ለመከላከያ ሰራዊታችን አባላት የሚገባቸዉን ክብርና ፍቅር እንስጣቸዉ!!

(ኮ/ል አስጨናቂ ገ/ፃድቅ)

Highlights

* ምንም እንኳን ፌዴራል መንግስቱ ከተጣለበት የሀገሪቱን ድህንነት የማስከበር ተቀዳሚ ሃላፊነት አኳያ በየትኛዉም ክልል ዉስጥ ለመላዉ ሀገሪቱና ህዝቦች ከፍተኛ ስጋት ሊፈጥር የሚችል ሁኔታ ሲከሰት ከክልሉ ጥያቄ ሳይቀርብለትም ቢሆን በራሱ ተነሳሽነትን ጣልቃ መግባት የሚከለክለዉ ነገር ባኖርም  አስካሁን የክልሎችን ስልጣን በመጋፋት ያለፈቃዳቸዉ ጣልቃ ለመግባት አልሞከረም፡፡

* ፌዴራል መንግስቱ ጣልቃ እንዳይገባ የሚፈልጉት የክልሉን ሉአላዊ ስልጣን ለማስጠበቅ አስበዉ አይደለም፡፡ ከዚያ ይለቅ ለተከሰተበት ችግር ዋነኛዉ መነሻ ምክንያት በራሱ በክልሉ አመራር  ደክመት የመነጩ ሲሆን ነዉ፡፡ የክልል አመራሩ ከኪራይ ሰብሳቢና ዘራፊዎች ጋር በተመሳጠረበት ሁኔታ ሆን ብለዉ የሚቀሰቅሱትን ቀዉስ በቶሎ መፍትሄ እንዲያገኝ ስለማይፈልጉ ችግር እንደሌለ በማስመሰልና በመደባበቅ ፌዴራል መንግስቱን እጁን እንዳያስገባ በተለያዩ መንገዶች እንቅፋት ሊፈጥሩበት ይችላሉ፡፡ ይህ ሁኔታ በቅርቡ በሀገራችን በተግባር ደርሶ አይተናል፡፡

* በሀገራችን አስከ ቅርብ ግዜ ከደረሱት ሁኔታዎች መረዳት እንደሚቻለዉ ፌዴራል መንግስቱ ሳይሳተፍበት በክልል አቅም ብቻ የተፈታ የጸጥታ ችግር አለመኖሩ ነዉ፡፡  ይህ ሆኖም እያለ ፌደራል መንግስት ፈጥኖ አልደረሰልንም፡፡  አስታዋሽም አጥተናል የሚሉ የቅሬታ ድምጾች በተደጋጋሚ መሰማታቸዉ አልቀረም፡፡  የፌዴራል መንግስቱ መዘግየት እዉነት ከሆነ ለምን ፈጥኖ ጣልቃ መግባት  አልቻለም የሚል ጥያቄ እንድናነሳ ያደርገናል፡፡

በአሁኑ ሰዓት የወቅቱን ሁኔታ መነሻ ባደረገ መልኩ መከላከያ ሰራዊቱን በሚመለከት ሶስት የተለያዩ አመለካከቶች ከተለያዩ ወገኖች ሲንጸባረቁ ይደመጣሉ፡፡ የመጀመሪያዉ ፤.መከላከያ ሰራዊቱ ስርአቱን የማዳንና የዜጎችን ደህንነት የማስከበር ህገመንግሰታዊ ሃላፊነቱን ተገቢነት አምነዉ አሁን እየሰራ ባለዉ መንገድ አጠናክሮ እንዲቀጥል የሚፈልጉ ሲሆኑ በሁለተኛ ምድብ ያሉት ደግሞ ጸጥታ የማስከበር ተግባሩን አርግፍ አድርጎ አቁሙ አርፎ እንዲቀመጥ የሚፈልጉ ናቸዉ፡፡በሶስተኛ ደረጃ ያሉት ደግሞ መከላከያ ሰራዊቱ አስፈላጊ ከሆነ የመንግስትን ስልጣን አስከ መቆጣጠር የሚደርስ እርምጃ በመዉሰድ ሲቪሉን ተክቶ ሀገር እንዲያስተዳድር ፍላጎት ያላቸዉ ናቸዉ፡፡ ሰራዊቱ ጸጥታ ከማስከበር ሃላፊነቱ እንዲቆጠብ መፈለግም ሆነ በመንግስት አስተዳዳር ዉስጥ ጣልቃ እንዲገባ መሻት የተሳሳተ አመለካካት መሆን ብቻ ሳይሆን እጅግ አደገኛም ጭምር መሆኑ ሊታወቅ ይገባል፡፡

* መከላከያ ሰራዊታችን የህዝቡን ደህንነት ለማስከበር ህገ መንግስታዊ ሃላፊነቱን በሚወጣበት በዚህ ቀዉጥ ወቅት ለህዝቡ እስካሁን በተግባር ካሳየዉ ወገንተኝነት ሳያፈነግጥና ህዝባዊ አመለካከቱ ሳይሸረሸር የተጣለበትን ሃላፊነት ከፍተኛ ጥንቃቄ በተሞላበት ሁኔታ የመወጣት ብቃቱ ይበልጥ የሚለካበት ወቅት ነዉ፡፡ መከላከያ ሰራዊታችን በአንድ በኩል በዜጎችና በሀገሪቱ ላይ የተጋረጠዉን የጸጥታ ችግር እየተጋፈጠ በሌላ በኩል ደግሞ የህዝቡን ህገመንግስታዊ መብት ሳይደፍር በብልሃትና በከፍተኛ ጥንቀቄ ሃላፊነቱን የመወጣበት ብቃቱን በተግባር ሊየሳይ ይገባል፡፡

* የሰራዊታችን አባላት የኃይል አጠቃቀም ቅደም ተከተልና ኃይል መጠቀምን የግድ የሚያደርጉ ሁኔታዎችን ጠብቀዉና የግዳጅ አፈጻጸም ደንብን ሳይተላለፉ ሃላፊናቸዉን በከፍተኛ  ጥንቃቄ መፈጸም እንደሚገባቸዉ ለአፍታም መዘንጋት አይኖርባቸዉም፡፡ በተለይም በተቃዉሞ ማሰመት ሽፋን ህገወጥ ድርጊት የሚፈጽሙና የመንግስትና የህዝብ ንብረት የሚያወድሙና ሆን ብለዉም የህዝቡን ሰላምና ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥል ተግባር የሚፈጽሙ ሲያጋጥማቸዉ ከቅርብ አለቃቸዉ መመሪያ ወይም ትዕዛዝ ካልተሰጣቸዉ በስተቀር አለቅጥ ተቻኩለዉ በራሳቸዉ ግዜ የማይገባ እርምጃ ከመዉሰድ ሊቆጠቡ ይገባል፡፡ የሰራዊቱ አባላት በራሳቸዉ ላይ አደጋ እየደረሰም ቢሆን ገዳይ የሆነ መሳሪያ በመጠቀም በዜጎች ላይ ጉዳት ላለማድረስ መታገስ ይገባቸዋል፡፡

መግቢያ

በአሁኑ ወቅት ሀገራችን ከምንግዜም በላይ አሳሳቢ ሁኔታ ዉስጥ ትገኛለች፡፡  የወቅቱን አሳሳሰቢነትና አደገኛነት ማንም ከማንም ሳይለይ ሁሉም የተቀበለዉ ጉዳይ ነዉ፡፡  መንግስትና ገዥዉ ፓርቲም የወቅቱን አሳሳቢነት በራሳቸዉ መንገድ ተገንዝበዋል፡፡ ሀገር በቀል የፖለቲካ ፓርቲዎች ምሁራንና ሁሉም ዜጎች የወቅቱን አሳሳቢነት ላይ ተመሳሳይ አቋም አላቸዉ፡፡

ሌላዉ ቀርቶ በዉጭ የሚገኙ ኢትዮጵያዉያንም ቢሆኑ ስለወቅቱ ሁኔታ ከዚህ የተለየ አስተያየት የላቸዉም፡፡ የኢትዮጵያ ወዳጅ የሆኑም ሆነ ለኢትዮጵያ መልካም የማያስቡ መንግስታትም ቢሆኑ በአንድ ወይም በሌላ መንገድ በኢትዮጵያ እየታየ ያለዉን ሁኔታ አሳሳቢነት ተገንዝበዉ ከራሳቸዉ ጥቅም አንጻር የወደፊቱን ሁኔታ በማስላት ሲከሰት የሚችለዉን ለዉጥ በጥንቃቄ  እየተከታተሉ እንደሆነ እገምታለሁ፡፡

በወቅታዊዉ የሀገሪቱ ሁኔታ ላይ በሁሉም ወገኖች ዘንድ ልዩነት ባይኖርም ነገር ግን የችግሩ መንስኤና መፍትሄ ላይ ስምምነት ያለ አይመስልም፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የተፈጠረዉን ሁኔታ በቀጣይ ስልጣን ለመያዝ ካለዉ አመቺነት አንጻር የሚያዩት ሲሆን በተወሰኑ የገዥዉ ፓርቲ አባላትና ደጋፊዎቹ አካባቢ ደግሞ ሁኔታዉ እየተመዘነ ያለዉ ስልጣን ሊያሳጣ የሚችል መጥፎ አጋጣሚ ከመሆኑ አንጻር ነዉ፡፡  የቀረዉ የሀገሪቱ ዜጋ ግን ሁኔታዉን እያየ ያለዉ በሀገሪቱ አንድነት ላይ ሊከሰት ከሚችለዉ አደጋ አንጻር ነዉ፡፡

አሁን ላለንበት አደገኛ ሁኔታ የበቃንበት ዋነኛ ምክንያትም ሆነ የመፍትሄዉ እርምጃዉ ላይ አንድ ዓይነት አመለካከት ባለመኖሩ ምክንያት መፍትሄዉን ዉስብስብና አዳጋችም በማድረጉ በአጭር ግዜ ከችግሩ የመዉጣት ተስፋችን እንዲጨልም እያደረገ ነዉ፡፡ በችግሩ መነሻ ላይ ሳንስማማ መፍትሄዉ ላይ መስማማት አንችልም፡፡ መፍትሄዉ ላይ መስማማት ካልቻልን ደግሞ ከችግሩ ልንላቀቅ የምንችልበት ዕድል አይኖርምና ጉዳዩ የሚመለከታቸዉ ሁሉም ወገኖች ልዩነቶቻቸዉን በማጥበብ ወደ መፍትሄዉ መቅረብ እንዳለባቸዉ በዚህ አጋጣሚ ለማሳሰብ አወዳለሁ፡፡

ገዥዉ ፓርቲ የችግሩ መንስኤ ናቸዉ ያላቸዉን ከሞላ ጎደል በመለየት ለማስተካከል እያደረገ ያለዉ ጥረት በተቃዋሚዎች በኩል እምብዛም ድጋፍ ያለማግኘቱም ዋነኛ ምክንያትም የገዥዉን ፓርቲ እርምጃ ራስን ለማዳን የሚደረግ መፍጨርጨር አድርገዉ በመረዳታቸዉ ነዉ፡፡ ገዥዉ ፓርቲ እያደረገ ያለዉ ጥረት በተቃዋሚዎች አካባቢ እየተሰጠዉ ያለዉ ትርጉም ሀገር ከማዳን አንጻር ሳይሆን ስልጣኑን ላለማስነጠቅ የሚደረግ የመጨረሻ የሞት ሽረት ትግል አድርገዉ ነዉ፡፡  በዚህ ምክንያትም ገዥዉ ፓርቲ ለመፍትሄዉ እያሳየ ያለዉን ቁርጠኝነት ከማበረታታት ይልቅ በተቃራኒዉ ለማጣጣል ቢሎም እንቅፋት ለመሆን እየተሞከረ መሆኑን እየታዘብን ነዉ፡፡

በተመሳሳይ ሁኔታ ተቃዋሚዎች (ሁሉን ላይመለከት ይችላል) በሀገሪቱ የተፈጠረዉ ሁኔታ ገዥዉን ፓርቲ ከስልጣን በማዉረድ የሚጠናቀቅ ካልሆነ በስተቀር ከዚያ በመለስ የተለየ አንዳችም መፍትሄ እንዲቀርብ አይፈልጉም፡፡  በዚህ ምክንያትም ኢህአዴግን ህልዉና የሚያሳጣ ካልሆነ በስተቀር በሌላ በየትኛዉም የመፍትሄ እርምጃ ላይ ለመሳተፍም ሆነ ለመስማማት አይሹም፡፡

አንዳንድ በአንጻራዊነት ሃላፊነት የሚሰማቸዉ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች የወቅቱ ሁኔታ ኢህአዴግን ከስልጣን ለማዉረድ እጅግ አመቺ ነዉ የሚል አመለከካት ቢኖራቸዉም ነገር ግን ኢህአዴግን ከስልጣን ለማዉረድ ተብሎ ሀገሪቱ አስከመበታተን መድረስ አለባት የሚለዉን አመለካከት አይጋሩም፡፡

ሌሎች ጥቂት ታቃዋሚ ፓርቲዎች ደግሞ “የችግሩ መንስኤ ኢህአዴግ ነዉ፡፡  መፍትሄዉም የኢህአዴግ ስልጣን መልቀቅ ነዉ፡፡ “ በሚል ራሳቸዉን አሳምነዉ ገዥዉ ፓርቲ ያለ አንዳች ማንገራገር ነገ ዛሬ ሳይል ስልጣን አስረክቦ መዉረድ አለበት የሚል አቋም በመያዝ በይፋ እስከ መጠየቅም የደረሱ አሉ፡፡  ለአብነት “ኢራፓ”ን መጥቀስ ይቻላል፡፡  ኢራፓ አቋሙን ሳይደብቅ በድፍረት በይፋ መግለጹ ካልሆነ በስተቀር የሱን ሃሳብ የሚጋሩ ሌሎች ፓርቲዎች አይኖሩም ማለት አይቻልም፡፡  የሆኖ ሆኖ ኢራፓም ሆነ የዚህ ዓይነት “ስልጣን ይልቅቅ!” ጥያቄ ያላቸዉ ሌሎች ፓርቲዎች ኢህአዴግ ስልጣን ሲለቅ ሀገር የማስተዳዳሩን ሃላፊነት ማን እንዲረከብ እንደፈለጉ ወይንም ለዚያ ሃላፊነት ማንን እንዳዘጋጁ አሰስካሁን አልነገሩንም፡፡

ሌላዉ ቀርቶ ኢህአዴግ ስልጣን ለመልቀቅ የሚያስገድደዉ ደረጃ ላይ ገና አለመድረሱን እንኳን በሚገባ የተገነዘቡ አልመሰለኝም፡፡ ኢህአዴግን ከምርጫ ዉጭ በኃይል ስልጣን ለማዉረድ የሚቻልበት አንዳችም መንገድ እንደሌለና ኢህአዴግ  ለስልጣኑ ሲል ማንኛዉንም መስዋትነት ለመክፈል እንዳማያመነታ ኢራፓ የተረዳ  አልመሰለኝም፡፡ ለማንኛዉም ይህን ጉዳይ ማስታወሴ በሀገራችን ወቅታዊ ጉዳይ ላይ ልዩነታችን የት ድረስ እንደሆነ ለማመላከት ሲሆን በዚህ ልዩነት ዉስጥ ሆነን እንዴት ከችግር ልንወጣ እንደምንችል የተሰማኝን ስጋትና ጥርጣሬ ለማጋራትነዉ፡፡

አሁን በሀገራችን የሚታየዉ ሁኔታ አሳሳቢነቱ በግልጽ የሚታይ ቢሆንም አሳሳቢነቱ መመዘን ያለበት የገዥዉን ፓርቲ ስልጣን ከማሳጣት ወይም ስልጣን ከማስጠበቅ አንጻር ሳይሆን በሀገር ህልዉና ላይ የተጋረጠዉን ስጋት ከማስወገድ አንጻር ሊሆን ይገባል፡፡ በመንግስት በኩል ቅድሚያ ሰጥቶ መስራት  ያለበት ስልጣኑን እንዴት ማስጠበቅ እንዳለበት እያሰላ ሳይሆን ሀገሪቱ አንዳትበታተን ማድረጉ ላይ ነዉ፡፡  በእኔ እምነት ኢትዮጵያን እንደ ሀገር የማስቀጠል ጉዳይ ከሁሉም ጉዳይ ቅድሚያ ሊሰጠዉ ይገባል ባይ ነኝ፡፡

ገዥዉ ፓርቲ የፖለቲካ ጉዳይን ቅድሚያ እየሰጠና ለተጨማሪ ዓመታት በስልጣን ላይ እንዴት መቆየት እችላለሁ በሚል ሂሳብ የሚያመጣዉ የመፍትሄ መንገድ ዉጤታማ አይሆንም፡፡  የመንግስት ስልጣን በምንም ሁኔታ ቢሆን ከሀገር ህልዉናና ከህዝቦች ደህንነት አይቀድሙምና ገዥዉ ፓርቲ ዋነኛ ትኩረቱን ሀገር በማዳን ላይ ሊያደርግ ይገባል፡፡

የወቅቱን ሁኔታ አስመልክቶ የሀገሪቱና የፓርቲዉ ከፍተኛ አመራር የተሰማዉን ጭንቀት የማይጋሩና በሀገሪቱ ዉስጥ ምንም ቢከሰት ደንታ የሌላቸዉ ራስ ወዳድ የፓርቲዉ ሰዎች እንዳሉ በሚገባ ይታወቃል፡፡  የዚህ ዓይነቶቹ ከጥቅማቸዉ በስተቀር ለሀገርና ለህዝብ ደንታ የሌላቸዉ ግለሰቦች የገዥዉን ፓርቲ አስፋላጊነትና ፋይዳ የሚገነዘቡት ለህዝቡ በሚሰራዉ መልካም ስራዎቹ ሳይሆን ለነሱ የግል ጥቅም ማስጠበቂያ መሆን በመቻሉ ብቻ ነዉ፡፡  በዚህ ምክንያትም ከፍተኛዉ አመራር የራሱን ህልዉና አደጋ ላይ አስከሚጥል ድረስ ቆራጥ ዉሳኔ በመዉሰድ ሀገሪቱን ከቀዉስ ለመታደግ የሚያደርገዉን ጥረት በተለያዩ መንገዶች ከማደናቀፍና ቢሎም እንዳይሳካ ከማድረግ የማይቆጠቡ ናቸዉ፡፡

መንግስት መሆን የሚያስከትለዉን ከባድ ሃላፊነት ለመረዳትም ሆነ ሀላፊነቱን ለመሸከምም የማይፈልጉ ነገር ግን የመንግስት ስልጣንን ፋይደ ,የሀብት ምንጭ ከመሆኑ ዉጭ የማይረዱ ናቸዉ፡፡ “የኢህአዴግን ስልጣን የሚያሳጣ ከሆነ ሲፈልግ ሁሉም ነገር ገደል ይግባ! ኢትዮጵያም ካሻት ጥንቅር ትበል!” የሚል የእብደት አመለካካት የተጠናወታቸዉና  “አስፈላጊ ከሆነ የህይወት መስዋእትነት ከፍለንም ቢሆን ገዥዉ ፓርቲን ስልጣን እንዳይለቅ እናደርጋለን!” የሚሉ ለህዝብ ከፍተኛ ንቀት ያላቸዉና እጅግ የዘቀጡ ራስ ወዳድ የሆኑ የዚህ ዓይነቶቹ ግለሰቦች የገዥዉ ፓርቲ ወዳጅ እየመሰሉ በተግባር በህዝብ እንዲጠላ የሚያደርጉ ከዚህ የተዛባ አመለካካታቸዉና አደገኛ ድርጊታቸዉ እንዲታቀቡ ሊመከሩ ይገባል፡፡

በተቃዋሚ ጎራ ያለዉም ቢሆን ከዚህ ብዙም የተለየ አይደለም፡፡ ከዚህ በፊት ብዙም ባልተለመደ ሁኔታ ገዥዉ ፓርቲ ለሰላማዊ ዉይይትና ድርድር ፈቃደኛ ሆኖ መገኘቱን እንደ ድክመትና እንደ ሽንፈት ቆጥረዉ ሁኔታዉ አመቼን በሚል ስሜት በእልህ መንገድ ትርፍ ፍለጋ አጉል እየዳከሩ ስለሆነ ከዚህ አካሄዳቸዉ ሊቆጠቡ ይገባል፡፡

አንዳንድ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ገዥዉን ፓርቲ ሆን ብለዉ በማስቆጣትና እልህ በማጋባት በቁርጠኝነት ከጀመረዉ ሰላማዊ መንገድ ወጥቶ የኃይልና የጥፋት መንገድን እንዲመርጥ እያስገደዱት መሆናቸዉን እየታዘብን ሲሆን ተቃዋሚዎች ለዚህ ዓላማቸዉ መሳካት ቢለዉ በሚቆሰቁሱት ሁከት ምክንያት ለሚፈጠር ችግር ከተጠያቂነት እንደማያመልጡ ካሁኑ ልናስታዉሳቸዉ እንወዳለን፡፡  የሰላምና ደህንነት መስፈን ጠቀሜታዉ ለነሱም ጭምር መሆኑን ተረድተዉ ሰላም በማስፈኑ ረገድ ከገዥዉ ፐፓርቲ ጎን ቆመዉ የበኩላቸዉን ጥረት ሊያደርጉ ይገባል፡፡

በተረፈ መንግስትም ሆነ ተቃዋሚ ፖለቲከኞች ለስልጣን ከሚያደርጉት ፍልሚያ በፊት ለሀገሪቱ ህልዉናና ለሰላም ቅድሚያ ሰጥተዉ እርስበርስ እንደ ደመኛ ጠላት መተያየትን አቁመዉ አሁን በሀገራችን ላይ ከተጋረጠዉ አደጋ ለመዉጣት እጅ ለእጅ ተያይዘዉ በጋራ ሊሰሩ ይገባል፡፡  በዚህ አስተሳሳብ ላይ መግባባት ከተቻለ አሁን የተከሰተዉ ሁኔታ መፍትሄ ይጠፋለታል ብዬ አላስብም፡፡

እኔም ስለ ወቅታዊዉ የሀገራችን ሁኔታ ይሄን ያህል ካልኩ በዚህ ቀዉጥ ወቅት ላይ ሰላምና ድህነታችንን በማስከበር ተግባር ተጠምዶ እጅግ አስቸጋሪ በሆነ ሁኔታ ሃላፊነቱን እየተወጣ ስለአለዉ መከላከያ ሰራዊታችን ከወቅቱ ሁኔታ አንጻር አንዳንድ ጉዳዮችን ማንሳት ተገቢ ሆኖ አግኝቸዋለሁ፡፡ በተለይም የሰራዊቱን ድካምና ጥረት ዋጋ ለማሳጣትና ከህዝብ የተቸረዉን አክብሮትና ፈቅር ለመንፈግና ከሃላፊነቱ እንዲዘናጋ ለማድረግ ሆን ተብሎ በአንዳንድ ወገኖች የሚነዛዉ ስም የማጥፋት ዘመቻና የተዛቡ አመላካከቶች ጎጂነታቸዉ በቀላሉ የሚታይ ባለመሆኑ ሁላችንም ልንታገለዉ ይገባል ብዬ ስለማምን በዚህ ረገድ የማምንበትን አንዳንድ የግል አስተያየቴን ለማካፈል  እሞክራለሁ፡፡

በአሁኑ ሰዓት የወቅቱን ሁኔታ መነሻ ባደረገ መልኩ መከላከያ ሰራዊቱን በሚመለከት ሶስት የተለያዩ አመለካከቶች ከተለያዩ ወገኖች ሲንጸባረቁ ይደመጣሉ፡፡ የመጀመሪያዉ ፤.መከላከያ ሰራዊቱ ስርአቱን የማዳንና የዜጎችን ደህንነት የማስከበር ህገመንግሰታዊ ሃላፊነቱን ተገቢነት አምነዉ አሁን እየሰራ ባለዉ መንገድ አጠናክሮ እንዲቀጥል የሚፈልጉ ሲሆኑ በሁለተኛ ምድብ ያሉት ደግሞ ጸጥታ የማስከበር ተግባሩን አርግፍ አድርጎ አቁሙ አርፎ እንዲቀመጥ የሚፈልጉ ናቸዉ፡፡

በሶስተኛ ደረጃ ያሉት ደግሞ መከላከያ ሰራዊቱ አስፈላጊ ከሆነ የመንግስትን ስልጣን አስከ መቆጣጠር የሚደርስ እርምጃ በመዉሰድ ሲቪሉን ተክቶ ሀገር እንዲያስተዳድር ፍላጎት ያላቸዉ ናቸዉ፡፡ ሰራዊቱ ጸጥታ ከማስከበር ሃላፊነቱ እንዲቆጠብ መፈለግም ሆነ በመንግስት አስተዳዳር ዉስጥ ጣልቃ እንዲገባ መሻት የተሳሳተ አመለካካት መሆን ብቻ ሳይሆን እጅግ አደገኛም ጭምር መሆኑ ሊታወቅ ይገባል፡፡

Photo - Ethiopian solidiers at national flag day 2017
Photo – Ethiopian solidiers at national flag day 2017

መከላከያ ሰራዊቱ የህዝብን ሰላምና ደህንነት መጠበቅ ግዴታዉ እንጂ ትርፍ ስራ አይደለም

በዚህ በቀዉጥ ሰዓት ማንኛችንም ብንሆን ከሁሉም በላይ የሚያሳስበን ሰላማችን ይመስለኛል፡፡ ስለ ሰላማችንና ደህንነታችን ስናስብ ቀድሞ የሚታየን መከላከያ ሰራዊታችን ነዉ፡፡ ሁላችንም የስጋት ስሜት በተሰማን ቁጥር መከላከያ ሰራዊቱ በፍጥነት ደርሶ ሊታደገን እንደሚችል በእርግጠኝነት እንተማማናለን፡፡  የፖለቲካ ዉገና ችግር የሌለበት፤የወጣበት ብሄር፤ የጎሳ፤ የዘር ልዩነት ሳያግደዉ የሁሉም ህዝቦች የጋራ መመኪያ የሆነዉን መከላከያ ሰራዊት በችግር ገዜ አማራዉም ትግሬዉም ወላይታዉም ኮንሶዉም ሶማሌና ኦሮሞዉም ወዘተ ሁሉም ይፈልጉታል፡፡ በዚህ መንፈስም መከላከያ ሰራዊቱም በተፈለገበት ወቅትና አካባቢ ሁሉ በፍጥነት እየደረሰ ሃላፊነቱን እየተወጣ ይገኛል፡፡

መከላከያ ሰራዊታችን በዚህ ቀዉጥ ሰዓት እየሰራ ያለዉ በህገመንግስቱ የተቀመጠለትን ሃላፊነት እንጂ ከዚያ ዉጭ አይደለም፡፡ ከዉጭ ወራሪ ጠላት ሊሰነዘር የሚችል ምናልባታዊ ጥቃት ብቻ ሳይሆን  በዉስጥ የሚነሱ ማንኛዉም ዓይነት ጸረ-ህገመንግስት እንቅስቃሴዎችን ማምከን ቢሎም መቆጣጠር የመከላከያ ሰራዊቱ ህገ መንግስታዊ ሃላፊነት እንጂ እንደ ትርፍ ስራ ሊቆጠር የሚገባዉ አይደለም፡፡

ሀገር እየታመሰ፤ ህገ መንግስታዊ ስርአቱ ለአደጋ ተጋልጦና የዜጎች ደህንነት አደጋ ላይ ሲወድቅ እያየ በዝምታ ማለፍ አይጠበቅበትም፡፡ በየአካባቢዉ ሲከሰቱ የነበሩ የጸጥታ ችግሮችን ለመቆጣጠር መከላከያ ሰራዊቱ ጣልቃ መግባት አልነበረበትም የሚል የተቃዉሞ አስተያየት አስካሁን በህዝቡ ሲሰጥ አልሰማንም፡፡ ምናልባት ህዝቡ ቅሬታ ሲያቀርብ ነበረዉ የጸጥታ ችግር ሲገጥመን መከላከያ ለምን በፍጥነት አልደረሰልንም? የሚል እንጂ አስከነአካቴዉ ለምን መጣብን የሚል አልነበረም፡፡

በርግጥ ህዝቡ አሁንም ቢሆን በየአካባቢዉ የጸጥታ ችግር በተከሰተ ቁጥር መከላከያ ሰራዊቱ ፈጥኖ እንዲደርስለት መጎትጎቱን አልተወም፡፡ በተለያዩ አካባቢዎች ለከፍተኛ አደጋ ተጋልጠዉ ለድህንነታቸዉ ስጋት ግብቷቸዉ የነበሩ ዜጎች መከላከያ ሰራዊቱ በግዜ ባይደርስላቸዉ ኖሮ ለከፋ አደጋ ሊዳረጉ ይችሉ እንደነበር በመግለጽ ሰራዊቱንና መንግስትን ከማመስገንም ወደ ኋላ አላሉም፡፡  ስለዚህ ህዝቡ ደህንነቱ አደጋ ላይ ወድቆ እያለ መንግስት መከላከያ ሰራዊቱን ዝም ብለህ አርፈህ ተቀመጥ ሊለዉ አይችልም፡፡

ግብር ከፋዩ መላዉ የሀገራችን ህዝቦች ለመከላከያ ሰራዊቱ ቀለብ የሚሰፍሩት ይህን መሰል አደጋ ሲጋረጥባቸዉ ደርሶ እንዲታደጋቸዉ በመፈለጋቸዉ እንጂ እንደዚያ ባይሆን ኖሮማ ሰራዊት አለኝ ማለትስ ለምን ያስፈልግ ነበር፡፡  እንደዚህ በህዘቡ ደህንነት ላይ የሚጋረጥ ስጋት ሲኖር ህዝቡን ከጭንቀት ለመገላገል ካልሆነ በስተቀር ገና ለገና ከዉጭ ለሚሰነዘር ወረራ  ተብሎ ጦርነት በሌለበት በሰላም ጊዜ ያለስራ እየተቀለበ የሚቀመጥ ሰራዊት ህዝቡ አያሻዉም፡፡

ስለዚህ መከላከያ ሰራዊቱ የጸጥታ ችግር በተከሰተበት የትኛዉም አካባቢ እየተንቀሳቀሰ የህዝቡን ሰላምና ደህንነት ለማስከበር እያደረገ ያለዉ ጥረት ከህገመንግሰታዊ ተልእኮዉ ዉጭ ሳይሆን ህገመንግስታዊ ድንጋጌን መሰረት ያደረገና ህገመንግስቱን ለማስጠበቅም ያለመ መሆኑ ግንዛቤ ሊያዝበት ይገባል፡፡  ስለሆነም መከላከያ ሰራዊቱ አቅሙ አስከፈቀደ ድረስ በዚህ የሚያኮራ ተግባሩ እንዲቀጥልበት ከማበረታት ዉጭ ሰራዊቱ የማይመለከተዉንና ሊሰራ የማይገባዉን ስራ እየሰራ እንደሆነ ተደርጎ የሚገለጸዉ አሉባልታ መሰረት የሌለዉ መሆኑ ሊታወቅ  ይገባል፡፡

በሀገራችን በተከሰተዉ የጸጥታ ችግር የዜጎችን ደህንነት ዋስትና ለመስጠት መከላከያ ሰራዊቱ ከሌሎች የጸጥታ ኃይሎች ጋር ተቀናጅቶ እየሰራ ያለዉ ተግባር ህገመንግስታዊ ሃላፊነቱን መነሻ ያደረገና ተገቢም በመሆኑ አጠናክሮ መቀጠል ይገባዋል የሚል በአብዛኛዉ ህዝብ የሚታመን አመለካካት ነዉ፡፡ በዚህ በቀዉጥ ወቅት ላይ የሰራዊቱ ሚና ምን ያህል ነፍስ አድንና ምትክ የሌለዉ መሆኑን ከህዝቡ በላይ ሌላ ምስክር አያሻም፡፡

አስካሁን ባለዉ ሁኔታ  የህዝቡ ዋነኛዉ ጥያቄ የሆነዉ መከላከያ ሰራዊቱ ለምን መጣብን የሚል ሳይሆን ለምን ዘግይቶ ደረሰ የሚል ነዉ? የህዝቡ ጥያቄ ሰራዊቱ ፈጥኖ በመድረስ ከአደጋ ይታደገን የሚል እንጂ አስከነጭራሹ እንዳይመጣ የመፈለግ ጉዳይ አይደለም፡፡ በርግጥ ህዝቡ ይህንን ሃላፊነት ራሳቸዉን ችለዉ መፈጸም ይገባቸዉ በነበሩ የክልል ፖሊሶች ላይ ይልቅ በመከላከያ ሰራዊቱ ላይ ይበልጥ የመተማመን አዝማሚያ ማሳየቱ ለእኔ ብዙም የሚያስደስት አይደለም፡፡  ምክንያቱም ሁኔታዉ ከአቅም በላይ ካልሆነ በስተቀር ፖሊሶች ራሳቸዉን ችለዉ መስራት መልመድ አለባቸዉና፡፡

ህዝቡ በፖሊሶች ላይ እምነት ማጣቱ ያለምክንያት የሆነ ሳይሆን ይልቁንም በፖሊሶች ብቃትና ተአመምኒነት ላይ አንዳች እንከን አንዳለ በመረዳቱ ይመስለኛል፡፡  በተለይ የክልል ፖሊሶች ከአቅም ማነስም በላይ የገለልተኝነት ችግር ጎልቶ የሚታይባቸዉ የመሆኑ ጉዳይ እጅግ አሳሳቢ ስለሚመስለኝ በሂዴት መፍትሄ  ሊሰጠዉ የሚገባ ነዉ፡፡  ስለዚህ የክልል ፖሊሶች ከዚያም ቀጥሎ የፌዴራል ፖሊስን ያሉባቸዉን ዘርፈብዙ ችግሮች በመቅረፍ አስተማማኝ የሰላም ኃይል እንዲሆኑ የማብቃት አስፈላጊነት ሳይዘነጋ መከላከያ ሰራዊቱ አሁን እያዳረገ ባለዉ መንገድ አስፈላጊ በሆነ ግዜ ሁሉ የህዝብን ደህንነት የማስከበር ሃላፊነቱን አጠናክሮ መቀጠል ይገባዋል፡፡

የዜጎችን ደህንነት ለማስከበር  አስከሆነ ድረስ  ፌዴራል መንግስቱ በክልሎች ዉስጥ ጣልቃ መግባት ህገመንግስታዊ ሃለፊነቱም ግዴታዉም ነዉ፡፡  

ፌዴራል መንግስቱ የሀገሪቱን ሉአላዊነትና የህዝቡን ደህንነት የማስከበር ተቀዳሚ ኃላፊነት እንዳለዉ ይታወቃል፡፡ ይህ ሃላፊነቱም በቦታና በወቅት የሚገደብም አይደለም፡፡  በየትኛዉም የሀገሪቱ ግዛት ወይም በየትኛዉም ክልል ዉስጥ የሚከሰቱ የጸጥታ ችግሮች ሲኖሩ በቅድሚያ በክልሉ አቅም ለመፍታት ጥረት ማድረግና ከክልሉ አቅም በላይ ሆኖ ሲገኝ ደግሞ ፌዴራል መንግሰቱ ጣልቃ መግባቱ በህገመንግስቱ የተደገፈና ተገቢም አሰራር ነዉ፡፡

አስካሁን የጸጥታ ችግር በተከሰተባቸዉ አካባቢዎች መከላከያን ጨምሮ ሌሎች የፌዴራል የጸጥታ ኃይሎችን ሲያሰማራ የነበረዉ በክልል መስተዳድሮች እዉቅናና የድረሱልኝ ጥያቄ መሰረት ህገመንግስታዊ አግባብን ተከትሎ እንጂ በራሱ ፈቃድ ዘሎ የገባበት ወቅት የለም፡፡

ምንም እንኳን ፌዴራል መንግስቱ ከተጣለበት የሀገሪቱን ድህንነት የማስከበር ተቀዳሚ ሃላፊነት አኳያ በየትኛዉም ክልል ዉስጥ ለመላዉ ሀገሪቱና ህዝቦች ከፍተኛ ስጋት ሊፈጥር የሚችል ሁኔታ ሲከሰት ከክልሉ ጥያቄ ሳይቀርብለትም ቢሆን በራሱ ተነሳሽነትን ጣልቃ መግባት የሚከለክለዉ ነገር ባኖርም  አስካሁን የክልሎችን ስልጣን በመጋፋት ያለፈቃዳቸዉ ጣልቃ ለመግባት አልሞከረም፡፡

እንደሚታወቀዉ አንዳንድ የጸጥታ ችግሮች በተነጻጻሪ ከሌላዉ ቀለል ያሉና ያለማንም እገዛ በክልል የጸጥታ ኃይሎች ጥረት ብቻ ለመቆጣጠር አስቸጋሪነት የሌላቸዉ የመሆናቸዉን ያህል ሌሎች የጸጥታ ችግሮች ደግሞ ከዉስብስብነታቸዉና ለመፍትሄም አስቸጋሪነታቸዉ አንጻር በክልል አቅም መፍትሄ ማግኘት የማይችሉ እንዳሉ ይታወቃል፡፡  በተለይም ደግሞ በተለያዩ ህዝቦችና በተለያዩ አጎራባች ክልሎች መካከል የሚነሳ ግጭትን የመሳሳሉ ችግሮች ለመቆጣጠር የችግሩ ባህሪይ ከአንድ ክልል አቅም በላይ ስለሚሆን  በግዜ መፍትሄ ካልተፈለገለትም የዜጎችን ደህንነትና የሀገሪቱን ሉአላዊነት አደጋ ላይ ሊጥል ስለሚችል ፌዴራል መንግስቱ ጣልቃ መግባት ይጠበቅበታል፡፡

ይሁን እንጂ የዚህ ዓይነት በስርአቱ፤ በሀገሪቱና በህዝቡ ደህንነት ላይ የተጋረጠ ከፍተኛ አደጋ በተከሰተበትም ሁኔታ አንዳንድ የክልል መስተዳድሮች ሁኔታዉ ከአቅማቸዉ በላይ መሆኑን አያወቁም የፌዴራል መንግስቱን እገዛ ለመጠየቅ የማይፈልጉበትና እንዲያዉም ችግሩን ለመደባበቅ ሲሞክሩ ይታያል፡፡ ፌዴራል መንግስቱ ጣልቃ ገብቶ እንዲያግዛቸዉ ስለማይፈልጉ ራሳቸዉ ሆን ብለዉ ችግሩን ሲያርመጠምጡትና ቀዉሱን የበለጠ ሲያባብሱት በመጨረሻም ችግሩን ለመፍታትም አደጋች እንዲሆን ካደረጉት በኋላ ነዉ ችግር መኖሩን የሚያምኑት፡፡  የዚህ ዓይነቱ ዝንባሌ ያለምክንያት የሆነ አይደለም፡፡

ፌዴራል መንግስቱ ጣልቃ እንዳይገባ የሚፈልጉት የክልሉን ሉአላዊ ስልጣን ለማስጠበቅ አስበዉ አይደለም፡፡  ከዚያ ይለቅ ለተከሰተበት ችግር ዋነኛዉ መነሻ ምክንያት በራሱ በክልሉ አመራር  ደክመት የመነጩ ሲሆን ነዉ፡፡  የክልል አመራሩ ከኪራይ ሰብሳቢና ዘራፊዎች ጋር በተመሳጠረበት ሁኔታ ሆን ብለዉ የሚቀሰቅሱትን ቀዉስ በቶሎ መፍትሄ እንዲያገኝ ስለማይፈልጉ ችግር እንደሌለ በማስመሰልና በመደባበቅ ፌዴራል መንግስቱን እጁን እንዳያስገባ በተለያዩ መንገዶች እንቅፋት ሊፈጥሩበት ይችላሉ፡፡ ይህ ሁኔታ በቅርቡ በሀገራችን በተግባር ደርሶ አይተናል፡፡

በአጎራባች ክልሎች መካካል በማንኛዉም ሰበብ የሚነሱ ግጭቶች እንዲሁም የሌላ ክልል ተወላጆች ላይ የሚደረግ የኃይል እርምጃም ሆነ የማፈናቀል ህገወጥ ተግባር የፌዴራል መንግስቱን ጣልቃ መግባት የግድ የሚያደርጉ ሲሆን ፌዴራል መንግስቱ ባልተሳተፈበት ሁኔታ በምንም መንገድ ቢሆን በራሳቸዉ በክልሎቹ አቅም ሊፈታ የሚችል አይደለም፡፡  አንዳንድ ችገሮች ከአንድ ክልል አልፎ በመላዉ የሀገሪቱ ደህንነት ላይ ከፍተኛ አለመረጋጋት ሊፈጥር የሚችል በመሆኑ ለዚህ ደግሞ ተቀዳሚ ሃላፊነት ያለበትና ቅድሚያ ተጠያቂ የሚሆነዉም ፌዴራል መንግስቱ እንደሆነ ስለሚታሰብ  ችግር የተከሰተበት ክልል የአግዙኝ ጥያቄ ቢያቀርብም ባያቀርብም ፌዴራል መንግስቱ በራሱ ተነሳሽነት ጣልቃ መግባት ይገባዋል፡፡

ይህ ተገቢ የሆነና በሁሉም የፌዴራል ስርአት በሚከተሉ ሀገሮች የተለመደ አሰራር መሆኑ ቢታወቅም በሀገራችን የፌዴራል መንግስቱ አስካሁን ከክልሎች እዉቅና ፈቃድ ዉጭ ጣልቃ በመግባት የፌዴራል የጸጥታ ኃይሎችን ወደ ክልሎች ያስገባባት አጋጣሚ ያለ አይመስለኝም፡፡  በፌዴራል መንግስቱ በብቸኝነት የሚታዘዘዉ መከላከያ ሰራዊትም ችግር ባለባቸዉ አካባቢዎች ሁሉ ሲንቀሳቀስ የነበረዉም በክልል መስተዳድሮች ጥያቄና አግባብ ባለዉ ህግ መሰረት ብቻ ሆኖ ለዚያዉም ከአካባቢዉና ከፌዴራል ፖሊስ ጋር በመቀናጀት እንጂ የክልሉን ፖሊስን ተክቶና የክልሉን መስተዳዳር ከጫወታ ዉጭ በማድረግ ብቻዉን ለመስራት የተሞከረበት አጋጣሚ የለም፡፡

በሀገራችን አስከ ቅርብ ግዜ ከደረሱት ሁኔታዎች መረዳት እንደሚቻለዉ ፌዴራል መንግስቱ ሳይሳተፍበት በክልል አቅም ብቻ የተፈታ የጸጥታ ችግር አለመኖሩ ነዉ፡፡  ይህ ሆኖም እያለ ፌደራል መንግስት ፈጥኖ አልደረሰልንም፡፡  አስታዋሽም አጥተናል የሚሉ የቅሬታ ድምጾች በተደጋጋሚ መሰማታቸዉ አልቀረም፡፡  የፌዴራል መንግስቱ መዘግየት እዉነት ከሆነ ለምን ፈጥኖ ጣልቃ መግባት  አልቻለም የሚል ጥያቄ እንድናነሳ ያደርገናል፡፡

አንደእኔ አመለካካት ከሆነ ፌዴራል መንግስቱ በየክልሉ የሚከሰቱ ቀዉሶችን ፈጥኖ በመንቀሳቀስ መፍትሄ እንዳይሰጥ ያደረገዉ ዋነኛዉ ምክንያት በክልሉ አቅም ሊፈታ ይችላል በሚል እምነት ክልሎች ጥሪ አስኪያደርጉ ሲጠበቅ መዘግየት በመኖሩ ነዉ፡፡ በተለይም ክልሎች ራሳቸዉ የችግሩ ቆስቋሽ በሆኑበት ሁኔታ ፌዴራል መንግስቱ ፈጥኖ ጣልቃ እንዲገባ የሚጠይቁበት ምክንያት የለም፡፡ ጥያቄ አቅርበዉ ከሆነም ሁኔታም ከተባባሰ በኋላ  እንጂ እገዛ መጠየቅ በሚገባቸዉ ወቅት ላይ ባለመሆኑ ለፌዴራሉ መንግስት ሁኔታዉ አስቸጋሪ ይሆንበታል፡፡

የፌዴራል መንግስቱን ጣልቃ መግባት የግድ የሚያደርጉ ሁኔታዎች ሲፈጠሩ ክልሉ ጥያቄ ባያቀርብለትም እንኳ ፌዴራል መንግስቱ  ጣልቃ መግባት መቻል ይኖርበታል፡፡  ያለበለዚያ በክልልና በፌዴራል መካካል እርስበርስ መናበብ ከሌለ ዞሮ ዞሮ ጉዳቱ የሁላችምን ይሆናል፡፡  ከዚህ አንጻር በርካታ አብነቶች መጥቀስ ይቻላል፡፡

ለምሳሌ በአስርሺዎች የሚቆጠሩ ኦሮሞዎች ከሱማሌ ክልል ሲፈናቀሉና የሞት አደጋም ሲደርስባቸዉ፤ በተመሳሳይ ሁኔታ በሰሜን ጎንደር በትግርኛ ተነጋሪዎች ላይ ያ ሁሉ ችግር ሲደርስ ፌዴራል መንግስቱ በፍጥነት ደርሶ ከአደጋ ሊታደጋቸዉ ያልቻለዉ የማንን ፈቃድ መጠበቅ ስለ አስፈለገዉና ከየትኛዉ ወገን (ክልል) ጥያቄ አስኪቀርብለት ጠብቆ እንደሆነ ግልጽ አይደለም፡፡  ጉዳዩን የበለጠ ግልጽ ለማድረግ ፤ ኦሮሞዎች በገፍ እያተፈናቀሉ የነበረዉ ከሶማሌ ክልል መሆኑ እየታወቀ የሶማሌ ክልል ራሱ እንዲፈታዉ መጠበቅ ይገባን ነበር እንዴ? እንዴትስ ገለልተኛ ሆኖ ችግሩን ሊፈታ ይችላል ተብሎ ነዉ የታመነዉ? የተፈጠረዉ ሁኔታ የሁለት ክልል ህዝቦችን  የሚመለከት ጉዳይ በመሆኑ አላንዳች መዘግየት ፌዴራል መንግስቱ ጣልቃ መግባት ነበረበት፡፡

አስካሁን ከመጣበንበት አካሄድ መረዳት የቻልኩት ዋናዉ ችግር የፌዴራል መንግስቱ ከክልሎች እዉቅና ዉጭ ያለ አግባብ ጣልቃ መግባቱ ሳይሆን እንዲያዉም በተቃራኒዉ መዘግየቱና ማመንታት መኖሩ ነዉ ባይ ነኝ ፡፡  በሌላ አባባል የትኛቹም ክልሎች ቢሆኑ “ፌዴራል መንግስቱ ያለአግባብ ስልጣናችንን ተጋፍቷል፡፡  ያለኛ እዉቅና ሰራዊት ልኳል” የሚል ወቀሳ ሊያቀርቡ የሚችሉበት አንዳችም ምክንያት የለም፡፡  ይህ እንዳለ ሆኖ የትኞቹ የጸጥታ ችግሮች በክልል አቅም ይፈታሉ? የትኞቹ ደግሞ የፌዴራል መንግስቱን ጣልቃ መግባት ያስገድዳሉ? የፌዴራል መንግስቱን ጣልቃ መግባት በሚመለከት ክልሉ ፈቃዳኛ ካልሆነስ ምን ይደረጋል? በተለያዩ የፌዴራልና የክልል የጸጥታ ሃይሎች መካካል ሊኖር የሚገባዉ ቅንጅትና የሃላፊነት ድርሻ ምን መምስል አለበት ወዘተ የሚሉ ጉዳዮች ላይ የጠራ አሰራር ያለ አልመሰለኝም ጉዳዩ እንደገና ሊፈተሸ ይገባል እላለሁ፡፡

የመከላከያ ሰራዊቱ አባላት ሃላፊነታቸዉን ሲወጡ የቆዩት ራሳቸዉን ለአደጋ እያጋለጡ ነዉ

መከላከያ ሰራዊት አባላት አስካሁን በተሰማሩባቸዉ የህዝብን ደህንነትና ሰላም የማስከበር ተልእኮዎች ወቅት ሁሉ ሃላፊነታቸዉን ሲወጡ የነበሩት ራሳቸዉን ለአደጋ እያጋለጡ እንጂ በተመቻቸ ሁኔታ አልነበረም፡፡ ሰራዊቱ የህዝቡን ደህንነት ለመታደግ ጥረት ባደረገበት አጋጣሚ ሁሉ በጥፋት ኃይሎች የሰራዊቱ አባላት ለሞትና ለአካል ጉዳት እየተዳረጉና በርካታ ንብረቶቹም እየወደሙ እንደሆነ ልብ ልባል ይጋባል፡፡ ይህ ሁሉ እየደረሰበትም ቢሆን ሰራዊቱ የህዝብን ደህንነት ከማስከበር ችላ ያለበት ወቅት የለም፡፡ የሰራዊቱ አባላት አንዳንዴ ከነሱ ባልተናነሰ ሁኔታ ከታጠቁ ኃይሎች ጋር መጋፈጥ የግድ ይሆንባቸዋል፡፡

ሰራዊቱ የድረሱልን ጩሄት የሚያሰሙ ዜጎችን ህይወት ለመታደግ በተንቀሳቀሰባቸዉ አጋጣሚዎች ሁሉ መንገድ ላይ እያደፈጡ አደጋ እያደረሱ ጉዳት ከማድረሳቸዉም ሌላ በተፈለገዉ ፍጥነት ደርሶ ህዝቡን ከአደጋ እንዳይታደግና ሰላምን እንዳያሰፍን እንቅፋት ሲፈጥሩበት እንደነበረ ይታወቃል፡፡ ቅሬታዉንና ተቃዉሞዉን በሰላማዊ መንገድ በሚያቀርብ ህዝብ መሃል መሳሪያ በድብቅ ታጥቀዉ የተሸሸጉ የጥፋት ኃይሎች አጋጣሚዉን በመጠቀም  ወደ ጸጥታ ሃይሎች በመተኮስ ወታዳሮች በብስጭት በህዝቡ ላይ የአጸፋ እርምጃ እንዲወስዱ ለማደረግ አስበዉ የሚሰሩት ዴባና አንዳንዴ ደግሞ ራሳቸዉ ህዝብ ላይ እየተኮሱ መከላከያ ነዉ የገደለዉ ለማሰኘት ብዙ ተንኮል እንደሚሰሩ ሲታሰብ መከላከያ ስራዉን እየሰራ ያለዉ እጅግ ፈታኝ በሆነ ሁኔታ ዉስጥ መሆኑን ለመረዳት አያዳግትም፡፡

የመከላከያ ሰራዊቱን መልካም ስምና ክብሩን በማጉደፍ ከሃላፊነቱ ማዘናጋት ከቶ አይቻልም!

በገዛ ህዝቡ መሃል እየንቀሳቀሰ ጸጥታ የማስከበር ተግባር ማከናወን ለሰራዊቱ አባላት ምን ያህል አስቻጋሪና ሃላፊነቱም የከበደ መሆኑን መላዉ ሀገራችን ህዝቦች ሊገነዘቡ ይገባል፡፡ መከላከያ አስካሁን እያደረገ ያለዉ የህዝብን ደህንነት የማስከበር ተግባሩን ሲያከናዉን የቆየዉ በህዝቡ ሙሉ ድጋፍና በህዝቡ ፍላጎት እንጂ ያለ ህዝብ ፈቃድ አይደለም፡፡ ሰራዊቱ የህዝቡን ጥያቄ ተቀብሎ ከተጋረጠበት አደጋ ሊታደገዉ ተንቀሳቀሰ እንጂ በገዛ ህዝቡ ላይ የዘመተ ሰራዊት አይደለም፡፡ ይህ መሆኑ እየታወቀ አንዳንድ ወገኖች መከላከያ ሰራዊቱን ከሃላፊነቱ እንዲዘናጋና ሞራሉን ለመንካት በማሰብ  ሆን ብለዉ የሰራዊቱን መልካም ስምና  ክብሩንም በማጉደፍ ክብርና ፈቅር ከቸረዉ ህዝብ ጋራ በማጋጨት  ያልሰራዉን ጥፋት እንደሰራ እያደረጉና ጥቃቅን እንከኖቹን ደግሞ አጋኖ በማቅረብ ሲጥሩ ይታያል፡፡

በመሰረቱ የመከላከያ ሰራዊታችን ከስህተት የጸዳ ሊሆን የሚችልበት ሁኔታ ባይኖርም ነገር ግን ተፈጸሙ የሚባሉ ጥፋቶች እዉነት ከሆኑ ሆን ተብሎ የገዛ ህዝቡን ለመጉዳት ታስቦ የተደረገ ሳይሆን ግዳጁን በመወጣት ሂዴት ላይ በጫናና በስህተት የሚፈጠር ከመሆን የሚያልፍ አይደለም፡፡ በተለያዩ ግዜያት ግጭቶችን በማብረድ የህዝብን ሰላምና ደህንነት ለማስከበር ባደረገዉ እንቅስቃሴ ሂዴት በስህተትም ሆነ ከሁኔታዎች አስገዳጅነት የተነሳ የተፈጠረ የኃይል አጠቃቀም ችግር በጭራሽ አይኖርም ባይልም የዚህ ዓይነት መጥፎ አጋጣሚ ካለ በግል ጥፋት ያጠፉ የሰራዊቱ አባላት ተለይተዉ በሚመለከተዉ አካል ተገቢዉ እርምት ሊደረግ ይገባል እንጂ ገና ለገና በጥቂት አባላት ችግር ተፈጥሯል ተብሎም ሰላም ከማስከበር ተግባሩ የሚታቀብበት ምክንያት አይኖርም፡፡

በሌላ በኩል መታወቅ ያለበት ጉዳይ ቢኖር መከላከያ ሰራዊቱ ጸጥታ የማስከበር ስራ እየሰራ ያለዉ የገዥዉን ፓርቲ ዕድሜ ለማራዘም ሳይሆን የወጣበትን የራሱን ህዝብ ደህንነት ለማስከበርና ህገ መንግስታዊ ስርአቱን ለማዳን ነዉ፡፡ ስርአቱን ከአደጋ የመጠበቅና የህዝቡን ደህንነት የማስከበር ተግባር በምንም መልኩ ቢሆን የገዥዎችን ዕድሜ ለማስረዘም ተብሎ እንደተደረገ ሊቆጠር የሚገባዉ አይደለም፡፡  ይህ መሆኑ እየታወቀ መከላከያ ሰራዊቱ ህዝባዊ ሃላፊነቱን እንዳይወጣ ለማድረግ በአንዳንድ ወገኖች እየተደረገ ያለዉ አጉል ቅስቄሳ ጎጅነቱ ለማንም ሳይሆን ለህዝቡ መሆኑን ሊታወቅ ይገባል፡፡ የመከላከያ ሰራዊቱ አባላት በአንዳንድ ወገኖች ሆን ተብሎ በሚሰነዝርባቸዉ አግባብ ያልሆነ ክብረነክ ንግግር ተማረዉ ለአንድት ቀን እንኳን ስራቸዉን ቢያቆሙ በሚፈጠረዉ የጸጥታ ከፍተት ሊከሰት የሚችለዉን አደገኛ ሁኔታ ከማንም በላይ ሰላም ፈላጊዉ ህዝብ የሚገነዘብ ይመስለኛል፡፡

ስርአቱ አደጋ ላይ በወደቀበትና የዜጎች ደህንነት ስጋት ባየለበት በዚህ ቀዉጥ ሰዓት መከላከያ  ሰራዊቱ የአቅሙን ያህል ተንቀሳቅሶ የዜጎቹን ደህንነት ከማስከበርና ስርአቱን ከማዳን ዉጭ ሌላ  እንዲያደርግ አይጠበቅም፡፡ በዚህ መሰረትም  ባለፉት ሁለት ዓመታት ከሰሜን አስከ ደቡብ፤ ከምስራቅ አስከ ምእራብ የጸጥታ ችግር ተከሰተ በተባለበት ቦታ ሁሉ እንደ ሸማኔ መወርወሪያ እዚህም እዚያም እየተወረወረ የዜጎቹን ደህንነት ለማስከበር እጅግ ፈታኝ የሆነ ተግባር ሲያከናዉን እንደቆየ ማንም የሚያዉቀዉ ነዉ፡፡ መከላከያ ሰራዊታችን በወቅቱ ባከናወነዉ በዚህ አኩሪ ተግባር የሚሊዮኖች ምስጋና የተቸረዉ ቢሆንም ጥቂት ወገኖች ደግሞ መከላከያ ሰራዊቱን ዉለታ ቢስ ለማድረግ ከመሞከር ጀምሮ በሰራዉም ባልሰራዉም ሊወነጅሉት ሲሞክሩ ተደምጠዋል፡፡ የመከላከያ ሰራዊቱን ጸጥታ የማስከበር ተግባር በበጎ የማይመለከቱ ወገኖች መነሻ ምክንያታቸዉ ምን እንደሆነ ለማንም ግልጽ ነዉ፡፡

በተደጋጋሚ እንደገለጽኩት ከአቅም በላይ በሆነ ሁኔታ ዉስጥ የተከሰተ አንድም ችግር አይኖርም ባይባልም ነገር ግን ሆን ብሎ እንደተደረገና ለዚያዉም ተቋማዊ ገጽታ ያለዉ በማስመሰል በጅምላ የወታዳራዊ ተቋሙን ስም ለማጉደፍ መሞከሩ ተገቢነት አይኖረዉም፡፡ የየትኛዉም የሰለጠነ ሀገር ሰራዊትም ቢሆን በዚህ ሁኔታ ዉስጥ እንዲሰራ ሲደረግ ከቁጥጥሩ ዉጭ በሆኑ ሁኔታዎች አስገዳጅነት ለስህተት መዳረግ መቻሉ የማይቀር ነዉ፡፡

ይህ እንዳለ ሆኖ በመንግስት በኩልም ቢሆን ችላ ሊባል የማይገባዉ ነገር ቢኖር መከላከያ ሰራዊቱም ሆነ ሌሎች የጸጥታ ኃይሎች መዉሰድ የሚገባቸዉን ጥንቃቄ ላይ ተገቢዉ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት በየግዜዉ እንዲሰጣቸዉ ማድረግና አፈጻጸሙን በቅርብ ከመቆጣጠር ባሻገር በግዳጅ አፈጻጸም ወቅት የሚፈጠር ስህተት ካለ በአጥፊዎች ላይ አስተዳዳራዊ  እርምጃ የሚወሰድበት ሁኔታ ዝግ ሊሆን አይገባዉም፡፡ አንድ ወታዳር በሰህተት በፈጠረዉ ችግር ምክንያት መላዉ የሰራዊት አባላት ሊወቀሱ አይገባምና ጥፋተኞች እየተለዩ ተገቢዉ ቅጣት ሊሰጣቸዉ ይገባል፡፤

በዚህ በቀዉጥ ሰዓት ከመከላከያ ሰራዊታችን አባላት የሚጠበቅ ትልቁ የባህሪይ መገለጫ ወገንተኝነቱን  ከሁሉም በላይ ለህዝብ ማድረጉና “ከራስ በፊት ለግዳጅ!” የሚባለዉን መሰረታዊ እሴቱን በመጠበቅ ራሱን ለአደጋ አጋልጦም ቢሆን ህገ መንግስታዊ ሃላፊነቱን መወጣት መቻሉ ነዉ፡፡ መከላከያ ሰራዊቱ ወገንተኝነቱ ለህዝቡ ታማኝነቱን ደገሞ ለህገመንግስቱ በማድረግ ከየትኛዉም የፖለቲካ ፓርቲ ጋር የተለየ ጠብም ሆነ ወዳጅነት ሳይኖረዉ  ስራዉን በገለልተኝነት የሚሰራ ተቋም በመሆኑ የህዝቡን ደህንነት የማስከበር ጥረቱን ከማማስገን ይልቅ በተለየ የፖለቲካ ትርጉም ለመስጠት የሚሞክሩ ወገኖች ከዚህ መሰሉ የተዛባ አመለካካታቸዉ እንዲታቀቡ እንመክራለን፡፡

መከላከያ ሰራዊቱ የገዥዉ ፓርቲ የስልጣን ማስጠበቂያ መሳሪያ አይደለም

መከላከያ ሰራዊቱ የህዝብን ደህንነት ለማሰከበር እያደረገ ያለዉን ጥረት የገዥዉ ፓርቲ ስልጣን ለማራዘም ያለመ ተደርጎ በአንዳንድ ወገኖች የሚሰነዘረዉ አስተያየት አንዳችም መሰረት የሌለዉ አሉባልታ ከመሆን ዉጭ ሌላ ትርጉም አያሰጠዉም፡፡  የህዝብን ሰላምና ደህንነት ማስከበር ለራሱ ለህዘብና ለሀገር ተብሎ የሚሰራ እንጂ የአገዛዙን ስልጣን ከማራዘም ጋር አንዳችም የሚያቆራኘዉ ነገር የለም፡፡ በመሰረቱ የመከላከያ ሰራዊታችን የገዥዉ ፓርቲ የስልጣን ማስጠበቂያ መሳሪያ አለመሆኑ ብቻ ሳይሆን ከገዥዉ ፓርቲ ጋር አንዳችም ቁርኝት የሌለዉና ወደፊትም የማይኖረዉ ይህም ዋነኛዉ የገለልተኝነቱ መገለጫዉ እንደሆነ ሊታወቅ ይገባል፡፡

የመከላከያ ሰራዊታችን ከገዥዉ ፓርቲም ሆነ ከየትኛዉም ሌላ የፖለቲካ ቡድን ጋር ግኑኝነት ሳይኖረዉ ስራዉን በገለልተኝነት የሚያከናዉን ተቋም ሊሆን የቻለዉ በመንግስት በጎ ፍላጎት ብቻ ሳይሆን በህገመንግስት ስለተደነገገ ነዉ፡፡ ስለዚህ መንግስት ራሱ መከላከያ ሰራዊቱን ከገለልተኝነት መሪህ ዉጭ ሊጠቀሚበት ቢፈልግ እንኳን ሰራዊቱ ፈቃደኛ እንደማይሆንለት መንግስት ራሱ ጠንቅቆ ያዉቃል፡፡ ስለዚህ ሰራዊቱ ጸጥታን እያሰከበረ ያለዉ በገዥዉ ፓርቲ ስልጣን በመጨነቅ ሳይሆን የዜጎችን ደህንነት መጠበቅ ህገመንገስታዊ ግዴታዉ ስለሆነ ነዉ፡፡

መከላከያ ሰራዊቱ ህዝብ እሰከፈቀደ ድረስ ማንም ስልጣን ቢይዝና ማንም ከስልጣን ቢወርድ የሚያሳስበዉና የሚያስጨንቀዉ ጉዳይ አይደለም፡፡ መከላከያ ሰራዊቱ በስልጣን ላይ ያለዉ መንግሰት ወይም ገዥ ፓርቲን ለመገምገም ሆነ ብቃቱ የለዉም በሚል እርምት ለመስጠትም ሆነ ለመንቀፍ የሙያዉ ስነምግባር አይፈቅድለትም፡፡ ኢህአዴግ ለምን በስልጣን ላይ ሃያ ስድስት አመት ለመቆየት እንደቻለ የመከላከያ ሰራዊቱ ጭንቀት አይደለም፡፡

በዚህ ጉዳይ ላይ አንዳችም አስተያየት እንዲሰጥ የሙያዉ ስነምግባርና የገለልተኝነቱ ባህሪይ አይፈቅድለትም፡፡ ኢህአዴግ ገና ለገና ብዙ ዓመት በስልጣን ላይ ቆይቷል በሚል አገዛዙን የማይፈልጉ ወገኖች ከሰልጣን በኃይል ለማዉረድ በሚያደርጉት አጉል ሙከራ ሰራዊቱን እንዲተባባራቸዉ የሚሹ ካሉ ይሄ እንደማይሆን ሊያዉቀት ይገባል፡፡ ሰራዊቱ የዚህ ዓይነት የትብብር ጥያቄን መቀበል ቀርቶ ገና እንደዚህ ዓይነት ህገመንግስታዊ ያልሆነ እንቅስቃሴ መኖሩን እንዳወቀ በራሱ ግዜ ተንቀሳቅሶ የማክሸፍ ህገ መንግስታዊ ሃላፊነት እንዳለበትም መዘንጋት አይኖርብንም፡፡

በስልጣን ላይ ያለዉ የግዜዉ መንግስት ህጋዊ መንግስት አስከሆነ ድረስ መከላከያ ሰራዊቱ ያለ ማንገራገር ይታዘዘዋል፡፡ አሁን በስልጣን ላይ ያለዉ መንግስት በሌላ ሲተካም መከላከያ ሰራዊቱ ያለምንም ችግር አዲሱን መንግስት ይታዘዛል፡፡ መከላከያ ሰራዊቱ ስልጣን ላይ የሚገኘዉን የግዜዉን መንግስት ለመታዘዝ ካልፈቀደ ታድያ በማን እንዲታዘዝ ነዉ የሚፈለገዉ? መንግስትን እየመራ ያለዉ ገዥ ፓርቲ ማንም ይሁን ማን መከላከያ ሰራዊቱ ከገዥዉ ፓርቲ ጋር አንዳችም ግኑኝነት ወይም ቁርኝት አይኖረዉም፡፡ ገዥዉ ፓርቲ ኢህአዴግ ይሁን ወይንም ኢዴፓ፤ ኦብኮ ይሁን ወይንም ኢራፓ የትኛዉም ፓርቲ ቢሆን በህጋዊ መንገድ ስልጣን የያዘ አስከሆነ ድረስ መከላከያ ሰራዊቱን የሚያሳሰብ ጉዳይም አይደለም፡፡

እንዲያዉም ይህ ገለልተኝነቱ የት ድረስ ሊዘልቅ አንደሚችል ግልጽ ለማድረግ  ብዙዎቻችን ለማመን የሚከብደንን አንድ ሁኔታ ልግለጽ፡፡  ኦነግ ፤ግንቦት ሰባት እንዲሁም ኦብነግ የሚባሉና በሽብርተኝነት የተፈረጁ ድርጅቶች  እንዳሉ እናዉቃለን ፡፡  እናም የኢትዮጵያ ህዝብና የሀገሪቱ ህግ አዉጭ ፈቅዶ ክልከላዉ ተነስቶላቸዉ ትላንት በሽብርተኝነት የሚታወቁት የተጠቀሱት እነዚህ ድርጅቶችና በተጨማሪም የደርግ ዘመኑ ኢሰፓና ኢህአፓም ቢሆኑ በህጋዊ መንገድ ለስልጣን ተወዳዳረዉ ቢያሸንፉና መንግስት ቢመሰርቱ መከላከያ ሰራዊቱ ትላንት ከተፋለምኩትና ጠላቴ የነበረ ድርጅት ለመሰረተዉ መንግስት ልታዘዘዉ አይገባኝም ማለት አይችልም፡፡ ምክንያቱም መከላከያ በህዝብ ፍላጎትና በሀገሪቱ ፖሊሲ ላይ የመወሰን ስልጣን የለዉምና፡፡ በተጨማሪ ለየትኛዉም ፓርቲ “ህጋዊና! ህገወጥ!”በሚል የዕዉቅና ሰርቲፍከት ሰጪም አይደለምና ፡፡

የመከላከያ ሰራዊታችንን ገለልተኝነት አምነዉ ለመቀበል የማይፈልጉ አንዳንድ ወገኖች ሰራዊቱ በተጨባጭ ገለልተኛ ሲላልሆነ ሳይሆን ገለልተኛ መሆኑ ሰራዊቱን እንዳሻቸዉ ለግል ፍላጎታቸዉ በመሳሪያነት ሊጠቀሙበት ስለማይፈቅድላቸዉ ገለልተኝነቱን ስለማይደግፉ ነዉ፡፡ ሰራዊቱ የህዝብን ሰላም ማስጠበቁና ህገመንግስቱን ማስከበሩ ገለልተኛ አይደለም የሚያሰኝ አይደለም፡፡ ስርአቱን ለማፍረስም ሆነ መንግስትን በኃይል ለመጣል የሚደረግ ሙከራን ለማክሸፍ መንቀሳቀሱ ግዴታዉ ስለሆነ እንጂ የገለልተኝነት ችግር ሲላላበት አለመሆኑን ሊረዱ ይገባል፡፡

ወታዳሩ የሲቪሉን መስተዳድር እንዲተካ የሚያስገድደን ደረጃ ላይ ገና አልደረስንም!

የትኛዉም ሀገር ወታዳር ተገቢዉን ቁጥጥር ካልተደረገበት በመንግስት አሰራር ዉስጥ ጣልቃ የመግባትና መንግስትን በማስገደድ ጫና ከማድረግ ሌላ  ሁኔታዉ ባመቸዉ በማንኛዉም ጊዜ  በስልጣን ላይ ያለዉን መንግሰት በጠበንጃ ኃይል ከስልጣን የማዉረድ(ኩዴታ) ባህሪይ አለዉ፡፡ ሁልግዜም ቢሆን ወታደሮች በሌሎች አገሮች የተቃጡ የተሳኩ ኩዴታዎችን ታሪክ አነፍንፌዉ ለማወቅ ጥረት ያደርጋሉ፡፡ የተሳካም ሆነ ያልተሳካም ቢሆን ስለ ኩዴታ ለማወቅ ትልቅ ትኩረት ሰጥተዉ በጉጉት ይከታተላሉ፡፡

በጦር ሜዳ ጠላትን ለማሸነፍ ከሚጠቅማቸዉ ከ“ሳን ዙ ” የጦርነት ጥበብ ሆነ “ከክላዉስዊዝ” የጦርነት መሪሆዎች የበለጠ ቀልባቸዉን የሚስበዉ የኩዴታ ሴራ ነዉ፡፡ በጦር ትምህርት ቤቶች እንደሚሰጠዉ የዉጊያ ጥበብ  የኩዴታ ስልት (coup tactics) ትምህርትም አለመሰጠቱ በጣም ያስቆጫቸዋል፡፡ ለዚህ ሁሉ የሚገፋፋቸዉ ጠበንጃ መታጠቃቸዉና ወደ ስልጣንና ሀብት የሚያደርስ አቋራጩ መንገድም ኩዴታ ነዉ የሚል እምነት ሲላላቸዉ ነዉ፡፡ ስለዚህ አመቺ በመሰላቸዉ ግዜ ሁሉ ሙከራ ከማድረግ አይቆጠቡም፡፡

ወታዳሮች በፖለቲካ ዉስጥ አዘዉትረዉ ጣልቃ የሚገቡት ሁልግዜ በራሳቸዉ ፈቃድና ተነሳሽት ላይሆን ይችላል፡፡ እንዲያዉም በአብዛኛዉ ወታዳሮችን ለዚህ ተግባር የሚገፋፉት መሴሪ ዓላማ ያላቸዉ ሲቪል ፖለቲከኞች ናቸዉ፡፡ ወታደሩን ለፖለቲካ ዓላማቸዉ በመሳሪያነት ለመጠቀም የሚፈልጉ ጥቂት ፖለቲከኞች በተለያዩ መንገዶች በመገፋፋትም ሆነ አጉል ቃል በመግባት ወታደሩን በጥቅም በማማለል ነዉ፡፡ የኛን ጨምሮ የትኛዉም ሀገር ወታዳር ከዚህ ሁኔታ ነጻ ነዉ ሊባል አይችልም፡፡ እንግዲህ ይህ አጠቃላይ እዉነታ በሚገባ የሚታወቅና በተግባርም በደርግ ዘመን ደርሶብን ያየነዉ ሆኖ እያለ አሁን በሀገሪቱ አመራር አካባቢ የታየዉን መጠነኛ ክፍተት ምክንያት በመድረግ ወታደሩ ሲቪሉን ተክቶ ሀገር እንዲስተዳዳር መፍቀድ ወይም መመኘት በገዛ እጅ ራስን ለአደጋ መጋበዝ ነዉ፡፡

የተቃዉሞ ፖለቲካዉ ዉስጥ ያሉ ጥቂት ግለሰቦች በስልጣን ላይ ያለዉን መንግስት ስለተቹ ወይንም ገዥዉ ፓርቲ ዛሬዉኑ ስልጣን ይልቅቅ ቢለዉ ሲላወጁ ብቻ መከላከያ ሰራዊቱ አገዛዙን ከስልጣን ለማዉረድ ይተባበራል ቢሎ መጠበቅም የዋህነት ነዉ፡፡ በስልጣን ላይ ያለዉ መንግስት ህዝቡ አልፈልገዉም ብሎ ከስልጣን ካላወረደዉ በስተቀር ከዚያ ዉጭ በኃይል መንገድ መንግስትን ለመለወጥ የሚደረጉ ሙከራዎችን ሰራዊቱ በዝምታ እንዲያይ አይጠበቅም፡፡ እናም በህገመንግስቱ በተቀመጠለት ሃላፊነት መሰረት የኃይል ሙከራዉን እንዲያከሽፍ ይገደዳል፡፡

በሌላ በኩል ገና ለገና መንግስት የሆነ ችግር ዉስጥ ገብቷል ወይንም ከህብረተሰቡ በተወሰነ ክፍል መንግስት ላይ ተቃዉሞ እያሰማ ነዉ ተብሎ ወታዳሩ አገዛዙን ከስልጣን ለማዉረድ የሚቃጣበት እንዳችም ሁኔታ የለም፡፡ እንደዚያ እንዲሆን የህዝቡ ፍላጎትም አይደለም፡፡ የዚህ ዓይነቱ ጣልቃገብነት አንዴ ከተለመደ ጉዳቱ መልሶ ለህዝቡ ነዉ የሚሆነዉ፡፡ በትንሽ በትልቁ እየተነሳ አገዛዙን ከስልጣን ለሚዉረድ የሚቃጣ ሰራዊት ወደፊትም ቢሆን እንዲኖረን አንሻም፡፡

የመከላከያ ሰራዊታችን ዕለታዊ ስነምግባር መሪሆዎችን ለማንበብ እድሉን ያገኘ የትኛዉም ሰዉ ከመሪሆዎቹ ዝርዝር ዉስጥ ቢያንስ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት መከላከያ ሰራዊቱ የሲቪሉ የበላይነትና በአምነት እንዲቀበልና ወገንተኝነቱ ለህዝቡ እንዲሆን የሚያስገድዱ ናቸዉ፡፡ በኢፌዲሪ ህገመንግስትም ቢሆን መከላከያን በሚመለከት ከተደነገጉት የመከላከያ መሪሆዎች እንዲሁም የመከላከያ ማቋቋሚያ አዋጁም ሆነ በሰራዊቱ መተዳዳሪያ ደንብ አጽንኦት የተሰጠዉ ጉዳይ ሰራዊቱ ህዝባዊነትን እንዲላበስ ወገንተኝነቱን ለህዝብ እንዲያደርግ የሚያስገድዱ ናቸዉ፡፡ የዚህ ዓይነት ሰራዊት “ግርግር ለሌባ ያመቻል!” እንደሚባለዉ  በሀገሪቱ የተፈጠረዉ ግዜያዊ የጸጥታ ችግር  አመችቶኛል  በሚል  ለጣልቃገብነት የሚነሳሳበት አንዳችም ሁኔታ አይኖርም፡፡

ባለፉት ሁለት ዓመታት ጀምሮ በሀገሪቱ ዉስጥ ትንሽ ያለመረጋጋት ሁኔታ በተፈጠረ ቁጥር ሰራዊቱን ለጣልቃገብነት የሚገፋፉ ድምጾችን ከዚያም ከዚህም እየሰማን ነዉ፡፡  ባለፈዉ ዓመትም ቀዉሱ ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰ በመሰለበት ወቅት ላይም አንዳንድ ወገኖች መከላከያ ሰራዊቱ ሲቪል አመራሩን በመተካት ሀገር ለማስተዳዳር ስልጣን ሊረከብ ይችላል በሚል የተሳሳተ ግምት መነሻ አድርገዉ ስጋት የገባቸዉ ወገኖች እንደነበሩ እናስታዉሳለን፡፡ እነዚህ የዋህ ዜጎች ለዚህ ስጋት የተዳረጉት መከላከያ በሲቭሉ ጉዳይ ጣልቃ እንዲገባና የፌዴራል መንግስቱንም ሆነ የክልሎችን  መስተዳድር እንዲረከብ ፊላጎት በነበራቸዉ አንዳንድ ወገኖች ሰራዊቱን ለዚህ ዓላማ በተዘዋዋሪ መንገድ ለመገፋፋት  እያደረጉ ያለዉን ሙከራ በማስተዋላቸዉ ነዉ፡፡  አሁን ባለንበት ሁኔታም እነዚሁ ወገኖች መንግስት ለማስተዳዳር ተስኖታል  ከሚል የተሳሳተ ግምገማ በመነሳት ወታደሩ ጣልቃ እንዲገባና ራሱን ወደ መንግስትነት ቀይሮ የሲቭል አስተዳዳሩን ተክቶ  ሀገር እንዲያስተዳዳር በተለያዩ መንገዶች አጉል ቅስቄሳ ከማድረግ እንዳልተቆጠቡ እያየን ነዉ፡፡

በመሰረቱ መከላከያ ሰራዊቱ  ህገመንግስቱ በሚፈቅደዉ አግባብ መሰረት በስልጣን ላይ ባለዉ መንግስት ሲታዘዝ ጸጥታ በማስከበር ህዝቡን የማረጋገትና አጥፊዎችን ለህግ አቅርቦ ሁኔታዎች ወደ ነበረበት እንዲመለስ ከማድረግ ባለፈ ለአጭር ግዜም ቢሆን ራሱን ወደ መንግስትነት ቀይሮ ህዘብን እንዲያስተዳዳር መመኘት ሆን ተብሎ በህዝብ ላይ የሚሰነዘር  የጠላትነት አስተሳሰብ ከመሆን ዉጭ ሌላ ሊሆን አይችልም፡፡ በዚህ በአሁኑ ቀዉጥ ወቅት ላይ መከላከያ ሰራዊታችን  የዜጎችን ደህንነትና ሰላም በማረጋጋጥ ረገድ ሃላፊነቱን በተገቢዉ ሁኔታ እየተወጣ እንደሆነ የሚታወቅ ነዉ፡፡ ነገር ግን ይህ የመከላከያ ሃላፊነት  በምንም መንገድ ቢሆን በህዝብ የተመረጡ አስተዳዳሪዎችን ተክቶ ህዝብን አስከ ማስተዳዳር ሊደርስ የሚገባዉ አይደለም፡፡

መከላከያ የሲቪል መስተዳድሩን ተክቶ ከቀበሌ ጀምሮ ወረዳ ክልልና በፌዴራልም ጭምር እንዲያስተዳድር ወይም አመራር እንዲሰጥ የምንፈቅድ ከሆነ ያን ግዜ ያለ ጥርጥር በወታዳራዊ አገዛዝ ስር ለመግባት ፈቅደንና ወደን በጸጋ ተቀብለናል ማለት ነዉ፡፡ እንደዚያ ከሆነ ስልጣን በወታዳሩ እጅ በመግባቱ ምክንያት ለሚከሰተዉ  መዘዝ ሁሉ ማንንም ማማረር አይኖርብንም፡፡  የሰራነዉን ስህተት የምንገነዘበዉ በገዛ ፈቃዳችን ያስረከብናትን ስልጣን መልሰን ለመንጠቅ ፈጽሞ እንደማንችል ዘግይተንም ቢሆን ስንረዳ ነዉ ፡፡ ስልጣን አንዴ የተቆናጠጠን ወታደር በሌላ ግዜ ቃሉን ጠብቆ መልሶ ያስረክበናል ማለት ከአምበሳ መንጋጋ ስጋ ፈልቅቆ ለመንጠቅ የመሞከር ያህል የማይቻል ነዉ፡፡

በአሁኑ ሰዓት በሀገራችን የተፈጠረዉ ሁኔታም አሳሳቢነቱ ባይካድም ነገር ግን መከላከያን ወደ ስልጣን በማዉጣት በሲቪል መስተዳዳሩ ምትክ ወታዳራዊ አገዛዝን በመተካት የሚፈታ ችግር አይደለም፡፡ ለነገሩ ሁኔታዉም አንዳንድ ሰዎች አለቅጥ አጋነዉ እንደሚገልጹት ተስፋ ቆርጠን  የመከላከያን ጣልቃገብነት የምንመኝበት ደረጃ ላይም ገና አልደረስንም፡፡  እንደዚያ ዓይነት ወቅትም እንዲመጣ አንመኝም፡፡ ሌላዉ ቀርቶ መንግስት ማስተዳዳር አልቻልኩም ቢሎ በይፋ ቢያዉጅ እንኳን ሌላ መፍትሄ ከመፈለግ ዉጭ ወታደሩን አምነን ስልጣን እንዲረከከብ  የምናደርግ እብዶች አይደለንም፡፡

ምን መደረግ አለበት?

ወቅቱ የሁላችንም ጥንካሬ የሚለካበትና ለመፍትሄዉም የሁላችንንም የጋራ ጥረት የሚጠይቅ ነዉ! እያንዳንዳችን የሚጠበቅብንን ሃላፊነት መወጣት ከቻልን ከተጋረጠብን ችግር ለመላቀቅ አያዳግተነም፡፡ ዚህ ረገድ ጥቂት ሃሳቦችን ለመስጠት እሞክራለሁ፡፡

 ) መንግስትን በሚመለከት፤

መንግስታችን የተነሳበትን ተቃዉሞና የተጋረጡበትን አደጋዎች በኃይል ለመደፍጠጥ ሳይሞክር በዜዴ የማለፍ ጥንካሬዉ ከምንግዜዉ በላይ የሚለካበት ወቅት ነዉ፡፡ በተለይ ገዥዉ ፓርቲ ከሀገሪቱ ዕጣ ፈንታ ይልቅ ያየዘዉ ስልጣን በልጦበት ህዝባዊ ተቃዉሞዎችን በብልሃትና በትእግስት መስተናገድ ተስኖት መከላከያንም የድክመቱ ማካካሻ አድርጎ በመቁጠር ተቃዉሞዉን በኃይል ለማዳፈን በሚል ያልተጋባ እርምጃ በመዉሰድ ሁኔታዉን በማባባስ ሀገሪቱን ለበለጠ አደጋ ከሚያጋልጥ እርምጃ ሊቆጠብ ይገባዋል፡፡

ገዥዉ ፓርቲ የህዝቡ ጥያቄ ምን እንደሆነ በሚገባ የሚገነዘብ በመሆኑ ለነዚህ ጥያቄዎች ተገቢዉን ምላሽ ለመስጠት ቁርጠኝነት ሊኖረዉ ይገባል፡፡ ኢህአዴግ ከዚህ ቀደም አምኖ ለመቀበል የከበዱትና ዘግይቶም ቢሆን አምኖ የተቀበላቸዉን አንዳንድ እንከኖቹንና ድክመቶቹን በተግባር ማስተካካል በጀመረበት በአሁኑ ወቅት ህዝባዊ ተቃዉሞዉና ቁጣዉ ከመብረድ ይልቅ ለምን ጭራሽ እየተባባሰና እየተስፋፋ ሊሄድ እንደቻለ ምክንያቱን ሊደርስበት  ይገባል፡፡

ገዥዉ ፓርቲ አሁን በሚስተዋለዉ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ጫና ተገፋፍቶ ከህዝብ  ወገንተኝነት ባህሪዉ በማፈንገጥ ከህዝቡ ጋር የሚያቀያይመዉና ህዝብን የበለጠ የሚያስቆጣ አጓጉል እርምጃዎችን እንዳይወስድ ሊጠነቀቅ ይገባዋል፡፡ ገዝዉ ፓርቲ ለህዝቡ ፈቅርና አክብሮት ሲል አስካሁን ለዚህች ሀገር የሰራዉን ግዙፍ ስራና በዚህም ከህዝብ የተቸረዉን አክብሮት የሚያበላሽ ተግባር ላለመፈጸም ቆራጥ ሊሆን ይገባዋል፡፡ ስርአቱን ወደፊት የሚያስቀጥልና የሀገሪቱን ህዝቦች ሰላምና ደህንነት የሚያከበር አስከሆነ ድረስ ከሌሎች ወገኖች ለሚመጡ የመፍትሄ ሃሳቦች በሩን ዝግ ማድረግ አይኖርበትም፡፡

) ተቃዉሞ አድራጊ ዜጎች በተለይ ወጣቶችን በተመለከትም፤

ወጣቶቻችን ለቁጣና ለተቃዉሞ መነሻ የሆኑ ከበቂ በላይ ምክንያቶች እንዳላቸዉና ጥያቄያቸዉም ተገቢ እንደሆነ መንግስትም ሆነ መላዉ ህዝብ ያምናል፡፡ መንግስት ችግር መኖሩን አምኖም የሀገሪቱ አቅም በፈቀደ መጠን መፍትሄ ለማስቀመጥ ጥረት እያደረገ እንደሆነም ይታወቃል፡፡ መንግስት መፍትሄ ለማስቀመጥ ጥረት ማድረጉን አጠናክሮ ቀጥሎበት እያለም ተቃዉሞዉ ሊበርድ አለመቻሉንም እያየን ነዉ፡፡ ወጣቶች ጥያቄያቸዉ ተገቢ መሆኑ ብቻ ሳይሆን   በአደባባይ ቅሬታ የማቅረብም ሆነ ተቃዉሞ የማሰማት ህገመንግስታዊ መብት እንዳላቸዉ በሚገባ የሚታወቅ ሆኖ እያለ ነገር ግን አጋጣሚዉን ለመጠቀም በሚፈልጉ በዉጭ ኃይሎች መሴሪ ቅስቀሳ  በስሜት ተጋፋፍተዉና በደምፍላትና በቁጣ ተነሳስተዉ በጥላቻና አጉል ጥርጣሬ በገዛ ወገኖቻቸዉ ላይ ጥቃት ማድረሳቸዉና የሀገር ሃብትን ለማዉደም መሞከራቸዉ ተገቢ ነዉ አንልም፡፡

በዜጎች ህይወትና በንብረት ላይ አደጋ ማድረስ ሳያስፈልጋቸዉና  የሀገራቸዉን  ህልዉናም ስጋት ላይ ሳይጥሉ ተቃዉሞአቸዉን በሰላማዊ መንገድ ብቻ መግለጽ እንደሚገባቸዉ ማስታወሱ ተገቢ ነዉ፡፡ በተቃዉሞ መግለጫነት አስካሁን የተሞከረዉ አዉዳሚ የሆነ የኃይል መንገድ አግባብ አለመሆኑን ተረድተዉ ከዚህ ድርጊት ሊቆጠቡ ይገባል፡፡  ወጣቶች ያልተመለሱላቸዉ በርካታ የመብት ጥያቄዎች መኖራቸዉ ብቻዉን የዉድመት አማራጭን እንዲከተሉ ሊያደርግ እንደማይችልና በሰላማዊ መንገድ ተቃዉሞን ማራመድም ከፍተኛ ጀግንነት የሚጠይቅ ተግባር መሆኑን ተረድተዉ ኃይል ከመጠቀም እንዲቆጠቡ ይመከራሉ፡፡

) የመከላከያ ሰራዊታችንን በሚመለከት፤

መከላከያ ሰራዊታችን የህዝቡን ደህንነት ለማስከበር ህገ መንግስታዊ ሃላፊነቱን በሚወጣበት በዚህ ቀዉጥ ወቅት ለህዝቡ እስካሁን በተግባር ካሳየዉ ወገንተኝነት ሳያፈነግጥና ህዝባዊ አመለካከቱ ሳይሸረሸር የተጣለበትን ሃላፊነት ከፍተኛ ጥንቃቄ በተሞላበት ሁኔታ የመወጣት ብቃቱ ይበልጥ የሚለካበት ወቅት ነዉ፡፡ መከላከያ ሰራዊታችን በአንድ በኩል በዜጎችና በሀገሪቱ ላይ የተጋረጠዉን የጸጥታ ችግር እየተጋፈጠ በሌላ በኩል ደግሞ የህዝቡን ህገመንግስታዊ መብት ሳይደፍር በብልሃትና በከፍተኛ ጥንቀቄ ሃላፊነቱን የመወጣበት ብቃቱን በተግባር ሊየሳይ ይገባል፡፡

በርግጥ መከላከያ ሰራዊታችን በዚህ አስቸጋሪ ወቅት በጥብቅ ሊከተለዉ የሚገባዉ ባህሪይና ቁልፍ እሴት ወገንተኝነቱን ለህዝብና ለህዝብ ብቻ ማድረግን ነዉ፡፡ ሊኖረዉ የሚገባ ብቃትም አመጽን በኃይል የማፈን ወታደራዊና ቴክንካዊ ብቃት ሳይሆን ዜጎችን ለጉዳት ሳይዳርግ ደህንነታቸዉን ማስከበር መቻል ነዉ፡፡ የዜጎችን ደህንነት የማስከበር ተልእኮ ተሰጥቶት እያለ በዜጎች ላይ አደጋ ማድረስ ስለማይጠበቅበት ሃላፊነቱን በከፍተኛ ጥንቃቄ ሊወጣ ይገባል፡፡

ወደ አደባባይ ለተቃዉሞ የወጡ ወጣቶች በመንግስት ድርጊት የተቆጡና የመብት ጥያቄ ያነሱ የራሱ ወንድሞች እንጂ የጠላት ሰራዊት አለመሆናቸዉን ተረድቶ በወጣቶቹ ድርጊት ሳይደናገጥ በማመዛዘንና በጥንቃቄ ሁኔታዉን ለመቆጣጠር መሞከር ይገባዋል፡፡ እያንዳንዱ ወታዳር በግሉ የሚሰራዉ ጥፋት መንግስትን የሚያስኮንንና ወታደራዊ ተቋሙንም በህዝብ እንዲጠላ የሚያደርግ መሆኑን ተረድቶ ሃላፊነቱን በመወጣት ወቅት ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊያደርግ ይገባል፡፡

በተረፈ መከላከያ ሰራዊታችን ሊከተለዉ በሚገባ ጥንቃቄ ላይ አንዳንድ ነጥቦችን ማስታወሱ ተገቢ ይመስለኛልና በጥቂቱ እነሆ፤

የሰራዊቱ አባላት አሁን በሚታየዉ የእርስበርስ መቆራቆዝ  ዉስጥ ወደ አንዱ ወገን የሚያዳላ አቋም ሳይዙ በገለልተኝነትና ሁሉንም ህዝቦች በእኩል ዓይን በማየት የዜጎችን ደህንነት የማስከበር ህገመንግስታዊ ሃላፍነታቸዉን መወጣት ይጠበቅባቸዋል፡፡ የሰራዊቱ አባላት ከየትኛዉም ብሄር ወይም ጎሳ ጎን ተሰልፈዉ ሌላዉን ማስፈራራትና ማጥቃት እንደማይኖርባቸዉ ጠንቅቀዉ የሚያዉቁ ቢሆንም ለአንድ ብሄር ተቆርቋሪ ነን በሚሉ ሰሬኞች ተንኮል ተታለዉም ሆነ አሁን በሚታየዉ ሁኔታ ስሜታቸዉ ተጠልፎ ለወጡበት ብሄር ብቻ የተለየ ተቆርቋሪነት በማሳየት የማይገባ ተግባር እንዳይፈጽሙ  መጠንቀቅ ይኖርባቸዋል፡፡

በህዝብ መሃል ጸጥታ በማስከበር ተግባር የተሰማሩ የሰራዊት አባላት ከበላዮቻቸዉ የሚሰጣቸዉ ትዕዛዝ ግልጽና ከህግ ጋር የማይቃረን መሆኑን ወይም ትእዛዙ ህገወጥ አለመሆኑን እርግጠኛ ካልሆኑና ትዕዛዙ አጠራጣሪና ግልጽነት የጎደለዉ መስሎ ከተሰማቸዉ በሰራዊቱ መተዳደሪያ ደንብ መሰረት በቅድሚያ ማብራሪያ በመጠየቅ ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል እንጂ እንደ ወረደ በጭፍን ትዕዛዝ ተቀብለዉ ወንጀል ከመፈጸም ሊቆጠቡ ይገባል፡፡ ወታደራዊ ትዕዛዝ አክባሪነትና(military obedience) በህግ ተጠያቂ (liability)ከመሆን የሚያድን አለመሆንን ተገንዝበዉ የበላይ መመሪያንና የህግ የበላይነትን እየመዘኑ ስራቸዉን ሊሰሩ ይገባል፡፡ ከሁሉም በላይ ጸጥታ በማስከበር ወቅት በገዛ ወገናቸዉ ላይ አላስፈላጊ ጉዳት እንዳያደርሱ ተገቢዉን ጥንቃቄ ሊወስዱ ይገባል፡፡

የሰራዊታችን አባላት የኃይል አጠቃቀም ቅደም ተከተልና ኃይል መጠቀምን የግድ የሚያደርጉ ሁኔታዎችን ጠብቀዉና የግዳጅ አፈጻጸም ደንብን ሳይተላለፉ ሃላፊናቸዉን በከፍተኛ  ጥንቃቄ መፈጸም እንደሚገባቸዉ ለአፍታም መዘንጋት አይኖርባቸዉም፡፡ በተለይም በተቃዉሞ ማሰመት ሽፋን ህገወጥ ድርጊት የሚፈጽሙና የመንግስትና የህዝብ ንብረት የሚያወድሙና ሆን ብለዉም የህዝቡን ሰላምና ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥል ተግባር የሚፈጽሙ ሲያጋጥማቸዉ ከቅርብ አለቃቸዉ መመሪያ ወይም ትዕዛዝ ካልተሰጣቸዉ በስተቀር አለቅጥ ተቻኩለዉ በራሳቸዉ ግዜ የማይገባ እርምጃ ከመዉሰድ ሊቆጠቡ ይገባል፡፡ የሰራዊቱ አባላት በራሳቸዉ ላይ አደጋ እየደረሰም ቢሆን ገዳይ የሆነ መሳሪያ በመጠቀም በዜጎች ላይ ጉዳት ላለማድረስ መታገስ ይገባቸዋል፡፡

ሰራዊቱ በጸጥታ ማስከበር ወቅት የዜጎች ህይወት ላይ አላስፈላጊ ጉዳት እንይደርስ ተገቢዉን ጥንቃቄ የማድረጉ አስፈላጊነቱ እንደተጠበቀ ሆኖ እያከናወነ ያለዉ ተግባርም ህገመንግስቱን መሰረት ያደረገና  በዜጎችም ከፍተኛ ድጋፍ የተቸረዉ መሆኑን ተረድቶ  ጸጥታ የማስከበር ሃላፊነቱ ላይ ፈጽሞ ማመንታትና መጠራጠር አይኖርበትም፡፡ ምናልባት በስህተት ወይም በሁኔታዎች አስገዳጅነት የተፈጠረ ችግር ወይም የደረሰ ጉዳት ካለም ሁኔታዉን ለመደባበቅ ሳይሞክር ለበላዩ ማሳወቅ ይኖርበታል፡፡

የሰራዊቱ አባላት በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ላይ ከሃላፊነታቸዉ ለሚያዘናጋቸዉ አፍራሽ ቅስቄሳ ሰለባ ላለመሆን መጠንቀቅ ይኖርቸዋል፡፡ የአፍራሽ ፕሮፖጋንዳዎች ሰለባ በመሆን በስሜት ከመነዳት ተቆጥበዉ አግባብነት ካለዉ የበላይ ሃላፊ መመሪያ ዉጭ የትኛዉንም ትዕዛዝና መመሪያ አንዳይቀበሉ መጠንቀቅ ይኖርባቸዋል፡፡ በአንዳንድ ወገኖች የሰራዊቱን ስም ለማጉደፍ ሆን ተብሎ በሚሰጡ የተዛቡ አስተያየቶች ስሜታቸዉ ሳይነካ የተጣለባቸዉን ሃላፊነት በጽናጽ መወጣት ይጠበቅባቸዋል፡፡

ማጠቃለያ

ዛሬ በሀገራችን በተከሰተዉ ሁኔታ ሁላችንም ጉዳቱ ሳይሰማን እንደማይቀር እገምታለሁ፡፡ ከዚህ ችግር ሊያወጣን የሚችለዉ መፍተሄ ያለዉም በኛዉ በራሳችን እጅ እንጂ ከዉጭ የምንጠብቀዉ ሊሆን አይችልም፡፡ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ተቋሞቻችንን በገዛ እጃችን ማፈራረሳችን ሳያንስ እርስበርሳችን እንደጠላት መተላለቃችን እጅግ አሳዛኝ ክስተት ነዉ፡፡ ከሁሉም በላይ ሊያስስበን የሚገባዉ ዉስጣዊ አንድነታችን ተሸርሽሮ ለዉጭ ጠላትና ለሽብር ኃይሎች ጥቃት ተመቻቻተን እንዳንገኝ ነዉ፡፡ ከተጋረጠብን አደጋ የሚያወጣን መፍትሄ ከኢህአዴግ ብቻ የሚመጣ ሳይሆን የሁላችንንም የጋራ ተሳትፎና ጥረት የሚጠይቅ ነዉ፡፡ የዚህች ደሃ ሀገራችንን ንብረት ማዉደምና ወንድሞቻችንን መግደልና ማፈናቀል ነገ ዛሬ ሳይል ሊቆም ይገባል፡፡  በተከሰተዉ ሁኔታ  ሁሉ መንግስት ከሁላችንም የተለየ ሃላፊነትና ተጠያቂነት እንዳለበት ተገንዝቦ  “ምን እንዳዳርግ ትፈልጋላችሁ?” በሚል ህዝቡን በግልጽ በመጠየቅ ለመፍትሄዉ በድፍረት መትጋት ይኖርበታል፡፡

የሀገራችን ወቅታዊ ሁኔታ ከዉስብስብነቱ አንጻር ለኛ አዲስና ብዙም ያልተለመደ መስሎ ቢታይም በሌሎች ሀገሮች በተደጋጋሚ ሲከሰት የነበረ ነዉ፡፡  ስለዚህ በሁኔታዉ ተስፋ መቁረጥና ሁሉም ነገር ሊያበቃ እንደሆነ ማሰብ ጥቅም እንደሌለዉ ተገንዝበን የችግሩን መንስኤ ለይተን ሁኔኛ መፍትሄ ማስቀመጡ ነዉ የሚበጀን፡፡ ከእልህ መንገድ ወጣ ብለን እስካሁን ልታዩን ያልቻሉና አምነን ለመቀበል የከበደኑን ድክመቶቻችን ለይተን መፍትሄ ማስቀመጥ ይኖርብናል፡፡ መፈትሄዉም ማዕከል የሚያደርገዉ  ሀገርን በማዳንና ስርአቱን በማስቀጠል ላይ ከሆነ በአጭር ግዜም ባይሆን በሂዴት ከችግሩ መዉጣት አይሳነንም፡፡

ነገር ግን መፍትሄ ብለን የምናቀርበዉ ከሀገሪቱ ይልቅ የራስን ጥቅም ማዕከል በማድረግ ከሆነ ከችግሩ መዉጣት አለመቻል ብቻ ሳይሆን አስከነአካቴዉ ልንበታተንም እንደምንችል ልናዉቅ ይገባል፡፡ ገዝ ፓርቲ ከዚህ በኋላ በስልጣን ላይ መቆየት አይገባዉም የሚል ጽኑ እምነትና አሳማኝ ምክንያት ካለን ሌሎች የኃይል መንገዶችንና የጎዳና ላይ አመጽን ተወት አድርገን በቀጣዩ ምርጫ ኢህአዴግን በድምጻችን ከስልጣን ለማዉረድ መሞከሩ ይመረጣል፡፡ ከዚያ ዉጭ የትኛዉም ዓይነት የኃይል መንገድ ሀገራችንን ለማያበራ ቀዉስ ሊዳርጋት እንደሚችል ለአፍታም መዘንጋት አይኖርብንም፡፡

በገዥዉ ፓርቲ በኩልም በማንኛዉም ኪሳራ በስልጣን ላይ የመቆየት ዓላማ ካለዉ አስካሁን ፍቅሩን ላልነፈገዉ ህዝብ ከበሬታ ሲል ይህን ሃሳብ እርግፍ አድረጎ በመተዉ አስከሚቀጥለዉ ምርጫ ሀገሪቱን በአግባቡ እያስተዳዳረና የህዝቡን ሰላምና ደህንነትን እያከበረ ማቆየት ይኖርበታል፡፡

ሙሉ ትኩረታችንን አሁን በተጋረጠብን ችግርና በተከሰተዉ ሁኔታ ላይ ብቻ አድርገን የሀገር ሉአላዊነት ጉዳይ ትኩረት ተነፍጎት ለዉጭ ጠላቶቻችንና ለሽብር ኃይሎች ጥቃት ተጋላጭ እንዳንሆን መጠንቀቅ ይገባናል፡፡ በተለይም ዉስጣዊ አንድነታችንን ከሚሸረሽሩና ከፋፋይ ከሆኑ አካሄዶች ተቆጥበን በአንድነታችን ጸንተን ልንቆም ይገባል፡፡ መከላከያ ሰራዊታችንም ቢሆን  በተፈጠረዉ ሁኔታ ሳይደናገጥ ጉዳዩን ለፖለቲከኞች ትቶ የሀገር ሉአላዊነት የማስከበር መደበኛ ተግባሩ ላይ በማተኮር ሃላፊነቱን መወጣት ይገባዋል፡፡

መከላከያ ሰራዊታችን ህገመንግስታዊ ባልሆነ መንገድ ስልጣን ለመንጠቅም ሆነ ስልጣን ላለማስረከብ የሚደረግ ማንኛዉም ዓይነት የኃይል መንገድን በዝምታ እንደማያይ ሊታወቅ ይገባል፡፡  በተረፈ የሰራዊቱን አባላትና ወታደራዊ ተቋሙን ያለ ስሙ ስም በመስጠት በህዝብ የተቸረዉን ክብርና ፈቅር ለማጉደፍ የሚፈልጉ ወገኖች እንዳሉ ተረድቶ ለአፍታም ቢሆን ከሃላፊነቱ እንዳይዘናጋ ማሳሰብ እንወዳለን፡፡ መላዉ የሀገራችን ህዝቦችም በዚህ ቀዉጥ ሰዓት መከላከያ ሰራዊታችን የዜጎችን ደህንነት ለማስከበር እያከናወነ  ያለዉን እጅግ ፈታኝ ሃላፊነት ተገንዝበዉ ተገቢዉን ትብብር ከማድረግ ጀምሮ ለሰራዊታችን የሚገባዉን ፈቅርና ክብር ሊሰጡት ይገባል፡፡

********

ኮ/ል አስጨናቂ በአየር ኃይል ዉስጥ ከ1970ዓ/ም ጀምሮ ሲያገለግሉ ቀይተዉ ከ2002 ዓ/ም ጀምሮ በጡረታ ላይ የሚገኙ ናቸዉ፡፡ በአየር ኃይል ዉስጥ በዘመቻና መረጃ መምሪያ ኃላፊነት፤ በአየር ምድብ አዛዥነትና በአይር መከላከያ ኃላፊነትና በሌሎች የሃላፊነት ቦታዎች ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡ በኤርትራ ጦርነት ወቅት በሰሜን አየር ምድብ በምክትልነትነና የአየር መከላከያዉን ስራ በተለይ በሃላፊነት በማስተባበር ሲሰሩ ነበር፡፡ ኮ/ል አስጨናቂ ከቀድሞዋ ሶቭት ህብረት በወታደራዊ ሳይንስ የማስተርስ ድግሪ አላቸዉ፡፡

more recommended stories