Leaked tape: አበበ ገላው ኢሳትንና ግንቦት 7ን ሲያማ

Editor’s note: የተቃዋሚ አክቲቪስት የሆነው አበበ ገላው በግንቦት 2004 የቀድሞው ጠ/ሚኒስተር መለስ ዜናዊ የተገኙበት ስብሰባ ላይ የተቃውሞ ጩኸት ካሰማ ከወራት በኋላ፤ ከግንቦት ሰባት ድርጅት መሪ ከዶ/ር ብርሀኑ ነጋ የበለጠ ትኩረት ስቧል በሚል ከኢሳት ገለል እንዲል ተደርጎ በነበረበት ወራት በግል ያደረጋውን ንግግር የድምጽ ቅጂ፤ HornAffairs ከታማኝ ምንጮች አግኝቷል፡፡
የአበበ ገላውን ኑዛዜ የHornAffairs ብሎገር የሆነው ከበደ ካሣ እንደሚከተለው አቅርቦታል፡፡
**************

(ከበደ ካሣ)

ይህን የ11 ደቂቃ የተቀረፀ ድምፅ ጋብዣችኋለሁ፡፡ ከየት አመጣኸው እንዳትሉኝ፡፡ ዊክ ሊክስ ወይም ስኖውደን ብቻ ናቸው እንዴ አፈትልኮ የወጣ መረጃ የሚያሰረጩት? በመረጃው ትክክለኛነት ላይ ተማምናችሁ ዝም ብላችሁ ኮምኩሙት፡፡

እንደኔ እንደኔ ሙሉውን ቅጂ ብታዳምጡት መልካም ነው፡፡ በደካማ ኢንተርኔትና በጊዜ ማጣት የተነሳ ሙሉውን ማድመጥ ካልቻላችሁ ግን ሙሉ መረጃው በዚህ ፅሁፍ ቀርቦላችኋል፡፡ ልዩነቱ ይሄኛው በፅሁፍ ሲሆን ያኛው በድምፅ መቅረቡ ነው፡፡ ታዲያ ልክ እንደ አበበ ገላው እዚህም እዚያም መዝለል እንዳይሆንባችሁ ታዲያ ሙሉ ንግግሩ በሶስት አበይት ርዕሶች ተደራጅቶላችኋል፡፡ ሲያስፈልግ ደግሞ ንግግሩ እንደወረደ በጥቅስ ምልክት ውስጥ ተቀምጧል፡፡

በርግጥ ያመንከው ሰው ሲከዳህ ወይም የተማመንክበት ሰው ከንቱ መሆኑ ሲነገርህ ሁኔታውን መርምረህ እውነቱን ከመቀበል ይልቅ የወዳጅህን ጉድ ያጋለጠብህን ሰው ማጥላላት የማህበራዊ ድረ-ገፆቻችን መገለጫ ከሆነ ሰንብቷል፡፡ እና ቢሆንም እንዲህ አይነት አመል ያላችሁ ቢያንስ ለዚች ጉዳይ ብቻ አደብ ገዝታችሁ እንድታመዛዝኑ እጠይቃችኋለሁ፡፡

1. አበበ ገላውና የተቃውሞው ጎራ

በሀገር ውስጥ ባለው የተቃዋሚ ጎራ መካከል የይስሙላ ካልሆነ በቀር የአላማ አንድነት እንደሌለ በተደጋጋሚ በተፈፀሙ ድርጊቶች ተጋልጧል፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በውህደት ድርድር የሚያሳልፉትን ጊዜ ያክል በፍቺ ድርድር ላይም ያሳልፋሉ፡፡ ከመዋሃዳቸው በፊት ርስ በርስ የሚደናነቁትን ያክል ርስ በርስ ለመነቃቀፍም ፋታ አይወስድባቸውም፡፡ እድሜውን አንዱን በመቀበልና ሌላውን በመሸኘት እየገፋ ያለው ‹‹መድረክ›› (በረጅሙ – ‹‹የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ››) ለዚህ ህያው አብነት ነው፡፡ ተጨማሪ ዐብነት ካስፈለገ የ1997ቱን ቅንጅትን መመረቅ ይቻላል፡፡ በዚህ በኩል የማይታማው ሰማያዊ ፓርቲ ብቻ ነው፡፡ እድሜው አጭር ቢሆንም ራሱን ተራራ አሳክሎ ሌሎቹን በንቀት ቁልቁል ስለሚያያቸው በቀላሉ የሚዋሃዱት አይሆንም፡፡ እንትፍ ትፍ፤ ከአይን ያውጣህ ብያለሁ፡፡

በውጭ ያለው የተቃውሞ ሃይልም አንድ የሚያደርገው ፅንፈኛነቱና ጭፍን ጥላቻው ብቻ እንጅ የአላማ አንድነትም ሆነ እርስ በርስ የመተማመን ባህል እንዳልፈጠረበት ፊት አውራሪው አበበ ገላው በራሱ ቃል እንዲህ ሲል አጋልጧል፡፡

“ወደፊትም ትግሌን እቀጥላለሁ በተዘዋዋሪ መንገድ፡፡ ይሄ ግን ከተቃዋሚ ጋር ሆኖ መስራት አያዋጣኝም፡፡ ቤትሬይ {betray} ነው የሚያረግህ፡፡ አንደኛ ተቃዋሚዎቹ ራሳቸው ቅንነት የጎደላቸው ሰዎች ናቸው፡፡ ስም በማጥፋት ምናምን ቶሎ ይሰማራሉ፡፡ አንድ ኢሹን {issue} አድሬስ {address} ከማድረግ ይልቅ፡፡ እኔ አሁን ኮንሰርኔን {concern} እንደ ጓደኛ አድርጌ ሬይዝ {raise} ያደረግሁላቸው ሰዎች በጣም ነው የታዘብኳቸው፡፡ ያንን ነገር በቁም ነገር ከመውሰድ ይልቅ እኔ ራሴን ታላቅ አድርጌ እንደገመትኩ አርገው ያልሆነ አይነት ተራ ወሬ ጀመሩ፡፡”

ለዚህ ሁሉ ምክንያቱ ደግሞ ሁሉም ራሳቸውን ትልቅ አድርገው የማየት ችግር ስላለባቸው መሆኑን አበበ ይጠቅሳል፡፡

“አንድ ነገር ስታነሳበት ዲስቶርት {distort} አድርጎ ያስበዋል፡፡ አንዳንዱ ደግሞ የራሱ የሆነ ችግር ስላለበት የከለልከው የሚመስለውም አለ፡፡ ሳትከልለው፡፡ ለምን? ራሱ በቃ፤ ራሳቸውን ከፍ አድርገው ስለሚያዩ በዚህ ሌቭል /level/ አንዳንድ ኢሹዎች ስታነሳ በቃ ያንን የተጋፋህ የሚመስላቸው አሉ፡፡”

እንደ አበበ ገለፃ ይህ ችግር የአባሎቹ ብቻ ሳይሆን የአመራሮቹም ነው፡፡ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋን ጎሸም ባደረገበት ንግግር መሪዎቹ እየተቃወሙ ሳይሆኑ የራሳቸውን ኑሮ እያመቻቹ ነው ብሏል፡፡

“ደሞ አንዳንዶቹ ኤግዛጅሬትድ ፊሊንግ {exaggerated feeling} ነው እንጅ ያላቸው እየታገሉ አይደለም፡፡ ኦነስትሊ ስፒኪንግ {honestly speaking}፡፡ አንዳንዶቹ የድርጅት መሪ ስለሆኑ ራሳቸውን እንደ ታላቅ፡፡ ኢጎ {ego} ማለት ያ ነው እንደውም፡፡ ትንሽ ሰርተህ ራስህን እንደ ታላቅ ስትገምት ነው ኢጎ ችግር የሚፈጥርብህ፡፡ አንዳንዶቹ ኢጓቸው የጋረዳቸው ሰዎች እየታገሉ አይደሉም፡፡ የራሳቸውን ላይፍ {life} ነው እየኖሩ ያሉት፡፡”

2. አበበ ገላውና ኢሳት ቴሌቪዥን

በጥቅል ፅንፈኛ የተቃውሞ ሃይሉና ኢሳት ቴሌቪዥን በተለይ ደግሞ አበበ ገላውና ኢሳት ቴሌቪዥን ምንና ምን እንደሆኑ ለናንተ መንገር ለቀባሪ እንደማርዳት ነው የሚሆንብኝ፡፡ በአጭሩ እጅና ጓንት ናቸው ብሎ መግለፅ ይቀላል፡፡ እርስ በርስ ሲወዳደሱ ለሰማቸው የጫጉላ ሽርሽር /honeymoon/ ላይ ያሉ ሙሽሮች ነው የሚመስሉት፡፡ አበበ ለኢሳት ጀግናው ነው፤ ኢሳትም ለአበበ ድምፁ ነው፡፡ ኢሳት አበበ ገላውን <የአመቱ /2012/ ምርጥ ሰው> ሲል ሰይሞታል:: አበበም ኢሳትን የህዝብ ድምፅ ብሎታል፡፡

ለነገሩ ኢሳትን ነፃና ገለልተኛ የህዝብ ድምፅ ነው ብለው የሚያስቡ፤ ባያምኑትም የሚሰብኩለት ሌሎችም ሞልተዋል፡፡ እውን ግን ኢሳት ደጋፊዎቹ እንደሚያወሩለት ነው? እነኚህ ደጋፊዎች አበበ ገላው <<እኛ ነፃ ጋዜጠኞች ነን፤ ኢሳትም ገለልተኛ ሚዲያ ነው>> ሲላቸው ያመኑትን ያክል አሁን ጥያቄው <<አይ እኔ ብቻ ነኝ እንጅ ሌሎቹ ጋዜጠኞች ለጥቅማቸው ያደሩ ናቸው፤ ኢሳትም የግንቦት 7 ሎሌ ነው>> ቢላቸው ያምኑት ይሆንን? የሚለው ነው፡፡ አበበ ኢሳትን በተመለከተ እንዲህ ይላል፡፡

“በኢሳት ላይ ያለኝ አንዱ ትልቅ፤ እኔ ብዙ ቅሬታ የለኝም ግን የድርጅት ልሳን ሆኖ ለድርጅት ሎሌ መሆን ደግሞ አልፈልግም፡፡ እኔ በበኩሌ፡፡ ይሄ ሲሪየስ {serious} የሆነ ኢሹ ነው፡፡ እኔ ይሄ ሚዲያ ኢንዲፐንደንት ራን {independently run} መሆን አለበት፡፡ ይደብርሀል – ራሱ መስራቱም ማገልገሉም፡፡ እኔ ማገልገል የምፈልግው ማንን ነው? ግንቦት ሰባትን አይደለም ማገልግል የምፈልገው፡፡ ወይም ግንቦት ዘጠኝን አይደለም ወይም ግንቦት 20ን አይደለም፡፡ እኔ ሰርቭ {serve} ማድረግ የምፈልገው የኢትዮጵያን ህዝብ ነው፡፡”

አበበ ምን ያህል የህዝብ አገልጋይ ነው የሚለው ሌላ ጥያቄ ሆኖ፤ የግንቦት 7 ሎሌ ሆኖ ማገልገል እንዳስመረረው ግን ተናግሯል፡፡ ኢሳት የግንቦት 7 አፈ ቀላጤ ለመሆኑ በአብነት ያነሳው ደግሞ የሚዲያውን የአመስተርዳም ስቱዲዮ ዘገባዎች ነው፡፡

“አሁን ከዜና አቀራረብ ጀምሮ አመስተርዳም የሚሰሩ ዜናዎች መዓት ችግር ነው ያለባቸው፡፡ እነ መሳይ [ከበደ] ዝም ብሎ ኳሊቲ {quality} የሌለው ነገር ነው ፕሮዲውስ {produce} የሚያደርጉት፡፡ በነሱ በኩል ደግሞ የሚመጡ፣ ድርጅት ኢንቮልቭ {involve} የሚያደርግባቸው ነገሮች ደግሞ ብዙ ደካማ የሆኑ ነገሮች ነው ያሉት፡፡”

አበበ ግን ለምን እንዲህ መረረው ከተባለ መልሱ የጥቅም ግጭት /conflict of interest/ ነው ፡፡ እሱ ከጥቅም አንፃር ሁለት ጉዳዮችን ነው የሚያነሳው፡፡

“አንደኛ ገባህ ቤተሰብ አስተዳድራለሁ፡፡ አንድ አመት ሳክሪፋይስ {sacrifice} ልትከፍል ትችላለህ፡፡ በማይረባ ሲቾሺን {situation} ውስጥ እየሰራህ ማለት ነው፡፡ ከዛ በላይ ግን ልትሄድ አትችልም፡፡ ሁለተኛ ደግሞ ማነው ሴኩሪቲህንና ሴፍቲህን {security and safety} ጋራንቲ {guarantee} የሚያደርግልህ? ዱ ዘይ ሪሊ ኬር {do they really care?} አንተ ነገ ብትሞት ኬር የሚያደርግ ሰው አለ?”

አበበ እዚህ ላይ እውነት ተናግሯል፡፡ ይሄ ራስን የመጥቀም እንጅ ድሆችን የማበልፀግ ትግል አይደለም፡፡ ይሄ የራስን ደህንነት አስተማማኝ የማድረግ እንጅ የዜጎችን ሰላም የማስጠበቅ ትግል አይደለም፡፡ ይሄ በምቹ ሀገር እየኖሩ በህዝብ የመነገድ እንጅ ባልተመቸ ቦታ ሆኖ ራስን ለለውጥ መስዋዕት የማድረግ ትግል አይደለም፡፡ ታዲያ ለምንና ለማን ብሎ ራሱን መስዋዕት ያደርጋል? ለምንስ ብሎ በአነስተኛ ክፍያ ይሰራል?

“እኔ በኮዙ {cause} ስለማምንበት ነው እንጅ የራሴን ገንዘብ ሰብሲዳይዝ {subsidize} እያደረግሁ ነው የኖርኩት፡፡ በፋሚሊ ሴቪንግ {family saving} ነው እኛ የኖርነው፡፡ እነሱ በሚከፍሉኝ አይደለም የኖርኩት፡፡ እነሱ የሚከፍሉኝ የቤት ኪራይ ሊከፍልልህ ይችላል፡፡ እንደው የተወሰነ ወጭ ሊሸፍን ይችላል፡፡ ሁለት ልጅ ሲኖርህ ፤ ቤተሰብ ሲሮርህ ግን ወጪህ ከዛ በላይ ነው፡፡ ኤክስፔንሲቭ {expensive} ነው ዲሲና አካባቢው መኖር፡፡”

“በሙሉ ፍላጎትና በቅን ስሜት ልሰራ የምችለው ያ ነገር ኢንሹርድ {insured} መሆኑን ሳይ ነው፡፡ እነሱ የራሳቸው የሆነ ኮምፕሌክስ ስትራክቸር {complex structure} አዋቅረው ለዛውም ደግሞ ቴክ ኬር {take care} አያደርጉም፡፡ ዱ ዘይ ቴክ ኬር አባውት ሚ፤ አባውት ዘሪስክ ዛት ዩ አር ፌሲንግ? ዘይ ዶንት {do they take care about me, about the risk you are facing? They do not.} ብዙ ሪስክ አለው፡፡”

3. አበበ ገላውና የደህንነት ሰጋቱ

አበበ ገላው ዋሽንግተን ዲሲ በተካሄደው የቡድን 8 ስብሰባ ላይ <<መለስ ዲክታተር>> ብሎ ከጮኸ በኋላ ራሱን የነፃነት አርበኛ አድርጎ ይቆጥራል፡፡ መለስ ዜናዊን እኔ ነኝ የገደልኩት ብሎ ስለሚያምንም ቅጠል በተንኮሻኮሸ ቁጥር እንደደነገጠ ነው፡፡ አይዞህ በአንተ ቂም ይዞ የሚበቀልህ የለም የሚሉትንም አይሰማም፡፡ ስለሆነም አሁን የሱ ዋና ስጋት በሰላም ወጥቶ በሰላም የመግባት ጉዳይ ነው፡፡ እንደውም ከንግግሩ መረዳት የሚቻለው ከፅንፈኛው ሃይል ጋር አጣብቆ ያቆየው ይሄው ስጋቱ ብቻ ነው፡፡

“የኔ ኮንሰርን የሴኩሪቲ ኮንሰርን {security concern} ነው፡፡ ሌላ ነገር አይደለም፡፡ ያ የሴኩሪቲ ኮንሰርኔ ደግሞ ሪል {real} ነው፡፡ ሪል ነው፡፡ በጣም በጣም ሪል ነው፡፡ ለነሱ ላይታያቸው ይችላል፡፡ እኔ ግን የጉዳዩ ባለቤት ስለሆንኩ አውቀዋለሁ፡፡ ኤቭሪዴይ ፔይናንስ {everyday penance} አደርገዋለሁ፡፡ ከአንድ ቦታ ተነስቼ አንድ ቦታ እስከምሄድ ድረስ የሚያጋጥመኝ ሰው ግማሹ በመልካም አይን ነው የሚያየኝ ግማሹ ደግሞ ቢገለኝ ደስ ይለዋል፡፡ እኔ ብቻዬን ነኝ፡፡ አንድ ሰው፡፡ በዛ ሌቭል {level} በርካታ ጠላቶች ካሉህ እንዴት ብለህ ኮንፍሮንት {confront} ታደርጋለህ? ያንን በርካታ ጠላትህን፡፡”

እሱ እንደሚለው በዚህ የተነሳ ያጋጠመው ጉዳት ከመኖሪያ መንደሩ እስከ መራቅ ይደርሳል፡፡ ችግሩን ይባስ ያከፈው ደግሞ መፍትሄውን ያለማወቁና አማራጮቹም ውስን መሆናቸው ነው፡፡ ቃል በቃል እንደሚናገረው አሁን የሚያስጨንቀው የኢሳት ፖለቲካ ሳይሆን የራሱ ህይወት ነው፡፡

“እኔ ከዚያ ግዜ ጀምሮ ላይፌ ዲፈረንት {different} ነው፡፡ አሁን ለምንድን ነው ርቄ የምኖረው ከ[ዋሽንግተን] ዲሲ? ከኮሚኒቲዬ? ለእኔ እኮ ሎስ {loss} ነው፡፡ የራሱ የሆነ መጥፎ ኢምፕሊኬሽን {implication} ያለው ነው፡፡ ከኮሚኒቲህ ርቀህ ምናምን እስከመወሰን ካደረሰህ ሲሪየስ የሆነ ነገር አለብህ ማለት ነው፡፡ አሁን ትልቁ ኢሹዩ ኦነስትሊ ትልቁ ኢሹዬ ኢሳት ሳይሆን በአጠቃላይ በዛ አካባቢ መኖር የሴኩሪቲ ኢሹ ነው፡፡ እኔን መግደል የሚፈልግ መዓት ሰው አለ፡፡ ይህንን ማንም ሊነግረኝ አያስፈልግም፡፡ እኔ ራሴ አውቀዋለሁ፡፡ ይህንን ካወቅሁት ይሄንን በምን አይነት ሁኔታ ነው የምትቋቋመው? በመጋፈጥ ነው? ወይስ ሄጄ ሽጉጥ በመግዛት? ነው ወይስ ጫካ በመግባት ነው? ምርጫህ ሊሚትድ ነው፡፡”

<<አስተሳሰባቸው ጠባብ ነው፤ ስትራቴጂካሊ አያስቡም>> የሚላቸው ፅንፈኛ ፖለቲከኞ ተደላድለው ስለሚኖሩ የሱን ችግር እንዳልተረዱለትም ነው የሚገልፀው፡፡ በቡድን 8 ስብሰባ ላይ የነበረውን ምስል በኤዲቲንግ በማቀነባበር አበበ ገላው ሲያንባርቅ መለስ ዜናዊ እንደደነገጠለት ለማስመሰል ብዙ ተደክሟል፡፡ ይህ የአበበ ንግግር ግን የደነገጠው ራሱ አበበ ገላው መሆኑን፤ ከዛን እለት ጀምሮ ሁልግዜ በጭንቅ ውስጥ እንደሚኖር ነው የሚያሳየው፡፡

“አሁን እኮ እኔ የምልህ ወደድኩም ጠላሁም ፐብሊክ አይ {public eye} ውስጥ ገብቻለሁ፡፡ የዱሮው አበበ አይደለሁም፡፡ ፐብሊክ አይ ማለት ግማሹ አድማየር {admire} ያደርግሃል፤ ግማሹ ደግሞ ደምህን መጠጣት የሚፈልግ አለ፡፡ የከረረ ፖለቲካ ያለበት ሃገር ነው ወደድንም ጠላንም፡፡ እኔ ደግሞ፤ የነካሁት ሰው ደግሞ መለስ ዜናዊ ነው፡፡”

የተቀረፀው ድምፅ በዚሁ አብቅቷል፡፡ እኔም ፅሁፌን በዚሁ አበቃሁ፡፡

***********

[Editor’s note: የአበበ ገላውን ድምጽ የያዘውን ቴፕ ከታች ያሉትን አማራጮች በመጠቀም፡- እዚሁ ያዳምጡ ወይም ዳውንሎድ ያድርጉ]

Download: Leaked tape – Abebe Gelaw on Ginbot7, ESAT, diaspora opposition

Listen:

Kebede Kassa

more recommended stories