ኢትዩጲያ ውስጥ “ምሁር” አለ እንዴ?

በተለያዩ ሚዲያዎች፤ “አንዳንድ የዘርፉ ‘ምሁራን’ በሰጡት አስተያየት…፣ ‘ከምሁራን’ ጋር በተደረገ ውይይት…” ሲባል መስማት የተለመደ ሆኗል። እንደው በየቦታው “ምሁራን” ሲባል ስቅጥጥ ይለኛል። ምክንያቱም፣ ክብር ያለ ቦታው ሲሰጥ ትርጉም ያጣል። በዚህ ፅሁፍ፣ ከግል ሰብዕና፣ ሥራና ተግባር አንፃር “ማን ነው ‘ምሁር’ (Intellectual)?” የሚለውን በዝርዝር እንመለከታለን።

የኣማርኛ መዝገበ ቃላት “ምሁር” የሚለውን ቃል “በትምህርት፥ በዕውቀት የበሰለ አዕምሮ ያለው ሰው” እንደሆነ ይጠቅሳል። በዚህ መሰረት፣ ምሁር ሲባል፤ በትምህርት ዕውቀት የቀሰመ፣ በዚህም ሰፊ ግንዛቤ ያለው፣ ነገሮችን ከተለያየ አቅጣጫ ማየትና ማገናዘብ የሚችል ሰው ነው።

ምሁር ለመሆን ትምህርት መማር፣ መመራመርና ማወቅ ያስፈልጋል። ለማወቅ የሚማር ሰው “ተማሪ” ይባላል፣ ለዕውቀት የሚመራመር ሰው “ተመራማሪ” ሲባል፣ ሌሎችን ለማሳወቅ የሚያስተምር ደግሞ “መምህር” ይባላል። ነገር ግን፣ ከእነዚህ ውስጥ አንዱም “ምሁር” ለሚለው ቃል በአቻነት የሚጠቀስ አይደለም። በእርግጥ “መምህር” የሚያውቀው ለማሳወቅ የሚሰራ እንደመሆኑ ቃሉ “ምሁር” ከሚለው ጋር ተቀራራቢ ሊመስል ይችላል። ሆኖም ግን፣ “መምህር” የሚለው ቃል ቀጥተኛ ፍቺ “በማስተማር ሙያ ላይ የተሰማራ ሰው” የሚል ነው። ለረጅም ግዜ ማስተማር፣ እንደ ማንኛውም የሙያ ዘርፍ፣ ልምድና ክህሎቱን ያሳድጋል እንጂ መምህርን “ምሁር” አያደርገውም።

በመሰረቱ፣ ምሁር ለመሆን መማር ያስፈልጋል፣ በትምህርት ደግሞ ዕውቀት ይገኛል። በዚህም ብዙ የተማረ ሰው ሊኖር ይችላል፣ ብዙ ነገር የሚያውቁ ሰዎች ይኖራሉ። ከእነዚህ ውስጥ ግን “ምሁር” ለመባል የሚበቁት በጣት የሚቆጠሩ ሰዎች ናቸው። በትምህርት የሚገኘው ዕውቀት በተግባር ለውጥና መሻሻል ካላመጣ ትምህርት መማሩና ማስተማሩ በራሱ ትርጉም የለውም። የአንድ ሰው በትምህርት የተገኘ ዕውቀት ፋይዳ የሚኖረው በራስና በሌሎች ሰዎች ሕይወት ላይ ትርጉም ያለው ለውጥ ማምጣት ሲያስችል ነው።

የምሁር ዕውቀት የሰዎችን ኑሮና አኗኗር ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሻሻል የራሱን አስተዋፅዖ ማበርከት አለበት፡፡ በእያንዳንዱ የዕውቀት ዘርፍ የሚደረግ ጥናትና ምርምር የሰዎችን ሕይወት በማሻሻል ላይ ማዕከል ያደረገ መሆን አለበት። ይህ ለሌሎች ሰዎች ሲባል የሚደረግ አይደለም። ከዚያ ይለቅ፣ በሰዎች ሕይወት እሴት የማይጨምር ነገር ለራሳችን ሆነ በሌሎች ሰዎች ዘንድ ፋይዳ-ቢስ ተደርጎ ስለሚወሰድ ዘለቄታና እርካታ አይኖረውም። ስለዚህ፣ አንድ ሰው በትክክል “ምሁር” ለመባል የሚበቃው ዕውቀቱን ከራሱ አልፎ በሌሎች ሕይወት ላይ ለውጥና መሻሻል ለማምጣት የሚጠቀምበት ከሆነ ነው፡፡ ምሁርነት ከዚህ አንፃር ታይቶና ተመዝኖ የሚሰጥ ክብር ነው። 

እስካሁን ድረስ “ምሁርነት” ከትምህርትና ዕውቀት ባለፈ በተግባራዊ እንቅስቃሴ የሚገኝ ከብር እንደሆነ ለማየት ሞክረናል። በመቀጠል ምሁራንን ልዩ የሚያደርጋቸውን ሥራና ተግባር እንመልከት። ለዚህ ደግሞ Edward Said በዚህ ጉዳይ የተሰጠውን ጥልቅ ትንታኔ እንደ መነሻ መውስድ ይቻላል። ፀኃፊው “ምሁር ማለት እንዴት ያለ ሰው ነው?” ለሚለው ጥያቄ እንዲህ ብሏል፤

“The intellectual is the individual endowed with a faculty for representing, embodying, articulating a message of you, attitude, philosophy or opinion to as well as for a public in public. This role has an edge to it, and cannot be played without the sense of being someone whose place it is, publically, to raise embarrassing questions, to confront orthodoxy and dogma rather than to produce them, to be someone who cannot easily co-opted by governments and corporations.”

“ምሁር” ማለት በህዝቡ ውስጥ እየኖረ የህዝብን ጥያቄ (መልዕክት)፣ አመለካከት፣ ፍልስፍና ወይም ሃሳብ ለመወከል፣ ለመያዝና ለመግለፅ የሚያስችል ብቃት የለው ግለሰብ ነው። ይህ የምሁራን ድርሻ የራሱ ደረጃ ያለው ሲሆን፤ በአደባባይ አሳፋሪ ጥያቄዎችን ለማንሳት፣ ኋላቀር አመለካከትንና ግትር ቀኖናዊነትን ለመጋፈጥ፣ እንዲሁም ለመንግስትና ተቋማት ፍላጎት በቀላሉ እጅ ላለመስጠት ድፍረትና ቁርጠኝነት የሌላቸው ሰዎች ሊወጡት እንደማይችሉ ተጠቅሷል። በዚህ መሰረት፣ “ምሁራን” ማለት ሃሳብና አስተያየታቸውን በአደባባይ በመግለፅ የህዝብን ጥያቄ የሚያንፀባርቁ፣ እንዲሁም ኋላ-ቀር አመለካከትና ግትር አቋምን በይፋ የሚሞግቱ ናቸው።

በእርግጥ ምሁራን ይህን የሚያደርጉት ከግል ወይም ከተወሰነ ቡድን ጥቅም አኳያ ሳይሆን በመሰረታዊ የነፃነትና የፍትህ መርሆች ላይ ተመስርተው ነው። በየትኛውም ግዜና ቦታ፤ የሰዎች ነፃነት ሲገፈፍና ፍትህ ሲዛባ በይፋ በመናገርና በመፃፍ ተቃውሟቸውን ይገልፃሉ። ነፃነትና እኩልነትን ሲረጋገጥም ድጋፍና ደስታቸውን በይፋ ይገልፃሉ። በአጠቃላይ፣ ምሁራን በትምህርት ዕውቀት ያገኛሉ፤ በዕውቀት ግለሰባዊ ነፃነትን ይጎናፀፋሉ። እነዚህ የነፃነትን ጣዕም የሚያውቁ በሁሉም ግዜና ቦታ ለሰው ልጆች ነፃነትና እኩልነት ይሟገታሉ፣ ድንቁርናና ጭቆናን ፊት-ለፊት ይጋፈጣሉ።

ከዚህ አንፃር፣ የኣማርኛ መዝገበ ቃላት “ምሁራን” ለሚለው ቃል “በትምህርት፥ በእውቀት የበሰለ አዕምሮ ያላቸው” በሚል የተሰጠው ፍቺ በእንግሊዘኛ ”Intellectuals” ከሚለው ቃል ጋር አብሮ አይሄድም። በአማርኛ “ምሁር” የሚለው ቃል ከትምህርትና ዕውቀት ክምችት የዘለለ ትርጉም አይሰጥም። ነገር ግን፣ እንደ Edward Said አገላለፅ፣ “ምሁርነት” በትምህርትና ዕውቀት ብቻ የሚገኝ ሳይሆን፣ የህዝብን ኑሮና አኗኗር ለመቀየር፣ የዜጎችን ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ሕይወት ለማሻሻል ከምናበረክተው አስዋፅዖ አንፃር ነው።

ምንም ዓይነት ትምህርት እንማር፣ ምንም ያህል ዕውቀት ይኑረን፣ በዙሪያችን ባሉ ሰዎች ሕይወት ላይ ለውጥና መሻሻል ማምጣት ካልቻልን ፋይዳ-ቢስ ነው። ትምህርትና ዕውቀት ለራሳችን ትርጉም፣ ለሌሎችም ፋይዳ የሚኖረው በማህበረሰቡ ውስጥ ለውጥና መሻሻል ለማምጣት ሲያስችለን ነው። ለዚህ ደግሞ ግለሰቦች በግል መስማት የማይፈልጉትን ነገር መናገር፣ በሕብረተሰቡ ውስጥ ያሉ ኋላ-ቀር ልማዶችን እና አሰራሮችን መተቸት፣ በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ሥርዓት ውስጥ የሚታዩትን ጨቋኝና አድሏዊ አሰራሮችን በግልፅ መተቸት፣ መንቀፍና የማሻሻያ ሃሳቧችን መጠቆም፣…ወዘተ በመሳሰሉ ተግባራት መሳተፍ ያስፈልጋል።

በአብዛኛው የኢትዮጲያ ከፍል ከላይ የተጠቀሰው ዓይነት ስብዕናና ተግባር ያላቸው ግለሰቦች መጠሪያቸው ስማቸው “ምሁር” የሚለው አይደለም። ኢትዮጲያ ውስጥ ኋላቀር አመለካከቶችና ልማዶች እንዲወገዱ፣ የፖለቲካ ንቃተ-ህሊና እንዲያድግ፣ የኢኮኖሚያ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ የሚተጉ ግለሰቦች መጠሪያቸው “ሙር” የሚል ነው። “ሙር” ማለት “የተማረና ዕውቀት ያለው ሆኖ ወፈፍ ስለሚያደርገው ብዙ የሚለፈልፍና የሚናገር፥ ንግግሩ ግን ፍሬ ነገር ያዘለ ሰው” ነው፡፡ እዚህ ሀገር ግን “ፖለቲካ እሳት ነው” እያለ ፈርቶ-የሚያስፈራራ ሁሉ “ምሁር” ሲባል ከፊት ቀድሞ ይሰለፋል።

ዩጋንዳዎች “የዝሆን ኩምቢ ያለ ቅጥ ያደገው በትችት እጥረት ምክንያት ነው” ይላሉ፡፡ የሀገራችን የኢኮኖሚ፣ ፖለቲካና ማህበራዊ እንቅስቃሴዎች በኋላ-ቀር አሰራሮች እየተዝረከረኩ፣ በትችት እጦት ምክንያት መንግስት እየተሳሳተ፣ ስህተቱን ለማረም ሌላ ስህተት እየተሳሳተ፣ ዜጎች በመልካም አስተዳደርና ፍትህ እጦት እየተሰቃዩ፣ አንዲት ቃል የማይወጣቸው ግለሰቦች “የምሁርነት” ክብር ሲሰጣቸው ትንሽ አይከብድም? ለዚህ ነው “ምሁር” የሚለው የክብር ስያሜ ያለ ቦታው ሲወድቅ ትርጉም ያጣ እየመሰለኝ ዘወትር ስቅጥጥ ይለኛል።

********

Seyoum Teshome is a Lecturer at Ambo University Woliso Campus and head of Management Department. He was born in Arsi, Assela, in 1979 and studied Management at Harameya University and MBA at Mekelle University. He also blogs at http://ethiothinkthank.com

more recommended stories