የኢህአዴግ ተሃድሶና የምርጫ 2012 ሞት-ሽረት

የኢህአዴግ ተሃድሶ መጀመሪያና መጨረሻ በሚለው ፅሁፍ ተሃድሶው ከየት ተነስቶ የት መድረስ እንዳለበት ለመጠቆም ሞክሬያለሁ፡፡ ይህ ፅሁፍ ደግሞ በተሃድሶው መነሻና መድረሻ መሃል ምን መደረግ አለበት በሚለው ዙሪያ ያጠነጥናል፡፡ አሁን ሀገሪቱ ያጋጠማትን የፀጥታና አለመረጋጋት ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ምን ዓይነት ለውጥና መሻሻል ያስፈልጋል? ተሃድሶው እንዴትና እስከ መቼ ተግባራዊ ሊደረግ ይገባል? የሚሉትንና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን በዝርዝር ለማየት እንሞክራለን፡፡

ከልማታዊ መንግስት (developmental state) አቅጣጫ በተጨማሪ፣ እ.አ.አ በ1987 ዓ.ም በደቡብ ኮሪያ ተከስቶ የነበረው ከኢትዮጲያ ጋር ተመሳሳይ የሆነ ሕዝባዊ አመፅና ተቃውሞ፣ እንዲሁም የደቡብ ኮሪያ መንግስት የወሰደው የለውጥ እርምጃን እንደ መነሻ ሊወሰድ የሚችል ነው፡፡ በተጠቀሰው ወቅት በደቡብ ኮሪያ የተደረገው ተሃድሶን አስመልከቶ “Political Liberalization and Economic Development” በሚል ርዕስ የቀረበው አንድ ጥናታዊ ፅሁፍ የሚከተለውን የድምዳሜ ሃሳብ አስቀምጧል፡-

¨…It can be generalized that a bureaucratic authoritarian regime will not be efficient unless it can co-opt societal interests, especially when prolonged economic success nullifies the effectiveness of material gains at the cost of political freedom. …For its own survival the authoritarian regime will need to adjust its political structure in a more inclusive and democratic direction.” Korea Journal of Population and Development, Volume 20, Number l, July 1991

የልማታዊ መንግስት አቅጣጫን በመከተል ፈር-ቀዳጅ የሆነው የደቡብ ኮሪያ መንግስት ከወሰደው የለውጥ እርምጃ መገንዘብ የሚገባን ዋና ነጥብ ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ለዴሞክራሲያዊ መብትና ነፃነት ተለዋጭ ሆኖ ሊቀጥል አለመቻሉን ነው፡፡ “3ኛው ማዕበልና የልማታዊ መንግስት ፈተና” በሚለው ፅሁፌ በዝርዘር ለማሳየት እንደሞከርኩት፣ ሀገራት ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት እያስመዘገቡ በሄዱ ቁጥር በአብዛኛው የሕብረተሰብ ክፍል ዘንድ የእኩልነት፣ ነፃነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጥያቄዎች እያቆጠቆጡ ይመጣልሉ፡ በሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ላይ የተጣሉ ገደቦች ከግዜ ወደ ግዜ ይበልጥ እየተጋለጡ ስለሚሄዱ የሕዝቡ አመፅና ተቃውሞ እየተጋጋለ ይሄዳል፡፡ ከዚህ አንፃር፣ ከፊል ተሃድሶ (partial reform) ለማድረግ መሞከር ችግሩን ይበልጥ ከማባባስ የዘለለ ፋይዳ የለውም፡፡ ስለዚህ፣ እንደ ኢህአዴግ ያሉ ፈላጭ-ቆራጭ መንግስታት ያላቸው ብቸኛ አማራጭ ሙሉ ተሃድሶ (full reform) በማድረግ ስኬታማ የሆነ ተሃድሶ ማድረግ ነው፡፡

ስኬታማ የሆነ የተሃድሶ ፕሮግራም ለማካሄድ በቅድሚያ “በየትኛው ዘርፍ ምን ዓይነት ለውጥና መሻሻል ሊደረግ ይገባል?” ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡ ይህ ደግሞ “ተሃድሶው ለምን አስፈለገ?” ከሚለውን ጥያቄ ይጀምራል፡፡ በእርግጥ የኢህአዴግ መንግስት ተሃድሶ ለማድረግ የተነሳበት ዋና ምክንያት ከቅርብ ግዜ ወዲህ ታይቶ የማይታወቅ የፀጥታና አለመረጋጋት ችግር ስላጋጠመው ነው፡፡ ከፀጥታና አለመረጋጋት ችግሩ በስተጀርባ ያሉት ደግሞ የእኩልነት፣ ነፃነትና ፍትህ ጥያቄዎች ናቸው፡፡

በመሰረቱ ዴሞክራሲ ማለት የብዙሃኑ እኩልነት፣ ነፃነትና ፍትህ የሚረጋገጥበት ፖለቲካዊ ሥርዓት ነው፡፡ ስለዚህ፣ የተሃድሶው ዋና ምክንያት በአብዛኛው የሕብረተሰብ ክፍል ዘንድ እየተነሳ ያለው “የዴሞክራሲ ጥያቄ” ነው፡፡ በመሆኑም፣ በሀገሪቱ እየታየ ያለውን የፀጥታና አለመረጋጋት ችግር በዘላቂነት ለመፍታት በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ረገድ ሥር-ነቀል የሆነ ለውጥና መሻሻል ሊደረግ ይገባል፡፡ ስለዚህ፣ የኢህአዴግ መንግስት ሕልውናውን ለማረጋገጥ የሚያስችል ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት ምን ዓይነት ለውጥና መሻሻል ማድረግ ይጠበቅበታል?

በተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ዘንድ እየተነሱ ያሉትን ጥያቄዎች በጥቅሉ ለሁለት ክፍሎ ማየት ይቻላል፡፡ የመጀመሪያው የዴሞክራሲያዊ መብትና ነፃነት መከበር ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የመልካም አስተዳደር እጦት ነው፡፡ ከዚህ አንፃር፣ የኢህአዴግ መንግስት ከሕዝቡ እየተነሱ ያሉትን የዴሞክራሲ ጥያቄዎች በአግባቡ ለመመለስ የሚያደርገውን የተሃድሶ እንቅስቃሴ ፖለቲካዊ እና አስተዳደራዊ ብሎ ለሁለት መክፈል ይቻላል፡፡

1ኛ፡- ፖለቲካዊ ተሃድሶ (Political reform)

የፖለቲካ ተሃድሶ መሰረታዊ ዓላማው የብዙሃኑ የሕብረተሰብ ክፍል እኩልነት፣ ነፃነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት የተረጋገጠበት ፖለቲካዊ ሥርዓት – ዴሞክራሲ – መገንባት ነው፡፡ ይህ በሕገ-መንግስቱ ዋስትና የተሰጣቸውን የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ያለ ምንም መሸራረፍ ማክበርና ማስከበር ይጠይቃል፡፡ ይህ ደግሞ በተራው በተለያየ ግዜ የወጡና የዜጎችን መብትና ነፃነት የሚገድቡ ፖሊሲዎችን፣ አዋጆችን፣ ደንቦችንና መመሪያዎችን፣ እንዲሁም ከሕገ-መንግስታዊ መርሆች ውጪ የሆኑ ሥራና አሰራሮችን ሙሉ ለሙሉ መቀየር ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ አንፃር፣ የኢህአዴግ መንግስት ስኬታማ የሆነ ፖለቲካዊ ተሃድሶ ለማድረግ እንዲችል ሊያከናውናቸው ከሚገቡ ዋና ዋና ተግባራት ውስጥ የሚከተሉት ይጠቀሳሉ፡-

* የታሰሩ ፖለቲከኞችን፣ ጋዜጠኞችን፣ የመብት ተሟጋቾችን እና ሌሎች የፖለቲካ እስረኞችን ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ መፍታት፣

* የዜጎች ዴሞክራሲያዊ መብቶችን የሚገድበውን የፀረ-ሽብር አዋጁን መሻርና ከሕገ-መንግስቱ ጋር በተጣጣመ መልኩ እንደገና ማርቀቅ፣

* የመንግስትና የግል ሚዲያ ተቋማትን ሥራና አሰራር ከፖለቲካ ወገንተኝነት ነፃ ማድረግ፣ ለዘርፉ እድገት ማነቆ የሆነውን የመረጃ ነፃነትና ሚዲያ አዋጅ ከሕገ-መንግስቱ ጋር በተጣጣመ እንደገና ማርቀቅ፣

* የሙያና ሲቪል ማህበራት በሀገሪቱ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ምቹ ሁኔታ መፍጠር፣ ለተቋማቱ አንቅስቃሴ ማነቆ የሆነውን የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ማቋቋሚያ አዋጅ እንደገና ማርቀቅ፣

* የተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶችን እና ሌሎች የፖለቲካ ኃይሎችን “ፀረ-ስላም…ፀረ-ሕዝብ…ፀረ-ልማት” ብሎ በመፈረጅ የጠላትነት መንፈስ እንዲያቆጠቁጥ ከማድረግ ይልቅ መልካም ግንኙነት ማዳበርና ለብሔራዊ መግባባት መስራት ይጠበቅበታል፡፡

2ኛ፡- አስተዳደራዊ ተሃድሶ (Administrative reform)

ከሕዝቡ እየተነሱ ያሉትን ጥያቄዎች ሕገ-መንግስታዊ መብቶችን በማከበር ብቻ ምላሽ መስጠት አይቻልም፡፡ ሕዝቡን ከዴሞክራሲ መብቱና ነፃነቱ በተጨማሪ የመልካም አስተዳደር እጦት ክፉኛ አማሮታል፡፡ ከተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች እየተነሱ ያሉት የእኩልነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጥያቄዎች ከመልካም አስተዳደር እጦት ጋር በቀጥታ የተያያዙ ናቸው፡፡ ስለዚህ ከፖለቲካ ተሃድሶ በተጨማሪ በመንግስት አስተዳደራዊ መዋቅር ላይ ሥር-ነቀል የሆነ ለውጥ ያስፈልጋል፡፡

የመልካም አስተዳደር ችግርን ለመፍታት ግልፅነትና ተጠያቂነት የሰፈነበት የአስተዳደርና አገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓት መዘርጋት ያስፈልጋል፡፡ በዚህ መልኩ የአስተዳደርና አገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓቱን ጥራት ለማሻሻል በቅድሚያ ብቃት ያለው አመራር ሊኖር ይገባል፡፡ ነገር ግን፣ በመንግስት አስተዳደራዊ መዋቅር ውስጥ ከታች እስከ ላይ ድረስ ያለው አመራር፣ እንዲሁም በሀገሪቱ የሲቪል ሰርቪስና የልማት ተቋማት ጭምር በሙያተኞች ሳይሆን በፖለተካ ተሿሚዎች የሚመሩ ናቸው፡፡ ከሙያዊ ብቃት ይልቅ በፖለቲካ ታማኝነት ላይ የተመሰረተ አመራር ግልፅነትና ተጠያቂነት የሰፈነበትና ጥራት ያለው አስተዳደርና የአገልግሎት አሰጣጥ ለመዘርጋት ዋና ማነቆ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ሥር-ነቀል የሆነ ለውጥ ማድረግ ካልተቻለ ሕዝቡን ክፉኛ እያማረረ ያለውን የመልካም አስተዳደር እጦት ችግርን በዘላቂነት መቅረፍ አይቻልም፡፡

ስለዚህ፣ የኢህአዴግ የፖለቲካ ሹመኞች በተለይ ከሀገሪቱ የሲቪል ሰርቪስ መዋቅር ውስጥ ማስወጣት አለበት፡፡ “ኢህአዴግ ቢሸነፍም-ባይሸነፍም ለውጥ አይመጣም” በሚለው ፅሁፍ በዝርዘር ለማሳየት እንደሞከርኩት፣ የሀገሪቱ ሲቪል ሰርቪስ መዋቅር በፖለቲካ ሹመኞች የሚመራ እስከሆነ ድረስ የመልካም አስተዳደር ችግርን መቅረፍ አይቻልም፡፡ ከአመራር ብቃት ማነስ በተጨማሪ፣ እነዚህ የፖለቲካ ሹመኞች እንዴት በአመራር ወጥመድ (leadership trap) እንደተጠለፉና ለውጥና መሻሻል ዋና እንቅፋት እንደሆኑ “ኢህአዴግን የጠለፈው የአመራር ወጥመድ” በሚለው ፅሁፍ በዝርዝር ተገልጿል፡፡

ስለዚህ፣ የኢህአዴግ ተሃድሶ በተለይ የሀገሪቱን ሲቪል ሰርቪስ መዋቅርን ከታማኝ የፖለቲካ ሹመኞች እጅ ፈልቅቆ በማውጣት ብቃት ላላቸው ሙያተኞች መስጠት ያስፈልጋል፡፡ ይህ ሲሆን ከማንኛውም የፖለቲካ ወገንተኝነት ነፃ የሆነ፣ ግልፅነትና ተጠያቂነት የሰፈነበት የአስተዳደርና አገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓት በመዘርጋት የመልካም አስተዳደር እጦት ችግርን በዘላቂነት መቅረፍ ይቻላል፡፡

የምርጫ 2012 ሞት-ሽረት

ከላይ በዝርዝር ለማሳየት እንደተሞከረው፣ በቀጣይ ሦስት ዓመታት ውስጥ በሚደረጉ ሥር-ነቀል የሆኑ ፖለቲካዊ እና አስተዳደራዊ ለውጦችና መሻሻሎች በ2012 ዓ.ም ለሚካሄደው ሀገራዊ ምርጫ ምቹ ሁኔታ መፍጠር ይቻላል፡፡ በዚህም ምርጫ 2012 የኢህአዴግ ተሃድሶ ስኬት መለኪያ ሆኖ ያገለግላል፡፡ በዚህ መሠረት፣ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ያለ ገደብና ጫና በነፃነት ተንቀሳቅሰው ፕሮግራማቸውን የሚያስተዋውቁና የሚቀሰቅሱ ከሆነ፣ የሲቪል ማህበራት በምርጫው ዙሪያ ንቁ ተሳትፎ የሚያደርጉ ከሆነ፣ ምርጫ ቦርድና የሚዲያ ተቋማት ከፖለቲካ ወገንተኝነት ነፃ በሆነ መልኩ ተግባርና ኃላፊነታቸውን የሚወጡ ከሆነ፣ ዜጎች ሃሳባቸውን በነፃነት የመግለፅ፥ እንዲሁም የመሰብሰብ፥ የመደራጀትና በአደባባይ አቤቱታቸውን የመግለፅ መብታቸው ከተከበረ፣ የሀገሪቱ የሲቪል ሰርቪስ ከገዢው ፓርቲ ተፅዕኖ በፀዳ መልኩ መንቀሳቀስ ከቻለ፣ በአጠቃለይ በ2012 ዓ.ም ነፃና ግልፅ የሆነ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ማድረግ ከተቻለ፣ በምርጫው አሸናፊ ማንም ይሁን ማን፣ ኢህአዴግ ግን ደማቅ ታሪክ ፅፎ ያልፋል፡፡

በ2012 የሚካሄደው ምርጫ ልክ እንደ 2002ቱ እና 2007ቱ ዓይነት ከሆነ ግን ኢህአዴግ አጉል አወዳደቅ ይወድቃል፡፡ ከሶስት ዓመት በኋላ ኢህአዴግ በሕዝቡ ውስጥ ያለውን ተቀባይነት አንጠፍጥፎ ጨርሶ፣ እንደ ጨው አልጣፍጥ ብሎ እንደ ድንጋይ ተወርውሮ ይወድቃል፡፡ ይህ እስካሁኑ በሕዝባዊ አመፅና ተቃውሞ ብቻ የሚሆን አይደለም፡፡ ከዚያ ይልቅ፣ የሀገሪቱ የፀጥታና ደህንነት ኃይሎች እንኳን ለሀገርና ሕዝብ ለራሱም የማይበጅ የፖለቲካ ቡድንን እንዳይወድቅ ታቅፈውና ደግፈው የሚቀጥሉበት ምክንያት ያጣሉ። ይህ ሲሆን ምን ሊከሰት እንደሚችል መገመት ቀላል ነው፡፡ ስለዚህ፣ ምርጫ2012 የኢህአዴግ ተሃድሶ ስኬት ወይም ውድቀት፣ የሥርዓቱ ሞትና ሽረት በግልፅ የሚለይበት ይሆናል፡፡ ምርጫ2012 ከማንም በላይ ኢህአዴግ ሕለውናውን ለማረጋገጥ የሞት-ሽረት ትግል የሚያደርግበት ወቅት ነው። 

********

Seyoum Teshome is a Lecturer at Ambo University Woliso Campus and head of Management Department. He was born in Arsi, Assela, in 1979 and studied Management at Harameya University and MBA at Mekelle University. He also blogs at http://ethiothinkthank.com

more recommended stories