“ያደቆነ ሰይጣን ሳያቀስስ አይተውም”

(ኤቢሳ ከጨፌ ዶንሳ)

አዋሳዎች ኮራንባችሁ! ከምንም ነገር በፊት ምስጋናዬን ላድርሳችሁ፡፡ የኛ ክለብ የናንተም ነውና እንዲሁም የጋራችን ልጃችሁ ጥቅም ደልሎት ባደረገው አስነዋሪ ተግባር ለመገሰፅና ለማስተማር እንዲሁም ከአባ ቡና ጎን ቆማችሁ እውነትን ለመፋረድ የወሰዳችሁት እርምጃ ኩራታችን ነው፡፡ የእግር ኳስ  ፌዴሬሽንን ሴራ ግን ባናነሳው በተሸለ፡፡ ባቡሩን አንሻፎ መንዳት ከተፈለገ ከእግር ኳስ ፌዴሬሽን ባቡር ጓዝን ጠቅልሎ መውረድም እንደሚቻል እንኳን አለማሰቡ! ምነው ጎበዝ! ስናብር ያምርብናል ተብሎ እንጂኮ ለዚህ ለዚህማ ከሚመስሉን ጋር ኳሳችንን መፈደር ይቻል የለንዴ?

እኛ ሰለ ጂማ አባቡና ዝም አንልም፡፡ የሸነን ጊቤው አርበኛ ጂማ አባቡና ከማንነት ገፃችን አንደኛው ክፍል ነውና፡፡ በርግጥ የፌዴራል ስርዓቱ ፅንሰ ሀሳብ በደንብ ለገባው ለመላው ሀገሪቱም እየወደቀ እየተነሳ ዛሬ ዛሬን መነሳሳት እየፈጠረ ያለው እግር ኳሳችን ድርብ ጌጥም ነው፡፡ አብሮነት፤ መቻቻልና የህብረ ብሔራዊነት ውበትኮ ሁሉም ዓይኖች እኩል ሲመለከቱና ሲፈርዱ ነው፡፡ የዓይን ውሃልክ የተዛባ ለታ ግን ፈር ይስታል፡፡ ፈሩን እንዳይስት ነው ጩኸታችን፡፡

በርግጥ ፌዴራላዊ ስርዓቱንና ህገ መንግስቱን ከማንም በላይ እኛ እንፈልገዋለን፡፡ እኛ እንፈልገዋለን፤ እንዋደቅለታለን ስንል ግን ለብቻችን ጥቅም አይደለም፡፡ አሊያም ከሆነ እኛ ላይ ብቻ ከሚናድ ተራራ መሸሸጊያ ስለሆነም አይደለም፡፡ ከዛ ድንበር ያለፈው አሰራርና ድርጊት ሁላችንንም ጎርፍ አድረጎ ስለሚጠራርገን እንጂ፡፡

እኔ ስፖርቱን ፖለቲካዊ የማድረግ ፍላጎት የለኝም፡፡ ሊኖረኝም አይችልም፡፡ ሲጀመር እኔ የእግር ኳስ ስፖርት ደጋፊም ወዳጅም አይደለሁም፡፡ ነገር ግን ስፖርቱን ከራሱ የጨዋነት ስርዓት አውጥተው እነ እንቶኔ ሊኮፈሱበት፤ ሊዘውሩትና ለአንዱ ግኝት ለሌላው ሽኝት ሲያደርጉት ማየት ደግሞ ፈፅሞ ስለማልሻ ነው፡፡ አሁን ማይ ሙት ይህ የእግርኳስ ፌዴሬሽን ተብዬ ከሀዋሳ ከተማ ማዘጋጃ ቤት (ከስፖርት ክለቡም ጭምር) አንሶ የተገኘው በብቃት ማነስ ወይስ በእብሪት?

የታሪክ አጋጣሚ ሆኖ ይሆናል ያሉት ቀርቶ አይሆንም ያሉት ሊሆን ሲቃረብ ስርቆት የለመዱ እጆች በአቋራጭ ያሰቡትን ለማግኘት፤ የሌላውንም እድል ለመቀራመትና ያለብቃት ማማ ላይ ራስን ለመስቀል ጥረት ያደርጋሉ፡፡ የኢትዮ ኤሌክትሪክ እግርኳስ ክለብ አንዳንድ ግለሰቦችን ስራ ከዚህ አርቄ ማየት አልሻም፡፡

ነገር ግን ለኔም፤ ለሀገሬም፤ ለወንድም ክለብም ሆነ ህዝብ የማይገባ ድርጊት ከምፈፅም ሁሉም ቢቀርብኝ ይሻላል ያለው የአዋሳ ከነማ ይህን ያህል አጥልቆ ሲመለከትና የሚወደውና ያሳደገውን ልጁን ሊቀጣ አባታዊ ልምጭ ሲቆርጥ ፌዴሬሽን ተብየው እንዳላዬ እንዳልሰማ የሚሆነው ምን አሽቶ ይሆን? ምንም ያሽት ምንም እድሉን ሲቀማ ዝም የሚል ህዝብ እዚህ ሀገር ላይ መፈጠር ከቆየ ሰነባበቷልና ቶሎ ወደመስመር መመለሱ ይሻላል፡፡ ይህንን ፌዴሬሽን ከእንዲህ አይነት ድርጊት ማፅዳት ካልተቻለ ምኑን ሀገርን ከብልሹ አሰራር ስለማጥራት ተወራ ብላችሁ ነው ወዳጆቼ!

በርግጥ ይሄኔ ለዚህ ተቋም ለማጫፈርና የሸነን ጊቤውን አርበኛ አባ ቡናን ለመድፈቅ ዱላ ለመምዘዝ የሚቃጡ ጣቶች በአትሌቲክሱም፤ በአፋን ኦሮሞውም፤ በፊንፊኔ ትምህርት ቤትና ጥቅሙም ላይ እንደቋመጡት ሁሉ አሁንም እያቆበቆቡ ለመሆኑ ማሳያዎች እልፍ ናቸው፡፡ ነገር ግን ይህ ስርዓት እነዚህን አስተሳሰቦች መሸከም የማይችል፤ ለአንዱ አድልቶ ሌላውን የሚቀማ ላለመሆኑ ግልጽ ማረጋገጫው እነዚህ ተግባራት ናቸውና መስመር ይይዛሉ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ይህ እሰኪሆን ትግላችን ይቀጥላል፡፡

ሸነን ጊቤና መላው የምእራብ ኦሮሚያ ከሚያቀርበው ቡና ለመቋደስ ቀድሚያ የሚሰለፈው ዜጋ ሁሉ የአባ ቡናን መብት ለማስከበር አብሮን ሊሰለፍ ይገባል፡፡ ጥሪም ማነሳሳትም ሳይሆን የፌዴራል ስርዓታችን ህልውና የሚረጋገጠው ሁላችንም ስለሁላችን እኩል ፍርድና ውግንና ሲኖረን ነውና! በዚህ ሁኔታ ውስጥ ልክ እንደ ሀዋሳ ከተማው ክለብ ተግባር ሁሉ ፌዴሬሽኑን የሚያስተካክል አስተሳሰቦች ይራመዳሉ፤ በፌዴሬሽኑ የፌዴራላዊ እኩልነት ፀጋችን ተግባራዊ ይደረጋል፡፡ ካልሆነም ይህ ፌዴሬሽን ተብዬ ከሚሾፍረው ባቡር ጠቅልሎ መውረድም ይቻላል፡፡ የእግር ኳስ ፌዴሬሽን የመሰረትነው እኩል ልንስተናገድና ልንተዳደርበት እንጂ ልንጎዳዳበት አይደለምና፡፡

ቸር እንሰንብት!

*********

Guest Author

more recommended stories