(Addis Admass)

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በዓለም ዋንጫው ማጣሪያ የሁለተኛ ዙር ግጥሚያ ጋቦሮኒ ላይ ከቦትስዋና አቻው ጋር ባደረገው ጨዋታ ሁለት ቢጫ ያየውን ምንያህል ተሾመ በማሰለፉ በፊፋ የቀረበው ክስ ለመላው የእግር ኳስ ቤተሰብ ያልተጠበቀ መርዶ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ለቀረበበት ክስ በቂ መከላከያ ማቅረብ ካልቻለ ከቦትስዋና ጋር ተጫውቶ ያስመዘገበው የ2-1 ውጤት ተሰርዞ ለቦትስዋና ቡድን በፎርፌ 3 ነጥብ እንደሚመዘገብላት ተገልጿል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ኢትዮጵያ 130ሺ ብር ቅጣት መክፈል ይጠበቅባታል፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ወደ ዓለም ዋንጫ ለማለፍ መስከረም 6 ቀን 2006 ዓ.ም ከመካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ ጋር የሚያደርገውን ጨዋታ የግድ ማሸነፍ ይኖርበታል፡፡ ለዚህ ሁሉ ተጠያቂው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ዝርክርክ አሰራር ነው፡፡

ከዋልያዎቹ የ2ለ1 ድል በፊት የደረሰው መርዶ መርዶው በይፋ የተሰማበት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ጋዜጣዊ መግለጫ ማክሰኞ እለት በጊዮን ሆቴል ሳባ አዳራሽ ሲሰጥ በደስታ መግለጫና በምስጋና ነበር የተጀመረው፡፡ ከዚያም የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በደቡብ አፍሪካ ላይ 2ለ1 በሆነ ውጤት ካስመዘገበው ድል ጋር በተያያዘ በመላው ኢትዮጵያ በነበረው የደስታ አገላለጽ ለሞቱ ሁለት ወጣቶችም የ1 ደቂቃ የህሊና ፀሎት ተደርጓል፡፡ ሁለቱ የባህርዳር ወጣቶች የ16 ዓመት ተማሪ እና የ13 ዓመት ሊስትሮ ናቸው፡፡ ፌዴሬሽኑ በደስታ አገላለፁ የሞቱት ሁለት ወጣቶች መሆናቸውንም ቢገልጽም በመግለጫው ላይ የተገኙ አንዳንድ ጋዜጠኞች የሟቾች ቁጥር 4 ይሆናል የሞት አደጋ ያጋጠመው በባህርዳር ብቻ አልነበረም በሱልልታና በአዳማም ጭምር እንጅ ብለው እርማት አድርገዋል፡፡

ጋዜጣዊ መግለጫውን የመሩት የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ሳህሉ ገ/ወልድ፣ በደቡብ አፍሪካ ላይ በተመዘገበው የ2ለ1 ድል ዘግተናል ያልነውን ምዕራፍ እንደገና ለመክፈት ተገደናል በሚል የመግቢያ ንግግራቸው መግለጫውን የጀመሩት ፤ አስደንጋጩ መርዶ ፌዴሬሽኑ ፅህፈት ቤት የደረሰው ረቡዕ ዕለት መሆኑን በመግለፅ ነበር፡፡ ኢትዮጵያና ደቡብ አፍሪካ በአዲስ አበባ ስታድዬም ከመገናኘታቸው ሶስት ቀናት ቀደም ብሎ ማለት ነው፡፡ ከፊፋ የመጣው የክስ “ኮምኒኬ” ረቡዕ 5 ሰዓት ላይ ለፌዴሬሽኑ በፋክስ ሲደርስ በጽ/ቤቱ ስለ እሁድ ጨዋታ አጠቃላይ ዝግጅት ለመነጋገር ተሰብስበው የነበሩት የፌዴሬሽኑ ኃላፊዎች፣ የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ሳህሉ ገ/ወልድ ፤ተቀዳሚ ም/ፕሬዚዳንቱ አቶ ብርሃኑ ከበደ ፤ ዋና ፀሐፊው አሸናፊ እጅጉ ናቸው፡፡ ለፌዴሬሽኑ ኃላፊዎች አስደንጋጭ፣ የሚረብሽና ከፍተኛ የሃዘን ስሜት ውስጥ የከተተ መርዶ ሆኖባቸው እንደነበርም ገልፀዋል፡፡ ዋና ተቀዳሚ ም/ፕሬዚዳንት አቶ ተካ አስፋው፣ በአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን ስብሰባ ካይሮ ሄደው ነበርና ሐሙስ ሲመለሱ የፌዴሬሽኑ ኃላፊዎች አስቸኳይ ስብሰባ ተቀመጡ፡፡ እንዲህ በሚልም ተነጋገሩ፡፡ “እሁድ ጨዋታ አለን፡፡ ህዝቡ ጉጉት ላይ ነው፡፡ ተጨዋቾቹ ስሜታቸው የተነሳሳበት ወቅት ነው፡፡ ያለውን ድባብ ማፍረስ ስለሌለብን ጉዳዩን በከፍተኛ ምስጢር መያዝ አለብን” በማለት ተማማሉ፡፡ መማማሉ በየትኛውም መንገድ መረጃው እንዳይወጣ፣ የብሔራዊ ቡድን ተጨዋቾች እንዳይረበሹ፣ ህዝቡ ስሜቱ እንዳይጎዳ በሚል ነበር፡፡

እንደ አቶ ሳህሉ ገለፃ፣ ዋልያዎቹ የእግዚአብሔር ፈቃድ ሆኖ ከደቡብ አፍሪካ ጋር የተደረገውን ጨዋታ በድል በመወጣታቸው ለፌደሬሽኑ ሃላፊዎች ከእነጭራሹ ደብዝዞና ከስሞ የነበረው ተስፋቸውን አለመለመላቸው፡፡ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ግን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለዓለም ዋንጫው የመጨረሻ ማጣሪያ ምዕራፍ መግባቱን ባረጋገጠ ደስታ ተውጦ ነበር፡፡ ስለመርዶው ምንም የሚያውቀው ነገር አልነበረም፡፡ የፌዴሬሽኑ ሥ/አስፈፃሚ አባላት ሰኞ ዕለት 10 ሰዓት ላይ አስቸኳይ ስብሰባ ተቀመጡ፡፡ ስብሰባው የተፈጠረውን ሁኔታ በመገምገም እና ችግሩን ለይቶ አጠቃላይ የጋራ አቅጣጫ ለማስቀመጥ ነበር፡፡ በዚህ የስራ አስፈፃሚ ስብሰባ ላይ ከ11 አባላቱ ባሻገር ዋና አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻውና የጽ/ቤት ኃላፊዎች በሙሉ ተገኝተውበታል፡፡ እንደ ፌደሬሽኑ አመራሮች ማብራርያ፣ በስብሰባው የፊፋን የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ህገ ደንብ በማጣቀስ በቀረበው ክስ ዙርያ መከራከርያ ነጥቦች ተነስተው ተመክሯል፡፡

ከቀኑ 10 ሰዓት ተጀምሮ እስከ ምሽቱ 2 ሰዓት ተኩል በዘለቀው ስብሰባ፣ የፌዴሬሽኑ ስራ አስፈፃሚዎች እንደየሃላፊነታቸው እና የስራ ድርሻቸው በቡድንና በተናጠል ተገማግመዋል፡፡ ስብሰባው የመደናገጥ እና የመላቀስ ድባብ እንደነበረውና ስፖርታዊ ጨዋነትን በተላበሰ መንገድ እንደተከናወነ በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ የተናገሩት የፌደሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ሳህሉ፣ በመገማገም መድረኩ ስህተት መፈፀሙ እንደተረጋገጠ ፤ በቀረበው ክስ ለፊፋ ይግባኝ ለመጠየቅ እና ለመከራከር እንደማይቻል ታወቀ ብለዋል፡፡ ለደረሰው ጥፋት ተጠያቂ መኖር እንዳለበት በመተማመን በየደረጃው ተጠያቂ አካላትን በመለየት በጋራ መግባባት ውሳኔ ላይ መደረሱን ሲያብራሩም ምንም አይነት ሆን ተብሎ የተደረገ (Deliberate) የተሸረበ ሴራ (sabotage) ፣ የታቀደ ተንኮል (Intentional) እንዳልሆነ ተረድተናል ብለዋል፡፡ ዋልያዎቹን ነጥብ ያስጣለው ዝርክርክ አሰራር፤ ተጠያቂዎቹ እና ቃላቸው በፌደሬሽኑ የስራ አስፈፃሚ ግምገማ ላይ ለተፈፀመው ጥፋት የመጀመርያው ተጠያቂ የሆኑት ተቀዳሚ ም/ፕሬዚዳንት አቶ ብርሃኑ ከበደ ናቸው፡፡ አቶ ብርሃኑ ከበደ የቡድን መሪ ሆነው የተሾሙት የዓለም ዋንጫው የምድብ ማጣርያ በደቡብ አፍሪካ እና ኢትዮጵያ ጨዋታ ሩስተንበርግ ላይ ሲጀመር እና ከዚያም በኋላ በሁለተኛ ዙር የምድብ ማጣርያ አዲስ አበባ ላይ ኢትዮጵያ እና ሴንትራል አፍሪካ ባደረጉት ግጥሚያ የቡድን መሪ ከነበሩት አቶ አፈወርቅ አየለ ሃላፊነቱን በመረከብ ነበር፡፡ ከሁሉም በላይ በእኔ ኃላፊነት ይህ ጥፋት በመድረሱ የተሰማኝን ሃዘን መግለጽ እፈልጋለሁ በማለት ቃላቸውን መስጠት የጀመሩት አቶ ብርሃኑ ከበደ፤ በዋልያዎቹ የቡድን መሪነት ስራቸውን የጀመሩት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በጋብሮኒ ከቦትስዋና አቻው ጋር በተጋጠመበት ወቅት ነበር፡፡

የፌደሬሽኑ ፅህፈት ቤት የዚሁን ጨዋታ ኮሚኒኬ አስፈርሞ እንደሰጣቸው ቢገልፅም፤ አቶ ብርሃኑ ግን በሰጡት ቃል ፈረሙበት የተባለው ደብዳቤ ኮፒ እጃቸው ላይ እንደማይገኝ፤ እንደተሰጣቸው እንደማያስታውሱ፣ ተሰጥቷቸውም ከሆነ ደብዳቤው እንዴት ከእጃቸው እንዳመለጠ እንደማይገባቸው ነው የገለፁት፡፡ በጋብሮኒ ለተካሄደው ጨዋታ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ልዑካን የቪዛ ጉዳዮች እና ሌሎች ጉዳዮች የማስፈፀም ድርብ ሃላፊነት እንደነበረባቸው ያስታወሱት አቶ ብርሃኑ ከበደ፣ በወቅቱ ዋና ተቀዳሚው ም/ፕሬዚዳንት አቶ ተካ አስፋውና ዋና ፀሐፊው አቶ አሸናፊ እጅጉ ሞሪሽዬስ ውስጥ በሚደረግ የካፍ ስብሰባ ላይ ለመካፈል ሄደው ስለነበር በሎጀስቲክ ስራዎች ላይ አተኩረው እንደነበር ፣ ተቀጥረው የሚሰሩበት ከፌደሬሽኑ ውጭ ያለ ስራቸውም ለተጨማሪ ውጥረት እንደዳረጋቸው፣ በዚህ ውዥንብር ውስጥ “ደብዳቤው እንዳመለጠኝ ነው የሚገባኝ” ብለዋል፡፡ ልጆቹ ወደ ሜዳ ሲመጡ እኮ እንደ ቡድን መሪነት ብቻ ሳይሆን እንደ አሰልጣኞቹ ረዳት ሆኜ ኳሶችና የመለማመጃ ቁሳቁሶችን ይዤ ነው የምጠብቃቸው፣ ዋናው ነገር ከእጅ ላይ መጥፋቱን እንዴት ላስተውል በማለት በተሰበረ ስሜት ማብራርያቸውን የቀጠሉት አቶ ብርሃኑ፤ ከጽ/ቤት በኩልም ብርሃኑ እንደዚህ አይነት ወረቀት ሰጥተንሃል ብሎ ያስታወሳቸው እንዳልነበር በመጥቀስ፣ የልጆቹን መነሳሳት በጣም እፈልገው ስለነበር ስለሚገጥሙን ውጣ ውረዶች ለማንም ሳልናገር የጉዞ እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን በማስፈፀም አተኮርኩ እንጂ የቀይና ቢጫ ጉዳይ ትዝ አላለኝም ነበር በማለት አስረድተዋል፡፡ በተፈጠረው ስህተት ጥፋተኛው ራሴ እንጅ ማንም ላይ ለማላከክ አልፈልግም ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ብርሃኑ ከበደ፤ ደብዳቤው አምልጦኛል፡፡ ለምን አመለጠህ ቢባል እንኳን አላውቀውም፡፡ ከማናችንም በላይ ያዘንኩት እኔ ነኝ፡፡

ወደዚህ የመጣሁት ላገለግል ልሠራ ነው፡፡ በህይወቴ እንደዚህ አይነት ነገር እንዲያጋጥመኝ አልጠብቅም ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብን በጣም ይቅርታ እጠይቃለሁ በማለት ንግግራቸውን ቋጭተዋል፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ተጠያቂ የሆኑት ደግሞ የብሄራዊ ቡድኑ ዋና አሰልጣኝን ሰውነት ቢሻውና ሌሎች አካላት ናቸው፡፡ ያጋጠመው ጥፋት ሁላችንንም ከልብ አሳዝኖናል ያሉት አሰልጣኝ ሰውነት፤ለደረሰንበት ደረጃ ሚዲያው፣ ህብረተሰቡ፣ ስራ አስፈፃሚው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ሁሉም አካላት ከፍተኛ ጥረት ማድረጋቸውን ከገለፁ በኋላ በቡድን ነው እየተሰራ የነበረው ችግር ቢኖር ኖሮ ከሚዲያው በኩል ይጠቆመን ነበር ብዬ ነው አስብ የነበረው ብለዋል፡፡ አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው አስተያየታቸውን ሲቀጥሉ ‹‹ከፅህፈት ቤቱ ተሰጥቶታል የተባለው ኮሚኒኬ ለአቶ ብርሃኑ ደርሶ ይሆናል፣ እኔ አልወሰድኩም፡፡ እሱ ባይደርሰው እኔ ከደረሰኝ መረጃው አለ ማለት ነው፡፡ በእንግሊዝኛ ቢፃፍም አነባለሁ፡፡ እንግሊዝኛ ማንበብ ባልችል ኖሮ ተተርጉሞ ይላክልኝ ነበር፡፡ ወረቀቱ አልደረሰኝም፡፡ ያ በመሆኑ እጅግ አዝናለሁ፡፡ ለአንዳችን ቢደርሰን ምናለበት፡፡ እኛ ወረቀቱም አንጠብቅም፡፡ ቢጫ ያዩትን ልጆች እናውቃቸዋለን፡፡ ምንያህል በደቡብ አፍሪካው ጨዋታ ያየው ቢጫ ካርድ አለ፣ ከዚያ በኋላ አፍሪካ ዋንጫ ተካሂዶ ከቦትስዋና ጋር ባደረግነው ጨዋታ ሁለተኛውን ቢጫ ካርድ አየ፡፡ ያንን የሚገልጽ ወረቀት ግን አልደረሰኝም፡፡

ከዚህ ውጭ የተቀጡ ልጆችን በሚደርሰን መረጃ መሰረት እንዳይሰለፉ እናሳርፋቸዋለን፡፡ ቢጫና ቀይ ያላቸው ተጨዋቾች ጋር እንነጋገራለን፡፡ ተጨዋቾችም ያለባቸውን ቅጣት በሜዳ ላይ ከሚያደርጉት እንቅስቃሴ ጋር በማያያዝ ይነግሩናል፡፡›› በማለት አጠቃላይ ሁኔታውን ለማብራራት ሞክረዋል፡፡ ስህተቱን ሰርተን አንድ ደረጃ እንድደርስ የተፈጠረ ሁኔታ ይመስለኛል ያሉት ዋና አሰልጣኙ፤በምንሰራቸው ስራዎች ሁሉ በቂ ጥንቃቄና ትኩረት እንዲኖረን ያስተማረን ነው በማለት አሁንም ቡድናቸው የማለፍ ሰፊ ዕድል እንዳለው ለማስገንዘብ ጥረዋል፡፡ ‹‹የተሰደብንበት፣ ኢትዮጵያ የተሰደበችበት ውድድር ነው፣ በቢጫና ቀይ ጥፋት የምንተወው ነገር አይደለም፡፡ አንድ ታሪክ ሰርተን ቆመን በአደባባይ የምንናገርበት ስራ እኮ ነው፡፡ ማንም አሳልፎ የሚሰጠው ነገር የለም፡፡ በቃ 3 ነጥብ አጣን፣ ቦትስዋና ትወስደዋለች፡፡ ደቡብ አፍሪካን እንበልጣታለን፡፡ አስቀድሞ በነበረን እቅድ ከሴንትራል አፍሪካ ጋር ከምናደርገው ጨዋታ ሁለተኛውን ቡድን ለማሳለፍ ነበር፡፡ ያንን ማድረግ አንችልም፡፡ እስከመጨረሻው የማጣሪያ ጨዋታ ባለን ጊዜ ተጨዋቾችንን በሙሉ አቅም ሰብሰብ አድርገን አደራጅተን፣ በቂ ዝግጅት አድርገን መስከረም 6ቀን 2006 ዓ.ም ሴንተር አፍሪካን ገጥመን በማሸነፍ ለመጨረሻው የማጣሪያ ምዕራፍ እንገባለን፡፡

ለወደፊት የሚደገም ስህተት አይሆንም፡፡›› በማለትም ብሄራዊ ቡድኑ በውጤታማነት እንደሚቀጥልም በልበሙሉነት ተናግረዋል፡፡ ከአሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ጋር በፌደሬሽኑ ስራ አስፈፃሚ በሁለተኛ ደረጃ የተጠየቁት የቀድሞው የብሄራዊ ቡድን ረዳት አሰልጣኝ ስዩም ከበደ እና የስራ አስፈፃሚው አባል እና በደቡብ አፍሪካ እና ኢትዮጵያ ጨዋታ የቡድን መሪ የነበሩት አቶ አፈወርቅ አየለ ናቸው፡፡ አሰልጣኝ ስዩም ከበደ፣ ባለህ የዳበረ ልምድ እንዲሁም ከኮምፒውተርና ከኢንተርኔት ጋር በነበረህ የተሻለ ቅርበት የደቡብ አፍሪካው ጨዋታ ላይ የነበረውን የቢጫ ካርድ ጥፋት እያወቅህ በቅንነት አልተናገርክም በሚል ተገምግሟል፡፡ የቡድን መሪ የነበሩት አቶ አፈወርቅ አየለ ደግሞ በ2014 የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ሲጀመር፣ የቡድን መሪ ሆነው በሰሩበት ወቅት፣ የፊፋ የውድድር ህገ ደንብ ተሰጥቷቸው ለሚመለከታቸው ባለመስጠታቸውና ለተጨዋቾች በቂ ግንዛቤ እንዲፈጠር ባለመስራታቸው እንዲሁም ለተተኪው የቡድን መሪ መረጃዎችን ባለማስተላለፋቸው በቅንነት መጓደል ጥፋተኛ ተብለዋል፡፡

የፌዴሬሽኑ ስራ አስፈፃሚ በ3ኛ ደረጃ ተጠያቂ ያደረገው ምንያህል ተሾመን ነው፡፡ ምንም እንኳን በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ በርካታ ጋዜጠኞች በተጨዋቹ ተጠያቂነት ላይ ፌደሬሽኑ የደረሰበት ድምዳሜ የልጁን ድካምና አስተዋፅኦ ከግምት አላስገባም በሚል ውሳኔው በድጋሚ እንዲጤን ግፊት ቢያደርጉም የፌደሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ሳህሉ ገብረወልድ ተጨዋቹ ለተፈፀመው ጥፋት የኢትዮጵያ ህዝብን በግልፅ ይቅርታ ሊጠይቅ እንደሚገባ ነው ያሳሰቡት፡፡ ምንያህል ተሾመ ለስራ አስፈጻሚው ስብሰባ ተጠርቶ ሊገኝ አለመቻሉን በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ የጠቆሙት የፌደሬሽኑ ፕሬዝዳንት፤ በተፈፀመው ጥፋት ተጨዋቹ በጣም ማዘኑንና መከፋቱን ከመገናኛ ብዙሃን መረዳታቸውን ገልፀው፣ ፌዴሬሽኑ ጥሪ ያደረገለት በጉዳዩ ላይ ለሚቀርብበት ጥያቄ ምላሽና ማብራሪያ እንዲሰጥ እንደነበረና እንደ ፕሮፌሽናል ተጨዋች ሙያውን አክብሮ ስህተቱ እንዳይፈፀም ባለመጠንቀቁ፣ እንዲሁም እኔ አይደለሁም ቢጫ ካርዱ የተሰጠኝ፣ አጠገቤ ለነበረው ለሌላ ተጨዋች ነው በማለት አሳማኝ ያልሆነ አስተያየት መስጠቱን ኮንነዋል፡፡ ዳኛ በቃሬዛ ለሚወጣ ተጨዋች እንኳን የካርድ ቅጣት ይሰጣል፡፡ አላወቅሁም አላስተዋልኩም ማለቱ አያሳምንም ያሉት ፕሬዝዳንቱ፣ ማሰብ ያለበት ለብሔራዊ ቡድን፣ ለአገራዊ ኃላፊነትና ግዴታ ነበር፡፡ ያለበትን ኃላፊነት ስነምግባራዊ በሆነ መንገድ አልተወጣም፤ ስለዚህም ተጠያቂ ነው ብለዋል፡፡ የፌደሬሽኑ ስራ አስፈፃሚ በ4ኛ ደረጃ ተጠያቂ ያደረገው ጽ/ቤቱ እና ዋና ፀሐፊውን አቶ አሸናፊ እጅጉ ነው፡፡

የፌዴሬሽኑ ዋና ፀሐፊ አቶ አሸናፊ እጅጉ፤ በጋዜጣዊ መግለጫ መጀመርያ ላይ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የዓለም ዋንጫውን ማጣሪያ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ችግሩ እስከተፈጠረበት የቦትስዋና ጨዋታ ድረስ ያለውን የስራ ሂደት አስረድተው ነበር፡፡ “በማንኛውም ጊዜ በወንዶቹም በሴቶችም ብሔራዊ ቡድኖች የአፍሪካና የዓለም አቀፍ ውድድር በሚመጣበት ጊዜ ለፌዴሬሽኑ ጽ/ቤት ኮሚኒኬ ይደርሰናል” ያሉት ዋና ፀሃፊው አቶ አሸናፊ እጅጉ፤ ኮሙኒኬዎች ሲደርሱ በቀጥታ የሚሰጣቸው አካላት አሉ፡፡ ኮሚኒኬዎች በተለያዩ የሰነድ ወረቀቶች ተደብቀው እንዳይቀሩ በአስቸኳይ ወዲያውኑ ለሚመለከተው አካል የምንሰጥበት አሰራር አለ በማለት ዝርዝር ማብራርያ አቅርበዋል፡፡ በአጠቃላይ ዋና ፀሐፊው የአራቱ የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ግጥሚያዎች ኮሚኒኬዎች ከፊፋ ተልከው ወደ ፅህፈት ቤቱ በደረሱ ማግስት ለቡድን መሪዎች በማስፈረም፤ ኮሚኒኬው እንዲደርሳቸው መደረጉን በቀረን ማስረጃ አረጋግጠናል በማለት ለፅህፈት ቤቱ በኮፒ የቀሩ ማስረጃዎችንም አሳይተዋል፡፡

ጽ/ቤቱ ምን ማድረግ ሲገባው ምን እንዳላደረገ መግለጽ እንዳለበት የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ካሳሰቡ በኋላ፤ ዋና ፀሐፊው አሸናፊ ተጠያቂ ስለመሆናቸው በራሳቸው አንደበት እንዲናገሩ እድል በተሰጣቸው ጊዜ “ግዴታዬን በሚገባ ተወጥቻለሁ፣ ማስተዋል ነበረብህ ለሚባለው እያወቅሁ ያጠፋሁት አይደለም፡፡ ኮሙኒኬዎች ለቡድን መሪው በአስቸኳይ እንዲሰጥ አድርጌያለሁ፡፡ ተጨዋቹ ሁለት ቢጫ እንዳለበት አላየሁም፤ አለማስታወሴ ጥፋት ሊሆን ይችላል፡፡” በማለት አጠር ያለ ቃላቸውን ሲሰጡ፤ የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ሳህሉ ዋና ፀሃፊው ለምን ተጠያቂ እንደሆኑ አብራርተዋል፡፡ ዋና ፀሐፊው ለፌደሬሽኑ ከፍተኛ አመራሮች እና ሃላፊዎች ትኩረት በመስጠት ደብዳቤዎችን ማድረስ ሲገባው፤ በጽሕፈት ቤት በኩል ወይም በፀሐፊው አማካኝነት ደብዳቤው ይሰጠው በሚል መስራቱ ትክክል አልነበረም ያሉት ፕሬዝዳንቱ ፤ አቶ አሸናፊ እጅጉ ተገቢውን የአሰራር ስነምግባር እና ስነስርዓት በመጠበቅ በስልክ ጠርቶ በአካል ተገናኝቶ ደብዳቤዎችን ለሚመለከታቸው መስጠት ሲገባው ይህን ባለማድረጉ ተጠያቂ ነው፡፡

ለዋና አስልጣኙም ይህን አላደረገም፡፡ ስለዚህ ጽ/ቤቱ በነፈገው ትኩረት ተጠያቂ ነው፡፡ ተገቢ የሆነ ክብርና ስነምግባር ባለመከተል ለተፈጠረው ችግር አስተዋጽኦ እንደነበረው በግምግማችን አምኖ ተቀብሏል በማለት አስረድተዋል፡፡ የፌደሬሽኑ ቀጣይ ተስፋ በጋዜጣዊ መግለጫው ከበርካታ የስፖርት ጋዜጠኞች የተነሱ ጥያቄዎች የፌደሬሽኑን ስራ አስፈፃሚዎች ያስጨነቁ ነበሩ፡፡ የፌደሬሽኑ ስራ አስፋፃሚ በጋዜጣዊ መግለጫው የደረሰውን ጥፋት በወረቀት መጥፋት ማሳበቡ፤ በጠቅላላው ስራ አስፈፃሚው ሙሉ ለሙሉ ተጠያቂ መሆን ሲገባው ግለሰቦችን በተናጠል ተጠያቂ ማድረጉ ተገቢ አለመሆኑን፤ የፌደሬሽኑ አሰራር የተበላሸ እና በአማተሪዝም የወደቀ መሆኑ ለችግሩ መንስኤ እንደሚሆን እንዲሁም ፌደሬሽኑ በሀምሌ ወር መጨረሻ ጠቅላላ ጉባኤ ያደርጋል ተብሎ ሲጠበቅ ይሄው ቀነ ቀጠሮ እንዲራዘምለት ስፖርት ኮሚሽን መጠየቁን በተመለከተ በተነሱ አንኳር ጉዳዮች እና አጀንዳዎች ላይ የፌደሬሽኑ አመራሮች ምላሾችንም ሰጥተዋል፡፡ የተሳሳትነው በርካታ ፈታኝ የውድድር ምእራፎችን በማለፋችን በተደራራቢ የእድገት እና የለውጥ ምእራፎች ስንቀሳቀስ በመቆየታችን ነው ሲሉ የተናገሩት አቶ ሳህሉ ገብረወልድ ‹‹በአጠቃላይ በውስጥ አካሎች ድክመት በፌዴሬሽኑ የተሰራው ስራ ሁሉ ጥላሸት ተቀብቷል፡፡ የኃላፊነትና ተጠያቂነት ስራ በየደረጃው ባለመፈፀሙ ለተፈጠረው ስህተት አዝነናል፡፡

በተጠያቂዎች ላይ ርምጃ ለመውሰድ ሰኞ የተደረገው የስራ አስፈፃሚ ስብሰባ በቂ ግዜ አልነበረም፡፡ ጊዜ ባለመኖሩ በተጠያቂዎች ላይ የሚተላለፈው ቅጣት አልተላለፈም፡፡ በተጠያቂዎች ላይ በየደረጃው በማድረጉ ስብሰባዎች የቅጣት ውሳኔዎችን እናስተላልፋለን›› ብለዋል፡፡ የፌደሬሽኑን አመራር በፕሮፌሽናሊዝም የአሰራር መዋቅር ለማጠናከር ስንቀሳቀስ ቆይተናል የሚሉት አቶ ሳህሉ ገብረወልድ፤ ባለፉት አራት አመታት የሰው ሃይል በማደራጀት፤ አሰራሮችን በማሻሻል የገቢ ምንጮችን በማስፋት ብዙ ተግባራት እንደተከነወኑ ገልፀው እውቀትና ችሎታ ያላቸውን ባለሙያዎች ከያሉበት አሰባስበን በእድገት እና ለውጥ ለመቀጠል በያዝነው እቅድ እንቀጥላለን ብለዋል፡፡ ፌደሬሽኑ ሃላፊነትን ወስዶ ተጠያቂነትን የሚሸሽበት ምንም ምክንያት የለም ያሉት የፌደሬሽኑ ዋና ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ተካ አስፋው ሲሆኑ የምንሰራው በጋራ አመራር ስለሆነ ሃላፊነት አለብን ሁላችንም ጥፋት ፈፅመናል እንጅ ጥፋት ፈፅመዋል አላልንም ሲሉ አስረድተው የትም አገር ላይ ስህተት ይፈፀማል፤ አምስት አገር ተሳስቷል፡ ብቸኛዎቹ እኛ ብንሆን ምን ሊፈጠር ነበር፡፡

ስህተቱን ማሳነስ አይደለም ብሄራዊ ቡድኑ 3 ነጥብ አሳጥተነዋል ለዚህ ሁላችንም ተጠያቂ ነን፡፡ በህግ አነጋገር ሆን ተብሎ ወይም በቸልተኝነት ጥፋት አለ፡፡ እኛ የሰራነው ስህተት ግን ሁለቱንም አይደለም ›› በማለት የፌደሬሽኑን ተዓማኒነት ለመከላከል ሞክረዋል፡፡ የደረሰው ጥፋት የተቋሙ ውድቀትን አያሳይም ድክመት ግን እንዳለ ቢያመለክት ነው ያሉት አቶ ተካ፤ አስቀድመው ከነበሩት ፌዴሬሽኖች የተሻለ ሰርተናል ፤ ለውጦችም አሳይተናል፡፡ ከደቡብ አፍሪካው 29ኛው አፍሪካ ዋንጫ ስንመለስ ህዝብ በደማቅ አቀባበል ነው የተቀበለን፡፡ ዋንጫ ስላሸነፍን አይደለም ጥሩ ተሳትፎ ስለነበረን ነው፡፡ ህዝብ ዳኝነት ያውቃል፡፡ አሁን በተፈጠረው ስህተት ህዝቡ ፌደሬሽኑን አይንህን ላፈር ይለዋል ብለን አንጠብቅም፡፡ 4 ዓመታትን ሰርተናል፡፡ ለ12 አምስት ጉዳይ በተፈፀመ ስህተት መኮነን የለብንም፤ የሚሰራ ነው የሚሳተተው እኛስ መጥኔ ለሚመጣው ፌደሬሽን ነው የምንለው›› በማለትም ተጨማሪ ማብራርያ ሰጥተዋል፡፡

*********

Source: Addis Admas – June 24, 2013, titled “የፌዴሬሽኑ ቅሌት“.

Related:- (on Addis Admas) የፌዴሬሽኑ ቅሌት ሊያስከስስ ይችላል ተባለ

Daniel Berhane

more recommended stories