የደሞወዝ እድገት ቀርቶብኝ የአካዳሚክ ነፃነቴን ስጡኝ

በከፍተኛ የትምህርት ተቋም ውስጥ የ10 ዓመት የማስተማር ልምድ አለኝ። ላለፉት ሁለት ዓመታት ደግሞ የአንድ ት/ት ክፍል ኃላፊ ሆኜ እየሰራሁ እገኛለሁ። የማስተማር ሥራውን በጣም እወደዋለሁ። ከተማሪዎቼ ጋርም ልዩ ፍቅርና ቀረቤታ እንዳለኝ አምናለሁ። በሃሮማያ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ድግሪ አብረውኝ የተማሩ የክፍል ጓደኞቼ አብዛኞቹ በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ በመምህርነት በመቀጠር ነው ወደ ስራ አለም የገቡት። ሆኖም ግን፣ ከእነዚህ ውስጥ አብዛኞቹ ለትምህርት በተላኩባቸው የውጪ ሀገራት በመቅረት ኑሯቸውን እዚያ አድርገዋል። የሁለተኛ ድግሪ ት/ት የተከታተልኩት እዚሁ ሀገር ውስጥ በመቐለ ዩኒቨርሲቲ ነው። ምንም እንኳን ሁሉም የክፍል ጓደኞቼ ከምረቃ በኋላ በመምህርነት ለመቀጠል ከመጡበት ዩኒቨርሲቲ ጋር ከ2-4 ዓመት የሚደርስ ውል የገቡ ቢሆንም፣ በተመረቁ በዓመቱ ብዙዎቹ ከዩኒቨርሲቲ ለቀው በንግድ ባንኮችና ሌሎች መስሪያ ቤቶች ተቀጥረው እየሰሩ ይገኛሉ።

በሀገር አቀፍ ደረጃም ቢሆን ችግሩ እጅግ የከፋ ነው። ለምሳሌ፣ የኢትዮጲያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) አንድ ጥናትን ዋቢ አድርጎ ባቀረበው ዘገባ መሰረት፣ በኢትዮጲያ በየአመቱ እስከ 20ሺህ የሚደርሱ መምህራን እንደሚፈልሱ ተጠቅሷል። በአጠቃላይ፣ በአብዛኞቹ የሀገሪቱ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ በተለይ ደግሞ በሀገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ለሚታየው ከፍተኛ የመምህራን ፍልሰት ሁለት መሰረታዊ ምክንያቶች አሉ። አንደኛ፣ እንደ አብዛኞቹ የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት በሀገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥም የሙያና የሥራ ነፃነት አለመኖር ሲሆን፣ ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ የመምህራን ተጠቃሚነት ጋር ተያይዞ ያለው ችግር ነው። በዚህ ፅሁፍ፣ በዋናነት በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ላይ ትኩረት በማድረግ ጉዳዩን በዝርዝር ለማየት እንሞክራለን።

ከላይ በአንደኝነት የተጠቀሰውን ችግር በዝርዝር ለማስረዳት እንዲያመቸኝ የራሴን የግል ገጠመኝ እንድጠቅስ ይፈቀድልኝ። አጋጣሚው በ2008 ዓ.ም የመጋቢት ወር መጀመሪያ ላይ የሆነ ነገር ነው። አብዛኞቻችሁ እንደምታስታውሱት፣ ከህዳር – መጋቢት ባለው ግዜ፣ በተለይ በኦሮሚያ ክልል በሚገኙ የት/ት ተቋማት ውስጥ በክልሉ ከታየው የሕዝብ ተቃውሞ ጋር ተያይዞ የመማር-ማስተማር ሂደቱ በተደጋጋሚ ይቋረጥ ነበር። ለምን እንደሆነ ባላውቅም፣ እኔ በማስተምርበት ካምፓስ ውስጥ ተማሪዎች የትምህርት ማቆም አድማ የሚመቱት ሐሙስ ዕለት ነበር። እኔ ደግሞ ሐሙስ እለት ጠዋት ተመራቂ ተማሪዎች ጋር የምገባበት ክፍለ ግዜ ነው። በዚህ ምክንያት፣ ሐሙስ ዕለት ጠዋት ከእንቅልፌ እንደነቃሁ የመጀመሪያ ተግባሬ የሚሆነው በመስኮት የመማሪያ ክፍሎቹን መመልከት ነው። ተማሪዎቹ ወደ መማሪያ ክፍል ላለመግባት አድማ ሲመቱ በመማሪያ ህንፃው ላይ የአንድም ሰው አይኖርም።

ታዲያ ከዕለተ-ሐሙስ በአንዱ ከመማሪያ ክፍሎቹ አከባቢ ከወትሮው የተለየ የተማሪዎች ጩኸትና ፉጨት ተሰማ። ሁላችንም በድንጋጤ “ምንድነው?” ስንል፣ “3ኛ ዓመት ተመራቂ ተማሪዎች ያሰሩትን አዲስ ቲ-ሸርት ስለለበሱ” መሆኑን ተረዳን። በዚያን ሰሞን ጩኸትና ፉጨት ሰምቶ ያልበረገገ ሰው አልነበረም። ምክንያቱም፣ በእንዲህ ያለ ወቅት አንድ ግለሰብ ይቅርና፣ አንዲት ትርፍ ቃል እንኳን አመፅና ብጥብጥ ሊያስነሳ ይችላል። ለማስተማር ወደ ክፍል ስገባ ተማሪዎቹ ለእኔም አንድ ቲ-ሸርት ሰጡኝና እሱን እንድለብስ ይወተውቱኝ ጀመር። “እሺ” ብዬ በለበስኩት ልብስ ላይ የተማሪዎቹን ቲ-ሸርት ስደርብ በሽንኩርት የተሞላ ኩንታል አስመሰለኝ። በዚህ ምክንያት ወደ ቢሮ ሄድኩና፣ ጠዋት የለበስኩትን አውልቄና ተማሪዎቹ የሰጡኝን ቲ-ሸርት ማስተማር ቀጠልኩ። “ታዲያ ይሄ ምኑ ነው ገጠመኝ?” ልትሉ ትችላላችሁ። አዎ…እስካሁን የገለፅኩት አጋጣሚው የተከሰተበትን አውድ ለመግለፅ ያህል እንጂ ዋናው ጉዳይ ከዚህ በኋላ የሆነው ነው።

ከክፍል እንደወጣሁ የኮሌጁ ዲን ከእኔ ትምህርት ክፍል ሁለት ተማሪዎች ለስብሰባ እንደሚፈለጉ ነግሮች እነሱን ለማስጠራት ወደ ተማሪዎች መኖሪያ አከባቢ ሄድኩ። ወደዚያ እየሄድኩ ሳለ፣ አራት ካድሬዎች የእኔን ተማሪዎች በዙሪያቸው ሰብስበው ሲያናግሩ ከርቀት ተመለከትኩ። “ከርቀት ‘ካድሬ’ መሆናቸውን እንዴት አወቅክ?” ለሚለው መልሱ ቀላል ነው። በወፍራም ተክለ-ሰውነቱ ላይ ጃኬት የደረበና በእጁ አጀንዳ የያዘ ሰው ያለ ምንም ጥርጥር እሱ ካድሬ ነው። የእኔ ተማሪዎች እንደሆኑ ከርቀት የለየሁት ደግሞ ከላይ በጠቀስኩት ቲ-ሸርት አማካኝነት ነው። ከላይ እንደገለፅኩት፣ በዚያን ወቅት አራት ማንነታቸው ያልታወቀ ግለሰቦች ቀርቶ አንዲት ትርፍ ቃል እንኳን ለአመፅና ብጥብጥ በቂ ምክንያት ነበረች። ስለ ሰዎቹ ማንነት ለመጠየቅ እንዱን ተማሪ ወደ እኔ እንዲመጣ ስጠራው፣ ከአራቱ ሰዎች አንዱ ፍፁም ባልጠበቅኩት መልኩ “አንተ ራስህ ና!” አለኝ። በድጋሜ ተማሪውን ስጠራው በድጋሜ “አንተ ራስህ ና!” አለኝ። በተማሪዎቼ ፊት እንዲህ ማለቱ በጣም ስላናደደኝ “አንተ ራስህ ና!” አልኩት። በመቀጠል፣ በጣም ትልቅ ተክለ-ሰውነት ያለው ሰውዬ ወደ እኔ መጣና እጅግ በሚያስጠላ ንቀት “ማን ስለሆንክ ነው “ና” ስትባል የማትመጣው?” ሲለኝ ”እኔ ስለሆንኩ!” አልኩት። “ማን ነህ አንተ?” ሲል “ስዩም” ብዬው ወደ ቢሮ ተመልሼ መሄድ ጀመርኩ።

በእርግጥ ከላይ እንደገለፅኩት፣ ከላይ የለበስኩት ቲ-ሸርት ከተማሪዎቹ ጋር አንድ ዓይነት ስለሆነ ተማሪ ሊመስለው ይችላል። ነገር ግን፣ ተማሪዎቹ መምህርና የት/ት ክፍሉ ኃላፊ መሆኔን ከነገሩት በኋላ ያደረገው ነገር ስህተቱ ባለማወቅ ሳይሆን በማን-አለብኝነት ንቀት የተፈፀመ እንደሆነ ያሳያል። ይህ ሰው ወደ በሮዬ ተመልሼ ስሄድ በአከባቢው ከነበሩት የካምፓስ ፖሊሶች አንዱን ጠርቶ እንዲይዘኝ አዘዘ። እኔ በኃላፊነት በምሰራበት መ/ቤት መጥቶ እኔ እንድታሰር ለማዘዝ መድፈሩ አስገረመኝ። ወዲያው ቢሮ ሄጄ ስለማንነታቸው ስጠይቅ “የኢህአዴግ አደረጃጀት ኃላፊዎች ናቸው” የሚል ምላሽ ተሰጠኝ። ከየት እንደመጡ ስጠይቅ የተሰጠኝ ምላሽ ግን በጣም ያስቃል። አራቱም ሰዎች እዚያው እኔ በማስተምርበት ዩኒቨርሲቲ ያሉና ለኢህአዴግ የአደረጃጀት ሥራ የሚሰሩ የፓርቲ ተወካዮች መሆናቸውን ተረዳሁ።

ጉዳዩ በዚህ ብቻ አላበቃም። ወደ የበላይ አለቃዬ ሄደው ከሰሱኝ። “በንቀትና ሥነ-ስርኣት በጎደለው መልኩ አመናጭቆናል” በማለት ያቀረቡትን ክስ በከፊል እኔም እቀበላለሁ። ምንም እንኳን እነሱም በተመሣሣይ ቢያመናጭቁኝም፣ እኔም እንደ እነሱ ማድረግ እንዳልነበረብኝ አምናለሁ። የእነሱ ክስ ግን ይህ ብቻ አልነበረም። “ከተማሪዎች ጋር አንድ ዓይነት ልብስ በመልበስ የአለባበስ ሥርዓት የሌለኝ መሆኑ፤ ከፍተኛ የብቃት ችግር ስላለብኝ እንደ እኔ ያለ ሰው የዩኒቨርሲቲ መምህር ሆኖ መቀጠሉ በራሱ አሳፋሪ እንደሆነ፤ በተማሪዎቹ ቲ-ሸርት ላይ ያለውን፡ “We envision, plan & work for the future. So, we are the future – Managers” የሚለውን ድብቅ አጀንዳ የያዘ ፅሁፍ ለተማሪዎቹ በመስጠት ለአመፅ በማናሳሳት፣ …ወዘተ” በሚል ተከሰስኩ። የእኛ ማህብረሰብ ስለ ራስ ብቃትና ችሎታ ለመናገር ያለንን የራስ-መተማመን ወደ ባዶ ጉረኝነት ደረጃ ስለሚያወርደው፣ “ስለ እኔ ብቃትና ችሎታ አስተማሪዎቼና ተማሪዎቼ ይመስክሩ” ብዬ አልፈዋለሁ። ከዚያ በተረፈ ያለው ውንጀላ ግን ምላሽ እንኳን አይገባውም።

እርግጠኛ ባልሆንም፣ እንዲህ ያለ አሰራር የተጀመረው ከ1997 ዓ.ም በኋላ ይመስለኛል። ይሁን እንጂ፣ አንድ ራሱን-በራሱ በሚያስተዳድር ተቋም ውስጥ ገዢው ፓርቲ የራሱን የፖለቲካ አደረጃጀት የሚሰሩ ተወካዮች ማስቀመጡ በምንም አግባብ ቢሆን ተቀባይነት የለውም። በእርግጥ እነዚህ ተወካዮች ለመንግስትና ለፓርቲው ውሳኔ ግብዓት የሚሆኑ የማሻሻያ ሃሳቦችና አስተያየቶች ያቀርባሉ ተብሎ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን፣ በዚህ መልኩ በድብቅ ከሚሰበሰብ መረጃ ይልቅ ከጉዳዮ ባለቤቶች በቀጥታ የሚሰነዘሩ ትችቶችና ነቀፋዎች ጥሩ ግብዓቶች ናቸው። በተጠቀሱት የኢህአዴግ የአደረጃጀት ኃላፊዎች ተጠናቅረው የሚቀርቡ መረጃዎች የበላይ የመንግስት ኃላፊዎችን ለተሳሳተ ውሳኔ ይዳርጋቸዋል። ከዚህ አንፃር፣ ለምሳሌ በቅርቡ የትምህርት ሚኒስትሩ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ በሰጡት ቃለ-ምልልስ ላይ “የመምህራንን ኑሮ እና አለባበስ የሚያሻሽል” በማለት የተናገሩት የሚጠቀስ ነው። የሚኒስትሩ አስተያየት በዚህ ፅሁፍ እንደ ማሳያ ከተጠቀሰው ክስተት ጋር ተያያዥነት አለው እያልኩ አይደለም። ከላይ የተጠቀሰው ጣልቃ-ገብነት እንዳለ ሆኖ፣ መንግስት ለመምህራን የሚሰጡ የተለያዩ ጥቅማ-ጥቅሞችን ከማሳደግ ባለፈ፣ የመምህሩን ልብስ ዓይነትና ስፋት መቆጣጠር ከጀመረ ግን የግለሰብና የሙያ ነፃነት ብሎ ነገር ከእነአካቴው ይጠፋል። አሁን በጣም በዛ የተባለው የመምህራን ፍልሰት በእጥፍ ያድጋል የሚል እምነት ነው ያለኝ።

የትምህርት ሚኒስትሩ ሰኔ 11/2008 ዓ.ም “ለመምህራን የሚሰጡ ልዩ ልዩ ጥቅሞችን ይፋ” ባደረጉበት ንግግር ውስጥ ዋና ትኩረቴ የነበረው “የመምህራን አለበባበስ” የምትለዋ ሐረግ ተደግማ እንደሆነ ማረጋገጥ ነበር። ነገር ግን፣ በተለያዩ የዜና ዘገባዎች ውስጥ ብፈልጋት አጣኋት። እንዲህ ያሉትን የግለሰብና የሙያ ነፃነትን የሚጋፉ ተግባራትን ማስቀረት መልካም ነው። ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ በተለይ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ ከአገልግሎት ጋር ተያይዞ ያሉት ችግሮች በአዲሱ ማሻሻያ መፍትሄ ሊሰጣቸው ይገባል።

ሰሞኑን ይፋ በተደረጉት ለመምህራን የሚሰጡ ልዩ ልዩ ጥቅሞች ውስጥ የብዙዎችን ትኩረት የሳበው ከደሞዝ እርከን አንፃር የተደረገው ማሻሻያ ነው። በኢትዮጲያ የክፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ ለሚሰሩ የአካዳሚክ ዘርፍ ሰራተኞች ሰባት የሥራ ደረጃዎች አሏቸው። እነሱም፡- ረዳት ምሩቅ-1፣ ረዳት ምሩቅ-2፣ ረዳት ሌክቸረር፣ ልክቸረር፣ ረዳት ፐሮፌሰር፣ አሶሴት ፐሮፌሰር እና ፐሮፌሰር ናቸው። በቅደም ተከተል ረዳት ምሩቅ-1 እስከ ረዳት ሌክቸረር ድረስ ያለው የደረጃ እድገት በቆይታ ግዜ የሚወሰን ነው። ከሌክቸረርነት ጀምሮ ባሉት ደረጃዎች ግን እድገት የማግኘቱ እድል በተጨማሪ የትምህርት እድል ወይም በጥናትና ምርምር ሥራዎች አማካኝነት የሚገኙ ናቸው።

አሁን ባለው አሰራር መሰረት፣ መምህራን ከደረጃ እድገቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ሰፊ የትምህርት እድል እና ለጥናትና ምርምር ሥራዎች ምቹ የሆነ ሁኔታ መፈጠር አለበት። የሁለተኛና ሦስተኛ ድግሪ ትምህርትን በሀገር ውስጥ ሆነ በውጪ ዩኒቨርሲቲዎች ለመከታተል ያለው እድል እጅግ በጣም ጠባብ ነው። በአብዛኞቹ የሀገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ያለው አሰራር የጥናትና ምርምር ሥራዎችን ለመስራት አመቺ አይደለም። ለምሳሌ፣ እኔ በምሰራበት ዩኒቨርሲቲ አንድ መምህር በዩኒቨርሲቲው የበጀት ድጋፍ ለሚሰራው የጥናትና ምርምር ሥራ ለሚያጠፋው የግል ግዜና ዕውቀት ክፍያ መጠየቅ አይችልም። አሁን ባለው አሰራር መሰረት፣ የዩኒቨርሲቲው በጀት የሚውለው ለምርምር ሥራው እንጂ ሥራውን አስቦ፣ አቅዶና ሰርቶ ለሚያቀርበው ተመራማሪ የሚውል በጀት የለም። በዚህ መልኩ፣ በጥናትና ምርምር ሥራ ውስጥ ለመሳተፍ የሚያነሳሳ ነገር የለም። በመሆኑም፣ የመምህራኑ የደረጃ እድገት በጠባብ የትምህርት ዕድልና በነፃ መስራት በሚጠይቅ የጥናትና ምርምር ሥራ ላይ የታጠረ ነው። ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ የመምህራኑ የአገልግሎት ዘመን እና ልምድ በደረጃ እድገቱ ውስጥ ታሳቢ አይደረጉም። ለምሳሌ፣ እኔ በግሌ በሌክቸረርነት ማዕረግ የ3 ዓመት የማስተማር ልምድ ያለኝ ቢሆንም የማገኘው ደሞወዝ በተጠቀሰው የት/ት ደረጃ ዜሮ ዓመት የሥራ ልምድ ካለው መምህር ጋር እኩል ነው። በተመሣሣይ፣ ሁለተኛ ድግሪውን ከያዘ በኋላ ለ9 ዓመት ያስተማረ መምህር የሚያገኘው ደመወዝ በተጠቀሰው የት/ት ደረጃ የ3ዓመት ልምድ ብቻ ካለው ጋር እኩል ነው። 

ከላይ ለማሳየት የተሞከረው፣ ገዢው ፓርቲ እንደ ሁሉም የሀገሪቱ ሲቨል ሰርቪስ ተቋማት፣ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሥራና አሰራር ውስጥ ያለውን ጣልቃ-ገብነት ማስወገድ አለበት። ከዚህ በተጨማሪ፣ የመምህራን የደረጃና የጥቅማ-ጥቅሞች እድገት የአገልግሎት ዘመንና ልምድን ታሳቢ ሊያደርጉ ይገባል። ለእነዚህ ሁለት መሰረታዊ ችግሮች ዘላቂ የሆነ መፍትሄ መስጠት እስካልተቻለ ድረስ በዘርፉ የሚታየውን ከፍተኛ ፍልሰት ማስቆም የሚቻል አይመስለኝም። በአጠቃላይ፣ እንደ አንድ የዩኒቨርስቲ መምህር ከምንም በላይ የሙያና የሥራ ነፃነት ያስፈልገኛል፡፡ ነፃነት የሌለው መምህር እንኳን ዜጎችን በዕውቀት ሊያንፅ ራሱን ከፍርሃት ቆፈን ማላቀቅ ይሳነዋል።

*********

Seyoum Teshome is a Lecturer at Ambo University Woliso Campus and head of Management Department. He was born in Arsi, Assela, in 1979 and studied Management at Harameya University and MBA at Mekelle University. He also blogs at http://ethiothinkthank.com

more recommended stories