ከድሮ ጀምሮ ‹‹ትግሬ›› ስንላችሁ ነበርና እንቀጥልበታልን ማለት ድሮ ‹‹ጋ*›› ስንላችሁ ስለነበረ አሁንም ‹‹ጋ*›› እንላችኋለን ማለት ነው

(አስፋው ገዳሙ)

ድሮ የሰው ልጅ ‹‹ባርያ›› ተብሎ እንደ እቃ ይሸጥ ይለወጥ ስለነበረ ዛሬም መሸጥ መለወጥ አለበት ብሎ የሚከራከር ሰው ምን ትለዋለሀ? ድሮ ‹‹ወላሞ›› እንላችሁ ነበርና አሁንም ‹‹ወላሞ!›› ስንላችሁ ቅር ሊላችሁ አይገባም ብለው የሚከራከሩ ፍጡራን ባሉበት ሃገር ከቶ እንዴት መግባባት ይቻላል?ድሮ ሽፍቶ እንዳሻው እየዘረፈ፣ በጉልበቱ እየመዘበረ፣ሴቶችን አስገድዶ እየደፈረ ይኖር የነበረው ሁሉ አሁንም እንደድሮ ይኑር ብሎ ሙግት ምን ይባላል?

አዲሱ ቸኮል የሚባል የፌስቡክ ጓደኛየ በከተሞች ፎረም ያወዛገበው “ትግሬ” ሚለው መጣጥፉ እንዲፅፍ ከነሳሱት ነገሮች አንዱ እንደሚከተለው አስቀምጦታል፤‹‹ ‹ድሬዳዋ ከየት ወደየት› በሚል ርዕስ በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲና የድሬዳዋ አስተዳደር ትብብር የተዘጋጀ ጥናታዊ ፅሑፍ ውስጥ በአስተዳደሩ የሚኖሩ ብሔር ብሔረሰቦችን የሚዘረዝርበት ክፍል ላይ ትግሬ የሚል ቃል መኖሩ ሁለት የትግራይ ክልል ተወላጆች ቃሉን ተቃዉመው አስተያየት እንዲሰጡ ያስገደደ ነበር፡፡›› ይልና በመቀጠልም ‹‹የተቃዉሟቸው መነሻ ደግሞ ብሔሩ ትግራይ እንጂ ትግሬ አይባልም የሚል ነበር፡፡ህገ መንግስቱን ሁሉ ዋቢ ያቀረቡ አሉ(ምንም እንኳ በህገ መንግስቱ የተቀመጠው የክልሉ ስም እንጂ የብሔሩ ስም ባይሆንም)፡፡›› በማለት የሁለቱ የትግራይ ተወላጆች የተቃውሞ አስተያየት ውድቅ ለማድረግ ይሞክራል፡፡

አዲሱ በዚሁ አላበቃም ‹‹እነኚህ ሰዎች በአማርኛም፣ በኦሮምኛም ሆነ በሶማሊኛ፣ . . . .ትግራይ የሚባለው ክልሉ እንደሆነና የክልሉ ተወላጆች ግን ትግሬ እንደሚባሉ ሳያውቁ ቀርተው ነው እንደዚህ የሚከራከሩት እንዴ?›› በማለት ራሱን እንዲጠይቅ መገደዱን ጠቅሶ ሲያበቃ ቀጥሎም ‹‹ትግሬ የሚል ቃል ‹ትምክህተኞች ለትግራይ ህዝብ ያወጡለት የስድብ ስም ነው› እያሉ አንዳንዶች በፌስቡክ ላይ የሚያደርጉት ክርክር ነበር ትዝ ያለኝ፡፡ እነኚህ ከክልሉ ከተሞች የተወከሉ አመራሮች/ባለሙያዎችም እንደዚያ ነው የሚያስቡት ማለት ነው?››› በማለት ይጠይቃል፡፡

አዲሱ መጣጥፉን የደመደመው እንደሚከተለው ነበር፡ ‹‹ትግሬ የሚለውን ቃል ስልጣን ወደትግራይ ከመሔዱ፣ ከትግራይም ወደሸዋ ከመሻገሩ በፊት፣ ሁሉም ጠቅላይ ግዛቶች ተመሳሳይ በነበሩበት የአፄ ቴዎድሮስ ዘመነ መንግስት ሁሉ ጥቅም ላይ ይውል እንደነበር በአፄ ቴዎድሮስ ዘመን የተገጠሙ ግጥሞች ማስረጃ ናቸው፡፡››

ይህ ድምዳሜ ‹‹ትግሬ››የሚባለው አጠራር ከድሮ ጀምሮ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ መሆኑን ለማስረገጥ የቀረበ ታሪካዊ ማስረጀ መሆኑን ነው፡፡ መቼም፣ በማለት ይቀጥላል ወንድማችን፣ ‹‹መቼም በዛ ዘመን የአሁን ፖለቲከኞቻችን የሚያወሩት መናናቅ/መሰዳደብ አለ የሚሉ አይመስለኝም፡፡ እናም ቃሉ ስድብ አለመሆኑን መግባባት ይቻላል፡፡›› ይልና የማመዛዘንና የስነ መጎት ድህነቱን ቅልብጭ አድርጎ ያሳየናል፡፡ቀጥሎ የፃፈው እንተፍንቶም በጥቁር አሜሪካኖች ላይ የሚደርሰው ዘረኝነት ጥቁሮቹ ስለተቃወሙት ነው እየቀጠለ ያለው የሚል ብያኔ ያለው ነውና እሱን ትተን በእኛ ሃገር ስላለው ሁኔታ እንመልከት፡፡

ሲጀመር በአፄ ቴዎድሮስ ዘመን ‹‹መናናቅ/መሰዳደብ አለ የሚሉ አይመስለኝም›› ብሎ ስነ መጎት የለም፡፡ ‹‹አይመስለኝም›› በሚሉት መንደርደርያ ድምዳሜ ላይ መድረስ አይቻልም፡፡ ድምዳሜ ላይ ከመድረሱ በፊት በቃሉ አጠቃቀም ቅር የሚሰኙትን መጠየቅ ነበረበት፡፡ በአፄ ቴዎድሮስ ዘመን መናናቅና መሰዳደብ ይቅርና ጉልበቱ እስካለህ ድረስ መግደል መገዳደልም እንደ ጀብድ ሲቆጠር የነበረበት ጨለማ ዘመን ነው፡፡ ንጉሱን የተቃወሙ ሁሉ እጅና እግራቸው ታስረው ወደ ገደል የተወረወሩበት ዘመን ነው፡፡ እጅና እግር መቁረጥ የተለመደ ነበር፡፡ በአጠቃላይ የያኔው ህግ ህገ አራዊት እንደነበር መታወቅ አለበት፡፡ በተለይም አፄው ለመውደቅ እየተቃረቡ ሲሄዱ ወደ አውሬነት መቀየራቸውና ደጋፊዎቻቸው ጭምር ያገሏቸው እንደበር የፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ መፅሐፍ ያትታል፡፡

ሲቀጥል ደሞ ‹‹ትግሬ›› የሚለው ስያሜ ከድሮ ጀምሮ የነበረ መሆኑን መዛግብ ያወሳሉና ስድብ አይደለም ብሎ መደምደም አይቻልም፡፡ አይ የግድ መደምደም አለብን የሚለን ከሆነ ግን በዚሁ ስሌት መሰረት ድሮ የሰው ልጅ ‹‹ባርያ›› ተብሎ ይሸጥ ይለወጥ ስለነበረ ዛሬም መሸጥ መለወጡን ሊቀጥል ይገባል ማለት ነው፡፡ የሲዳማ ብሔረሰብ ተወላጆች ድሮ ‹‹ወላሞ›› ተብለው ይጠሩ እንደነበረ የታሪክ መዛግብት ይጠቅሳሉና ዛሬም ‹‹ወላሞ›› እያልን ልንጠራቸው ይገባል እያለን ነው፡፡ ድሮ የኦሮሞ ተወላጆች ‹‹ጋ*›› ይባሉ እንደነበር በአፄ ቴዎድሮስና በአፄ ሚኒሊክ ዘመን የተፃፉ የታሪክ መፃሕፍት ይመሰክራሉና እነዚህ ወንድሞችም በዚሁ አጠራር ብንጠራቸው በህግ የሚያስቀጣ ወንጀል መሆኑን ቀርቶ ቅር ሊሰኙ አይገባም ማለት ነው፡፡ የሴት ልጅ ግርዛት ድሮ ይዘወተር ስለነበረ ዛሬም መዘውተር አለበት ማለት ነው፡፡ ድሮ በጠለፋ ማግባት ይቻል ነበርና ዛሬም አንዷን ጉብል ጠልፌ ባገባ ማንም ሊቃወመኝ አይገባም ብሎ ድርቅ እንደ ማለት ነው፡፡

ድሮ ሲነገርና ሲደረግ እንደነበረው ግን መጓዝ አንችልም፡፡ ኋላ ቀር አስተሳሰቦችንና ልምዶችን ቀስ በቀስ እያስወገድን ዘመኑ ከሚዋጀው አካሄድ ጋር የማንራመድ ከሆነ መቼም መሻሻል አንችልም፡፡ ድሮ ከቤት እስከ ቤተ እምነት፣ከሐወልቶች እስከ መሸጋገርያ ድልዮች ለመገንባት ድንጋይ የሚጠርበውን ግንበኛ፤ ብራታ ብረት እያቀለጠና እየቀጠቀጠ ማረሻ፣ ማጭድ፣ ሞዶሻ፣ አካፋ፣ ጌጣጌጦች፣ … በአጠቃላይ ሸክላን ጨምሮ ለኑሮ አስፈላጊ የሆኑ መሳርያዎችን የሚሰራው ሁሉ ቀጥቃጭ፣ ቡዳ፤ የምንለብሳቸው ልብሶችን የሚሰራው ሸማኔ፣ ክር በጣሽ፤ አርሶ አደፋርሶ ሃገር የሚመግበውን አፈር ገፊ፣ ነግዶ የሚያተርፈውን መጫኛ ነካሽ ይባል ነበር፡፡ በአጠቃላይ ሰርቶ የሚኖሮው ሁሉ የሚያሸማቅቁ ስሞች ይለጠፉበት ነበር፡፡ እጅና እግሩን አጣጥፎ ሌላ በደከመለት ከቤት ቤት እየዞረ የሚበላ የሚጠጣው ደሞ ከበርቴ፣ ጭዋ፣ ባላባት ነበር የሚባለው፡፡ አሁን ግን ጊዜው ስለተቀየረ በሰው ጫንቃ ተፈናጥጦ መኖር አይቻልም፡፡ በእነ አዲሱ እሳቤ ግን የድሮ ታሪኮች ስለሚያወሱት አሁንም መቀጠል አለበት ነው፡፡

በአጠቃላይ፣ ድሮ በሰው ልጆች ይደርሱ የነበሩ አስቀያሚ፣ አስነዋሪ፣ ኋላ ቀር፣ ኢሰብአዊና ልቅ አነጋገሮችና ልምዶች ዛሬም መቀጠል አለባቸው እያለን ነው፤ አቶ አዲሱ፡፡ ድሮ ለአምልኮተ ጣኦት የሰው ልጅ መስዋእት ይሆን ነበርና ዛሬም ይቀጥል ማለቱን ነው፡፡ በበኩሌ ባንተው ይጀመር ብዬ አልከራከረውም፤ማንኛም ዓይነት ኢሰብአዊ ተግባር በማንኛውም ሰው እንዲደርስ አልፈቅድምና፡፡

ለማንኛውም ግን፣አዲሱንና የአዲሱ ዓይነቱን ያልተገራ አቋም የሚያራምዱ ወገኖች ለአሁኑ እንርሳቸው፡፡ ይህን ፅሑፍ ለማዘጋጀት የተነሳሁትም እንደ እነ አዲሱ ከመሳሰሉ ወገኖች ጋር ለማስረዳት አይደለም፡፡ ምክንያቱም የእነ አዲሱ ዓይነቱ ‹‹እንኳንስ ሰድቤህ በአደባባይ ብደፋህስ ምን ታመጣለህ?›› የመሳሰሉ ግትር አቋሞች በስነ አመክንዮ ማስረዳት ስለማይቻል ነው፡፡ ውይይት የሚያስፈልገው በቀንዱ ከሚተማመነው በሬ ወይም ጎሽ፣ በጥርሱ ከሚመካው ጅብ ወይም አውሬ ሳይሆን ንፁኅ ህሊና፣ የሚያስብና የሚያመዛዝን አእምሮ ከታደሉ ሰዎች ብቻ ነው፡፡ መግባባት የሚቻለው የተግባቦት ትርጉምና ጥቅም ከሚያውቁ ሰዎች ብቻ ነው፡፡

ለመሆኑ፣ እኛ የትግራይ ተወላጆች የጋራ መጠርያችን ተጋሩ ሲሆን፣ እያንዳንዳችን ስንጠራ ደሞ ትግራዋይ(ለወንድ) ትግራወይቲ(ለሴት) እንባላለን እንጂ ‹‹ትግሬ›› መባል የለብንም ስንል ምን ማለታችን ነው? ‹‹ትግሬ›› ማለት ምን ማለት ነው? በ‹‹ትግሬ››ና በትግራዋይ እንዲሁም ተጋሩ ያለው ልዩነት ምንድነው? ‹‹ትግሬ›› የሚለው ቃል እንስድብ የሚቆጠረው በምን ሁኔታ ሲተረጎም ነው? የሚሉና ተመሳሳይ ጥያቄዎች ለሚሰነዝሩ ቅን ኢትዮጵያውያን የቻልኩትን ያህል እንደሚከተለው ለማብራራት እሞክራለሁ፡፡

ማንኛውም የዓለም ማህበረሰብ መጠራት ያለበት በራሱ ስያሜ እንጂ ሌሎች በሓይል በሚለጥፉበት ስም መሆን የለበትም፡፡እኛ የትግራይ ተወላጆች የጋራ መጠርያችን ተጋሩ ሲሆን፣ እያንዳንዳችን ስንጠራ ደሞ ትግራዋይ(ለወንድ) ትግራወይቲ(ለሴት) እንባላለን እንጂ ‹‹ትግሬ›› መባል የለብንም ካልን ማንም ሊያስገድደን አይገባም፡፡በቃ፣ አልፈለግነውማ፡፡የግድ እኛ ያልናችሁ ተቀበሉ ብሎ ድርቅ ማለት በእኛ ላይ ያላችሁ አመለካከት በእኩልነት፣በፍቅር፣ እርሰ በርስ በመፈቃቀድና በመግባባት ላይ ያልተመሰረት መሆኑን የሚያመለክት ነው፡፡እናም ተስማምተን፣ እንደ አንድ ህዝብ በፍቅርና በመተሳሰብ ተግባብተን እንድንኖር ከተፈለገ እኛ በመረጥነው እንጂ እናንተ በመረጣቹብን፣ የድሮ ስርዓቶች ያለ ፍቃዳችን ይጠሩን እንደነበረው ስትጠሩን መሆን የለበትም፡፡

‹‹ትግሬ›› እያልን ብንጠራችሁ ችግሩ ምንድን ነው? የሚል ካለ፣ መልሱ እኛ ‹‹ትግሬ›› አይደለንም፤ መልሳችን ነው፡፡ የአማርኛ ተናጋሪዎች በተለምዶ‹‹ትግሬ›› እያሉ የሚጠሩን፡

1. በትግራይ ክልል የሚኖሩ ተወላጆች ( ተጋሩ)ና በኤርትራና ሱዳን ድንበሮች የሚኖሩ ትግረዎች ያለው ልዩነት ስለሚምታታባቸው ሊሆን ይችላል፡፡የትግረ ብሔረሰብ ተወላጆች በአብዛኛው ሞስሊሞች ሲሆኑ አኗኗራቸው ደሞ ከትግራይ ክልል ተወላጆች በጣም የተለየ ነው፡፡እነሱ አርብቶ አደርና ከፊል አርብቶ አደሮች ናቸው፡፡ቋሚ የሆነ መኖርያ የላቸውም፤ ከቦታ ቦታ እየተዟዟሩ ነው የሚኖሩት፡፡የሚኖሩበት አከባቢም በሰሜናዊ፣ምዕራባዊና ቆላማው የኤርትራ መታሕት ነው፡፡በሱደን የሚኖሩት ደሞ ሐይሻ(አይሻ) ተብለው ይጠራሉ፡፡ቋንቋቸው መሰረቱ ግዕዝ ስለሆነ ከትግርኛ ጋር በጣም የሚቀራረብ ቢሆንም ትግርኛ አይደለም፡፡በእርግጥ ትግርኛና ትግረ በአፍሮ ኤሽያቲክ የቤተሰብ ቋንቋ ይመደባሉ፡፡ሆኖም ግን አንድ ዓይነት አይደሉም፡፡የትግረ ተናጋሪዎች ቁጥር ከስምንት መቶ ሺ አይበልጥም፤ የትግርኛ ተናጋሪዎች ብዛት ግን (ኤርትራውያን ትግርኛ ተናጋሪዎችን ሳይጨምር) ከአምስት ሚልዮን በላይ ነው፡፡

አማርኛ ተናጋሪዎች በርሀ፣ ሽረ፣ ትግረ ማለት አይፈልጉም፤ በርሄ፣ሽሬ፣ትግሬ ማለት ይቀናብናል ይላሉ፡፡ታድያ በየነ፣ታደለ፣ከበደ፣አበበ፣አየለ፣ተሻለ፣ተጫነ…ወዘተ ማለቱን ትታችሁ በየኔ፣ታደሌ፣ከበዴ፣አበቤ፣አየሌ፣ተሻሌ፣ተጫኔ…ወዘተ ለምን አትሉም ብትላቸው ከስድብ በስተቀር መልስ የላቸውም፡፡እናም የትግረ ማሕበረሰብ ተወላጆችን ትግሬ እያሉ የሚጠሯቸው ሲሆን ለእኛ ለተጋሩም በዚሁ አጠራር ይጠሩን ነበር፡፡ይህ ግን ከላይ እንደገለፅኩት ትልቅ ስሕተት ነው፡፡እኛ ትግረ ከተባልን( እንደ አማርኛ ተናጋሪዎች አጠራር ትግሬ)ትግረዎቹንስ ምን እንበላቸው? በተለያዩ አከባቢዎች ይምንኖር፣ የተለያየ ባህል፣ቋንቋና እምነት ያለን ህዝቦች በአንድ ዓይነት ስያሜ መጥራት ተገቢ አይደለም፡፡በታሪክ፣ በመልከዓ ምድራዊ አኗኗራችን፣ በእምነታችን፣ በቋንቋችን፣ በባህላችን ወዘተ የተለያየን ነን፤ እኛ ተጋሩና እነሱ ትግረዎች፡፡ከእውቀት ማነስ የተነሳ ‹‹ትግሬ›› እያላችሁ የምትጠሩን ወገኖች ይህን ልዩነት ከወቃችሁ በኋላ በትታረሙ የተሻለ ይመስለኛል፡፡

2. ‹‹ትግሬ›› አለመሆናችን እያወቁ በዚሁ ስያሚ የሚጠሩን ወገኖች ለእኛ ለተጋሩ ያላቸው ንቀት ለማሳየት ነው፡፡የትግራይ ክልል የኢትዮጵያ መሰረት መሆኗን ይታወቃል፤ ይሐና አክሱም የሚገኙት በትግራይ ክልል ውስጥ መሆኑን የማያውቅ ካለ ከወዲሁ ይወቅ፡፡የስልጣን ሃረጋቸው ከሰለሞናዊው ስርወ ንግስነት የሚመዘዝው ነገስታት ሁሉም መንበረ ንግስናቸው አክሱም እንደሆነ ነበር የሚሰብኩት፡፡ይህ ካልሆነ ተቀባይነት አይኖራቸውም ነበርና፡፡እናም እኛ ተጋሩን ከዚሁ ታሪካዊና ቀደምት የኢትዮጵያ ባላባቶች ጋር አንድ መሆናችን ቆሽታቸው ስለሚያቃጥላቸው፤የበታችነት ሰሊሚሰማቸው፣በራሳቸው መተማመን ስለሚያቅታቸው ያለ ስማችን ስም ለመስጠት ተገድዷል፡፡‹‹ትግሬ›› በማለት ሲጠሩን ትንሽ ለመረጋጋት፣ በራሳቸው ለመተማመን ይሞክራሉ፡፡በራሱ (በማንነቱ) የማይተማመን ሰው ክርሱ በልጦ የሚታየው ሰው ሲያጋጥመው ከሰውነት በታች የወረደ ያህል ስለሚሰማው ይሸማቀቃል፤የሚገባበት ያጣል ይቀበጠበጣል፣ ከቻለም ማጣጣል ይጀምራል፡፡

ይሁን እንጂ፣ተወደደም ተጠላም እኛ ተጋሩ መሰረታችን አክሱም ሲሆን ክልላችን ደሞ ትግራይ ነች፡፡መጠርያችንም ትግራዋይ፣ትግራወይቲ፣ ተጋሩ ነው፡፡

3. ትምክህተኞቹ የለጠጡትን ያህል እንለጥጠው ከተባለ ደሞ ‹‹ትግሬ›› ስድብ ነው፡፡በቁጥር 2 እንደነካካሁት ለእኛ ለተጋሩ ለማሸማቀቅ፤በታሪካችን፣ በባህላችን፣በቋንቋችንና በአኗኗራችን አፍረን ማንነታችን እንድንቀይር የተዘየደ ሴራ ነው፡፡ፅንፈኛ ዘረኞቹ ‹‹ትግሬ›› የሚሉን በቅኔ መሳደብ እንደሚችሉ ለማሳየት ነው፤የእውቀት ደረጃቸው እኛን ለማሳወቅ፡፡‹‹ትግሬ›› ሲሉ በአሽሙር መሳደባቸውን ነው፤ ተግሬ (ከእግሬ ስር) ናችሁ፤ እኛ ለዘልዓለም እንረግጣችኋለን፣እንገዛችኋለን እናንተ ደሞ ከመገዛት ውጪ ሌላ አማራጭ የላችሁም፤ ከእግራችን ስር የምትኖሩ ውዳቂዎች ናችሁና እያሉን ነው፡፡ያለፉት አግላይ ጠቅላይ ስርዓቶች አማርኛ የማይናገር ሁሉ እንደ አደጋ ነበር የሚመለከቱት፤ በተለይ እማ የስልጣናቸው ተቀናቃኝ ለነበረው ትግራዋይ፡፡የስልጣናቸው አደጋ እንደ ሆነ ነበር የሚያስቡት፡፡እናም ‹‹በአንዲት ኢትዮጵያ፣ አንድ ቋንቋ፣አንዲት ሃይማኖት›› ብለው ያወጁ፤ የለየላቸው ፅንፈኛ አክራሪዎች ነበሩ፡፡እነዝያ ኋላ ቀር ስርዓቶች ላይመለሱ ተደምስሷል፣ ዳግም ላይነሱ ታሪክ ቀብሯቸዋል፡፡ስለሆነም ከዘመኑ ጋር ልንራመድ ይገባል፡፡

ለማጠቃለል ያህል፣ ከታሪክ ተምረን መታረም የማንችል ከሆነ እኛ ሰዎች ሳንሆን እንስሶች ነን፡፡እንስሳ ብቻ ነው ድሮ ሲጫን ስለነበረ ዘንድሮም ሲጭኑት ዝም ብሎ የሚጫነው፡፡እንስሳ ብቻ ነው ድሮ ጫካ ውስጥ ይኖር ስለነበረ አሁንም ጫካ ውስጥ የሚኖረው፡፡እንስሳ ብቻ ነው ድሮ ዋሻ ውስጥ ይኖር እንደነበረው ዛሬም ዋሻ ውስጥ የሚኖሮው፡፡እንስሳ ብቻ ነው ድሮ በበላበት ሲፀዳዳ እንደነበረው ዛሬም በበላበት የሚፀዳዳው፡፡ከሰዎች ጋር ስንኖር እንደሰው እናስብ፣እንደሰው እናመዛዝን፣እኛን የሚያስከፋው ነገር ሌሎችንም ሊያስከፋ እንደሚችል ማወቅ አለብን፡፡ካልሆነ ግን መግባባት አይቻልም፡፡መግባባት ካልተቻለ ደሞ የጋራ ችግሮቻችንን በጋራ አስወግደን በሰላም፣በፍቅር፣በመተሳሰብ አብሮ መኖር አይቻልም፡፡

*********
* ሌሎች የአስፋው ገዳሙን ጽሑፎች
ጦፎኛ ብሎግ ላይ ያገኛሉ፡፡

Guest Author