በትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ እስካሁን የተደረሰባቸው ግቦች – በከፊል

የሚኒስትሮች ምክር ቤት የካቲት 14/2006 ባካሄደው ስብሰባ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ያለፉትን ሦስት ዓመታት አፈጻጸም የመገምገም ሲሆን፤ በኢዜአ ዘገባ መሠረት ምክር ቤቱ፡-

• በአገሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥ መዋቅራዊ ለውጥ ለማምጣት በተደረገው ጥረት – የግብርና ዘርፍ በ2002 ከአገር ውስጥ ጠቅላላ ምርት ከነበረበት የ46 ነጥብ 5 በመቶ ድርሻ በ2005 ወደ 42 ነጥብ 9 በመቶ ዝቅ ያለ፤  ኢንዱስትሪ ከ10 ነጥብ 3 በመቶ ወደ 12 ነጥብ 4 በመቶ ከፍ ያለ፤ እንዲሁም የአገልግሎት ዘርፍ ከ44 ነጥብ 1 በመቶ ወደ 45 ነጥብ 2 በመቶ ከፍ ማለቱን፤

• ከድህነት ወለል በታች የሚኖረው ህዝብ ብዛት በ2003 ዓመት 29 ነጥብ 6 በመቶ የነበረ ሲሆን፤ በ2005 ወደ 26 በመቶ ዝቅ ማድረግ የተቻለ በመሆኑ፤ በ2007 ይደረስበታል ተብሎ የታቀደውን 22 ነጥብ 2 በመቶ ማሳካት እንደሚቻል፤

• ጠቅላላ የአገር ውስጥ ቁጠባ ምጣኔ በ2002 ከነበረበት 5 ነጥብ 2 በመቶ በ2005 ወደ 17 ነጥብ 7 በመቶ ማደጉን፤ ይህም በ2007 ሊደረስበት ከተያዘው የ15 በመቶ ግብ በላይ በመሆኑ፤ በ2007 ወደ 20 በመቶ ከፍ ለማድረግ ጥረት መደረግ እንዳለበት፤፡

• የኢንቨስትመንት ወጪ ከጠቅላላው የአገር ውስጥ ምርት ድርሻ በ2002 ከነበረበት 24 ነጥብ 7 በመቶ በ2003 ወደ 33 በመቶ ከፍ ማለቱን፤ የወጪ ንግድ አፈፃፀም በ2005 የ3 ነጥብ 1 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ገቢ አፈፃፀም መመዝገቡንና ያለፉት ሶስት ዓመታት አማካኝ ዕድገቱ 16 ነጥብ 5 በመቶ እንደሆነ በመገምገም፤ ከታየዘው ግብ ሲነፃፀር ወደ ኋላ የቀረ በመሆኑ በቀሪው ጊዜ አካክሶ መሄድ እንደሚገባ፤

• የግብርና ምርት በ2002 ዓ.ም. 202 ነጥብ 4 ሚሊዮን ኩንታል የነበረ ሲሆን፤ በ2005 ዓ.ም. 251 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል መድረሱን እና ምርታማነቱም በአማካኝ በ2002 ከነበረበት 15 ነጥብ 4 ኩንታል በሄክታር ወደ 17 ነጥብ 82 ኩንታል ማደጉን፤

• አዳዲስ የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች እንዲደራጁ የመደገፍና ነባሮቹም እንዲጠናከሩና ወደ መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች እንዲሸገጋሩ ለማድረግ በተሠሩ ሥራዎች በ2005 ለ2 ሚሊዮን 21 ሺህ 670 ዜጎች ጊዜያዊና ቋሚ የሥራ እድል ለመፍጠር መቻሉን፤

• 2002 አጠቃላይ በአገሪቱ የነበረው 48 ሺህ 800 ኪሎ ሜትር መንገድ በ2005 ወደ 58 ሺህ 338 ኪሎ ሜትር ማድረስ እንደታቸለ፤

• ሁሉን አቀፍ የገጠር መንገድ ተደራሽ ፕሮግራም እስከ 2005 መጨረሻ 27 ሺህ 628 ኪሎ ሜትር መገንባቱን እንዲሁም የገጠርና የከተማ የመጠጥ ውሃ፣ የቴሌኮም ማስፋፊያዎች፣ የባቡር መስመር ዝርጋታ እና የኃይል ማመንጫ የታላቁ ህዳሴ ግድብን ጨምሮ የተጀመሩ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ዕቅድ መሠረት እየተሰሩ መሆናቸውን፤

• በማህበራዊ ልማት መስክ የተደረገውን እንቅስቃሴ የተመለከተ ሲሆን በ2002 በአገሪቱ 26 ሺህ 951 1ኛ ደረጃ ወይም ከአንድ እስከ ስምንት ትምህርት ቤቶች በ2005 ወደ 34 ሺህ 495 ከፍ ማድረግ የተቻለ መሆኑን፤

• የተማሪዎች ቁጥርም በ2002 ከነበረት 15 ነጥብ 8 ሚሊዮን በ2005 17 ነጥብ 4 ሚሊዮን ማደጉን፤

• የ1ኛ ደረጃ ጥቅል ተሳትፎ ምጣኔ 95 ነጥብ 1 በመቶ አፈጻጸም የተመዘገበ ሲሆን ንጥር ተሳትፎ 85 ነጥብ 9 በመቶ መድረሱም አበረታች መሆኑን፤

• የ2ኛ ደረጃ ትምህርትን በተመለከተም በ2002 ዓ.ም. 1 ሺህ 335 የነበሩ ትምህርት ቤቶች በ2005 ወደ 1 ሺህ 912 እንዲሁም የተማሪዎች ብዛት በ2005 ዓ.ም. 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን መድረሱን፤

• የከፍተኛ ትምህርት ለሁሉም የቅድመ ምረቃ ትምህርት ፕሮግራም ተሳትፎ በግልና በመንግስት 553 ሺህ 848 የደረሰ ሲሆን በአጠቃላይ በከፍተኛ የትምህርት ፕሮግራም በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ለመድረስ የተያዘውን ግብ አስቀድሞ ለመድረስ የተቻለ እንደሆነ፤

• የጤና ተቋማት ግንባታ በተመለከተ በ2002 ዓ.ም. 14 ሺህ 192 የነበረው የጤና ኬላ ብዛት በ2005 ዓ.ም. 14 ሺህ 48 መድረሱን፤

• የጤና ጣቢያ በ2002 በጀት ዓመት 2 ሺህ 142 የነበረውን በ2005 ዓ.ም. ወደ 3 ሺህ 100 ያደገ በመሆኑ በዘርፉ የተቀመጠውን ስታንዳርድ በአጭር ጊዜ ማሳካት እንደሚቻል አረጋግጧል።

********

Content gathered and compiled from online and offline media by Hornaffairs staff based on relevance and interest to the Horn of Africa.

more recommended stories