ለብአዴንም እንደአብይ እና ለማ ያስፈልገዋል!

(መክብብ)

ዛሬ ላይ የኦሮሞ ብሄርተኝነት ከማደግ አልፎ ከዚህ በፊት ለሀገሩ ከሚያደርገው በላቀ መልኩ አስተዋፅኦውን ለማበርከት የጠቅላይ ሚኒስተርነቱን ቦታ ተረክቧል፡፡ በዚህም አመራር ሀገራችን ኢትዮጲያ የላቀ እርምጃ ትራነዳለች ተብሎ ይጠበቃል፡፡

የወጣቱን አብዮት ቅርፅ በማስያዝ እና ሀገርን በሚለውጥ መልኩ አመራር በመስጠት ትግሉ እምርታ እንዲያሳይ በማድረግ ረገድ የሁለት አብዮተኞችን ሚና ከቶ ልንዘነጋ አንችልም፡፡ እነሱም አቶ ለማ እና ዶክተር አብይ ናቸው፡፡የነዚህ አብዮተኞች አርቆ አስተዋይነት እና በሳል አመራር በኦሮሞ ወጣቶች ዘንድ የተቀጣጠለውን አብዮት ሀገርን ከብተናና ከቀውስ በሚያድን መልኩ ተጠቅመው ሶስተኛውን አብዮት ለስኬት አብቅተዋል፡፡ ሶስተኛው አብዮት ያልኩበት ምክንያት ንጉሡን ከስልጣን ካስወገደው የ1966  አ ም ህዝባዊ አብዮት እና በዛው ማግስት ተቀጣጥሎ ደርግን ከስልጣን በማስወገድ በ1983 ከተጠናቀቀው የህዝቦች ትግል በመቀጠል ሰፊ የህዝብ ንቅናቄ በመሆኑ ነው፡፡

ስለዚህ እነዚህ ሁለት አብዮተኞች የወጣቱን አብዮት ለኦሮሞም ህዝብ ሆነ ለሰፊው የኢትዮጲያ ህዝብ እንዲጠቅም ሆኖ እንዲሳካ ከነድክመቱ በሳል የአመራር ሚና ተጫውተዋል፡፡ አብዮቱ በተቀጣጠለበት ማግስት ኦህዴድ ራሱን እንዲፈትሽ እና ከከፍተኛ አመራሩ እስከታችኛው መዋቅር ድረስ ለተነሳው ህዝባዊ አብዮት በሚመጥን መልኩ ራሱን እንዲያስተካክል እና ተገቢውን አመራር እንዲሰጥ የነዚህ ሁለት ግለሰቦች ሚና በምንም መልኩ የሚተካ አልነበረም፡፡ በሚቀጥሉት ጊዜያትም ህዝቡ የጣለባቸውን አደራ ይወጣሉ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡

የሆነ ሆኖ የዚህ ፅሁፍ ዋና አላማ ስለ ክቡር አቶ አብይ ወይም ስለ ክቡር አቶ ለማ ለማውራት አይደለም፡፡ ይህንን ሁላችንም የታዘብነው እና ታሪክ በደማቅ ቀለም የመዘገበው ታላቅ እውነታ ነው፡፡ የፅሁፉ ትኩረት በተመሣሣይ ህዝባዊ አብዮት ተነስቶበት ስለነበረው የአማራ ክልል እና ስለ መሪ ድርጅቱ ብአዴን አንዳንድ እውነታዎችን ለማንሳት ነው፡፡

የአማራ ህዝብ እንደሌሎች የኢትዮጲያ ህዝቦች ከፍተኛ የአስተዳደር በደል የደረሰበት ህዝብ ነው፡፡ በሌብነት፣ በፍትህ መጓደል፣ የአርሶ አደሩ ያላግባብ ከመሬቱ መፈናቀል እና ስራ አጥነት  በከፋ ሁኔታ ተንሰራፍቶ የመተንፈሻ ቀዳዳ በማጣት ምሬቱ እየታመቀ በመሄድ በስተመጨረሻም ሊፈነዳ ችሏል፡፡ ልክ እንድ ኦሮሚያው ሁሉ በዚህ ክልል በፈነዳው ህዝባዊ አብዮት ወጣቶች ከፍተኛውን ሚና ይዘው ነበር፡፡

ታዲያ እዚህ ጋር የምናነሳው ጥያቄ ሁለቱ ድርጅቶች በሚመሯቸው ክልሎች የተነሳውን ህዝባዊ ንቅናቄ እንደምን ተጠቀሙበት የሚለው ይሆናል?

ይህን መልስ ከመመለሳችን በፊት ሁለት ነጥቦችን ላንሳ

1ኛ በሁለቱም ክልሎች የተነሳው ህዝባዊ አብዮት ተመሳሳይ እና የሚናበቡ ነበሩ፡፡

2ኛ ከአመፆቹ መናበብ በተጨማሪ ከመቼውም ጊዜ በላቀ መልኩ ሁኔታ ኦህዴድ እና ብአዴን መቀራረብ እና አብሮ የመንቀሳቀስ አዝማሚያ አሳይተዋል፡፡ ለዚህም እንደማሳያ ከኦሮሚያ ክልል የተወጣጡ ወጣቶች የእንቦጭ አረምን ችግር የኛም ችግር ነው በማለት ወደባህር ዳር ማቅናታቸው እና በክቡር አቶ ለማ እና በክቡር ዶክተር አብይ የተማራ የኦሮሞ ህዝብ ልዑክ ባህር ዳር ላይ ህዝባዊ ኮንፈረንስ ማድረጋቸው ማንሳት ይቻላል፡፡( እዚህ ጋር ሁለቱ ድርጅቶች የነበራቸውን ልዩነት ማንሳቱ ተገቢ ይመስለኛል፡፡ ኦህዴድ ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ የአመራር ለውጥ አድርጎ ነበር ብአዴን ግን ያው የችግሩ ምንጭ የነበረውን አመራር ማልያ የገለበጠውን ነበር የያዘው፡፡)

ስለዚህ እንደታዛቢ በወቅቱ የነበረን እይታ ሁለቱም በተነሣሣይ ሁኔታ እየሄዱ ያሉ እና ለህዝብ የወገኑ መስሎን ነበር፡፡

አሁን እንደምን ተጠቀሙበት ወደሚለው እንምጣ

የመጀመሪያውና ዋነኛው የችግሩ ምንጭ በግልፅ እና እውነት ላይ ተመስርቶ እወክልሃለሁ ብለህ ለቆምክለት ህዝብ በማስረዳት እና ለመለወጥ የህዝቡ አብዮት ግፊት ሆኖ የሚረዳበትን መንገድ በመጠቀም ደረጃ የተከተሉት መንገድ ነበረ፡፡

በዚህ ረገድ ኦህዴድ የተከተለውን መንገድ ባጭሩ እንመልከት፡፡

የነበረውን አጠቃላይ ችግር ለህዝቡ ሲገልፅ በሁለት በመክፈል ነበር፡፡ ይሀውም ክልላዊ ችግር እና ሀገራዊ ችግር በሚል ነበረ፡፡ ኦህዴድ ለክልላዊ ችግሮች ሃላፊነቱን ሙሉ በሙሉ በመውሰድ መብረቃዊ አብዮት ሊባል በሚችል ደረጃ ከላይ እስከታች መዋቅሩን ለማስተካከል በቃ፡፡ ከስራ አስፈፃሚው እስከታችኛው መዋቅር ድረስ አመራር መቀየሩ አንድ እርምጃ ሆኖ ከብዙ በጥቂቱ ሌሎች እርምጃዎችን እናንሳ፡፡ ወይ ለሌላ ጥቅም አልዋሉ እንዲሁ በደፈናው የታጠሩ መሬቶችን በአሃዝ 50 ሺ ካሬ ሜትር በላይ ለመሬት ባንክ ገቢ እንዲሆን አድርገዋል፡፡ ክልሉ አሁንም በመሬት አስተዳደር ዙሪያ መስራት አለበት የሚለውን ሳልጠቁም ማለፍ አልፈልግም፡፡ ሌላኛው ደግሞ የራሱ ክፍተቶች ቢኖሩትም ስራ አጥ ወጣቶችን በማዕድን ማውጣት የስራ ዘርፍ ተደራጅተው ወደስራ እንዲገቡ የተሰራውን ስራ እንደማሳያ ማንሳት ይቻላል፡፡

ኦህዴድ ሀገራዊ ችግሩንም ለህዝቡ በግልጽ በማስረዳት እንዲፈቱ ትግሉን እንደሚያቀጣጥልና ህዝቡም ከጎኑ እንዲሰለፍ ጥሪ አቅርቧል፡፡ ህዝቡም ጥሪውን ተቀብሎ መሪ ድርጅቱ ያደረገውን ትግል በስኬት እንዲወጣው ረድቷል፡፡

ከላይ ያለውን እውነታ ይዘን የብአዴንን አካሄድ ስንመዝን ከዚህ የተለየ እውነታ እናገኛለን፡፡ ብአዴን የተፈጠሩ ችግሮችን ለይስሙላ ቢናገራቸውም ኦህዴድ እንዳደረገው ለህዝቡ ለማስገንዘብ እና እውነታውን እወቆ ህዝባዊ አብዮቱ ከጎኑ እንዲሰለፍ ጥሪ አላቀረበም፡፡ ይልቁንስ ችግሮችን ሁሉ ውጫዊ በማድረግ ለፍትህ፣ ለእኩል ተጠቃሚነት እና ለዲሞክራሲያዊ አስተዳደር የተቀጣጠለውን የአማራ አብዮት በመጠምዘዝ ስልጣኑን በማራዘም የተጠቀመበት መሆኑን የማታ ማታም ቢሆን እየተገነዘብን ለመምጣት ችለናል፡፡ ለምን ቢባል አንደኛ ኦህዴድ እንዳደረገው ችግሮችን ለሁለት ከፍሎ ለአማራ ህዝብ ለማስረዳት አልሞከረም፡፡ በክልልህ ላይ በድህነት እንትቆራመድ፣ ፍትህ አጥተህ እንድትንገላታ፣ በሰርቆ አደሮች የምትበዘበዘው፣ ለተሻለ ኑሮ ስትል የምትሰደደው፣ አርሰህ በቂ ምርት በማስገኘት በምግብ እህል ከአገሪቷ ውራዎች አንዱ እንድትሆን ያደረኩህ እኔ አምነህ የወከልከኝ ብአዴን ነኝና ይቅር በለኝ ብሎ ንስሃ አልገባም፡፡

እንዲሁም እንደወልቃይት ሌሎች ተመሳሳይ የድንበር ጥያቄዎችም ህዝቤ ሆይ ይሄ ደግሞ ሀገራዊ ነውና ከክልሎች እና ከፌደራል መንግስቱ ጋር በጋራ በመሆን በህገ መንግስቱ መሰረት የምፈታቸው ችግሮች ናቸውና ከጎኔ ተሰለፍ ብሎ አልጠየቀም፡፡ የትኛው፣ ምን እና እንዴት ሊፈታ እንደሚችል ለህዝቡ ለመንገር የሞራል ደረጃው አልፈቀደለትም፡፡ ስልጣኑን መጠበቅ እስከቻለ ድረስ የሰፊው አማራ ህዝብ ጥያቄ ደንታ አልነበረም፡፡

ይህ የብአዴን አካሄድ በተለይ እርቃኑን የወጣው የኢትዮጲያን ህዝቦች ፍላጎት የአማራውንም ጨምሮ በጫንቃው ተሸክሞ ኦህዴድ ለድል ካበቃው በሗላ ነበረ፡፡

ለብአዴን የአማራ ህዝብ የጣለበትን አደራ ለመብላቱ ደግሞ ሁለት ነገሮችን ማንሳት እንችላለን፡፡

1ኛ ልክ እንደ ኦህዴድ ችግሮችን ለሁለት ከፍሎ ክልሉ ላይ ላለው ችግር ራሱ ሙሉ በሙሉ ሃላፊነቱን ቢወስድ ኖሮ ለችግሩ ተጠያቂ የሆኑ አመራሮች ከከፍተኛው እስከ ታችኛው ድረስ የመዋቅር ለውጥ ለማድረግ ይገደድ ነበረ፡፡ ነገር ግን ይህን ለማድረግ በፓርቲው ውስጥ ልክ እንደኦህዴዶቹ አብይ እና ለማ አይነት የህዝብ ወገንተኞች ባለመኖራቸው ወይም በመሞታቸው ሊሆን ይችላል፡፡ እንዲያውም አንዳንዴ ብአዴን ከታምራት ላይኔ በሗላ ማንንም እንዳይነካ የደም ማሃላ የተማማለ ይመስልኛል፡፡

2ኛው ደግሞ ክልላዊ ችግሩን አምኖ ከላይ እስከታች ከቀየረ በሗላ ሀገራዊ ችግሩን ለመፍታት (የድንበር ጉዳዮችን ማለት ነው) የሚሰራበት መንገድ ደግሞ የመጀመሪያው እክል ከላይ እስከታች አመራሩን አለመቀየሩ እንዳይሞክራት ያደርገዋል፡፡ የመበስበስ ደረጃው አይፈቅድለትም፡፡

ባጠቃላይ ብአዴን ለህዝብ ያልቆመ እና ቆሞ ቀር ፀረ ህዝብነቱን እውነተኛውን የአማራ ህዝብ ጥያቄዎች በማድበስበስ እና በመጠምዘዝ ስልጣኑን እያራዘመ ይገኛል፡፡ ህዝቡ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በማተኮር ክልላዊ እና እውነተኛ መፍትሄዎችን እንዳያገኝ በፈጠራቸው ሚዲያዎች ጭምር ሀገርን አደጋ ላይ በሚጥል መልኩ የአማራ ህዝብን ለማታለል ዛሬም እኩይ ትጋት እየተጋ ይገኛል፡፡

ብአዴንና ብዙ የበሰበሱ የህዝብ ወኪል ነን ባዮች ብዙ ግዜ የሚስቱትን እውነት ላንሳ፡፡ ህዝብን እንደ ህዝብ እያታለልክ መዝለቅ አይቻልም፡፡ የአማራም ህዝብ በተሟላ መልኩ የነቃባችሁ ሰአት የትም ልታመልጡት አትችሉም፡፡

የአማራ ህዝብ በርስቱ አይድራደርም የሚለውን እሴቱን እያጦዙ ምን ያህል ግዜ በስልጣን መቆየት ይቻላል የሚለውን አብረን የምናየው ይሆናል፡፡

እዚህ ጋር አንድ ጥያቄ የአማራን ህዝብ መጠየቅ እፈልጋለሁ፡፡ ለመሆኑ በወልቃይት ጉዳይ የብአዴን አቋም ምን እንደሆነየሚያውቅ አለ? ብአዴንስ በግልፅ አቋሙን አሳውቆ ያውቃል?

አንድም ቀን ብአዴን በዚህ ጉዳይ ላይ አቋሙን ገልፆ አያውቅም፡፡ ህዝቡ አነሳ እያለ በሚዲያው ከማስተላለፍ በስተቀር የኔም ጥያቄ እኮ ነው ብሎ አያውቅም፡፡ ለምን ቢባል በሁለት ቢላ እየበላ ለረዥም ጊዜ በስልጣን ላይ መቆየት የሚፈልግ የብስባሾች ጥርቅም ነው፡፡

የመጨረሻው መልዕክቴ ለብአዴን ነው፡፡

ብአዴን ሆይ የአማራ ህዝብ በኦህዴድ ስኬት የተወሰነ ጥያቄው ቢመለስለትም ይህ ምላሽ ግን ዋነኛ ክልላዊ ጥያቄዎችን ያልመለሰ በመሆኑ እና ይህንንም ህዝቦ በቶሎ እየተረዳው ነውና በአፋጣኝ ህዝቡን ለምሬት የዳረገውን አካልህን ቆርጠህ ጣል፡፡ አለበለዚያ የሚመጣውን ለመገመት አያዳግትም፡፡

ቻው::

***********

Guest Author

more recommended stories