ጠላት አንገቱን ሲደፋ ቀና ስለሚልበት ቀን እያሰበ ይሆናል

(ተምሳሌት ከፊንፊኔ)

በፖለቲካ ዓለም ዘለዓለማዊ ጠላትነትም ሆነ የማያበቃ ወዳጅነት የለም፡፡ ተለዋዋጭ በሆነው ዓለም ውስጥ በየእለቱ የሚከሰተው ፈጣን ለውጥ የፖለቲካ አጀንዳዎችን ከሁኔታዎች ጋር ለማጣጣም እንዲቻል አዳዲስ አስተሳሰቦችን በተቻለ ፍጥነት ማፍለቅን፤ እልፍ ሲልም እነዚህን አስተሳሰቦች ማስረጽን ማእከል ባደረገ ተግባር መጠመድን ማስከተሉ አይቀሬ ይሆናል፡፡ ፖለቲካዊ አመለካከቶቹ የሚቀረጹለት ህዝብ ደግሞ አስተሳሰቦቹ ጋር ለመተዋወቅ ያለው ፍጥነትና የአቀባበል ደረጃው እንደየ ንቃተ ህሊናው የሚለያይበት ነባራዊ ሀቅ ይኖራል፡፡

በዚህ መካከል በየአጀንዳዎቹ ላይ የሚኖረው የድጋፍም ሆነ የተቃውሞ እንስቃሴ በቡድን መከፈሉም ሆነ በየቡድኖቹ መካከል መግባባትም አለመግባባትም ማስከተሉ አይቀርም፡፡ በአንድ ወቅት የሚያቃቅር አጀንዳ ሲፈጠር በሌላ ጊዜ ደግሞ እልል በቅምጤ የሚያሰኝና ህዝብን በደስታ ማእበል ከዳር እዳር የሚያስነሳ አስተሳሰብ ሊፈልቅ ይችላል። /የማስተር ፕላኑንና ኢኮኖሚ አብዮቱን አጀንዳዎች ልብ ይሏል/።

ስለዚህ ጠላት ወይም ወዳጅ ሲባል በአብዛኛው በፖለቲካ መድረክ የታክቲክ መድረክ እንጂ የስትራቴጂ ባለመሆኑ የፖለቲካ ንደፈ ሀሳቦች ረጅም ጊዜ ገዢ ሆነው እንዲቀጥሉ የሚያበቃቸውን አቅም እንዲፈጥሩ ያስችላቸዋል፡፡ ስለዚህም በፖለቲካው ምህዳር ምንም እንኳን ፈጽሞ ሊታረቁ የማይችሉና በሁለቱም ወገኖች እውቅና የተሰጣቸው አስተሳሰቦች ያሉ ቢሆንም በአብዛኛው ጠላትና ወዳጅ ተብሎ ሲገለጥ ቋሚነት የሌለው ክስተት መሆኑን ልብ ማለት ለተነሳሁበት ጉዳይ አይነተኛ መገለጫ ይሆናል፡፡

የኦሮሞ ህዝብ በተፈጠረባትና ብዝሃነቷን እንደውበት ቆጥራ አንድም ብዙም መልክና ህብር ያላት ሆና እንድትቆይ በደሙ ማህተም ለማነፅ ቁርጠኛ ተጋድሎ ያደረገባት ሀገር፤ ነገስታቱ በቁም ግዞት የጭቆና ቀንበር ጭነውበት ፍዳ ሲያስቆጥሩት ከሌሎች ወንድም ህዝቦቹ ጋር ፍቅሩን በመጋራት የኖረ የመቻቻል የዴሞክራሲያዊ ባህል ባለቤትና የእኩልነት ተመሳሌት ህዝብ ለመሆኑ የሚመሰክሩ የታሪክ እውነቶች አልጠፉም፡፡

አዲሲቷን ሀገር በመመስረት ዋዜማ በአብዮታዊ ልማታዊ ዴሞክራሲ ቅኝት ጠላትም ወዳጅም አቃቂር ሊያወጡለት የሚቸግራቸውን የህገመንግስት ዋስትና ሰነድ ለመቅረጽ በተደረገ ተጋድሎ ግንባር ቀደም ሚና የተጫወተ የክፍለ ዘመኑም ስመ ጥር ህዝብ ነው፡፡ ይህ ሙገሳ የብቻውም እንዳልሆነ ልብ ሊባል ይገባል፡፡ የወንድም ህዝቦችን ትግል ከራሱ የጭቆና እምቢተኛ መስዋእትነት ጋር በመደመር የጋራ ፈርጣማ ክንድ ሆኖ እብሪተኞችን እንዲያስከነዳ፤ ሀገርን ከመበተን ስጋት እንዲያድንና የመጨራረስ ትንቢት ነጋሪ ተንታኞችን እፍረት ያከናነበ ታሪክ የፃፈ ህዝብም ነው፡፡

ታዲያ በነዚህ የድል ቀናት ሳይቀር የጠሉት የጠላትነት አታሞ የደለቁበትና ከነበረበት ዓለም በፍጥነት ወጥቶ አዲሱን ዓለም እንዳይቀላቀል፤ የብሔሩን ነገ በሰለጠነ ቅኝት መርቶ በፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓቱ ማእቀፍ ጥቅሞቹን ሁሉ አሟጦ ለንቃት እንዳይበቃ ታክቲካዊ ሴራ ሲሸርቡ የነበሩና ዛሬም ያሉትን ቤት ይቁጠራቸው፡፡ ታዲያ እነዚህ አካላት ሲላቸው የዚህ ለዘመናት ተገፍቶ የኖረ ህዝብ መብቶች መከበር እንዳስደሰታቸው፤ ሲመጣባቸው ደግሞ አቅሞቹን አስተባብሮ ለለውጥ መነሳሳቱ ወዴት ወዴት የሚል ጥርጣሬ ፈጥሮ በሌለ ነገር እንዲበረግጉ እያደረጋቸው ህዝቡን ግራ እንዲያጋቡት ሲያደርጋቸው ታዝበናል እየታዘብንም ነው፡፡

ከላይ በርእሴ እንዳልኩት ጠላት አንገቱን ሲደፋ ቀና የሚልበትን ቀን እያሰበ ነው፡፡ እንዳልኩት የህዝብ ወዳጅ እንጂ ጠላት የለም፡፡ አይኖርምም፡፡ ከህዝብ የወጡ የፖለቲካ አቀንቃኞች ግን ሲሻቸው ወዲህ ሲላቸው ወዲያ በመሆን ስሙን ይለብሱታል፡፡ የነሱ ሳያንስም አብዛኛውን ህዝብ በዙሪያቸው የማሰለፍ አቅም የሚያጎናጽፍ አጀንዳ ያገኙ ለታ እነሱን አያድርገኝ፡፡ ደግሞም ለነሱ እርስ በርሱ የሚጠራጠር ህዝብ እንዲኖር ማድረግ ዋና ስራቸው ነው፡፡ አለዚያማ ገበያው እንዴት ሊደራ፡፡

ለዚህ ማሳያ እንግዲህ ህዝባችን የመልካም አስተዳደር፤ በተለይም የአገልግሎትና የመሰረተ ልማት ጥያቄዬ መልስ ማግኘት ይቅርና ጥቅሞቼን እንዳላይ ዓይኖቼን ከልለሀል ብሎ በራሱ ድምጽ ከራሱ ቀዬ የመረጠውን አመራር የተነሳበት ጊዜ የሆነውን የቅርብ ጊዜ ትዝታ ማስታወስ በራሱ በቂ ነው፡፡ ያለመተማመንና ያለመደማማጥ አባዜ ተጠናውቶን ከህገ መንግስቱ ጀምሮ የሚቆጠሩ አእላፍ ለውጦችን ያስመዘገበን ስርዓት መጠራጠር አልፎ ያገኘናቸውን ድሎች በአንዲት ጀንበር እስከ መናድ፤ በዚህም ሳቢያ ክቡር ህይወት የሚቀጠፍበትን ሁኔታ እንዲፈጠር የሆነበትን ሁኔታ ማስታወስ በራሱ በቂ ይመስለኛል፡፡

በርግጥ ለዚህ ጥፋት የአንበሳውን ድርሻ የሚወስደው ህዝባዊነት ተላብሻለሁ ብሎ በሃሳብ ሲምል በግብር ራስወዳድነት ያቀሰሰው የየደረጃው አመራራችን ነው፡፡ ወዲህ መለስ ደግሞ በጥልቅ ተሃድሶ ራሱ ላይ በቂ እርምጃ ወስዶ በወራት እድሜ ለውጦችን ማስመዝገብ ሲጀምር ዛሬ ለድጋፍ የሚተም ህዝብ በዓይናችን ብሌን ማየት የጀምርንበትን አግራሞትም የፈጠረው ከዚሁ ስርዓት አብራክ የወጣ አመራር ነው፡፡ ዋናው ችግር ዋና ችግርን በጋራ ተረድቶ እሱላይ ለመዝመት የጋራ ወኔ የማጣት፤ ያንን ወኔ የመፍጠር አቅም ያለመታጠቅ፤ የርዕዮቱን ዋና ማቀንቀኛዎች ከነመገለጫቸውና በተግባር ሲገለጹ ስለሚፈጥሩት ደስታ፤ ትንግርትና ግርታ በአግባቡ ያለመረዳት፤ ብሎም እየተረዱ ያለመረዳት ችግር ይመስለኛል፡፡

እኛ አንድ ሆነን ችግሮቻችን ላይ ስንዘምት ጠላታችን አንገቱን ይደፋል ሲሉ የክልሉ ፕሬዝዳንት ለማ መገርሳ የገለፁትም ለዚህ ይመስለኛል፡፡ ለፍትህ፤ እኩልነትና አስተማማኝ አብሮነት አብሮ በሚተጋ ህዝብ ወስጥና ዙሪያ የበግ ለምድ ለብሶ የሚያደባ፤ የህዝብን ጥቅሞች በአድር ባይነት ለማይገባው ህገውጥ ነጋዴ ሚያስረክብ፤ ታግሎ ማታገል አቅቶት የናቴ መቀነት አደናቀፈኝ ሰበበኛ፤ የህዝብን እጣ ፈንታ የመኮርኮምና የመደቆስ ዘላለማዊ ስጦታ አድርጎ በጠባሳ የሚያላዝን ትውልድ ለመፍጠር የሚታትርና እከሌ ላቡ እስኪንቆረቆር ለህዝብ ጥቅም የሚቆመው አንተን ሊደፍቅ ነው ሲል ለሚተነብይ፤ በዴሞክራሲያዊና ልማታዊ መስመር ጉዞ ውስጥ የሚጥምን ከማይጥም ለይቶ ለሚሰነዝር ቅጽል ስም ሲያወጣ የሚውልን ጠላት ቢሉት ትክክል ነኝ ባይ ነኝ፡፡ ደግሞ በሌላ ገጽ ሁለንተናችንን ለህዝብ ጥቅም ሰጥተን፤ ህዝቦች በጋራና በፍትሀዊ እኩልነት የሚመሰርቷት ሀገር ውስጥ በምንከፍለው ህዝባዊ መስዋእትነት እንኖራለን ሲባል በጋለ ግለኝነት ነገር ሲጠመዝዝ የሚውልን፤ አልፎም እኔ የምኖረው ለኔ እንጂ ለኛ አይደለምና ከኔ ወዲያ ላሳር የሚልንም ከዚህ ወገን መፈረጁ ምንም ክፋት የለው፡፡ ታዲያ ነገሩ ነባራዊ ሀቅ ሆኖ ይኸው ጠላት አንገቱን ሲደፋ መልሶ ቀና የሚልበትን ቀን እያሰበ ነውና አያያዝን ማሳመር ይጠይቃል ስል አሰብኩ፡፡

ምነው ቢሉ የሀገሬ ህዝብ አንገቱን መስበር ሰልችቶታል፡፡ ሁልጊዜ ጠባሳውን እያከከ የሚብሰከሰክም ሳይሆን አዲስ የታሪክ ምእራፍ የሚዘረጋበት እድሎቹን ህገ መንግስቱ እንብርት ውስጥ ቀድሞ አስቀምጧቸዋልና እነሱን እድሎች አሟጦ መጠቀምን የሚሻ፤ እኩልነቱንና እኩል ተጠቃሚነቱን የሚያረጋግጥለትን ስርዓት ዘብ ሆኖ መጠበቅን፤ ሰንካላ አስተሳሰቦችንና ጥቅሞቹን ለማስቀረት የሚሰነዘሩ የጠላትነት ድርጊቶች በብቃት መመከትንና ፍትሃዊ የአብሮ መኖር መርህን በብቃት ለመተግበር የሚፈልግ ህዝብ ነው፡፡

የክልሉ መንግስትና መሪ ድርጅቱ ዋና ዓላማም ይሄው መሆኑን ባረጋገጠበት ሁኔታ ከጎኑ ተሰልፎ አጋርህም አጋዥህም አቅምህም ነኝ ሊለው ቅንጣት የሚያወላውልም አይደለም፡፡  ይህ ሁኔታ ደግሞ ጠላታዊ አስተሳሰቦች አንገታቸውን እንዲደፉ ያስቻለ ሁኔታን ይፈጥራል፡፡ ታዲያ መንግስትም መሪ ድርጅቱም ሆኑ ህዝብም በትኩረት ማሰብ ያለባቸው እንዚህ አንገት የደፉ ታክቲካዊ ጠላቶች ቀና የሚሉበትን የናንተን መዘናጋት ቀን እየጠበቁ እንደሆኑ ለአፍታም መርሳት የለባችሁም ስል ሀሳብ ላነሳ ፈለግሁ፡፡

ሰትዘናጉ አሊያም አመጣን በምትሉት ውጤት ተኩራርታችሁ ለማረፍ ስትሹ የሀሳብ መንበሩን ከዓይን ጥቅሻ በፈጠነ ሁኔታ የሚቆናጠጡ መሆናቸውን ላለመዘንጋት ዋስትና ሊኖራችሁ ይገባል፡፡ በተለይ ጥልቅ ተሃድሶው ከመድረክ ባለፈ በልባችሁ ያልዞረ አመራሮችና ሞያተኞች ቆም ብላችሁ አስቡ፡፡ አሁን በተለይ በክልላችን በኦሮሚያ የተጀመረው ለውጥ ለዚህ ሀገር ተስፋ ጅምሩም ጭርሱም ይመስለኛልና ልብን አንድ አድርጎ ወደፊት መቀጠል ያሻል፡፡ ክቡር ፕሬዝዳንት ለማ እንደሚሉት ወደኋላ የምንመለስበት ድልድይ ተሰብሯልና፡፡

********

Guest Author

more recommended stories