ሚ/ር ጌታቸዉ ረዳ:- ሕይወት ከማዳን በላይ ለገጽታ ግንባታ ተብሎ የሚደበቅ ችግር የለም

የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ኃላፊ ሚኒስትር ጌታቸዉ ረዳ ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ የዜጎችን ሕይወት ከማዳን በላይ ለገጽታ ግንባታ ተብሎ የሚደበቅ ችግር የለም አሉ።

በኤልኒኖ ምክንያት በተፈጠረው ድርቁ ምክንያት ከመንግሥት አቅም በላይ ወደሚሆንበት ደረጃ ላይ አለመድረሱን እና የኢትዮጵያ መንግሥት አንድም ሰዉ በድርቁ ምክንያት እንዳይሞት ሰፊ ሥራዎችን ሲያከናዉን መቆየቱን እና ለአስቸኳይ የምግብ እርዳታ እስካሁን 6 ቢሊዮን ብር እንዳወጣ ገልፀዋል፡፡ 

መንግስት እርዳታውን በራሱ አቅም እያካሄደ መሆኑን የገለጹት ሚንስትሩ መንግስት ለድርቁ ድጋፍ ከሚያደርጉ አካላት ጋር በመሆን አብሮ ለመስራትና ተገቢውን ድጋፍ ለማድረግ ፍላጎት እንዳለው አስረድተዋል፡፡ እስከ አሁን ባለው ተጨባጨ መረጃ ግን ቃል ከመግባት ያለፈ ተግባራዊ እንቅስቃሴ አልታየም ብለዋል፡፡Photo - Minister Getachew Reda

የችግሩን ሁኔታና የሚደረገዉ ድጋፍ በየሳምንቱ የሚከታተል በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር የሚመራ የአደጋ መከላከል ቡድን ተቋቁሞ ቅርብ ክትትል እያደረገ እንደሆነም ገለጸዋል።

ሚኒስትር ጌታቸዉ ረዳ ከጋዜጠኞች ለተነሱላቸዉ ጥያቄዎች ምላሽ በሰጡበት ወቅት የኢትዮጵያ መንግሥት የሚያስጨንቀዉ ቁጥር ጨመረ ቀነስ የሚለው እንዳሆነ ያሰመሩበት ሚኒተር ጌታቸው፤ ቢቢሲ የተባለ የአለም አቀፍ ሚዲያ ተቋም “በድርቁ በአንድ አካባቢ ቢያንስ በየቀኑ ሁለት ህፃናት ይሞታሉ” በማለት እና የተጎጂዎችም ቁጥር 15 ሚሊዮን ደረሰ በሚል ያወጣዉ ዘገባ ስህተት መሆኑንም ጠቁመዋል።

እርዳታ ሰጪ ድርጅቶች ድጋፍ ለማግኘት ሲባል ሰፋ ያለ ቁጥር የመጥራት ዝንባሌ ሊኖራቸው እንደሚችል የሚገመት ነው ያሉት ሚኒስትር ጌታቸዉ ረዳ ፤ መንግሥት ቢቢሲ ዘገባዉን እንዲሰራ ሁኔታዎችን እንዳመቻቸ ሁሉ ሌሎች ሚዲያዎችም ያለውን እውነታ እንዲያዩ ሁኔታዎችን ያመቻቻል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ገጽታ የሚገነባዉ በሚሰሩ የልማትና ዴሞክራሲ ግንባታ ሥራዎች ዉጤት መሆኑን ያስታወሱት ሚኒስትር ጌታቸዉ የዜጎችን ሕይወት ከማዳን በላይ ለገጽታ ግንባታ ተብሎ የሚደበቅ ችግር የለም ብለዋል።

‹‹ከፍተኛ መጠን ያለዉ እህል እየገባ በመሆኑ ከወደብ ወደ ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት የትራንስፖርት ችግር አያጋጥምም ወይ?›› ለሚል ጥያቄ በሰጡት ምላሽ ከዚህ በላይ ቅድሚያ የሚሰጠዉ ጉዳይ ስለሌለ ያሉትን አማራጭ ወደቦች እና የትራንስፖርት አማራጮች ሁሉ ይጠቀማል፤ እንዲሁም በጥቂት ሳምንታት ውስጥ በባቡር ከጅቡቲ ወደ አዳማ ለማጓጓዝ መታቀዱን ገልጸዋል።

ለተጎጂዎች እርዳታ የሚሰራጨዉን እህል ለግል ጥቅም ለማዋል የሚያውሉ ግለሰቦችን አስመልክቶ ለቀረበላቸው ጥያቄም እርዳታው ለተረጂዎቹ በአግባቡ መድረሱንም የሚከታተል የአሠራር ሥርዓት መዘርጋቱን ገልጸው፣ ችግሮች ካሉም ህብረተሰቡ መጠቆም እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ በእንደዚህ አይነት ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት ዉስጥ የተገኘ አካላል ካለ ጠንከር ያለና አስተማሪ እርምጃ እንደሚወሰድበት በአፅንዎት ገልጸዋል።

ሚኒስትር ጌታቸዉ ረዳ ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ በደረሱ ሰብሎች ላይ ጉዳት እንዳያስከትል መንግሥት ባለው አቅም የመከላከያ ሰራዊትና የሚመለከታቸውን ተቋማት በመጠቀም ምርቱ በወቅቱ እንደሚሰበሰብ የገለጹ ሲሆን፤ ለምግብ እርዳታ ሲባልም በተፈጸመው የእህል ግዢ ሳቢያ የተጋነነ የውጭ ምንዛሬ እጥረት እንዳልተፈጠረም አስረድተዋል።

********
(ከዋልታ፣ ከኢዜአ፣ ከመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጽ/ቤት፣ ከፋና የተጠናቀረ)

Daniel Berhane

more recommended stories