ያስጠበቡኝ ጠባብ የኦሮሞ ልሂቃንና ያስጠበበኝ አመለካከታቸው

(በአማን ነጸረ)

ባለፈው ጽሑፍ እንዳመለከትኩት፡- ሁለት ጽንፍ የያዙ ኃይላት ያገሪቱን የፖለቲካ መድረክ ተቆጣጠረዋል–ያንድነት ኃይላት ነን ባዮችና ብሔረሰባውያን፡፡ የየራሳቸው በጎ ጎን እና መነሻ እንዳላቸው የምረዳ ቢሆንም በጎ በጎውን ላቆየውና የሚያሥከፋኝን ልናገር፡፡ (ባለፈው ጽሑፍ ስለአማራ ልሂቃንና አስተሳሰባቸው ያወሳሁ ሲሆን አሁን ደግሞ የኦሮሞ ልሂቃንን እቃኛለሁ፡፡

1– ያለፈው ሥርዓት የሕዝብ ለሕዝብ ማኅበራዊ ገጽታ የሌለው ይመስል ስለጭቆና ዘላለም እያወሩ ፖለቲካውን ብቻ ማጮኽ ርካሽነት ነው!!በፖለቲካውም ቢሆን የኃይለሥላሴን ከፊል-ፊውዳል ሥርዓት በመታገል ረገድ እንደ ልሂቅም፤እንደ ማኅበረሰብም በግልና በነጠላ የሰሜኑ ክፍል ያደረገው ጥረት ከኦሮሚያው ያነሰ አይመስለኝም፡፡ትረካው ቢስተካከል!!

2— “ለእኛ እስከተመቸን ድረስ ሌላው ስለ እኛ ፖሊሲ አያገባውም” የሚል አስበርጋጊና በተለይ ሀቀኛ የኦሮሞ ትግልን ሳይቀር ሌላው ማኅበረሰብ በጥርጣሬ እንዲመለከት ማድረግ ለሌላው ስሜት አለመጨነቅ ነው–ራስ ወዳድነት!!ቢቻል ትግላችን ጭቆናውን ለሚያለባብሰው ልሂቅ የሚተርፍ እንዲሆን መስራት፣ካልሆነም መብታችን ላይ የቆመውን ልሂቅ ነጥሎ ብቻውን ማስቀረት ሲቻል በልሂቁ ሰበብ ሕዝብ ማስቀየም ማንንም አይጠቅምም!!መጀመል ይቅር!!

3– ምኒልክ በሰላም እጅ ያልሰጠውን የኦሮሞ ክፍል በኃይል ማስገበሩ ባይካድም በሂደቱ በተፈጠው አብሮነት አድዋ ላይ የውጭ ወራን በጋራ መመከታችንና በዚህም ዛሬ ማንኛውም የኦሮሞ ተወላጅ የትም አገር ቀና ብሎ እየሄደ፣በግንኙነቱ እንደ ነጭና ጥቁር የልዩነት አጥር ሰርተን ሳይሆን በማ/ሰብ ደረጃ እንደ ማንኛውም ኢ/ዊ ርስ በርስ ከመሳፍንቱ ሳይቀር ተጋብተን ተዋደን መኖራችን እየታወቀ፣“የኢ/ያ ታሪክ የ100 አመት ነው” የሚለውን ትረካ በበኩሌ በፍጹም ባልቀበለውም እሱም ቢሆን የጋራ ማንነት ለመገንባት ከበቂ በላይ መሆኑን ባለማስተዋል፣ምኒልክ ሲዘምቱ በአከባቢያዊ ገዥዎች ቅርምት የተያዘች እንጅ አንድ ሉዐላዊትና በተመሳሳይ ሥነ – ልቡና ውስጥ የነበረች ኦሮሚያ አለመኖሯ እየታወቀ፣አገራዊ አንድነት በሌሎች ሀገሮችም ከሞላ ጎደል በኃይል እንጅ በሪፈረንደም አለመደረጉን ባለመገንዘብ፣በዛ ዘመን የነበሩ ገዥዎች እኛ በምናስበው ልክ የፖለቲካ ስሌት ሰርተው ጨቆኑን የሚለው አሁንም ሊያከራክር የሚችል መሆኑን ባለማሰብ፣ዘመን የነገሥታቱ አስተሳሰብ ላይ ያለውን ተጽእኖ ግምት ውስጥ ሳንሰገባ ባለ በሌለ ሀይል ፍርድ ማዥጎድጎዱ ለሌላ ጽንፍ መፈጠር ምክንያት ይሆናል፡፡

4– መሰረታዊ መርሆዎችን አስቀምጦ እሱን በዘላቂነት ለማስፈጸም ከመጣር ይልቅ ኮሽ-ጠሽ-ተሸ የሚሉ ትናንሽ ግጭቶችን እየጠበቁ ብሔረሰባዊ ማንነት በማላበስ ላይ መንጠልጠሉ ጊዜውን የሚመጥን የትግል ስልት አይመስለኝም፡፡ትግሉ የመሪና የዐላማ ጥራት ሳይሆን ስሜታዊነት እና ወቅታዊ ብሶት መራሽ ሆኗል፡፡

5– ትግሉ ደንብሹዋል!!ሩቅ መሄድ አያስፈልግም!!ህወሓት መራሹ የትግራይ ልሂቅ ትግል አካሄድ ላይ ያለኝ ቅሬታ ከሌሎቹ ልሂቃን ያላነሰ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ከሕወሓት ትግል ግን ሌሎቹ የሚማሩት እንዳለ አስባለሁ፡፡ህወሓት ሲነሳ በነበረውና አሁን ባለው አቋሙ መሀል ቀላል የማይባል የአቋም ለውጥ ጊዜውን እየተመለከተ አድርጓል፡፡ለምሳሌ፡- ሲጀምር ለመገንጠል እና የማሌሊት ሥርዓት ለመፍጠር ነበር፡፡ነገር ግን የሕዝቡን ሥነ – ልቡና እና የዓለምን የፖለቲካ አዝማሚያ ተመልክቶ የራሱን ርእዮት የምትሸከም ኢ/ያ ወደ ማዘጋጀት ነው የሄደው፡፡ኦሮሞው ኤሊት በተለይ ኦነግን ታዛ አድርጎ የሚንቀሳቀሰው ኃይል በኦሮሚያ ሪፐብሊክ ላይ እንደተቸከለ ነው–እስካሁን ድረስ፡፡ሚያሳዝነው ይህን አካሄድ ፈትሸው አማራጭ ሀሳብ ያቀረቡት ወዲያ በጠቅላዩ ኢ/ዊ፤ወዲህ በኢህአዴግ የሚሰራባቸው ቀጥተኛ ያልሆነ የተንበርካኪነት ፕሮፖጋንዳ ሳያንስ ለስንት አመት ታግለው መንገድ የከፈቱለት ተተኪ ልሂቅ በከሃዲነት ሲከሳቸው ይውላል፡፡ልክ የአማራው ጽንፈኛ ልሂቅ ከእኔ ጋር ያልሆነ ሁሉ ኢ/ዊነት የራቀው የወያኔ/ሻዕቢያ ባንዳ ነው እያለ ሀሳብ እንደሚደፍቀው እዚህ ደግሞ የነፍጠኛ ፈረስ፣የወያኔ ተላላኪ፣ዳግማዊ ጎበና የሚሉ ትናንሽ ቅርጫቶች አሉ፡፡

6– በቁቤ መጻፍና መተዳደር ከተጀመረ ሁለት አሠርት አመታት ቢያልፉም ሥልጣን ላይ ብቻ አተኩሮ ስለሚሰራ ይህ ነው የሚባል ሥነ – ጽሑፋዊ አሻራ እንኳ ሳያስቀምጥ ቅጥር ደራሲ ላይ ተንጠልጥሎ በኤርትራ የብረት ዘንግ ኢ/ዊነትን ለመቀጥቀጥ የሚጥር ጠርዘኛ ልሂቅ ማየት ያሳምማል፡፡ያ! ሁሉ ትግል የታለ ፍሬው፤የተመነዘረው??!!የታል የኦሮሚፋ ፊልሙ፣ድርሰቱ፣ጋዜጣው፣ታሪኩ…??ያለውን እድል በቅጡ ሳይጠቀሙ ዝምብሎ ስለትናንቱ ታላቅ ሰው ስለ ኦናሲሞስ በነፍጠኞች መጨቆን ደጋግሞ መተረክ ያስተዛዝባል!!ሌላውን በታሪክ የሚኖር የምንለውን ያህል እኛም በጭቆና ትርክት የምንኖር ከሆንን ለአዲሱ ትውልድ የሚቆይ ውርሳችን ቂም እንጅ የጭቆናን ታሪክ በስራ ገልብጦ መጻፍን አይሆንም!!

7– ከሁሉም በላይ የሐበሻ ልሂቃን የኛን ታሪክ በ“ዘረ – እኛነት” ክደው “ዘረ – እኝኝ” ሆነዋልና እኛም የእነሱን ታሪክ “ተረት-ተረት” እያልን እናሳንሳለን ባዮችን በየአደባባዩ ማጀገን የሀገሪቱን የዘመናት ታሪክ አጥፍቶ ለመጥፋት እንደመሞከር ነው የማየው፡፡ምክንያቱም ታሪኩ የአንድ ንጉሥ አይደለም፤የህዝብ ነው–ያውም እንደ አድዋ፣አክሱም፣ላሊበላ፣የሰሎሞናዊው ሥርዓት የመካከለኛ ዘመን የሥነ – ጽሑፍ ቅሪት፣የመሳሰሉት…ሀብትነታቸው ከኢ/ያም አልፎ የአፍሪካ ኩራት ነውና ነጭ ከጥቁር የተቀበለውን ታሪክ በእልህ ተሞልቶ ተረት-ተረት ማለት ያስቀይማል!!ጥፋትን በጥፋት!!

8– የሆነ ዩኒቨርሲቲ ኦሮሞዎች ከሌሎች ብሔሮች ስለተጋጩ እንገነጠላለን (ግለሰባዊ ጸቦችን ቡድናዊነት ማላበስ ከተለመደ ቆየ)፣የሰንዳፋና ቡራዩ አርሶ አደሮች ስለተፈናቀሉ መፍትሔው ሪፐብሊክ ማቋቋም ነው፣ዶ/ር እንትና ያልሆነ ንግግር ስለተናገሩ ፌደራሊዝሙን አቋርጠን እንወጣለን፣የተፈጥሮ ሀብታችንን እነ እንትና ስለያዙት መፍትሄው ተለያይቶ በምስራቅ አፍሪካ ደረጃ መጎራበት ነው….እንሄዳለን!…እንዲህና የመሳሰሉ አመለካከቶች ዘወትር ያስገርሙኛል፡፡በደል ካለ በደሉን በመዘርዘር ካጀንዳው ጎን ሌሎችን አስተባብሮ በማሰለፍ በዳዩን አብሮ ማስወገድና የተሻለች ለሁሉም ብሔረሰብ የምትሆን ኢ/ያ እንገንባ ማለት ሲቻል …በእንገነጠላለን..አስፈራርቶ ጥቅም ለማስከበር መሞከር በሌላ ወገን ላለው ማ/ሰብ ክብር አለመስጠት ነው!!ይብዛም ይነስም ገዥው መደብ ፈለቀባቸው የሚባሉት አካባቢዎች ከኦሮሚያ ጋር የነበረው የግዛት አንድነት በተቋረጠበት ወቅትም ኖረዋልና!!እኔ የምመኛት ኢ/ያ “በብሔሬ ቁመት ልክ የበላይ ሆኘ ልግዛባት” የምትባል ሳትሆን የሕግና ተቋማት የበላይናት የሰፈነባትን ኢ/ያ ነው!! እንጅ ልክ ከ1984 ዓ.ም እስከ ቅርብ ጊዜ ድረሱ የማስተር ፕላን እሰጥ አገባ ድረስ ኮሽ ባለና መንበረ – መንግሥት በተነቀነቀ ቁጥር እንደ ጦስ ዶሮ በክልሉ የሚኖር ደሃ አማራ ላይ የኖረ ሂሳብ ለማወራረድ የሚጥር ህሊና በጉያ ይዞ እንዳላዩ ማለፍ ያሳምማል!!

9– ከሌላ ብሔር የተገኙና አገራዊ ተግባር የፈጸሙ ሰዎችን ማሳነሳችን ሳያንስ ከኦሮሞ አብራክ ተገኝተው ኢ/ዊ ለሆነ ዐላማ በሕይወትም፣በንብረትም፣በእውቀትም ላገለገሉ ሰዎች ለምን ለይተው ለኦሮሚያ ብቻ አልሰሩም በሚል ሰበብ ዋጋቸውን ለማሳነስ የሚካሄደው ዘመቻ አሳፋሪ ነው!!ልክ በአሁን ሰዓት ጠቅላዩ ልሂቅ እያደረገ እንደሚገኘው የቁቤው ትውልድም ሆነ ባለሀብቱ የኦሮሚያ ተወላጅ በመንግሥት የልማትና የፖለቲካ መድረክ እንዳይሳተፍ ግፊት እያደረግን መልሰን በአገዛዙ ውስጥ ቁጥራችን አነሰ ማለት ራስን መቃረን ነው!!መች ተበረታታና–ቢበረታታስ በሙሉ ሀሳቡ ልቡ ሳይከፋፈል እንዲሳተፍ መች የሞራል ድጋፍ ተሰጠው–ባንዳ ተላላኪ በሚል የስድብ ናዳ እየተሳደደ!!ከሌላው ኢ/ዊ በመቻቻል መርህ ቁጭ ብሎ እንዳይነጋገር “ድሮ የተሸወድነው ይበቃናል” በሚል ሰበብ ከመድረኩ እንዲሸሽ እየተገፋ!!

10– ልደምድም፡- (1) ትናንት ለደረሱ በደሎች ኀዘኑን እጋራለሁ–እናንት የቆሰላችሁ ቁስላችሁ ቁስሌ ነው–እላለሁ፡፡(2) በዚያው መጠን የትናንቱን በደል ዛሬ ላይ ለማወራረድ መነሳትንና የሚያወራርዱትን ወይም ለማወራረድ የሚገፋፉትን እንዳላዩ ማለፍን እጸየፋለሁ!!ምክንያቱም የ2ቱንም ውጤት ለማየት ብቻ ሳይሆን ጽዋውንም ለመቅመስ እድል ነበረኝ!!

የበትረ – ሥልጣኑን መሪ ስለሚዘውረው ልሂቅ ያለኝን ቅሬታደግሞ ሰብስቤ ይዤ እመለሳለሁ፡፡ ማን ታፍኖ ይሞታል!!

**********

Guest Author

more recommended stories