የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ ተወልደ ሙልጌታ፣ የካቲት 18/2008 ዓ.ም በሰጡት መግለጫ “የኢትዮጲያ መንግስት በታገቱት 80 ኢትዮጲያዊያን ምክንያት በኤርትራ ላይ ተመጣጣኝ ዕርምጃ እንደሚወስድ” ተናግረዋል። መግለጫውን ተከትሎ ከጋዜጠኞች፤ ታጋቾቹ ስለተያዙበት ሁኔታ፣ ማንነት እና መንግስት ሊወስደው ስላሰበው አፀፋዊ እርምጃ ዙሪያ ለቀረበላቸው ጥያቄ የሰጡት ምላሽ ግን በጣም የሚገርም ነው፦”ከዚህ በላይ ምንም ዝርዝር ማብራሪያ ልሰጥ አልችልም”።

በእርግጥ ቃለ አቀባዩ ስለታጋቾቹ ማንነት፣ ስለታገቱበት ሁኔታ ዝርዝር ማብራሪያ መስጠት አይችሉ ይሆናል። ነገር ግን፣ 80 ሰዎች በአንድ ሽፍታ መንግስትና ጋሻ-ጃግሬዎቹ ታፍነው ተወሰዱና 90 ሚ.ህዝብ ለምን ወደ ጦርነት እንደሚገባ ዝርዝር ማብራሪያ እንሻለን። መንግስት በጉዳዩ ዙሪያ ዝርዝር ማብራሪያ መስጠት እንደማይችል ገልጿል።  ታሪክ ግን በዚህ ዙሪያ ሰፊና ዝርዝር ማብራሪያ ይሰጣል። ስለዚህ፣ ከመቶ አመት በፊት በተመሣሣይ ችግር ምክንያት የተካሄደን ጦርነት ዋቢ በማድረግ በጉዳዩ ዙሪያ “ዝርዝር ማብራሪያ” ለመስጠት እንሞክራለን።

ከመቶ አመት በፊት፣ ሰኔ 28/1914 (እ.አ.አ) የተጀመረው የአንደኛው ዓለም ጦርነት (WWI) አሁን በኢትዮጲያና በኤርትራ መካከል ስላለው ሁኔታ ጥሩ ማሳያ ነው። በተጠቀሰው ዕለት የኦስትሪያ-ሃንጋሪ አልጋ-ወራሽ የነበረው “Franze Ferdinand” እና ባለቤቱ በሰርቢያ አሸባሪዎች በመገደሉ ምክንያት ሁለቱ ሀገራት ወደ ጦርነት ገቡ። ወዲያው ሩሲያና ፈረንሳይ ከሰርቢያ ጎን፣ ጀርመን ደግሞ ከኦስትሪያ-ሃንጋሪን ደግፈው ወደ ጦርነቱ ገቡ። እንዲህ…እንዲህ እያለ፣ የአንድ አሸባሪ ቡድን ጥቃት ከ15 የሚበልጡ ሀገራት የተሳተፉበት ጦርነት ለመሆን በቃ። በሁለት ሰዎች ሞት የተጀመረው ጦርነት ለ15 ሚ. በላይ ሰዎች ሞት፣ ለ20 ሚ. ሰዎች መቁሰል መነሻ ምክንያት ሆነ። ያን ያህል አሰቃቂ ጉዳት ካስከተለ በኋላ እንኳን የታሪክ ተመራማሪዎች “የ1ኛ ዓለም ጦርነት ለምን ተጀመረ?” ብለው ይጠይቃሉ።

አሁን በኢትዮጲያ እና ኤርትራ መካከል በፖለቲካ፣ ኢኮኖሚ እና በጦር-መሣሪያ የበላይነት ለመያዝ የሚደረገው ፉክክር ልክ የ1ኛው የዓለም ጦርነት ከመጀመሩ በፊት ከነበረው ሁኔታ ጋር ተመሣሣይ ነው። በእንደዚህ ያለ ሁኔታ ውስጥ፣ የ2 ሰዎች ሞት የዓለም ሀገራት ወደ ጦርነት እንዳስገባ ሁሉ፣ የ80 ሰዎች ታግቶ መወሰድ ሁለቱን ሀገራት ወደ ጦርነት ሊያስገባ እንደሚችል እርግጥ ነው። ሆኖም ግን፣ በአንደኛው ዓለም ጦርነት ተሳታፊ የነበሩ ሀገራት ከዚያን ዓይነት አሰቃቂ ጦርነት መቶ አመት ወደፊት ርቀው ሄደዋል። እኛ ግን እነሱ ከመቶ አመት በፊት በነበሩበት ሁኔታ ውስጥ ነው ያለነው።

ሀገራት መተባበር ካልቻሉ መተማመን ይሳናቸዋል። ላለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በኢትዮጲያ እና ኤርትራ መካከል ጦርነት እንጂ ትብብር አልነበረም። ሁለቱ መንግስታት ችግሮቻቸውን በጠረጴዛ ዙሪያ ተነጋግረው በመፍታት ትብብር መፍጠር ስላልቻሉ በሁለቱ ሀገራት መካከል መተማመን ሊኖር አልቻለም። በሁለቱ ሀገራት መካከል ሌላ ምንም አሳማኝ ምክንያት ሳይኖር የመተማመን መንፈስ ባለመኖሩ ብቻ ጦርነት ሊነሳ ይችላል። አንዱ በሌላኛው ላይ “የሃይል ዕርምጃ እወስዳለሁ” ሲል፣ ሌላኛውም “እርምጃ ሊወሰድብኝ ይችላል” እያለ ባለበት ሁኔታ ውስጥ የሚከሰቱ ነገሮች ወደ አልታሰበና ማለቂያ የሌለው ጦርነት ውስጥ ይገባል። በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በድርድርና በውይይት ሊፈታ የሚችል ነገር ሀገራቱን ወደ አሰቃቂ ጦርነት ውስጥ አስገብቷቸዋል። በተመሣሣይ፣ በተለያዩ የዲፕሎማሲ ዕርምጃዎች መፍትሄ ሊሰጠው የሚችል ነገር “የአፀፋ እርምጃ እንወስዳለን” በሚል የፖለቲካ ግብዝነት ኢትዮጲያና ኤርትራ ዳግም ወደ ጦርነት ሊገቡ የሚችሉበት ሁኔታ ተፈጥሯል።

አንድ መንግስት በልማትና ዴሞክራሲ ረገድ የህዝብን ጥያቄ መመለስ ሲሳነው በጦርነት የሀገራዊ አንድነት መንፈስ ለመፍጠር መሞከሩ የታወቀ ነው። ለዚህ ሲባል የሚያደርጋቸውን ትንኮሳዎች በተለያዩ የዲፕሎማሲ ዕርምጃዎች መፍትሄ መስጠት ሲገባ በጦርነት መፍትሄ ለመስጠት መሞከር ፍፁም ስህተት ነው። በመሰረቱ፣ ጦርነት የሚሻ መንግስትን ጦርነት መግጠም ሌባን ለሌብነቱ እንደ መሸለም ነው።

በኢትዮጲያና ኤርትራ መካከል ትብብር ላለመፈጠሩ የሁለቱም ሀገራት መንግስታት እኩል ተጠያቂ ናቸው። የሁለቱ ሀገራት የፖለቲካ መሪዎች እርስ-በእርስ መተማመንና መነጋገር ስለተሳናቸው ብቻ የሁለቱ ሀገራት ህዝቦች በጦርነት መከራና ሥቃይ ማየት የለባቸውም። በፖለቲካ መሪዎቻችን የዲፕሎማሲ አቅም ማነስ ወደ ጦርነት መግባት የለብንም።

በተለይ እኛ ኢትዮጲያኖች በድርቅ ምክንያት፤ 10.1 ሚሊዮን ሰዎች ራሳቸውንና ቤተሰባቸውን በበቂ ሁኔታ መመገብ ባልቻሉበት፣ 400,000 ህፃናት ለከፍተኛ ለምግብ ዕጥረት በተጋለጡበት፣ ከ2.5 ሚሊዮን በላይ ህፃናት ትምህርታቸውን በሚያቋርጡበት ሁኔታ ውስጥ እያለን ሺህዎችን ደግሞ በጦርነት ለሞትና ቁስለት መዳረግ አንሻም። እነዚህ በሚሊዮን እና በሺህ የተጠቀሱት ቁጥሮች ብቻ ሳይሆኑ የሀገራችን ዜጎች ናቸው። ለዕለት ጉርስ ከመጨነቅ ባለፈ የተሻለ ሕይወት የሚገባቸው ሰብዓዊ ፍጡሯን ናቸው፡፡

ኤርትራዊያኖችም ቢሆን በአስገዳጅ ውትድርና የሚሰቃዩ፣ በስደት ከሀገር-ሀገር የሚንከራተቱ፣ …እንደ እኔና እናንተ የመኖር ተስፋ ያላቸው ሰብዓዊ ፍጡራን ናቸው። ሁላችንም በመሪዎቻችን አቅም ማነስ፣ ለውይይትና ድርድር ፍቃደኛ ባለመሆን፣ ችግሮችን በሰለጠነ የፖለቲካ መንገድ መፍታት ስለተሳናቸው ብቻ ወደ አሰቃቂ ጦርነት መግባት የለብንም። 

*********

Seyoum Teshome is a Lecturer at Ambo University Woliso Campus and head of Management Department. He was born in Arsi, Assela, in 1979 and studied Management at Harameya University and MBA at Mekelle University. He also blogs at http://ethiothinkthank.com

more recommended stories