ድርቁ በደረቁ ሲቆጠር 10.2ሚ ድህነት፣ 2.5ሚ ድንቁርና፣ 0.7ሚ በሽተኛ ይሆናል!

በኢትዮጲያ የ”Save The Children” ዳይሬክተር ጆን ግራሃም (John Graham) በሀገራችን የተከሰተውን ድርቅ አስመልክቶ ለተባበሩት መንግስታት እና ለአለም-አቀፉ ማህብረሰብ ያቀረቡትን ጥሪ ትኩረት ሰጥቶ ለተመለከተ፣ በህፃናት እና እናቶች ሞትን ከመቀነስ አንፃር ሀገሪቷን 10 ዓመት ወደኋላ ሊመልሳት እንደሚችል መገንዘብ ቀላል ነው፡፡ የበጎ አድራጎት ድርጅቱ በኢትዮጲያ ያጋጠመው ድርቅ እና በሶርያ እየተካሄደ ያለው ጦርነት በአለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ የሰብዓዊ ቀውስ አደጋዎች እንደሆኑ ይጠቅሳል፡፡ በተለይ በኢትዮጲያ ባለፉት 50 ዓመታት ውስጥ ከታዩት ሁሉ የከፋ ድርቅ መከሰቱ ብቻ ሳይሆን፣ አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት እየታየ ያለውን ቸልተኝነት ችግሩን የበለጠ አሳሳቢ ያደርገዋል፡፡

በተለይ ድርቁ በእናቶችና ህፃናት ላይ የሚያስከትለው አካላዊና ስነ-ልቦናዊ ተፅዕኖ በጣም አስከፊ ከመሆኑም በላይ፣ በቀጣዩ ትውልድ ላይ ሳይቀር ጠባሳውን የሚያሳርፍ መሆኑ ለእኔ በጣም አሰቃቂ ሆኖብኛል። የችግሩ አስከፊነት በአይነ-ህሊናዬ እየተመላለሰ ላለፉት ሁለት ቀናት አዕምሮዬ በሃሳብ እንደተወጠረ ነው። በህሊናዬ እየተመላለሰ ያስጨነቀኝ ምስል ግን ብዙዎቻችሁን ግር ሊያሰኝ ይችላል።

የድርቁን አስከፊነት የሚያሳዩ የተለያዩ ፎቶዎች ብመለከትም በህሊና እየተመላለሰ ያስቸገረኝ ግን የእናቶች እና ህፃናት ምስል አይደለም። የተጎሳቆሉ እናቶች የታቀፏቸው አጥንታቸው የገጠጠ፣ አይናቸው የፈጠጠ ህፃናት አይታዩኝም። ከሰዎች እናት ይልቅ የሚታዩኝ አይጦች ናቸው፣ ከህፃናት ይልቅ በአዕምሮ የሚመላለሱት የአይጥ ግልገሎች ናቸው። ታዲያ፣ በድርቅ ስለተጎዳው አከባቢና ይህን ተከትሎ በሚከሰተው የምግብ እጥረት ተጠቂ ስለሚሆነው የሀገራችን ህዝብ፣ እንዲሁም በቀጣይ ትውልድ ላይ ስለሚያሳድረው ተፅዕኖ እያወራሁ፣ በሰው ፋንታ ስለአይጥ የማስብበት ምክንያት ምንድነው?

Photo credit Elias Meseret Taye (The Associated Press Reporter in Addis).
Photo credit Elias Meseret Taye (AP Reporter in Addis).

በሀገራችን ስለተከሰተው ድርቅና በቀጣይ ትውልድ ላይ ስለሚያሳርፈው አሉታዊ ተፅዕኖ ሳስብ ወደ አዕምሮ የሚመጣው በአንድ ጀርመናዊ የሥነ-አዕምሮ ሳይንቲስት በአይጦች ላይ ያደረገው ምርምርና ያገኘው ውጤት ነው። ይህ፣ “በአንድ ሀገር እንዴት እርቅና ይቅርታን ማስፈን ይቻላል?” በሚል በቢቢሲ ሬድዮ በተዘጋጀ የውይይት ፕሮግራም ላይ በማስረጃነት ቀርቦ የነበረ የምርምር ውጤት ነው። ምርምሩ በዋናነት በወላጆች እና ልጆች መካከል የፍርሃት ማስተላለፍ (Fear Transmission) መኖሩን ለማረጋገጥ የተደረገ ሲሆን፣ ችግር፥ መከራ፥ ጭንቀት፥ … እና የመሳሰሉ አስከፊ የሕይወት ገፅታዎች በቀጣዩ ትውልድ ላይ ስለሚያሳድሩት አሉታዊ ተፅዕኖ ጥሩ ማሳያ ነው፡፡ በድርቅ የተጎዳውን የሀገራችንን ህዝብ ከምርምር ውጤቱ ጋር ያለውን ተያያዥነት ለማስረዳት በቅድሚያ ስለምርምሩ ሂደቱ የተወሰነ ነገር ልበላችሁ።

ሙከራው (Experiment) የአስደሳች የምግብ ሽታን ከኤሌክትሪክ ንዝረት (Electric Shock) ጋር በአንድነት በማጣመር የተደረገ ነው። አስደሳቹ የምግብ ሽታ ለአይጦቹ እንዲደርስ እያደረጉ በተመጠነ የኤሌክትሪክ ሃይል ያነዝሯቸዋል። ክስተቱ እየተደጋገመ ሲሄድ አይጦቹ የምግቡን ሽታ ከኤሌክትሪኩ ንዝረት ጋር የሚያይዝ ተግባራዊ ተሞክሮ (Experience) ያዳብራሉ። በዚህም፣ ሽታውን በፍጥነት ለመለየት የሚያስችል የስሜት ህዋሳት ያዳብራሉ። ይህም ሽታውን ለመለየት የሚያገለግሉ ብዛት ያላቸው ነርቮች በአፍንጫቸው ውስጥ እንዲገኙ ያደርጋል። በምርምሩ የተገኘው አስገራሚ ውጤት ግን ሙከራው ከተደረገባቸው አይጦች በተወለዱ የአይጥ ግልገሎች ላይ የታየው ነው። ምንም እንኳን ለምግቡ ሽታ እና ለኤሌክትሪኩ ንዝረት ተጋላጭ ያልነበሩ ቢሆንም፣ ሙከራው ከተደረገባቸው አይጦች የተወለዱት ግልገል አይጦች የምግቡን ሽታ የሚለዩበት ብዛት ያላቸው ነርቮች ያሏቸውና ለሽታውም የበለጠ ስሜታዊ መሆናቸው በጣም አስገራሚ ነው፡፡ ይህ የእንስሳት ተፈጥሯዊ ባሕሪ እንዴት በአከባቢያዊ ሁኔታ እንደሚቀየር ጥሩ መሳያ ነው፡፡ በተለይ ወላጆች በሕይወት ዘመናቸው ያጋጠሟቸውን እንደ ፍርሃትና ጭንቀት ያሉ መጥፎ አካላዊና ስነ-ልቦናዊ ተፅዕኖዎች እንዴት ወደ ልጆቻቸው እንደሚያስተላልፉ፣ በአንድ ወቅት የተከሰተ አከባቢያዊ ለውጥ የሚፈጥረው ተፅዕኖ በግዜውና በቦታው ከነበሩት ወላጆች አልፎ-ተርፎ በልጆቻቸው ላይ’ም ጠባሳውን እንደሚያሳርፍ ያሳያል።

ከላይ የተጠቀሰው የምርምር ውጤት፣ መጥፎ የሕይወት አጋጣሚዎች፣ እንደ ማንኛውም እንስሳ፣ በሰው ልጆች ላይም የሚያስከትሏቸውን ጉዳቶች ለመገንዘብ ጠቃሚ ነው፡፡ በእርግጥ ስለምርምሩ ያወቅኩበት አጋጣሚ በራሱ ለዚህ ጥሩ ማሳያ ነው፡፡ ከ19ኛው ክ.ዘመን መጨረሻ ጀምሮ የካናዳ መንግስት 80,000 የሚሆኑ የሀገሪቱ የመጀመሪያ ሰፋሪ (Aborigines) ልጆችን ወደ አድሃሪ ትምህርት ቤቶች በግድ እንዲገቡ በማድረግ፤ የሰባት ትውልድ ህፃናትን ከወላጆቻቸው ተነጥለው እንዲያድጉ፣ በባዕዳን ቋንቋ እንዲማሩ በማድረግ፣ በባዕዳን እምነት፣ ሃይማኖትና እሴት እንዲጠመቁ አድርጓል፡፡ በዚህ ፅሁፍ የተዳሰሰው የምርምር ሥራ፣ የካናዳ መንግስት በመጀመሪያ ሰፋሪ ቤተሰቦች፣ በተለይ ደግሞ በህፃናቱ ላይ የፈፀመውን በደል እና በቀጣይ ትውልድ ላይ የፈጠረውን ዘላቂ ተፅዕኖ ማሳያ ተደርጎ የቀረበ ነው፡፡

[Photo - Megenta area of Afar, Ethiopia. AP Photo/Mulugeta Ayene]
[Photo – Megenta area of Afar, Ethiopia. AP Photo/Mulugeta Ayene]

በኢትዮጲያ የ”SAVE THE CHILDREN” ዳይሬክተር፣ ጆን ግራሃም ከሰጡት መግለጫ ውስጥ የድርቁን አስከፊነት የሚያሳዩ የተወሰኑ ቁጥሮችን ለመጥቀስ ያህል፤ በሰብል እህል ምርት እጥረትና የቤት እንስሳት ሞት ምክኒያት 10.1 ሚሊዮን ሰዎች ራሳቸውንና ቤተሰባቸውን በበቂ ሁኔታ መመገብ አይችሉም፣ እስከ ነሃሴ 2008 ዓ.ም ድረስ ባለው ግዜ ውስጥ በእነዚህ አካባቢዎች ብቻ ወደ 350,000 ህጻናት ይወለዳሉ፣ በድርቁ ምክኒያት ከ2.5 ሚሊዮን በላይ ህፃናት ትምህርታቸውን ያቋርጣሉ፣ እንዲሁም 400,000 ህፃናት ከፍተኛ የርሃብ አደጋ ያጋጥማቸዋል፡፡

ከላይ በሚሊዮን እና በሺህ የተጠቀሱት ቁጥሮች ብቻ አይደሉም፣ የሀገራችን ዜጎች፥ ሰዎች ናቸው፡፡ ልክ እንደ እኔና እናንተ የመኖር ተስፋ ያላቸው፥ ለዕለት ጉርስ ከመጨነቅ ባለፈ የተሻለ ሕይወት የሚገባቸው ሰብዓዊ ፍጡሯን ናቸው፡፡ እንደ አለመታደል ሆኖ፣ እዚህ ሀገር ሁሉ ነገር ቁጥር ነው! መከራና ችግራቸው እንዲገባን፣ የደረሰባቸው የማጣት ሰቆቃ እንዲሰማን፣ ያጠላባቸው የችጋር ጣዕረ-ሞት እንዲታየን፣… ከቁጥር በላይ ለሰብዓዊነት ቅድሚያ ሰጥተን ማሰብ አለብን፡፡

“በድርቁ ምክንያት 10.1 ሚሊዮን ሰዎች ራሳቸውንና ቤተሰባቸውን በበቂ ሁኔታ መመገብ አይችሉም” ማለት እነዚህ ሁሉ ሰዎች ኑሮና ሃሳብ ስለ የዕለት ጉርሻ መጨነቅና ማሰብ ሆኗል፣ ከዚያ ያለፈ ነገር ለማሰብ የሚያስችል አካላዊና ሥነ-ልቦናዊ አቅም አጥተዋል ማለት ነው፡፡ “በቀጣዮቹ ስድስት ወራት ውስጥ ብቻ 350,000 ህጻናት ይወለዳሉ” ማለት፣ 350,000 እናቶች በርሃብ በታጠፈ አንጀታቸው በምጥ ይሰቃያሉ፣ በምጥ ይሞታሉ፡፡ በምጥ ከመሞት ቢተርፉ፣ በወጉ አይታረሱም፡፡ እነዚህ ሁሉ እናቶች እንኳን የሚያጠቡት የሚበሉት የላቸውም፡፡ “400,000 ህፃናት ከፍተኛ የርሃብ አደጋ ያጋጥማቸዋል” ማለት ከእነዚህ ውስጥ የተወሰኑት አንድ ዓመት ሳይሞላቸው ይሞታሉ፣ ሌሎቹ የ5ኛ ዓመት ልደታቸውን የማክበር እድል የላቸውም፣ ከዚህ መዓት የተረፉት ደግሞ ቀጣይ የሕይወት ዘመናቸውን ከበሽታ ጋር ተጣብቀው ይኖራሉ ማለት ነው፡፡ ”ከ2.5 ሚሊዮን በላይ ህፃናት ትምህርታቸውን ያቋርጣሉ” ማለት እነዚህ ሁሉ ህፃናት የዕውቀትን ብርሃንን ሳያዩ በድንቁርና ተጋርደው ይኖራሉ ማለት ነው፡፡

መቼም እዚህ ሀገር ሁሉም ነገር ቁጥር ነው። በሀገራችን የተከሰተው ድርቅ’ም ለቆጣራዎች ያው ቁጥር ነው። ነገር ግን፣ ድርቁን በሚያስከትለው አስከፊ የሕይወት ገፅታ መጠን ለክተን ከቆጠርን፣ “ከዚህ የከፋ ከቶ ምን አለ….?” ያስብላል። ምክንያቱም፣ አሁን በሀገራችን የተከሰተው ድርቅ በደረቁ ሲቆጠር፡ “10,200,000 ድህነት፣ 2,500,000 ድንቁርና፣ 750,000 በሽተኛ ያክላል።

በዚህ ፅሁፍ እንደ ማሳያ የተጠቀሰችው ተራ እንስሳ፥ የቤተ-ሙከራዋ “አይጥ” እንኳን በአቅሟ ከምግብ ሽታ ጋር ተያይዞ የደረሰባትን የኤሌክትሪክ ንዝረት ፍርሃት ለልጆቿና ለልጅ-ልጆቿ አስተላልፋለች፡፡ በምግብ እጥረት በተጎሳቆለ አካሏ እርግዛ፣ በረሃብ አንጀቷ ተጣብቆ ለምጥ የሚሆን ሃይል አጥታ በተዓምር ከሞት የተረፈች እናት፣ ደረቅ ጡቷን እየጋጠ ላደገው ልጇ የምታስተላልፈው ምንድነው? አዎ፣… በድርቅ ምክንያት ሃብትና ንብረቱን ካጣ ቤተሰብ፣ በምግብ እጥረት ከተጎሳቆሉ እናትና አባት የሚወለድ ልጅ ውርሱ እና ቅርሱ ማቆሚያ የሌለው የድህነት ስቅታ፥ የበሽታ ሰቀቀን፥ የሞት ሰቆቃ ናቸው፡፡ እና ታዲያ…እንደ ሀገር ከዚህ የከፋ ነገር ከቶ ምን አለ….?
**************

Seyoum Teshome is a Lecturer at Ambo University Woliso Campus and head of Management Department. He was born in Arsi, Assela, in 1979 and studied Management at Harameya University and MBA at Mekelle University. He also blogs at http://ethiothinkthank.com

more recommended stories