ከተስፋዉ በተቃራኒ ሰኬት እየናፈቀዉ የቀጠለዉ የቤቶች ግንባታ ፕሮግራም

(ኖህ ሙሴ)

ባሳለፍናቸዉ አስራ ሁለት ዓመታት ስለኮንዶሚንየም ግንባታ ፕሮግራም ብዙ ከመባሉ የተነሳ ቃሉ ከህፃን እሰከ አዋቂዉ ከምሁሩ እሰከልተማረዉ ድረስ ከንግግሩ ያልተለየ ከሃሳቡ ጋር የተዋሃደ ሆኖ ቆይተዋል፡፡ ሆኖም ሲነገርም ሆነ ሲታሰብ ከአንድ አቅጣጫ ብቻ አይደለም፡፡ ከጥሩም ከመጥፎዉም ጎኑ እንጂ፡፡

እሰቲ የፕሮግራሙ መልካምና መጥፎ ገፅታ አይተን የትኛዉ ገፅተዉ እንደሚያመዝንና በሂደትም ሊገጥመዉ የሚችለዉን አደጋ እንይና ከርእሱ ጋር እያስተያየን የራሳችን ድምዳሜ ላይ እንድረስ::

ለመመዘን እንድያመቸን ደግሞ ይህ የኮንዶሚንየም ፕሮግራም ሲነደፍ አሳካዋለሁ ብሎት ከነበረዉ ዓላማዎች እንፃር እያየን ቢሆን የተሸለ ሰለሚሆን በቅድምያ ዋና ዋና ዓላማዎቹ ምን ነበሩ በሚል ቢሆን ይመረጣል::

Photo - Government built condominium building, Addis Ababa
Photo – Government built condominium building, Addis Ababa

ዋና ዋና ዓላማዎቹ በአጭሩ፡

1ኛ. በአገሪቱ ከግዜ ወደ ግዜ አየከፋ የመጣዉን የመኖርያ ቤት እጥረት ለማቃለል፡

2ኛ. በአገሪቱ ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል እዉን ማደረግ፡፡ ይህ ማለት ለዜጎች በድጎማ መልክ በሚበጀት በጀት በአንሰተኛ ወጪ የቤት ባለቤት በማድረግ ከአገሪቱ ኃብት በራሳቸዉ መንገድ በቀጥታ መጠቀም ያልቻሉትን በተዘዋወሪ ተጠቃሚ ማድረግ፡

3ኛ. በዚህ የኮንዶሚንየም ፕሮግራም መሰረት ብዙ ዜጎችን በተለይም ወጣቶችን የሰራ እድል እንድያገኙ በማድረግ ተጠቃሚነታቸዉን ማሳደግ፤-

4ኛ. በግንባታዉ መሰክ በቂ ባለሙያዎች እንዲፈጠሩ በማድረግ በቀጣይ ራሳቸዉን ወደተሻለ ደረጃ በማሰደግ ብቁ ኮንተራክተሮችን በመፍጠር አገራዊ አቅም ማጎልበት፡-

5ኛ. ከላይ በተዘረዘሩት መንገዶች ማህበራዊ ፍትህን በማስፈን የአገሪቱ ሰላም፡ ልማትና እድገት ዘላቂነት እንዲኖረዉ ማስቻል ናቸዉ፡፡

ከነዚህ ዓላማዎች በተሻለ መንገድ የተሳኩት የትኞቹ ናቸዉ፡

ከላይ በተራ ቁጥር 3 የተገለፀዉ ተሳካ ከሚባሉት የሚመደብ ነዉ፡፡ በዚህ የኮንዶሚንየም ፕሮግራም አማካኝነት ሰፊ የስራ እድል እንዲፈጠር ማድረግና በዚህም ብዙ ዜጎች የእለት እንጀራቸዉን እንዲያገኙ ያስቻለና የተወሰነም ቢሆን ጥሪት እንዲsጥሩ በማድረግ ስኬታማ ሆኗል፡፡

በትንሹ የተሳኩትስ የትኞቹ ናቸዉ፡-

1ኛ. በተራ.ቁ 4 የተጠቀሰዉ ያን ያሀል የሚያስመካ ባይሆንም በግንባታዉ ዘርፍ የነበረዉ የአቅም ዉስንነት በትንሹ የቀረፈና ከነችግሩም ቢሆን ቤቶችን መገንባት የሚችል የሰዉ አቅም በብዛት መፍጠር በማስቻሉ በትንሹ የተሳካ ነዉ ማለት ይቻላል፡፡

ያልታሰኩት ዓላማዎችስ የትኞቹ ናቸዉ፡-

1ኛ.በተ.ቁ 1 ላይ የተጠቀሰዉና መሰረታዊ የኮንዶሚንየም ፕሮግራም ዓላማ የነበረዉ የመኖርያ ቤት እጥረትን የመቅረፍ ዓላማ ካልተሳኩት ዉስጥ ይመደባል፡፡ ይህን ስል ብዙ ሰዉ ግራ ሊያጋባ ይችል ይሆናል፡፡

ምክንያቱም ያ ሁሉ በአስር ሺ የሚገመቱ ቤቶች ተገንብተዉና ተላላፈዉ እንዴት አልተሳካም ይባላል የሚል ሰዉ መኖሩ የሚጠበቅ ነዉ፡፡ እኔም ይህን እዉነታ ለማካድ ፈልጌ ሳይሆን ተጨባጭ አዉነታዉ ነዉ ይህ እንድል ያሰገደደኝ፡፡

ይህ የምልበትም ዋነኛ ምክንያቴም የቤት ችግር ሲብሰበት እንጂ ሲቀንስ ባለማየቴ— የቤት ኪራይ ዋጋ ከጥዋት ወደ ማታ ሲጨመር እንጂ ባለበት እን£ን ለትንሽ ግዜም መቆየት ሲሳነዉ በመታዘቤ — አብዛኞቹ ቤቶቹ ቤት በቸገራቸዉ ሰዎች እጅ ሳይሆኑ ከቤትም ቤቶች ያላቸዉና በአዳዲስ የቤት ባለባቶች እጅ መገኘታቸዉ ግር ሲለኝ ግዜ —ቤት ፈላጊዎቹ የቤት ባለቤቶች ያለመሆናቸዉ ብቻ ሳይሆን አቅማቸዉ የሚመጥን የኪራይ ቤት በነዚህ ኮንዶሚንዮሞች ያለማግኝተቻዉ ሳይ፤ አንደንዶቹ ቤቶቹ ሆን ተብሎ ሳይተላለፉ በሰበብ አሰባቡ በማሰቀረት ባለቤት አጥተዉ ደላላዎችና ጥበቃዎች ሰብረዉ በመዉሰድ ማከራየታቸዉ ስሰማ ወዘተ ነዉ፡፡

ስለዚህም ዋናዉ ዓለማ አልተሳካም ብቻ ሳይሆን ወድቀዋል ማለቱ ቀለለኝ፡፡ በእርግጥ የተጠቀሙ ሰዎች የሉም ብዬ ለመካድ አይዳዳኝም፡፡ ሆኖም ያንድ ነገር ሰኬት የሚለካዉ በአመዛኙ የታሰበለተን ግብ ሲያሳካ እንጂ እዚህም እዝያም በታዩ አነስተኛ ሲኬት ስላልሆነ፡፡ እናንተሰ ምን ትላላቹሁ?

2ኛ. በተራ ቁ. 2 የተጠቀሰዉ መንግስት በዜጎች መካከል ፍትሃዊ የኃብት ክፍፍል እንዲኖር ብሎ በድጎማ መልክ ይህን ያሀል ቤት ቢገነባም ልክ እንደቤት ችግር ማቃለሉ ላይ እዚህም ያለተሳካለት መሆኑን ነዉ ያየሁት፡፡ ምክንያቱም ቤቱ ለተገቢዉ ቤት ፈላጊ ካልደረሰ ድጎማዉ ለእርሱ የሚደርስበት እድል ሊኖር አይችልም፡፡

በተቃራኒዉ ከዜጎች በግብር መልክ የተሰበሰበዉ ገንዘብ የከተማዉ አስተዳደር 30 በመቶ ቅድሚያ ለሴቶች በሚል ፈሊጥና ምንም ትርጉሙ ባለተዘረዘረ መንገድ ያወጣዉን የመመርያ ክፍተት ተጠቅመዉ ከገጠር ምንም ፍላጎት ሳይኖራቸዉና ለምን እንደመጡ በማያወቁና በኃላም በየቀበሌዉ በጉቦም ይሁን በማታለል ነዋሪ ናቸዉ ተብለዉ መታወቅያ በወጣላቸዉና ትንሽ መደለያ እየተሰጡ በሚሸኙት ሴቶች ሰም ለሚነግዱት የተወሰኑ ሰግብግብ ነጋዴዎች ይህ ድጎማ በመዋሉና በማይገባቸዉ ሰዎች እጅ መዉደቁን እያየን በመሆኑ ነዉ፡፡ ይህን ለማረጋገጥ የነዚህ ቤቶች (የስም ሳይሆን) እዉነተኛ ባለቤቶችና ከቤቶቹ በኪራይ መልክ በወር አስር ሺዎችን የሚሰበስቡትን ማየቱ በቂ ነዉ፡፡

ሌላዉ ቤቶቹና ድጎማዉን ለትክክለኛዉ ሰዉ የማይደርስበት ምክንያት የቤቶቹ ግንባታ ከሚፈለገዉ በላይ በመዘግየታቸዉ ምክንያትና በግንባታ ወቅት በሚከሰት ብክነትና ምዝበራ ምክንያት በዛ ላይ ከፍተኛ የባንክ የብድር ወለድ ተጨምሮባቸዉ የቤቶቹ ዋጋ እን£ን ድጎማ የተደረገባቸዉ ሊመስሉ ሳይደጎሙም ቢሆን ያን ያሀል ሊደርሱ አይቻላቸዉ በሚባል ዋጋ ስለሚተላለፉና ከእዉነተኛዉ ተጠቃሚ አቅም ጋር የማይቀራረቡ ስለሆነ በማይረባ ትንሽዬ ጥቅም ለነጋዴዎች በብድር ሰም ሰለሚተላለፉ ነዉ፡፡

3ኛ. በተ.ቁ 5 የተጠቀሰዉ ማህበራዊ ፍትህ ማንገስ የተባለዉም ከነዚህ ካልተሳኩት ዉስጥ ነዉ፡፡ በመሰረቱ ማንኛዉም ግዴታዉን እየተወጣ ያለ ዜጋ በእኩል የመታየትና በመንግሰት አገልግሎት እኩል የመጠቀም ህገ-መንግሰታዊ መብት አለዉ፡፡ በማንኛዉም መልክ በዜጎች መካከል ልዮነት የመፍጠር መብት የተሰጠዉ መንግሰትም የለም፡፡

ይሁንና በዚሁ ፕሮግረም ከመነሻዉ ያልነበረና እየቆየ በመጣዉ 30 ከመቶ ቅድምያ ለሴቶች ፤ በኃለ 20 በመቶ ለመንግስት ሰራተኛ አሁን ደግሞ 5 በመቶ ለአካል ጉዳተኞች (በመሰረቱ ምዝገባዉ ላይ ስለአካል ጉዳተኝነት የተጠቀሰ ነገር የለም) በሚሉ ሰበቦች በዜጎች መካከል ልዮነት የፈጠሩና አንዳችም የህግ መሰረት የሌላቸዉና ማህበራዊ ፍትህን በማረጋገጥ ረገድ ምንም ገንቢ ተራ የሌላቸዉና አንዳንዴም ተራ የፖለቲካ ድጋፍ ከማግኘት የሚመደቡ በሌላ አገላለፅ (ፖለቲካዊ ሙስና) በሚሰኙ ምክንያቶች የተነሳ ዜጎች በእኩልነት በመብታቸዉ የመጠቀም እድሉ የነፈገ በመሆኑ ነዉ፡፡

የሚገርመዉ ነገር በአንድ ወቅትም አትሌቶች ድል ተቀደጁ ተብለዉ ኮንዶምንየም በሽልማት ዉሰዱ መባላቸዉ ስንሰማ ለመሆኑ ዋናዉ ዓላማ ወደ ጎን እየተወረወረ ማንም ባለስልጣን በስሜት ተነሳስቶ ብቻ ቤቶችን የማደል መብት አለዉ እንዴ አሰኝቶን ነበር፡፡

ለመሆኑ ነፃ ገበያ እከተላለሁ በሚል መንግሰት ይቅርና በሌላ ስርዓትም ቢሆን የግልና የመንግስት ሰራተኛ እያለ በዜጎች መካከል ልዮነት መፍጠርስ ይቻላል ወይ? እንዲህ ከሆነ ደግሞ የግሉ ሰራተኛዉ ግብር የመክፈል ግዴታም የለበትም ማለት ነዉ? ለዚህ ሁሉ ተገቢዉን ምላሽ መሰጠት ከመንግስት ይጠበቅ ነበር፡፡ ግን ይህ ሲሆን አልታየም እንድያዉም ሌላ እየተጨመረበት ሄደ እንጂ፡፡

ሌላዉ ዛሬ የመንግሰት ሰራተኛ ስለሆነ ብቻ ቤት ያገኘዉስ የመንግስት ስራዉን ሲለቅ ቤቱን መልሰህ አስረክብ ሊባል ነዉ? ጨርሶ ግራ የሚያጋባ ነገር ሆኖብኛል፡፡ አካሄዱ እንዲህ ከሆነስ የግል ሰራተኛዉ የመንግሰት ሰራተኛዉን የሚደጉምበት ምድራዊ ምክንያት እንዴት ሊኖር ይችላል?

ሌላዉ የማይገባኝ ጉዳይ ቅድምያ ለሴቶች ሲባልስ የትኛቹ ሴቶች ማለቱ ነዉ? ላላገቡት— ለፈቱት ወይስ ለባለትዳሮች ምንም የተብራራ ነገር የለዉም፡፡ እንድያዉ ሾላ በድፍኑ ነዉ፡፡ ይህ ግን በኃላ ከተከሰተዉ ሴቶችን በስፋት እያመጡ ከማስመዝገቡ ጋር ስናያይዘዉ በደንብ ታስቦበት የተፈጠረ ክፍተት መሆኑን መገንዘብ አይቸግርም፡፡ ምክንያቱም ከህ/ሰብ ዉጭ የሆነች ሴት በበኩሌ አላዉቅም፡፡

እርግጥ ነዉ ባሎቻቸዉ በሞት የተነጠቁ ወይም በፍቺ ተለያይተዉ ብቻቸዉን የቤተሰብ ሃለፊነት ተሸክመዉ የሚኖሩትን የለየ ቢሆን ኑሮ ህጋዊም ባይሆን ፍትሃዊነቱ በማንም ዘንድ አጠያያቂ ባልሆነ ነበር፡፡ ነገር ግን በድፍኑ ለሴቶች ቅድምያ ይሰጥ ማለት ጨርሶ አሳማኝ ሊሆን አይችልም፡፡

በዚህ የተነሳ ቤቶቹ ለተገቢዉ ሰዎች ያለመድረሳቸዉ አይነተኛ ምክንያት ሆነዋል፡፡ይህም ጉዳት እንጂ ጥቅም አላስገኘም፡፡ ይህ በመሆኑም ማህበራዊ ፍትህ በማረጋገጥ ረገድ ፕሮግራሙ በእጀጉ ዋጋ አሳጥቶታል፡፡

ከዚህ ዉጭ ያሉት የፕሮግራሙ እጥረቶችስ ምንድን ናቸዉ?

* መቸስ ማንኛዉም ሰዉ መጠለያ የማግኘት መብት አለዉ፤ ቢያንስ በመርህ ደረጃ፡፡ ሆኖም መጠለያ የማግኘት መብትና የቤት ባለንብረት የመሆን መብት የተለያዩ ናቸዉ፡፡ እን£ን እኛን በመሰለ ድሃ አገር ይቅርና በበለፀጉት አገራትም ይህ የማይታሰብ ነዉ፡፡ ስለዚህ ሁሉም ሰዉ የቤት ባለቤት እናደርጋለን የሚል መነሻ በራሱ እጅግ የተሳሳተ ነዉ፡፡

በመሰረቱ እንኴን አቅም የሌለዉ ይቅርና አቅም ኖሮትም እኮ ቤት መግዛቱ ላያስፈልገዉ ይችላል፡፡ ምክንያቱም ተማጣጣኝ የቤት ኪራይ እካገኘ ድርስ ገንዘቡን ለስራና ለተሻለ ኢንቨስትመንት ቢያዉለዉ ሰለሚሻል ነዉ፡፡ ለዚህ በቂ ማሳያ የሚሆነን በደርግ ግዜ በመንግሰት በሚተዳደሩት የኪራይ ቤቶች የተከራዩ ሰዎች አቅሙና እደሉ እያላቸዉ ቤት መስራትን በቅድምያነት አላዩትም ነበር፡፡

ምክንያቱም ዞሮ ዞሮ ቤት የሚያስፈልገዉ ተረጋግቶ ለመኖር ተብሎ ነዉ የሚሰራዉ፡፡ ስለዚህም ተረጋግቶ የሚኖርበት የኪራይ ቤት የሚያገኝ ሰዉ ሚልዮኖች እያወጣ ቤት ሰርቶ ለንግድ ስራ ማሰኬጃ የሚሆን ገንዘብ በማጣት የባንክን ብድር ፍለጋ ግቦ እሰከመሰጠትም አይደርስም ነበር፡፡ ሰለዚህ ቤት መስራት እንደብቸኛ የመኖርያ አማራጭ ተደረጎ መወሰዱም ትክክል አይሆንም፡፡ በኢኮኖሚያዊ ምክንያት ጭምር፡፡

* በኔ እምነት ሌላዉ መንግሰት የሰራዉ ስህተት ሁሉም ሰዉ እንደየአቅሙ ተከራይቶም ቢሆን የሚኖርበትን መንግድ ከማመቻቸት ይልቅ ሁሉም ሰዉ የቤት ባለንብረት ማደረግ ብቻ በመፈለግ ይህንን በማደረግና ለኪራይ የሚሆኑ ቤቶችን ገንብቶ በተመጣጣኝ የማከራየት ልምዱና አቅሙ የነበረዉን በቀድሞ ስሙ ኪራይ ቤቶች የአሁኑ የመንግሰት ቤቶች ኤጄንሲ ያለስራ እንዲቀመጥ በማድረግ ይህንን አማራጭ ፍፁም ዝግ ማደረጉ ላይ ነዉ፡፡

* ሌላዉ የዚህ ፕሮግራም እጥረት ቤቶቹ በተለያየ ሳይትና በብዛት የሚገነቡ በመሆናቸዉ ለቁጥጥሩ በቂ የሰዉ ኃይል ሳያዘጋጅ የጀመረዉ በመሆኑና በሙያዉ ከተሰማሩት ባለሙያዎችም ቀላል የማይባሉት ከኮንትራክተሮቹ ጋር በበመሳጠር ደረጃዉን ያልጠበቀ ግንባታ እየተካሄደም ያለአንዳች ተቆርuሪነትና በግድየለሽነት አንዳንዴም በጥቅም ትስስር ሆን በለዉ በማለፍ በተጠቃሚዉ ላይና በአገር ላይ ከፍተኛ ጉዳት ከማድረሳቸዉም በተጨማሪ ራሳቸዉም ለዚሁ ህገወጥ ስራ ተገላጭ በመሆን ገሚሶች ባደረሱት ጥፋት ሌሎችም በየዋህነት በመፈረማቸዉ ብቻ በህግ ቁጥጥር ሲወድቁ ቤተሰቦቻቸዉን ለከፍተኛ ችግር በማጋለጣቸዉ ምክንያት አጠቃላይ ማህበራዊ ቀዉስ ያባባስ ሆነዋል፡፡ ይህም ፕሮግራሙ በከፍተኛ ደረጃ ለሙስናና ለብክነት በመጋለጡ በስኬቱ ላይ መጥፎ ገፅታ ሊጥል ችለዋል፡፡

* ሌላዉ ችግር የቤቱ ክፍያ እየናረ መሄድና የባንክ ወለዱ ከፍተኛ መሆን ታክሎበት ኣብዛኛዉ ሰዉ መክፈል እያቃተዉ እንዳንዱም ወለዱ ብቻ እየከፈል ዋናዉን የሚከፍልበት መንገድ እየጨነቀዉ ምነዉ በቀረብኝ ወደሚልበት ደረጃ ወድቆ ያዉ እሱም ወደ መሸጡ በመሄድ አዳዳስ የቤት ባለባቶች በማበራከት ላይ ይገኛል፡፡

ስለዚህ ከግዜ ወደ ግዜ ፕሮግራሙ የታለመትን ዓላማ ሳያሳካ በመቅረት ላይ ይገኛል፡፡ ከዚህም ሌላ የቤቱ ዕጣ ከወጣበት ግዜ እሰከሚተላለፍበት ያለዉ ግዜ በጣም እየረዘመ በአንድ በኩል በባንክ ወለድ በሌላ በኩል በኪራይ የነበረዉን ገንዘብ ጨረሶ እዳዉን መክፈል እንዳይችል የሆነዉ ቁጥሩ ቀላል አይደለም፡፡ ይህም ሌላዉ የፕሮግራሙ ድክምት ሆኖ ተመዝግበዋል፡፡

* ከዚህ ሌላ በብቸኝነት የቤቱን ብድር በማመቻቸት ረገድ እንዲያስተናግድ የተፈረደለት ወይም የተፈረደበት ንግድ ባንክ በማይከፈል የብድር እዳ ክምችት ከግዜ ወደግዜ እየተቸገረ በኃላ ወይ የህዝብ ገንዘብ ባክኖ ባንኩን ለኪሳራ ይዳርገዋል አለያም ባንኩ ዋናዉ ስራ ትቶ የኪራይ ቤቶች (መንግሰት ቤቶች ኤጄንሲ) የስራ ድርሻ ወስዶ አከራይ ይሆናል አለያም ቤቶችን በሃራጅ ለባለሃብቶች ይሸጣል ማለት ነዉ፡፡

መቼስ ለመስርያዉ በብልዩን የሚቆጠር በድጎማ መልክ ገንዘብ አዉጥቻለሁ ያለ መንግሰት እንደገና የሰዉ እዳ ይሸፍናል ብሎ አይጠበቅም፡፡ ሊሽፍን ቢጀምር ደገሞ ሁሉም እኔስ ባልከፈል ምን እንዳይመጣበኝ ያዉ መንግሰት ይከፈልልኛል እያለ መክፈል የሚችለዉም እየተወዉ ይሄድና መንግሰት በማይወጣበት እዳ ዉስጥ ይዘፈቃል ማለት ነዉ፡፡ በዚህም ተባለ በዚያ ያዉ ከችግር ዉጭ የሚሆንበት አማራጭ የለም ማለት ነዉ፡፡ ይህም ሌላዉ የፕሮግራሙ ዉድቀት እንዳይሆን በእጅጉ ያሰጋል፡፡

* በመሰረቱ ለአንድ ሰዉ መኖርያ ቤት ማለት የሚተኛበትን ክፍል ማግኘት ብቻ ሳይሆን ለመኖር የሚያስችል አመቺ አካባቢ መኖርም ጭምር ስለሆነ በዚህ ረገድ የፕሮግራሙ ሌላዉ ችግር በአንድ ብሎክ እጣ የሚወጣላቸዉ ሰዎች ፈፅሞ የማይተዋወቁና ማህበራዊ ስብጥራቸዉም በእጀጉ የማይቀራረብ በመሆኑ በኑሯቸዉ ላይ ከፍተኛ ተፅእኖ አየፈጠረ መሆኑ ነዉ፡፡

በዚሁ በጣም የተራራቀ ፍላጎትና ማህበራዊ መሰረት ላይ ለጭቅጭቅ የሚጋብዙ በግንባታ ወቅት ከጥራት መÕደልና ከፍሳሽና መሰል ችግሮች በተያያዘ ያሉ ችግሮች ታክሎዉበት በመካከላቸዉ ከፍተኛ ያለመግባባት እየተፈጠረ የዚህ እድል ተጠቃሚ የሆኑት እዉነታኛ ቤት ፈላጊዎች ኑሮን በእጅጉ አሰቀያሚ እያደረገባቸዉ መሆኑንና ብዙም ሳይቆዩ ቤት በማግኘታቸዉ ያገኙት ደስታ በሚገባ ሳያጣጥሙ ወደ ምሬት እንዲቀይሩት ማድረጉ ነዉ፡፡

* በተጨማሪም ለተላያዩ ችግሮች መፍትሄ እንዲሰጡና ነዋሪዉን እንዲያስተባብሩተብለዉ በሚuuሙት ኮሚቴዎች ላይ ምርጫ ሲካሄድ የኃላ ታሪካቸዉ ካለመተዋወቃቸዉ የተነሳ ይህንን ክፍተት ተጠቅመዉ ፈጥነዉ በኩሜቴ ዉስጥ እየገቡ ኮሚቴዉን ለግል ጥቅም ማካበቻ የሚያደርጉ — የነዋረዉን የጋራ መጠቀምያ ቦታ እንደግል ንብረታቸዉ በህገ-ወጥ መንገድ በማከራየት የሚዘርፉ ይህንን በታቃወመ ነዋሪዎች ላይ የማስፈራራትና የኃይል እርምጃ እሰከመዉሰድ የሚደርሱ በየቦታዉ መበራከት በፕሮግራሙ ላይ መጥፎ ጥላ እያጠሉ መሆኑ ላይ ነዉ፡፡

* ከዚህ ዉጭ ከስር ያሉት ቤቶች በጨረታ ለንግድ ቤቶች በሽያጭ ሰለሚተላለፉና ከዛ በኃላ ተገቢዉን ቁጥጥር ሰለማይደረግባቸዉ ነዋሪዉን በሚያወኩ የጭፈራና ቡና ቤቶች እየተያዙ በድምፅ ብክለት ነዋሪዉን ክፉኛ በማስመረር አቤት ቢልም ሰሚ እያጣ መኖርያዉን ጥሎ የሚሄድ መብዛቱ ፕሮግራሙ የታለመለት ዓለማ ሳያሰካ እንዲቀር አይነተኛ ምክንያት ሆነዋል፡፡ወዘተ፡፡

ሰለዚህ ምን ቢደረግ ነዉ የሚሻለዉ?

1ኛ. እስከአሁን በተላለፉት ቤቶች የሚኖረዉ ነዋሪ ችግር ባለሙያዎችን በማሰማራት ያሉት የግንባታ ጥራት ያስከተላቸዉ ችግሮችና ቤቶችን በማስተዳደር ያሉ የአሰራር ችግሮች በቅረበት ከነዋሪዉ ጋር በመነጋገርና ለዚሁ የሚሆን በጀት በመመደብ ማስተካከል እንዲሁም የህግ አሰገዳጅነት የሚፈልጉትን ተግባራዊ ማደረግና የነዋሪዉን ምቾት በተቻለ መንገድ ማስጠበቅ፡-

2ኛ. ከህግ ዉጭ የተያዙትና ለሌላ ሶስተኛ ወገን የተላለፉትን በሚገባ በማጣራት ይህን ያደረጉትን አካላት ያለምህረት በህግ ተጠያቂ ማደረግና ለሌላዉ ትምህርት እንዲሆን በሚችል መልኩ በመገናኛ ብዙሃን ለህዝቡ ማሳወቅ፡-

3ኛ. የተለያየ አይነት ቤቶች በመንግሰት ቤቶች ኤጄንሲ አማካኝነት በስፋት ተሰርተዉ በተመጣጣኝ ዋጋና በየግዜዉ በማይቀየር የኪራይ ተመን ተገቢዉን መሰፈርት ተቀምጦለትና በግልፅነት ለሚገባዉ ሰዉ ማከራየት፤-

4ኛ. መንግሰት የሚሰራቸዉ ኮንደሚንዮሞች መቀጠላቸዉ የግድ አሰፈላጊ መስሎ ከታየዉ ደግሞ ተመሳሳይ አቅምና ባህሪ ያላቸዉ ፍላጎታቸዉ የሚጣጠም ሰዎችን በማደራጅትና ቤት አልባ መሆናቸዉ በማጣራት ተገቢዉን የቅድምያ ክፍያ ከፍለዉና አነሰተኛ የባንክ ወለድ ተመቻችቶላቸዉ ከመጀመርያዉ እንደሚከፍሉና ቤቱንም ያለምንም ጥያቄ እንደሚያገኙ አዉቀዉ ቢመዘገቡ፡፡

አለበለዝያ ከ12 ዓመታት በላይ ሲጠብቁ ቆይተዉ ድንገት ቢደርሳቸዉ እንኴ ሲመዘገቡ የነበረበት ሁነታ ተቀይሮ ወይ ጡረታ ወጥተዉ ወይ ካባል ወይ ከሚስት እንዳቸዉ በሞት ተለይተዉ ገብያቸዉ ቀንሶ መክፈል ሳይችሉ ቀርተዉ እድላቸዉን ለሌላ አሳልፈዉ በመሰጠት መንግስትን እንዲያመሰግኑ ሳይሆን እንዲረግሙ ሆነዉ መቅረታቸዉ በምንም መልክ የሚመረጥ አይሆንምና አሰራሩ በደንብ ቢሻሻል፡፡

3ኛ. ማንኛዉም ዜጋ በእኩልነት ማስተናገድ እንጂ ለቁጥጥር በማያመችና በዜጎች መካከል አላስፈላጊ ልዩነት በሚፈጥርና ለማጭበርብርም በሚያመች መንገድ ማስተናገድ ጨርሶ መቅረት አለበት፡፡ ምክንያቱም አንዴ ለተፋናቃዮች ተብሎ ነዉ ሌላ ግዜ ለሴቶች ተብሎ የተቀመጠ ነዉ አሁን አሁን ደግሞ ለመንግሰት ሰራተኛና ለአካል ጉዳተኞች ተብሎ ነዉ እየተባለ ተመዝጋቢዉ እርስ በርሱ ስለማይተዋወቅ ይሆን ይሆናል እየተባለ በኃላ በቅርቡ በማጣራቱ ሂደት ላይ እንደተገኘዉ ለ7 እና ከዛ በላይ ለሆኑ ዓመታት ቤቶች ያለነዋሪ ማስቀረትና በህገ-ወጥ መንገድ እያከራዩ መጠቀምን ያስከትላል፡፡ ይህም የፕሮግራሙ ዉድቀት ያባብሳል፡፡ ሰለዚህም ይህንኑ አሰራር መቀየር፡፡

4ኛ. መንግሰት በራሱ ከሚገነባዉ በላይ አቅም ላላቸዉና የቤት ችግር ላለባቸዉ ሰዎች በቂ የመሬት አቅርቦት በማመቻቸት ላይ ቅድምያ ትኩረት ሊሰጠዉ ይገባል፡፡ ይህን ባለማድረጉ ምክንያት ሁሉም ሰዉ መንግሰት እንዲሰጠዉ ብቻ በመጠበቅ ለዓመታት መጠበቅና አዲሱ ትዉልደም እድሜዉ እየደረሰ እድሜ ልኩ በቤት እጦት ጭንቀት እንዲቀጥል ስለሚያደርገዉ ይህንን አወቆ በዚሁ ላይ መረባረብ፡፡

ከዚህ ዉጭ ሁሉም ሰዉ ያለምርጫ መዝግቦ ከፍተኛ በሚባል የባንክ ወለድ ከባንክ ጋር አስተሳስሮ ቤት ማደል ሸጠዉ ዘወር በል ከማለት ዉጭ ምንም የረባ ትረጉም እንደሌለዉ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ አሁን እየሆነ ያለዉም ይሀዉ ስለሆነ፡፡ አብዛኞቹ ቤቶች ወይ በነጋዴዎች እጅ ገብተዋል ከዛ ባለፈም የአንዳንድ ባለስልጣናት ቅምጦች መቀመጫ ወደ መሆን ተቀይረዋል እየተባለ በህ/ሰቡ ዘንድ ዋነኛ መነጋገርያ ርእስ መሆኑም ልብ ማለት ይገባል፡፡

በዚህም የተነሳም ደህናዉ ነዋሪ መኖር የማይችልበትና ያገኘዉን እድል መጠቀም ወደማይችልበት ደረጃ ወርዶ ቤቱን በኪራይ አለያም በሽያጭ እያስተላለፈ ወደነበረበት የቤት ፍለጋ አዙሪት ገብተዋል፡፡ ሰለዚህ ይህንኑ በጥልቀት በማየት ማሻሻል ከአስተዳደሩ በእጅጉ ይጠበቃል፡፡

ማጠቃለያ

ምን ቢደረግ ይሻላል በሚለዉ ላይ የጠቃቀሰኩዋቸዉ መፍትሄዎችና ሌሎች ያልተጠቀሱት ተጨማመረዉ በግዜዉ የፕሮግራሙ አካሄዶች ካልተስተካከሉ በቀር ያን ያክል ሃብትና አዉቀት  እየፈሰሰበት ያለ እና ለበጎ ዓላማ ተብሎ የተጀመረ ፕሮግራም ከቀን ወደ ቀን ችግሩ ብሶ ራሱ በራሱ ተጠልፎ መዉደቁ ሰለማይቀር ተሎ መፍትሔ ይበጅለት እያልኩኝ ለዛሬዉ በዚሁ አበቃለሁ፡፡

*****

Guest Author

more recommended stories