የአብዮት እና የዴሞክራሲ ትውልድ ግጭት

የቀድሞ የኢትዮጲያ አየር ኃይል አዛዥ ሜጀር ጄኔራል አበበ ተክለሃይማኖት ግንቦት ሃያን አስመልክቶ ከሪፖርተር ጋዜጣ ጋር ያደረጉትን ቃለ-ምልልስ አነበብኩት። ከቃለ-ምልልሱ ውስጥ በእሳቸው ዘመን ትውልድና በአዲሱ ትውልድ መካከል ስላለው ልዩነት የተናገሩት ነገር በጣም ትኩረት የሚስብ ነው። ከሁሉም በላይ ግን፣

“…ኢሕአዴግ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ የእኛ ትውልድ የአማፂ ትውልድ ነው። የአማፂ ትውልድ የዴሞክራሲ ትውልድ መሆን አይችልም። …ስለዚህ የእኛ ትውልድ የዴሞክራሲ ትውልድ አይደለም። የአመፅ ትውልድ ነው።”

የሚለው አስተያየት በጣም አስገርሞኛል። ከመገረም ባለፈ በሁለቱ ትውልዶች መካከል ያለውን ልዩነት በዝርዝር እንድመለከት ምክኒያት ሆኖኛል። ወደ ዝርዝር ጉዳዩ ከማለፌ በፊት ግን፣ በቅድሚያ ለሜ/ጄ አበበ ተክለሃይማኖት ያለኝን አክብሮት መግለፅ እፈልጋለሁ።

ብዙዎች በራሳቸው ትውልድ እሳቤ ውስጥ መሸሸግ ይመርጣሉ። ወደ እውነት ከመሄድ ይልቅ፣ እውነት ወደ እነሱ እንድትመጣ ይጠብቃሉ። ነገር ግን፣ ሰው እውነትን ፍለጋ ይሄዳል እንጂ እውነት ሰውን ፈልጎ አይመጣም። ከዚህ አንፃር ሜ/ጄ አበበ ብዙ ርቀት የተጓዙ ይመስለኛል። በሁለት ትውልዶች መካከል ያለውን መሰረታዊ ልዩነት ለመረዳትና ይህንንም ለማሳወቅ ያደረጉት ጥረት የሚያስመሰግን ነው። ለሁሉም ነገር “ድሮ ቀረ…” ማለት በሚያዘወትረው ማህብረሰብ ውስጥ “ድሮ ቀረ፣ በአዲስ ተቀየረ…” የሚል ሰው መገኘቱ በራሱ ትልቅ ነገር ነው። በአጠቃላይ፣ “እኔ ብቻ ልክ ነኝ” በሚል “አክራሪ” ትውልድ ውስጥ ስህተትን ለመቀበል ዝግጁ በመሆናቸው ብቻ ለሜ/ጄ አበበ የተለየ አክብሮት አለኝ። 

ከላይ ወደ ተነሣው ሃሳብ ስንመለስ፣ ሜ/ጄ አበበ የእሳቸው ትውልድ ለዴሞክራሲ የማይመች አማፂ ትውልድ መሆኑን በግልፅ አስረድተዋል። አሁን በስልሳዎቹ አማካይ እድሜ ላይ ያለው አመፂ ትውልድ (የሜ/ጄ አበበ የእድሜ እኩያዎች) እና በአዲሱ ትውልድ መካከል ትልቅ ልዩነት ተፈጥሯል። ይህ ልዩነት ሀገሪቱን ወደ ለየለት ግጭት እየወሰዳት ይገኛል። ይህ ነገር አስቸኳይ መፍትሄ ካልተሰጠው ኢትዮጲያን ሁሉን-አቀፍ ወደ ሆነ ግጭት ውስጥ ያስገባታል። ግጭቱ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ፣ እንዲሁም ወታደራዊ ሊሆን ይችላል። ከዚህ ግጭት ነፃ የሆነ ቀጠና ወይም ገለልተኛ የሆነ አካል ሊኖር አይችልም። ምክንያቱም ይህ ግጭት የትውልድ ግጭት ነውና። አዎ…የሁለት ዘመን ሰዎች፡- የአብዮት እና የዴሞክራሲ ትውልድ ሰዎች ወደ ግጭት እያመሩ ነው። 

በየትኛውም ሀገር የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ላይ የሁለት ትውልድ አሻራ ያርፍበታል። የአብዮታዊው ትውልድ እና የዴሞክራሲያዊው ትውልድ አሻራ። በመጀመሪያ ደረጃ ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ የሚያስፈልገውን መሰረት የሚያቆመው የአብዮቱ ትውልድ ነው። በመቀጠል፣ የግንባታ ሂደቱን በማስቀጠል ከፍፃሜ የሚያደርሰው ደግሞ የዴሞክራሲ ትውልድ ነው። ይህን ሂደት በአግባቡ ለማስቀጠል ሁለቱ ትውልዶች የኃላፊነትና የሥልጣን ርክክብ ሊያደርጉ ይገባል። ይህ ካልሆነ ግን፣ በአብዮት የተገነባው የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መሰረት በሌላ አብዮት ይፈርስል። የግንባታ ሂደቱ ይቋረጣል፣ የተገነባው መሰረት ፈርሶ፣ ሂደቱ እንደ አዲስ ከዜሮ ይጀምራል። አሁን ባለው ሁኔታ ኢትዮጲያ ወደዚህ አጣብቂኝ እየገባች ነው፤ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ሂደቱን ማስቀጠል ወይም እስካሁን የተገነባውን አፍርሶ እንደ አዲስ ከዜሮ መጀመር።

ለግጭቱ ዋና መነሻ ምክንያት፣ ሜ/ጄ አበበ ተክለሃይማኖት “የእኛ ትውልድ” ያሉት፣ በኢትዮጲያ ዘመናዊ ታሪክ “የአብዮት ትውልድ” የሚባለው፣ ሀገሪቱን የመምራት ኃላፊነትና ሥልጣንን ሙሉ-ለሙሉ ለተተኪው ትውልድ ለማስረከብ ዳተኛ ስለሆነ ነው። በእርግጥ አሁንም በአብዛኛው የአመራር ሚና እየተጫወተ ያለው የ1960ዎቹ ትውልድ ነው። ነገር ግን፣ የአንድ ትውልድ ዘመን አማካይ እድሜ 30 ዓመት እንደመሆኑ፣ የእዚህ ትውልድ ዘመን እስከ 1990ቹ ድረስ ብቻ ነው። ከዚያ በኋላ በሥልጣን ላይ በቆየባቸው አመታት ኮትኩቶ የሚያሳድገው የዴሞክራሲ ቡቃያን ሳይሆን የአምባገነንነት አረምን ነው።

ጭቆናና አምባገነንነትን ታግሎ ለዴሞክራሲ መሰረት ያቆመ አብዮተኛ ትውልድ፣ ከቆይታ ዘመኑ በላይ በስልጣን ላይ በቆየ ቁጥር ራሱን ወደኋላ መልሶ ጨቋኝና አምባገነን ይሆናል። የዳበረ የፖለቲካ ሥርዓት ያላቸው ሀገራትን ተሞክሮ በአንክሮ ላስተዋለ፣ የአብዮት ትውልድ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ መሰረት ከማቆም ባለፈ ግንባታውን ከጫፍ አያደርስም።

በፅሁፉ መግቢያ ላይ እንደተጠቀሰው፣ ይህ አብዮተኛ ትውልድ በባህሪው ዴሞክራሲያዊ አይደለም። እንደ ሜ/ጄ አበበ አገላለፅ “የአማፂ ትውልድ” እሳቤና አመለካከት ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ግብዓት የሚሆን አይደለም። በአጠቃላይ፣ አብዮተኛ ትውልድ ዴሞክራሲያዊ ትውልድ አንፆ ያሳድጋል እንጂ ራሱን በራሱ ዴሞክራሲያዊ ማድረግ አይቻለውም። በዚህ መሰረት፣ የ1960ዎቹ አብዮተኛ ትውልድ የአሁኑን አዲስ – ዴሞክራሲያዊ ትውልድ ወልዶ አሳድጓል። ይህን ፅንሰ-ሃሳብ በግልፅ ለመረዳት በሁለቱ ትውልዶች መካከል ያለውን መሰረታዊ ልዩነት በዝርዝር መመልከት ያስፈልጋል።

በመጀመሪያ ደረጃ፣ የአብዮታዊ ትውልድ የፖለቲካ እንቅስቃሴ መነሻው ጭቆናና አምባገነንነት ሲሆን መድረሻው ደግሞ እኩልነትና የሕግ-የበላይነትን ማረጋገጥ ነው። ለዴሞክራሲ ትውልድ ፖለቲካ እንቅስቃሴ መነሻው የፍትህና መልካም አስተዳደር እጦት ሲሆን መድረሻው ደግሞ ፍትህና ነፃነትን ማረጋገጥ ነው። የብዙሃን እኩልነት ባልተረጋገጠበት ስርዓት ውስጥ የሚወጣ ሕግ የተወሰኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጥቅም ከማስከበር የዘለለ ፋይዳ የለውም። ስለዚህ፣ እኩልነት እንዲረጋገጥ ሁሉም ሰዎች እኩል የሚዳኙበት ሕግ ያስፈልጋል። በመሆኑም፣ እኩልነትን ለማረጋገጥ የሕግ የበላይነት መረጋገጥ አለበት። የሕግ-የበላይነት ባልተረጋገጠበት እኩልነት ሊረጋገጥ አይችልም። ለምሳሌ የቀድሞ ዘውዳዊ አገዛዝ የሀገሪቱን ዜጎች እኩልነት ያረጋገጠ አልነበረም። ይህን ሥርዓት በመቃወም የተጀመረው የፖለቲካ እንቅስቃሴ በዋናነት በእኩልነትና የሕግ-የበላይነት መርሆች ላይ የተመሰረተ ነበር።

የደርግ እና ኢሕአዴግ አመራሮች የዚህ ትውልድ አባል እንደመሆናቸው፣ የሁለቱም እንቅስቃሴ ተመሣሣይ ነበር፡- በሀገሪቱ ውስጥ አብዮታዊ ለውጥ በማምጣት እኩልነት እና የሕግ-የበላይነትን ማረጋገጥ። ዘውዳዊ ሥርዓትን በመገልበጥና በዚህም የብዙሃንን እኩልነት በማረጋገጡ ረገድ ደርግ፣ እንዲሁም ሕጋዊ መሰረት ያለው አስተዳደራዊ ስርዓት በመዘርጋቱ ረገድ ደግሞ ኢሕአዴግ ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል። በመሆኑም፣ አሁን በኢትዮጲያ ያለው ሥርዓት ደርግና ኢሕአዴግ በጋራ በወሰዷቸው የለውጥ እርምጃዎች የመጣ ነው። ደርግ በእኩልነት ላይ፣ በተለይ የመሬት ለአራሹ እና የከተማ መሬትና መኖሪያ ቤት አዋጆች የመሳሰሉት፣ እንዲሁም የኢሕአዴግ ሕገ-መንግስታዊ ሥርዓት፣ የአብዮተኛ ትውልዱ የመጨረሻ ግቦች ነበሩ/ናቸው። ይሁን እንጂ፣ እነዚህና የመሳሰሉት የዚያ ትውልድ የለውጥ እርምጃዎች በኢትዮጲያ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ የመሰረት ምንጣፍ ብቻ ናቸው። ይህ ከ1960ዎቹ -1990ዎቹ ባሉት የአንድ ትውልድ ዘመን ውስጥ ተፈፅሟል ማለት ይቻላል፡፡

የአብዮተኛ ትውልድ የመጨረሻ ግብ ለተተኪው የዴሞክራሲ ትውልድ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ መነሻ የሆነ መሰረት ማቆም ነው። ምክንያቱም፣ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መሰረታዊ ዓለማ ፍትህና ነፃነትን ማረጋገጥ መቻል ነው። ሁሉም የሀገሪቱ ዜጎች በእኩልነት በማይዳኙበት ስርዓት ውስጥ ፍትህ ሊኖር አይችልም። በሕገ-መንግስቱ የተቀመጡ፤ በነፃነት የማሰብ፣ የመናገርና የመፃፍ መብትን ማክብርና ማስከበር፣ እንዲሁም ሌሎች ዴሞክራሲያዊ መብቶችን ማረጋገጥ እስካልተቻለ ድረስ የሕግ-የበላይነት ሊረጋገጥ አይችልም።  ፍትህና ነፃነትን በሌለበት እኩልነትና የሕግ-የበላይነት ትርጉም አልባ መፈክሮች ናቸው። በመሆኑም፣ በአብዮት ትውልድ የእኩልነትና የሕግ-የበላይነት ያረጋገጥ እንጂ የመጨረሻ ግባቸው ግን ፍትህና ነፃነት ነው።

የአብዮት ትውልድ ፖለቲካ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት መነሻ ነው። የዚህ ትውልድ እንቅስቃሴ ዓላማው ግን ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን ማረጋገጥ ነው። የአብዮት እንቅስቃሴ ሲጀምር “የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች እኩልነትና የሕግ-የበላይነት ይረጋገጥ” የሚል መፈክር ይዞ ነው። የዚህ ዘመን ትውልድ ግን የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች እኩልነትን ተቀብሎ እና በሕግ-የበላይነት አመኖ፣ “ፍትህና ነፃነት ይከበር!” ብሎ ነው። የአብዮት ትውልድ እንቅስቃሴ የጀመረው “እኛ” በሚል እሳቤ ነው። አሁን ያለው የዴሞክራሲ ትውልድ እያነሳ ያለው ጥያቄ ግን “እኔ” በሚል እሳቤ ነው። “የእኛ” ጥያቄ የቡድን መብትን ስለማክበርና ማስከበር ነው። በቡድን መብት ውስጥ የእኛ፤ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የእኩልነት እና ይህን ለማረጋገጥ አስፈላጊ የሆነው የሕግ የበላይነት ይዘረጋል። “የእኔ” ጥያቄ የግለሰብ መብትን ስለማክበርና ማስከበር ነው። በግለሰብ መብት ውስጥ ፍትህና ነፃነት ይረጋገጣል። “እኛ” ብሎ የተነሳው ትውልድ መነሻ ግቡ አሮጌውን ሥርዓት በማፍረስ፣ መንግስታዊ መዋቅሩን በመቀየር የብዙሃንን እኩልነትና የሕግ-የበላይነትን ለማረጋገጥ ነው። “እኔ” ብሎ እየጠየቀ ያለው አዲሱ ትውልድ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለመገንባት የተነሳ ነው። ጥያቄው የመዋቅር ለውጥ ሳይሆን የአስተዳደራዊ ሥርዓቱን ማሻሻል ነው።

የአዲሱ ትውልድ ትግል ለድንገታዊ አብዮት ሳይሆን የዳበረ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለመገንባት ነው። የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታን ለማስቀጠል፣ በሁሉም የሕይወት ዘርፎች ለውጥና መሻሻል እንዲኖር፣ የአብዮቱ ትውልድ ሀገሪቱን የማስተዳደር ሙሉ ሥልጣንና ኃላፊነት ለአዲሱ ትውልድ ማስረከብ አለበት። ነገር ግን፣ ላለፉት አስር አመታት እንደታየው፣ የአብዮቱ ትውልድ ሥልጣንና ኃላፊነቱን ለማስረከብ ፍቃደኛ አይመስልም። በዚህ ምክንት፣ በሁለቱ ትውልዶች መካከል ግጭት ተፈጥሯል። የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ሂደቱን የሚያቋርጥ፣ እስከ አሁን የተገነባው መሰረት የሚያፈርስ ግጭት ተፈጥሯል። በአጠቃላይ፣ ግጭቱ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታን የማስቀጠል ወይም የማቋረጥ ጉዳይ ሆኗል።

**********

Seyoum Teshome is a Lecturer at Ambo University Woliso Campus and head of Management Department. He was born in Arsi, Assela, in 1979 and studied Management at Harameya University and MBA at Mekelle University. He also blogs at http://ethiothinkthank.com

more recommended stories