የጎንደር ሕዝብ ጥያቄና ተጠያቂዎቹ

 እሁድ ሐምሌ 24/2008 በጎንደር ከተማ የተካሄደው ታላቅ ሰላማዊ ሰልፍ በብዙዎች ዘንድ ያልተጠበቀና ያልተለመደ ክስተት “በጎንደሩ ሰላማዊ ሰልፍ የሕዝቡ ጥያቄ ምን ነበር?” የሚለውን የተለያዩ የሚድያ ተቋማት በአግባቡ ይዘግቡታል የሚል እምነት ነበረኝ። ሆኖም ግን፣ የክልሉ መንግስት በሰጠው መግለጫ “ሕዝቡ የልማትና መልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን” እንዳነሳና መንግስትም በዚሁ አግባብ ምለሽ እንደሚሰጥ ገልጿል። በእርግጥ የኢህአዴግ መንግስት የሕዝብን ጥያቄ በቀጥታ የመቀበልና መረዳት፣ እንዲሁም ፈጣን የሆነ የማስተካከያ እርምጃ ለመውሰድ የአቅምና አመለካከት ችግር አለበት። በተመሣሣይ፣ አብዛኞቹ የሀገሪቱ የሚዲያ ተቋማት አንደዚህ ያሉ ክስተቶችን ከማጣጣልና ከማጋነን ባለፈ በዕውቀት ላይ የተመሰረተ ትንታኔ ሲያቀርቡ አይስተዋሉም። ስለዚህ፣ “የጎንደርና አከባቢው ሕዝብ እሁድ እለት ባልተጠበቀና ባልተለመደ መልኩ በቁጣ ገንፍሎ አደባባይ የወጣበት ዋና ምክንያት ምንድነው?” የሚለውንና ሌሎች ተያያዥ ጥያቄዎችን መመለስ አስፈላጊ ነው። ይህ ፅሁፍ “የሕዝቡ ጥያቄና ለችግሩ ተጠያቂዎቹ እነማን ናቸው?” በሚለው ላይ ትኩረት ያደርጋል።

የጎንደርም ሆነ የሌላ አከባቢ ሕዝብ ለተቃውሞ ወደ አደባባይ የሚወጣው በጣም ስለተከፋና አቤቱታውን ለሚመለከተው አካል መግለፅ ስለፈለገ ነው። ምክንያቱም፣ መከፋትና ደስታን በንግግር፣ በፅሁፍና በሰላማዊ ሰልፍ መግለፅ የሰው-ልጅ ተፈጥሯዊ ባህሪና መብት ነውና። ነገር ግን፣ በሀገራችን ካለው ነባራዊ እውነታ አንፃር፣ ሰላማዊ ሰልፍ በፖለሲና ወታደር ከመደብደብ፣ መታሰርና መገድል ጋር ተነጥሎ አይታይም።

በመሆኑም፣ በጎንደር የታየው አይነት የተቃውሞ እንቅስቃሴ ለመውጣት በቅድሚያ የሕዝቡ መከፋት ከፍርሃቱ መብለጥ አለበት። ስለዚህ፣ የጎንደርን ሕዝብ እንደዚህ ያስከፋውና ያስቆጣው ነገር ምንድነው? በእርግጥ የጎንደር ሕዝብ ጥያቄ መንግስት እንደሚለው “የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄ” ነበርን? ናጄሪያዊው ሎሬት ዋሌ ሶይንካ (Wale Soyinka)፣ የጎንደሩ ዓይነት የሕዝብ ተቃውሞና አመፅ የተቀሰቀሰው “የክብር” (Dignity) ጉዳይ ስለሆነ ነው ይላል፡

“Nothing is more fascinating, but permanently contentious than the kind of binarism attributed to the motoring force of the evolution of the social order by Hegel, Nietzsche, Hobbes and Locke among others. The historic man, according to them, would appear to be a product of a choice between abject submission or bondage on the one hand, for the sake of self-preservation and, on the other, a quest for dignity, even if this leads to death….

In one form or the other, the quest for human dignity has proved to be one of the most propulsive elements for wars, civil strife and willing sacrifice. … [t]he Yoruba have a common saying: ‘Sooner Death, than Indignity’. It is an expression that easily finds equivalents in numerous cultures, and captures the essence of self-worth, the sheer integrity of being that animates the human spirit, and the ascription of equal membership of the human community… which appears to give the most accessible meaning to human self-regarding. Its loss, in many cultures, Japan most famously, makes even death mandatory, exile coming as a second best.”

እንደ ዋሌ ሶይንካ አገላለፅ፣ የመደብ ትግል ክብርን ለማስጠበቅ (self-preservation) ወይም ክብርን ለማግኘት (quest for dignity) የሚደረግ የሁለትዮሽ ትግል ውጤት ነው። ታሪካዊ ሰዎች የራሳቸውን፣ የማህብረሰባቸውንና የሀገራቸውን ክብር ለማስጠበቅ ወይም ለማረጋገጥ በሚደረገው ትግል ገድል የሰሩ ናቸው። ይህ የሁሉም ሀገራት ታሪክና ባህል ውስጥ የሚንፀባረቅ እውነታ ነው። ለምሳሌ ከላይ የተጠቀሰው፤ “Sooner death, than Indignity” የሚለው የናይጄሪያዎች አባባል በኢትዮጲያኖች ዘንድ “ከውርደት ሞት ይሻላል” የሚባለው ነው። ክብርን ከማጣት የሞትን ፅዋ ስለመጎንጨት ደግሞ የጎንደሩን አፄ ቴዎድሮስ መጥቀስ ይቻላል። አፄ ቴዎድሮስ በዘመናቸው ክብርን ለማረጋገጥ ሆነ ለማስጠበቅ በተደረገው ትግል ክብር ያላቸው ንጉስ ናቸው። የሀገራቸውን የቀድሞ ክብርና አንድነት ለማረጋገጥ ባደረጉት ትግል ከሽፍታነት ተነስተው የሀገር ንጉስ ለመሆን የበቁ ሲሆን በእንግሊዝ ጦር ሲሸፉ ደግሞ ከውርደት ሞትን መርጠዋል። ይህ የአፄ ቴዎድሮስ ስብዕና በእያንዳንዱ የጎንደር ተወላጅ ስነ-ልቦና ውስጥ ይንፀባረቃል። ባሳለፍነው ወር ስነ-ልቦና በግልፅ ተንፀባርቋል። ለምሳሌ፣ “አፄ ቴዎድሮስ ልጆች” የሚለውን ሐረግ ጨምሮ፣ የንጉሱ ምስል እና አለባበስ ሳይቀር ለሰላማዊ ሰልፉ ዋና መቀስቀሻ ነበር። 

ክብር በአንድ ግለሰብ ስነ-ልቦና ላይ ብቻ የሚንፀባረቅ ባህሪይ ብቻ አይደለም። ከዚያ ይልቅ፤ ግለሰብ፣ ቡድን፣ ሕብረተሰብ፣ ሀገር፣ እንዲሁም ዘርና ብሔር ሣይቀር፣ አንዱ ከሌላው ጋር በሚኖረው ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ግንኙነት ላይ የሚንፀባረቅ ነው። ዋሌ ሶይንካ በ2004 (እ.አ.አ) በሰጠው ትምህርታዊ ትንታኔ፣ በኃይልና በጉልበት የሚፈፀም ጭቆና በማህብረሰቡ ዘንድ የውርደት (Humiliation) እና የተስፋ መቁረጥ ባህሪ እንዲፈጠር በማድረግ፤ በመጀመሪያ ለአመፅና ረብሻ፣ በመቀጠል ለጦርነትና ግጭት፣ በመጨረሻም ራስን-በራስ እስከማጥፋት (ለመሰዋዕትነት) እንደሚያደርስ ይገልፃል። ለዚህ ደግሞ ከሁለት አመት በፊት በፍልስጤም የታዘበውን ሁኔታ፤ “I shall sum up my apprehension of the Palestinian situation in one word: Humiliation” በማለት ማሳያ ይጠቅሳል። እንደሱ አገላለፅ የእስራኤል ወታደሮች፤ በየፍተሻ ጣቢያው (Check point) ሲፈትሿቸው፤ ተወልደው ባደጉበት መንደር የቤት-ለቤት አሰሳ ሲያደርጉ ሲያዩ፣ የቀድሞው ፕረዜዳንት ያሲር አራፋት ከተባበሩት መንግስታት ዋና ፀኃፊ ጋር ስብሰባ ላይ እያሉ የፕረዜዳንቱ ፅ/ቤት በእስራኤል ጀቶች ሲደበደብ ሲመለከቱ፣…ወዘተ በፍልስጤማዊያንና በአጠቃላይ በአረቡ ዓለም የሽንፈትና ውርደት ስሜት እንዲሰርፅ እንዳደረገውና ይህ ደግሞ ለሽብርተኝነት መስፋፋት ዋና ምክንያት ነው። በመቀጠል፣ “ሐምሌ 05/2008 ዓ.ም በጎንደር ከተማ የተከሰተው ነገር ከላይ ከተጠቀሰው ሁኔታ ጋር ተመሣሣይነት ነበረው?” የሚለውን እንመለከታለን። 

በመጀመሪያ ደረጃ “የወልቃይት ኮሚቴ” አባላት የወልቃይት ሕዝብን የማንነት ጥያቄ በማስተባበር ጉዳዩን፤ ከወረዳ፣ ዞን፣ ክልል፣ እስከ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ድረስ ያቀረቡ ግለሰቦች ናቸው። እነዚህ ግለሰቦች የመኖሪያ አከባቢያቸው ካለበት ትግራይ ክልል ለቀው የወጡበት ዋና ምክንያት ምንድነው? የአከባቢው ሕዝብ እያነሳ ያለውን የማንነት ጥያቄ በማስተባበራቸው በትግራይ ክልላዊ መንግስት እንታሰራለን፣ እንገላታለን፣…ወዘተ የሚል ስጋት ስላለባቸው ነው።

የተጠቀሱት የኮሚቴ አባላት ለምን ወደ ጎንደር ከተማ መጡ? አንደኛ፡- ለደህንነታቸውም ሆነ ጉዳዩን በቅርብ ለመከታተልና ሕዝቡን ለማስተባበር ከአስመራ ይልቅ ጎንደር ተመራጭ ስለሆነ፤ ሁለተኛ፡- “እኛ አማራ ነን” የሚል አቋም ስለያዙ። “አማራ ነን” ማለታቸው መብታቸው ነው። አስመራ ሄደው የኤርትራ መንግስት መሳሪያ ከመሆን ይልቅ ወደ ጎንደር መምጣታቸው እሰየው የሚያስብል ነው። የወልቃይት ሕዝብን የማንነት ጥያቄ ማንሳታቸው እንደ ወንጀል የተቆጠረበት አግባብ ግን ፍፁም ስህተት ነው። በሕገ-መንግስቱ መሠረት እንደዚህ ያሉ ራስን-በራስ የማስተዳደር ጥያቄዎች የሚስተናገዱበት አግባብ ስላለ በዚያ መሠረት ከማስተናገድ አልፎ ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን ስለጠየቁ ከመኖሪያ አከባቢያቸው እንዲሰደዱ ማድረግ አምባገነንነት ነው፡፡

የጎንደር ሕዝብ ተቃውሞውን በሁለት መንገዶች ገልጿል፤ በአመፅ እና ሰልፍ። በጥቅሉ ሲታይ የመጀመሪያው በትግራይ ክልላዊ መንግስት እና የክልሉ ተወላጆች ላይ ያነጣጠረ ነበር። በዚህም የዜጎች ሕይወትና ንብረት ጠፍቷል። ሁለተኛው የፌደራሉን መንግስትና የፀረ-ሽብር ግብረ ኃይሉን ተግባር የሚያወግዝና ሰላማዊ ነው። በሁለቱም አጋጣሚዎች ግን የጎንደር ሕዝብ ለአመፅና ተቃውሞ የወጣው ክብሩ (dignity) ስለተደፈረ ነው። ምክንያቱም፣ ክብርና ነፃነት የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታዎች ናቸው (Dignity is simply another face of freedom)። ከጎንደር ሕዝብ የተቃውሞ እንቅስቃሴ በስተጀርባ ግን ሁለት መሰረታዊ ስህተቶች አሉ።

1ኛ፡- የትግራይ ክልላዊ መንግስት ስህተት  

የትግራይ ክልላዊ መንግስት የወልቃይት ሕዝብን የማንነት ጥያቄ በአግባቡ ተቀብሎ ከማስተናገድ ይልቅ በኮሚቴው አባላት ላይ የደህንነት ስጋት በመፍጠር ከመኖሪያ አከባቢያቸው ሸሽተው ወደ ጎንደር ከተማ እንዲሄዱ ምክንያት ሆኗል። በዚህም በወልቃይት ኮሚቴ አባላትና ደጋፊዎቻቸው ዘንድ የአመፅና ተቃውሞ ስሜት፣ ለክልሉ የፀጥታና ደህንነት ሰራተኞች ጥላቻና የጠላትነት አመለካከት እንዲያዳብሩ አድርጓቸዋል። በዚህ መሰረት፣ በኮሚቴው አባላት ላይ ሊደርስ የሚችል ማንኛውም የደህንነት ችግር በትግራይ ክልላዊ መንግስት ትዕዛዝ እና/ወይም በክልሉ የፀጥታና ደህንነት ኃሎች አማካኝነት ነው የሚል እምነት አሳድሯል። ይህ ሐምሌ 05/2008 ዓ.ም በፌደራል ፀረ-ሽብር ግብረ ሃይል እና በወልቃይት ኮሚቴና የጎንደር አከባቢ ሕዝብ መካከል ለተፈጠረው ግጭት ከፍተኛ አስተዋፅዖ አለው።

በአጠቃላይ፣ የዚህ ዓይነት ጥላቻና የጠላትነት አመለካከት ከወደየት መጣ? የትግራይ ክልላዊ መንግስት ከሕዝቡ ያቀረበለትን ጥያቄ በአግባቡ ተቀብሎ ቢያስተናግድ ኖሮ እንደዚህ ያለ አመለካከት በኮሚቴው አባላትና በደጋፊዎቻቸው ዘነድ ይንፀባረቅ ነበር? የአከባቢውን ሕዝብ ወክለው ጥያቄያቸውን ከወረዳ እስከ ፌደሬሽን ምክር ቤት ድረስ ያቀረቡ ሰዎች በክልሉ መስተዳደር ላይ እምነት እንዲያጡና ወደ አማራ ክልል ሸሽተው እንዲሄዱ፤ በሰላማዊ መንገድ ተስፋ አንዲቆርጡና የፀረ-ሰላም ኃይሎች መጠቀሚያ እንዲሆኑ አልገፋቸውም? የኮሚቴው አባላት በአግባቡ ላቀረቡለት ጥያቄ ምላሽ ሳይሰጥ ከርሞ ክስ ለመመስረት አልፈጠነም። ስለዚህ፣ የትግራይ ክልላዊ መንግስት በጎንደር ከተማ ለተፈጠረው ችግር ተጠያቂ ነው። 

2ኛ፡- የፀረ-ሽብር ግብረ ሃይሉ ስህተት   

የኢትዮጲያ ፌደራል ፖሊስ እና የአማራ ክልል ፖሊስ በጋራ ሆነው ወደ ሀገር ውስጥ ሊገባ የነበረ የጦር መሳሪያ በቁጥጥር ስር ሲያውሉ እንዴ? እንኳን የሀገር ውስጥ የውጪ ሀገር ዜጎችን የገደሉ ሰዎችን ይዞ ለፍርድ በማቅረብ የፌደራል ፖሊስ ሥራን ሲሰራ አልነበረም አንዴ? ሐምሌ 05/2008 ዓ.ም የሆነው ግን ከዚህ የተለየ ነው። ሌላው ቀርቶ የሰሜን ጎንደር ዞን የአስተዳደርና ፀጥታ ጉዳዮች ኃላፊዎች እንኳን ሳያውቁ ነው ከተጠርጣሪዎቹ ጋር ግብግብ ውስጥ የተገባው። በዚህ ላይ የዞኑ የአስተዳደርና ፀጥታ ጉዳዮች ምክትል ኃላፊ የሰጡትን አስተያየት የፌደራል ፀረ-ሽብር ግብረ ኃይል ለምን ወደ ጎንደር እንደመጣ መረጃ አልነበረንም ብለዋል። 

በአጠቃላይ፣ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎትና የፌደራል ፖሊስ የጋራ ፀረ-ሽብር ግብረ ሃይል የወልቃይት ኮሚቴ አባላትን ለማሰር የሚያበቃው ወንጀል እስኪሰሩ ድረስ ዳር ቆሞ ሲጠብቅ አልነበረም? በሕጋዊ መንገድ ጥያቄያቸውን ለፌደሬሽን ምክር ቤት ያቀረቡ ሰዎች፣ በሂደቱ ተስፋ ቆርጠው ከፀረ-ሰላም ኃይሎች ጋር ግንኙነት እስኪፈጥሩ ድረስ ጠብቆ፣ ለሥራ ተኝቶ ለማሰር አልፈጠነም? ከአከባቢው የመንግስትና የፀጥታ ኃላፊዎች ጋር ተገቢውን የሥራ ግንኙነትና አስፈላጊውን ቅድመ-ዝግጅት ሳያደርግ ተጠርጣሪዎቹን ለማሰር በመሞከሩ በራሱና በአከባቢው ማህብረሰብ ላይ የሕይወትና የንብረት ውድመት አላስከተለም? ስለዚህ፣ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎትና የፌደራል ፖሊስ በጎንደር ከተማ ለተፈጠረው ችግር ተጠያቂዎች ናቸው። 

*********

Seyoum Teshome is a Lecturer at Ambo University Woliso Campus and head of Management Department. He was born in Arsi, Assela, in 1979 and studied Management at Harameya University and MBA at Mekelle University. He also blogs at http://ethiothinkthank.com

more recommended stories