የገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ አመራሮችና ደጋፊዎች፤ “ከኢህአዴግ በስተቀር ኢትዮጲያን ለመምራት የሚያስችል አቅም ያለው ፓርቲ የለም”፣ እንዲሁም “በፌስቡክ (Facebook) የመንግስት ስልጣን መያዝ አይቻልም” የሚሉ አስተያየቶችን በተደጋጋሚ ሲሰጡ ይሰማል። ለምሳሌ፣ “ኢትዮጲያ የማን ናት፡ የወጣቶች ወይስ የባለስልጣናት” በሚል ርዕስ ባወጣሁት ፅሁፍ ላይ ከተሰጡ አስተያየቶች አንዱ እንዲህ ይላል፤ “Except EPRDF nobody is qualified to lead Ethiopia at this time. So that it is better to stop confusing the people each of you. And you can’t get power by Facebook.”
በእርግጥ አስተያየቶቹን የሚሰጡት የተወሰኑ ግለሰቦች ሊሆኑ ይችላሉ። ነገር ግን፣ የዚህ አይንት አመለካከት በአብዛኞቹ የኢህአዴግ አመራሮችና ደጋፊዎች ዘንድ ስለመኖሩ አያጠራጥርም። እውነት ግን በሀገራችን ከኢህአዴግ የተሻለ አቅም ያለው የፖለቲካዊ ድርጅት የለም? በፌስቡክስ የመንግስት ስልጣንን መቆጣጠር አይቻልም? እነዚህ ሁለት ሃሳቦች ተያያዥነት ይኖራቸው ይሆን? ይህ ፅሁፍ ለእነዚህና ሌሎች ተያያዥ ጥያቄዎች ዙሪያ ዝርዝር ትንታኔ ይሰጣል።
እንደ ጥያቄዎቹ ቅደም-ተከተል “ከገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ ጋር የተሻለ ወይም ተወዳዳሪ የሆነ የፖለቲካ ድርጅት አለ?” ከሚለው ጥያቄ እንጀምር። እንደው በጥቅሉ ሲታይ፣ ‘በኢትዮጲያ ከኢህአዴግ ጋር ሊወዳደር የሚችል አቅምና አደረጃጀት ያለው የፖለቲካ ድርጅት የለም’ ማለት ይችላል። ከቅርብ ግዜ ወዲህ በህዝቡ ዘንድ እየታየ ያለው የፖለቲካ ንቃት፣ ተሳትፎ እና ንቅናቄ አንፃር ከታየ ግን ምላሻችን የተለየ ይሆና። እንደ እኔ “ኢትዮጲያ ውስጥ ከኢህአዴግ የተሻለ አቅምና አደረጃጀት ያለው ድርጅት አለ ወይ?” ለሚለው ጥያቄ ትክክለኛው መልስ “አዎ” ነው። በእርግጥ በተቃዋሚ ጎራ ያሉ የፖለቲካ ድርጅቶች እንኳን ሕዝቡን ራሳቸውን በአግባቡ ለመምራት የሚያስችል አቅም አላቸው ብሎ አፍን ሞልቶ መናገር በራሱ ይከብዳል። ከኢህአዴግ የተሻለ አቅም እንዳለው እያስመሰከረ ያለው የፖለቲካ ድርጅት ግን ከእነዚህ ተርታ የሚሰለፍ አይደለም። የድርጅቱን ስም ከመጥቀሳችን በፊት ግን፤ “ተቃዋሚ ፓርቲዎች ለምን ከኢህአዴግ ጋር ተወዳዳሪ መሆን ተሳናቸው?” የሚለውን በአጭሩ እንይ::
በእርግጥ አብዛኞቹ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች ባለባቸው ውስጣዊ ችግር ምክንያት ከሀገሪቱ ነባራዊ እውነታ አንፃር የተቃኘ ፕሮግራም እና ጠንካራ አመራር የላቸውም። ከዚህ በተጨማሪ፣ የኢህአዴግ መንግስት በተቃዋሚ ፓርቲ አባላትና አመራሮች ላይ በውሃ-ቀጠነ ምክንያት የሚያሳድረው ጫና ለችግሩ ትልቅ አስተዋፅዖ አለው። ከሁሉም በላይ ግን፣ የተቃዋሚዎችን አቅምና አደረጃጀት በጣም ደካማ እንዲሆን ያደረገው ነገር የኢህአዴግ መንግስት በሕዝቡ ላይ የሚያደርሰው ጫና ነው። የኢህአዴግ አባል/ደጋፊ መሆን ለእድገትና ሹመት ያበቃል። በተቃራኒው የተቃዋሚ ፓርቲ አባል/ደጋፊ መሆን ግን ለእስርና እንግልት ይዳርጋል። ከምንም በላይ የተቃዋሚዎችን ድርጅታዊ አቅመና አደረጃጀት ያቀጨጨው ነገር ይሄ ነው። ስለዚህ፣ ‘በሀገሪቱ ውስጥ ያሉና የነበሩት ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች ከኢህአዴግ አንፃር ተወዳዳሪ የሆነ አቅምና አደረጃጀት እንዳይኖራቸው ያደረገው የኢህአዴግ መንግስት የፖለቲካ ምህዳሩን ክፉኛ በማጥበቡ ምክንያት እንደሆነ ጥርጥር የለውም።
![Photo - Ethiopian internet cafe [Credit: UNICEF Ethiopia/2013/Sewunet]](https://hornaffairs.com/am/wp-content/uploads/sites/10/2016/08/Photo-Ethiopian-internet-cafe.jpg)
ባለፉት አስር አመታት ከፖለቲካ ምህዳሩ መጥበብ ጋር ተያይዞ ብዙ ነገሮች ተለውጠዋል። ሕዝቡ እንደ ቀድሞ የፖለቲካ ፓርቲዎች አባልነት እና ቅስቀሳ ሳያስፈልገው፣ ራሱን በራሱ በማደረጃት የራሱን የፖለቲካ አጀንዳ ይዞ መውጣትና ተፈፃሚነት እንዲኖረው ማድረግ የቻለበት ሁኔታ ተፈጥሯል። በተለይ ከቅርብ ግዜ ወዲህ የህዝቡን የፖለቲካ ንቃተ-ህሊና በማዳበር እና ንቅናቄ በመፍጠር ረገድ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ያለው የኢንፎርሜሽን ኮሚዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ (Information Communication Technology – ICT) ነው። እስከ ቅርብ ግዜ ድረስ የፓርቲ አመራርና ግንኙነት ድርጅታዊ መዋቅርን የተከተለ ነበር። የኢንፎርሜሽን ኮሚዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ መምጣት ግን ይህን አካላዊና አዝጋሚ የሆነ የአመራርና ግንኙነት ስርዓት ወደ ምናባዊና ፈጣን የሆነ የግንኙነት መረብ (Communication Network) ቀይሮታል። ይህ የፓርቲ የአመራርና አደረጃጀት ሥራውን ከጥቂት ግለሰቦች እጅ ወጥቶ ለሁሉም የሀገሪቱ የፖለቲካ ልሂቃን (political elites) እጅ እንዲገባ አድርጎታል። ለዚህ ደግሞ ከፍተኛውን ሚና እየተጫወቱ ያሉት እንደ ፌስቡክ (Facebook) ያሉ ማህበራዊ ድረገፆች ናቸው።
የኢንተርኔት አገልግሎት መጀመርን ተከትሎ ወደ ሀገራችን የገባው ማህበራዊ ድረገፅ “Hi5” የሚባል ነበር። ከዚህ በመቀጠል “MySpace” የተባለው ማህበራዊ ድረገፅ መጣ። ምንም እንኳን በሌሎች ሀገራት ተመራጭ የነበረ ቢሆንም፣ በኢትዮጲያ ግን ብዙ ተጠቃሚዎች አልነበሩትም። ለዚህ ደግሞ ሁለት መሰረታዊ ምክንያቶች የነበሩ ሲሆን፤ አንደኛ፡- የዘርፉ መሰረተ ልማት በጣም ኋላ-ቀር ስለነበረ፤ የኢንተርኔት ግንኙነት 54Kps (አብዛኛውን ግዜ 14kps) በመሆኑ፣ ሁለተኛ፡- ከተወሰነ ግዜ በኋላ መንግስት የ“MySpace” ድረገፅ አገልግሎት እንዳይሰጥ እገዳ በመጣሉ ነበር። በአጠቃላይ ግን፣ ከአስር አመት በፊት የኢንተርኔት አገልግሎት ተጠቃሚዎች እና ታዳሚዎች የዉጪ ሀገር ዜጎች እና አንዳንድ የመንግስት ተቋማትና ሰራተኞች ነበሩ።
የፌስቡክ ሚዲያ መምጣት ግን በኢትዮጲያ የነበረውን የኢንተርኔት አገልግሎት አሰጣጥና ተዳሚዎች ሙሉ-ለሙሉ ቀይሮታል። የኢንተርኔት አገልግሎት ከመንግስትና የወጪ ሀገር ዜጎች አውጥቶ ባለቤትነቱ ብዙሃኑ የሀገሪቱ ዜጎች እንዲሆን አስቻለ። አቶ ማርቆስ ለማ የተባሉ የዘርፉ ምሁር ፌስቡክ በኢትዮጲያዊያን ዘንድ ያበረከተውን አስተዋፅዖ አንዲህ ሲል ይገልፀዋል፤ “The social network platform Facebook has helped transfer Internet ownership out of the hands of foreigners and governmental organizations to Ethiopians.”
ከአስር አመት በፊት በኢትዮጲያ የኢንተርኔት ተጠቃሚ ብዛት 450ሺህ የነበረ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ ከ400ሺህ በላይ የሚሆነው የፌስቡክ ተጠቃሚ ነበር። ከአስር አመት በኋላ የኢንተርኔት አገልግሎት ተጠቃሚው ቁጥር ወደ 2.5 ሚሊዮን ሲያድግ የፌስቡክ ተጠቃሚዎች ብዛት ደግሞ ወደ 3 ሚሊዮን አሻቅቧል። ኢትዮጲያው ውስጥ ያለው የፌስቡክ ተጠቃሚ ብዛት ከአጠቃላይ የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ብዛት ይበልጣል። ለምሳሌ፣ በአለፈው አመት በጉዳዩ ዙሪያ በቀረበ ዝርዝር ዘገባ መሰረት፣ ምንም እንኳን ኢትዮጲያ በኢንፎርሜሽን ኮሚዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ (ICT) መሰረተ ልማት ከአለም የመጨረሻ ደረጃ ላይ የምትገኝ ቢሆንም፣ ማህበራዊ ሚዲያዎች ግን ባልተጠበቀ መልኩ በፍጥነት እያደጉና የአከባቢያዊና ዓለማቀፋዊ ጉዳዮች የመረጃ ምንጭ እና የውይይት መድረክ እንደሆኑ ተገልጿል።
ከላይ እንደተገለፀው፣ ኢትዮጲያ ውስጥ ያሉት የፌስቡክ ተጠቃሚዎች ቁጥር ከአጠቃላይ የኢንተርኔት አገልግሎት ከሚያገኙት ዜጎች ብዛት ይበልጣል። አንዳንድ የዘርፉ ምሁራን ደግሞ በኢትዮጲያ እየታየ ያለው ለውጥ ከተጠቃሚዎች ቁጥር አንፃር ብቻ እንዳልሆነ ይገልፃሉ። ከሌላው ዓለም ክፍል በተለየ ኢትዮጲያኖች በማህበራዊ ድረገፆች ላይ የሚያወጧቸው መረጃዎች በድንገት ወይም በዘፈቀደ የመጣላቸውን ሳይሆን የተለየ ግብና ዓላማ አለው። በዋናነት በእነዚህ ሚዲያዎች ላይ የሚወጡት መረጃዎች የተጠቃሚዎችን ግንዛቤ ለማዳበር አላማ ያደረጉ፤ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና በልማታዊ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ያደረጉ እንደሆነ ምሁራኑ ይገልፃሉ።
በዚህ መሰረት፣ በኢትዮጲያ የማህበራዊ ድረገፆች አጠቃቀምና ፋይዳ ከሌላው ዓለም የተለየ፣ በማህበራዊና ፖለቲካዊ ዘርፍ ሚናቸው የላቀ እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል። የእነዚህን ሚዲያዎች አጠቃቀምና ፋይዳ በቅርበት የሚከታተሉ ምሁራን፣ ፌስቡክ የህትመትና ኤሌክትሮኒክስ ሚዲያዎች ተደራሽነትን ከማሳደጉ በተጨማሪ፣ ዋና የመረጃ ምንጭ ሆኖ እንደሚያገለግል ይገልፃሉ። በአጠቃላይ፣ በሀገሪቱ ውስጥ የተለያየ አቋምና አመለካከት፣ እንዲሁም ለብዙሃኑ የህብረተሰብ ክፍል ተደራሽ የሆኑ የህትመት ዉጤቶች በሌሉበት፣ የኤሌክትሮኒክስ ሚዲያዎቹ ግልፅና አሳታፊ ባለመሆናቸው ምክንያት ማህበራዊ ድረገፆች ዋንኛ የመረጃ ምንጭ እንዲሆኑ አስችሏቸዋል።
እንደ ኢትዮጲያ ነፃና ገለልተኛ የሆነ ፕሬስና ሚዲያ በስፋት በሌለበት ሀገር፣ ፌስቡክ የመረጃ ምንጭና የውይይት መድረክ ከመሆኑ በተጨማሪ፣ በራሱ አንድ የግንኙነት መዋቅር ሆኖ እያገለገለ ይገኛል። ፌስቡክ በኢትዮጲያ ውስጥ የሚካሄዱ የተለያዩ የፖለቲካ አንቅስቃሴዎችን ለማደራጀትና ለመምራት እንደ መዋቅር ሆኖ ያገለግላል። የጋራ አጀንዳ ያላቸው ግን በተለያየ የዓለም ክፍል የሚገኙ ልሂቃንን አንድ ላይ በማገናኘት ሃሳብና የተግባር እቅዶቻቸውን እንዲለዋወጡ፣ በዚህም የተቀናጀ የፖለቲካ እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል።
ከዚህ በተጨማሪ፣ ከመደበኛ የፖለቲካ ፓርቲዎች አደረጃጀት በተለየ መልኩ፣ በማህበራዊ ድረገፆች ላይ የተዘረጋው መዋቅር በጣም ብዙ ተሳታፊዎች እና አመራሮች ያሉት እንደመሆኑ ሥራና የአሰራር ሂደቱን በቀላሉ ለመቆጣጠር አይቻልም። ለምሳሌ፣ ከ12ኛ ክፍል ብሔራዊ መልቀቂያ ፈተና ጋር ተያይዞ የተፈጠረውን ችግር እንደ ማሳያ መጥቀስ ይቻላል። በወቅቱ በዋናነት ፈተናው እንዲራዘምላቸው የጠየቁት ተፈታኝ ተማሪዎች ነበሩ። እንቅስቃሴውን በማቀድ፣ በማደራጀት እና በመምራት ተሳታፊ የነበሩት ሰዎች ደግሞ ብዛታቸው ከተማሪዎቹ ቁጥር ብዙም የሚያንስ አይሆንም። በአጠቃላይ፣ እንደ ፌስቡክ ያሉ ማህበራዊ ድረገፆች በግልፅ ተለይቶ የማይቀመጥ፣ ቀጥተኛ የሆነ የፖለቲካ አመራር ለመስጠት እና ተግባራዊ የሆነ ለውጥ ለማምጣት የሚያስችል መዋቅር ሆኖ እያገለገለ ይገኛል።
ከላይ ለመጥቀስ እንደተሞከረው፣ በሀገሪቱ ውስጥ ያሉ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች አቅምና አደረጃጀት በጣም ደካማ የሆነው የኢህአዴግ መንግስት በፓርቲ አመራሮች፣ አባላትና ደጋፊዎች ላይ በሚያሳድረው ተፅዕኖ ምክንያት ነው። በመሆኑም፣ የተሻለ የትምህርት ደረጃ እና ንቃተ-ህሊና ያለው የሕብረተሰብ ክፍል በፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ተሳትፎ ለማድረግ ከመደበኛ የፓርቲ መዋቅር ይልቅ ማህበራዊ ደረገፆች የተሻለ አማራጭ አግኝቷል።
ምክንያቱም፣ አንደኛ፡- በማህበራዊ ድረገፆች አማካኝነት የሚደረገው እንቅስቃሴ በመንግስት ለሚደረገው ጫና በቀጥታ ተጋላጭ አይደለም፣ ሁለተኛ፡- ለአብዛኞቹ የዘመኑ ወጣቶች በቀላሉ ተደራሽ ናቸው። ለምሳሌ፣ ሐምሌ 24/2008 ዓ.ም ቀን በጎንደር ከተማ የተደረገው ሰላማዊ ሰልፍ ተከትሎ፣ ሐምሌ 30/2008 ዓ.ም በተለያዩ የኦሮሚያ ክልል አከባቢዎች በተመሣሣይ ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ እንደቀረበ እናስታውሳለን።
በእርግጠኝነት፣ ኢህአዴግን ጨምሮ፣ የትኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ኢትዮጲያ ውስጥ በስድስት ቀናት እንደዛ ያለ የህዝብ ንቅናቄ ለመፍጠር አይችልም። ለዚህ ደግሞ ዋናው ምክንያት፣ የሕዝቡን በመቀስቀስም ሆነ በመምራቱ ረገድ ተሳታፊ የነበሩት የተወሰኑ የፓርቲ አመራሮችና አባላት ሳይሆኑ “የፌስቡክ” ተጠቃሚዎች ነበሩ። በእንቅስቃሴው የአመራርና መረጃ ግንኙነት ሲደረግ የነበረው በዋናነት በፌስቡክ አማካኝነት ነበር።
በአጠቃላይ፣ በፖለቲካ ዘርፍ ንቁ ተሳትፎ የሚያደርገውን የህብረተሰብ ክፍል ማዕከል በማድረግ፣ በማህበራዊ ድረገፆች አማካኝነት የተዘረጋው የአመራር መዋቅር እና የውይይት መድረክ ከኢህአዴግ የተሻለ አቅምና አደረጃጀት ያለው ነው። ይህ ምቹ የሆነ አጋጣሚ እየጠበቀ ያለ “የተዳፈነ” (Latent) የፖለቲካ ፓርቲ ነው። በተገኘው አጋጣሚ በጣም በትንሽ ግዜ ውስጥ ወደ ትልቅ ሀገር-አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲ ሊቀየር የሚችል ነው። አባላቱ እንደቀድሞ በጉርብትና፥ ዝምድና ወይም በትውውቅ ሳይሆን በሃሳብና አመለካከት፤ በግል ጥቅም ሳይሆን በነፃ ፍላጎትና ተነሳሽነት የሚቀላቀሉ እንደመሆኑ የዓላማ ፅናትና ቁርጠኝነት ይኖራቸዋል። ስለዚህ፣ መቶዎች ሺህዎችን፣ ሺህዎች ሚሊዮኖችን በአባልነትና ደጋፊነት መመልመል ይችላሉ። በዚህም፣ ከኢህአዴግ ብዙ እጥፍ የሚበልጡ አባላትና ደጋፊዎች ይኖሩታል።
ይህ የተዳፈነ የፖለቲካ ቡድን እንዲህ እየተጠናከረ የመጣው የመንግስትን ጫና እና ጥብቅ ቁጥጥር ተቋቁሞ መሆኑ ነው። እንደ ”Freedom_house” ሪፖርት፣ የኢትዮጲያ መንግስት የኢንተርኔት አገልግሎትን በማስተጓጎል፣ ይዘቶቹን በመቆጣጠርና የተጠቃሚዎቹን የግለሰብ መብት በመጣስ ከመቶ 82 ነጥብ አስመዝግቧል (0 ነጥብ ምርጥ የሚባል ሲሆን 100 ነጥብ ደግሞ መጥፎ እንደማለት ነው)። በተለይ በዘንድሮው አመት የመንግስት ገደብና ቁጥጥር ይበልጥ ተጠናክሮ የቀጠለ ቢሆንም፣ በፌስቡክ አማካኝነት የተዘረጋውን የመረጃ መረብ፣ የውይይት መድረክ እና የአመራር መዋቅር ለማፍረስ ፈፅሞ አይቻልም። ምክንያቱም፣ ይህን የፖለቲካ አደረጃጀት ለማፍረስ የሚያደርገው ጥረት ሊሳካ የሚችለው የሀገሪቱን የኢንፎርሜሽን ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ሙሉ-በሙሉ በማቋረጥና ሀገሪቷን ከሌላው ዓለም በማቆራረጥ ብቻ ነው። ይህ ሲሆን፣ ኢህአዴግ በአዲሱ የፖለቲካ ፓርቲ ተሸንፎ በብስጭት ራሱን-በራሱ እንዳጠፋ ይረጋገጣል።
*********
አቶ ሀይሉ እውነትን ወያኔ ባስተማረህ የፈጠራ ወሬ( ፕሮፖጋንዳ) መቀየር አይቻልም፡፡ አህአዴግ መንግስት ልታመሰግነው ይገባል ያልከው በጣም አሳፋሪም አሳቂም ነው፡፡በ internet ( social media) ሀሳብን መገለጽ የኢህአዴግ ውጤት ነው ልትለን እንዳትሞክር ስላለቻለ ነው እንጅ ዘግቶ መቆጣጠር በቻለ ደስታው ነበር፡፡ የዘጋቸውን print media ስለምናውቅ
ሌላው እንደ ዘመዶችህ( ከጋሻ አጃግሬዎችህ የወረስከው ታሪክ ማጥፋትና ማጣመም አጀንዳ ማስቀየሪያ እንደሆነ ህዝብ ያውቃል፡፡ ህዝብና ከህዝብ በማባላት ስልጣን ማራዘም እንደማይቻል ሁሉም ተረድቶባችኋል፡፡ አማራና አሮሞ ከመቸውም ጊዜ በበለጠ ሴራችሁን አውቀዋል፡፡ የአማራ ህዝብም የአማራን ጨቋኝ ገዥዎች(ጨቋኝነታቸው ከወያኔ ባይበልጥም) እንደማይወከል ሁሉም ተረድቷል፡፡
የምታወራው ልማትና ዲሞክራሲም ሰፊውን ህዝብ አይመለከትም ለአንተና ለጌቶችህ ካልሆነ በስተቀር፤ልማት ደግሞ ቁሳዊ ብቻ አለመሆኑን ይልቁንስ ማህበራዊና አዕምሮአዊ ልማት እንደሚበልጥ ማወቅ አለብህ፡፡ ቀሳዊውም ቢሆን የእነ ጎይቶም እና ገብረ እግዚአብሔር ህንጻ ለከርታታው አማራና ለተፈናቃዊ አሮሞ ምኑ ነው?
በተረፈ ማስተዋልን ይስጥህ
Seyoum Teshome, please keep doing what you are doing now. you are the only one i know who understands the power Internet not the government. keeps saying what need to be said on behalf of voiceless and powerless and the reward will be great at the end
ለአቶ ኃይሉ ለማ
ስለ ያኔው ግፈኛ ስርዓቶች ጭፍጨፋ ጥሩ ብለሃል ወንድሜ፡፡ እውነት ነው፡፡ ነገር ግን ያሁኑን ጨምሮ ከ1983 ወዲህ ኢህአዴግ በሰልፈኞች ላይ የፈፀማቸው ግድያዎች ከጡት መቁረጥና ከቦንብ በምን ይለያሉ? ኢህአዴግ ዲሞክራሲ አምጥተዋል ብለሃል፡፡ መሉእ ባይሆንም ይህም እውነት ነው ብየ ልቀበል፡፡ ነገር ግን በዲሞክራሲ ሰልፈኛ ሲገደል ገና ከአንተ ለመጀመርያ ጊዜ ስሰማ! አንተ እንደጣፈከው ጥያቄው አህአዴግ ይግዛ ወይስ ሌላ ሳይሆን ከግንባሩና ከፌስ ቡክ ማን ያሽንፋል የሚል ነው፡፡ የአርቲክሉ ትንተና ያንን ጥያቄ ለመመለስ ሆኖ እያለ ያንተ መልስ ግን ፈፅሞ የማይገናኝ (irrelevant ) ነው፡፡ እንዳውም የክርክርህ ጭብጥ በይዘቱ out of context የሚሉት አይነት ነው፡፡
ለዚህ ያበቃህ ኢህአዴግ ነው ያልከው አልገባኝም፡፡ ፀሃፊው ግን ጦማሪ መሆኑን አውቃለሁ፡፡ ጥሞራ (blog ) ማድረግ የተጀመረው ደግሞ በሳይንስና በቴክኖሎጂ እድገት ምክንያት የኢንተርነት አለም በመፈጠሩ ነው፡፡ ጦማሪዎች ኢህአዴግ በሌለባቸው የአለም አገራት ሁሉ (ግንባሩ እጅግ በሚወዳትና ለነፃነትዋ የተማጎተላት ኤርትራ ሳይቀር) ያለ የ21ኛው ክፍለ ዘመን እውነታ ነው፡፡ ታዲያ ለጥሞራ ያበቃህ ኢህአደጉ ነው ማለት ፈገግ አያሰኝም አለቃ? በጣም እንጂ! ያም ሆነ ይህ አርቲክሉን ደግመህ አንብበው፡፡ ከመናገር በፊት የተነገረውን መመርመር ብልህነት ነውና!
This is a nice analysis. Dictators may take control of the media; they may use their apparatus to meet their end – stay in power forever and with power rob, loot the nation and fill their bellies. But, they can never control the human brain, nor would they ever prevail over the people in the 21st century. The face book has brought tabled a big question to the EPRDF, the lifetime vassal of the Shabia, to democratize the nation, ensure freedom of its people, respect for the law itself wrote, and eventually restore Ethiopia portion of the red sea or perish for ever!