ስለማሕበረ ቅዱሳን የተሳሳተ ግንዛቤ ነበረኝ

‹‹ማኅበረ-ቅዱሳን›› በሚል አጭር ስያሜው የሚታወቀው (በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን) ድርጅት ሰሞኑን የፖለቲካዊ እና ሃይማኖታዊ የመወያያ አጀንዳ ሆኗል፡፡ ርዕሰ-ጉዳዩን አስመልክቶ ‹‹ሴቭ አድና›› በሚል የብዕር ስም የሚጠቀመው የፌስቡክ ፀሐፊ የላከልን አስተያየት እዚህ ያቀረብን ሲሆን፣ ሌሎች ዜና እና አስተያየቶችንም ለማቅረብ እንሞክራለን፡፡

(ሴቭ አድና)

ስለማሕበረ ቅዱሳን (ማ.ቅ) የነበረኝ ግንዛቤ ስህተት እንደነበር አሁን በማያወላዳ መልኩ ተገንዝቤያለሁ፡፡

የዛሬ ስድስት ዐመት ገደማ ከአንድ የዲላ ልጅ ከሆነ ጓደኛየ ጋር ዲያቆን በጋሻው ደሳለኝን አዲስ አበባ አግኝነተነው ነበር፡፡ ሁለቱም ከልጅነታቸው ጀምረው የሚተዋወቁ የቅርብ ጓደኛሞች ናቸው፡፡ በጋሻው ደስ የሚልና ተግባቢ ሰው ነው፡፡ ጊዜው በጋሻውና ሌሎች በርካታ መዘምራንና ሰባኪዎች ላይ የተዘመተበት ጊዜ ነበር፡፡ የዘመቻው ዋና አንቀሳቃሽም ማሕበረ ቅዱሳን ነበር፡፡ በእርግጥ በጋሻው ከጳጳሱም ጋር በጊዜው ጥሩ ግንኙነት አልነበረውም፡፡ ወቅቱ ወሬው ሁሉ ስለነበጋሻው የነበረበት ጊዜ ነው፡፡

በጋሻው በጨዋታ መኸል ይኸንን በተመለከተ አንስተንለት በሐዘንና ቁጣ ስሜት ያለንን አልረሳውም፡፡

“ጳጳሱ እንኳን ተዋቸው፡፤ በዙርያቸው ያሉ አማካሪዎችና የማሕበረ ቅዱሳን ሰዎች የሚሏቸውን ሰምተውና በነሱ ግፊት ነው፡፡ ቅዱስ አባታችን አንድ ቀን እውነቱን ማወቃቸው አይቀርም፤ እግራቸው ስር ወድቀንም ይቅርታ እንጠይቃለን፡፡ የገዜ ጉዳይ እንጂ ከእርሳቸው ጋር በአባትና ልጅ ፍቅር መተቃቀፋችን አይቀርም፡፡ ከጀርባ ሆኖ በኔም በተለያዩ መዘምራን፣ ዲያቆናትና ሰባኪዎች ላይ ጥላሸት የሚቀባንና ያልሆንነውን “ሆኑ’ ያልሰራነውን ‘ሰሩ” የሚለን፣ በመናፍቅነት ሁሉ የሚከሰን ይህ ማሕበረ ቅዱሳን የተባለ ስሙ ቅዱስ ምግባሩ እኩይ የሆነ ድርጅት ነው፡፡ እነሱ ከማሕበራቸው አባልና እነሱ ከሚፈልጉት ውጪ በሐይማኖታዊ እንቅስቃሴ ላይ ጎልቶ እንዲታይ፣ የተሸለ እንዲሰራ፣ ወጣቶችን እንዲያነቃቃ፣ ዘመናዊ መፅሐፍ ቅዱሳዊ ሀይማታዊ አስተምህሮት እንዲያገኝ አይፈልጉም፡፡

እውነቱን ንገረን ካላችሁ በዋናነት ከደቡብ (ብዙዎቻችን ደግሞ ከዲላ ነን) በመጣነው ላይ ግልፅ ጦርነት ነው የከፈቱብን፡፡ ይህ ምንም ሀይማኖታዊ ምክንያት የለውም፡፡ እነሱ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤ/ክርስትያን ዘማሪውም፣ ቀዳሹም፣ ሰባኪውም፣ የአድባር አለቃውም ሁሉም ነገር ከጎጃምና ከሽዋ ካልሆነ የሚል ግልፅ አቋም አላቸው፡፡ ከስራችንንና ከምንሰጠው አገልግሎት ይልቅ ለነሱ ከየት መጡ የሚለውን ጉዳይ የበለጠ ያሳስባቸዋል፡፡ እኔ ይህ ድርጅት ምንም ሃይማኖታዊ ዐላማ የሌለውና ጊዜ የሚያወጣው ስውር ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ታሪክን ማጣመም ሌላ ሰውር ዐለማ ያለው እጅግ አስፈሪ ድርጅት ሆኖብኛል፡፡ ቤተክርስትያኒቱም እንዳያሽመድማት በግሌ እሰጋለሁ፡፡ መቸም ይህን የማጋለጥና ቤ/ክርስቲያኒቱን ከተኩላዎች የመጠበቅ የሁላችን መንፈሳዊ ግዴታ ይመስለኛል፡፡”

በጋሻው ቃል በቃል ያለውን ማስታወስ ባልችልም መልእክቱ ግን ከላይ ያለውን ነው፡፡ እኔ ሀይማኖት ላይ ባለኝ የግል አቋም እንዲህ ዐይነት ጉዳዮች ብዙ ቦታ የምሰጣቸው ጉዳዮች ሆኖው አያውቁም፡፡ የማሕበረ ቅዱሳን ነገር ግን አሁን መለስ ብየ ሳይ፣ ነገሮች ሳጠና፣ አስተምህሮቶቹን ስመለከት፣ ፅሑፎቻቸውን ሳይ፣ በታሪክና በሐይማኖት ላይ የሚያደርጉትን ነገር ሳይ ይህ ድርጅት ብዙ ሩቅ ሳይሄድ (ለነገሩ በጣም ብዙ ርቀት ተጉዟል) አሁን ባለበት ደረጃ ከስሩ ተመንግሎ ካልተጣለ ለሀገራችን ትልቅ አደጋ ሊሆን እንደሚችል ድምዳሜ ላይ ደርሻለሁ፡፡

ዩኒቨርሲቲ በነበርኩበት ሰዐት የተወሰኑ የግቢ ጉባኤዎችን እከታተል ነበር፡፡ በእውነት ነው የምላችሁ መፅሐፍ ቅዱስ ከተሰበኩበት ቀን ይልቅ ሰው ሰው የማይሸቱና የማይመስሉ የቅዱሳት፣ የነቢያት፣ የቀድሞ ጳጳሳት ወ.ዘ.ተ እጅግ የተጋነነ ታሪክ ሲሰበክልኝ እኔም ሰልችቶኝ ተውኩት፡፡ በዚያ እንደወጣሁም ቀረሁ፡፡

መፅሐፍ ቅዱስ ላይ የሐዋርያት ታሪክ ስናይ ሁሉም ሰው ሰው የሚሸት ታሪክ ነው ያላቸውን:፡ እንኳን ሓዋርያቱ ክርስቶስ ራሱ እንኳ መሬት ላይ በነበረበት ሰዐት ከሐጥያት በስተቀር እንደሰው ነበር- እንደሰው የሚራብ፣ እንደሰው የሚጠማ፣ እንደሰው የሚታመም ፍፁም ሰው፡፡ አሁን አሁን ማሕበረ-ቅዱሳንና ተባባሪዎቻቸው እየፈጠሯቸው ያሉ ቅዱሳት ግን ብዙዎቹ ከአንድ ቦታ የመጡ ሲሆን ታሪካቸውም “ቅድስት እንትና ፈጣሪና ሰይጣን ካላስታረቅኩ ብላ” “ቅዱስ አባታችን እንትና ያለምግብ ለ7 ዐመታት ቆየ”፣ “እንትና የተባሉ አባት በራእይ እንትን አይተው ክርስቶስ በየሳልስቱ የሚጎበኘው እዚህ ቦታ ይሀንን ገዳም መሰረቱ”ና የማይመስሉና የማይታመኑ እናም የውሸት ቅድስና ለመፍጠርና ገንዘብ ለመሰብሰብ “እዚህ ቦታ ከሰማይ መስቀል ወረደ፣ እዚህ ቦታ ማርያም በራእይ ታየች፣ እዚህ ቦታ የደረሱ ከመሐንነት ተፈወሱ” ዐይነት መያዣ መጨበጫ የሌላቸውና ያልነበረን ቅዱስ ቦታ የመፍጠርና የሐይማኖቱ የስበት ማእከል ከአንድ ቦታ አንስቶ ወደ ሌላ ቦታ የመውሰድ እኩይ የታሪክና የሐይማት ሙስና ማድረግ የማሕበሩ ተቀዳሚ ዐላማ እደሆነ አሁን ማሕበሩን በቅርበት የሚያውቁ ሁሉ እየተናገሩት ያለ ነገር ነው፡፡Photo - Ethiopia Orthodox Axum Tsion Church

ማሕበሩም ገዳማት ብሎም መንበረ ፓትሪያርኩ ሁሉ በራሱ ሰዎች በማጠር የቤተክርስትያቱ አስተዳደራዊ መዋቅር ሁሉ ወደ እጁ ለማስገባት ከፍተኛ ጥረት አድርጓል፤ ብዙ ነገርም በቁጥጥሩ ስር አድርጓል፡፡ የማሕበሩ እጅ ከመርዘሙ ጳጳሱ ምንም አስተዳደራዊ ስራ እንዳይሰራ የሚያዝና ቤተክርስትያኒቱ ማሕበሩ እራሱ በመረጠው በስራ አስኪያጅ እንድትመራ የሚያደርግ ሕግ በማርቀቅ ሂደት ረጅም ተጉዞ ዛሬ ጳጳሱ የስም ጵጵስና ብቻ እንዲኖራቸው ለማድረግ ዝግጅቱ ሁሉ አልቋል፡፡

ለታሪክ ዝርፍያውና ሙስናው ቀላል መገለጫዎች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤ/ክርስትያን መሰረት የሆኑትንና ሀይማቱን ወደ ሀገራችን ያመጡን 9 ቅዱሳን አባቶች (ብዙዎቹ ሶርያውያን)፣ የመጀመርያው የኢትዮጵያ ጳጳስ አባ ሰላማ ከሳቴ ብርሀን ፤ እነዚህ የሐይማቱ መሰረቶች፣ የመሰረቷቸው ገዳማትም ከታሪክና ከሀይማኖት እንድምታ አንፃር የላቀ ቦታ ሊይዙ ሲገባ፤ በተለይም አባ ሰላማ ከሳቴ ብርሀን አሁን ያለውን የግዕዝ ፊደላት በጊዜው ከነበረበት የመጀመርያ ፊደል ተጨማሪ ከሁለተኛው እስከ ሰባተኛው ያሉትን (ለምሳሌ ፡ ሉ፣ ሊ፣ ላ፣ ሌ፣ ል፣ ሎ) እንደፈጠሯቸው ሁሉ በርካታ የተሪክ ማስረጃዎች እንዳሉ እየታወቀ፣ በርካታ ገዳማትም መመስረታቸው እየታወቀ ዛሬ ግን ማሕበረ ቅዱሳን የአባ ሰላማ ስም ለማንሳት እንኳን እንደሚፀየፍ ለማወቅ መቐለ ላይ ያለውን በስማቸው የተመሰረተ የሐይማኖት ት/ቤት ለማፍረስ ብዙ ጥረት ማድረጉን ማወቅ ብቻ በቂ ነው፡፤ ይህ ደግሞ ተረት ተረት ሳይሆን በተጨባጭ ከት/ቤቱ በተገኘ መረጃ መሰረት ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ አክሱም ላይ በቤተክርስትያኒቱ በ200 ሚልየን ብር ሊሰራ በጳጳሱ መሰረት የተጣለለት ሙዝየም እንዳይሰራም ማ.ቅ ጠንካራ ግፊት ማድረጉ ይሰማል: : ይህ ቀጣይ የሀይማኖቱን መሰረት የመናድ ዘመቻው አካል መሆኑ ነው፡፡

ምንኩስና ማለት እራስን ከግላዊ ሀይወት ርቆ ሀይወትን በአምልኮ እግዚአብሄር ብቻ ማሳለፍ፣ ጥሮ ግሮ መብላት እንደሆነ በግብፆቹ የመጀመርያዎቹ መነኮሳት አቡነ እጦስና አቡነ መቃስ እንዳስተማሩት ሀገራችንም ይሀንን በእነ አቡነ አረጋዊ ተጀመረ፡፡ ይህ ታጥፎ አቡነ ተ/ሀይማት በይኩኖ አምላክ ጊዜ መነኮሳትም የመሬት ከበርቴ እንዲሆኑ ሲሶ ለአራሽ፣ ሲሶ ለቀዳሽ፣ ሲሶ ለነጋሽ የሚል ሕግ ያስፀደቁትን የንጉሱ አሽቃባጭ የነበሩትን አቡን የሌላ ተመሳሳይ ስም ያላቸው ቅዱስ አባትን ታሪክ የሚያሸክሙ፤ በዘርአ ያቆብ ጊዜም ይሀንን የቤተ-ክርስትያንና የመንግስት ተገቢ ያልሆነ ግንኙነትን የተቃወሙትን የደቂቀ- እስጢፋኖስ ፍፁማውያን መነኮሳት መታረድን እንኳ የማይቃወም ማሕበር፤ እንደውም ይሀንን ነፍሰ-ገዳይ ንጉስን የሌላ ዘርአ-ያቆብ የተባለ የአክሱም ፈላስፋ ታሪክ ሊያሸክሙትና “ፈላስፋው ንጉስ” እስከማለት የሚደርስ የታሪክ ቀማኛ ማሕበር ነው፡፡ እውነትን ታሪክን የሚደፈጥጥ ማሕበር፡፡

በተጨማሪ ማሕበሩ ያለውን የኢኮኖሚ ዐቅም ያስተዋለ ሁሉ ማ.ቅ እውነትም እጅግ የሚያስፈራ ሐይል እንደሆነ መገንዘቡ አይቀርም፡፡ በተለይም ከቅርብ ዐመታት ወዲህ ባለሀብቶችንና ባለስልጣናትን በተለያዩ ዘዴዎችን ማጥመድና ወደ ራሱ መውሰድ በሰፊው የተያያዘው አጀንዳ መሆኑ ለሚያውቅ ሰው ማ.ቅ ከሀይማኖት ድርጅትነት በላይ እጅግ የረቀቀ ስውር ዐላማ እንዳለው መገንዘብ አያዳግተውም፡፡

ማሕበረ ቅዱሳን መጀመርያ በሰንበት ማደራጃ ትምህርት-ቤት ስር በቤተክርስትያን ሕጋዊ እውቅና በማግኘት ሂደት ላይ እያለ የቤተ-ክርስያኑ አባቶች ይሀንን ለመወሰን በተሰበሰቡበት ወቅት በጊዜው የትግራይ ሀገረ-ስብከት አቡን የነበሩና በቤተክርስቲያኒቱ ቀድምት ሊቅ የነበሩ አቡነ መረሀ ክርስቶስ ያሉትን ማስታወስም አስፈላጊ ይመስለኛል: “ይሀንን ማሕበር እንዲመሰረትና እውቅና እንዲሰጠው ማድረግ በቤተክርስትያኒቱ ውስጥ ነገ ለመንቀሉ አዳጋች የሚሆን እሾክ መትከል ነው፤ ተዉ ይቅርብን- ቤተክርስትያችንን አደጋ ውስጥ እንጥላታለን” ነው ያሉት፡፡

ዞሮ ዞሮ ማሕበረ ቅዱሳን ለኔ ሀይማታዊ ድርጅት አልመስልህ ብሎኛል፡፡ እንደውም የጊዜ ጉዳይ እንጂ ወደ ፖለቲካ ፓርቲነት እንደሚያድግም አልጠራጠርም፡፡ ያ ደግሞ በሀገሬ ውስጥ ሌላ መካረርንና የሐይማኖት ግጭት ሊያስከትል የሚችል አደጋ ነው፡፡ ማ.ቅ እውነትም ትልቅ አደጋ ነው፡፡

ኢትዮጵያችን ሰላሟንና አንድነቷን ጠብቃ ለዘላለም ትኑርልን! አሜን!

…….አሁን በፃፍኩት ጉዳይ ላይ ለመወያየት፣ ስህተትም ካለብኝ ለመታረም ዝግጁ ነኝ፡፡…….

*********

Guest Author

more recommended stories