አዲስ አበባ የኢትዮጵያ ግዛት ለመሆን የኦሮሚያ ግዛት መሆን እንዳለባት

(Betru Dibaba)

ይህ ጽሁፍ አዲስ አበባ ከህገ መንግስቱ አንጻር ያለችበትን ሁኔታ (status quo) ለማስረዳት ተጻፈ።

የኢፌዲሪ ህገ መንግስት አንቀጽ 2፣ ስለ የኢትዮጵያ የግዛት ወሰን፣ የኢትዮጵያ የግዛት ወሰን የፌደራሉን አባሎች ወሰን የሚያጠቃልል ሆኖ በዓለም አቀፍ ስምምነቶች መሰረት የተወሰነዉ ነዉ፤ በማለት ይደነግጋል።

አያይዘን መረዳት ያለብን የፌደራሉን አባላት ዝርዝር ነዉ። አንቀጽ 47 (1)፣ የፌደራል መንግስት አባላትን እንዲህ ይዘረዝራል፤

የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ አባላት የሚከተሉት ናቸዉ፤

፩. የትግራይ ክልል፣
፪. የአፋር ክልል፣
፫. የአማራ ክልል፣
፬. የኦሮሚያ ክልል፣
፭. የሱማሌ ክልል፣
፮. የቤንሻንጉል/ጉሙዝ ክልል፣
፯. የዳቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል፣
፰. የጋምቤላ ሕዝቦች ክልል፣
፱. የሐረሪ ሕዝብ ክልል።

ስለዚህ፣ የኢትዮጵያ የግዛት ወሰን የዘጠኙ ክልሎች የግዛት ድምር ነዉ። ማለትም፣ ከዘጠኙ ክልሎች ግዛት በላይ ወይም ከዘጠኙ ክልሎች ግዛት ያነሰ ኢትዮጵያ ግዛት የላትም።

ምናልባት አንዳንዶች የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር እና የድሬዳዋ ከተማ መስተዳደርን እንደ ክልሎች ወይም እንደ የፌደራል አባላት ሲቆጥሩ ኖረዋል።

ከህገ መንግስቱ አንጻር ስለ ድሬዳዋ፣ ስለ ሽሬ፣ ወልቂጤ፣ ደብረብርሃን በላይ የሚባል አይኖርም።

ሽሬ፣ መቐለ፣ ዓድዋ በክልልነት እስካልተጠቀሱ በትግራይ ክልል ስር ካልታቀፉ፣ የኢትዮጵያ ግዛት አይሆኑም።

ወልቂጤ፣ አዋሳ፣ ወላይታ ሳዶ በፌደራል አባልነት እስካልተጠቀሱ በደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ካልታቀፉ የኢትዮጵያ አካል ሊሆኑ አይችሉም።

ደብረብርሃን፣ ባህርዳር፣ ደብረማርቆስ በክልልነት እስካልተጠቀሱ የአማራ ክልል አካል ካልሆኑ፣ የኢትዮጵያ አካል አይሆኑም።

ድሬዳዋ፣ ነቀምቴ፣ ሱሉልታ በኦሮሚያ ካልታቀፉ፣ በኢትዮጵያ ግዛት ወሰን ሊታቀፉ አይችሉም።

አዲስ አበባ የራሷ መስተዳድር ያላት ከተማ መሆኗ በህገ መንግስቱ አንቀጽ 49(2) ሰፍሯዋል። ከዚህም በላይ፣ አዲስ አበባ የፌደራል መንግስት ርዕሰ ከተማ፣ አንቀጽ 49(1) እና የብዙ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች መቀመጫና መዳረሻ ናት።

ይህ  ግን አዲስ አበባን ወደ ክልልነት ወይም ወደ የፌደራል አባልነት አያደርሳትም።

የኢትዮጵያ የግዛት ወሰን ከክልሎች ወይም ከፌደራል አባላት ወሰን ግዛት አንጻር ብቻ የተወሰነ መሆኑን ተመልክተናል። እንዲሁም፣ አዲስ አበባ ከተማ እንጂ ክልል እንዳልሆነች ከህገ መንግስቱ አይተናል።

በዓለም ላይ፣ ‘ሀ’ የ’ለ’ ክልል አካል ነዉ፣ የሚል ህገ መንግስት የለም፤ አስፈላጊም አይደለም።

ከዚህ አንጻር፣ የፌደራል ህገ መንግስታችን፣ ዓለም ላይ ካሉት ህገ መንግስታት ያለፈ ተግቷል። አዲስ አበባ በክልል መታቀፏን ግልጽ አድርጓል።

አንቀጽ 49(5) ‘… አዲስ አበባ በኦሮሚያ ክልል መሀል የሚገኝ በመሆኑ …’ የሚል ሀረግ የጠቋሚነት ሚና አለዉ። በመሆኑም፣ አንቀጽ 2 እና 47(1)ን ብቻ አንብበዉ፣ አዲስ አበባ የኦሮሚያ አካል መሆኗን ለማይረዱ ሀረጉ አጋዥ ነዉ።

አዲስ አበባ የብሔር፣ ብሔረሰብና ህዝብ ከተማ ናት፤ ሲባል የተለመደ ነዉ። አባባሉ ግን የህግ መሰረት የለዉም።

ከህገ መንግስቱ አንቀጽ 8 እና 39 ስለ ብሔር፣ ብሔረሰብና ህዝብ እናነባለን። የብሔር፣ ብሔረሰብና ህዝብ ኢትዮጵያን ያቀፈ (conglomerative) ስያሜ ነዉ። እናም የብሔር፣ ብሔረሰብና ህዝብ ስያሜ፣ እዉቅና እና ሉዓላዊነት በዋናነት በኢትዮጵያ፣ በሃገር ደረጃ በመሆኑ፣ ዝቅ ካለ ደግሞ በክልሎች ዉስጥ ለሚኖሩ የተሰጠ ነው።

በአዲስ አበባ ደረጃ ብሔር፣ ብሔረሰብና ህዝብ የሚል ስያሜ አልተሰጠም። ይልቁን ‘ነዋሪዎች’ የሚል ስያሜ እና እዉቅና ተሰተዋል። ህገ መንግስቱ በአንቀጽ 49 (4) ‘የአዲስ አበባ ነዋሪዎች … ‘ በማለት አግባብነት ባለዉ ቃል ይጠራቸዋል።

ህገ መንግስቱ ስለ ብሔር፣ ብሔረሰብ፣ ህዝብና ነዋሪ ግልጽ ማብራሪያ ባይሰጥም፤ ስለ ክልሎች እና አዲስ አበባ የተለያዩ አግባብነትና ትርጉም እንዳላቸዉ እውን ነዉ።

የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን በነዋሪነታቸዉ ብቻ ካለፍን ወደ ብሔር፣ ብሔረሰብ እና ህዝብ ሉዓላዊነት ሊደርሱ አይችሉም።

ያለን አማራጭ፣ አዲስ አበባ የኦሮሚያ ግዛት እንደሆነች፣ የአዲስ አበባ ነዎሪዎችን በኦሮሚያ ክልል ስር ነዋሪነታቸዉን ወደ ብሔር፣ብሔረሰብና ህዝብ ሉዓላዊነት ማድረስ ነዉ።

የማጠቃለያ ነጥቦች፦

* የኢትዮጵያ የግዛት ወሰን የክልሎች የግዛት ወሰን ድምር ነዉ።

* ክልሎች ዘጠኝ ናቸዉ።

* አዲስ አባባ ከተማ እንጂ ክልል አይደለችም።

* አዲስ አበባ በኦሮሚያ መሀል የምትገኝ፣ የኦሮሚያ ግዛት ናት።

* አዲስ አበባ የኦሮሚያ ግዛት በመሆኗ፣ የኢትዮጵያ ግዛት ሙሉ ይሆናል።

* የብሔር፣ ብሔረሰብና ህዝብ ስያሜ፣ እዉቅና እና ሉዓላዊነት በሃገር ደረጃ ነዉ፤ ዝቅ ካለም በክልል ደረጃ ነዉ።

* የአዲስ አበባ የብሔር፣ ብሔረሰብና ህዝብ ከተማነት የህግ መሰረት የሌለዉ አባባል ነዉ።

* የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ወደ ብሔር፣ ብሔረሰብና ህዝብ ሉዓላዊነት ለመድረስ በኦሮሚያ ክልል መታቀፍ አለባቸዉ።

*********

Guest Author

more recommended stories