የኃ/ማርያምና የአዜብ ንግግር በመለስ 1ኛ አመት መታሰቢያ ላይ (+video)

(ጌቱ ላቀው)

ታላቁ መሪ መለስ ዜናዊ በድህነት ውስጥ የነበረችውን ኢትዮጵያ የነጻነት፣ የፍትህና የእኩልነት አምባ እንድትሆን በማስቻል ረገድ መስዋዕት እስከሆኑበት ቀን ድረስ በትጋት መስራታቸውን ወ/ሮ አዜብ መስፍን ገለጹ፡፡

የታላቁ መሪ አቶ መለስ ዜናዊ አንደኛ አመት መታሰቢያ ነሐሴ 14 ቀን 2005 ዓ.ም በጉለሌ የዕጽዋት ማዕከል ተከብሯል፡፡

በዝግጅቱ ላይ የአቶ መለስ ዜናዊ ባለቤትና የመለስ ፋውንዴሽን ፕሬዝዳንት ወ/ሮ አዜብ መስፍን መለስ ኢትዮጵያን በተረከበበት ወቅት በድህነት አዘቅት ውስጥ ነበረች ብለዋል፡፡

ዛሬ የምናከብረው የመለስ አንደኛ ዓመት መታሰቢያ ቀን የሃዘን ምንጭ ብቻ ሳይሆን አሁን ላይ የዕልህ ምንጭም በመሆን የመለስን አስተምህሮ ለማስቀጠል ለሚሊዮኖች ማዕበል መነሳት ምክንያት መሆኑንም ወ/ሮ አዜብ ገልፀዋል፡፡

መለስ ኢትዮጵያን ህገ መንግስታዊ ስርዓትና ዴሞክራሲ የሰፈነባት በማድረግ እንዲሁም በሌሎችም ረገድ የሰራውን ስራ ለማስቀጠል ኃላፊነቱ የወጣቱ እንደሆነ የጠቆሙት ወ/ሮ አዜብ ኢትዮጵያ የጀመረችውን ልማትና ዕድገት አጠናክራ እንደምትቀጥል ያላቸውን ዕምነት ገልጸዋል፡፡

በመለስ ዜናዊ አንደኛ ዓመት መታሰቢያ ዝግጅት ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ እንዳሉት ከመለስ ህልፈት በኋላ ጥቂቶች የኢትዮጵያ ዕጣ ፈንታ አበቃላት ቢሉም መለስ የገነቡት ህዝባዊው የኢ.ህ.አ.ዴ.ግ ፓርቲ የተጀመረውን ልማት እና የመለስን አስተምህሮ ማስቀጠል ችሏል ብለዋል፡፡

ታላቁ መሪ በልማታዊ መንግስት ያልተሞከረውን የልማታዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት በተግባር ማድረግ እንደሚቻል ያረጋገጡና በተግባርም ያሳዩ ብቸኛ መሪ ናቸው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም የመለስ ዴሞክራሲያዊ፣ ሰብዓዊና ልማታዊ አስተሳሰብ ማንም ምንም ሊያወጣለት የማይችል የጠለቀና ምጡቅ ነው ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም እንዳሉት መለስ ሃገራችንና አፍሪካ የምታካሂደው ልማት በአየር ንብረት ለውጥ እንዳይደናቀፍ በዓለም መድረክ ላይ ያበረከቱት አስተዋጽኦ እጅግ የጎላ እንደሆነም ገልፀዋል፡፡

መለስ ዴሞክራሲን በተግባር ያረጋገጡ መሪ መሆናቸውን የገለፁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተጀመረውን ልማትና የመለስን አስተምህሮ ለማስቀጠል በትጋት እንሰራለን ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ የጀመረችው ልማትና ዕድገት በሃገራችን ህዝቦች ተሳትፎ አሁንም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ገልፀዋል፡፡

በጉለሌ የዕጽዋት ማእከል በተካሄደው የመታሰቢያ ፕሮግራም የመለስ ፋውንዴሽን ቤተ መጽሐፍት ግንባታና ፓርክ በፋውንዴሽኑ ፕሬዝዳንት ወ/ሮ አዜብ መስፍን መሪነት የመሰረት ድንጋይ ተቀምጧል፡፡

የታላቁ መሪ መለስ ዜናዊን የህይወት ጉዞ የሚያመላክት የፎቶ ግራፍ ኤግዚቢሽንም ታይቷል፡፡

Source: ERTA – Aug. 20, 2013.

*********

*********

*********

Daniel Berhane

more recommended stories