ያለ ብሔራዊ መዝሙርም፣ ያለ ሰንደቅ ዓላማም ኖረን አናውቅም

(ሠይፈ ደርቤ)

ኢትዮጵያ ብሔራዊ መዝሙር ለመጀመሪያ ጊዜ ያስዘመረችው በንጉሱ ዘመን ነው። በንጉስ አፄ ኃይለስላሴ ዘመን ሦስት መዝሙሮች ነበሩ። «ኢትዮጵያ ሆይ (ብሄራዊ መዝሙር)፣ ደሙን ያፈሰሰ (ጠዋት ሰንደቅ ዓላማ ሲሰቀል በተማሪዎች የሚዘመር)፣ ተጣማጅ አርበኛ (ምሽት ባንዲራ ሲወርድ በተማሪዎች የሚዘመር) »

በንጉሱ ጊዜ የነበረው ብሔራዊ መዝሙር አዝማች ይህን ይመስላል።

«ኢትዮጵያ ሆይ ደስ ይበልሽ

በአምላክሽ ኃይል በንጉስሽ…

…ድል አድራጊው ንጉሳችን

ይኖራሉ ለክብራችን»

መዝሙሩ እ.አ.አ ከ1930 እስከ 1974 ድረስ ባሉት 44 ዓመታት ተዘምሯል። ግጥሙ የወል የሚባል ባይሆንም በጋራ የተሰራ ነው፣ ዜማውም አርመናዊ ዜግነት ባለው ኢትዮጵያዊ ነዋሪ ኬቮክ ናልባንዲያን እ.አ.አ በ1926 የተቀመረ ነው ሲባል ሰምቻለሁ።

በንጉሱ ዘመን የነበረውን መዝሙር ደርግ ስልጣን ሲይዝ ቀየረው ፤ የኢትዮጵያን ጭቁን ህዝቦች የማይወክል፣ የንጉሱንና የሰሎሞናዊውን ስርወ መንግሥት የበላይነት የሚሰብክ ነው በሚል። ከዚያም እሱም እንዲሁ የወቅቱ ወካይ ነው ያለውን ብሄራዊ መዝሙር አወጀ።

«ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ ቅደሚ

በህብረሰባዊነት አብቢ ለምልሚ…»

ይህ መዝሙርም እ.አ.አ ከ1975 እስከ 1992 ድረስ ተዘምሯል። አሰፋ ገብረማርያም ተሰማ የግጥሙ ደራሲ፣ ዳንኤል ዮናስ ሃጎስ የዜማው አቀናባሪ ናቸው።

ኢህአዴግ አዲስ አበባን ተቆጣጥሮ ሀገሪቱን በሽግግር መንግሥት መምራት ከጀመረ ባሉት የአንድ ዓመት ጊዜያት ኢትዮጵያ መዝሙር አልነበራትምን? ካልን አዲስ መዝሙር አልነበራትም። በዚህም ምክንያት የቀደመው መዝሙር ተግባራዊ ሆኗል። ይህ ጊዜ ከግንቦት 20/1983 እስከ ሐምሌ 2/ 1984 ዓ/ም ድረስ ያለው ነው።

«የዜግነት ክብር በኢትዮጵያችን ፀንቶ

ታየ ህዝባዊነት ዳር እስከዳር በርቶ…»

መዝሙሩ ሐምሌ 2/1984 ይፋ ሆነ፤ የግጥሙ ደራሲ ደረጀ መላኩ፣ የዜማው አቀናባሪ ሰለሞን ሉሉ ናቸው። ኢትዮጵያ ለ1 ዓመት ያለአዲስ መዝሙር ብትኖርም፣ ያለ ሰንደቅ ዓላማ ግን አልኖረችም። ሰንደቅ ዓላማዋ እንደተውለበለበ፣ ኢትዮጵያዊ ነታችንን እንደገለፀ ይኸው እስካሁን አለን፤ ሰኞ በጋራ ሰንደቃችንን ከፍ እናደርጋለን፣ ሀገርም ውስጥ ውጭም ያለን በልባችንም በተግባርም ከሰንደቅ ዓላማችን ጋር አገራችንን እናስብ። ክብር ለሰንደቅ ዓላማችንና ለክብሩ ለቆሙ ሁሉ ይሁን!!ግን አንድ ጥያቄ ልጠይቅ፣ አንወሻሽና እርስዎ የትኛውን መዝሙር ዘምረዋል?

ይህን እያሰብን በሦስቱ መዝሙሮች ላይ አጠር ያለ ሂሳዊ ቅኝት እናድርግ። ሂሱ ከገጣሚዎቹ አተያይ ጋር አይዛመድም፣ ብቻ እንደ አንባቢ ወይም መዝሙር ሰሚ ለማለት ነው።

የዚህን ጽሑፍ መነሻ አሁን እየተዘመረ ያለውን «የዜግነት ክብር» አድርገን መዝሙሩ ከርዕዮተ ዓለም አንፃር ምን መልዕክት ያስተላልፋል በሚል እንቃኝ፤ ኋለኞቹንም ለማንፀሪያነት እንጠቀም።

ምሁራን የርዕዮተ ዓለም ማደሪያው ቴክስት(text) ነው ይላሉ፤ ቴክስት ስንል እንደ ጉዳይ ማደሪያ ሰው ሊሆንም ይችላል። ጉዳይ ደግሞ በዚህ ጽሑፍ ቅኝት አንፃር ርዕዮተ ዓለም የተቀነቀነበት መዝሙር ነው ማለት ነው።

“Ideology resides in texts, especially in the meaning of texts. Texts are open to all kinds of interpretations associated with other text” – Silan Li V1-347.

“Fiction are not fixed and immutable entities, for they are always open to ideological manipulation” – de Man 1990:183.

ርዕዮተ ዓለም ለተለያዩ ትርጓሜዎች በስፋት የተጋለጠ ነው፡፡ ከደራሲው ፍላጎት ውጪ አንባቢው ወይም ተደራሲው ባሻው መልክ ቢረዳው ስህተት የለበትም፡፡

በሥነ ጽሑፋዊ ሥራዎች ውስጥ የሚፈጠር ርዕዮተ ዓለም ከአንድ ማህበረሰብ (ማህበረ መሰረት) ውስጥ የሚመነጭና የሚገኝ ነው። ርዕዮተ ዓለም የአንድን ማህበረሰብ ወይም ህዝብ ፍላጎት አጠቃልሎ የመያዝና የመጠበቅ ባህሪ አለው። የዚሁ ቃል ፈጣሪ ጀርመናዊው «ዴስቱስ ዴ ትረስ» ይህን ጨምሮ አንድ ታሪክ በራሱ የርዕዮተ ዓለም መገለጫ መሆኑን ይነግረናል። Ethiopia flag

ርዕዮተ ዓለም እንደ ሀሰተኛ ማነቃቂያ ይወሰድ የነበረና በስልጣን ላይ ያለውን ወገን አይነኬነት ለማቆየት አስተዋጽኦ እንደነበረው ደግሞ ማርክሳዊ ንድፈ ሃሳብ ያመለክተናል። ሆኖም በርካታ ምሁራን ይህን አስተሳሰብና ትርጓሜ ስህተት መሆኑን ነቅፈው ተችተውታል። ለምሳሌ እንደ ፖል ዲማን፣ ፒተር ስሎተርጂክ፣ ዴኒስ ተርነር፣ ራይሞንድ ገስ፣ ቴሪ ኢግላተን እና ፍሬዴሪክ ጀምስ ያሉ።

ፈረንሳዊው ፈላስፋ ሉዊስ ኦልትሰርም ርዕዮተ ዓለም ሰዎች በሚኖሩበት ማህበረሰብ ውስጥ እንዲሆንላቸው የሚመኙትንና የሚፈልጉትን የሚገልፁበት ነው ይለናል። ኢግላተን በበኩሉ የርዕዮተ ዓለም ትርጓሜ ይሆናል ብሎ 16 ፍቺዎችን አስቀምጧል። ከዚህ ውስጥ ርዕዮተ ዓለም እንደ ሥነ ጽሑፍ ከነባራዊ ሁኔታ (ጊዜና ቦታ) ሊነጠል የማይቻል ነው በሚል ይገልፃል።

የኢትዮጵያ ህዝብ መዝሙር ግጥም በቀላል ወይም ተነባቢ ቃላት የተዋቀረ ነው፤ ሆኖም የግጥሙ ሃሳብ ጥልቅና ታሪክ ተኮር ነው። ለዛሬው ንግርት የኋላውን ይታከካል፤ የኋላው ጊዜ ዘመን ጥሩ እንዳልነበር እያስታወሰ ያ ዘመን ፈፅሞ እንደማይመጣ አስረግጦ ይናገራል።

አሁን የተገኘችው ሀገር በአደራ የተረከብናት መሆኑን እያመላከተና ሀገር ከሌለ ህዝብ እንደማይኖር እየነገረ ኢትዮጵያዊነትና ህዝባዊነት ፈፅሞ እንደማይነጣጠሉ ያስገነዝበናል። የመጪውን ጊዜ ብሩህነትም ያሳየናል።

በአስር መስመር ግጥም በተዋቀረው የኢትዮጵያ ህዝብ መዝሙር (የዜግነት ክብር)ከመጀመሪያው ስንኝ ጀምሮ የኢትዮጵያ ህዝቦች ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ተዳስሰውበታል። ግጥሙ እንደ ቃል የተዘረዘሩትና እንደ መልዕክት የታመቁት እኩልነት፣ ፍትህ፣ ያልተሻረ ሰብዕና፣ አንድነት፣ ባህል፣ ሥራና ጀግንነት የዜጎች ክብር መሰረት መሆናቸውን ያስገነዝበናል።

ቃላቶቹ የደመቀ ትርጓሜና ግልፅነት የሚኖራቸው አሁን ካለው ሥርዓትና ካለፉት ጊዜ እውነታዎች ጋር እያነፃፀርን ስናያቸው ነው። ለምሳሌ አንድነት ስንል ምን ዓይነት አንድነት ብለን እንድንጠይቅ እንገደዳለን። ለምን ቢባል በደርግ ዘመን በነበረው «ኢትዮጵያ ቅደሚ…» ብሔራዊ መዝሙር ግጥም ውስጥ «አንድነት» ነበርና፤ «ለኢትዮጵያ አንድነት ለነፃነት…» የሚለው ማለት ነው።

ስለዚህም ከርዕዮተ ዓለም አንፃር የአሁኑን መዝሙር ግጥም ስንመለከት ግጥሙ ስለ ዴሞክራሲያዊ አንድነት እየነገረን መሆኑን እንረዳለን። ዴሞክራሲያዊ አንድነት የሚለው ገለፃ አሁን ካለው ርዕዮተ ዓለም ጋር በቀጥታ የተዛመደ ነው።

በዚህኛው የአሁን ዘመን የመዝሙር ግጥም ጎልተው የሚታዩን ሌላው የርዕዮተ ዓለም መገለጫዎች «ያልተሻረ ሰብዕና፣ ባህልና ፍትህ» ተብለው የተቀመጡት ቃላቶች ናቸው። እነዚህን ቃላቶችና ሃሳቦች ባለፉት መዝሙር ግጥሞች ላይ አናገኛቸውም፤ ቃላቶቹን አሁን ምን አመጣቸው ካልን ርዕዮተ ዓለም ብቻ ነው ሊሆን የሚችለው መልሱ።

«ያልተሻረ ሰብዕና» የሚለው ገለፃ ከዚህ ቀደም የተጨቆነ ሰብዕና መኖሩን ያስገነዝበናል። የባህሉም ጉዳይ ተመሳሳይ ነው። አውዱን ስንመለከት የምናገኘው መነሻ ከዚህ ቀደም በነበሩ ሥርዓቶች ህዝቦች ባህላቸውን፣ የባህላቸው መገለጫ የሆነ ቋንቋቸውንና ማንነታቸውን አጥተው ከርመዋል የሚል መልዕክት ይከሰትብናል። ፍትህ አልነበረም የሚለውን መልዕክትም ያሳየናል።

ከሀገራችን የዘርፉ ምሁራን እንደ ብርሃኑ ገበየሁ ያሉት «የሥነ ግጥማዊ ትንታኔ መዳኛው … የተፃፈውን ቃል በራሱ የንባብ አውድና ባህሉ ባፀደቃቸው ኪናዊ ስምሪቶች ማንፀሪያነት መተርጎም ነው» ይሉናል።

ከዚህ አኳያ ኢትዮጵያዊውን ባህልና አውድ ተመርኩዘን ግጥሙን እንደ ሌላው ሥነ ጽሑፍ ጊዜና ቦታ ከሚፈልገው ርዕዮተ ዓለም አንፃር ስንቃኘው የኢትዮጵያ ህዝቦችን ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ማንነት የሚያቀነቅን ሆኖ እናገኘዋለን። ልዕለ ሃሳቡ ገንኖና የብዙዎች ሆኖ እንዲሄድ የሚያደርግ ጥልቅ አስተሳሰብ መኖሩንም እንረዳለን። ያለፈው ጊዜ መለወጡንም እናረጋግጣለን።

የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ትንታኔውን ሊያጠናክር የሚችል ሃሳብ ጎልቶ ይታይበታል። በህገ መንግሥቱ አንቀፅ 4 «የኢትዮጵያ ብሔራዊ መዝሙር» በሚለው ርዕስ ስር « የኢትዮጵያ ብሔራዊ መዝሙር የሕገ መንግሥቱን ዓላማዎችና የኢትዮጵያ ህዝቦች በዴሞክራሲ ሥርዓት አብረው ለመኖር ያላቸውን እምነት፣ እንዲሁም የወደፊት የጋራ ዕድላቸውን የሚያንፀባርቅ ሆኖ በህግ ይወሰናል» ይላል።

ይህም ግጥሙ ገና ከመዘጋጀቱ በፊት ርዕዮተ ዓለማዊ አቅጣጫ ነበረው ማለት ይቻላል፤ የማህበረሰቡን ባህል፣ ፖለቲካ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ሁኔታዎች ቀድሞ ግምት ውስጥ አስገብቷል። የአሁኑን እምነታቸውንና የወደፊት ዕድላቸውንም ተልሟል።

በግጥሙ የርዕዮተ ዓለም አንዱ ፋይዳና ዋነኛ መገለጫ ይኸው መሆኑ እርግጥ ቢሆንም የኢትዮጵያ ህዝብ መዝሙር ግጥም ከርዕዮተ ዓለም አንፃር የማርክስ ያልሆነ፣ የሌሎች ሶሻሊስታዊ ንድፈ ሃሳቦችንም የማያቀነቅን የኢትዮጵያውያን ህዝቦች ብቻ የርዕዮተ ዓለም ማቀንቀኛ ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል።

የሰንደቅ ዓላማ ቀን ስናከብርም በዚህ እውነትና ታሪክ መካከል በመሆናችን ለሀገራችን፣ ለሉዓላዊ ነታችን፣ በውስጣችን ላለው ልዩ ኢትዮጵያዊነት ልዩ ክብር ሰጥተን በማንነታችን ላይ የተነሱ የእኛዎቹን ቅኝ ገዢዎች እባካችሁ ታሪካችሁን እወቁ እያልናቸው ይሁን።

********

Guest Author

more recommended stories