የችግሩ መንስዔው ፍርሃት – መፍትሄው ነፃነት ነው

የውይይት መፅሔት አዘጋጅ በፍቃዱ ኃይሉ በኢትዮጲያ እየታየ ላለው ግጭትና አለመረጋጋት መፍትሄ ለማፍለቅ ሁላችንም ቅንነቱ ሊኖረን እንደሚገባ በመግለፅ የራሱን የመፍትሄ ሃሳብ አቅርቧል። በፍቃዱ የሚያቀርበው የመፍትሄ ሃሳብ “አሁን ሁሉንም ኃይልና እድል የተቆጣጠረው ሕወሓት/ኢህአዴግን” ነፃ የሚያወጣ ስለሆነ ፓርቲው ለዚህ ፍቃደኛ መሆን እንዳለበት ይገልፃል። በዚህ ረገድ ዋናው ነጥብ ለመፍትሄው ስለሚያስፈልገው ቅንነት ወይም የገዢው ፓርቲ ፍቃደኝነት አይደለም። ለቅንነትማ እንደ እሱና ጓደኞቹ ለቅን እሳቤያቸው በማዕከላዊ፣ በቂሊንጦ፣ በዝዋይ፣ ቃሊቲ፣…ወዘተ መከራና ፍዳ እየተከፈላቸው ያሉ ስንትና ስንት ወጣቶች አሉ። ችግሩ የቅንነት መጥፋት አይደለም፣ የፍርሃት መብዛት ነው። 

በዚህ ፅሁፍ፣ የችግሩ ዋና መንስዔ የኢህአዴግ ፍርሃት፣ የችግሩም መፍትሄ ኢህአዴግን ከፍርሃት ነፃ ማውጣት እንደሆነ ለማሳየት እሞክራለሁ። አሁን ሀገሪቷ ካለችበት ግጭትና አለመረጋጋት እንድትወጣ ሕወሃት/ኢህአዴግ እና ሌሎች አባል ድርጅቶች የሚያስፈልገው “ቅንነት” ሳይሆን ነፃነት ነው። በቅድሚያ ግን “የኢህአዴግ ፍርሃት ከምን የመነጨ ነው?” የሚለውን በመመልከት እንጀምር። 

በመሰረቱ፣ የኢህአዴግ መንግስት አምባገነን (totalitarian) – “አምባገነንነት፥ የአንድ ፓርቲ መንግስት” ነው። እንዲህ ያለ አምባገነናዊ መንግስትን ለመታገል ወይም ለመቀየር የመንግስታዊ ሥርዓቱን መሰረታዊ ባህሪ ማወቅ ያስፈልጋል። በመሰረቱ፣ “አምባገነንነት” ፍፁም ነፃነትን መንፈግ ነው (Totalitarianism is the most radical denial of freedom)[PDF] ። ስለዚህ፣ አምባገነናዊ መንግስት ለሕዝቡ ቀርቶ ለራሱ እንኳን የሚሆን ነፃነት የለውም። 

የኢህአዴግ መንግስት በሕዝቡ ላይ የሚፈፅመው ጭቆና እና በደል ለማቆም ራሱን ከፍርሃት ነፃ ማውጣት ያስፈልጋል። “ነፃነት የፈጣሪ፣ ፍርሃት የሰይጣን ነው” በሚለው ፅሁፌ፣ ፍርሃት (Fear) የነፃነት ተቃራኒ ፅንፍ እንደሆነ ለመግለፅ ሞክሬያለሁ። በተመሳሳይ፣ “ከጓንታናሞ እስከ ማዕከላዊ፡ ክፍል.2- “ፍርሃትን በፍርሃት” በሚለው ፅሁፍ፣ የዜጎችን ነፃነት የሚጋፋ መንግስት ፍርሃትን በፍርሃት ለማሸነፍ የሚሞክር መንግስት መሆኑን ጠቅሼ ነበር። እዚህ ጋር “እንደ ኢህአዴግ አምባገነን የሆነ መንግስት ለምን ይፈራል?” የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል። ሕግ አውጪ፣ ትርጓሚና አስፈፃሚ የሚሉትን የመንግስት አካላት በመለየት የሚታወቀው ፈረንሳዊው ፈላስፋ “Montesquieu”- “what makes a government act as it acts?” የሚለውን ጥያቄ በማንሳት ፍርሃት የአምባገነን መንግስታት መርህ (principle) እና መመሪያ እንደሆነ ይገልፃል፡- 

 “[E]ach government has not only its “particular structure” but also a particular “principle” which sets it in motion. In a republic the principle of action is virtue; in a monarchy, the principle of action is honor; and in a tyranny, the principle of action is fear. These moving and guiding principles—virtue, honor, fear —are principles insofar as they rule both the actions of the government and the actions of the governed. … Fear in a tyranny is not only the subjects’ fear of the tyrant, but the tyrant’s fear of his subjects as well.”

ከላይ በግልፅ እንደተጠቀሰው፣ እንደ ኢህአዴግ ላሉ መንግስታት “ፍርሃት” መርህና መመሪያቸው ነው። ተግባርና እንቅስቃሴያቸውም የሚመራው በነፃነት ሳይሆን በፍርሃት መርህ ነው። የአምባገነንነት መንስዔው ፍርሃት ነው። የአምባገነኖች ተግባርና እንቅስቃሴ የሚመራው በፍርሃት ነው። እንደ ኢህአዴግ ያለ አምባገነን መንግስት ራሱን ብቻ ሳይሆን ህዝቡንም ጭምር በፍርሃት ለማስተዳደር ይጥራል። ስለዚህ፣ ዋናው ጥያቄ መሆን ያለበት “ኢህአዴግን እንዴት ከፍርሃት ቆፈን ነፃ እናውጣ?” የሚለው ነው። 

በመሰረቱ ዕውቀት ብርሃን ነው፣ ኣላዋቂነት ጭለማ ነው። በብርሃን ነፃነት፣ በጭለማ ፍርሃት ይነግሳል። አምባገነንነት ኣላዋቂነት ነው፣ አምባገነኖችም ኣላዋቂዎች ናቸው። ስለዚህ፣ እንደ ኢህአዴግ ያሉ አምባገነናዊ መንግስታት ያለማወቅ ውጤት ናቸው። ስለዚህ፣ በሰላማዊ መንግድ ኢህአዴግን ከፍርሃት ለማላቀቅ ያለው አማራጭ ስለ ነፃነት ማሳወቅ ነው። 

አሁን በሀገራችን የተከሰተው ግጭትና አለመረጋጋት መንስዔው ይሄ ነው። ህዝብ ነፃነቱን ለማስከበር አምጿል። መንግስት ግን እንደ ቀድሞው በማስፈራራት ለማፈን እየሞከረ ነው። የነፃነት ጥያቄ መልሱ ነፃነት። መንግስት ግን አሁንም የፍርሃት ቆፈን አልቀቀውም። የነፃነት ጥያቄን በፍርሃት ቆፈን ለማፈን እየጣረ ነው። በዚህ ትግል ከሁለቱ አንዱ ይሸነፋል – ነፃነት ወይም ፍርሃት። 

ነፃነትን ጠይቆ የወጣው ህዝብ ከአሸነፈ ፍትህና እኩልነት የሚረጋገጥበት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መሰረት ይሆናል። የነፃነትን ጥያቄ በጉልበት ለማፈን ጥረት እያደረገ ያለው መንግስት ካሸነፈ ደግሞ ፍፁም አምባገነንነት ይነግሳል። አሁን በሕዝቡ ፊት ላይ እየታየ ያለው የነፃነት ፈገግታ በፍርሃት ፅልመት ይዋጣል። በአደባባይ እየተነሱ ያሉት የማንነት፣ እኩልነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጥያቄዎች ወደ ሹክሹክታ ይቀየራሉ። በአጠቃላይ፣ የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች የተከበሩባት፤ የዳበረ ማህበራዊ ግንኙነትና የበለፀገ ኢኮኖሚ ለመገንባት የነበረን ራዕይ ይከስማል። 

ፍርሃት የሚሸነፈው በነፃነት ነው። የነፃነት ጥማት ከፖሊስ ዱላና ከወታደር ጥይት በላይ ሲሆን ፍርሃት ይሸነፋል። ስለዚህ፣ የነፃነት ጥያቄ በፍርሃት መመለስ አይቻልም። የነፃነትን እንቅስቃሴ በማስፈራራት መግታት አይቻልም። የዘንድሮው አመፅና ተቃውሞ ሕዝቡ ለፍርሃትና ማስፈራሪያ ተገዢ ላለመሆን መወሰኑን ያረጋግጣል።

በእርግጥ ሞት አስፈሪ ነው። ፍርሃት ግን ከሞት በላይ አስፈሪ ክስተት ነው። የሞተ ሰው አንዴ ሞቷል፤ መሞቱን አያይም፥ አይሰማውም። በፍርሃት ቆፈን ውስጥ ያለ ሰው ግን እንደ ሰው ያስባል፣ ሃሳቡን ግን መግለፅ አይችልም፤ የራሱ አመለካከት አለው፣ አመለካከቱን ማንፀባረቅ አይችልም፤ የመናገር፥ የመስማትና ሃሳብን የመግለፅ ሰብዓዊ መብት አለው ፣ መብቱን መጠየቅ ግን አይችልም፤ እንደ ዜጋ እኩልነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ይገባዋል፣ ዴሞክራሲያዊ መብቶቹን መጠየቅ ግን አይችልም። በአጠቃላይ በሕይወት አለ-ሕይወት ግን የለውም። በፍርሃት ውስጥ የሚኖር ሰው እያለ ሞቷል፣ ሞቶም መሞቱ ይታየዋል፣ ህመም፥ ስቃዩ ይሰማዋል። ስለዚህ፣ “ነፃነት ወይም ሞት” ብሎ አደባባይ ይወጣል። እንዲህ ብሎ ለተቃውሞ የወጣ ሰው ሞትን አይፈራም። ምክንያቱም፣ በፍርሃት ውስጥ የሙታን ኑሮ ከመኖር በጥይት መሞት እንደሚሻል ቆርጦ የመጣን ነውና። ስለዚህ፣ ፍርሃትን አሸንፎ “ነፃነት” ብሎ ለወጣ ሕዝብ መልሱ አንድና አንድ ብቻ ነው – “ነፃነት”። 

የችግሩ መንስዔ ፍርሃት ነው፣ መፍትሄው ነፃነት ነው። የነፃነት ጥያቄ መልሱ ነፃነት ነው። የችግሩ መፍትሄ የሕዝቡን ነፃነትና መብት ማክብርና ማስከበር ነው። ሕዝቡ የፍርሃት ኮፈንን ሰብሮ ወጥቷል። መንግስት ግን አሁንም በፍርሃት ቆፈን ውስጥ ነው። ህዝብ በነፃነት እውነተኛ ጥያቄውን አቅርቧል፣ ኢህአዴግ ግን ከፍርሀቱ መውጣት አቅቶታል፡፡ ሀገር ማለት ሕዝብ ነውና ሕዝብ ነፃነትን ጠይቋል። መንግስት ማለት ሕዝብ ከሆነ የሕዝብን ጥያቄ መመለስ ያስፈልጋል። በነፃነት ሀገር ይገነባል፣ በፍርሃት ሀገር ይፈርሳል!!!

********

Seyoum Teshome is a Lecturer at Ambo University Woliso Campus and head of Management Department. He was born in Arsi, Assela, in 1979 and studied Management at Harameya University and MBA at Mekelle University. He also blogs at http://ethiothinkthank.com

more recommended stories