በሕግ የተሰጠውን መብት በፍርድ ቤት የተገፈፈው ኩባንያ

(ኃይለሚካኤል ዘስላሴ)

በዓለም ያለት የተለያዩ የሕግ ሥርዓቶች ከሚሰማሙባቸው የሕግ ጽንስ ሐሳቦች አንዱ የሕጋዊ ሰውነት ጽንስ ሐሳብ ነው፡፡ በዚህ ጽንስ ሐሳብ መሠረት ከተፈጥሮ ሰው በተጨማሪ እንደተፈጥሮ ሰው የሚቆጠር ወይም ሰው የሆነ አካል አለ፡፡ በዚህም መሠረት ሁለት ዓይነት ሰዎች አሉ ማለት ነው፡፡ አንደኛው ሰው የተፈጥሮ ወይም ግለ ሰብ ሲሆን ሁለተኛው ሰው ደግሞ በሕግ የሰውነት መብት (ግዴታም ጭምር) ያለው ወይም የተሰጠው አካል ማለትም ማኅበር፣ የንግድ ማሕበር ወይም ድርጅት ነው፡፡ በመሠረቱ ማነኛውም ሰው የተፈጥሮም ይሁን በሕግ የሰውነት መብት የተሰጠው ወይም ያለው አካል የመብትና የግዴታ ባለቤት ነው፡፡ በዚህም ውል መዋዋል፣ የነብረት ባለቤት መሆን፣ መክሰስና መከሰስ ይችላል፡፡ ከቤተሰብ ሕጎች እና ከአንዳንድ የወንጀል ሕግ ድንጋጌዎች በስተቀር የየአገሩ ሕጎች በተፈጥሮ ሰውና በሕግ የሰውነት መብት ያለው አካል በእኩልነት ተፈጻሚነት አላቸው፡፡

የተፈጥሮ ሰው የመብትና ግዴታ ባለቤት የሚሆነው እና በሕግ ኃላፊነት የሚኖረው በተፈጥሮ ሰው በመሆኑ ነው፡፡ ግዑዝ የሆኑ አካላት ማለትም ማሕበራት የንግድ ማኅበራት እንዲሁም ድርጅቶች እንደ ተፈጥሮ ሰው የሚቆጠሩትና በሕግ የሰውነት መብት ይጣቸዋል የሚል ጥያቄ ለመመለስ በርካታ ንደፈ-ሐሳቦች ተቀምሯል፡፡ እነዚህ በርካታ ንድፈ-ሐሳቦች በሁለት ክፍሎች ከፍሎ ማየት ይቻላል፡፡ የመጀመሪያወ ምናባዊ ወይም ሕግ ወለድ ንድፈ ሐሳብ (fiction theory) የሚባለው ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ እርግጠኛ ንድፈ ሀሳብ (Real theory) በመባል የሚታወቀው ነው፡፡

እነዚህ ንደፈ ሃሳቦች ጥልቅ መሠረት እና ትንታኔ ያላቸውና አመሠራረታቸውና ዕድገታቸው ሰፊ እና ከመንስት አመሠራረት ጋር የተያያዘ ቢሆንም ለአጠቃላይ ግንዛቤ ይረዳል በሚል በሁለቱም ንድፈ ሀሳቦች የሚለያዩበት በአጭሩ ማስቀመጥ በቂ ነው፡፡ ምናባዊ ወይም ሕግ ወለድ ንድፈ ሐሳብ (fiction theory) እነዚህ አካላት ግዑዛን መሆናቸው፣ የራሳቸው የሆነ ፍላጎትና አስተሳሰብ የሌላቸው አካላት በመሆናቸው ለሕግ ሥርዓትና አሠራር ሲባል በሕግ የሰውነት መብት የተሰጣቸው ሕግ ሠራሽ ወይም ሰው ሠራሽ (Artificial) ሰዎች እንጂ በእርግጥ ሰዎች አይደሉም የሚል ነው፡፡ እርግጠኛ ንድፈ ሀሳብ (Real theory) በመባል የሚታወቀው እነዚህ አካላት ተመሳሳይ ሀሳብና ፍላጎት ያላቸው ሰዎች ስብስቦች ናቸው፡፡ በዚህም ያቋቋሙዋቸው ሰዎች ሃሳብና ፍላጎት የአካላቱ ሃሳብና ፍላጎት ነው፡፡ እነዚህ አካላት ከአንድ የተፈጥሮ ሰው በላይ የሆኑ ሰዎች ናቸው፡፡ ሕጉም ዕውቅና ይሰጣቸዋል እንጂ አይፈጥራቸውም፡፡ በዚህም እነዚህ አካላት ማለትም የንግድ ማኅበራትም ሆነ ሌሎች የሰውነት መብት የተሰጣቸው አካላት በሰው ምናብ ወይም በሕግ የተፈጠሩ እና የሰውነት መብት የተሰጣቸው ሳይሆን በእርግጥ ሰው በመሆናቸው የሰውነት መብት ያላቸው አካላት ናቸው፡፡

ለአንድ አካል የሰውነት መብት መኖር ምክንያት በተመለከቱ የተለያዩ ነድፈ ሀሳቦች ቢኖርም እነዚህ አካላት ግን የራሳቸው መብትና ግዴታ ያላቸው ስለመሆኑ፣ በዚህም ውል መዋዋል፣ የንብረት ባለቤት መሆን፣ መክሰስና መከሰስ የሚችሉ ስለመሆናቸው፣ ህልውናቸው ከመሠረትዋቸው ወይም ካቋቋቀምዋቸው ሰዎች የተለየ መሆኑ፣ የአባላቶች መብቶችና በሕግ የሰውነት መብት ያላቸው ወይም የተሰጣቸው አካላት መብትና ግዴታ የተለዬ በመሆኑ እና እነዚህ ኣካላት በተለይ ደግሞ የንግድ ማኅበራት አባላት ኃላፊነት ለማኅበሩ ባደረጉት መዋጮ በላይ ኃላፊነት የሌለባቸው መሆኑን በሚያረጋግጡ መሠረታዊ የሕግ መርሆች በተመለከተ በሁለቱም ንድፈ ሐሳብ አራማጆች መካከል ልዩነት የለም፡፡ እነዚህ የሕግ መሠረታዊ መርሆችም በሁሉም ሀገሮች የሕግ ሥርዓቶች የተካተቱ እና የተደነገጉ ናቸው፡፡ የአገራችን ሕግም በነዚህ ንደፈ ሀሳቦችና መሠረታዊ የሕግ መርሆች ተመስርቶ የተደነገገ ነው፡፡

Image - justice
Image – justice

እዚህ ላይ ለአንድ ሰው ያልሆነ ወይም በሰዎች ስብስብ ለተፈጠረ አካል ወይም ማኅበር በሕግ የሰውነት መብት እንዲሰጠው ለምን አስፈለገ የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል፡፡ አንድ አካል የሰውነት መብት እንዲኖረው ማደረጉ እና በሰዎች ስብስብ የተቋቋመ ማኅበር በሕግ እውቅና መስጠቱ በርካታ ጥቅሞች ቢኖሩትም በዋነኛነት የሚተቀሱ ምክንያቶች ግን ማኅበሩ ቀጣይነት ያለው ሕልውና ለማረጋጥ (perpetual existence) እና የአባላቱ ኃላፊነት ለመወሰን (limited liability) ናቸው፡፡ የማኅበሩ ቀጣይነት ሲባል አባላቱ ቢቀያየሩ ወይም በሕይወት ባይኖሩ የማህበሩ ሕልውና አያከትምም፣ ይቀጥላል፡፡ በዚህም የማህበሩ አባለት ቢቀያየሩ እና በሕይወት ባይኖሩ የማኅበሩ ግዙፍ እና ግዙፍ ያልሆነ ሀብት እንዲሆም ዓለማ ሳይበታተን ለረዥም ዘመን ይቆያል እንዲሁም ከትውልድ ትውልድ ይሸጋገራል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የማኅበሩ ድርጊት የአባላቱ ድርጊት እና የአባላቱ ድርጊትም የማኅበሩ ድርጊት ባለመሆኑ አባላቱም በማኅበሩ ድርጊት ተጠያቂ የሚሆኑት ወይም ኃላፊነት የሚኖራቸው ለማኅበሩ ባደረጉት መዋጮ እንዲወሰን በማድረግ ለንግድ ማኅበራት የሰውነት መብት እንዲኖራቸው ማድረግ ትልቅ ጠቀሜታ አለው፡፡ በዚህም በንግድ አሠራር ረገድ የግል ንብረትን ከኩባንያ ንብረት በመለየት በንግድ ሂደት ሊከሰት የሚችለውን አደጋ በመቆጣጠር ረገድ የንግድ ማኅበር በማቋቋም የንግድ ሥራ ማከናወን ሰፊ ጥቅም አለው፡፡

እነዚህ ንድፈ ሃሳቦች፣ መሠረታዊ ሕግ መርሆች እና የንግድ ማሕበር ጥቅሞች የአገራችን ሕጎች መሠረቶች ናቸው፡፡ የፍትሓ ብሔር ሕጋችን የተፈጥሮ ሰው በተመለከተ በፍትሓ ብሔር ሕጉ የመጀመሪያው ቁጥር ላይ ሰው ከተወለደበት እስከ ሞተበት ቀን ድረስ የሕግ መብት አለው በማለት ይደነግጋል፡፡ በሕግ የሰወነት መበት የተሰጠው አካል በተመለከተ የፍትሓ ብሔር ሕጉ “መንግስት በሕግ በኩል እንደ አንድ ሰው የሚቆጠር ነው”፣ የመንግስት የግዛት ክፍሎች፣ ሚኒስቴሮች፣ የህዝብ አስተዳደር ክፍሎችና ለትርፍ ያልተቋቋሙ ማህበራት እና የንግድ ማኅበራት በሕግ የሰው መብት ያላቸው ስለመሆናቸው ደንግጓል፡፡ በዚህ መሠረት እነዚህ አካላት ውል መዋዋል፣ የንብረት ባለቤት መሆን መክሰስና መከሰስ የሚችሉ ስለመሆናቸው ህልውናቸው ከመሠረትዋቸው ወይም ካቋቋቀምዋቸው ሰዎች የተለየ ህልውና ያላቸው መሆናቸው ከመደንገጉ በተጨማሪ “የማሕበሩ መብቶችና ግዴታዎች የአባሎቹ ግዴታዎችና መብቶች አይደሉም፣” እንዲሁም “የማኅበሩ አባሎች መብቶችና ግዴታዎች፣ የማኅበሩ መብቶችና ግዴታዎች አይደሉም::” በማለት በግልጽ ደንግጓል፡፡ እነዚህ የሕግ ድንጋጌዎችም ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበርና አክስዮን ማኅበር ጨምሮ በንግድ ሕጋችን ለሚቋቋሙ የንግድ ማኅበራት ተፈጻሚነት እና አግባብነት አላቸው፡፡

በኢትዮጵ ንግድ ሕግ መሠረት ተራ የሽርክና ማሕበር፣ የእሽሙር ማኅበር፣ የኅብረት ሽርክና ማኅበር፣ ሁለት ዓይነት ኃላፊት የሽርክና ማኅበር፣ የአክስዮን ማኅበር እና ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር የሚባሉ የንግድ ማኅበራት አሉ፡፡ የሽርክና ማሕበር፣ የእሽሙር ማኅበር፣ የኅብረት ሽርክና ማኅበርና ሁለት ዓይነት ኃላፊት የሽርክና ማኅበር ሽርክና (partnerships) ሲሆኑ የአክስዮን ማኅበር እና ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ደግሞ ኩባንያዎች (companies) ሲሆኑ ከእሽሙር ማኅበር በስተቀር ሁሉም የንግድ ማኅበራት በሕግ የሰው መብት እንዳላቸው ይቆጠራሉ፡፡ ከዚህ በላይ እንደተገለጸውም እነዚህ የንግድ ማኅበራት የራሳቸው የሆነ ከአባላቶቻቸው የተለዬ ህልውና ያላቸው ለተቋቋሙበት ዓላማ ማሳካት የሚስችል ውል መዋዋል ችሎታ ፣ የንብረት ባለቤት የመሆን መብት ፣ መክሰስና መከሰስ የሚችሉ አካላት መሆናቸው የኢትዮጵያ ሕግ ይደነግጋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የንግድ ማሕበሩ መብቶችና ግዴታዎች የአባሎቹ ወይም የባለአክስዮኖቹ ግዴታዎችና መብቶች እንዳልሆኑና የንግድ ማኅበሩ አባሎች ወይም ባለአክስዮኖች መብቶችና ግዴታዎች የንግድ ማኅበሩ መብቶችና ግዴታዎች እንዳልሆኑ በግልጽ በኢትዮጵያ ሕግ ተደንግጓል፡፡ በአገሪቱ ያለ ነጋዴም ሆነ የውጭ ባለሀብቱ በአገሪቱ የንግድ ሥራ የሚያከናውነውና ንዋዩ የሚፈሰው ይህንን ሕግና የሕግ ማዕቀፍ መሠረት በማደረግና በዚህ ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ባለው ሕግ ላይ እምነት በመጣል ነው፡፡ ይህ ሕግ ከላይ የተቀመጡት እና ሌሎች ንደፈ-ሐሳቦች፣ መሠረታዊ የሕግ መርሆችና ጠቀሜታች አካቶ በሕግ መፅሓፍት የተቀመጠ ቢሆንም ይህ በትክክል በተግባር ላይ ይውላል ወይ የሚለው ጥያቄ ማንሳቱና መመርመሩ አሰፈላጊ ነው፡፡ በዚህም ከዚህ በላይ የተመለከቱትን የንግድ ማኅበራት በተመለከተ አለም አቀፋዊ ገጽታ ያላቸው ንደፈ ሀሳቦች፣ መሠረታዊ የሕግ መርሆችና የኢትዮጵያ ሕግ ድንጋጌዎች አተገባበር እና የፍርድ ቤቶች አሠራር እየተካሄደ ያለው እንደ ህጉ ነው ወይስ በተቃራኒው ነው የሚለውን ጭብጥ አስመልከቶ አንድ በፌደራል ፍርድ ቤቶች ውሳኔ ያገኘ ጉዳይ አንስቶ መመልከቱ ለማረምም ለመማርም አስፈላጊም ጠቃሚም ነው፡፡

ይህ ጉዳይ የተጀመረው ወ/ሮ ክንዲሓፍቲ ኢታይ የተባሉ ሰው የፀጉ ብርሃነ ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ባለ አክስዮን ከሆኑት ከአቶ ፀጉ ብርሃነ ጋር ትዳር መስርተን ነበር በማለት ባቀረቡት የባልና ሚስት ክስ መነሻነት ነው፡፡ በዚህ የባልና ሚስት ክርክር ጉዳይ ወ/ሮ ክንድሓፍቲ ከአቶ ፀጉ ብርሃነ ገ/እግዚአብሔር ጋር የትዳር ግንኙነት አለኝ በማለት ባቀረቡት አቤቱታ መነሻነት ፀጉ ብርሃነ ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ለደንበኞቹ ከውጭ አገር ያስመጣቸው 1ኛ. በጉሙሩክሰነድ (ዲክላራሲዮን / ቁጥር S-763 የሞተርቁጥር 131107038387 እና 131107038487 2ኛ/ በጉሙሩክሰነድ (ዲክላራሲዮን / ቁጥር S-784 የሞተርቁጥር 131107038247 እና 131107038497 3ኛ/ በጉሙሩክሰነድ (ዲክላራሲዮን / ቁጥር S-705 የሞተር ቁጥር 9136003029 የሆነው ሎደር ማሽነሪ ይታገዱልኝ ሲሉ ለፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ጥያቄ ያቀርባሉ፡፡

በዚህ ጥያቄ መነሻነትም ፍ/ቤቱ ለገቢዎች እና ጉሙሩክ ባለስልጣን አቃቂ ቃሊቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት በላከው ትእዛዝ እነኝህ ንብረቶች በአቶ ፀጉ ብርሃነ ገ/ እግዚአብሔር ስም የተመዘገቡ ከሆኑ ብቻ ወደ ሶስተኛ ወገን እንዳይተላለፉ ሲል ትእዛዝ ይሰጣል፡፡ ቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ እነኝህ ንብረቶች የአቶ ፀጉ ብርሃነ ገ/እግዚአብሔር አለመሆናቸውን ንብረቶቹ የፀጉ ብርሃነ ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር መሆናቸው በመግለጽ በ29/12/2006 ዓ/ም በተጻፈ መልስ ለፍርድ ቤቱ ያሳውቃል፡፡ ይህ ሆኖ ሳለ ፍ/ቤቱ የቀድሞውን ትእዛዙን እራሱ በመሻር በነሐሴ 29 ቀን 2006 ዓ/ም በሰጠው ትእዛዝ ንብረቶቹ በኩባንያው ማለትም በፀጉ ብርሃነ ትሬዲንግ ኀኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ስም የተመዘገቡ ቢሆንም እስከ መስከረም 7 ቀን 2007 ዓ/ም ድረስ ወደሶስትኛ ወገን ሳይተላለፉ ታግደው ይቆዩ የሚል ትእዛዝ ይሰጣል፡፡ ፀጉ ብርሃነ ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ይህን ትእዛዝ በመቃወም በጳጉሜ 3 ቀን 2006 ዓ/ም አቤቱታ ለፌደራል ፍርድ ቤት ቢያቀርብም፣ በተደጋጋሚ በነበሩት የችሎት ቀጠሮዎች ም ንብረቶቹ የታገዱት ከህግ ውጪ መሆኑን እና በዚህም በኩባንያው ላይ ከባድ ጉዳት እየደረሰበት መሆኑን ያሳሰበ ቢሆንም ከፍ/ቤቱ ምንም አይነት ምላሽ ሳያገኝ ይቆያል፡፡

በመጨረሻም ፍ/ቤቱ በመስከረም 14 ቀን 2007 ዓ/ም በሰጠው ትእዛዝ አመልካች የክርክሩ ተካፋይ ባልሆነበት እና ባልተከሰሰበት ሁኔታ አቶ ፀጉ ብርሃነ ገ/እግዚአብሔር የፀጉ ብርሃነ ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ማለትም ኩባንያው ውስጥ ከፍተኛ የአክሲዮን ድርሻ ያላቸው በመሆኑ ምንም እንኳን መኪኖቹ እና ማሽኖቹ የፀጉ ብርሃነ ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ማለትም የኩባንያው ቢሆኑም አመልካች ብር 3000000 (ሶስትሚልየን) እስኪያሲዝ ድረስ ንብረቶቹ ታግደው ይቆዩ በማለት ትዕዛዝ ሰጠ፡፡ የፀጉ ብርሃነ ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ይህ በፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ውሳኔ ቅር በመሰኘት ይግባኙን ለፌደራል ከፍተኛው ፍ/ቤት የይግባኝ አቤቱታ አቀረበ፡፡ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሥር ፍርድ ቤት የሰጠውን ትዕዛዝ በማጽናት በሥር ፍ/ቤቱ የተፈጸመውን የህግ ስህተት ሳያርመው ቀረ፡፡ ፀጉ ብርሃነ ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር የፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤትና የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፍርዶች ፍጹም የሆነ መሠረታዊ የህግ ስህተት የተፈጸመባቸው መሆናቸውን መዘርዘር ለፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት አቤቱታ አቀረበ፡፡ ይህ ችሎቱም የፀ ጉ ብርሃነ ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር አቤቱታ ሳይቀበለው ቀረ፡፡

በዚህ ውሳኔያቸው ፀጉ ብርሃነ ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር የክርክሩ ተካፋይ ባልሆነበት ሁኔታ አንድ የኩባንያ አባል ወይም ባለአክስዮን የሆነ ግለሰብ በመከሰሱ ብቻ ማህበርተኛውን ከንግድ ማህበሩ በህግ የተለያዩ መሆናቸውን፣ የንግድ ማህበር እራሱን ችሎ እና ከማህበርተኞቹ ፍጹም ልዩ በሆነ ሁኔታ ሊከስ እና ሊከሰስ የሚችል መሆኑን፣ መብት እና ግዴታዎቹም ከማህበርተኞቹ ፍጹም የተለዩ መሆናቸውን፣ የንግድ ማህበሩም እራሱን ችሎ በስሙ ንብረቶች ሊያፈራ የሚችል መሆኑን የሚደነግገውን የሀገሪቱን የህግ ስርአት ወደጎን በማለት ግልጽ በሆነ ሁኔታ የጣሰ ትእዛዝ እና ፍርድ ነው፡፡

የኢትዮጵያ የፍ/ብሔር ህግ ቁ. 451 ድንጋጌ መሰረት አንድ በህግ አግባብ የተቋቋመ ማህበር በውስጡ ካሉት ሰዎች (ማህበርተኞቹ) ልዩነት ያለው መሆኑን፣ የማህበሩ መብቶች የማህበርተኞቹ መብቶች ሊሆኑ እንደማይችሉ ግልጽ በሆነ ሁኔታ ደንግጓል፡፡ ይህንኑ የህግ ትርጉም አስመልክቶም የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በመ/ቁ 34945 በሰጠው አስገዳጅ የህግ ትርጉም ማህበርተኛውን ከንግድ ማህበሩ በህግ የተለያዩ መሆናቸውን፣ የንግድማህበር እራሱን ችሎእና ከማህበርተኞቹ ፍጹም ልዩ በሆነ ሁኔታ ሊከስ እና ሊከሰስ የሚችል መሆኑን፣ መብት እና ግዴታዎቹም ከማህበርተኞቹ ፍጹም የተለዩ መሆናቸውን፣ የንግድ ማህበሩም እራሱን ችሎበ ስሙ ንብረቶች ሊያፈራ የሚችል መሆኑን አስምሮበታል፡፡

ሕጉና የሕጉ ትርጉም ይህ ሆኖ እያለ የፌደራል ፍርድ ቤቶች ከላይ የተገለጸውን የህግ መርህ በመከተል ማህበሩን እና ማህበርተኛውን በመለየት ንብረቶቹ በፀጉ ብርሃነ ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ስም የተመዘገቡ መሆናቸው ሲረጋገጥ ብቻ ታግደው ይቆዩ የሚል ትእዛዝ ከሰጠ በኋላ ይህንኑ ትክክለኛ የህግ መርህን በመተው ባለአክሰዮኑ በፀጉ ብርሃነ ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ድርጅት ውስጥ ያለው ድርሻ ከፍተኛ በመሆኑ ንብረቶቹ በፀጉ ብርሃነ ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ስም የተመዘገቡ ቢሆንም ፀጉ ብርሃነ ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ብር 3,000,000.00 (ሶስት ሚልየን ብር) እስኪያሲዝ ድረስ ታግደው ይቆዩ ሲል ትእዛዝ መስጠቱ የፌደራል ከፍተኛው ፍ/ቤት እና የጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ይህንኑ ሀሳብ በማጠናከር ትእዛዙን ማጽነቱ ከላይ ከተዘረዘረው ህግ እና የሰበር ችሎቱ የህግ ትርጉምን የጣሰ ነው፡፡

በዚህ በፍርድ ቤት በቀረበው ክርክር ፀጉ ብርሃነ ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር በህግ አግባብ የተቋቋመ እና እራሱን የቻለ የህግ ሰውነት ያለው መሆኑ ክርክር አላስነሳም ፡፡ በፍ/ቤቶችም የእግድ ትእዛዝ የተሰጠባቸው መኪኖች እና ማሽን ፀጉ ብርሃነ ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ንብረቶች መሆናቸውም ግልጽ ነው፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ በእነዚህ ንብረቶች ላይ ፍጹም የሆነ የባለቤትነት መብት ያለው እና በንብረቶቹም የማዘዝ መብት ያለው ፀጉ ብርሃነ ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ የማህበ ሩመብት ከማንኛውም ማህበርተኛ መብት ፍጹም የተለየ በመሆኑ ምማንኛውም ፀጉ ብርሃነ ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር በለአክስዮን በእነዚህ ንብረቶች ላይ በህግ የታወቀ እና የተረጋገጠ ምንም አይነት የባለቤትነት መብት የለውም፣ ሊኖረውም አይችልም፡፡ በዚህም መሰረት ባለእከስዮኑ አቶ ፀጉ ብርሃነ ገ/እግዚአብሔር የቱንም ያህል በፀጉ ብርሃነ ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ውስጥ ከፍተኛ የአክሲዮን ድርሻ ያለው ቢሆንም በእነዚሁ ንብረቶች ላይ የባለቤትነት መብት የለውም፡፡ አቶ ፀጉ ብርሃነ ገ/እግዚአብሔር ፀጉ ብርሃነ ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ውስጥ ከፍተኛ ባለአክሲዮን በመሆኑ በኩባንያ ውስጥ የተሻለ ተጠቃሚ ሊሆን የሚችለው ባለው አክሲዮን ድርሻ መጠን ፀጉ ብርሃነ ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር የሚያስገኘው ትርፍ ቢኖር በአክሲዮን ድርሻው መጠን የትርፍ ድረሻ ማግኘት፣ እንዲሁም አክሲዮኖቹን ለሌላ ሶስተኛ ወገን የማስተላለፍ መብት እንጂ ከዚህ ባለፈ ሁኔታ ፀጉ ብርሃነ ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ንብረቶች ላይ ባለመብት የሚሆንበት የህግ አግባብ የለም፡፡ አቶ ፀጉ ብርሃነ ገ/እግዚአብሔር በህግ የተሰጠው መብት ይህ ከሆነ ደግሞ በአቶ ፀጉ ብርሃነ ገ/እግዚአብሔር ላይ መብት አለኝ ሲል የሚጠይቅ ማንኛው ሶስተኛ ወገን ፀጉ ብርሃነ ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር አስመልክቶ ከአቶ ፀጉ ብርሃነ ገ/እግዚአብሔር ላይሊጠይቅ የሚችለው መብት ሁሉ አቶ ፀጉ ብርሃነ ገ/እግዚአብሔር ፀጉ ብርሃነ ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ውስጥ ባለው የመብት ወሰን ልክ እንጂ ከዚህ ባለፈ ሊጠየቅ የሚችል መብት ሊኖር አይችልም፡፡ በዚህም አግባብ አቶ ፀጉ ብርሃነ ገ/እግዚአብሔር በፀጉ ብርሃነ ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ውስጥ ባለው የመብት ልክ ብቻ ነው፡፡ በዚህም መሰረት የፌደራል ፍ/ቤቶች አቶ ፀጉ ብርሃ ገ/እግዚአብሔር በፀጉ ብርሃነ ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ያለውን መብት ወደ ሦስተኛ ወገን ሊያስተላልፍ ይችላል የሚል ግምትና እምነት እንኳን ቢኖራቸው የእግድ ትዕዛዝ ሊሰጥ የሚችለው አቶ ፀጉ ብርሃነ ገ/እግዚአብሔር በፀጉ ብርሃነ ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ውስጥ ያላቸው አክሲዮን፣ ወይም በፀጉ ብርሃነ ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ሊከፈላቸው የሚችል የትርፍ ድርሻ ቢኖር ወደ ሌላ ሶስተኛ ወገን እንዳይተላለፍ ታግዶ እንዲቆይ ከሚሆንው ጪ የአቶ ፀጉ ብርሃነ ገ/እግዚአብሔር ንብረት (መብት) ባልሆነ የፀጉ ብርሃነ ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ንብረት ላይ የፌደራል ፍርድ ቤቶቹ የእግድ ትእዛዝ መስጠታቸው እና፣ ፀጉ ብርሃነ ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ንብረቱን ለማስለቀቅ ብር 3,000,000.00 (ሶስት ሚልየን ብር) አስይዝ ማለታቸው ፍጹም የሆነ የህግ ስህተት ብቻ ሳይሆን መሠረታዊ የህግ መርሆች ጥሰት የተፈጸመባቸው ፍርዶች ናቸው፡፡

በእርግጥ በዚህ ጉዳይ ፍርድ የተሰጠው በመጽሓፍ ካለው ሕግ እና የሕግ መሠረታዊ መርሆች ከሚደነግጉት በተቃራኒው ነው፡፡ ጉዳይ ለአብነት ተነሳ እንጂ በዚህ መልክ የሕግ ጥሰት ብቻ ሳይሆን የሕጉ መሠረት የተናደባቸው በርካታ ጉዳዮችና ፍርዶች ይኖራሉ የሚል ግምት አለን፡፡ ለዚህ ግምትም መነሻ ስህተት ያርማሉ የተባሉት የበላይ ፍርድ ቤቶች ስህተቱን እየባረኩ የስህተቱ ተካፋዮች በመሆናቸው ነው፡፡ ይህ የህግ ጥሰት በአንድ ጉዳይ ብቻ የተፈጸመ ነው የሚባል ቢሆን እንኳን ፍርድ ቤቶች ተገማቾችና እምነት የሚጣሉባቸው አይደሉም የሚያሰኝ ነው፡፡ በዚህ የንግድ ማኅበር አቋቁሞ የሚነግድ የአገር ውስጥ ባለሀብት የሚጎዳ የውጭ ባለሀብትም የሚሸሽ ነው፡፡

************

Guest Author

more recommended stories