ለሕገ መንግሥቱ ታማኝ አይደሉም የተባሉት ዳኛ ከኃላፊነታቸው ተነሱ

(ዮሐንስ አንበርብርሪፖርተር ጋዜጣ)

ከ2006 ዓ.ም. ጀምሮ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በዳኝነት ሲያገለግሉ የቆዩት ዳኛ ግዛቸው ምትኩ ለሕገ መንግሥቱ ታማኝ ሆነው አልተገኙም በሚል ምክንያት በፓርላማው ከኃላፊነታቸው ተነሱ፡፡

ፓርላማው ዳኛውን ከሹመታቸው ያነሳው፣ ጥር 28 ቀን 2008 ዓ.ም. የፌዴራል ዳኞች አስተዳደር ጉባዔ ዳኛው ፈጽመውታል ያለውን የዲሲፕሊን ስህተት አዳምጦ ከተወያየ በኋላ ነው፡፡

በዳኛ ግዛቸው ላይ የቀረቡ የዲሲፕሊን ክሶች አራት ሲሆኑ፣ የቀረቡትን ክሶች የመመርመርና ምስክሮችን የመስማት፣ ተከሳሹም በቀረበባቸው ክስና የሰዎች ምስክርነት ላይ ምላሻቸውን እንዲሰጡ የፌዴራል ዳኞች አስተዳደር ጉባዔ አድርጓል፡፡

Photo - Ethiopian parliament session
Photo – Ethiopian parliament session

ዳኛ ግዛቸው ከተከሰሱባቸው አራት ክሶች መካከል በዳኞች ሥነ ምግባር ረቂቅ ደንብ የፍትሕ አካላት ውይይት ባደረጉበት ወቅት፣ ‹‹ዳኛ ሕገ መንግሥቱ ላይ ልዩነት (Reservation) ቢኖረውም ዳኛ ሆኖ መሥራት ይቻላል የሚል አቋም ሲያንፀባርቁ መታየታቸው፣ እንዲሁም በሌሎች አጋጣሚዎችና በተግባር ሕገ መንግሥቱ ላይ የማይቀበሏቸው ሐሳቦች መኖራቸውን የሚገልጹ መሆኑ›› የሚለው ዋነኛው ነው፡፡

በሌላ በኩል በ2006 ዓ.ም. ክረምት ወራት በፓርላማ አዳራሽ በተደረገ ሥልጠና፣ በተለይ ኢትዮጵያ የዓለም አቀፍ የወንጀል ፍርድ ቤት ፈራሚ አባል ያልሆነችው የኢትዮጵያ የመንግሥት አመራሮች የሰብዓዊ መብት ጥሰት ስለሚፈጽሙ መሆኑን፣ በ1997 ዓ.ም. ከምርጫ ጋር ተያይዞ በተደረገው አመፅ የአንድ ብሔር ጥቅም ለማስከበር ብዙ ሰዎች መገደላቸውንና መንግሥትም ሊጠየቅበት ሲገባ አለመጠየቁን ሲገልጹ ነበር የሚለው ሁለተኛ ክስ ነው፡፡

ከሌሎች ዳኞች ጋር ተግባብተው አይሠሩም የሚለውና የሰበር ችሎት ዳኞች ውሳኔ ከሕገ መንግሥቱ የሚቃረን ከሆነ የበታች ፍርድ ቤት ዳኞች መቀበል የለባቸውም በማለት እንደተከራከሩ የሚገልጹት ደግሞ ሦስተኛና አራተኛ ክሶች ናቸው፡፡

ጉባዔው ክስ የቀረበባቸውን ዳኛ ምላሽ እንዲሰጡ እንዳደረገ የቀረበው ሪፖርት ያስረዳል፡፡ በዚህም መሠረት የመጀመሪያውና ዋነኛውን ክስ በተመለከተ፣ ‹‹እንደ ዳኛና እንደ ዜጋ ሕገ መንግሥቱን በማክበርና ሕገ መንግሥቱን መሠረት በማድረግ የወጡ ሕጐችን፣ ፖሊሲና ስትራቴጂዎችን በማክበር ኃላፊነትን መወጣት ያለባቸው መሆኑን እንደሚያምኑ ገልጸዋል፤›› በማለት ጉባዔው ነጥባቸውን ያስቀምጣል፡፡

‹‹ለሕገ መንግሥቱ ያላቸው ተገዥነት መገለጫውም ሕግን መሠረት አድርገው መሥራታቸው መሆኑን፣ ሕገ መንግሥቱ ሊሻሻል የሚችልባቸውን ድንጋጌዎች የያዘ መሆኑ፣ ለፍትሕ አካላት ማሠልጠኛ ማዕከል ካሪኩለም ለማዘጋጀት በተደረገ መድረክ ላይ ዕጩ ዳኞችና ዓቃቤ ሕጐች ወደ ሥልጠና ማዕከሉ ሲመጡ ሕገ መንግሥቱ ላይ ልዩነት ቢኖራቸው እንኳን፣ የሙያ ብቃት ካላቸው ተቀብሎ አመለካከታቸውን በሥልጠና መለወጥ ይገባል የሚል አስተያየት ከመስጠታቸው ውጪ፣ የተሾመ ዳኛ ሕገ መንግሥቱ ላይ ልዩነቱ ሊኖረው ይችላል አለማለታቸውን›› ጉባዔው ያቀረበው ሪፖርት ያስረዳል፡፡

በሁለተኛነት የቀረበባቸውን ክስ አስመልክቶ በሰጡት ቃል ደግሞ በኢትዮጵያ ሕግና የዳኝነት ሥርዓት ቢኖርም፣ የ1997 ዓ.ም. ምርጫን ተከትሎ የተፈጠረውን ግርግር በተመለከተ ያለፈው አልፏል ለወደፊት በድጋሚ ቢከሰት ኢትዮጵያ የዓለም አቀፍ ፍርድ  ቤት (ICC) አባል መሆኗ ሊጠቅም እንደሚችል መጠቆማቸውን ለጉባዔው እንደገለጹ የቀረበው ሪፖርት ያስረዳል፡፡ የ1997 ዓ.ም. ምርጫ ክስተት የአንድን ብሔር ጥቅም ለማስጠበቅ የተደረገ ነው ወይም ይህ ቡድን ይህን ፈጽሟል አለማለታቸውን፣ የተባለው በመንግሥት ደረጃ የተፈጸመ ነገር አለ ወደፊት ቢደገም የሚዳኝ ገለልተኛ አካል ያስፈልጋል ማለታቸውን፣ ክስተቱ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በተቋቋመ አጣሪ ኮሚቴ ተጣርቶ መንግሥት የወሰደው ዕርምጃ ተመጣጣኘ ነው ቢባልም፣ ወደፊት ሌላ ተመጣጣኘ ያልሆነ ነገር ቢከሰት ይህንን በገለልተኝነት የሚዳኝ አካል ያስፈልጋል ማለታቸውን ለጉባዔው ገልጸዋል ተብሎ ሪፖርት ተደርጓል፡፡ የተቀሩት ክሶችን በአግባቡ በማስተባበላቸው ጉባዔው ከላይ የተጠቀሱትን ሁለት ክሶች በጭብጥነት ይዞ የማጣራት ሥራ ማከናወኑን ይገልጻል፡፡

በዚህም መሠረት በተካሄደው የፖሊሲ ሥልጠና መድረክ ከተሳተፉ አራት ሰዎች የምስክርነት ቃል መውሰዱን ጉባዔው ገልጿል፡፡ በተዘጋጀው የሥነ ምግባር ደንብ ላይ በንዑስ ቡድን ሲወያዩ የንዑስ ቡድኑ አወያይና የንዑስ ቡድኑ ጸሐፊ ምስክርነት እንዲሰጡ ተደርጓል፡፡

የንዑስ ቡድኑ አወያይ በሰጡት ቃል፣ ‹‹አንድ ሰው ሕገ መንግሥቱን ማክበር እንጂ ማመን አይጠበቅበትም፡፡ እኔ በርካታ የማላምንባቸው ድንጋጌዎች አሉ፡፡ ሕገ መንግሥቱ እንዲሻሻል የሚያስችሉ አንቀጾች አሉት …›› እያሉ ይናገሩ የነበረ መሆኑን፣ ተከሳሹ ሕገ መንግሥቱ መሻሻል አለበት የሚል ዕምነት እንዳላቸውና ሕገ መንግሥቱን እንደማይቀበሉ መረዳታቸውን እንደገለጹ ጉባዔው ለፓርላማው ያቀረበው ሪፖርት ያስረዳል፡፡

ሌላኛውም ምስክር በበኩላቸው፣ ‹‹ዳኛ ሊመርጥ ይችላል ወይ? ስለሚመርጠው ፓርቲ ውይይት ሊያደርግ ይችላል ወይ?›› የሚል ጥያቄ አንስተው መወያየታቸውን፣ በሌላ በኩል ደግሞ ትምህርታዊ በሆኑ መድረኮች፣ ‹‹ዳኛ ሕገ መንግሥቱን እንዳለ ነው መጠቀም ያለበት ወይስ ትችት ማድረግ ይቻላል? ወይ አይችልም ከተባለ የሥነ ምግባር ደንቡ ላይ አይችልም ተብሎ ግልጽ ሆኖ መቀመጥ አለበት የሚሉ ነጥቦችን አንስተው መወያየታቸውን፣ እነዚህንም ሐሳቦች ያነሷቸው ሕገ መንግሥቱን ከመቃረን ሳይሆን ለግልጽነት አንስተውታል፤›› ብለው እንደሚያምኑ ለጉባዔው ቃላቸውን ሰጥተዋል፡፡

በተቀረው የክስ ጭብጥ ላይ ምስክርነት የሰጡ ሌላ ግለሰብ ደግሞ፣ ‹‹ተከሳሽ ዳኛ በቡድን ውይይት ወቅት በአንዳንድ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የአንድ ብሔር አባላት የበላይነት የሚታይ መሆኑን፣ እንዲሁም አማራ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍል አላግባብ እየተፈናቀለ መሆኑን ሲገልጹ ነበር፡፡ በውይይት ጊዜም ከሌሎች የአማራ ብሔር ተወላጆች ጋር አላግባብ የመወገንና የመቧደን እንቅስቃሴ ሲያደርጉ እንደነበርና በአጠቃላይ ተከሳሹ እንደ ድርጊታቸው ሕገ መንግሥቱን የመቀበልና የማመን ነገር እንደማይታይባቸውና አመለካከታቸውን ለማስተካከልም ዝግጁ አለመሆናቸውን፤›› ገልጸዋል፡፡ ሌላ ቃላቸውን የሰጡ ምስክር ደግሞ በቡድን ውይይት ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ የሰብዓዊ መብት ጥሰት መኖሩን፣ ኢትዮጵያ የዓለም አቀፍ የወንጀል ፍርድ ቤት አባልነት መፈረም እንደሚኖርባት፣ በ1997 ዓ.ም. ምርጫ የሰብዓዊ መብት ጥሰት የተፈጸመ መሆኑን ኢትዮጵያ የዓለም አቀፍ ወንጀል ፍርድ ቤት አባል ብትሆን ትከሰስ ነበር፣ ወዘተ እያሉ አስተያየት ሲሰጡ የነበረ መሆኑን፣ የአማራ የነፍጠኛ ሥርዓት ድሮ ነበር እየተባለ መጻፍ በአሁኑ ትውልድ ቂም እንዲያዝ ያደርጋል፡፡ በትግራይ ተወላጆች የተሞላ የመከላከያ ሠራዊት ነው ያለን እያሉ ይናገሩ የነበር መሆኑን፣ ልትጫኑኝ አይገባም በሚል ተቃራኒ አመለካከትን ሲያንፀባርቁ ነበር፤›› በማለት ለጉባዔው ማስረዳታቸውን ሪፖርቱ ይገልጻል፡፡

በተጠቀሱት የምስክሮች ቃል ላይ ቃላቸውን እንዲሰጡ ለዳኛ ግዛቸው ምትኩ ዕድል መሰጠቱን ሪፖርቱ ያስረዳል፡፡

ለመጀመሪያዎቹ ሁለት ምስክሮች በሰጡት አስተያየትም፣ የመጀመሪያው ምስክር በቡድን ውይይቱ ወቅት ከሦስት ቀናት ስብሰባ ውስጥ አንድ ቀን ከግማሽ ብቻ የመጡ መሆናቸውንና የትኞቹን የሕገ መንግሥት አንቀጾች ተከሳሹ እንደማይቀበሉ አለመግለጻቸውን፣ እንዲሁም ቃላቸውን በገለልተኝነት አለመስጠታቸውን የሚያሳይ በመሆኑ ውድቅ እንዲደረግ ጠይቀው የሁለተኛውን ምስክርነት ግን ተቀብለዋል፡፡

የዳኞች አስተዳደር ጉባዔ በሁሉም ወገን የቀረቡ ማስረጃዎችን አገናዝቦ ዳኛው ለሕገ መንግሥቱ ያላቸውን ታማኝነትና አመለካከት በተመለከተ፣ ዳኛው ሕገ መንግሥቱን ሙሉ ለሙሉ ያልተቀበሉት መሆኑንና ሕገ መንግሥቱ እንዲሻሻል ፍላጐት ያላቸው መሆኑን እንደተረዳው በሪፖርቱ አስቀምጧል፡፡

‹‹ተከሳሹ ዳኛ ዕጩ ዳኛ ሕገ መንግሥቱን ሙሉ ለሙሉ ባይቀበልም ችግር የለውም ሲሉ ያስቀመጡት ነጥብ፣ በአመለካከት ደረጃ የተሾመ ዳኛ በሕገ መንግሥቱ ላይ ልዩነት ቢኖረውም ዳኛ ከመሆን አያግደውም ከማለት ተለይቶ የሚታይ አይደለም፡፡ ከዳኛ የሚጠበቀው ሙሉ ሕገ መንግሥታዊ ታማኝነት ነው፡፡ በመሆኑም ዳኛው ሕገ መንግሥቱን ሙሉ ለሙሉ ተቀብዬ አስከብራለሁ ማለታቸው አሳማኝ ሆኖ አልተገኘም፤›› በማለት ወስኗል፡፡

የዓለም አቀፍ የወንጀል ፍርድ ቤት አባልነትንና የ1997 ዓ.ም. ምርጫን በተመለከተ በያዙት አመለካከት፣ ዳኛው ተሾመው የሚሠሩበት ፍርድ ቤት ገለልተኝነትን ጭምር የሚጠራጠሩ መሆኑን በሚያሳይ አግባብ ለተፈጸመውም ሆነ ወደፊት ለሚፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ከአገሪቱ ፍርድ ቤት ይልቅ ዓለም አቀፍ ተቋማት የሕዝብ አለኝታ መሆናቸውን እንደሚያምኑ የሚያሳይ እንደሆነ ቆጥሮታል፡፡

በተጨማሪም የብሔር እኩልነት ሕገ መንግሥታዊ ዕውቅና የተሰጠው መርህ መሆኑን፣ ፅንፍ የወጣ ትምክህትም ሆነ ጠባብነት የዚህ ሕገ መንግሥታዊ መርህ አደጋዎች በመሆናቸው ዳኛ ግዛቸው ምትኩ ጥፋተኛ መሆናቸውን ጉባዔው በሪፖርቱ ለፓርላማው አሳውቋል፡፡ በውሳኔ ሐሳቡም ከዳኝነት ሥራቸው እንዲሰናበቱ ሲል ለፓርላማው አቅርቧል፡፡

ከምክር ቤቱ አባላት በጉዳዩ ላይ ሁለት መሠረታዊ ሐሳቦች የቀረቡ ሲሆን፣ የመጀመሪያው የቀረበውን የፌዴራል ዳኞች አስተዳደር ጉባዔ የውሳኔ ሐሳብ የሕግ፣ ፍትሕና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በዝርዝር ተመልክቶ ለፓርላማው ውሳኔውን ለምን እንዲያቀርብ አልተደረገም የሚል ነው፡፡ ሌላኛው ደግሞ በውይይት መድረክ የተነሳን ሐሳብ መነሻ አድርጐ እዚህ ድምዳሜ ላይ መድረስ ተገቢ ነው ወይ የሚል ጥያቄ ነው፡፡

በተለይ የሁለተኛው ጥያቄ ይዘት ግለሰቡ በውይይት መድረኮች ተሳትፎ ሲያደርጉ ሐሳብ አቀረቡ እንጂ፣ ከተግባር ጋር የተያያዘ የዲሲፕሊን ጥፋት መፈጸማቸውን የሚያሳይ አይደለም የሚል ጥያቄ ከምክር ቤቱ አባላት ቀርቧል፡፡

በጉዳዩ ላይ ምላሽ የሰጡት በፓርላማ የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትሩና የዳኞች አስተዳደር ጉባዔ አባል የሆኑት አቶ አስመላሽ ወልደ ሥላሴ ናቸው፡፡

ፓርላማው አሁንም ጉዳዩን ለሕግ፣ ፍትሕና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መምራት እንደሚችል፣ ነገር ግን ፓርላማው በመጀመሪያ ውይይት ሳያደርግበት ለቋሚ ኮሚቴ መምራት እንደማይቻል አብራርተዋል፡፡

‹‹ሌላው ጉዳይ ዳኛው አቶ ግዛቸው ሐሳባቸውን ስለገለጹ ነው የሚለው ጥያቄ መሠረታዊ ነው፡፡ ነገር ግን እንደዚያ አይደለም፡፡ አቶ ግዛቸው ዳኛ ናቸው፡፡ ለዳኛ የመጀመሪያው መሥፈርት ሕገ መንግሥቱን ለማክበርና ለማስከበር ፍፁም መሆን ነው፡፡ በምንም ዓይነት መሥፈርት ዳኛ በሕገ መንግሥቱ ላይ ልዩነት ሊኖረው አይገባም፤›› ብለዋል፡፡

‹‹አቶ ግዛቸው የሕግ ምሁር ናቸው፡፡ ስለዚህ ሕግ ተምረዋል፡፡ ሕግ ሲማሩ ደግሞ ሕገ መንግሥቱን ተምረዋል፡፡ ከዚያም አልፎ ወደ ዳኝነት ከመምጣታቸው በፊት የሕገ መንግሥት ሥልጠና ወስደዋል፡፡ አሁን ግን በየመድረኩ ነው በሕገ መንግሥቱ ላይ ያላቸውን ልዩነት የሚገለጹት፤›› ሲሉ አቶ አስመላሽ አብራርተዋል፡፡

በተግባር ሕግ ሲጥስ ነው አንድ ዳኛ ከኃላፊነት የሚነሳው የሚል በሕገ መንግሥቱም በዳኞች አስተዳደር ጉባዔም የሕግ አንቀጽ የለም ብለዋል፡፡

‹‹ከእንጨት መርጦ ለታቦት ከሰው መርጦ ለሹመት የሚለው የአገራችን አባባል በትክክል የሚገልጸው ዳኝነትን ነው፤›› ያሉት አቶ አስመላሽ፣ ለዳኛው አቶ ግዛቸውም ቢሆን የሚጠቅም ውሳኔ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም በቀጥታ ወደ ድምፅ መስጠት የተገባ ሲሆን፣ በሙሉ ድምፅ ፀድቋል፡፡ ዳኛ ግዛቸው ምትኩ ለመጨረሻ ጊዜ ከሌሎች ሁለት ዳኞች ጋር ሆነው ሲመረምሯቸው ከነበሩ ፋይሎች መካከል በሙስና ወንጀል የተጠረጠሩት የእነ አቶ መላኩ ፈንታ ጉዳይ ይገኝበታል፡፡

በዚሁ ዕለትም ሌሎች ሁለት ዳኞች ማለትም የመጀመሪያ ፍርድ ቤት ዳኛ የነበሩ አቶ ሀብታሙ ሚልኪና የከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛ የሆኑት አቶ አብርሃ ተጠምቀ ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት በፈጸሟቸው የዲሲፕሊን ጥሰቶች ተሰናብተዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ፓርላማው ከላይ የተጠቀሱትን ዳኞች ካሰናበተ በኋላ፣ ለመጀመርያና ለከፍተኛ ደረጃ ፍርድ ቤቶች አራት ፕሬዚዳንቶችን ሾሟል፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የቀረቡት ዕጩ ፕሬዚዳንቶች አቶ በላቸው አንሺሶ ለከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንትነት፣ ወ/ሮ ሌሊሴ ደሳለኝና አቶ በሪሁ ተወልደ ብርሃን ለምክትል ፕሬዚዳንትነት ናቸው፡፡

ለፌዴራል የመጀመርያ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንትነት በዕጩነት የቀረቡት ደግሞ አቶ መሐመድ አህመድ ናቸው፡፡ ምክር ቤቱ የዕጩ ዳኞቹን ሹመት ሙሉ ለሙሉ ተቀብሎ በጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ መድኅን ኪሮስ አማካይነት ቃለ መሀላ እንዲፈጽሙ ተደርጓል፡፡
************

Content gathered and compiled from online and offline media by Hornaffairs staff based on relevance and interest to the Horn of Africa.

more recommended stories