ጎንደር፡- ሕዝብ ተከፍቶም-ተገፍቶም አይችልም

ዛሬ በጎንደር ከተማ ስለተካሄደው ሰላማዊ ሰልፍ ዓላማ፣ ግብ፣ መልዕክቶች፣…ወዘተ ስለመሳሰሉት ጉዳዮች በማህበራዊ ድረገፆችና በዲያስፖራው ሚዲያዊች በሰፊው እንደሚዘገብ እገምታለሁ። በእነዚህ ጉዳዩዮች ዙሪያ በቂ መረጃ ይቀርባል። ስለዚህ፣ የእኔ ትኩረት “ከዛሬው ሰላማዊ ሰልፍ ምን እንማራለን?” በሚለው ነጥብ ላይ ነው። በተለይ ደግሞ የክልልና የፌዴራል መንግስታት ምን መማር አለባቸው የሚለውን እንመለከታለን።

የአማራ ክልላዊ መንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ፅ/ቤት ትላንት በሰጠው መግለጫ “በጎንደርም ሆነ በሌሎች ከተሞች የተጠየቀም የተፈቀደም ሰላማዊ ሰልፍ የለም” ብሎ የነበር፡፡ ዛሬ ደግሞ “በጎንደር ከተማ የተካሄደው ሰለማዊ ሰልፍ ምንም እንኳን በመንግስት የተፈቀደ ባሆንም ሰላማዊ ነበር…” እያለ ይገኛል።

በእርግጥ ይህ የብአዴን/ኢህአዴግ መግለጫ እናቴን ነበር ያስታወሰኝ። ልጅ እያለሁ፣ በተለይ ደግሞ ከእናቴ አጠገብ ስሆን ፈርዶብኝ የሆነ ነገር አጠፋለሁ፡፡ ታዲያ ይቺ እናቴ “እስኪ ትንፍሽ በል…ዋ! ዝም…ዝም በል…” እየለች ነበር የምተገርፈኝ፡፡ መግረፏ ሳያንሰኝ “ዝም በል” ማለቷ የባሰ ያስጨንቀኝ ነበር፡፡ ዝም እንዳልል ምቷ ሰለሚያመኝ አለቅሳለሁ … ሳለቅስ ደግሞ “ዝም በል” ብላ ከዱላው ትጨምርልኛለች፡፡ መጨረሻ ላይ ሲመረኝ ብንን ብዬ ከአጠገቧ በሩጫ አመልጣለሁ፡፡ ዛሬ የጎንደር ህዝብ ልክ እንደ እኔ በምሬት ሮጦ ወደ አደባባይ የወጣ ይመስለኛል፡፡

Photo - Gondar city protest - July 31
Photo – Gondar city protest – July 31 [Credit: Social media]

በተለምዶ “ሰው ፖለቲካዊ እንስሳ ነው” ይባላል። ይህ አባባል ለምን እንደሚባል አይገባኝም ነበር። ትርጉሙ የገባኝ “Aristotle” የተባለው የግሪክ ፈላስፋ “Politics” በሚለው መፅሃፉ ስለዚህ አባባል የሰጠውን ትንታኔ ካነበብኩ በኋላ ነው። እንደሱ አገላለፅ፣ ሰው ከሌሎች እንስሳት በተለየ ሕመም እና ደስታን (Pain and Pleasure) በቋንቋ መግለፅ ይችላል፡፡ የቋንቋ ችሎታውን በመጠቀም መከፋቱንና ደስታውን፣ ድጋፍና እና አቤቱታውን በቀጥታ በንግግር፣ በፅሁፍ ወይም በሰልፍ መግለፅ ይችላል።

በመሆኑም፣ እያንዳንዱ ግለሰብ በግል እና በቡድን የሚያደርገው ማህበራዊ ግንኙነት በዚህ ተፈጥሯዊ ባህሪ ላይ የተመሰረተ መሆኑን በመጥቀስ፣ “ሰው ፖለቲካዊ እንስሳ ነው!” (Man is a political animal) ይላል “Aristotle”። አባባሉ “ሰው ፖለቲካዊ እንስሳ ነው” ሲባል በአንድ ነገር ላይ የተሰማውን ጥሩም ይሁን መጥፎ ስሜት በግል ወይም በቡድን በቃል ንግግር፣ በወረቀት ፅሁፍ ወይም እንደ ዛሬው በአደባባይ ሰልፍ የመግለፅ ተፈጥሯዊ ባህሪ እንዳለው ያሳያል።

በአጠቃላይ፣ ሰው በአንድ ነገር ላይ የተለያየ አመለካከት መያዙና ሃሳቡን መግለፁ ተፈጥሯዊ መለያ ባህሪው ነው። ለዚህ ነው ዓለም-አቀፍ ድንጋጌዎችም ሆኑ ሀገር-አቀፍ ሕጎች ሰው ያለማንም ጣልቃ-ገብነት የመሰለውን አመለካከት መያዝና ሃሳቡን የመግለፅ ነፃነት እንዳለው የሚደነግጉት። ምክንያቱም፣ ይህ የሰው-ልጅ ተፈጥሯዊ ባህሪ እንጂ በሌላ አካል ፍቃድና ይሁንታ የሚሰጥ አይደለም።

የኢፊዴሪ ሕገ-መንግስት አንቀፅ 30 ለዚህ ጥሩ ማሣያ ነው።  

“ማንኛውም ሰው ከሌሎች ጋር በመሆን ማሣሪያ ሳይዝ በሰላም የመሰብሰብ፣ ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ ነፃነትና አቤቱታ የማቅረብ መብት አለው። ከቤት ውጪ የሚደረጉ ስብሰባዎችና ሰላማዊ ሰልፎች በሚንቀሳቀሱባቸው ቦታዎች በሕዝብ እንቅስቃሴ ላይ ችግር እንዳይፈጥሩ ለማድረግ…አግባብ ያላቸው ስርዓቶች ሊደነገጉ ይችላሉ።”

ከላይ በጥቅሱ ውስጥ እንደተጠቀሰው፣ በሕዝብ እንቅስቃሴ ላይ ችግር እንዳይፈጠር በሚል የሚወጣ ማንኛውም ዓይነት ስርዓት ከሕገ-መንግስቱ መሰረታዊ መርህ ጋር የሚጋጭ መሆን የለበትም። ሰላማዊ ሰልፉ በሚካሄድበት ቦታ የሚመለከተውን የመንግስት አካል ከማሳወቅ በስተቀር ሌላ ፍቃድ መጠየቅም ሆነ መጠበቅ የለበትም። ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ የሚካሄድበትን ቦታና ግዜን ከማሳወቅ ሌላ ፍቃድ የሚጠይቅ አሰራር ሊኖርም አይችልም። እንዲህ ያለ አሰራር ቢኖርም እንኳን ሕገ-መንግስቱን የሚጥስ ስለሆነ በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት የለውም።

ከዚህ አንፃር፣ የአማራ ክልል መንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ፅ/ቤት በጎንደር ከተማ ለሚደረገው ሰለማዊ ሰልፍ “ፍቃድ አልሰጠሁም” ሲል ያወጣው መግለጫ በራሱ በቂ ማስረጃ ነው። ምክንያቱም፣ በሕገ-መንግስቱ መሰረት በሰላማዊ ሰልፍ ተቃውሞና አቤቱታን ለመግለፅ የሚጠበቀው ማሳወቅ ብቻ ነው። የክልሉ የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ፅ/ቤት “በጎንደር ከተማ ነገ ለሚደረገው ሰላማዊ ሰልፍ ፍቃድ አልሰጠሁም” በማለት የሰጠው መግለጫ በራሱ ሰላማዊ ሰልፉ እንዲካሄድ ከመፍቀድ ጋር እኩልና አንድ ነው። በመሰረቱ ከሕዝቡ የሚጠበቀው ማሰወቅ ብቻ ስለሆነ የፅ/ቤቱ መግለጫ የክልሉ መንግስት ማወቅ ያለበትን አውቋል ማለት ነው። በአጠቃላይ፣ “ሰላማዊ ሰልፍ እንዲካሄድ አልፈቀድኩም” ማለት በራሱ “ፈቅጄያለሁ” እንደማለት ነው። 

መንግስት ማለት የጋራ ሰላምና ደህንነታችንን እንዲያስከብርልን በሚል ውክልና የተሰጠው አካል ነው። በውላችን (ሕገ-መንግስት) መሰረት ራስን-በራስ የማስተዳደር ስልጣናችንን እና የሀብታችንን አሳልፈን ሰጠነው። ሕዝብ የሰጠውን ስልጣንና አቅም ተጠቅሞ የብዙሃኑን መብትና ጥቅም ከማረጋገጥ ይልቅ የህዘቡን መብት ወደጎን ትቶ የራሱን ጥቅም አስቀደመ።

በህዝብ ፍቃድ ላይ የተመሰረተ መንግስት ያለእሱ ፍቃድ መናገር አትችሉም ሲል፣ ሕዝብ ወካይ፣ መንግስት ተወካይ መሆኑ ቀርቶ ነገሩ የተገላቢጦሽ ሆነ። መንግስት በተግባር ማስከፋቱ ሳያንስ፣ ህዝብ “ከፍቶኛልና አቤቱታዬን አደባባይ ወጥቼ ላሰማ” ሲል ያለእኔ ፍቃድ አይሆንም ይላል። ሲጀመር ሕዝቡን ያስከፋው እኮ መንግስት ነው፡፡ ያስከፋውን ሕዝብ አቤቱታውን እንዲገልፅ ፈቃጅ መሆን የሚሻውም መንግስት ነው። አንዴት ሕዝብን አስከፍቶ አቤቱታውን አልሰማም ይላል? ታዲያ ሕዝብን አስከፍቶም-ገፍቶም ይቻላል እንዴ?

በእርግጥ ዛሬ በጎንደር ከተማ የታየው ሰላማዊ ሰልፍ “ሕዝብን አስከፍቶም፣ ገፍቶም” መቀጠል እንደማይቻል ነው። በመጀመሪያ፣ የሚገፋውን አካል ገፍትሮ በመውጣት መከፋቱንና ብሶቱን ይገልፃል። በቀጣይ ሲመጣ ግን አስከፍቶ የሚገፋውን መንግስት ገፍትሮ ይጥለዋል። በኃላ ላይ ከመገፍተር አሁን መማር የሚበጅ ይመስለኛል።

******

Seyoum Teshome is a Lecturer at Ambo University Woliso Campus and head of Management Department. He was born in Arsi, Assela, in 1979 and studied Management at Harameya University and MBA at Mekelle University. He also blogs at http://ethiothinkthank.com

more recommended stories