ለውጥ ከብሔራዊ ድርጅቶች ሳይሆን ከኢህአዴግ (ከፌደራል) ብንጠብቅ ይሻላል

የኢህአዴግ ጉባዔ ከዚህ በፊት ተደርጎ የማያውቅ እስከሚመስል ድረስ በርካቶች በጉጉት የሚጠብቁት ሆኗል፡፡ ለመሆኑ ከጉባዔው ህዝቡ ምን ፈልጎ ነው እንደዚህ የሚጠብቀው የሚለውን እንይ እስኪ፡፡

በርግጥ በአሁኑ ሰዓት አንድ አፍጥጦ የወጣ ሀቅ አለ፤ አብዛኞቹ ከኢህአዴግ የሚጠበቁ ጥያቄዎች የራስን ክልል/ ብሔር እንጂ ሐገሪቱን የማይመለከቱ መሆናቸውን እያስተዋልን ነው፡፡ የትግራይ ብሔር ተወላጆች አብዛኞቹ ጥያቄዎቻቸው የትግራይ ክልልን የሚመለከቱ ናቸው፤ የኦሮሚም፣ የአማራም እንዲሁ፤ የጎላ ነገር የማይሰማው ከደቡብ እና አጋር ክልሎች ነው፡፡

በትግራይ ክልል ተወላጆቹ በዋናነት የሚያቀርቧቸው ጥያቄዎች ከፖለቲካ ይልቅ ልማት ላይ ያተኮሩ ናቸው፡፡የክልሉ መንግስት ልማታዊነት ይጎድለዋል፣ ትግራይን የእድገቱ ተጠቃሚ ማድረግ አልቻለም፣ ይልቁንም የክልሉ ተወላጅ የሆኑ ባለሀብቶች ክልሉን እንዲሸሽ እያደረጉ ነው ይላሉ፤ ወጣቶች የመሻሻል ተስፋ የማይታይበትን ህይወታቸውን በመሸሽ በገፍ እየተሰደዱ ቢሆንም ይህ ግን የከነከናቸው አይመስሉም፤ አሁንም ስለደርግና ኤርትራ ማውራት ነው የሚመርጡት ይላሉ፡፡ የፌደራል መንግስትም በቂ ትኩረት አልሰጠንም የሚሉም አሉ፡፡

የኦሮሚያ ክልል ተወላጆች በበኩላቸው ፖለቲካ ላይ ያተኮሩ ጥያቄዎች አሏቸው፡፡ ክልሉ በሀገሪቱ ፖለቲካ ላይ የሚገባውን ያህል ውክልና አላገኘም፣ ኦህዴድም ከየትኛውም ፓርቲ በላይ በርካታ ህዝብን የሚወክል ከመሆኑ አንፃር በሚገባው ደረጃ ተፅዕኖ ፈጣሪ መሆን አልቻለም (አንዳንዶች ጠቅላይ ሚኒስትርነት ይገባናል የሚሉት ጥያቄም በዚህ ስር ሊካተት ይችላል)፤ የኦሮምኛ ቋንቋ የፌደራል የስራ ቋንቋ እንዲሆንም የተጨበጠ ስራ እየሰሩ አይደሉም፤ የአዲስአበባን መስፋፋት በመግታት ረገድ በቁርጠኝነት አልቆመም፣ አዲስአበባ ላይ ኦሮምኛ ቋንቋ እና የኦሮሞ ባህል ኦሮሞ አናሳ ብሔር እስኪመስል ድረስ ጎልቶ የሚታይ አይደለም፣ ሆኖም ይህን ለማስተካከል በቂ ስራ አልተሰራም፤ በመልካም አስተዳደር ችግሮች፣ በሙስናና እና በፍትሀዊ ልማት ረገድም የሚነሱ ጥያቄዎች አሉ፡፡Photo - ANDM Congress, Bahirdar, Ethiopia

በአማራ ክልል ተወላጆችና የብሔሩ አባላትም የሚነሱ ፖለቲካዊና ልማትን የሚመለከቱ ጥያቄዎች አሉ፡፡ ከፖለቲካ አንፃር ብዙዎች ህዝባቸውን ለማነሳሳትና ብሔርተኝነትን ለማጠናከር የአማራን ህዝብ የጦስ ዶሮ ሲያደርጉ በዚህ ረገድ ትርጉም ያለው ስራ አልሰራም፤ የብሔሩ ተወላጆችን በርካታ ክልሎች በህገመንግስት የተደነገጉ መብቶችን በመጣስ ከክልላችን ውጡልን እያሉ ሲያስወጡ ክልሉ የተባረሩትን ከመቀበል ባለፈ ትርጉም ያለው ስራ ያለመስራቱና ይህም በየቦታው ለመደጋገሙ መንስዔ መሆኑ፣ ከክልሉ ውጪ ያሉ አማሮችን ወክሎ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ያለማድረጉና ከክልላቸው ውጪ የሚኖሩ አማሮች ህገመንግስታዊው በፖለቲካ የመወከልና የመመረጥ መብታቸውን እንዲጠቀሙበት አላደረገም፤ ሙስናና የመልካም አስተዳደር ችግሮች አሉ፣ በልማትም ክልሉ የበይ ተመልካች ነው፡፡ አርሶአደሮች የምርቶቻቸው ሙሉ ተጠቃሚ መሆን አልቻሉም. . . . የሚሉ ጥያቄዎችም ይነሳሉ፡፡

በደቡብ ከፖለቲካ አንፃር የሚነሳው ጥያቄ ከጠባብነት ጋር የተያያዘ ብቻ ሲሆን ከልማት አንፃር የሚነሳውም በሌሎች ክልሎች የሚነሳውን የሚጋራ ነው፡፡ ሌላው ከትግራጥ ክልል ውጪ ያሉት በመከላከያ ከፍ ተኛ አመራርነት ውክልኛ የሌላቸው መሆኑ፣ ይህ ደግሞ ከጀግንነት ይልቅ የታማኝነት ጥያቄ ለዚህ በሰበብነት መቅረቡና ከሌሎች ብሔሮች በኩል የእኩል እድል ያለመመቻቸት መሆኑ የሚቀርበው ስሞታ ደግሞ እንደጋራ ጥያቄ የሚነሳ ነው፡፡

ጉባዔው ምን ያህል መልስ ይሰጣቸዋል?

በልማቱ ያለመርካት ጥያቄዎችን በመመለስ ረገድ ክልሎች በራሳቸው ሊሰሩ የሚገቧቸው ነገሮች ቢኖሩም ዋናው መፍትሔ ያለው ፌደራል መንግስት ላይ ነው፡፡ የፌደራል መንግስት በሰርቪስ ሴክተር ላይ በሚደረጉ ኢንቨስትመንቶች ላይ በጣም ጥገኛ የሆነው፣ በዋናነት አዲስአበባ ላይ የተከማቸውና ድካም የማይፈልገውን ሀገራዊ የኢኮኖሚ እድገት እንደስኬት እየዘመሩ መቀጠልን ከመረጠ የዚች ሀገር መፃዒ ተስፋ ብሩህ አይሆንም፡፡

በአሁኑ ሰዓት ደቡብና አማራ ክልል የመሬት ባለቤት መሆንና ራሳቸውን መቻል ያቃታቸው በርካታ ወጣቶች ወደከተሞችና ወደሌሎች ክልሎች በስፋት እየተሰደዱ ነው፡፡ በእነኚህ አካባቢዎች ያለው ከፍተኛ የመሬት ጥበት እና ከፍተኛ የወሊድ ምጣኔ ወደፊትም መሬቱ ሊሸከማቸው ያልቻሉ ሚሊዮኖች ወደፊትም አካባቢያቸውን እየለቀቁ መሰደዳቸው አይቀሬ ነው፡፡ አካባቢውን ለቅቆ የመሔድ ባህሉና ፍላጎቱ ስለሌለው እንጂ በመሬት ጥበት በሀገሪቱ ከደቡብ ክልል ሰሜናዊ ክፍል ቀጥሎ በሁለተኛነት የሚጠቀሰው ምስራቅ ኦሮሚያም እንዲሁ ጊዜ የማይሰጥ አፋጣኝ መፍትሔን የሚፈልግ አካባቢ ነው፡፡

የፌደራል መንግስት እነኚህ ያፈጠጡ ችግሮች መኖራቸውን እያወቀ በፎቅ ግንባታ፣ ትራንስፖርት፣ ሆቴልና የመሳሰሉት ዘርፎች ላይ ባተኮሩ የሰርቪስ ሴክተር ኢንቨስትመንቶች እያስመዘገባቸው ባሉ ኢኮኖሚያዊ እድገቶች መርካትና ከራሳችን አልፎ ሌሎችም ካልኮረጁኝ እያለ ማስቸገርን ነበር የመረጠው፡፡ በሰርቪስ ሴክተር ላይ የሚደረግ ኢንቨስትመንት የመዋቅራዊ ሽግግርን (ትራንስፎርሜሽንን) የሚያስገኝ አይደለም- ምክንያቱም ሰፊ የስራ እድልን ስለማይፈጥር፣ ይሔ ነው ተብሎ የሚጠቀስ የቴክኖሎጂ ሽግግርን ስለማያስገኝ፣የውጭ ምንዛሪ ስለማያስገኝ፣ እና ጥቂቶች ብቻ ተጠቃሚ ስለሚሆኑበት!!

ግብርናው ሊሸከም የማይችለው በሚሊዮን የሚቆጠር ወጣት እየተፈጠረ ከሆነ ይህንን ሊሸከም የሚችል ኢንዱስትሪን ማስፋፋት ግድ ይለናል፡፡ አንድ የጨርቃጨርቅ ፋብሪካ እስከ10ሺ ሰራተኞችን መቅጠር ሲችል በየከተማው የገተርናቸው ፎቆች ግን ህንን ማድረግ አይችሉም፡፡ ስለሆነም መንግስት በጊዜ የለኝም መንፈስ እንደአሁኑ አቅጄ ነበር አልተሳካልኝም ብሎ ሪፖርት ማድረግ የማችልበት የኢንዱስትሪ መስፋፋት እቅድ ሊያዘጋጅና ትርጉም ያለው ተጨባጭ ለውጥ ሊያስመዘግብ ይገባል – አልተሳካልኝም ማለት አይቻልም!!

የመልካም አስተዳደርና ሙስና ችግሮችን መንግስት የዘመቻ ሳሆን ተቋማዊ መልክ ያለው ስራ እንዲሆን በቁርጠኝነት መስራት አለበት፡፡ በሙስና ተጨማልቆ ለፖለቲካው፣ ለድርጅቱ፣ ለመንግስት፣ . . . . ወዘተ በሚል ግለሰቦችን ማለፍ ፍፁምፍፁም መቅረት አለበት፡፡ ይህ አሰራር ለብልሹ ግለሰቦች ሽፋን መስጠት ካልሆነ መንግስትም ህዝብም ሀገርም አይጠቀምም፡፡ እንደእስከዛሬው ያዝለቀቅ የሚደረግ ከሆነ የፀረሙስና ርምጃው ራሱ ፖለቲካዊ ትርጉም ይሰጠዋል እንጂ ለመንግስት ምስጋናን ዌም ተዓማኒነትን አያስገኝለትም፡፡ ለዚህ ስኬታማነት በዋናነት ከጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚጀምር ቁርጠኝነት ሊኖር ይገባል፡፡ በሀገራችን ህዝብና ሲቪል ሰርቪስ ውስት ከህጎች ይበልጥ አመራሮች እንደሚከበሩ ከተገነዘብን(ህጎች እንዲከበሩ የሚደረገው ትረት እንዳለ ሆኖ) አመራሮች ሚናቸውን ህዝቡ ከሚጠብቅባቸው አንፃር ለምክትላቸውም የማይመለሱ፣ ህፀፅን የማይታገሱ ናቸው የሚል ስምን ካተረፉ ያለጥርጥር አብዛኛው መስመር ይይዛል፡፡ የዴሞክራሲ ተቋሞቻችን(ፀረሙስና፣ እንባ ጠባቂ፣ ፍርድ ቤቶች፣ ፖሊስ፣ . . .) ፣ ዋና ኦዲተርና ሚዲያዎችም ጥርስ ያላቸው አንበሳ እንዲሆኑ መፍቀድ ብቻ ሳይሆን ማስገደድ ተገቢ ነው፡፡

ፖለቲካዊ ጥያቄዎችን በተመለከተም ለብሔራዊ ድርጅቶች እየቀረቡ ያሉት አብዛኞቹ ጥያቄዎች በድርጅቶቹ የሚመለሱ ሳይሆኑ በኢህአዴግ ደረጃ መልስ የሚያስፈልጋቸው ናቸው፡፡ ለምሳሌ ኦህዴድ ከቁጥሩ አንፃር ውክልናውና ፖለቲካዊ ተፅዕኖ የማሳደር አቅሙ ከፍ ይበል፣ አዲስአበባ ላይ የኦሮሞ ባህልና ማንነት ጎልቶ ይውጣ፣ ኦሮምኛ የፌደራል የስራ ቋንቋ ይሁን፣ አዲስአበባ ወደኦሮሚያ አትስፋፋ፣ ብትስፋፋም የምትስፋፋባቸውን አካባቢዎች ዴሞግራፊ በማዛባ ሁኔታ ይሁን የሚሉ ጥያቄዎች ኦህዴድ ብቻውን ሊመልሳቸው የሚችሉ አይደሉም፡፡ ኦህዴድ በአዲስአበባ የባህል ማዕከል የኦሮምኛ ማስተማሪያዎችን ሊገነባ ይችላል፡፡ ሆኖም ኦህዴድ ፖለቲካዊ ሚናው ከሌሎች ከፍ እንዲል የሌሎች ይሁንታ ያስፈልጋል፡፡ ሌሎች ይቀበሉታል ወይ የሚለውን ካየን ደግሞ አሁን ባለው ሚና ምን ያጣው ነገር አለ፣ ከሌሎቻችን በላይስ መሆን ለምን ፈለገ የሚል ጥያቄን ያስከትል ካልሆነ ተቀባይነት የሚኖረው አይመስለኝም፡፡ኦሮምኛ የፌደራል የስራ ቋንቋ እንዲሆን ጥያቄ ቢያቀርብም ለጊዜው በነበረው መንገድ መቀጠልን እንጂ ተጨማሪ ወጪንና የእኔ ቋንቋስ የሚል የሌሎች ጥያቄን፣በአጠቃቀም ረገድም በፌደራልና በክልሎች ላይ ሊኖር የሚችል መዥጎርጎርን ማስተናገድ የሚፈልጉ አይመስለኝም፡፡

የአማራ ክልል የሚያነሳቸው አማራውን እንዲጠላ የሚያደርጉ የታሪክና ፖለቲካ አቀራረቦችን እንዲስተካከሉ ብአዴን ሳሆን በኢህአዴግ ደረጃ ነው አቋም መያዝ የሚችሉት እንጂ ብአዴን ምንም ሊያደርግ አይችልም፡፡ በዚህ ረገድ ኢህአዴግስ መሰረታዊ ለውጥን የሚያመጡ ስራዎችን መስራት ይቻላል ወይ የሚለው አጠራጣሪ ነው፡፡ ከክልላቸው ውጪ የሚኖሩ አማሮች ፖለቲካዊ ውክልና እንዲኖራቸው በአመራርነትም ተዋፅኦዋቸውን የጠበቀ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ይደረግ፣ ማንም ከክልላችን ውጡ እንዳይላቸው ይደረግ የሚሉትም ነጥቦች እንዲሁ ብአዴን በራሱ የሚሰራቸው ሳይሆኑ በኢህአዴግ ደረጃ ስምምነት ሊደረስባቸው የሚችሉ ናቸው፡፡ አተገባበራቸውን ስናይ ለምሳሌ ኦሮሚያ ወይም ቤኒሻንጉል ውስጥ 20 ፐርሰንቱ ነዋሪ አማራ ከሆነ የክልሉ ገዢ ፓርቲም 20 ፐርሰንት የምርጫ እጪዎቹን አማራ ያድርግ፣ አማሮች በሚኖሩባቸው አካባቢዎችም በአመራርነት ተሳትፎ ይኑራቸው ቢባል ይህ በብአዴን በኩል የሚደረግ ነው ወይስ የክልል ገዢ ፓርቲዎች በስራቸው አማራውን የሚያቅፍ ፖለቲካዊ አደረጃጀት በመፍጠር ነው የሚለው ውይይት የሚያስፈልገው ነው፤ በአሁኑ ነባራዊ ሁኔታ ስኬታማ ሆናል ብሎ መጠበቅም የዋህነት ሊሆን ይችላል፡፡

ህወሀትም በትግል ወቅት ያበረከትኩት አስተዋፅዖ በሚገባ እውቅና አልተሰጠውም ቢል ሌሎች አጋር ፓርቲዎች ለህወሀት ተጨማሪ ነገር ለማድረግ ይስማማሉ ወይስ ከቁትራችን አንፃር በበቂ አልተወከልንም፣ ህወሀት ግን ከበቂ በላ ተወክሏል፣ በመከላከያና ደህንነትም እንዲሁ ከበቂ በላ ነው የተወከለው የሚል ሌላ ጥያቄ ያቀርባሉ ብንል ሁለተኛው የመሆን እድሉ ሰፊ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡

ባጠቃላይ ፖለቲካን በተመለከተ ብሔራዊ ድርጅቶች ከህዝቦቻቸው የሚቀርቡ አብዛኞቹን ጥያቄዎች በራሳቸው መልስ የማይሰጧቸው መሆኑን መገንዘብ እና ብዙ አለመጠበቅ ጠቃሚ ይመስለኛል፡፡ ከኢኮኖሚም አንፃር እንዲሁ ክልሎች በራሳቸው ከሚያመጡት ለውጥ ይልቅ እንደሀገር የኢንዱስትሪ ኢንቨስትመንትን የማስፋት አቅማችን፣ ለኢንዱስትሪ መደላድል የመፍጠር አቅምና ዝግጁነታችን፣ አለም አቀፍ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ስራችን፣ . . . . .ወዘተ የሚወስኑት ነው፡፡

ስለሆነም ለውጥ የምንጠብቅ ከሆነ ከብሔራዊ ድርጅቶች ሳይሆን ከኢህአዴግ (ከፌደራል) ብንጠብቅ ይሻላል፡፡

**********

አዲስ ከድሬዳዋ - Frm. journalist; currently communicator

more recommended stories