የሚያስመርሩኝ የአማራ ልሂቃንና ያስመረረኝ አስተሳሰባቸው

(በአማን ነጸረ)

ሁለት ጽንፍ የያዙ ኃይላት ያገሪቱን የፖለቲካ መድረክ ተቆጣጠረዋል–ያንድነት ኃይላት ነን ባዮችና ብሔረሰባውያን!!

2ቱም የየራሳቸው በጎ ጎን እና ለሀሳባቸው አሳማኝ ምክንያቶች እንዳላቸው እረዳለሁ፡፡ሆኖም በጎ በጎውን ላቆየውና የሚያሥከፋኝን ልናገር፡፡ያደፋፈረኝ የልሂቃኑን የብሔር መነሻ ከአመለካከታቸው ለማስተሳሰር የደፈረው የዶ/ር መረራ መጽሐፍ ነው፡፡

1– ትናንት የተፈጸሙ በደሎችን ሽምጥጥ አድርገው ይክዳሉ ወይም ያለባብሳሉ፡፡ “እኔ አልጨቆንኩህም ሥርዓቱ ነው” ማለት አንድ ነገር ነው፡፡ነገር ግን ተጨቆንኩ ብሎ ያመነን ማኅበረሰብ–ያውም ስለጭቆናው ከአያት ቅድመ – አያቱ ብቻ ሳይሆን ከበዙ የአማርኛ ምሳሌያዊ አነጋገሮች ሊረዳ የሚችልን ፊደል የቆጠረ ትውልድ ስለ አንተ አለመጨቆን ታሪክ እጽፍልሀለሁ ማለት ግብዝነት ነው!! “ነገሥታቱ እናንተን ብቻ ሳይሆን እኛንም ጨቁነዋል” የሚለው መከራከሪያ እኔ ራሴ ብዙ ጊዜ ብጠቀምበትም በኢ/ያ የጭቆና ትረካ አቀራረቡ ትክክል አልሆንልህ ይለኛል፡፡ምክንያቱም የአንድ ብሔር የራስ በተባለ ሰው (ብሔር) መንገላታትና ከራስ ውጭ ባለ ሰው(ብሔር) መንገላታት ያለው ትርጉም ይለያያል፡፡ለምሳሌ፡- የአጼ ቴዎድሮስ የሸዋን መሳፍንት እጅ መቁረጥ እና የአጼ ምኒልክ የኤርትራውያንን ምርኮኞች እጅና እግር መቁረጥ ታሪኩን እንደሚዳኘው ሰው የብሔር ማንነት ትርጉሙ ሊለያይ እንደሚችል መረዳት አለብን፡፡የምኒልክ ንጉሥ ተ/ሃይማኖትን እምባቦ ላይ መውጋት ራሱን እንደ ምኒልክ ልጅ ለሚቆጥረው የዛሬ ዘመን የጎጃም ልሂቅ ምንም ላይመስለው ይችላል፤ለወላይታው ልሂቅ ግን የምኒልክ ጦናን መውጋት የአባት ተግባር ሳይሆን በማንነት ላይ የተቃጣ የጎረቤት ትንኮሳ ተደርጎ ነው የሚታየው፡፡የምኒልክ የደቡብ ሕዝቦችን የማስገበር ሂደት አፈጻጸሙ ታይቶ “ባልተወለደ አንጀቱ…” ቢባል አይግረመን፡፡ “እኔ ስላልተሰማኝ ለምን ይሰማችኋል??” አንበል!!በቃ!! የተሰማው የተሰማውን በተሰማው መጠን ይናገር!!ድርጊቱን እስካመንን ድረስ ቢያንስ ለድርጊቱ ጥፋተኝነቱን የሚወስድ አካል ሊኖር ግድ እንደሆነ እንስማማ–ባይሆን ለአባት እዳ ልጅ እንዳማይጠየቅ እናስረዳ!!

2– አዎ!!ትናንት “ጫልቱ” በሚለው ሥም ብቻ ሳይሆን በ“ዘቢደርም” ይሳቅ ነበር፡፡እናስ?? ዝም በሉ ነው?? ይሄ ማለት እኮ ስህተትን በስህተት ማረም ነው፡፡ከፈለጉ የዘቢደር ቤተሰቦችም አብረው ከጫልቱ ቤተሰቦች ጋር ሆነው የትናንቱ ድርጊት ልክ እንዳልነበረ መናገር እንጅ ትናንት በኛም ስለተፌዘበን የትናንቶቹ በእናንተ ልጅ ማፌዛቸው ትክክል ነው–ዝም በሉ– ማለት በምንም አመክንዮ ልክ ሊሆን አይችልም፡፡የት ላይ እንዳመመው የሚናገርን ታማሚ አንተ ብቻ አይደለህም እኔም እዚሁ ቦታ ላይ አሞኛልና ዝም በል እንደማለት እኮ ነው፡፡ያ ደግሞ የስሜት መጋራትን ቢፈጥርም ህመምን ማመቅ ነው፡፡የታመቀ (የተደበቀ) በሽታ መች ፈውስ አለውና–ውስጥ ውስጡን ተንፈቅፍቆ አመርቅዞ ይፈነዳል እንጅ!!ተውማ ያመመው ሕመሙን ይተንፍስ!!ቢቻል አብረነው እንታመም፣ካልተቻለ ህመሙን ይናገር–አንከልክለው!!

3– ማን ነው የብሔር ጥያቄን በብቸኝነት ለህወሓት ያሸከመው??የመገንጠልን አጀንዳ ያቀነቀነው ህወሃት ብቻ ነው እንዴ??ኋላ በኢህዴን/ብአዴንነት የተከሰተው ኢህአፓ የብሔር ብሔረሰቦችን መብት እስከ መገንጠል አራማጅ አልነበረ እንዴ??ይነበብ እንጅ የአስማማው ኃይሉ ኢህአሠ ክፍል-2 ገጽ-139!!እረረረ!! ይሰማ እንጅ የአማራ ሳይንቱ ያውም የቤተ – አምሐራው ዋለልኝ መኮነን!!እንዴት አንድ ወገን ላይ አበሳው ይደፈደፋል??ዋሽንግተን ዲሲ ላይ አማርኛ የስራ ቋንቋ በመሆኑ የሚኮራ ልሂቅ ሲዳማ በራሱ ቋንቋ መማሩ ለሀገር አንድነት አደጋ ስለመሆኑ ቢሰብከኝ እንዴት አምነዋለሁ?? “ሴትነት የሚለው ቡድናዊ የማንነት ጎራ ሰብእነት የሚለውን ግላዊ አቋም የሚቀበለውን ያህል ብሔረሰባዊነትም ግለሰባዊነትን መሸከም ይችላል” ብየ ብከራከርስ??ደግሞስ “እኔ ማን ነኝ??” የሚለውን ግለሰባዊ ጥያቄ ለመመለስ ራሴን ከቡድኑ ማነጻጸሬ ይቀራል??–የማንነቴ ትርጉም ከቡድኑስ ይቀዳ የለ??–ለዚያውም በማ/ሰብ ተኮሩ አፍሪካ እየኖርኩ??!! ስለ ግለሰብ መብት ዓለምዓቀፋዊ ተቀባይነት የሚሰብኩን አውሮፓውያን የኛ ስደተኛ ወገኖች ላይ ድንበራቸውን ዘግተው ለስጥመት የሚዳርጓቸው ዜግነት ወይም የአውሮፓ ኅብረት አባልነት የሚባል ሰፊ የቡድን ጭንብል ስላለ አይደለም ወይ??

4– እረ እንደው አያ፡- “የመገንጠል ጥያቄን ያነሱ ኃይሎች እንዴት የኃይል የበላይነት ሊያገኙ ቻሉ??” የሚለውን መርምሮ ያለፈ ኢፍትሀዊ ታሪክን የወደፊቱን አካሄድን ለመቅረጽ ማዋል ይሻላል?? ወይስ የብሔረሰብ ጥያቄን ባጓጉል ቁንጽል የግእዝ እውቀት “ብሔር ማለት ሀገር ነው ስለዚህ ጎሣ ነው የምንላችሁ” እያሉ በቋንቋ ሥም የእኩልነት ጥያቄዎችን ማንኳሰስ?? በግእዙ ዘይቤስ ቢሆን ‘በቦታ ነዋሪው፤በነዋሪው ቦታው’ መጠራቱ የተለመደ አይደል!!ያስ ባይሆን ነገደ – ይሑዳ፣ነገደ – ቢኒያም እንዲሉ ወይም ቤተ – አምሐራ፣ቤተ – ጉራጌ የመሰሉ ተለዋጭ ለዘብተኛ ቃላትን መጠቀም እየተቻለ ይሄን ያህል ሰዎችን በማንነታቸው ሆድ የሚያስብስና ለራሱ ለአማርኛ ተናጋሪው ማኅበረሰብ የማንጠቀመውን “ጎሣ” ብሎ አሳናሽ ስያሜ በየብሔረሰቡ ስንለጥፍ ፍልጥ ቢነሳብን ምን ይገርማል??!!

5– የጎሣ አስተዳደር አያሥፈልግም እያልን ስንዘምት አብረውን “አዎ እውነት ነው አያስፈልግም” የሚሉ ከሌላ ብሔር አባላት የተገኙ ልሂቃን ቁጥር አጥጋቢ ነው??እውነት አሁን እኛ በምንለው የኢትዮጵያዊነት ትርጉም ሀገራዊ መግባባት አለ??አሁን ያለው የፌደራሊዝም ሥርዓት ይቀየር ብንል ከአማራው ውጭ ያለው ልሂቅ ሀሳቡን ምን ያህል ይቀበለዋል??የምናቀርበው የተፍታታ አማራጭስ የታለ?? እስኪ ይውጣና እንየው!!እንዳንሸወድ!!በየክልሉ ያሉ ግጭቶች ዋና መነሻ ራሳችንን የማስተዳደር መብታችን ከዚህም በላይ ሊሰፋ ይገባል የሚሉና ትናንት ሊነሱ ቀርቶ ሊታሰቡ የማይችሉ ማንነትን የማስከበር ጥያቄዎችን የተመረኮዙ እንጅ ትናንትን የሚናፍቁ ጥያቄዎች አይደሉም፡፡ለምሳሌ፡- በጎፋ ወረዳ የሚገኙት የጎፋና የቁጫ ሕዝቦች ጥያቄ ‘የሰፋ ራስን የማስተዳደር መብት ይሰጠን’ የሚልና ‘ፌደራሊዝሙ ከዚህም በላይ ይለጠጥልን’ የሚል ነበር፡፡የእኛ አንዲት ኢ/ያ ተቆርቋሪዎች ግን ጭብጡን ሳይሆን ነገሩ ወያኔን ለማሳቀል ይረዳናል በሚል ሰበብ ጠልፈው ያጮኹታል፡፡የተሻለ የሥርዓት አማራጭ ካልቀረበ በቀር በወያኔ መውደቅ ብቻ የዘመናት ያገሪቱ ጥያቄ ሊመለስ እንደማይችል እያወቁ!!

6– አያቶቻችን ከማንም ብሔር በበለጠ የቁጥር ሚዛን ባካባቢው ካሉ ሌሎች ማ/ሰቦች ተባብረው የውጭ ወራሪን ታግለው ሊሆን ይችላል፡፡ታዲያ እሱ እኮ በሥርዓቱ የተሻለ ኢኮኖሚያዊ፣ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ተጠቃሚነት ስለነበራቸውና እንዲሁም ለረጅም ዘመናት ዘመነ – መሳፍንት እንኳ ሳይበግረው በኢትዮጵያዊነት ጥላ ስር የቀጠለ የአብሮነት ቆይታ ስለነበራቸው ነው፡፡ይሄ መላ ምት አይደለም!!ሀቅ ነው!!በኢህአዴግ ዘመን በነበረው የባድመ ውጊያ የትግራይ ተወላጆች የከፈሉት መስዋዕትነት ከማንም በላይ የነበረ መሆኑን ለመረዳት ከዘመቻው የተመለሱትን መጠየቅ ነው፡፡ያ የሆነው ተጠቃሚነት ብሔራዊ ስሜት ላይ ጫና ስላለው ነው፡፡የኛ አማሮች ብሔራዊ ስሜትም እኛ ሁላችን ባንጠቀም የሚዛመዱን መሳፍንት ስለተጠቀሙ ብሔራዊ ስሜቱ ሰረጸብን እንጅ ልዩ ፍጡራን ሆነን አይደለም!!ይሄ በአመክንዮ የተደገፈ ሀቅ ነውና ነገ የኦሮሞው ቁጥር በበትረ -ሥልጣኑ ቢበረክት ኦሮሞ ልሂቃንም በመንገዱ መንጎዳቸው እንደማይቀር እናምናለን–አምነን እንናገራል!!ላሁኑ ግን በታሪካዊ ያገር መገንባት ጉዞው ያልተጠቀመውና በሂደቱ የመገለል ስሜት የተሰማው ወገን “በመጀመሪያ ብሔር ነኝ–ከዜግነቴ ብሔሬ ይቀድማል” ቢል ምንድን ነው ብርቅና ድንቁ??እንዲህ ያሉትን ሰዎች አሳድደን ምን አተረፍን??ተጸጽተው ኢ/ያ ማሪኝ አሉ??ወይስ ይበልጥ ለአጀንዳቸው ማያያዣ ጭድ አገኙ??ንቃህ ንውም–አጉል ራስህን የርቱዕ ኢትዮጵያዊነት ሰጪና ነሺ አድርገህ አትመጻደቅ!!

7– ወልቃይት ከጎንደር፤አላማጣ ከወሎ ተወሰዱብን እያሉ፣ “የትግራይ ሰው ወያኔ ሲወድቅ ላግኝህ” እየዛቱ፣ትግራዋይ ስምና ቋንቋ ሲያዩና ሲሰሙ እየተንገፈገፉ፣የአማርኛ ተናጋሪ አረጋዊ ልሂቃን …ትግሬ ባንዳነት ልማዱ ነው፤በትግሬ መገዛት ለአማሮች አይሆንልንም፤ኦሮሞና እስላም መጤ ናቸው…ሲሉ እንዳላየን እያለፍን፣በየዲያስፖራው በፖለቲካ ቀርቶ በቤተ – እምነት ሳይቀር ራሳችን እስከ ቀበሌ በደረሰ ክፍፍል ውስጥ ሆነን፣አማሮች ሲፈናቀሉ ከጣራ በላይ በተለየ መልኩ እየጮህን፣በኢትዮጵያዊነት ጥላ ስር የሚንቀሳቀሱ የብሔረሰብ ድርጅቶች መሪዎችን ኢትዮጵያዊነታቸውን እንኳ መቀበል አቅቶን፣በኢ/ዊነቱ አንዳች ህጸጽ ከሌለበት የትግራይ ሕዝብ የፈለቀውን ህወሃት በፖሊሲውና በተግባሩ ብቻ መተቸት ሲቻል የፈለቀበትን ማ/ሰብ በሚያስከፋ መልኩ “ድሮስ ከትግሬ ምን ይጠበቃል??” በሚል ያፈጠጠ ዘረኛ አመለካከት እንደ ውጭ ወራሪ እተመለከትን፣ወዘተ….አጓጉል ራሳችንን የኢትዮጵያዊነት ሚዛን ማድረግ እቡይነት ነው!!ሼም!!

8– አዲሱ አማርኛ ተናጋሪ ትውልድም ሆነ የዲያስፖራው አማርኛ ተናጋሪ በኢኮኖሚውም ሆነ በፖለቲካው እንዳይሳተፍ መጠነ – ሰፊ ጩዋሂ ቅስቀሳ እያካሄዱ መልሶ ፖለቲካውም፣ኢኮኖሚውም፣ወታደራዊና የደህንነት ኃይሉም ወደ አንድ ወገን አጋደለ ብሎ መክሰስ ከንቱ ጩኸት ነው!!አላስ…መሆን–አላስገባ፣አላስወጣ!!አላስ!!

ልደምድም፡- የትናንቷ ኢትዮጵያ በአንድ ገጹዋ ወራሪን ተባብሮ በመመከትና የቋንቋና የብሔር ማንነትን ጥሶ በተሻገረ የሕዝብ ለሕዝብ ያብሮነት ግንኙነት፣በሌላ ገጹዋ ደግሞ አንዱ ገዥ ሌላውን ገዥ ለማስገበር ባደረገው ጦርነት ማንነት አብሮ የተደፈጠጠባትና በተለይ የደቡብና የምዕራብ ያገሪቱ ማ/ሰብ ከሰሜኑ በተለየ መልኩ በገዛ መሬቱ ላይ ጪሰኛ ሆኖ ሲማቅቅ መኖሩን በመገንዘብ እነዚህን ድልና በደሎች የሚያስታርቅ አካሄድ ሳንተልም ለጊዜው በኢትዮጵያ ሰማይ ላይ ገና የበላይነቱን ባልተነጠቀው ጩዋሂና የውሸት አጀጋኝ (ጀግና ፈጣሪ) ሚዲያችን ነገሮችን የማይነቃ መስሎን በአማራዊ እይታ ብቻ እያተነተንን፣ቀድመን ተማርን ብለን ስሜታችንን ምክንያታዊነት እያለበስን ‘ኢትዮጵያ-ኢትዮጵያ’ ማለት ከንቱ ድካም ነው!!ቢያንስ ከአማራው ልሂቅ ውጭ ያሉ የየብሔረሰቡ ልሂቃን ስለምናራምደው አቋም ያላቸውን እይታ እንቃኝ!!ስለትናንት ስንተርክ የዛሬዋ ኢ/ያ እያመለጠችን ነው፤በዚህ አካሄዳችን የነገዋም አትቀበለንም!!በተለይ አረጋዊ የአማራ ልሂቃን ከእኛ ውጭ የሆነ ሀሳብ ያሰበ ሁሉ ኢ/ዊ አይደለም እያላችሁ ትውልድ ባታሸማቅቁ፤አዳዲስ አስተሳሰብ ባትደፍቁ ሸጋ ነው!!

ጠቢብነታቸውን ለጠባብነት ባዋሉት ላይም ገና እናገራለሁ – በቀጣዩ ክፍል፡፡ ማን ታፍኖ ይሞታል!!

**********

Guest Author

more recommended stories