የተሃድሶ እንቅስቃሴና ታጋይ መለስ በአብዮታዊ ዴሞክራሲ ትግል

(ህዳሴ ኢትዮጵያ)

አገራችን ኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛ እንደመሆንዋ መጠን ስለ ሰው ታሪክ ስለ ማህበረሰብ ታሪክ ሲወሳ ኢትዮጵያም ኣብራ እንደምትወሳ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ ሆኖም ግን በኣሁኑ ወቅት ስለ ኢትዮጵ ታሪክ ሲወሳ ኣብዛኛው የሚስማማበትና የታሪክ ቅርሶች የሚያመላክቱት ሶስት ሺ ዓመታትን ወደኋላ ይወስደናል፡፡ እነዚህ የታሪክ ኣሻራዎቻችን እንደሚያሳዩን ከሆነ፣ ከሶስት ሺ ዓመታት በፊት ዓለም ደርሶበት የነበረውን የስልጣኔ ማማ ላይ እንደነበርን፣ በዛን ጊዜ ዘመናዊ የመንግስት ኣስተዳደር ነበራቸው ከሚባሉት ታላላቅ የኣለማችን መንግስታት ኣንዷ ኢትዮጵያ እንደነበረች ያሳዩናል፡፡ ታሪክና ጊዜ ወደኋላ ኣይመለስም እንዲሉ ታሪክም ጊዜም ፍጥነታቸውን ሳይስተጓጎል ሽቅብ ሲጓዚ እዚህ ደርሷል፡፡ በዚህ የታሪክና የጊዜ ጉዞ ተፈጥሮን መቋቋም የቻለ የሚኖርበት መቋቋም ያልቻለ ደግሞ የሚከስምበት የተፈጥሮ ህግጋት እንዳለ ሁሉ፤ የማህበረሰቦችን የዕድገት ሁኔታ እንደሚያመላክተው የዓለማችንን የለውጥና የተፈጥሮ ሁኔታ የተገነዘቡ፣ ሁኔታቸውን ከለውጡ ጋር ያጣጣሙ ከጊዜና ከታሪክ ኣቅጣጫ ኣብረው ሲጓዙ፣ ይህን ለውጥ መቋቋምና ሁኔታቸውን ከለውጡ ጋር ማጣጣም ያቃታቸው ደግሞ ሲወድቁና ሲነሱ፣ ሲጠቡና ሲሰፉ፣ ሲያድጉና ሲቀጭጩ፣ እንደቆዩ ታሪክ ያስተምረናል፡፡ ኣገራችን ኢትዮጵያም በኣንድ ወቅት በዓለማችን ከነበሩት ገናና አገሮች መካከል ኣንድዋ እንዳልነበረች የተፈጥሮና የማሕበራዊ ዕድገት ለውጥ መቋቋም ኣቅቷት ለዘመናት የማሽቆልቆል ጉዞ በመጓዝ ከኋላዎቹ የመጀመሪያው ረድፍ እንድትሰለፍ በቅታለች፡፡

ኣሁንም ታሪክና ጊዜ ተፈጥሮኣዊ ፍጥነታቸው ጠብቀው ወደፊት ሲጓዙ የተፈጥሮና የማሕበራዊ ዕድገት ለውጥ ራሳቸውን ማጣጣም የቻሉትን በተነፃፃሪ ፍጥነት በመጓዝ ወደ መጀመሪያዎች ረድፍ ሲሰለፉ፣ ይህን መቋቋም ያልቻሉትን ደግሞ ሲፈረካከሱ ማየት ባህሪያዊ የተፈጥሮ ክስተት ሆኖ ቀጥሏል፡፡ በኣሁኑ ወቅት የታሪክና የጊዜ ወደፊት የመሮጥ ሁኔታ፣ የተፈጥሮና የማሕበረሰብ ዕድገት ፍላጎት ሁኔታ ተንትኖ በመረዳትና ኣጣጥሞ ማህበረ ኢኮኖሚያቸውን መምራት በመቻላቸው ከሩቅ ምስራቅ ኣገሮች እንደነ ቻይና፣ ኮርያ፣ ታይዋን እንዲሁም ከኣፍሪካ ኢትዮጵያ በፍጥነት በማደግ ወደ ፊተኛው ረድፍ ቦታቸውን ለመያዝ በመጓዝ ላይ ይገኛሉ፡፡ በኣንፃሩ ደግሞ የተፈጥሮና የማሕበራዊ ዕድገት ለውጥ መቋቋም ተስኗቸው፣ በመካከለኛው ምስራቅ እንደነ ኢራቅና ሶሪያ እንዲሁም በኣፍሪካ ሶማሊያና ሊብያ በምስቅልቅል ላይ ይገኛሉ፡፡ የዚህ ፅሁፍ ዋናው ዓላማ የተፈጥሮና የማሕበረሰብ ዕድገት ዕድገት ለውጦችና የታሪክና የጊዜ ወደፊት የመጓዝ ሁኔታዎች ለመተንተን ሳይሆን ከነዚህ ተፈጥሯዊ ክስተቶች የአገርን ሁኔታ አጣጥሞ በመምራትና የህዝቦች /የኣገሮችን/ የዕድገትና የለውጥ እንቅስቃሴ ከማራመድ ጀርባ ቁልፍ ሚና የተጫወቱትን ሃይሎችን ለማየት ነው፡፡

በኣንድ አገር የለውጥ ጉዞ በመጥፎም በጥሩም ጎኑ በታሪክ ሲታወሱ የሚኖሩ ኣካላት ኣሉ፡፡ በኮርያ ተኣምራዊ ፈጣን ልማት ጀርባ እነ ጀነራል ፓርክ፣ በታይፋን ፈጣን ልማት ጀርባ የኮሚታንግ ፓርቲ የሚወሱ ሲሆን በተቃራኒ በፀረ ህዝብና በሰው በላነት የሚጠሩ ደግሞ በኡጋንዳ ከ100 ሺ እስከ 500 ሺ ዜጎችን የጨፈጨፈ ኢድኣሚንና በኢትዮጵያ ደግሞ በቀይ ሽብር ብቻ ከ500 ሺ በላይ ዜጎችን የጨፈጨፈ ኢሰፓ እንደ ፓርቲ ሲሆን መንግስቱ ኋ/ማርያም ደግሞ እንደ ጨካኝ ፀረ ህዝብ መሪሆኖ ምንጊዜም ታሪክ የማይረሳቸው ናቸው፡፡

ኢትዮጵያ ከዘመናት የኋልዮሽ ጉዞ በስተመጨረሻ በ1966 ዓ.ም. ብሶት የወለደው የህዝቦች ዓመፅ በመክሸፉ የተራማጅ ሃይሎች እንቅስቃሴ ተወልዶ ከ17 ዓመት መራራ የትጥቅ ትግል ቦኋላ የድህነት ዘበኛ የነበረውን ፀረ ህዝብና ፀረ ዴሞክራሶያዊ የደርግ ስርዓት ለኣንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ተደምስሶ በምትኩ ህዝባዊና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ተተክሎ እነሆ ኣገራችን ኢትዮጵያ በልማት በኩል ፈጣን፣ ፍትሃዊና ዘለቄታ ያለው ልማት በማረጋገጥ በዓለማችን ከሚጠቀሱ ጥቂት ኣገራት ኣንዷ ለመሆን በቅታለች፡፡ በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባተ በኩልም ኢትዮጵያ ከደርግ ውድቀት ቦኋላ ዘመናዊና ዴሞክራሲያዊ የሚባል ህገመንግስት በህዝብ ተሳትፎ ኣፀድቃ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ 5 ተከታታይ ነፃ፣ ዴሞክራሲያዊና ተኣማኒነት ያተረፈ የህዝብ ምርጫዎች በማስተናገድ ህዝባዊ መንግስት ለመመስረት በቅታለች፡፡ ከዚህ የ42 ዓመታት የድልና የስኬት ጉዞ ጀርባ እንደ ድርጅት ኢህአዴግ ሲወሳ እንደ መሪ ደግሞ ታጋይ መለስ ዜናዊ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ ጓድ መለስ ዜናዊ ገና በለጋ ወጣት ዕድሜው ጀምሮ የትጥቅ ትግሉን የተቀላቀለ ሲሆን ከተራ ኣባል ጀምሮ እስከ የድርጅትና የኣገር መሪ በመሆን በዚህ 39 ዓመት የድልና የስኬት የትግል ጉዞ ቁልፊ ሚና የተጫወተ መሪ ነበር፡፡

መለስ ልዩ ፍጡር ስለነበር ኣይደለም ብቁ መሪ የሆነው፡፡ መለስ እንደ ማንኛውም ንቁና ትጉህ ኢትዮጵያዊ የነበረና በትምህርቱ፣ ስነምግባሩና ሰብኣዊ ርህራሄው የታወቀ፣ እንደነበርና በትምህርቱም ሰቃይ ከሚባሉት የሚመደብ ጎበዝ ተማሪ እንደነበር የግል ታሪኩ ያሳያል፡፡ ታጋይ መለስ ዜናዊ ወደ ትጥቅ ትግል ሲገባም እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ወጣት፣ በዛን ጊዜ የነበረውን የህዝብ ጥያቄ ኣንግቦ በኣገራችን የተሟላ የዴሞክራሲ መብቶችን ተከብሮ ህዝቡ ይሆነኛል የሚለውን መንግስት የሚመርጥበት ስርዓት እንዲኖር የሚል የወቅቱ ኣንገብጋቢ ጥያቄ ተጋርቶ ነበር በረሃ የወጣው፡፡ በዚህ ጊዜ የህዝብን ጥያቄ ኣንግቦ የተነሳው ወጣቱ ሃይል ተኪ የሌለው ብቸኛ ሂዎቱ ስለ ህዝብ ስለ አገር መስዋእት ለመክፈል ብሎ የተነሳ ነበር፡፡ ታጋይ መለስም ከነዚህ ወገኖች ኣንዱ ነበር፡፡ እነዚህ ተራማጅ ኣስተሳሰብ ተላብሰው የተነሱ ኣብዮታውያን ታጋዮች፣ ይዘውት የተነሱ ነገር ቢኖር የዓላማ ፅናትና ቁጥጠኝነት ነበር፡፡ በኣብዮታዊ ዴሞክራሲ ድርጅት ስር ተደራጅተው መታገል የጀመሩትን ታገዮች የነበራቸውን መነሻ የዓላማ ፅናትና ቁርጠኝነት፣ በድርጅታቸው በበለጠና ጥልቀት ባለው ሁኔታ እንዲዳብር ያገዛቸው፣ ጓዳዊነትን፣ ህዝባዊነትን ችግርና መከራ መጋፈጥና በፅናት መቆምን በኣጠቃላይ ብቁ የህዝብ ታጋይና መሪ ሆኖ መገኘትን ዓቅም የፈጠረላቸው እንደሆነ ሁሉም ታጋዮች በአንድ ቃል ይመሰክራሉ፡፡ በመሆኑም ኣብዮታዊ ዴሞክራሲ ድርጅት በማንም የትምህርትና የስልጠና ተቋም የማይተካ ዓቅም የሚያስጨብጥና ብቁ ህዝባዊ አመራር የሚፈራበት ትምህርት ቤት ነው የሚባለው፡፡

መለስም ወደ ድርጅቱ ሲገባም እንደማንኛውም ታጋይ በድርጅቱ ውስጥ እነኝህ ብቃቶችን ተላብሶና በቅቶ እንዲገኝ ድርጅቱ ረድቶታል፡፡ ታጋይ መለስ እንደማንኛውም ታጋይ በነኚህ ብቃቶችና የህዝብ ወገንተኝነትን ተላብሶ በረሃ ቢወጣም ካለው የግሉ ተሰጥዎ ታክሎበት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየበቃና በተመደበበት ቦታ ውጤታማ በመሆን እስከ የድርጅቱ መሪ ለመሆን የበቃ ትጉ ታጋይ ነበር፡፡ ስለ መለስ ብዙ ነገር ሊባል የሚችል ቢሆንም እዚህ ለመጥቀስ የፈለግኩት በታጋይ መለስ ዜናዊ ስብእና ተሸርሽረውበት የማያውቁትና ኣብዛኛውን ሰው ከሚያደንቁለት ነገሮችን ሁለት ጉዳዮችን ለማውሳት እፈልጋሎ፡፡ ህዝባዊ ወገንተኝነትና የዓላማ ፅናትን፡፡

በትጥቅ ትግሉ ጊዜ ወደ ትግል ለመግባት የፈለገ ሰው የመጀመሪያ መስፈርት ህዝባዊ ወገንተኝነትና ለመስዋእትነት ዝግጁ መሆንን ዋናዎቹ ነበሩ፡፡ ይህ መስፈርት የማያሟላ በኣብዮታዊ ዴሞክራሲ የሚመራ ትግል ፈፅሞ ሊደራጅ ኣይችልም፡፡ ህዝባዊ ወገንተኝነቱ ደግሞ እንደመነሻ ይኑሮው እንጂ በሂደት በትግሉ ውስጥ እየጠነከረና ጥልቀት እያገኘ የሚዳብር ሆኖ ለሌሎች ፖለቲካዊ ብቃቶች ሁሉ እንደ መነሻ የሚሆን ነው፡፡ በዚህን ጊዜ ከሞላ ጎደል ሁሉም ታጋይ ህዝባዊ ወገንተኝነቱ የላቀ እንደነበርና የድርጅቱ መለያ ባህሪ እንደሆነ ማንም የሚያውቀው ጉዳይ ነው፡፡ ይህን ባህል ከድርጅቱ ኣልፎ ወደ ሌላው ህብረተሰብ እንዲተላለፍ በማድረግ ህዝቡ በድርጅቱ ዙርያ ተሰባስቦ እንዲታገል ብሎም የደርግ ውድቀት እንዲፋጠን ካስቻሉት ቁልፍ እሴት ውስጥ ህዝባዊ ወገንተኝነትና የዓላማ ፅናትን የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ ይህ እሴት በሁሉም ታጋይና ኣባል የተያዘና እንደ ባህል ተቆጥሮ የነበረ ሲሆን እንደ ማሳያ ለማስታወስ ያክል የ’ነ ታጋይ ኣሞራውና የ’ነ ታጋይ ቀሺ ገብሩ ቪድዮ መጥቀስ ይቻላል፡፡ ከነዛ ቪድዮዎች ለመገንዘብ እንደሚቻለው ሰማዕታቱ የሚናገሩት የነበረ ሁሉ ከነበራቸው ህዝባዊ ዓላማ በመነሳት በጠላት ስር ሆኖ ያለምንም ፍርሃት የተነሱለትን ዓላማ በመግለፅ የደርግን ማንነት በድፍረት ሲያጋልጡ ምንያክል የዓላማ ፅናትን እንደነበራቸው ያሳየነ ነበር፡፡ ኢህኣዴግ በ1983 ዓ.ም. ኣዲስ ኣበባን እንደተቆጣጠረ የኢህኣዴግ ታጋዮች ለህዝብ ካላቸው ፍቅር የተነሳ፣ ህዝብን ሳይጠረጥሩ ዓላማቸውን ለማስረፅ በሚያደርጉት ሰላማዊ እንቅስቃሴ የደርግ ወንጀለኞችና ሰውበላ ካድሬዎች በህዝቡ ውስጥ ተደብቀው የሽብር ጥቃት ሲሰነዘር ታጋዮች ህዝብን ላለመጉዳት ብለው ከፍተኛ የሂይወት መስዋእትነት ከፍለዋል፡፡ ኦነግ ከሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ የትግል ኣጥር ፈርጥጦ ሲወጣም ለህዝቡ ሲባል ቢተኩሱብህ ኣትተኩስባቸው የሚል መመሪያ በመተላለፉም ከፍተኛ መስዋእትነት ተከፍለዋል፡፡ እንደ ኣሁኑ ኣያርገውና በዛን ጊዜ ማንኛውን የኢህኣዴግ ታጋይ ተላብሶት የነበረ እሴት ተመሳሳይ ነበር፡፡ ይህ የሚያሳየው ህዝባዊ ወገንተኝነትን ና የዓላማ ፅናት ከከፍተኛ ኣመራር እስከ ተራ ታጋይ ምን ያክል ስር ሰዶ እንደነበር ያሳያል፡፡

ህዝባዊ ወገንተኝነትና የዓላማ ፅናትን ጥልቀት እያገኘ የሚሄደው በትግል ወይም በውስጥ-ድርጅቱ በሚደረገው ትግል ውስጥ ነው፡፡ የድርጅት ውስጥ ትግል እየተጋጋለ ሲሄድ ህዝባዊ ወገንተኝነትንና የዓላማ ፅናትን በዛው መጠን እየተጋጋለ ለበለጠ ተኣምራዊ ውጤት የሚያደርስ ሲሆን፤ የውስጠ ድርጅት ትግል እየበረደ የሚሄድ ከሆነም ደግሞ ህዝባዊ ወገንተኝነትና የዓላማ ፅናትን በዛው መጠን እየወረደ ሂዶ ትግሉ ለኣደጋ የሚጥልና ድርጅቱ ለዝቅጠት የሚዳርግ ይሆናል፡፡ ይህም በመሰረተ-ሓሳብ /በቲኦሪ/ ደረጃ የሚነገር ብቻ ሳይሆን በኢህኣዴግ ኣባል ድርጅቶች በተግባር የታየ ጉዳይ ነው፡፡

በተግባር ያየነው ነገር ቢኖር በማንኛውም የሚደረግ ትግል በተለይ ህዝባዊ ዓላማና ፅናት ይዞ የሚታገል ድርጅት መንገዱ ኣልጋ ባልጋ እንዳልሆነና ከጠላት ጋር ከሚደረገው ትግል ባልተናነሰ የውስጠ ድርጅት ትግል ትልቅ ቦታ የሚሰጠው እንደሆነ የኢህኣዴግ የትግል ታሪክ ያሳየናል፡፡ ህዝባዊ ዓለማና ፅናት ይዞ የሚታገል ድርጅት በየጊዜው ድርጅቱን ውስጣዊ ሁኔታ እየፈተሸ መስመሩን እያጠራ ካልሄደ ውጤታማ እንደማይሆን ብሎም ዓላማውን ሳያሳካ ወደ ውድቀት እንደሚያመራ የአገራችን የፖለቲካ ፓርቲዎች ታሪክ በግልፅ ያሳየናል፡፡

ከኢህአዴግ ኣባል ድርጅቶች ውስጥ ቀድሞ የተቋቋመው ብሄራዊ ድርጅት ህወሓት ሲሆን፣ ከተቋቋመ በየ 10 ዓመታት እየታደሰ እንደመጣና መስመሩ እያጠራ በየተሃድሶውም ህዝቡን በበለጠ እያነሳሳ ከፍተኛ ድል ሲጎናፀፍ እንደነበር የድርጅቱ ታሪክ ያሳየናል፡፡ በያንዳንዱ 10 የተሃድሶ ዓመታት የታዩ ክስተቶች ስናይ የመጀመሪያው 2ና 3 ዓመታት የዝግጅት ምዕራፎች ሆነው በተሃድሶው መሰረት አዳዲስ ኣደረጃጀት፣ ኣሰራርና ስምሪት የሚደረጉበት የዝግጅት ጊዜ ሲሆን፤ ቀጥሎ ያሉትን 5ና 6 ዓመታት ደግሞ ተሃድሶው መሬት በማስነካት ተኣምራዊ ለውጥና ውጤት የሚታይበት ጊዜ ሆን፤ ቀጥሎ ያሉት ተከታታይ ጥቂት ዓመታት ደግሞ ድርጅቱ እንደገና መታደስና ማጥራት የሚፈልግበት ጊዜ ይሆናሉ፡፡ ማንኛውም ህዝባዊ ዓላማ ያነገበ ትግል ዑደቱ ይህ ይመስላል፡፡

ህወሓት ከምስረታ እስከ 1977 ዓ.ም. የተለያዩ ሚኒ-ተሃድሶዎችን ያካሄደ ሲሆን ትልቁና የመጀመሪያው ተሃድሶ የተካሄደው በ1977 ዓ.ም. ነበር፡፡ የዚህ ተሃድሶ ዋና መሃንዲስ ክቡር መሪው መለስ ዜናዊ ነበር፡፡ ህወሓት ከየካቲት 1967 ዓ.ም. በጥቂት ታጋዮችና ጥቂት መሳሪያዎች ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ እስከ መጀመሪያው የተሃድሶ ወቅት፣ 10 ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በጣም ከፍተኛ ሊባል የሚችል ውጤትና ዕድገት ያስመዘገበ ድርጅት ሲሆን ሄዶ ሄዶ ግን ወደ መቆምና ብሎም ወደ ኋላ የመመለስ ኣዝማሚያ ታይቶበት ነበር፡፡ በነዚህ ኣጭር ዓመታት የገጠር የህዝቡ የራስ ኣስተዳደር በመዘርጋት፣ የመሬት ይዞታ ከፊውዳሎች ነጥቆ ለህዝቡ በመማከፋፈል፣ ህዝቡም በድርጅቱ ስር ተሰልፎ ደርግን እንዲታገል በማድረግ፣ በኣጠቃላይ በሽምቅ ውጊየያ ሊደረስ የሚችለውን ከፍተኛ የሚባለው ደረጃ በ7ና 8 ዓመታት ውስጥ ሊደረስ ተችሏል፡፡ በትግራይ ውስጥ ከደርግ መንግስት የበለጠና የሰፋ የኣስተዳደር መዋቅር መዘርጋት የቻለ ህወሓት ይህን ሰፊ የህዝብ መዋቅርም ትግሉም በሽምቅ ውግያ ኣካሄድ መምራትም ማስኬድም ወደማይቻልበት ደረጃ በመድረሱ፣ ካለው መድረክ ኣኳያ የሃይሎች ኣሰላለፍና የድርጅቱ ኣቋም ብዥታ መታየት የጀመረ በመሆኑ የተሃድሰውን ኣስፈላጊነት ወለል ብሎ ታየ፡፡

በዚህ ጊዜ በሁሉም የህወሓት ታጋይ የነበረውን ህዝባዊ ወገንተኝነትና የዓላማ ፅናት በተመሳሳይ ደረጃ የነበረ ቢሆንም የተሃድሶ ኣስፈላጊነት፣ የመስመር ማጥራት፣ የሃይሎች ኣሰላለፍ ከህዝባዊ ወገንተኝነትና ካለው አገራዊና ዓለማዊ ሁኔታ ተነስቶ መተንተንና ነጥሮ ማውጣት፣ ድርጅቱ በመርህ ተመስርቶ ኣቋሙና ዓላማው ለህዝብ፣ ለወዳጅም ለጠላትም ግልፅ ማድረግ፣ የሽምቅ ውግያ ስልትን በመቀየር በምትኩ መድረኩ የሚጠይቀው በ “የድርጅት የሰላ ጫፍ ሚናና የህዝቡን የተደራጀ እንቅስቃሴ ቅንጅት” እንዲተካ በማድረግ በኩል የክቡር መሪያችን ነበር የታጋይ መለስ ዜናዊ ሚና የላቀ ነበር፡፡ በ1977 ዓ.ም. የተሎከሰው የተሃድሶ ችቦ እንደ ኣመራር ያልተገደበ ነፃና ዴሞክራሲያዊ ውይይት በማድረግ ወደ ኣንድ የጋራ አመለካከት እንዲደረስ የተደረገ ሲሆን ከዚሁ ኣዲስ የጋራ አመለካከት መጓዝ ያልቻለውን ጥጉን እንዲይዝ በማድረግ ወደታች ታጋይ፣ ኣባልና ህዝብ እንዲወርድ በማድረግ የጋራ ኣመለካከት እንዲያዝ ተደርጓል፡፡ የተለየ ኣቋም የያዙ ኣመራርና ኣባላትም ኣቋማቸcውን በማክበርና እውቅና በመስጠት ከፈለጉ ኣዲስ ድርጅት እንዲያቋቁሙ ካልፈለጉ ወደ ፈለጉበት ኣገር እንዲሄዱ ኣማራጭ ተሰጥቷቸው ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ፍት/ስንብት ተፈፅሞ ትግሉ እንዲቀጥል ተደርገዋል፡፡ በወቅቱ ተከስቶ የነበረ ድርቅ የራሱ ጫና የነበረበት ቢሆንም ከተሃድሶው ቀጥሎ የነበሩት 2ና 3 ዓመታት የስልጠና፣ የኣደረጃጀት፣ የኣሰራርና የስምሪት ዝግጅቶች ተደርገው በ3ና 4 ዓመት ውስጥ ደርግን ለመደምሰስ በቅቷል፡፡ ከደርግ ድምሰሳ ቦኋላም ሰላምና መረጋጋትን በመፍጠር የህዝቡን ይሁንታ ያለበትን ዘመናዊና ዴሞክራሲያዊ የሚባል ህገ-መንግስት በማፀደቅ ከፍተኛ ውጤት ተመዝግቧል፡፡

በዑደቱ መሰረት በትግል ወቅት የሚያስፈልገውን ተሃድሶ እንደ እርጉዝ ቀኑን ጠብቆ ሁለተኛው የመታደስ ፍላጎት ሲያንዣብብ ከክቡር ጠቅላይ ሚንስተር መለስ ዜናዊ በቀር ማንም ሊገነዘበው ኣልቻለም ነበር፡፡ ማለትም በድርጅቱ ውስጥ ችግሮች መኖራቸው፣ ኣደጋዎች ማጋጠማቸውና የትግል እንቅስቃሴው መዳከሙ ላይ የነበረው ግንዛቤ በሁሉም ከፍተኛ ኣመራር ልዩነት ያልነበረ ቢሆንም በችግሮቹ ምንጭና የኣፈታት ኣቅጣጫ ግን ከፍተኛ ልዩነቶች ሲንፀባረቁ ነበር፡፡ የተሃድሶው ችቦ መሎኮስ በሻዕብያ ወረራ ምክንያት 2ና 3 ዓመት በመዘግየቱ ችግሮቹ እየተባባሱ በመሄዳቸው ኢህአዴግን ትልቅ ኣደጋውስጥ አስገብቶት ነበር፡፡ በመሆኑም የ1993 ዓ.ም. የተለኮሰው ተሃድሶ ከ1977 ዓ.ም. ሲነፃፀር በኣፈታቱ ላይ ከባድ ችግር የነበረበት እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ምክንያቱ የ1993ቱ ተሃድሶ ድርጅታችን በመበስበስ ኣደጋ ቀላል የማይባል ርቀት ተጉዞ፣ ፀረዴሞክራሲያዊነት ስር ሰዶ፣ ህዝባዊ ወገንተኝነት ተሸርሽሮ የነበረ በመሆኑ በድርጅቱ የስራኣስፈፃሚ ደረጃ ይካሄዱ የነበሩትን የተሃድሶ የግምገማ መድረኮች ዴሞክራሲያዊ ና ሰላማዊ ነበሩ ለማለት ኣያስደፍርም፡፡ ምክንያቱ በፀረህዝብነትና በፀረዴሞክራሲያዊነት የተለከፈ ኣመራር ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ የውይይት መድረክ ያካሂዳል ተብሎ ኣይጠበቅም፡፡ በተግባርም የታየውም ይኸው ነው፡፡

በተለይ በኣንጃነት የተፈረጀው የስራኣስፈፃሚው ቡዱን የሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ መድረኮችን በመርገጥ፣ የትግራይ የህወሓት ከፍተኛ ካድሬዎችን መድረክ በትዕቢት በመርገጥ፣ ፀረ ዴሞክራሲያዊና ቢሮክራሲያዊ መንገድን ተከትሎ በፓርላማ የመንግስት ግልበጣ ለማድረግ ቆርጦ በመነሳቱና ተግባራዊ ለማድረግ እንቅስቃሴ በማድረጉ በህወሓት/ኢህኣዴግ ታሪክ ውስጥ ወደር የሌለው የፀረዴሞክራሲ ክስተት የታየበት ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ ነበር ክቡር መሪያችን ታጋይ መለስ ዜናዊ የተሃድሶውን ችቦ በመለኮስ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ እንዲሁም ግልፅና ኣሳታፊ እንዲሆን በማድረግ ልዩ ሚና ነበራቸው፡፡

በዚህ የተሃድሶ መባቻ ወቅት ነበር የኢህአዴግ ስራኣስፈፃሚ እንደ ኣካል ህዝባዊ ወገንተኝነቱን ተሸርሽሮ በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ወቅት ከህዝባዊ ባህሪው ውጭ የሆኑ ውሳኔዎች ሲወስን ጓድ መለስ ዜናዊ ግን በኣብዮታዊ ዴሞክራሲ ዓላማና መስመር፣ በህዝባዊ ወገንተኝነት ኣቋም ቆሞ የተከራከረው፡፡ ይሁንና ኢህአዴግ በዝቕጠት ጎዳና መጓዝ ጀምሮ ስለነበር የኣብዮታዊ ዴሞክራሲ ኣመለካከት ተሸንፎ በኪራይ ሰብሳቢ ኣመለካከት ተገዢ ሆኖ ለጥቂት ዓመታት ተጉዟል፡፡ የህዝባዊ ወገንተኝነቱ፣ ለዴሞክራሲ ተገዢነትና የዓላማ ፅናት በኣብዛኛው የስራኣስፈፃሚ ኣካል በማይታመን መልኩ ተሸርሽሮ ሲታይ ታጋይ መለስ ዜናዊ ግን ልክ እንደ በትጥቅ ትግሉ ወቅት የነበረው ታጋይ ልክ እንደ ኣሞራውና ቀሺ ገብሩ ቪድዮ ላይ ያየናቸው ሰማእታት፣ የሰማዕታቱ ኣደራ ጠብቆ የቆመና የተከራከረ መሪ ነበር፡፡ የመለስን ህዝባዊነት ለመረዳት የኣብዮታዊ ዴሞክራሲ የህዝባዊነትን ትርጉም ማየት ኣስፈላጊ ይመስለኛል፡፡ በኣብዮታዊ ዴሞክራሲ ኣመለካከት ህዝባዊነት ሲባል ድንበር የለውም፡፡ የኢትዮጵያ ህዝቦች ከኤርትራ ወይም ከሌሎች ኣጎራባች አገር ህዝቦች ተለይቶ የሚታይበት ነገር የለም፡፡ በሃይማኖት እምነቶች ለሁሉም የዓለም ህዝቦች በእኩል ዓይን እንደሚያዩ ሁሉ በኣብዮታዊ ዴሞክራሲ እምነትም ለሁሉም የዓለም ህዝቦች በእኩል በማየት ለሁሉም ሰላም፣ ዴሞክራሲ፣ ብልፅግና ሲመኝ ለተደራጀለት አገር ህዝብ ደግሞ መመኘት ብቻ ሳይሆን እውን እንዲሆን ህዝቡን በማሰለፍ ይታገላል፡፡ በቃ ይህ ነው የኣብዮታዊ ዴሞክራሲ እምነት፡፡ ይህም ነው ታጋይ መለስ ሳይታክት ሲሰብክ የነበረው፡፡

በዝቅጠቱ ጊዜግን ይህንን እምነት ተሸርሽሮ ህዝባዊ ወገንተኝነትን ድንበር ተበጅቶለት ዘር ቆጠራ ተገባ፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብን ፍላጎት ለማርካት የሌላን ህዝብ መብት መጣስ ምንም ችግር የለውም ተባለ፣ ስለዚ የኢትዮጵያ ስትራቴጂያዊ ጥቅም ለማስከበር ዓሰብን ከተቻለ በድርድር ካልተቻለ በሃይል የኢትዮጵያ ኣካል ማድረግ ኣለብን ተባለ፡፡ ኣብዮታዊ ዴሞክራሲ በኢትዮጵያ መምራት የሚችለው አጥንት፣ ደምና ስጋ ተቆጥሮ ነው ተባለ፡፡ ሻዕብያን ለመውጋት የተሸነፈውን ፀረህዝብና ፀረዴሞክራሲያዊ የደርግ ሰራዊት ለማሰባሰብ ሙከራ ተደረገ፡፡ አረ ስንቱ ያልተደረገ የለም ብዙ ነገር ተደርጓል፡፡ በዝቅጠቱ ጊዜ ኢህአዴግ እንደ ድርጅት በኣንዳንድ ጉዳዮች ከደርግም ተለይቶ በማይታይበት ሁኔታ ነበር እንቅስቃሴ ሲያደርግ የታየው፡፡ በዚህ ጊዜ ታጋይ መለስ ሁሉንም በኣብዮታዊ ዴሞክራሲ መስመር መልኩን ለማስያዝ ከፍተኛ መስዋእትነት ከፍሏል፡፡ መለስ የማያምንበትን ጉዳይ በብዙሃን ድምፅ ተገዢ በመሆን የተሳሳተ ታክቲክም ቢሆን ከኣብዮታዊ ዴሞክራሲ እንዳይወጣ ኣድርጎ በመምራት ውጤትን ማስመዝገብ የሚችል ልዩ መሪ ነበር፡፡

በዛን ወቅት መለስ ኢህኣዴግን እንደ ድርጅት በዝቕጠት ጎዳና መሆኑ በውል የተገነዘበ ብቸኛ መሪ በመሆኑ ይህን ድርጅት ለማቃናት ሓላፊነቱ ያለማንም ኣጋዥ ብቻውን ተሸክሞ ነበር ለጥቂት ኣመታት የተጓዘው፡፡ መለስ የአገርን መምራት ሓላፊነት ተሸክሞ፣ ጊዜ የማይሰጥ የሻዕብያ ወረራ የመመከት ሓላፊነት ተሸክሞ፣ በከባድ መስዋእትነት እዚህ የደረሰ ኢህኣዴግ ከገባበት የውድቀት ጎዳና የመግታት ሓላፊነት ተሸክሞ፤ ለዛውም ድጋፉ ይቅርና በከሃዲነት እየተፈረጀ፣ ለሚፅፋቸው ፅሁፎችና ከውጭ ለሚያደርጋቸው ግንኙነቶችን በሙሉ ሳንሱር እየተደረጉ ሰላዮች ተመድበውለት መቆሚያና መቀመጫ ሲያሳጡት፤ ይህን ችሎ የዓላማ ፅናትን ኖሮት ችግሮችን ተቋቁሞ የቆመ ብቸኛ መሪያችን ነው፡፡

ህዝባዊ ወገንተኝነትና የዓላማ ፅናት የማንኛውም ታጋይ መለያ ባህሪ ሲሆን ይህ ባህሪ በሁሉም ታጋዮችና ኣባሎች ተጠብቆ ሊቀጥል የሚችለው የተጋጋለ የውስጠ ድርጅት ትግል ሲኖር ብቻ ነው፡፡ ታጋይ መለስ ልዩ የሚያደርገው ኣንዱ ይህ የተጋጋለ የውስጥ ድርጅት ትግል በሌለበትም ባህሪዉን ጠብቆ መቆሙ ነው፡፡ የድርጅታችን ኢህኣዴግ የውስጠ ድርጅት ትግል ተቀዛቅዞ፣ ህዝባዊ ወገንተኝነትና የዓላማ ፅናትን በኣብዛኛው ታጋይና ኣመራር በዛው መጠን ተሸርሽሮ እያለ ለኣብዮታዊ ዴሞክራሲ ዓላማና መስመር በህዝባዊ ወገንተኝነት ኣመለካከት ቆሞ ድርጅቱን ከዝቅጠትና ከብተና ማዳኑ ልዩ ያደርገዋል፡፡ ከሚደርስበት የነበረ የማግለልና የተለያዩ ኣፀያፊ ጫናዎች በመነሳት እንደማንኛውም ሰው፣ መለስ ምን ኣገባኝ፣ የትግል ኣጋሮቼና ጓዶቼ እንዲህ እየጠረጠሩኝ ለምን እሰራለሁ፣ ለግሌ ቢሆን ወፈር ያለ ደሞዝ ኣግኝቼ ለቤተሰቤም ለሌላም እሆናለሁ ስለዚ ትቼላቸው ለምን ኣልሄድም ኣላለም፡፡ ይህ ሁሉ ፈተና ሲገጥመው መለስ የሚታየው የግል ኑሮ ሳይሆን፤ በትጥቅ ትግሉ በረሃላይ ቀብሯቸው የመጣ ሰማእታትና ስለህዝብ ጥቅም ሲሉ መስዋእት የከፈሉ የህዝብ ልጆች፣ እንዲሁም ለዚ ዓላማ መስዋእት የከፈሉ ስማቸውን የወረሰው (እንደ መለስ፣ ስየ፣ ስዩም፣ ስብሓት፣ ወዘተ) ታጋዮችን ስለሚያስታውስ ነበር፣ እሱ ራሱ የቀሰቀሳቸው፣ ያሳመናቸው፣ ያስታጠቃቸው፣ ያታገላቸውና ቃል የሰጡትን ሰማእታት ስለሚያስብ፣ በኢህአዴግ ሙሉ እምነት የጣለ ጭቁን ህዝብ ስለሚያስብ ነበር መለስ በፅናት የታገለው፡፡

ከመለስ ያልተናነሰ ብቃትና ተቀባይነት የነበራቸው ኣንዳንድ ታጋይ ኣመራሮች ይህን 17 ዓመት ሙሉ የታገሉለትን ድርጅት፣ የወጣትነት ዕድሜያቸው ሙሉ መስዋእት የከፈሉለትንና በኣስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰማእታት የተከፈለለትን ዓላማ፣ እነሱ በመሩት ለድል ያበቁትን መስመር ረግጠው ሲወጡ፣ ሰማእታትን ሲክዱ፣ በኣደባባይ “ተሳስተን ነበር በመሳሳታችን ለተከፈለው ከ60 ሺ በላይ መስዋእትነት ለተከፈለው ከ100 ሺ በላይ ኣካል ጉዳተኞች ሓላፊነቱ እንደ ድርሻችን በመውሰድ ተጠያቂዎች እንሆናለን ስለዚ ኣሁን ይቅርታ እንዲደረግልን እንጠይቃለን” ሲሉ ለዛውም ያቀረቡት የይቅርታ ጥያቄ በጦር ሜዳ ለተሸነፈው ኣመለካከት ለተሸከሙ ስለነበር፤ ወደ ስሜት ያልገባና ያላዘነና ያልተከፋ የኢህአዴግ አባልና ደጋፊ ኣልነበረም፡፡ ግን ደግሞ የትግላችን ውጤት ነው ብሎ ተፅናናበት እንጂ፡፡ መለስ ግን ይህን አስቀድሞ በትንታኔ ደርሶበት ነበር፡፡

የምንመካባቸውና የምንኮራባቸው መሪዎቻችን በክህደት ስናጣቸው ድርጅታችን ምን ትሆን ብሎ ያልተጨነቀ ጓድ ኣልነበረም፡፡ ከዚህ ሁሉ ጭንቀት፣ መደናገርና ብዥታ ድርጅቱን ያወጣው ጓድ መለስ ዜናዊ ነበር፡፡ ድርጅታችን በነፃ ገበያ ካፒታሊዝምና በሶሻሊዝም ኣስተሳሰቦች ግራና ቀኝ ሲዋዥቅ መንገዱን ጠፍቶት ሲደናበርና መውጫ መንገድ ሲያማትር ቅድም ከገለፅኩት ተደራራቢ ሃላፊነቶችን ሳይገድበው ለኛ ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን ለመላው የዓለማችን ድሃ አገሮች ማወጣጫ መንገድ የቀየሰው መለስ ዜናዊ ነው፡፡ በተለያዩ ሚድያዎች እንደተገለፀው መለስ 5 ዋና ዋና የፖሊሲ ሰነዶችን ጨምሮ ከ200 ሺ በላይ ገፆችን የፖሊሲና ስትራቴጂ፣ የኣቅጣጫና መመሪያ፣ የስልጠናና የግንዛቤ ማስጨበጫ ሰነዶችን ፅፎ የተወልን መሪ ነው፡፡ ለዚህ ነው መለስ በኣካል ቢለየንም በስራዎቹና በኣስተሳሰቦቹ ኣለ ከኛጋር የምንለው፡፡ የመለስ ስራ ማንም ኢትዮጵያዊ የሚያውቀውና የሚያደንቀው ስራ ነው፡፡ ሌላ ቀርቶ ኣጭበርባሪና ኪራይ ሰብሳቢም የመለስ ስም ሲጠራ በፈፀመው ተግባር /የኪራይ ሰብሳቢነት ተግባራት/ የሚፀፀት ብዙ ነው፡፡ አንድ ወቅት ሞዴል ልማታዊ ባለሃብት ለሽልማት መረጣ ሲደረግ በኣንድ ከተማ አለቃ X የሚባሉ ሞዴል ተመርጠው በጠቅላይ ሚኒስተር መለስ ዜናዊ ተሸለሙ፣ ኣለቃው የሰሩትን የኪራይ ሰብሳቢነት ተግባራት በማስታወስና በመፀፀት በስሜት የተናገሩት ነገር “እኔ ኣንድ ጨምላቃ የመለስ እጅን እንዴት ሰላም እላሎ፣ እንዴት እጁን ኣራክሳሎ” በማለታቸው ኣሁን “ሃለቃ ጨምላቕ” ተብለው በቅፅል ስም ይጠራሉ፣ ትርጉሙም የተጨማለቀ አለቃ እንደ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ነው የመለስን ስም ሲነሳ ልዩ ስሜት የማይሰማው የለም የሚባለው፡፡ ለዚህ ነው የመለስ ህልፈተ-ሞት ሲነገር ያላለቀሰ፣ ያላዘነ የኢትዮጵያ ህዝብ ኣልነበረም፡፡

ኣሁን መለስ የተወልን ኣደራ ተቀብለን ዳር ለማድረስ በምናደርገው እንቅስቃሴ ኣበረታች ውጤቶችን ብናስመዘግብም የተፈጥሮም ሰውሰራሽም ችግሮችን እያጋጠሙን ናቸው፡፡ በትጥቅ ትግሉም ሆነ በ1993 ዓ.ም. ኣጋጥመው የነበሩትን የዝቅጠት ኣደጋ አሁንም እንደ እርጉዝ ቀኑን ጠብቆ ሶስተኛው የመታደስ ፍላጎት በላይ ላያችን እያንዣበበብን ነው፡፡ ስለዚ መለስ በተወልን የኣፈታት መንገድ ተከትለን መፍታት የግድ ይላል፡፡ ለዚህ ይረዳን ዘንድ መለስ ችግሮችን ሲገጥመው ያደርገው የነበረውን ወደ ህዝቡ ዘንድ ቀረብ ብሎ ፍላጎቱን መረዳት፣ ችግሮችን ማወቅ፣ የሰማእታት ኣደራን ማስታወስ፣ ያለፉትን ኣስቸጋሪ የትግል ወቅቶችና ቃልኪዳኖችን ማስታወስ፣ ኣሁን ካለው ሁኔታ ራስን መገምገምና የራስ ክብርና ምቾት ትቶ የዓላማንና መስመርን ቀጣይነትና ቅድሚያ በመስጠት ችግሮችን ለመፍታት ግንባር ቀደም መሆንን ይጠይቃል፡፡ ስለዚ በክቡር መሪያችን ህልፈተ ሞት ወቅት የሱን ሌጋሲ ለማስቀጠል ሁላችን ቃል እንደገባነው ሁሉ፣ በዚህ 5ኛው የሙት ዓመት መታሰብያ ኣጋጣሚ የአብዮታዊ ዴሞክራሲ መስመርና ዓላማን የሚያሰናክሉ ኣባላትና ኣመራሩ እንደ “ሃለቃ ጨምላቕ” ተፀፅተው ከመንገዱ ገለል እንዲሉ ይጠበቃል፡፡ ካልሆነ ደግሞ ከህዝቡ የሚደበቅ ነገር ስለሌለ እነዚህ መዥገሮችን በመንቀል የህዳሴ ጉዞውን የማስቀጠል ሃላፊነት የሁሉም ዜጋ ሓላፊነት ነው፡፡

ዘልኣለማዊ ክብር ለመለስና ለሁሉም የትግል ሰማእታት

********

* የዚህን ጽሑፍ ጸሐፊ በነዚህ ኢሜይል አድራሻዎች ማግኘት ይቻላል [email protected] [email protected]

Guest Author

more recommended stories