚያዘጋጁ ድረስ ለጊዜዉ አማራጭ የሚሉትን መስመር እያሰቡበት ቢቆዩ ይመረጣል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፓርቲያቸዉ ዉስጥ ድርጅታዊ ሰላም ከሌላቸዉ በስተቀር በአንድ ልብ ተረጋግተዉ ስራቸዉን መስራት አይችሉም፡፡ እናም ከፓርቲያቸዉ አባላት በተለይም መካካለኛና ከፍተኛ አመራሩን ከጎናቸዉ ማሰለፍ መቻል ይጠበቅባቸዋል፡፡ አሁን እንደሚታየዉ አመራሩ እርስበርሱ በሚናቆርበትና አንዱ ብሄራዊ ድርጅት ሌላዉን በሚያብጠለጥልበት ሁኔታ ላይ ድርጅታዊ ሰላም አለ ለማለት አያስደፍርም፡፡

አንዳንድ አክራሪ የድርጅቱ ካድሬዎች የጠቅላይ ሚኒስትሩ ዋነኛ ተግባር እንዲሆን የሚፈልጉት እየተዳከመ ያለዉን ፓርቲያቸዉን ማጠናከርና ለቀጣይ ምርጫ ድርጅቱ ስልጣን እንዳይነጠቅ ማድረግን ነዉ፡፡ በአንጻሩ የሀገሪቱ ህዝብ እየጠየቀ ያለዉ ገዥዉ ፓርቲ እየተዳከመ ነዉና አጠናክሩልኝ የሚል ሳይሆን የዲሞክራሲ፤የፍትህና የመልካም አስተዳዳር ጥያቄ ነዉ፡፡ በተለይም ወጣቱ በቁጣ የራሱን ንብረት አስከማዉደም ያደረሰዉ ጥያቄዉ የኢህአዴግ አብዮታዊ ዲሞክራሲ መስመር ተቀለበሰ በሚል አይደለም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ህዝቡ እንዲመለስለት የሚፈልጋቸዉ ጥያቄዎች ምን እንደሆኑ በጣም ግልጽ ሆኖላቸዋል፡፡

ስለሆነም ቅድሚያ ሰጥተዉ መፍትሄ መፈለግ ያለባቸዉም ለነዚህ የህዝብ ጥያቄዎች ነዉ፡፡ ሆኖም ድርጅቱን እንደመሳሪያ ሳይጠቀሙ ለብቻቸዉ ሊሰሩት የሚችሉት አንድም ነገር አይኖርም፡፡ የድርጅቱ ነባር አባላትን ስጋትና ጥርጣሬ አስካነአካቴዉ ማጣጣልም አይገባቸዉምና፡፡ ሰፊ የህዝብ ድጋፍ መኖሩ ከፓርቲዉ ዉጭ እንዲንቀሳቀሱም አያደርጋቸዉም፡፡ ስለዚህ ዶ/ር አብይ የድርጅቱንና የመንግስትን ሃላፊነቶች አቀናጅተዉ መስራት ይጠበቅባቸዋል፡፡ የሩሲያዉ አብዮተኛ ቭላድምር ሌኒን “ድርጅት ስጡኝኛ ሩሲያን ልገለባብጣት!” ማለቱ የድርጅትን ወሳኝኘት በመገንዘቡ ነዉ፡፡

በዶክተር አብይ አካሄድና አዝማሚያ ስጋት የገባቸዉ የፓርቲያቸዉ ሰዎች የሚያነሱት አንዱ ስጋታቸዉ የድርጅቱ ርእዮትዓለም የሆነዉ አብዮታዊ ዲሞክራሲ አደጋ እየተጋረጠበት ነዉ የሚል ነዉ፡፡ እሳቸዉ ወደ ስልጣን እንዲመጡ ያስገደደዉ የኢትዮጵያ ህዝብ ዘርፈብዙ ጥያቄዎች ምላሽ ማግኘት ይልቅ አክራሪ ካድሬዎች እጅግ ያሳሳበቻዉ የአብዮታዊ ዲሞክራሲ መስመር ሊቀለበስ ይችላል የሚለዉ ስጋት ነዉ፡፡ ለነገሩ ዶ/ር አብይ ከአብዮታዊ ዲሞክራሲም ሆነ ሌሎች የፓርቲዉ ፖሊሲዎች ጋር የቆየ ጠብ ያላቸዉ አልመሰለኝም፡፡ አሁን ስጋት ላይ የጣለዉ ጉዳይ ጠ/ሚኒስትሩ እየጎረፈላቸዉ ባለዉ የህዝብ ድጋፍ መነሾ ምናልባት “በህዝብነት” ስሜት ተዘፍቀዉ የግል ሰብእና ግንባታ ላይ አትኩረዉ በግብታዊነት ከመስመር አፈንግጠዉ ሊወጡ ይችሉ ይሆናል የሚል ስጋት መኖሩ ይመስለኛል፡፡

3.1/ ገዥዉ ፓርቲንና መንግስትን እንከን አልባ አድርጎ የመቁጠር አባዜ፤

የኢህአዴግ ዋናዉ አመራር “ብዙ ነገር አበላሽተናል፡፡ ለተከሰተዉ ሁሉ ጥፋቱ የኛ ነዉ ወዘተ “እያለ ህዝብን በይፋ ይቅርታ ሲጠይቅ የድርጅቱ አባላት በተለይም ካድሬዎች ድርጅቱ አንድም እንከን የሌለበት አድርገዉ የሚሞግቱበትን ምክንያት መረዳት ተስኖናል፡፡ የዲሞክራሲ ምህዳር መጥበብ፤ ኪራይ ሰብሰቢነት፤ የፍትህ መጓደል ፤ ፍትሃዊ የሃብት ተጠቃሚነት አለመኖር፤ የሚዲያ ነጻነት አለመከበር፤ ከፖለቲካ ገለልተኛ የሆነ ምደባ አለመኖር ፤የመልካም አስተዳዳር እጦት ህዝብን ማስመረሩ፤ የማስፈጸም አቅም ደካማነት የህዝብ ሃብትን ለብክነት መዳረጉ፤ የሀገሪቱ ፓርላማ አስፈጻሚዉን መቆጣጠር የተሳነዉ መሆኑ ወዘተ የመሳሰሉ እንከኖቹን አምኖ ተቀብሎ ለማስተካካል እየጣረ ባለበት ሰዓት እነዚህ ካድሬዎች ግን ለምን የድርጅቱ እንከን በአደባባይ ይገለጻል በሚል የማኩረፋቸዉ ምክንያት ያቺዉ የለመዷት ጥቅም እንዳትቀርባቸዉ በመስጋት እንጂ እዉነት የድርጅታቸዉን እንከን ስለማያዉቁ አይደለም፡፡

እናም በአቶ ኃይለማርያም የተጀመረዉ የድርጅቱን ድክመቶች የማመን ሙከራ በዶ/ር አብይ ይበልጥ ተጠናክሮ አስካሁን አይነኬ ሆነዉ የቆዩ ህገመንገስታዊ ጉዳዮች ላይ ሳይቀር ማሻሻያ ከማድረግ የማይመለሱ ሰዉ መሆናቸዉን ካንዳንድ ፍንጮች ሲረዱ ካሁኑ የማጣጣልና የህዝብ አመኔታ የማሳጣት ዘመቻ ጀምረዋል፡፡ የድርጅቱ ካድሬዎች ህዝብን እንደአላዋቂ በመቁጠር ያለአንዳች ይሉኝታ አሰካሁን የተደረጉት አምስት ሀገራዊና የአካባቢ ምርጫዎች ሁሉ ነጻና ዲሞክራሲያዊ ምርጫዎች ነበሩ እያሉ ሲሞግቱ መስማት አጅግ አስገራሚ ነዉ፡፡ ለዲሞክራሲያዊ ምርጫ መለኪያ የሚሆን ሌላ መስፈርት ወጥቶለት ካልሆነ በስተቀር አንድም ተቃዋሚ ለመድሃኒት ያህል እንኳን ፓርላማ ባልገባበት ምርጫ ዲሞክራሲያዊ ነዉ ማለት የጤና አይመሰለኝም፡፡

3.2/ እስረኞችን የመልቀቅ ብሎም ማእከላዊን የመዝጋት ዉሳኔን እንደ ክህደት መቆጠሩ፤

የሀገሪቱና የገዥዉ ፓርቲ አመራሮች የወቅቱ ሁኔታ አስገድዷቸዉና ለሀገርም ይጠቅማል በሚል የወሰዷቸዉ እርምጃዎች በፓርቲዉ አክራረ ካድሬዎች የሰላ ትችት እየተሰነዘረባቸዉ ነዉ፡፡ ከነዚህ መካከል አስረኞችን ለመለቀቅና ማእከላዊ የሚባለዉን ተቋም ለመዝጋት መወሰናቸዉ ይገኝበታል፡፡

የማእከላዊ መዘጋት ያስቆጣቸዉ እነዚህ ወገኖች በቁጭትና በብስጭት መንፈስ እርምጃዉን መንቀፉቸዉ እጅግ አሰተዛዛቢ ነዉ፡፡ መንግስት ማእከላዊን ለመዝጋት የተገደደዉ በድሮ ታሪኩ ብቻ እንዳልሆነ ይታወቃል፡፡ በደርግ ዘመን ከፍተኛ የስቃይ ምርመራ ሲካሄድበት የነበረዉ ይህ ተቋም ፍትህ ሰፍኗል፤ ሰብአዊ መብት ተረጋግጧል በተባለለት በዚህ ዘመንም በሚያሳዝን ሁኔታ የድሮ ስራዉን በትጋት ሲሰራ መቆየቱን ከህዝቡም ከፓርቲዉ አባላትም የተደበቀ አይደለም፡፡ የኢህአዴግ አመራሮች በጋራ ወስነዉ ማእከሉ እንዲዘጋ ሲወስኑ ይህንኑ ተረድተዉ እንደሆነም እናዉቃለን፡፡ የሚያሳዘነዉ ግን ማእከላዊን እንደ ማሰቃያ ሳይሆን ልክ እንደ አንድ የዲሞክራሲ ተቋም በሚቆጥሩ ወገኖች በማእከሉ መዘጋት በመቆጨት የመንግስትን ዉሳኔ ክፉኛ ሲነቅፉ መታየታቸዉ ነዉ፡፡

የአስረኞችን መፈታት በተመለከተም የሀገሪቱ ጠ/አቃቤ ህግ እየመረመረ ዉሳኔ የሰጠበትና መለቀቅ ያለባቸዉ እየተጣራ የተፈጸመ በመሆኑ አስረኞች በመለቀቃቸዉ ሊያናድደን ባልተገባ ነበር፡፡ ደረቅ ወንጀል የሰሩ እንዲለቀቁ ተደርገዉ ከሆነ አላዉቅም፡፡ ነገር ግን አገዛዙን በመቃወማቸዉ ብቻ ለአስር የተዳረጉ ጋዜጠኞችና የተቃዋሚ ፖለቲካ አመራሮች በመለቀቃቸዉ ልንከፋ ባልተገባ ነበር፡፡ እነዚህ ሰዎች ለዉጥ ለማምጣት የታገሉ እንጂ ወንጀለኞች ባለመሆናቸዉ በሚሊዮን የሚቆጠር የሀገር ሃብት የዘረፉ ሌቦችና ቦንብ እያፈነዱ ወገኖቻቻን የጨፈጨፉ ሽብርተኞች ጋር እኩል በአስር ቤት መማቀቅ ያለባቸዉ አይመስለኝም፡፡ እናም የተለየ ወንጀል ያልሰሩ ተለይተዉ ከአስር በመለቀቃቸዉ መንግስትን ማመስገን እንጂ ልንናደድ ባልተገባ ነበር፡፤ለመሆኑ ተመስገን ደሳለኝ፤ አስክንድር ነጋ ፤አንደዷለም አራጌ፤ በቀለ ገርባ፤ መራራ ጉድናን የመሳሰሉት ምን የሽብር ወንጀል ስለሰሩ ነዉ ለአስር የተዳረጉት?አገዛዙን በመቃወማቸዉ ካልሆነ በስተቀር፡፡

ህዝቡ በመንግስት የሰብአዊ መብት አያያዝ ደስተኛ አለመሆኑ የሚያጠያይቅ አይደለም፡፡ ሰብአዊ መብት ተከብሮአል በተባለበት ሀገር በበርካታ አጋጣሚዎች የዜጎች ሰብአዊ መብት እንደሚጣስ በተለይም በረባ ባልረባዉ በአስርቤቶች በታጎሩ ዜጎች ላይ አካላዊ ጉዳትን የሚያስከትል የስቃይ ምርመራና ክብረነክ ድርጊቶች እንደሚፈጸሙ፤ ተከብሯል የሚባለዉም ሰብአዊ መብት የይስሙላ እንደሆነ ቢያስብ ህዝቡን ልንፈርድበት አይገባም፡፡ ሀገሪቱ ገና ከዉጭ ጥገኝነት ባልተላቀቀችበት ወቅት ላይ መንግስት በሰብአዊ መብት ተከሶ ሀገሪቱ ላይ ማእቀብ መጣሉን ሲሰማ ህዝቡ ደስተኛ የሚሆንበት ምክንያት አይኖርም፡፡ እናም የሰብአዊ መብት ጥሰት ማሳያ የሆኑ ተቋማት እንዲዘጉ ማድረግ አንድ በጎ እርምጃ ተደርጎ ሊቆጠር ይገባዋል፡፡

ከዚህ አኳያ “ማዕከላዊ ”የሚባለዉ ተቋም በቀዳሚነት የሚጠቀስ ሲሆን ከስንት ጊዜ በኋላ መዘጋቱ መልካም ነዉ፡፡ አመራሩ ማእከላዊን ባለፉት 27 ዓመታት የመልካም ዜጋ ማፍሪያ ሆኖ ሲያገለግል እንደነበር ደፍሮ ባይነግረንም ማእከላዊን ለመዝጋት የተገደደዉ ተቋሙ ባለፈዉ የደርግ ስርአት ማሰቃያነቱ በህዝቡ ስነልቡና ላይ የተፈጠረዉ መጥፎ ትዉስታ አሁን ድረስ አለመወገዱን በማሰብ መሆኑን ነግሮናል፡፡ የተሰጠዉ ምክንያት ምንም ይሁን ምን ለመዝጋት መወሰኑ በራሱ ትልቅ ነገር ነዉ፡፡

ባለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት ማእከላዊ እንዴት ሲሰራ እንደነበር አቶ ኃይለማሪያምን ጨምሮ ሌሎቹ የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች አመራሮች በዝምታ ቢያልፉም ህዝቡ ጠንቅቆ በሚያዉቀዉ የተቋሙ ትክክለኛ ታሪክ ላይ የሚያመጣዉ አንዳችም ለዉጥ አይኖርም፡፡ ስለዚሁ ጉዳይ በዚሁ በሆርን አፈርስ ( HORN AFFAIRS) ላይ ገና ከዓመት ከመንፈቅ በፊት ማዕከላዊን ከጓንታናሞ ጋር እያነጻጸረ “ከጓንታናሞ እስከ ማዕከላዊ” በሚል ርአስ በማስረጃ አስደግፎ ሰፊ ሀተታ ያቀረበዉ ጦማሪ ስዩም ተሾመ በዚህ ድፍረቱ ምክንያት ቢያንስ ጥቂት ግልምጫ ሳይደርስበት እንዳልቀረ እገምታለሁ፡፡

ስዩም ስለ ማእከላዊ ትዝብቱን ያቀረበበትን ጽሁፉን ሲጀምር በቀይ-ሽብር ዘመን በዜጎች ላይ ብዙ ስቃይና ሰቆቃ የተፈፀመበት የስቃይ አምባ ዛሬም ድረስ ክፍት መሆኑንና “ማዕከላዊ” እንደ የቀድሞ ታሪክ በትውስታ የሚነሳ ሳይሆን ዛሬም ድረስ በእውን ያለ መሆኑ ይበልጥ እንዳስፈራዉ ስሜቱን ሳይደብቅ ይህን ‘አስቀያሚ እውነት’ ፊት-ለፊት ከመጋፈጥ በስተቀር መሸሽ እንደማያዋጣዉ መወሰኑን ይነግረናል፡፡ በመጨረሻም ይህ የስቃይ ቦታ ዛሬ ነገ ሳይል መዘጋት እንዳለበት ለሚመለከተዉ ሁሉ በማሳሰብ የዜግነት ሃላፊነቱን ተወጥቷል፡፡ እንዲህ በማለት፤

“—-ማዕከላዊ እስር ቤት አንድ ትውልድ እርስ በእርሱ የተጫረሰበት፣ የነጭ-ሽብር እና የቀይ-ሽብር ፍርሃት የወለደው የስቃይ አምባ ነው። በዚያ ሀገርን መሃን ባደረገ የሽብር ዘመን ማዕከላዊ የትውልድ ማጨናገፊያ ሆኖ ሲያገለግል የነበረ ቦታ ነበር። ይህ ቦታ እስካልተዘጋ ድረስ የዚያ ክፉ ዘመን ቁስል እንዳመረቀዘ ይቀጥላል። የትውልድ ስቃይና ሰቆቃ የተሰመባት ተቋም ተዘግቶ፣ ለዚያ ክፉ ዘመን መታሰቢያ መሆን ሲገባው፣ አሁንም ድረስ ለተመሣሣይ አላማ እየዋለ መሆኑ ፣ እንደ ሀገርና እንደ መንግስት ትልቅ የፖለቲካና የሞራል ኪሳራ ነው። ስለዚህ፣ ማዕከላዊ እስር ቤት መዘጋት አለበት!!” ~ ስዩም ተሾመ

ስዩም ይህን ጽሁፉን ያስነበበን ከአስራ ስምንት ወራት በፊት በሀምሌ ወር መጀመሪያ በ2016 ወይም በኛ አቆጣጠር 2008 ዓ/ም ላይ ነዉ፡፡ ስዩም ማሳሰቢያ ከሰጠበት ጊዜ በፊት የነበረዉን ትተን ከዚያ በኋላ እንኳን በነበሩት አስራ ስምንት ወራት ዉስጥ በማእከላዊ ምን ሲደረግ እንደነበር በግምት ደረጃም ቢሆን እያሰብን ማዘናችን አይቀርም፡፡ የተገለጸዉን ዓይነት የስቃይ ምርመራ እንዲደረግ መቼም የኢትዮጵያ ህዝብ ፍላጎት ሊሆን አይችልም፡፡ ስቃዩና አስከፊ የነበረዉ የአስረኛ አያያዝ ለኢትዮጵያ ህዝብ ታስቦ እንዳልሆነ እንረዳለን፡፡ እነሆ ስዩም ማእከላዊ እንዲዘጋ ማሳሰቢያ ከሰጠ ከአስራ ስምንት ወራት በኋላ መንግስት ለመዝጋት መወሰኑን ሲያበስረን በመንግስት እርምጃ መላዉ ህዝብ መደሰቱ ባይቀርም ከመጀመሪያዉኑ ኢህአዴግ የምሁራኑን ምክርና ትችት ሰምቶ ቢሆን ኖሮ ከብዙ ችግሮች በጊዜ መላቀቅ በቻለ ነበር ብዬ አስባለሁ፡፡ የማእከሉ መዘጋት ያስከፋቸዉ ወገኖች መንግስት በዚህ ተቋም መዘጋት ምክንያት ያተርፍ እንደሆን እንጂ የሚያጣዉ ነገር ስለማይኖር አመለካከታችሁን እንድስታስተክሉ ሊመከሩ ይገባል፡፡

3.3/ የዶ/ር አብይ “ኢትዮጳያዊነት” ከብዝሃነት ጋር ይስማማል እንጂ አይጋጭም!

በዶ/ር አብይ ላይ እየተሰነዘረ ያለዉ መሰረተ ቢስ ወቀሳ ኢትዮጵያዊነትን በተደጋጋሚ በአደባባይ በኩራት መግለጻቸዉን አስመልክቶ የሚሰጠዉ አሳፋሪ አስተያየት ነዉ፡፡ እሳቸዉ እንደማንኛችንም በሀገሪቱ ካሉት ብሄሮች ከአንዱ የፈለቁ እንጂ ከፉጂ ወይም ከማርስ የመጡ አይደሉም፡፡ እናም በወጡበት ብሄር ቢኮሩበት እንጂ የሚያፍሩበት አይደለም፡፡ አክራሪዎች ለመቀበል ያልፈለጉት እሳቸዉ ግን እጅግ ያሳሰባቸዉና እንቅልፍ የነሳቸዉ ጉዳይ በተዳከመች ኢትዮጵያ ዉስጥ ጠንካራ ኦሮሞ ፤ጠንካራ አማራ ፤ጠንካራ አፋር፤ጠንካራ ትግራይ— ጉራጌ -ኮንሶ– ደራሼ– ወላይታ ሲዳማ- ሶማሌ ወዘተ ሊኖር እንደማይችል መረዳታቸዉ ነዉ፡፡ የሁላችንም ቤት የሆነችዉን ኢትዮጵያን ስም በአደባባይ ለመጥራት እያፈርንባት በኦሮሞነት ፤በሲዳማነት ወይንም በጉራጌነት ወዘተ መኩራት እንደማንችል በመረዳታቸዉ ነዉ፡፡

ለዘመናት ተቻችሎና ተከባብሮ ከዚያም አልፎ እርስበርስ ተጋብቶ የኖረ ህዝብ ዘረኝነት ባመጣዉ ጣጣ ምክንያት እርስበርሱ ግጭት ዉስጥ እየገባና በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ለዘመናት ከኖሩበት ቀዬ በገፍ እየተፈናቀሉ እየታየ ችግር እንደሌለ ለመካድ መሞከር አያዋጣም፡፡ ዛሬ ዘረኝነት የሃይማኖት ተቋማትን ጭምር ሲያዉክ እየታየ ፤በኳስ ሜዳና በትምህርት ተቋማት ዘርን መነሻ ያደረገ ጠብ እያስተናገድን ከዚህ በላይ ምን አስከሚሆን ነዉ የምንጠብቀዉ፡፡ ዶ/ር አብይ አጉል የተጣባንን ይህን ክፉ በሽታ ለማከም ጥረት ማድረጋቸዉ ሊያስመሰግናቸዉ እንጂ ሊያስተቻቸዉ ባልተገባ ነበር፡፡

አርቆ አሳቢ በሆነዉ ህዝባችን ታጋሽነት ፤ለዘመናት ጸንቶ በቆየዉ ጠንካራ ኢትዮጵያዊነትና የህዝቦች እርስበርስ መቻቻል ባህል ብርታት ባይሆን ኖሮ ባላፉት ሁለት አሰርተዓመታት ነጋ ጠባ ሲነዛ እንደቆየዉ የዘረኝነትና የጥላቻ ዘመቻ ብዛት ቢሆን ኖሮ ይህች ሀገር አስካሁን ህልዉናዋ ተጠብቆ መቆየት ባልቻለች ነበር፡፡ ክቡር ጠ/ሚኒስትራችን በጀመሩት መንገድ ነባሩን የህዝቦች እርስበርስ ፍቅር፤ ወዳጅነትና አብሮነት እንደሚመጣ ቅንጣት አልጠራጠርም፡፡ የሳቸዉን ያህል ህዝብን ያከበረ መሪ፤ እንደእሳቸዉ የሁሉንም ህዝብ ፍቅርና ከበረታ በአጭር ጊዜ ያተረፈ መሪ በበኩለ አስካሁን አላየሁም፡፡ እናም ዶ/ር አብይ ብሄር ብሄረሰብ ወዘተ እያሉ ደጋግመዉ ሲናገሩ አለመደመጣቸዉ ለህዝቦች እኩልነትና መብት ያላቸዉን ከበሬታ ጥያቄ ዉስጥ ሊያስገባ የሚችል አይደለም፡፡ ኢትዮጵያዊነትን አብዝተዉ ማወደሳቸዉ ለመላዉ የሀገሪቱ ህዝቦች ያላቸዉን ከበሬታ ከማሳየቱ ዉጭ ለህዝቦች ማንነት ደንታ እንደሌላቸዉ የሚያስቆጥራቸዉ አይደለም፡፡

ኢህአዴግ በተደጋጋሚ እንደነገረን እሱ የሚከተለዉ አብዮታዊ ዴሞክራሲ በመርህ ደረጃ በአንድነት ላይ የማያወላዳ አቋም ያለዉ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያ አንድነት መከበር የብሄር ብሄረሰቦች መብትን እንደቅድመ ሁኔታ ማስቀመጡ ነዉ፡፡ ኢህአዴግ ይታገልለት የነበረዉን የብዙሃን መብትና የብሄር ብሄረሰቦች መብት በአንድነት ስም ችላ ማለትና በሱ ፋንታ አንድነትን መተካት ከመጣ አብዮታዊ ዴሞክራሲ አደጋ ላይ ይወድቃል በሚልም ይሞግታል፡፡ ያ ብቻ ሳይሆን ባለፉት 27 ዓመታት ለኢትዮጵያ አንድነት ጠንክሮ ሲሰራ እንደነበር በኩራት ይገልጻል፡፡ ነገር ግን በተግባር ምን ያህል እንደተሳካለት ምስክሩ ለዓመታት እርስበርሱ እየተናጨ የቆየዉ የኢትዮጵያ ህዝብ ነዉ፡፡

ኢህአዴግ አንድነትን ከአብዮታዊ ዲሞክራሲ ዉጭ ማምጣት የማይቻል አድርጎ የሚያይበት ምክንያት ብዙም ግልጽ ባይሆንልኝም ብዝሃነትና ኢትዮጵያዊነት የሚጋጩበት ሁኔታ እንደሌለ በእርግጠኝነት መናገር እችላለሁ፡፡ ስለኢትዮጰያ ስንናገር በዉስጧ ስላሉት ህዝቦች ነዉ፡፡ ስለኢትዮጵያ አንድነት ስንነጋገር በህዝቦች አንድነት ላይ የተገነባች ኢትዮጵያ ከማለት ዉጭ ሌላ ትርጉም የሚያሰጥም አይደለም፡፡ ክቡር ጠ/ሚኒስትር አብይም እየቀሰቀሱ ያሉት ኢትዮጵያዊነት የብሄር ብሄረሰቦችን ማንነትና መብት የበለጠ የሚያጠናክር እንጂ አንዳንዶች እንደሚያስቡት ብሄራዊ ማንነትንና ብዝሃነትን የሚጋፋ ባለመሆኑ አክራሪዎች ከዚህ መሰሉ አጓጉል ዉንጀላ እንዲታቀቡ ይመከራሉ፡፡

3.4/ ለተቃዋሚዎች የተደረገዉን የሰላም ጥሪ እንደ ሽንፈት መቆጠሩ፤

ዶ/ር አብይ ቃለመሃላ ከፈጸሙበት ቅጽበት ጀምሮ ግልጽ ያደረጉት አንድ ጉዳይ ቢኖር በሀገር ዉስጥ ላሉት ብቻ ሳይሆን ከሀገር ዉጭ የሚገኙ ተቃዋሚዎችና ከመንግስት ጋር በተለያዩ ምክንያቶች ያኮረፉ ኢትዮጵያዊያንን “የአብረን እንስራ!” ጥሪ ማድረጋቸዉ ነዉ፡፡ በተለይም የተቃዋሚ ፓርቲ አባላትን እንደ ጠላት በመቁጠር በነጻነት እንዳይንቀሳቀሱ የተደረገበትን የቆየ ልማድ በመቀየር “ተቀዋሚን” እንደ “ተፎካካሪ”ና እንደ ወንድም መቁጠራቸዉ ፤ያለነሱ ተሳትፎ ዲሞክራሲ ትርጉም የለሽ መሆኑም ከመግለጽ ጀምሮ አብሮ ለመስራት ማሰባቸዉን ማብሰራቸዉ ለአክራሪ የገዥዉ ፓርቲ ሰዎች በጭራሽ የሚዋጥላቸዉ አልሆነም፡፡

የክቡር ጠ/ሚኒስትሩ አቋም መላዉን የሀገሪቱን ዜጎች ያሰደሰተ ከመሆኑም ሌላ በዲሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ ረገድም ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚኖረዉ ቅንጣት የሚያጠራጥር ባይሆንም ይህ ሁኔታ በነዚህ አክራሪ የድርጃታቸዉ ሰዎች ዘንድ በበጎ አልታየላቸዉም፡፡ በተለይም በዉጭ ሀገር የሚገኙ ተቃዋሚዎችን በተመለከተ የሰላም ጥሪ መደረጉ ለሀገሪቱ ከሚሰጠዉ ጥቅም ይልቅ የሰላም ጥሪዉን በደፈናዉ ለሽብር ኃይሎች እዉቅና እንደመስጠት ነዉ የቆጠሩት፡፡ ይሄ መቼም አሳዛኝ ነዉ፡፡

ትላንት ሲቃወመን ከነበረ ቡድን ጋር እንዴት ለእርቅ እንቀመጣለን በሚል የሰላም እቅዳቸዉን ተስፋ ለማስቆረጥ ካሁኑ የማጥላላት ዘመቻ ተከፍቶባቸዋል፡፡ የሚገርመዉ ደግሞ ለዚህ ስርአት እዉን መሆኑን ለአስራ ሰባት ዓመታት ደርግን ታግለዉ ለድል ያበቁና በ93 ዓመተምህረት በተፈጠረዉ የአቋም ልዩነት ከድርጅቱ የለቀቁ የቀድሞ አመራሮች ጋር ገና ለገና የሰላም ንግግር ሊጀመር ይችላል በሚል ጥርጣሬ ካሁኑ አምርረዉ ሲቃወሙ መሰማቱም ነዉ፡፡

3.5/ በቀጣዩ ምርጫ ተሸናፊ ልንሆን እንችላለን የሚል ስጋት ማየሉ፤

የዶክተር አብይ ሁኔታ ያላማራቸዉ አንዳንድ የድርጅታቸዉ ካድሬዎች አንዱ ስጋታቸዉ በሳቸዉ ምክንያት በቀጣዩ ምርጫ ተሸናፊ ልንሆን እንችላላን ከሚል ስጋት የመነጨ ነዉ፡፡ ስጋቱ የጀመረዉ በአቶ ኃለማርያም ወቅት ሲሆን በሀገሪቱ ዉስጥ ለተፈጠረዉ ችግር ሁሉ ገዥዉን ፓርቲና መንግስትን በግልም ራሳቸዉን ተጠያቂ ማድረጋቸዉና ለተፈጠረዉ ሁሉ ህዝቡን በይፋ ይቅርታ መጠየቃቸዉ፤ ባልተለመደ ሁኔታም የድርጅቱ ገመና በአደባባይ መዘርገፉ ፤በዚህ ምክንያትም የገዢዉ ፓርቲ ህዝባዊ አመኔታዉ በእጅጉ መዉረዱ ሲሆን አሁን ዶ/ር አብይ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ደግሞ ለድርጅታቸዉ ነባር አሰራር ብዙም ቦታ ሳይሰጡት እየወሰዱ ባለዉ ቁርጠኛ እርምጃና እያስተላላፉ ባለዉ መልእክት፤ ይባስ ብሎም ገና ካሁኑ የጠ/ሚኒስተርነት የስልጣን ቆይታን በሁለት ዙር ለመገደብ እቅድ እንዳላቸዉ መግለጻቸዉ ከተሰማ ወዲህ ይሄ ሰዉዬ ነገ ደግሞ ምን ጉድ ያመጣብን ይሆን እየተባለ ስጋት መፍጠሩ አልቀረም፡፡

ለስጋታቸዉ ዋናዉ መነሻ የሆነዉ በገዥዉ ፓርቲ ሰዎች አካባቢ እስካሁን በሀገሪቱ የተካሄዱት ምርጫዎች ሁሉ ዲሞክራሲያዊ ናቸዉ የሚል አስገራሚ አቋም ይዘዉ መቆየታቸዉ ሳያንስ ለወደፊቱም በአዉራ ፓርቲ ሽፋን አስከዘላለሙ በስልጣን የመቆየት ህልም ያላቸዉ በመሆኑ ነዉ፡፡ በሚቀጥለዉ ምርጫ እንደድሮዉ የምርጫ ድራማ ለመስራት በዶ/ር አብይ ምክንያት ከእንግዲህ የማይሞክር አድርገዉ ማሰባቸዉና ዶክተር አብይ ኢህአዴግ ድንገት በምርጫ ቢሸነፍ ስልጠን ለአሸናፊዉ ድርጅት ያለምንም ግርግር እንደሚያስረክቡ እርግጠኛ በመሆናቸዉ ስጋቱ ቢይዛቸዉ አያስገርምም፡፡

ማጠቃለያ

ክቡር ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር አብይ ወደዚህ ኃላፊነት የመጡት እጅግ አስቸጋሪ ወቅት ላይ በመሆኑ ሃላፊነቱ የያዙት ቀላል እንዳማይሆንላቸዉ እረዳለሁ፡፡ በተለይም መንግስትን መጠራጠር በለመደ ህብረተሰብ ዉስጥ አሁን ያገኙትን ሰፈ ድጋፍ ሳይሸረሸር እንደተጠበቀ ለመዝለቅ ብዙ መልፋት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ለኢኮኖሚያዊ ፖለቲካዊ ማህበራዊ ወዘተ ጥያቄዎች ሁሉ ዛሬዉኑ ምላሽ ማግኘት የሚሻ ህዝብ እያስተዳደሩ ሃላፊነቱ የሚያዝናና እንዳልሆነ ግልጽ ነዉ፡፡ ዙሪያገባዉ እንቅፋቶች የበዙበት ደጋፊና ተቃዋሚዉን፤ ሀገር ገንቢና አፍራሹን በዉል መለየት በማይቻልበት ሁኔታ ቀላል ያልሆነ ተግዳሮት ስለሚጠብቃቸዉ ጠ/ሚንስትራችን አንዴ ገብተዉበታልና ወገባቸዉን ጠበቅ አድርገዉ በቆራጥነት ወደፊት ከመግፋት ዉጭ ወደኋላ ለመመለስ ሌላ አማራጭ አይኖራቸዉም፡፡

እንደችግሩ ስፋትና ቃል እንደተገባዉ ተስፋ መበርከትና ለአተገባበርም አስቸጋሪ ከመሆኑ አንጻር በሚጠበቀዉ ደረጃ እዉን ሆኖ ለማየት ዘለግ ያለ ጊዜ መጠየቁ አይቀርም፡፡ ችግሩ ሰፊ ነዉ ስንል ጠ/ሚሩ ከዘሮ ነዉ የሚጀምሩት ማለትም አይደለም፡፡ መስተካከል የሚሻና እንደ አዲስ መሰራት የሚጠይቅ ብዙ ጉዳዮች ቢኖሩም አስካሁን ምንም አልተሰራም ማለት ግን አይደለም፡፡ ያለፉትን ሃያ ሰባት ዓመታት ከዉድቀት ዉጭ ያተረፍነዉ አንድም ነገር የለም ከተባለ ብዙም የሚያስማማን አይሆንም፡፡ ብዙ እንከን ያለበትም ቢሆን ድርጅቱን አጠናክረዉ ሊጠቀሙበት ይገባል፡፡

በድርጅቱ ኪሳራ የሚመጣ መሰረታዊ ለዉጥ ስለማይኖር እርጅና የተጫጫነዉን ፓርቲያቸዉን እንደአዲስ ማደስ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ጠ/ሚንስትሩ ለህዝቡ የገቡት ቃል እጅግ ከባድ በመሆኑ ሙሉ በሙሉ መፈጸም ባይችሉ እንኳን ቢያንስ ጠንካራ መሰረት በመጣል ትክክለኛ አቅጣጫ ማስያዝ ከቻሉ በራሱ ቀላል አይደለም፡፡ ነገር ግን እንደ ሶቭየቱ መሪ ኒኪታ ክሩስቾቭ “Politicians are the same all over. They promise to build bridges even when there are no rivers.” (ፖለቲከኞች ሲባሉ ሁሉም አንድ ናቸዉ፡፡ ወንዝ በሌለበትም ቢሆን ድልድይ ለመስራት ቃል ይገባሉ፡፡ ””) እንዳሉት እንደማይሆን ተስፋ እናደርጋለን፡፡ በተረፈ ያሰቡልንን ሁሉ እንዲያሳኩ ፈጣሪ ይርዳዎች እላለሁ::

*********

ኮ/ል አስጨናቂ በአየር ኃይል ዉስጥ ከ1970ዓ/ም ጀምሮ ሲያገለግሉ ቀይተዉ ከ2002 ዓ/ም ጀምሮ በጡረታ ላይ የሚገኙ ናቸዉ፡፡ በአየር ኃይል ዉስጥ በዘመቻና መረጃ መምሪያ ኃላፊነት፤ በአየር ምድብ አዛዥነትና በአይር መከላከያ ኃላፊነትና በሌሎች የሃላፊነት ቦታዎች ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡ በኤርትራ ጦርነት ወቅት በሰሜን አየር ምድብ በምክትልነትነና የአየር መከላከያዉን ስራ በተለይ በሃላፊነት በማስተባበር ሲሰሩ ነበር፡፡ ኮ/ል አስጨናቂ ከቀድሞዋ ሶቭት ህብረት በወታደራዊ ሳይንስ የማስተርስ ድግሪ አላቸዉ፡፡

more recommended stories