ኢቴቪ የአልጀዚራን ግብፃዊ ፕሮፓጋንዳ ሲያስተጋባ

በኳታር መንግስት ሃብት የተቋቋመውና ስነ አፈጣጠሩ ሲጠናም የምዕራቡን አለምና የእስራኤል ሚዲያን የአረብ ሀገራት ጉዳይ አዘጋገብ ለመገዳደር የተፈጠረው የአልጀዚራ ቴሌቪዥን ጣቢያ ስትራግል ኦቨር ናይል በሚል ርዕስ አንድ ዘጋቢ ፊልም አዘጋጅቶ ነበር። ጣቢያው ይህን ፊልም በቴሌቪዥኑ ያስተላለፈው ሲሆን በድረ ገፁ ላይ ስለጫነውም በርካቶች ተመልክተውታል።

የዘጋቢ ፊልሙ ይዘት በናይል ወንዝ የተነሳ በላይኛውና በታችኛው የተፋሰሱ ሀገራት መካከል ስለነገሰ ውጥረት ሲሆን ትኩረት ያደረገው ደግሞ ከላይኛው ተፋሰስ ኢትዮጵያ ላይ፤ ከታችኛው ተፋሰስ ደግሞ ግብፅ ላይ ነው። ይህን ፊልም የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ከሞላ ጎደል እንደወረደ በሚባል ደረጃ ወደ አማርኛ ተርጉሞ አቅርቦታል። ‘ጠብቁን’ የሚል ማስታወቂያ መሰራቱና ፊልሙ በተደጋጋሚ መታየቱ የአባይ ፍጥጫ ከሚለው ጩኸታም ርዕሱ ጋር ተዳምሮ በርካታ ኢትዮጵያዊያን እንደተከታተሉት ለመገመት አይከብድም።

ይህን ዘጋቢ ፊልም የተከታተሉ የምቀርባቸውን ሰዎች ስለ ዘገባው ያላቸውን አስተያየት ጠይቄያቸው ነበር። የሚበዙቱ እንዳደነቁት ነግረውኛል። ሁሉም ለማለት በሚቻልበት ደረጃ በምስል አጠቃቀሙ፤ በትረካው ፍሰትና በታሪክ አወቃቀሩ በጥቅሉ በአቀራረብ ደረጃ ምርጥ የሚባል ዘጋቢ ፊልም እንደሆነ ይስማማሉ። እኔም በዚህ ረገድ ልዩነት የለኝም። ሆኖም አንዳንድ ያሳሰቡኝን ጥያቄዎች ሳነሳ የጠየቅኋቸውም እንደኔው ግር ይላቸዋል አለያም “እውነትክን ነው፤ ከኢትዮጵያ ጥቅምና አቋም ጋር ይጋጫል”ይሉኛል።

በእኔ እምነት ዘገባው ከኢትዮጵያ ይልቅ ለግብፅ ጥቅም ያደላ፤ ሶስተኛ ወገን ለኢትዮጵያ ሳይሆን ለግብፅ እንዲጨነቅላት/እንዲያዝንላት የሚያደርግና ኢትዮጵያ ከምትከተለው አብሮ የመልማት ወይም በጋራ የመጠቀም እሳቤ ይልቅ ለፍጥጫና ግጭት መንስዔነት የቀረበ ነው። ይህን የምለው አልጀዚራ የአረብ አለም ሚዲያ ነው፤ ግብፅ ደግሞ የአረቡ አለም እምብርት ነች ከሚል አጠቃላይ ፍረጃ ተነስቼ ሳይሆን ከራሱ ከዘገባው ይዘት በመነሳት ነው። የማነሳቸው መከራከሪያዎችም በፊልሙ ውስጥ ቃል በቃል የሰፈሩ ናቸው።

ይህ ዘጋቢ ፊልም ለኢትዮጵያ አይበጅም ስል ምክንያት ከማደርጋቸው አንዱ የአባይ/ናይል ወንዝ ከኢትዮጵያ ይልቅ ለግብፅ እጅግ አስፈላጊ እንደሆነ አድርጎ ማቅረቡ ነው። እንደ ፊልሙ አባይ ለግብፅ የህልውና ጉዳይ ሲሆን ለኢትዮጵያ ግን የልማት ወይም የእድገት ጉዳይ ነው። በዘገባው ላይ እንደተገለፀው ካይሮ የተፈጠረችውና ያደገችው በናይል ወንዝ የተነሳ ነው። ያለ ናይል አካባቢው ሰው ሊኖርበት የማይችል በረሃ ነው። ማንኛውም ግብፃዊ በወንዙ ዙሪያ የመስፈር ፍቅሩም ከፍተኛ ነው። ስለሆነም “ሄሮዲተስ ግብፅን የአባይ ስጦታ ብሎ ገልጧታል። ትክክለኛ አገላለፅ ነው” ሲል ይደመድማል።

“በ1959ኙ ስምምነት መሰረት ግብፅ ከአባይ ወንዝ 55.5 ቢሊዮን ሜትሪክ ኪውብ ውሃ ይደርሳታል። ሆኖም ግን ከዚያን ግዜ ጀምሮ የግብፅ ህዝብ በሶስት እጥፍ አድጎ 80 ሚሊዮን በመድረሱ የውሃ እጥረት አጋጥሟታል።” ተብሏል በፊልሙ ውስጥ። ቃለ ምልልሱ ያካተታቸው የግብፅ ወታደራዊ ተንታኝ “በህልውናና በደህንነት መካከል ልዩነት አለ፤ እኛ ሙሉ በሙሉ የአባይ ዉሃ ጥገኞች ነን። ሌላ የዉሃ ምንጭ የለንም። ስለዚህ ሃቁ ያለው በአባይ ዉሃ ላይ ስጋት የሚፈጥር ነገር ሲኖር በግብፆች ህልውና ላይ ያነጣጠረ ነው ማለት ነው። ይህ ደግሞ በእኛ ላይ የዉሃ ጥምና የሞት አደጋን እንዳያስከትል ያሰጋናል” ይላሉ።ስለተጠቃሚነት የተጠየቁት ኢትዮጵያዊ ወ/ሮ አጀበች ደግሞ በመብራት እጦት መሰቃየታቸውን ይናገራሉ። የነዚህ ንግግሮች ድምር አባይ/ናይል ለግብፃዉያን የህይወት ምንጭ፤ ለኢትዮጵያዉያን ግን የመብራት ምንጭ ነው የሚል ነው።

እኔ ወንዙ ለግብፅ በምን ያህል ደረጃ ያስፈልጋታል? የሚል ክርክር ውስጥ መግባት አልፈልግም። ወንዙ ከነሱ ህልውና ጋር አይተሳሰርም ብዬም አልከራከርም። ከግብፅ በላይ ለእኛ ያስፈልገናልም አልልም። ግን ሶስት ጥያቄዎችን አነሳለሁ።

አንደኛው ናይል ለግብፆች የሞት የሽረት ጉዳይ ስለመሆኑ ማውራቱ ለኢቲቪ ምን ይፈይድለታል? የሚል ነው። ይህንንማ ግብፃውያን ከውልደት እስከሞታቸው የሚሰበኩት አይደለም እንዴ። ይህንንማ በራሳቸው ሚዲያ ሁሌ የሚደጋግሙልን አይደል እንዴ? ትክክል አለመሆናቸውን ለማሳየት ነው እንዳልል እንዲያ የሚል ነገር አልሰማሁበትም።

ሁለተኛው ጥያቄዬ ምን የሚያሰጋ ነገር ስለመጣ ነው የግብፆችን ስጋት ማንፀባረቅ ያስፈለገበት? የሚል ነው። ኢትዮጵያ የዉሃው መጠን አይቀንስም፤ ማንም ሳይጎዳ ወንዙን በጋራ መጠቀም እንችላለን እያለች ባለችበት ሁኔታ የነሱን “በዉሃ ጥም እናልቃለን” ስጋት ማውራት ‘እንትን ያለበት ዝላይ አይችልም‘ እንደሚባለው አያስመስልምን? ይህ ነገር በተለይ ኢትዮጵያና ብሪታኒያ ወንዙን ግብፅን ለማንበርከክ ይጠቀሙበት ነበር ተብሎ ከቀረበው ታሪክ ጋር ሲዳመር የግብፅ ስጋት ተገቢ ነው ወደሚል ማደማደሚያ አያደርስም? በፊልሙ ውስጥ ቀደምት የኢትዮጵያ ገዢዎች ከግብፅ ወርቅ ለማግኘት ሲሉ አባይን እንገድበዋለን እያሉ ያስፈራሩ እንደነበርና ብሪታኒያም የግብፆችን የፀረ ቅኝ ግዛት እንቅስቃሴ ለመግታት ስትል በጥቁር አባይና በነጭ አባይ መካከል ግድብ መስራቷ ተመልክቷል። አልጀዚራ በተዘዋዋሪ እየተናገረ ያለው አሁንም ኢትዮጵያ ግድቡን ግብፅን ለማንበርከክ ልትጠቀምበት ትችላለች ነው።

ሶስተኛው ጥያቄዬ ሁለቱ ሀገሮች በፍትሃዊ አጠቃቀም ላይ ስምምነት ባልደረሱበት ሁኔታ ይህን ፊልም ያየ ሶስተኛ ወገን ምን ሊያስብ ይችላል? ነው። በፊልሙ ላይ ግብፆች ገና ከአሁኑ በዉሃ እጥረት እየተሰቃዩ እንደሆነ ለማሳየት ታስቦ የገቡ ምስሎች ብዙ ናቸው። በርካታ ግብፃውያን ጀሪካኖችን ይዘው በአንድ ቧንቧ ዙሪያ ሲራኮቱ ይታያሉ። ይህ ግን አጠቃላዩን የግብፅ ሁኔታ ገላጭ አይደለም። ይልቁንም ግብፆች የሚታወቁትና ራሳቸውም የማይክዱት በዉሃ አጠቃቀማቸው አባካኝ እንደሆኑ ነው። እንግዲህ ሶስተኛ ወገን ሲባል ለጋሽ ድርጅቶችን፤ ሃያላን መንግስታትን፤ ሌሎች የአፍሪካ ሀገራትን ያካትታል። ይህን ፊልም ሲመለከቱ የሚያዝኑት ለማን ይሆናል? መብራት ለምትፈልገውና ሌሎች አማራጮች አሏት ተብላ በፊልሙ ለተፈረጀችው ኢትዮጵያ? ወይስ ህይወቷ በሙሉ በናይል ላይ የተንጠለጠለና የመጠጥ ዉሃ አጥታ የምትሰቃይ ተደርጋ ለተሳለችው ግብፅ?

ሁለተኛው የመከራከሪያ ነጥቤ ዘጋቢ ፊልሙ አባይ/ናይልን ከትብብር ይልቅ የግጭት ምንጭ አድርጎ ስሎታል የሚል ነው። ይህን የምመዝነው ኢትዮጵያ ከያዘችው አባይ/ናይል የትብብር እንጂ የግጭት ምንጭ ሊሆን አይችልም ከሚለው አቋም ተነስቼ ነው። የዘጋቢ ፊልሙ ርዕስ በእንግሊዘኛው ስትራግል ኦቨር ናይል የሚል ሲሆን ኢቲቪ የተረጎመውም የአባይ ፍጥጫ በሚል ነው። የፊልሙ ችግር ከዚህ ይነሳል። የአልጀዚራን ቀልብ የሳበው ኢትዮጵያ የምትከተለው አባይ/ናይል ለሁላችንም በቂ ነው የሚለው የትብብር መንፈስ ሳይሆን ግብፅ የምትሰብከው የዜሮ ድምር ውጤት ነው። በግልፅም “ናይል የህይወትም የግጭትም ምንጭ ነው” ይላል። የህይወት ምንጭ የተባለው ለግብፅ ሲሆን የግጭት ምንጭ የተባለው ለሁለቱ ሀገራት መሆኑ ነው። የትብብር ምንጭ መሆን እንደሚችል ግን አያረጋግጥም።

ኢትዮጵያና ግብፅ ያላቸው ባላንጣነት እድሜ ጠገብ መሆኑን የሚገልፀው ይህ ፊልም ሁለቱም ሀገራት የስልጣኔ ምንጭ ከሆኑበት የጥንቱ ታሪካቸው ጀምሮ ተቀናቃኝ ሆነው መኖራቸውን ያሳያል። አፄ ኃይለስላሴ እና ገማል አብደል ናስር ሁለቱም ራሳቸውን የአፍሪካ ግንባር ቀደም መሪ አድርገው ስለሚወስዱ በያዟቸው ተቃራኒ የፖለቲካ አስተሳሰብ ልዩነት /ኢምፔሪያሊስትና ፀረ ኢምፔሪያሊስት/ ውስጥ ሆነው በተቀናቃኝነት መኖራቸውን ያትታል። ውጥረቱ በደርግ መንግስት ወቅትም መቀጠሉንና የዚህም ምንጩ መንግስቱ ኃይለማርያም ፊቱን ወደ ሶቪየት ሲያዞር አንዋር ሳዳት ደግሞ ወደ ምዕራባውያን በማዞሩ ሁለቱ ሀገሮች በሁለቱ የአለም ጎራዎች ማዶና ማዶ መሰለፋቸው እንደሆነ ያስታውሳል። አሁን ደግሞ ኢትዮጵያ አስቸጋሪ ፈተና ውስጥ ገብታለች ይላል የአልጀዚራው ጋዜጠኛ።እንደዘገባው “አሁን ኢትዮጵያ በሁለት አማራጮች የተወጠረች ሀገር ሆናለች። በአንድ በኩል ወንዙን ለልማት የማዋል በሌላ በኩል ደግሞ ከታችኞቹ የአባይ ተፋሰስ ጎረቤቶቿ ጋር ያላትን ግንኙነት በማሻከር መካከል ያሉትን አማራጮች በትኩረት ታያቸዋለች።”

እዚህም ላይ ዘገባው እውነትን አልያዘም ብዬ አልከራከርም። ጥያቄዬ ይህ እውነት ትብብርን በምንሻው በእኛ በኢትዮጵያውያን መዘገቡ ፋይዳው ምንድን ነው? የሚል ነው። የኔ ጥያቄ ለምን ያለፉትን የግጭት መንስዔዎቻችንን ከምናጎላ አዳዲሶቹን የትብብር አማራጮቻችንን አንተነትንም? የሚል ነው። አሁን አፄዎቹ የሉም፤ ደርግም ተገርስሷል። በምትኩ ያለው‘በጠላቶች ተከብቤያለሁ’ ከሚል የቆየ ስሜት ራሱን አውጥቶ ከጎረቤቶቹ ጋር በጥቅም የተሳሰረ፤ ይህንንም ወደ ሌላ ታላቅ ምዕራፍ ለማሸጋገር እየሰራ ያለ መንግስት ነው። ታዲያ ፊልሙ ምነዋ ይህን ተግባራችንን ዘነጋው? ምነውስ ከጎረቤቶቻችን ጋር ያለንን ግንኙነት ሳናሻክር አብረን መበልፀግ ይቻላል የሚለውን ሶስተኛውን አማራጭ ሳያቀርበው አለፈ?

ወደ ሶስተኛው ምክንያቴ ልለፍ። በዚህ ዘጋቢ ፊልም ላይ የኢትዮጵያን ጥቅም የሚጎዱ ነገር ግን በአግባቡ ምላሽ ያልተሰጠባቸው ሃሳቦች አሉ። አንደኛው ግብፃዊው የፖለቲካ ተንታኝ አብዱል ዋሂብ ያነሱት ሃሳብ ነው። “የቀድሞ ስምምነቶችን ማክበር አለብን። ይህ ለአለም አቀፋዊ የሀገራት ድንበርም የሚያገለግል አካሄድ ነው። ለምሳሌ ከነፃነት በፊት የነበሩ በርካታ የአፍሪካ ሀገራት ድንበሮችን መቀየር አንችልም። እነዚህ በቅኝ ገዢዎች የተከለሉ ድንበሮች ከነፃነትም በኃላ ህጋዊ ሆነው እንዲያገለግሉ ከስምምነት ተደርሷል። ስለዚህ በአባይ ዉሃ አጠቃቀም ዙሪያ የተፈረሙትንም ስምምነቶች በተመሳሳይ መልኩ ማየት ነው።” ይላሉ። የ1929ኙን ስምምነት መሆኑ ነው። ጋዜጠኛው ደግሞ “የላይኛው ተፋሰስ ሀገራት ግን እነኚህ ስምምነቶች የቅኝ ግዛት ቅሪት ስለሆኑ ተቀባይነት የላቸውም ሲሉ ይከራከራሉ” ይላል።

የኢትዮጵያ መከራከሪያ ግን ይህ ሊሆን አይችልም። የስምምነቱ አካል ስላልሆንኩ ለመቀበል የሚያስገድደኝ ምንም አይነት ህግ የለም ነው የምትለው ኢትዮጵያ። የቅኝ ግዛት ቅሪት በሚለው ከሆነማ አብዱል ዋሂብ እንዳሉት የድንበር ማካለሉን ተቀብለን ስምምነቶቹን እንቢ የምንልበት ምክንያት አይኖርም። አልጀዚራ ይህ ጠፍቶት ሳይሆን ኢትዮጵያ የያዘችውን ትክክለኛና ምክንያታዊ አቋም አለባብሶ ለማለፍ ስለፈለገ ነው።

በሌላ መልኩ “በአለም አቀፉ ህግ መሰረት የላይኛው ተፋሰስ ሀገራት ግድብ ከመስራታቸው በፊት የታችኞቹን ተፋሰስ ሀገራት የማማከር ግዴታ ስላለባቸው ለግብፅ ማሳወቅ አለባቸው” ይላሉ። ይህም እንደ ሃቅ ተቀባይነት አግኝቶ ያለፈ ነው በዘጋቢ ፊልሙ። እውነታው ግን ይህን አይነት አስገዳጅ አለም አቀፍ ህግ ያለመኖሩ ነው። ይልቁንም ህጉ የሀገራትን ሉዓላዊ መብት የሚያከብርና ፍትሃዊና በሌላው ላይ ትርጉም ያለው ጉዳት ያለማድረስ መርሆችን የሚያበረታታ መሆኑ ነው።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በ1997 ያወጣው ለመጓጓዣነት የማያገለግሉ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች አጠቃቀም ስምምነት እኩል/ሚዛናዊ ተጠቃሚነትና ከፍተኛ ጉዳት ያለማድረስን ነው መሰረት የሚያደርገው። እኩል/ሚዛናዊ ተጠቃሚነት ደግሞ የህዝብ ብዛትን፤ የቆዳ ስፋትን፤ ሊታረስ የሚችል መሬትን፤ ሌሎች አማራጭ ምንጮችንና የዉሃውን ደህንነት መጠበቅ የሚባሉ ጉዳዮችን ያቀፈ ነው። ስትራግል ኦቨር ናይል ግን እነዚህን ጉዳዮች ዘወር ብሎ አላያቸውም።

ሌላው ግብፆች የሚመኩበትና እስካሁንም አወዛጋቢ የሆነው በአፄ ሚኒሊክና በብሪታኒያ መንግስት መካከል ተፈርሟል የሚባለው ስምምነት ነው። ይህንን የግብፆችን መከራከሪያ ነጥብ ሳያስተባብሉ እንደወረደ ከማቅረብ በላይ የኢቲቪን ወገንተኝነት ጥያቄ ውስጥ የሚከት ጉዳይ አይኖርም። ፊልሙ ላይ እንዲህ ይላል። እንግሊዝ እ.አ.አ በወርሃ ግንቦት 1902 ከአፄ ሚኒሊክ ጋር አንድ ስምምነት ተፈራረመች። በዚህ ስምምነት አፄ ሚኒሊክ የአባይ ወንዝ ወደ ግብፅ የሚያደርገውን ፍሰት የሚያሰናክል ወይም የዉሃውን መጠን የሚቀንስ ምንም አይነት ግድብ እንደማይገነቡ ቃል ገቡ።” የሚገርመው በቅርቡ በናይል ቲቪ በተካሄደ የቀጥታ ስርጭት ውይይት ላይም የቀድሞው የግብፅ የዉሃ ሚኒስትር ዶ/ር ናስር አደም ይችን ነጥብ አንስተዋታል።

አፄ ሚኒሊክ ፈርመውታል የተባለው ስምምነት ፕሮፌሰር አሊ አብዱላህ አሊ እንደሚሉት ቢያንስ በሁለት መሰረታዊ ነጥቦች የተነሳ በአሁኑ ወቅት ተቀባይነት የለውም። አንደኛ ስምምነቱን የሁለቱ ሀገራት የወቅቱ የዘውድ ም/ቤቶች አላፀደቁትም። ሁለተኛ የስምምነቱ የአማርኛና የእንግሊዝኛ ትርጉም ግጭት ፈጥሮ ስለነበር አፄ ሚኒሊክ በወቅቱ አልተቀበሉትም። አልጀዚራ ያዘጋጀውና ኢቲቪ የተቀበለው ዘጋቢ ፊልም ይህንን የግብፅን የክስ ነጥብ ያሳይና የኢትዮጵያን መከራከሪያ ነጥብ ግን አያስቀምጥም። በዚህም በህግ የመርታት አዝማሚያው ለግብፅ ያጋደለ እንዲመስል አድርጓል።

የመጨረሻውን ነጥቤን ላንሳ። እንደፊልሙ ከሆነ የኢትዮጵያን የአፈር ማዕድን ጠራርጎ የሚሄደው ደለል ለግብፃዊያን ሲሳያቸው ነው። ፊልሙ “ለም አፈር ለግብፃውያን ዋና ስጦታ ነው” ይልና ምክንያቱን ሲያብራራ መሬታቸው በለም አፈር ይበለፅግላቸውና አጥጋቢ ምርት ያገኛሉ ይላል። ይህን ከተቀበልን ኢትዮጵያ ‘ግድቤ ደለልን በመቀነስ የታችኞቹን ሀገራት ተጠቃሚ ያደርጋል’ የምትለው ድለላ /lip service/ ነው ማለት ነው። አልጀዚራ ይህን ይበል እንጂ እውነታው ግን እሱ አይደለም። ግብፅ የአስዋን ግድብን ከገነባች በኋላ ደለሉ በግድቡ የታችኛው ክፍል ላይ ስለሚተኛ ተጠቃሚ ሳይሆን ተጎጂ ነው የነበረችው። ስለዚህም የኢትዮጵያ አቋም ትክክል ተብሎ ነበር መወሰድ ያለበት።

ልብ በሉ፤ አሁን ልክ አይደለም የምለደው አልጀዚራን አይደለም፤ ኢቲቪን ነው። አልጀዚራማ ከሚዲያው ጥቅም ተነስቶ የሚፈልገውን መልዕክት አቅርቧል። እኔ የምተቸው የኢትዮጵያ የሆነውን ኢቲቪን ነው። ዘገባው ከላይ ያስቀመጥኳቸው የይዘት ጉድለቶች ሳሉበት ለምን ኢቲቪ አስተላለፈው? ነው የኔ ጥያቄ። ለአንድ ደቂቃ ማስታወቂያ በሺዎች የሚቆጠር ብር የሚቀበለው ኢቲቪ ለምን የአየር ሰዓቱን በዚህ ማቃጠል አስፈለገው? ነው የእኔ ጥያቄ። የኢትዮጵያን ጥቅም ማስጠበቅ የሚችል የፀዳ ዘጋቢ ፊልም በውስጡ ባለው የዶክመንታሪ ክፍል መስራት የሚችለው ኢቲቪ ለምን የአልጀዚራን ዥጉርጉር ፊልም መኮረጅ አስፈለገው? ነው የኔ ጥያቄ።

እያንዳንዱ ሚዲያ ሲቋቋም የራሱ ተልዕኮ ይዞ ነው። ለጥቅሙ የሚቆምለት ወገንም አለው። አልጀዚራ የኳታርን ብሔራዊ ጥቅም በሚጎዳ ተግባር ውስጥ እጁን አያስገባም። በአንፃሩ የኳታርን ሲያልፍ ደግሞ የአረቡን አለም አጀንዳዎች ከፍ ከፍ አድርጎ ያሰማል። ኢቲቪ የሚከተለው የሚዲያ ፍልስፍና ልማታዊ ጋዜጠኝነት ነው። በልማታዊ ዴሞክራሲ የፖለቲካ ኢኮኖሚ ውስጥ እንደመሆኑ በተለይ እንደ ኢቲቪ ያለ የህዝብ ሚዲያ ግልፅ ተልዕኮዎችን ይዞ መንቀሳቀሱ የማይቀር ነው። እናም የኢትዮጵያን ሕዳሴ ማብሰር ዋና ተልዕኮው ነው።

ሁለቱ ተቋሞች በተልዕኮም በሚከተሉት ፍልስፍናም የማይታረቁ ባህሪዎች አሏቸው። ኢቲቪ ከአልጀዚራ ያገኘውን ዘገባ እንደወረደ ለአድማጭ ተመልካቹ የሚዘረግፍ ከሆነ ተሸውዷል ማለት ነው። አሁንም የሚታየኝ ይሄው ነው። ግድ የላችሁም፤ አልጀዚራ በውብ ምስሎቹና በማራኪ አቀራረቡ የተነሳ ኢቲቪን ሸውዶታል። ግን ለሌላ ግዜ ትምህርት ይሆነዋል ብዬ አስባለሁ።

*********
ይህ ጽሑፍ  በሳምንታዊው ሰንደቅ ጋዜጣ የካቲት 26-2006 ታትሟል፡፡

Kebede Kassa

more recommended stories