(በስንታየሁ ግርማ)

ምንም እንኳን አብዛኛው ግብፃውያን አባይን በተመለከተ የቀድሞ አቋማቸው እየተቀየረ ቢሆንም እንዳንዶች በድሮው የተንሸዋረረ ሀሳብ ውስጥ ይገኛሉ፡፡ ለመጥቀስ ያህል የህዳሴው ግድብ ሙሉ ስምምነት እስከሚደርስ ድረስ ግንባታው ለምን እንዳልተቋረጠ ከኢትዮጵያ መንግስት ማብራሪያ ጠይቀናል የሚለው ይገኝበታል፡፡

ከዚህ በመነሳት ከአለም አቀፍ ህግ አኳያ ወንዙን የመጠቀም መብታችን ምን ይመስላል የሚለውን ማየት ተገቢ ነው፡፡ አንዳአንድ ግብፃውያን የቀኝ ጊዜ ውሎችን በመጥቀስ ናይልን በመጠቀም አለም አቀፍ መብት ከፍተኛ ነን ይላሉ የናይል ወንዝ በተመለከተ የመጀመሪያው ስምምነት የተካሄደው እ.ኤ.አ በ1891 ነበር፡፡

በዚህ ስምምነት መሠረት ጣሊያን በአታቦራ/ተከዜ ወንዝ ላይ ግድብ ላለመስራት ከእንግሊዝ እንደተስማማች የሚያትቱ አሉ፡፡ ፕሮፌሠር አሊ አብደላ አሊ ግን ሥምምነቱ በግልፅ ቋንቋ ያልተቀመጠ ነው ይላሉ፡፡

ሁለተኛው ስምምነት እ.ኤ.አ በ1902 በእንግሊዝ ፣በጣሊያን እና በአፄ ሚኒሊክ መካከል ተፈረመ የሚለው ነው፡፡ በዚህ ስምምነት መሠረት አፄ ሚኒሊክ የአባይን ወንዝ ላለማስቆም እንዳይፈስ ለማድረግ (Arrest) እንደተስማሙ የሚያስቀምጡ አሉ፡፡

በሌላ በኩል ስምምነት በወቅቱ በእንግሊዝ መንግስት የዘውድ ም/ቤት ስላልፀደቀ ተቀባይነት የለውም የሚሉ አሉ፡፡ የእንግሊዘኛው እና የአማርኛው ፍቺዎች የተለያዩ በመሆናቸው ኢትዮጵያ እንዳላፀደቀችው ፕሮፌሠር አሊ ይናገራሉ፡፡ የ1929 እና የ1959 ስምምነት ለታሪካዊ መብት ማነኛዎቹ መነሻዎች ናቸው ይላሉ፡፡ በእነዚህ ስምምነቶች መሠረት፡-

*  ግብፅ ሱዳን አንድ ጠብታ ውሃ ሳያስቀሩ ሙሉ በሙሉ በራሳቸው ተከፋፍለውታል፡፡

*  ሌላ ይገባኛል የሚል ሀገር ከመጣ ከሁለቱ ሀገራት እኩል እንዲቀንስ ተስማምተዋል፡፡

*  ግብፅ በናይል ወንዝ ላይ የሚሠራ ግድብ ድምፅን በድምፅ የመሻር መብት አጎናፅፏታል፡፡

*  በሌሎች ሀገሮች በወንዝ ላይ የሚሠራ ስራዎችን  ለመከታተል የሚያስችል የቴክኒክ ቡድን ለማቋቋም ተስማምተዋል አለ፡፡

የተጠቀሱትን ሀሳቦች ከአለም አቀፍ ህግ እና ተቀባይነት አለው መርህ አንፃር ማየቱ ተገቢ ነው፡፡

Photo - Grand Ethiopian Renaissance Dam, November 2017
Photo – Grand Ethiopian Renaissance Dam, Nov 2017

በመጀመሪያ ደረጃ ግብፅ እና ሱዳን በ1929/በ1959 እኩል ተጠቃሚ ናቸው ብሎ መውሰድ ተገቢ አይደለም በ1929 ስምምነት ግብፅ ሱዳንን አላማከረችም ምክንያቱም በወቅቱ ሱዳን የግብፅ አንድ የግዛት አካል ተደርጋ ስለምትወሰድ ነበር፡፡ በ1959 ስምምነት ደግሞ የሱዳን የውሃ ባለሙያዎች አስተያየት ግምት ውስጥ ሲያስገባ የሱዳን ባለስልጣናት ግብፅን በመፍራት እንዲፈርሙት ፕሮፌሰር አሊ ታሪክን በመጥቀስ ይከራከራሉ፡፡

ከሁሉም በላይ በስምምነቱ የታችኛው የተፋሰስ ሀገራት በተለይም 86% የውሃ ምንጭ የሆነችው ኢትዮጵያ ሀሳቧ አልተካተተም የስምምነቱም አካል አይደለችም፡፡ አንድ ስምምነት ተቀባይነት ያለው አለም አቀፍ ህግ ሊሆን የሚችለው ስምምነቱን በፈረሙት እና ባፀደቁት አካላት መካካል ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያም ሆነች ለሌሎች የተፋሰሱ ሀገራት በሁለቱ ስምምነቶች የመገዛት ግዴታ የለባቸውም፡፡

ድንበር ተሸጋሪ ወንዞችን በተመለከተ ደግሞ በአሁኑ ሰዓት ተቀባይነት ያለው መርህ የእኩል ተጠቃሚነት እና ከፍተኛ ጉዳት ያለማድረስ መርሆዎች ናቸው፡፡ በእነዚህ መመዘኛዎች መሠረት የ1929 እና የ1959 ስምምነት ከ11 የተፋሰሱ ሀገራት ዘጠኙን ያገላል በመሆኑ እና ከላይ የተጠቀሱትን መርሆዎች የሚጥስ በመሆኑ በአለም አቀፍ ፍ/ቤት ቢሄድ ተቀባይነት አይኖረውም፡፡ ስምምነቶቹ በይዞታቸው የእኩል ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ሳይሆኑ የሚያገሉ (Discriminatory) በመሆናቸው በአለም አቀፍ ህግ ተቀባይነት የላቸውም፡፡ ለነገሩ ጉዳዩ ወደ ፍ/ቤት ለመላክም ኢትዮጵያ መስማማት ይኖርባታል፡፡

እ.ኤ.አ. ሜይ 21 1997 የተመድ ለመጓጓዣነት የማይውሉ ድንበር ተሸጋሪ ወንዞችን አጠቃቀም በወጣው ኮንቬሽን መሠረት ሁሉም የተፋሰሱ ሀገርት ወንዙን በሚጠቀሙበት ጊዜ የዕኩል (ፍትሀዊ) (ሚዛናዊ) አጠቃም መርህን በዋነኝነት መከተል እንዳለባቸው ያስቀምጣል፡፡ እኩል የመጠቀም መብት መርህ በተመለከተ አንዳንዶች ለሁሉም ሀገራት እኩል ማከፋፈል ነው በማለት ይተረጉሙታል፡፡ ይህ ግን በአብዛኛው ተቀባይነት የለውም በኮኔቬክሽኑ መሠረት የእኩል (ፍትሃዊ) (ሚዛናዊ) መርህ የሚከተሉትን መስፈርቶች የሚይዝ ነው (በአንቀፅ 6 መሠረት)

1) የጆኦግራፊ፣ የሃይድሮ ግራፊክ፣ የሃይድሮ ሎጅክ፣ የአርኪዮሎጂክ እና ሌሎች የተፈጥሮ ሁኔታ መመዘኛዎች

2) በተፋሰሱ የሚገኙ ሀገራት ያለው የኢኮኖሚ እና ማህበራዊ ፍላጎቶች

3) አንድ ሀገር ውሃውን ሲጠቀም በሌላኛው ተፋሰስ ሀገር ላይ ያለው ተፅዕኖ

4) በጥቅም ላይ ያለ እና እውቅ የውሃ አቅም

5) ውሃውን ለመጠበቅ፣ ለመከላከል፣ ለማበልፀግ ያለው ጠቀሜታ እና ለዚህ የሚውለው ወጪ

6) አማራጭ ውሃ ምንጮች

በእነዚህ መመዘኛዎች መሠረት ሀገራት መከፋፈል እንዳለባቸው ኮንቬሽኑ ያስቀምጣል፡፡

በእነዚህ መመዘኛዎች መሠረት ያልተከፋፈለ ድንበር ተሸጋሪ ወንዝ አጠቃቀም በድርጅቱ ተቀባይነት አይኖረውም፡፡ ለእነዚህ መመዘኛዎች ቀረቤታ ያለው የቀኝ ግዛት ውሎች ሳይሆኑ የናይል ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት ነው፡፡ ስለዚህ ለግብፅ እና ሱዳን ዘላቂነት የሚያወጣቸው፡፡ የትብብር መዕቀፍ ስምምነት መሠረት መፈረም ነው፡፡

ለነገሩ ስምምነቱ ነፃ አባል ሀገራት 2/3ኛው ከፀደቁት አለም አቀፍ ተቀባይነት እና አስገዳጅነት ያለው ህግ ይሆናል፡፡ እስካሁን ስምምነቱ ኢትዮጵያ አጽድቃዋለች፡፡ ለመጀመሪያም ጊዜም ናይል በተመለከተ አለም አቀፍ ተቀባይነት ያለው ህግ ይሆናል፡፡

በ1997 የተመድ ኮንቬክሽን መሠረት ከእኩል ተጠቃሚነት በተጨማሪ የከፋ ጉዳት ያለመድረስ መርህ ሌላኛው መመዘኛ ነው፡፡ የህዳሴው ግድብ በተመለከተ በግብፅ ላይ ትርጉም ያለው ጉዳት እንደማይደርስ በተደጋጋሚ ኢትዮጵያ አስቀምጣለች፡፡ እንደውም የግድቡ ስራ ሲጀመር ታላቁ መሪ ጠ/ሚ/ር መለስ ዜናዊ ፍትሃዊ አጠቃቀም የሰፈነ ቢሆን ኖሮ የግድቡን ወጪ ሱዳን 20 በመቶ ግብፅ 30 በመቶ ሊሸፍኑ ይገባ ነበር ብለዋል፡፡  

ባለሙያዎች እንደሚገልፁት በኢትዮጵያ የሚሠራ ግድብ ትነትን በመቀነስ ተጨማሪ ውሃ ያስገኛል፡፡ በኢትዮጵያ የሚሰራ የተፈጥሮ ሀብት እንክብካቤ የታችኛው የተፋሰስ ሀገራት ከጎርፍ እና በደለል ከመሞላት ይከላከላል፡፡ የተመጠነ የውሃ ፍሠት አመቱን ሙሉ እንዲኖር ያስችላል፡፡ በተመጣጣኝ ዋጋ የሃይል አቅርቦት እንዲኖር ያስችላል ይላሉ፡፡

አንዳአንድ የዘርፉ ባለሙያዎች ምክራቸውን ሲለግሱ ዘላቂው ስትራቴጂ የአባይን ወንዝ በዘላቀቂነት ለመጠቀም ውሃው የሚከማችበትን እንደ አስዋን ግድብ ከፍተኛ ትነት ካለበት ግብፅ እና ሱዳን ይልቅ ወደ ቀዝቃዛው የኢትዮጵያ ክፍል ማሸጋገር ነው ይላሉ (Will Ethiopia’s ‘grand’ new Dam Steal Nile Waters from Egypt” William Davison The Christian Science Monitor June 25,2013) ይመለከቱ፡፡

ለነገሩማ ጉዳት ያለመድረስ ለእኩል ተጠቃሚነት ተገዢ እንደሆነ አለም አቀፍ ልምድ ያሣያል፡፡ ለአለም አቀፍ የፍትህ ፍ/ቤት በዳንቡ ወንዝ አጠቃቀም ውዝግብ በተመለከተ ሀንጋሪ እና ስሎባኪያ ጉዳዩን አቅርበውለት ነበር፡፡ ፍ/ቤቱም የእኩል ተጠቃሚነት መርህ ሁለት ጊዜያት በመጥቀስ ብይን ሰጥቷል፡፡ ጉዳት ያለመድረስ መርህን ፍ/ቤቱ አልተጠቀመበትም፡፡ ይህ ማለት ደግሞ እኩል ተጠቃሚነት ቀዳሚ ጉዳት ያለመድረስ መርህ ከዛ ቀጥሎ የሚታዩ መሆኑን ያሳያል፡፡ በ3 ሀገራት የተቋቋመው የሦስትዮሽ ኮሚቴ የህዳሴው ግድብ አለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ እና በታችኛው የተፋሰስ ሀገራት የጎላ ጉዳት እንደሚያደርስ አስቀምጧል፡፡

ስለዚህ ግብፅ የ1929 እና የ1959 ስምምነት በመጥቀስ በአለም አቀፍ ህግ ተቀባይነት ያለው መብት አለኝ የምትለው ስምምነቶቹ ሌሎችን የሚያገሉ እና ሚዛናዊ አጠቃቀም የሚጥሱ በመሆናቸው ተቀባይነት እንደሌላቸው መገንዘብ ይቻላል፡፡

አንዳአንድ ግብፃውያን  ሌላኛው የሚያቀርቡት የመከራከሪያ  ነጥብ 55.5 ቢሊዮን ኪዪብ ሊትር ውሃ የመጠቀም ታሪካዊ መብት አለኝ፡፡ ይህም ተለምዳዊ አለም አቀፍ ህግ ሆኗል የሚል ነው፡፡ አንድ ልምድ ተቀባይነት ያለው አለም አቀፍ ህግ ተቀባይነት የሚሆነው ተቃዋሚ ወገን ሳይኖር ሲቀር ነው፡፡

ይሁንና ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ የመጠቀም መብት እንዳላት ለግብፅ እና ለሌሎችም በየጊዜው ከማሳወቋም በላይ ቀኝ ገዢዎች እና ግብፅ ኢትዮጵያን በማግለል የተዋወሉትን ስምምነቶች እንደማትቀበላቸው በተደጋጋሚ ለሀገራቱ እና ለአለም አቀፍ ተቋማት (ሊሊጎ ኦፍኔሽን እና ለተ.መ.ድ) በፁሁፍ መገለፃቸው ይታወቃል፡፡ በተለይ አፄ ሚኒሊክ አፄ ሃይለሥላሴ ተቋውሞዎች በፁሁፍ ሰፍረው ይገኛሉ፡፡ ስለዚህ ታሪካዊ መብት እና ልማዳዊ ህግ የሚለው ኢትዮጵያ ተቋውሟን የገለፀችበት ስለሆነ በአለም አቀፍ ህግ ተቀባይነት አይኖረውም፡፡

ሲጠቃለል የአባይን ወንዝ በተመለከተ ለኤሌክትሪክም ሆነ ለሌላ አገልግሎት የሚውል አለም አቀፍ ህግ ኢትዮጵያን የሚደግፍ እንጂ የሚከላከል አይደለም የሚሻለው እውነታውን መቀበል እና በጋራ ማልማቱ ነው፡፡   

*********

Guest Author

more recommended stories