መግለጫ፡- “የፖትሪያርክ ጽ/ቤት ጋዜጠኞችን በማሳደድ ወደር አልተገኘለትም”

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፖትሪያርክ ጽ/ቤት ጋዜጠኞችን በማሳደድ ወደር አልተገኘለትም።

መንግስት በጋዜጠኞች ላይ ማሳደዱንና ክስ መመስረቱን እያቋረጠ በሚገኝበት በዚህ ወቅት የቤተ ክርስቲያኒቷ አመራሮች ራሳቸውን ከሀገሪቱ ህግ የበላይ በማድረግ ማስተባበያ እና ምላሽ ለጋዜጠኞች ከመስጠት ይልቅ ምንም የህግ ጥሰት ያልፈጸመውን የሰንደቅ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ፍሬው አበበን ከሰው በማንገላታት ላይ እንደሚገኙ የኢትዮጵያ ብሄራዊ የጋዜጠኞች ህብረት ሪፖርት ተደርጎለታል።

ህብረታችን የፓትሪያርክ ጽህፈት ቤት ውሳኔ የሀገሪቱን ህግ ያላከበረና በማን አለብኝነት የተፈጸመ ሃላፊነት የጎደለው ተግባር በመሆኑ ያወግዘዋል።

መንግስት የሀገሪቱን ህግ የጣሰውን ይህን ተግባር ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ጣልቃ በመግባት እንዲያርምና ጫና ለመፍጠር ታስቦ የቀረበውን ተደራራቢ ክስ ውድቅ አድርጎ ለባልደረባችን ወገናዊነቱን እንዲያሳይ በጥብቅ እንጠይቃለን።

መላው የሀገራችን ጋዜጠኞችና የህብረታችን አጋሮች ሁሉ ይህንኑ ጉዳይ በሚመለከት የህብረታችን የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ከአለም አቅፉ የጋዜጠኞች ፈዴሬሽን፣ ከአፍሪካ ጋዘጠኞች ፌዴሬሽንና ከምስራቅ አፍሪካ ጋዜጠኞች ጋር በመቀናጀት በሚያወጣው ዝርዝር እቅድ መሰረት ንቁ ድጋፍና ተሳትፎ እንድታደርጉ ጥሪ እያቀረብን ዝርዝር ተግባሩን በቅርቡ የምናሳውቅ መሆኑን በጥብቅ እናስታውቃለን።

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ጋዜጠኞች ህብረት

ግንቦት 23 ቀን 2008

አዲስ አበባ

——-  

የአዘጋጁ ማስታወሻ፡- ሰንደቅ ጋዜጣ ላይ የወጣው ዜና እንደሚያትተው ከሆነ፤ ቤተ ክህነት ክሱን የመሰረተችው በመጋቢት 25 ቀን 2008 ዕትሙ ላይ “ፓትርያርኩ ለኢትዮጵያ የደህንነት ስጋት ለምዕመናን የድህነት ስጋት” በሚል ርዕስ የተፃፈውን ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ፅሁፍ በማተሙ ነው፡፡ ቤተ ክህነት ጋዜጠኛው አድርሶብኛል ላላቸው የህሊና ጉዳት በፍትሐ ብሔር የ100 ሺህ ብር ካሳ የጠየቀችበት ሲሆን፤ በወንጀል ክስ ደግሞ ፍርድ ቤት ቀርቦ በ5ሺህ ብር ዋስ አቀርቦ ክሱን በውጨ እየተከታተለ ነው፡፡

*******

Guest Author

more recommended stories